በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 31

“ተስፋ አንቆርጥም”!

“ተስፋ አንቆርጥም”!

“ስለዚህ ተስፋ አንቆርጥም።”—2 ቆሮ. 4:16

መዝሙር 128 እስከ መጨረሻው መጽናት

የትምህርቱ ዓላማ *

1. ክርስቲያኖች የሕይወትን ሩጫ ለማጠናቀቅ ምን ማድረግ አለባቸው?

ክርስቲያኖች በሕይወት ሩጫ ላይ ናቸው። ሩጫውን የጀመርነው በቅርቡም ይሁን ከብዙ ዓመታት በፊት፣ የውድድሩን የመጨረሻ መስመር እስክናልፍ ድረስ መሮጥ ያስፈልገናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች የሰጠው ማበረታቻ በጽናት እስከ መጨረሻው እንድንሮጥ ያነሳሳናል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ጳውሎስ ደብዳቤውን በላከበት ወቅት አንዳንዶቹ የፊልጵስዩስ ጉባኤ አባላት ይሖዋን ማገልገል ከጀመሩ በርካታ ዓመታት አልፈው ነበር። እነዚህ ክርስቲያኖች በአግባቡ እየሮጡ ነበር፤ ያም ቢሆን ጳውሎስ በሩጫው መጽናታቸው አስፈላጊ እንደሆነ ማሳሰቢያ ሰጥቷቸዋል። ጳውሎስ “ግቡ ላይ ለመድረስ [እየተጣጣረ]” እንደነበረ ሁሉ እነዚህ ክርስቲያኖችም እንዲሁ እንዲያደርጉ ፈልጎ ነበር።—ፊልጵ. 3:14

2. ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች የሰጠው ምክር ወቅታዊ ነበር የምንለው ለምንድን ነው?

2 ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች የሰጠው ምክር ወቅታዊ ነበር። ይህ ጉባኤ ገና ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ስደትና ተቃውሞ ገጥሞት ነበር። እንዴት? ጳውሎስና ሲላስ ‘ወደ መቄዶንያ እንዲሻገሩ’ የቀረበላቸውን መለኮታዊ ግብዣ ተቀብለው በ50 ዓ.ም. ወደ ፊልጵስዩስ ሄዱ። (ሥራ 16:9) በዚያም ሊዲያ የተባለች አንዲት ሴት አገኙ፤ ሊዲያ ጳውሎስ የሚናገረውን ‘ያዳመጠች’ ሲሆን ይሖዋም ምሥራቹን እንድትሰማ “ልቧን በደንብ ከፈተላት።” (ሥራ 16:14) ብዙም ሳይቆይ ሊዲያና በቤቷ የሚኖሩ ሰዎች ተጠመቁ። ይሁንና ዲያብሎስ ይህን በዝምታ አልተመለከተውም። የከተማዋ ነዋሪዎች፣ ጳውሎስንና ሲላስን እየጎተቱ በሕግ አስከባሪዎቹ ፊት ያቀረቧቸው ሲሆን ‘ሁከት እየፈጠሩ ነው’ ብለው በሐሰት ከሰሷቸው። በዚህም ምክንያት ጳውሎስንና ሲላስን ደብድበው አሰሯቸው፤ በኋላ ላይ ደግሞ ከተማዋን ለቀው እንዲሄዱ ጠየቋቸው። (ሥራ 16:16-40) ታዲያ ጳውሎስና ሲላስ ተስፋ ቆረጡ? በፍጹም! አዲስ በተቋቋመው ጉባኤ ውስጥ የነበሩት ወንድሞችና እህቶችስ? ደስ የሚለው እነሱም ጸኑ! ጳውሎስና ሲላስ የተዉት ግሩም ምሳሌ እነዚህን ክርስቲያኖች በእጅጉ እንዳበረታታቸው ጥርጥር የለውም።

3. ጳውሎስ ምን ተገንዝቦ ነበር? በዚህ ርዕስ ላይ የየትኞቹን ጥያቄዎች መልስ እንመረምራለን?

3 ጳውሎስ ተስፋ ላለመቁረጥ ቁርጥ ውሳኔ አድርጎ ነበር። (2 ቆሮ. 4:16) ያም ቢሆን ሩጫውን ማጠናቀቅ ከፈለገ ምንጊዜም ግቡ ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለበት ያውቅ ነበር። እኛስ ከጳውሎስ ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? በዘመናችን ያሉ የእምነት ሰዎች፣ በጽናት እንዳንሮጥ እንቅፋት የሚሆኑብንን ነገሮች መወጣት እንደምንችል ያሳዩት እንዴት ነው? በተስፋችን ላይ ማተኮራችን ፈጽሞ ተስፋ ላለመቁረጥ ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ለማጠናከር የሚረዳንስ እንዴት ነው?

ከጳውሎስ ምሳሌ ምን እንማራለን?

4. ጳውሎስ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እያለም በይሖዋ አገልግሎት የተጠመደው እንዴት ነው?

4 ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች በጻፈበት ወቅት እያከናወናቸው ስለነበሩት ነገሮች ለማሰብ እንሞክር። በወቅቱ ሮም ውስጥ የቁም እስረኛ ነበር። ሰዎች ወዳሉበት ቦታ ሄዶ መስበክ አይችልም ነበር። ያም ቢሆን ሊጠይቁት ለሚመጡ ሰዎች በመመሥከርና ራቅ ባሉ ቦታዎች ለሚገኙ ጉባኤዎች ደብዳቤ በመጻፍ ተጠምዶ ነበር። በዛሬው ጊዜም ከቤት መውጣት የማይችሉ ብዙ ክርስቲያኖች፣ ሊጠይቋቸው ወደ ቤታቸው ለሚመጡ ሰዎች ምሥራቹን ለማካፈል ያገኙትን አጋጣሚ ሁሉ ይጠቀማሉ። በተጨማሪም ወንድሞች በቀጥታ አግኝተው ሊያነጋግሯቸው ለማይችሉ ሰዎች የሚያበረታቱ ደብዳቤዎችን ይጽፋሉ።

5. ጳውሎስ በፊልጵስዩስ 3:12-14 ላይ እንደተናገረው ግቡ ላይ ለማተኮር የረዳው ምንድን ነው?

5 ጳውሎስ ቀደም ሲል ያገኘው ስኬትም ሆነ የሠራቸው ስህተቶች ትኩረቱን እንዲከፋፍሉበት አልፈቀደም። እንዲያውም ‘ከፊት ወዳሉት ነገሮች ለመንጠራራት’ ማለትም ሩጫውን በጽናት ለማጠናቀቅ ‘ከኋላ ያሉትን ነገሮች መርሳት’ እንደሚያስፈልግ ተናግሯል። (ፊልጵስዩስ 3:12-14ን አንብብ።) የጳውሎስን ትኩረት ሊከፋፍሉበት ይችሉ የነበሩ አንዳንድ ነገሮች የትኞቹ ናቸው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ጳውሎስ ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት በአይሁድ እምነት ውስጥ ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር። ያም ቢሆን ይህን ስኬቱን “እንደ ጉድፍ” እንደሚቆጥረው ተናግሯል። (ፊልጵ. 3:3-8) ሁለተኛ፣ ቀደም ሲል ክርስቲያኖችን በማሳደዱ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማው ነበር፤ ይህ ግን ይሖዋን ከማገልገል እንዲያግደው አልፈቀደም። ሦስተኛ፣ በይሖዋ አገልግሎት ያከናወነው ነገር በቂ እንደሆነ በማሰብ ረክቶ አልተቀመጠም። ጳውሎስ ቢታሰርም፣ ቢደበደብም፣ በድንጋይ ቢወገርም፣ የመርከብ መሰበር አደጋ ቢያጋጥመውም አልፎ ተርፎም በምግብና በልብስ እጦት ቢቸገርም ውጤታማ የሆነ አገልግሎት ማከናወን ችሏል። (2 ቆሮ. 11:23-27) ጳውሎስ ቀደም ሲል ብዙ ነገሮችን ማከናወኑም ሆነ የተለያዩ ችግሮችን በጽናት መወጣቱ በይሖዋ አገልግሎት ወደፊት መቀጠል እንዳለበት እንዲዘነጋ አላደረገውም። እኛም ብንሆን እንዲሁ ሊሰማን ይገባል።

6. ልንረሳቸው ከሚገቡ ‘ከኋላችን ያሉ ነገሮች’ መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

6 ‘ከኋላ ያሉትን ነገሮች’ በመርሳት ረገድ የጳውሎስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? አንዳንዶቻችን ቀደም ሲል በሠራነው ኃጢአት የተነሳ ከሚሰማን የጥፋተኝነት ስሜት ጋር መታገል ይኖርብን ይሆናል። አንተም እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ የክርስቶስን ቤዛዊ መሥዋዕት በተመለከተ ጥልቀት ያለው ጥናት ማድረግህ ይጠቅምሃል። እንዲህ ስላለው የሚያበረታታ ርዕሰ ጉዳይ ማጥናታችን፣ ማሰላሰላችንና መጸለያችን በውስጣችን የሚሰማን አላስፈላጊ የጥፋተኝነት ስሜት እንዲቀንስ ያደርጋል። አልፎ ተርፎም ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር እንዳለን ስለምንተማመን የጥፋተኝነት ስሜታችን ሙሉ በሙሉ ሊወገድ ይችላል። ከጳውሎስ የምንማረው ሌላም ነገር አለ። አንዳንዶች በይሖዋ አገልግሎት የበለጠ ለመካፈል ሲሉ ጥሩ የሚባል ሥራቸውን ትተው ሊሆን ይችላል። እኛም እንዲህ አድርገን ከሆነ ልናገኛቸው እንችል የነበሩ ቁሳዊ ነገሮችን እያሰብን ከመቆጨት ይልቅ ‘ከኋላ ያሉትን ነገሮች ለመርሳት’ ጥረት እናደርጋለን? (ዘኁ. 11:4-6፤ መክ. 7:10) ‘ከኋላ ያሉት ነገሮች’ የሚለው አገላለጽ ቀደም ሲል በይሖዋ አገልግሎት ያከናወንናቸውን ነገሮች አሊያም በጽናት ያሳለፍናቸውን ችግሮች ሊጨምር ይችላል። እርግጥ ነው፣ ባለፉት ዓመታት ይሖዋ እንዴት እንደባረከንና እንደደገፈን መለስ ብለን ማሰባችን ወደ አባታችን ይበልጥ እንድንቀርብ ይረዳናል። ይሁን እንጂ ያከናወንነው ነገር በቂ እንደሆነ በማሰብ በዚህ ረክተን መቀመጥ አንፈልግም።—1 ቆሮ. 15:58

በሕይወት ሩጫ ስንካፈል ሌሎች ነገሮች ትኩረታችንን እንዳይከፋፍሉት መጠንቀቅና ግባችን ላይ ማተኮር አለብን (አንቀጽ 7⁠ን ተመልከት)

7. በ1 ቆሮንቶስ 9:24-27 መሠረት በሕይወት ሩጫ ለማሸነፍ ምን ያስፈልጋል? በምሳሌ አስረዳ።

7 ኢየሱስ “ከፍተኛ ተጋድሎ አድርጉ” በማለት የተናገረውን ሐሳብ ጳውሎስ በሚገባ ተረድቶት ነበር። (ሉቃስ 13:23, 24) እንደ ክርስቶስ ሁሉ እሱም እስከ መጨረሻው ተጋድሎ ማድረግ እንዳለበት ያውቅ ነበር። ጳውሎስ የክርስትናን ሕይወት ከሩጫ ውድድር ጋር ያመሳሰለው ለዚህ ነው። (1 ቆሮንቶስ 9:24-27ን አንብብ።) በውድድር የሚሳተፍ አንድ ሯጭ በመጨረሻው መስመር ላይ ትኩረት የሚያደርግ ሲሆን ሌሎች ነገሮች ትኩረቱን እንዲከፋፍሉበትም አይፈቅድም። ለምሳሌ ያህል፣ በዛሬው ጊዜ ከተማ ውስጥ በሚደረጉ ውድድሮች የሚካፈሉ ሯጮች፣ በመንገዳቸው ላይ የንግድ ቦታዎችና ትኩረት የሚከፋፍሉ ሌሎች ነገሮች ያጋጥሟቸው ይሆናል። አንድ ሯጭ ሱቆች ውስጥ የተቀመጡ ዕቃዎችን ለማየት ሲል ሩጫውን የሚያቋርጥ ይመስልሃል? በውድድሩ ማሸነፍ ከፈለገ እንዲህ እንደማያደርግ የታወቀ ነው! እኛም በሕይወት ሩጫ ስንካፈል ትኩረታችን በሌሎች ነገሮች እንዳይከፋፈል ጥረት ማድረግ አለብን። ግባችን ላይ በማተኮር ልክ እንደ ጳውሎስ ከፍተኛ ተጋድሎ ካደረግን ሽልማቱን እናገኛለን!

የሚያጋጥሙንን የእምነት ፈተናዎች መቋቋም

8. ስለ የትኞቹ ሦስት ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንመለከታለን?

8 በሕይወት ሩጫ ላይ ፍጥነታችንን እንድንቀንስ ሊያደርጉን የሚችሉ ሦስት ተፈታታኝ ሁኔታዎችን እስቲ እንመልከት። እነሱም የምንጠብቀው ነገር ባሰብነው ጊዜ አለመፈጸሙ፣ አካላዊ ጥንካሬያችን መቀነሱ እንዲሁም ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ ችግሮች ናቸው። ሌሎች ክርስቲያኖች እንዲህ ያሉ ሁኔታዎችን እንዴት እንደተቋቋሙ መመልከታችን ይጠቅመናል።—ፊልጵ. 3:17

9. የምንጠብቀው ነገር ባሰብነው ጊዜ አለመፈጸሙ ምን ዓይነት ስሜት እንዲያድርብን ሊያደርግ ይችላል?

9 የምንጠብቀው ነገር ባሰብነው ጊዜ አለመፈጸሙ። ይሖዋ ቃል የገባቸው መልካም ነገሮች ሲፈጸሙ ለማየት መጓጓታችን ተገቢ ነው። ለምሳሌ፣ የይሖዋ ነቢይ የሆነው ዕንባቆም በይሁዳ የነበረው አስከፊ ሁኔታ ተወግዶ ለማየት ያለውን ጉጉት ገልጾ ነበር፤ ይሖዋም ቢሆን “በተስፋ ጠብቀው” በማለት አበረታቶታል። (ዕን. 2:3) ሆኖም የጠበቅነው ነገር ሳይፈጸም እንደዘገየ ሲሰማን ቅንዓታችን ሊቀዘቅዝ ይችላል። እንዲያውም ተስፋ እንቆርጥ ይሆናል። (ምሳሌ 13:12) በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ የኖሩ ወንድሞቻችን እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሟቸው ነበር። በዚያ ወቅት የኖሩ ብዙ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በ1914 ሰማያዊ ሽልማታቸውን እንደሚያገኙ ይጠብቁ ነበር። ታዲያ ታማኝ የሆኑት ክርስቲያኖች የጠበቁት ነገር ሳይፈጸም መቅረቱ ያሳደረባቸውን ስሜት የተቋቋሙት እንዴት ነው?

ሮያል እና ፐርል ስፓትዝ በ1914 የጠበቁትን ነገር ባያገኙም ለአሥርተ ዓመታት በታማኝነት አገልግለዋል (አንቀጽ 10⁠ን ተመልከት)

10. አንድ ባልና ሚስት የጠበቁት ነገር እነሱ ባሰቡት ጊዜ ባይፈጸምም ምን አድርገዋል?

10 ይህን ተፈታታኝ ሁኔታ የተቋቋሙ ሁለት ታማኝ ክርስቲያኖችን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ወንድም ሮያል ስፓትዝ በ1908 ሲጠመቅ 20 ዓመቱ ነበር። ይህ ወንድም ብዙም ሳይቆይ ወደ ሰማይ እንደሚሄድ በጣም እርግጠኛ ነበር። እንዲያውም ሊያገባት ያሰባትን ፐርል የተባለች እህት በ1911 ለጋብቻ ሲጠይቃት “በ1914 ምን እንደሚከሰት ታውቂያለሽ። ቶሎ ብንጋባ የሚሻል አይመስልሽም?” ብሏት ነበር። ታዲያ እነዚህ ባልና ሚስት በ1914 ሰማያዊ ሽልማታቸውን ባለማግኘታቸው በሕይወት ሩጫ መካፈላቸውን አቆሙ? በፍጹም! ትኩረታቸው በዋነኝነት ያረፈው ሽልማታቸውን በማግኘታቸው ላይ ሳይሆን የአምላክን ፈቃድ በታማኝነት በመፈጸማቸው ላይ ነበር። የሕይወትን ሩጫ በጽናት ለመሮጥ ቆርጠው ነበር። ደግሞም ሮያልና ፐርል ከበርካታ አሥርተ ዓመታት በኋላ ምድራዊ ሕይወታቸውን እስካጠናቀቁበት ጊዜ ድረስ በይሖዋ አገልግሎት በትጋትና በታማኝነት ተካፍለዋል። አንተም ይሖዋ በስሙ ላይ የተሰነዘረውን ነቀፋ ሲያስወግድ፣ ሉዓላዊነቱ ትክክለኛ መሆኑን ሲያረጋግጥና ቃል የገባቸውን ነገሮች በሙሉ ሲፈጽም ለማየት በጣም እንደምትጓጓ ጥርጥር የለውም። እነዚህ ነገሮች ይሖዋ በወሰነው ጊዜ እንደሚፈጸሙ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። እስከዚያው ድረስ ግን በአምላክ አገልግሎት እንጠመድ፤ እንዲሁም የምንጠብቀው ነገር ባሰብነው ጊዜ አለመፈጸሙ ተስፋ እንዲያስቆርጠን አንፍቀድ።

አርተር ሲኮርድ ዕድሜያቸው ከገፋ በኋላም በይሖዋ አገልግሎት አቅማቸው የፈቀደውን የማድረግ ፍላጎት ነበራቸው (አንቀጽ 11⁠ን ተመልከት)

11-12. አካላዊ ጥንካሬያችን እየቀነሰ ቢሄድም ይሖዋን በታማኝነት ማገልገላችንን መቀጠል እንችላለን የምንለው ለምንድን ነው? ምሳሌ ስጥ።

11 አካላዊ ጥንካሬያችን መቀነሱ። በውድድር ከሚካፈል ሯጭ በተለየ ክርስቲያኖች ጠንካራ መንፈሳዊ አቋም ለማዳበር አካላዊ ጥንካሬ አያስፈልጋቸውም። እንዲያውም አካላዊ ጥንካሬያቸው እየቀነሰ የመጣ በርካታ ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ እድገት ማድረጋቸውን ለመቀጠል ያላቸው ቁርጠኝነት ይበልጥ ተጠናክሯል። (2 ቆሮ. 4:16) በቤቴል ለ55 ዓመታት ያገለገሉትን ወንድም አርተር ሲኮርድን * እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ እኚህ ወንድም 88 ዓመታቸው ሲሆን በዕድሜ ምክንያት አቅማቸው ደክሞ ነበር። በወቅቱ ወንድም ሲኮርድን የምትንከባከባቸው ነርስ ወደ አልጋቸው ጠጋ ብላ በአሳቢነት ዓይን ዓይናቸውን እያየች “ወንድም ሲኮርድ፣ በርካታ ኪሎ ሜትሮችን በመጓዝ ይሖዋን በደንብ አገልግለዋል” አለቻቸው። ወንድም ሲኮርድ ግን ትኩረት ያደረጉት ከዚያ ቀደም ባከናወኑት ነገር ላይ አልነበረም። ቀና ብለው ካዩዋት በኋላ ፈገግ ብለው እንዲህ አሏት፦ “ልክ ነሽ። ሆኖም ዋናው ነገር ከዚህ በፊት ያከናወንነው ሳይሆን ከዚህ በኋላ የምናከናውነው ነገር ነው።”

12 አንተም ይሖዋን ለበርካታ ዓመታት ስታገለግል ቆይተህ ይሆናል፤ በአሁኑ ወቅት ግን የጤንነትህ ሁኔታ በማሽቆልቆሉ የቀድሞውን ያህል ማድረግ አትችል ይሆናል። ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ። ይሖዋ እሱን በታማኝነት በማገልገል ያከናወንከውን ነገር ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው እርግጠኛ ሁን። (ዕብ. 6:10) በአሁኑ ወቅት ያለህበትን ሁኔታ በተመለከተ ደግሞ፣ ለይሖዋ ያለን ፍቅር የሚለካው በእሱ አገልግሎት ማከናወን በምንችለው መጠን ላይ እንዳልሆነ አስታውስ። ይሖዋን በሙሉ ነፍሳችን እንደምንወደው የሚያሳየው አዎንታዊ አመለካከት መያዛችንና አቅማችን የሚፈቅደውን ሁሉ ማድረጋችን ነው። (ቆላ. 3:23) ይሖዋ ያለብንን የአቅም ገደብ የሚረዳ ከመሆኑም ሌላ ከምንችለው በላይ አይጠብቅብንም።—ማር. 12:43, 44

አናቶሊ እና ሊዲያ ሜልኒክ ብዙ መከራ ቢደርስባቸውም በታማኝነት ጸንተዋል (አንቀጽ 13⁠ን ተመልከት)

13. የወንድም ሜልኒክና የባለቤቱ ተሞክሮ ለዓመታት ብዙ ችግሮችን የተቋቋምን ቢሆንም ይሖዋን በታማኝነት ማገልገላችንን እንድንቀጥል የሚያበረታታን እንዴት ነው?

13 ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ ችግሮች። አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች ለአሥርተ ዓመታት የዘለቀ መከራንና ስደትን መቋቋም አስፈልጓቸዋል። የወንድም አናቶሊ ሜልኒክን * ምሳሌ እንመልከት። አናቶሊ ገና የ12 ዓመት ልጅ እያለ አባቱ ተይዞ ታሰረ፤ ከዚያም አባትየው በሞልዶቫ ከሚኖሩት ቤተሰቡ ተነጥሎ ከ7,000 ኪሎ ሜትር በላይ ርቆ ወደሚገኘው ወደ ሳይቤሪያ በግዞት ተወሰደ። ከአንድ ዓመት በኋላ አናቶሊ፣ እናቱ እና አያቶቹም ወደ ሳይቤሪያ ተጋዙ። ውሎ አድሮ በሌላ መንደር በሚደረግ ክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ መገኘት የቻሉ ቢሆንም እዚያ ለመድረስ ከዜሮ ዲግሪ በታች በሆነ ኃይለኛ ቅዝቃዜ በእግራቸው 30 ኪሎ ሜትር መጓዝ ነበረባቸው። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ወንድም ሜልኒክ ከባለቤቱ ከሊዲያ እና ከአንድ ዓመት ሴት ልጃቸው ተለይቶ ለሦስት ዓመት ታስሯል። ወንድም ሜልኒክና ቤተሰቡ ለዓመታት መከራ ቢደርስባቸውም ይሖዋን በታማኝነት ማገልገላቸውን ቀጥለዋል። አሁን 82 ዓመት የሆነው ወንድም ሜልኒክ በማዕከላዊ እስያ ውስጥ የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባል ሆኖ እያገለገለ ነው። እኛም የወንድም ሜልኒክንና የባለቤቱን ምሳሌ በመከተል፣ ችግሮችን በጽናት መቋቋማችንን እንቀጥል፤ እንዲሁም በይሖዋ አገልግሎት አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እናድርግ።—ገላ. 6:9

በተስፋችን ላይ ትኩረት ማድረግ

14. ጳውሎስ ግቡ ላይ ለመድረስ ምን ማድረግ እንዳለበት ተገንዝቧል?

14 ጳውሎስ ሩጫውን እንደሚያጠናቅቅና ግቡ ላይ እንደሚደርስ እርግጠኛ ነበር። ቅቡዕ ክርስቲያን እንደመሆኑ መጠን “የሰማያዊውን ሕይወት ሽልማት” እንደሚያገኝ ይጠብቅ ነበር። ሆኖም ጳውሎስ እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ምንጊዜም ‘መጣጣር’ እንዳለበት ያውቅ ነበር። (ፊልጵ. 3:14) ጳውሎስ የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ምንጊዜም ግባቸው ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ለመርዳት ግሩም ንጽጽር ተጠቅሟል።

15. ጳውሎስ የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖችን ግባቸው ላይ ለመድረስ ምንጊዜም ‘እንዲጣጣሩ’ ለማበረታታት ዜግነትን እንደ ምሳሌ የተጠቀመው እንዴት ነው?

15 ጳውሎስ፣ የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖችን “የሰማይ ዜጎች” እንደሆኑ አስታውሷቸዋል። (ፊልጵ. 3:20) ይህን ማስታወሳቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? በዚያ ዘመን የሮም ዜግነት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ነበር። * ቅቡዓን ክርስቲያኖች ግን ከዚህ የላቀ ዜግነት የነበራቸው ሲሆን ይህም ከሮም ዜግነት የበለጡ ጥቅሞች ያስገኝላቸዋል። ከዚህ አንጻር የሮም ዜግነት ከቁጥር የሚገባ ነገር አልነበረም። በመሆኑም ጳውሎስ “ዜጎች እንደመሆናችሁ መጠን ስለ ክርስቶስ ከሚገልጸው ምሥራች ጋር በሚስማማ መንገድ ኑሩ” በማለት የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖችን አበረታቷቸዋል። (ፊልጵ. 1:27 ግርጌ) በዛሬው ጊዜ ያሉ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሰማይ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ግባቸው ላይ ለመድረስ ምንጊዜም በመጣጣር ግሩም ምሳሌ ይሆናሉ።

16. ተስፋችን ወደ ሰማይ መሄድም ሆነ በምድር ላይ መኖር በፊልጵስዩስ 4:6, 7 መሠረት ምን ማድረጋችንን መቀጠል ይኖርብናል?

16 ተስፋችን ወደ ሰማይ መሄድም ሆነ ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም መኖር፣ ግባችን ላይ ለመድረስ ምንጊዜም መጣጣር ይኖርብናል። ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን፣ ከኋላችን ያሉትን ነገሮች መርሳት ይኖርብናል፤ እንዲሁም ማንኛውም ነገር ወደፊት ከመጓዝ እንዲያግደን መፍቀድ የለብንም። (ፊልጵ. 3:16) የምንጠብቃቸው ነገሮች እኛ ባሰብነው ጊዜ አይፈጸሙ ይሆናል፤ ወይም አካላዊ ጥንካሬያችን እየቀነሰ ሊሄድ ይችላል። አሊያም ለበርካታ ዓመታት ስደትንና መከራን መቋቋም አስፈልጎን ሊሆን ይችላል። በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ብትሆኑ “ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ።” ከዚህ ይልቅ ልመናችሁንና ምልጃችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ እሱም ከምታስቡት ሁሉ በላይ የሆነ ሰላም ይሰጣችኋል።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7ን አንብብ።

17. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?

17 አንድ ሯጭ ወደ መጨረሻው መስመር ሲጠጋ ትኩረቱን ውድድሩን በማጠናቀቅ ላይ እንደሚያደርግ ሁሉ እኛም የሕይወትን ሩጫ ለማጠናቀቅ እየተቃረብን በሄድን መጠን ትኩረታችን በሙሉ በሽልማታችን ላይ ይሁን። ከፊታችን የሚጠብቁንን አስደናቂ ነገሮች ለማግኘት አቅማችንና ሁኔታችን በፈቀደው መጠን ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረጋችንን እንቀጥል። ታዲያ በትክክለኛው አቅጣጫ በጽናት መሮጥ እንድንችል ምን ማድረግ ይኖርብናል? የሚቀጥለው የጥናት ርዕስ “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች” ለይተን እንድናውቅና ለእነዚህ ነገሮች ቅድሚያ እንድንሰጥ ይረዳናል።—ፊልጵ. 1:9, 10

መዝሙር 79 ጸንተው እንዲቆሙ አስተምሯቸው

^ አን.5 ይሖዋን ለበርካታ ዓመታት ስናገለግል የቆየን ብንሆንም እንኳ የጎለመስንና የተሻልን ክርስቲያኖች ለመሆን ጥረት ማድረጋችንን መቀጠል እንፈልጋለን። ሐዋርያው ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹን ፈጽሞ ተስፋ እንዳይቆርጡ አበረታቷቸዋል! ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች የጻፈው ደብዳቤ፣ የሕይወትን ሩጫ በጽናት ለመሮጥ የሚረዳንን ማበረታቻ ይዟል። ይህ ርዕስ ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት የተናገረውን ሐሳብ እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደምንችል ያብራራል።

^ አን.11 በሰኔ 15, 1965 (እንግሊዝኛ) መጠበቂያ ግንብ ላይ “ንጹሕ አምልኮ እንዲስፋፋ ያበረከትኩት አስተዋጽኦ” በሚል ርዕስ የወጣውን የወንድም ሲኮርድን የሕይወት ታሪክ ተመልከት።

^ አን.13 በጥቅምት 22, 2004 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ላይ “አምላክን እንድወድ ከልጅነቴ ጀምሮ ተምሬያለሁ” በሚል ርዕስ የወጣውን የወንድም ሜልኒክን የሕይወት ታሪክ ተመልከት።

^ አን.15 ፊልጵስዩስ በሮም አገዛዝ ሥር ስለነበረች የከተማዋ ነዋሪዎች የሮም ዜግነት የሚያስገኛቸውን አንዳንድ መብቶች ያገኙ ነበር። በመሆኑም የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ጳውሎስ የተጠቀመበትን ምሳሌ መረዳት አይከብዳቸውም ነበር።