በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመጥምቁ ዮሐንስ ታሪክ ደስታን ጠብቆ ስለ መኖር ምን ያስተምረናል?

የመጥምቁ ዮሐንስ ታሪክ ደስታን ጠብቆ ስለ መኖር ምን ያስተምረናል?

በጣም የምትወደው ሆኖም ካለህበት ሁኔታ አንጻር ልታከናውነው የማትችለው የጉባኤ ሥራ አለ? ምናልባት ይህን ሥራ ሌላ ሰው እያከናወነው ሊሆን ይችላል። ወይም በአንድ ዓይነት የአገልግሎት ምድብ ላይ ስታገለግል ቆይተህ ይሆናል። አሁን ግን በዕድሜ፣ በጤና እክል፣ በኢኮኖሚ ጫና ወይም በቤተሰብ ኃላፊነት የተነሳ ማድረግ የምትችለው ነገር ውስን ሊሆን ይችላል። አሊያም ደግሞ በድርጅቱ ውስጥ በተደረጉ ለውጦች ምክንያት፣ ለረጅም ጊዜ የነበረህን ኃላፊነት መተው አስፈልጎህ ይሆናል። በዚያም ሆነ በዚህ፣ በአምላክ አገልግሎት ማከናወን የምትፈልገውን ያህል እየሠራህ እንዳልሆነ ሊሰማህ ይችላል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ገጥሞህ ከሆነ አንዳንድ ጊዜ ሐዘን ቢሰማህ የሚያስገርም አይሆንም። ሆኖም እንደ ተስፋ መቁረጥና ምሬት ባሉት አፍራሽ ስሜቶች እንዳትዋጥ ምን ሊረዳህ ይችላል? ደስታህን ጠብቀህ መኖር የምትችለውስ እንዴት ነው?

የመጥምቁ ዮሐንስን ታሪክ መመርመራችን ደስታችንን ጠብቀን መኖር የምንችለው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ ይረዳናል። ዮሐንስ ግሩም መብቶች ነበሩት፤ ይሁንና በይሖዋ አገልግሎት ሲካፈል ያጋጠሙት ሁኔታዎች ፈጽሞ ያልጠበቃቸው ሊሆኑ ይችላሉ። በአገልግሎቱ ካሳለፈው የሚበልጥ ጊዜ እስር ቤት ውስጥ እንደሚያሳልፍ ጨርሶ አላሰበ ይሆናል። ያም ቢሆን ዮሐንስ ደስታውን አላጣም፤ በቀረው ሕይወቱም ደስታውን ጠብቆ መኖር ችሏል። ይህን እንዲያደርግ የረዳው ምንድን ነው? እኛስ ያልጠበቅናቸው ሁኔታዎች በሚያጋጥሙን ጊዜም እንኳ ደስታችንን ጠብቀን መኖር የምንችለው እንዴት ነው?

አስደሳች ተልእኮ

ዮሐንስ የመሲሑ መንገድ ጠራጊ ሆኖ አገልግሎቱን የጀመረው ሚያዝያ 29 ዓ.ም. ገደማ ሲሆን “መንግሥተ ሰማያት ስለቀረበ ንስሐ ግቡ” እያለ ያውጅ ነበር። (ማቴ. 3:2፤ ሉቃስ 1:12-17) ብዙ ሕዝብ ለመልእክቱ ጥሩ ምላሽ ሰጠ። እንዲያውም የእሱን መልእክት ለመስማት በርካታ ሰዎች ርቀው ከሚገኙ ቦታዎች መምጣት ጀመሩ፤ ብዙዎችም ንስሐ ገብተው ተጠመቁ። ዮሐንስ፣ ራሳቸውን የሚያመጻድቁትን የሃይማኖት መሪዎችም ንስሐ ካልገቡ ፍርድ እንደሚጠብቃቸው በመግለጽ በድፍረት አስጠንቅቋቸዋል። (ማቴ. 3:5-12) ጥቅምት 29 ዓ.ም. ገደማ ኢየሱስን ባጠመቀበት ወቅት ደግሞ በአገልግሎቱ ከሁሉ የላቀውን መብት አግኝቷል። ከዚያ ጊዜ አንስቶ ዮሐንስ፣ ተስፋ የተደረገበት መሲሕ ኢየሱስ መሆኑን በመግለጽ ሰዎች እሱን እንዲከተሉ ማበረታታት ጀመረ።—ዮሐ. 1:32-37

ዮሐንስ ከነበረው ልዩ ተልእኮ አንጻር ኢየሱስ “ከሴት ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሳም” ብሎ መናገሩ አያስገርምም። (ማቴ. 11:11) ዮሐንስ ባገኛቸው በረከቶች ተደስቶ እንደሚሆን ጥያቄ የለውም። በዛሬው ጊዜም ብዙዎች እንደ ዮሐንስ የተትረፈረፈ በረከት አግኝተዋል። ቴሪ የተባለውን ወንድም እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እሱና ባለቤቱ ሳንድራ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ከ50 የሚበልጡ ዓመታት አሳልፈዋል። ቴሪ እንዲህ ብሏል፦ “ብዙ ግሩም መብቶች አግኝቻለሁ። አቅኚ፣ ቤቴላዊ፣ ልዩ አቅኚ፣ የወረዳ የበላይ ተመልካችና የአውራጃ የበላይ ተመልካች ሆኜ አገልግያለሁ፤ አሁን ደግሞ በድጋሚ ልዩ አቅኚ ሆኜ እያገለገልኩ ነው።” በእርግጥም ቲኦክራሲያዊ መብቶች ማግኘት አስደሳች ነገር ነው፤ ከዮሐንስ ተሞክሮ እንደምንማረው ግን ሁኔታችን ሲቀየር ደስታችንን ጠብቀን መኖር ጥረት ይጠይቃል።

ምንጊዜም አድናቆት ይኑርህ

መጥምቁ ዮሐንስ ደስታውን ጠብቆ እንዲኖር ያስቻለው ዋነኛው ነገር ያሉትን መብቶች ምንጊዜም ያደንቅ የነበረ መሆኑ ነው። አንድ ምሳሌ እንውሰድ። ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ዮሐንስ የሚያከናውነው አገልግሎት እየቀነሰ ሲሄድ የኢየሱስ አገልግሎት ግን እየጨመረ ሄዷል። የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ይህ ጉዳይ ስላሳሰባቸው ወደ እሱ ቀርበው “በዮርዳኖስ ማዶ ከአንተ ጋር የነበረውና ስለ እሱ የመሠከርክለት ሰው እያጠመቀ ነው፤ ሰዉም ሁሉ ወደ እሱ እየሄደ ነው” አሉት። (ዮሐ. 3:26) ዮሐንስ ግን እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፦ “ሙሽራይቱ የሙሽራው ናት። ይሁን እንጂ የሙሽራው ጓደኛ በዚያ ቆሞ ሲሰማው በሙሽራው ድምፅ የተነሳ እጅግ ደስ ይለዋል። በመሆኑም የእኔ ደስታ ተፈጽሟል።” (ዮሐ. 3:29) ዮሐንስ ከኢየሱስ ጋር አልተፎካከረም፤ አሊያም ደግሞ ኢየሱስ የላቀ ሥራ እያከናወነ መሆኑ የእሱን አገልግሎት ዋጋ እንዳሳጣው አልተሰማውም። ከዚህ ይልቅ ዮሐንስ “የሙሽራው ጓደኛ” የመሆን መብቱን ከፍ አድርጎ ስለተመለከተ ደስታውን ጠብቆ መኖር ችሏል።

ዮሐንስ የነበረው አመለካከት፣ የተሰጠውን ተልእኮ ለመወጣት የሚጠበቅበት ነገር ቀላል ባይሆንም እንኳ ደስታውን ጠብቆ እንዲቀጥል ረድቶታል። ለምሳሌ፣ ዮሐንስ ሲወለድ ጀምሮ ናዝራዊ በመሆኑ የወይን ጠጅ መጠጣት አይፈቀድለትም ነበር። (ሉቃስ 1:15) ኢየሱስ ስለ ዮሐንስ ሕይወት ሲናገር “ዮሐንስ ሳይበላና ሳይጠጣ መጣ” ብሏል። በሌላ በኩል ግን ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ዓይነት ገደብ ስላልነበረባቸው አኗኗራቸው እንደ ማንኛውም ሰው ነበር። (ማቴ. 11:18, 19) በተጨማሪም ዮሐንስ አንድም ተአምር አልፈጸመም፤ ሆኖም ቀደም ሲል የእሱ ተከታዮች የነበሩትን ጨምሮ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ተአምር የመፈጸም ችሎታ እንደተሰጣቸው ያውቅ ነበር። (ማቴ. 10:1፤ ዮሐ. 10:41) ዮሐንስ ግን እነዚህ ልዩነቶች ትኩረቱን እንዲከፋፍሉት ከመፍቀድ ይልቅ ይሖዋ የሰጠውን አገልግሎት በቅንዓት ማከናወኑን ቀጥሏል።

እኛም አሁን ያለንን የአገልግሎት ምድብ ከፍ አድርገን የምንመለከተው ከሆነ ደስታችንን ጠብቀን መኖር እንችላለን። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ቴሪ “አዲስ የአገልግሎት ምድብ በተሰጠኝ ቁጥር ሙሉ ትኩረቴን የማደርገው በዚያ ኃላፊነት ላይ ነው” በማለት ተናግሯል። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ስላሳለፈው ሕይወት ሲገልጽ “አስደሳች ትዝታዎች አሉኝ፤ ምንም የሚቆጨኝ ነገር የለም” ብሏል።

በይሖዋ አገልግሎት የሚሰጠንን የትኛውንም መብት ወይም ኃላፊነት ልዩ የሚያደርገው ምን እንደሆነ ማሰላሰላችን በአገልግሎታችን የምናገኘው ደስታ እንዲጨምር ያደርጋል። ማንኛውንም የአገልግሎት ምድብ ልዩ የሚያደርገው “ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ” መሆናችን ነው። (1 ቆሮ. 3:9) አንዳንድ የከበሩ ማዕድናት ሲወለወሉ ድምቀታቸው ይበልጥ እንደሚጨምር ሁሉ እኛም ከአምላክ ጋር አብረን መሥራታችን ባስገኘልን ክቡር መብት ላይ የምናሰላስል ከሆነ የተሳሳቱ አመለካከቶች ደስታችንን አያደበዝዙትም። እንዲሁም እኛ የምናደርገውን ጥረት ሌሎች ከሚያከናውኑት ሥራ ጋር አናወዳድርም። እኛ ያለንን መብት፣ ሌሎች ከተሰጣቸው የአገልግሎት መብት ጋር በማነጻጸር ዝቅ አድርገን አንመለከተውም።—ገላ. 6:4

በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ትኩረት አድርግ

ዮሐንስ አገልግሎቱ ለረጅም ጊዜ እንደማይቀጥል ተገንዝቦ ሊሆን ቢችልም በድንገት አገልግሎቱን እንደሚያቆም አላሰበ ይሆናል። (ዮሐ. 3:30) ዮሐንስ ኢየሱስን ካጠመቀ ከስድስት ወራት ገደማ በኋላ ማለትም በ30 ዓ.ም. ንጉሥ ሄሮድስ አሰረው። ያም ቢሆን ዮሐንስ ሁኔታዎች በፈቀዱለት መጠን ምሥክርነት መስጠቱን ቀጥሏል። (ማር. 6:17-20) እንዲህ ያሉ ለውጦች ቢያጋጥሙትም ደስታውን ጠብቆ እንዲኖር የረዳው ምንድን ነው? በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረጉ ነው።

ዮሐንስ እስር ቤት እያለ ኢየሱስ አገልግሎቱን በስፋት እያከናወነ መሆኑን ሰማ። (ማቴ. 11:2፤ ሉቃስ 7:18) ዮሐንስ፣ ኢየሱስ መሲሕ እንደሆነ እርግጠኛ ነበር፤ ይሁንና በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ መሲሑ እንደሚያከናውናቸው የተገለጹትን ነገሮች በሙሉ ኢየሱስ የሚፈጽመው እንዴት እንደሆነ ማወቅ ሳይፈልግ አልቀረም። መሲሑ ንጉሥ እንደሚሆን ስለተነገረ ኢየሱስ በቅርቡ መግዛት ይጀምር ይሆን? ከሆነ ደግሞ ዮሐንስን ከእስር ያስፈታው ይሆን? ዮሐንስ፣ ኢየሱስ ስለሚጫወተው ሚና የተሻለ ግንዛቤ ማግኘት ስለፈለገ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል ሁለቱን ጠርቶ “ይመጣል የተባልከው አንተ ነህ ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” ብለው እንዲጠይቁት ወደ ኢየሱስ ላካቸው። (ሉቃስ 7:19) ኢየሱስም ለዮሐንስ እንዲህ ብለው እንዲነግሩት መልሶ ላካቸው፦ “ዓይነ ስውሮች እያዩ ነው፤ አንካሶች እየተራመዱ ነው፤ የሥጋ ደዌ የያዛቸው እየነጹ ነው፤ መስማት የተሳናቸው እየሰሙ ነው፤ ሙታን እየተነሱ ነው፤ ድሆችም ምሥራቹ እየተነገራቸው ነው።” ደቀ መዛሙርቱ ተመልሰው ኢየሱስ ስላከናወነው ተአምራዊ ፈውስ ሲነግሩት ዮሐንስ በጉጉት አዳምጧቸው መሆን አለበት።—ሉቃስ 7:20-22

ዮሐንስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ባመጡት ዜና እንደተበረታታ ጥያቄ የለውም። የነገሩት ነገር ኢየሱስ መሲሑን አስመልክቶ የተነገሩትን ትንቢቶች እየፈጸመ መሆኑን አረጋግጦለታል። ዮሐንስ፣ ኢየሱስ መሲሕ ሆኖ መገለጡ እሱ ከእስር እንዲፈታ ባያደርግም እንኳ አገልግሎቱ ከንቱ ሆኖ እንዳልቀረ ያውቅ ነበር። ያለበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን፣ ደስተኛ ለመሆን የሚያበቃው ምክንያት ነበረው።

በዓለም ዙሪያ ስለሚከናወነው የስብከት ሥራ በሚገልጹ ጥሩ ሪፖርቶች ላይ ትኩረት ማድረጋችን ደስታችንን ጠብቀን ለመኖር ይረዳናል

እኛም እንደ ዮሐንስ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ትኩረት የምናደርግ ከሆነ በደስታና በትዕግሥት መጽናት እንችላለን። (ቆላ. 1:9-11) መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባችንና ባነበብነው ላይ ማሰላሰላችን ለመጽናት ይረዳናል፤ እንዲሁም በአምላክ አገልግሎት የምናከናውነው ሥራ ከንቱ ሆኖ እንደማይቀር እንድናስታውስ ያደርገናል። (1 ቆሮ. 15:58) ሳንድራ እንዲህ ብላለች፦ “በየቀኑ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አንድ ምዕራፍ ማንበቤ ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድቀርብ ረድቶኛል። በራሴ ላይ ሳይሆን በእሱ ላይ እንዳተኩር አድርጎኛል።” በተጨማሪም ስለ መንግሥቱ የስብከት ሥራ በሚገልጹ ሪፖርቶች ላይ ትኩረት ማድረግ እንችላለን፤ ይህም እኛ ስላለንበት ሁኔታ ብቻ ከማሰብ ይልቅ ይሖዋ እያከናወነ ባለው ነገር ላይ እንድናተኩር ይረዳናል። ሳንድራ “JW ብሮድካስቲንግ ላይ የሚወጡት ወርሃዊ ፕሮግራሞች ድርጅቱን ይበልጥ እንድናውቀው እንዲሁም በአገልግሎት ምድባችን ደስተኞች ሆነን እንድንቀጥል ረድተውናል” ብላለች።

መጥምቁ ዮሐንስ ለአጭር ጊዜ የቆየውን አገልግሎቱን ያከናወነው “በኤልያስ መንፈስና ኃይል” ነው፤ እንደ ኤልያስ ሁሉ እሱም “እንደ እኛው ዓይነት ስሜት ያለው ሰው ነበር።” (ሉቃስ 1:17፤ ያዕ. 5:17) እኛም አድናቆት በማሳየትና በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ትኩረት በማድረግ እሱን የምንመስለው ከሆነ ምንም ዓይነት ለውጥ ቢያጋጥመን በአገልግሎታችን ደስተኛ ሆነን መቀጠል እንችላለን።