በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 33

“የሚሰሙህ” ሰዎች ይድናሉ

“የሚሰሙህ” ሰዎች ይድናሉ

“ለራስህና ለምታስተምረው ትምህርት ምንጊዜም ትኩረት ስጥ። በእነዚህ ነገሮች ጽና፤ ይህን በማድረግ ራስህንም ሆነ የሚሰሙህን ታድናለህና።”—1 ጢሞ. 4:16

መዝሙር 67 “ቃሉን ስበክ”

የትምህርቱ ዓላማ *

1. ሁላችንም ብንሆን የቤተሰባችን አባላት ምን እንዲያደርጉ እንፈልጋለን?

ፖሊን የተባለች እህት “እውነትን ከሰማሁበት ጊዜ አንስቶ፣ የቤተሰቤ አባላት በሙሉ ወደፊት በገነት አብረውኝ እንዲኖሩ እመኝ ነበር” ብላለች። * አክላም “በተለይ ደግሞ ባለቤቴ ዌን እና ትንሹ ልጃችን አብረውኝ ይሖዋን እንዲያገለግሉ እፈልግ ነበር” በማለት ተናግራለች። አንተስ ስለ ይሖዋ ተምረው እሱን ማገልገል ያልጀመሩ የቤተሰብ አባላት አሉህ? ከሆነ የፖሊንን ስሜት ትጋራ ይሆናል።

2. በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመለከታለን?

2 የቤተሰባችን አባላት ምሥራቹን እንዲቀበሉ ማስገደድ አንችልም፤ ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መቀበል ቀላል እንዲሆንላቸው መርዳት እንችላለን። (2 ጢሞ. 3:14, 15) ለመሆኑ ለቤተሰባችን አባላት ምሥራቹን መናገር ያለብን ለምንድን ነው? ስሜታቸውን ለመረዳት ጥረት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው? የቤተሰባችን አባላት እንደ እኛ ይሖዋን እንዲወዱ ለመርዳት ምን ማድረግ እንችላለን? የጉባኤያችን አባላት በዚህ ረገድ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችሉትስ እንዴት ነው?

ለቤተሰባችን አባላት መመሥከር ያለብን ለምንድን ነው?

3. በ2 ጴጥሮስ 3:9 ላይ እንደተገለጸው ለቤተሰባችን አባላት መመሥከር ያለብን ለምንድን ነው?

3 በቅርቡ ይሖዋ ይህን ሥርዓት ያጠፋዋል። ከጥፋቱ መትረፍ የሚችሉት “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው” ሰዎች ብቻ ናቸው። (ሥራ 13:48) በአካባቢያችን ላሉ የማናውቃቸው ሰዎች ለመመሥከር ጊዜያችንን እና ጉልበታችንን መሥዋዕት እናደርጋለን፤ ከዚህ አንጻር የቤተሰባችን አባላትም አብረውን ይሖዋን እንዲያገለግሉ ስንል ለእነሱ ለመመሥከር ጥረት ማድረጋችን የተገባ ነው። አፍቃሪው አባታችን ይሖዋ “ሁሉ ለንስሐ እንዲበቃ እንጂ ማንም እንዲጠፋ [አይፈልግም]።”2 ጴጥሮስ 3:9ን አንብብ።

4. ለቤተሰባችን አባላት ስንመሠክር ምን ስህተት ልንሠራ እንችላለን?

4 የመዳንን መልእክት የምንናገርበት መንገድ አንዳንድ ጊዜ የተሳሳተ ሊሆን እንደሚችል ማስታወስ ይኖርብናል። ለማናውቀው ሰው ስንመሠክር ዘዴኛ ለመሆን ጥረት እናደርጋለን፤ ለቤተሰባችን አባላት ስንመሠክር ግን ለስሜታቸው ያን ያህል አንጠነቀቅ ይሆናል።

5. ለቤተሰባችን አባላት እውነትን ስንመሠክር ልናስታውሰው የሚገባው ነገር ምንድን ነው?

5 ብዙዎቻችን ለመጀመሪያ ጊዜ ለቤተሰባችን አባላት ለመመሥከር ያደረግነውን ጥረት ስናስታውስ ‘ምነው እንዲህ ባደረግሁ’ ብለን እንቆጭ ይሆናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖችን “ለእያንዳንዱ ሰው እንዴት መልስ መስጠት እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ምንጊዜም በጨው የተቀመመ ያህል ለዛ ያለው ይሁን” ሲል መክሯቸዋል። (ቆላ. 4:5, 6) ለቤተሰባችን አባላት በምንመሠክርበት ወቅት ይህን ምክር ማስታወሳችን በጣም ጠቃሚ ነው። ካልሆነ እነሱን ከማሳመን ይልቅ ከእውነት እንዲርቁ ልናደርጋቸው እንችላለን።

የቤተሰባችንን አባላት ለመርዳት ምን ማድረግ እንችላለን?

የሌሎችን ስሜት ለመረዳት ጥረት ማድረጋችሁና መልካም ምግባር ማሳየታችሁ ትልቅ ምሥክርነት ይሰጣል (ከአንቀጽ 6-8⁠ን ተመልከት) *

6-7. የማያምን የትዳር ጓደኛን ስሜት ለመረዳት ጥረት ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ የሚያሳይ ምሳሌ ጥቀስ።

6 ስሜታቸውን ለመረዳት ጥረት አድርጉ። በመግቢያው ላይ የተጠቀሰችው ፖሊን እንዲህ ብላለች፦ “መጀመሪያ ላይ፣ ከባለቤቴ ጋር ማውራት የምፈልገው ስለ መንፈሳዊ ነገሮች ብቻ ነበር። ከዚያ ውጭ ሌላ ምንም የማዋራው ነገር አልነበረም።” የፖሊን ባል ዌን ግን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያውቀው ነገር አልነበረም፤ በመሆኑም ፖሊን የምታወራውን ነገር መረዳት አልቻለም። ከሃይማኖቷ በቀር የምታስበው ነገር እንደሌለ ተሰምቶት ነበር። እንዲያውም አደገኛ የሆነ ኑፋቄ ውስጥ እንደገባችና እየተታለለች እንደሆነ ስላሰበ ሰግቶ ነበር።

7 መጀመሪያ አካባቢ ፖሊንም ብትሆን ምሽት ላይ እንዲሁም ቅዳሜና እሁድ ብዙ ጊዜዋን የምታሳልፈው በስብሰባ፣ በአገልግሎትና ወንድሞችና እህቶች ቤት ተጋብዛ እንደነበረ ታስታውሳለች። ፖሊን “አንዳንድ ጊዜ ዌን ወደ ቤት ሲመለስ፣ ባዶ ቤት ስለሚጠብቀው ብቸኝነት ይሰማው ጀመር” ብላለች። ዌን ባለቤቱና ልጁ እየራቁት እንደሆነ ቢሰማው የሚገርም አልነበረም። ባለቤቱና ልጁ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ከእነማን ጋር እንደሆነ አያውቅም፤ በዚያ ላይ ደግሞ ፖሊን አዲስ ላገኘቻቸው ወዳጆቿ ከእሱ የበለጠ ቦታ የምትሰጥ ይመስል ነበር። በመሆኑም ዌን ፖሊንን እንደሚፈታት መዛት ጀመረ። ፖሊን የባለቤቷን ስሜት ይበልጥ ለመረዳት ምን ማድረግ ትችል እንደነበረ አስተዋላችሁ?

8. በ1 ጴጥሮስ 3:1, 2 ላይ እንደተገለጸው የቤተሰባችንን አባላት ይበልጥ ሊማርክ የሚችለው ምንድን ነው?

8 በምግባራችሁ ምሥክርነት ስጡ። ብዙውን ጊዜ፣ ከምንናገረው ነገር ይልቅ የቤተሰባችንን አባላት ይበልጥ የሚማርከው ድርጊታችን ነው። (1 ጴጥሮስ 3:1, 2ን አንብብ።) ፖሊን ውሎ አድሮ ይህን እውነታ ተገንዝባለች። እንዲህ ብላለች፦ “ዌን መፋታት እንደሚፈልግ የተናገረው ከልቡ እንዳልሆነና እንደሚወደን አውቅ ነበር። ሆኖም የፍቺ ጥያቄ ማንሳቱ ነገሮችን በይሖዋ መንገድ ማከናወን እንዳለብኝ እንድገነዘብ አደረገኝ። ብዙ ከማውራት ይልቅ ጥሩ ምሳሌ በመሆን ምግባሬ እንዲናገር ማድረግ እንደሚያስፈልገኝ አስተዋልኩ።” ፖሊን ከባለቤቷ ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያወሩ ጫና ማድረጓን አቆመች፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ዕለት ተዕለት ጉዳዮች ታዋራው ጀመር። ዌን ባለቤቱ ይበልጥ ሰላማዊ እንደሆነችና ልጃቸውም ቢሆን ጠባዩ እንደተሻሻለ አስተዋለ። (ምሳሌ 31:18, 27, 28) ዌን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት በቤተሰቡ ላይ ያሳደረውን በጎ ተጽዕኖ ሲያስተውል በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን እውነት መቀበል ቀላል ሆነለት።—1 ቆሮ. 7:12-14, 16

9. የቤተሰባችንን አባላት ለመርዳት ጥረት ማድረጋችንን ማቋረጥ የሌለብን ለምንድን ነው?

9 የቤተሰባችሁን አባላት ለመርዳት የምታደርጉትን ጥረት አታቋርጡ። ይሖዋ በዚህ ረገድ ምሳሌ ይሆነናል። ሰዎች ምሥራቹን በመቀበል ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ‘ደግሞ ደጋግሞ’ አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። (ኤር. 44:4) ሐዋርያው ጳውሎስም ጢሞቴዎስን፣ ሌሎችን ለመርዳት በሚያደርገው ጥረት እንዲጸና አበረታቶታል። ለምን? ምክንያቱም ይህን ሲያደርግ ራሱንም ሆነ የሚሰሙትን ያድናል። (1 ጢሞ. 4:16) እኛም የቤተሰባችንን አባላት ስለምንወዳቸው በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን እውነቶች እንዲያውቁ እንፈልጋለን። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ፖሊን የምትናገረው ነገርና ምግባሯ ውሎ አድሮ በቤተሰቧ ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳደረ። በአሁኑ ጊዜ ባለቤቷም አብሯት ይሖዋን እያገለገለ ነው። ሁለቱም አቅኚዎች ሲሆኑ ዌን ደግሞ የጉባኤ ሽማግሌ ነው።

10. ትዕግሥተኛ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

10 ትዕግሥተኛ ሁኑ። ሕይወታችንን በአምላክ መሥፈርቶች መሠረት ለመምራት ጥረት ማድረግ ስንጀምር፣ የቤተሰባችን አባላት በምናምንባቸው ነገሮች ላይ እንዲሁም በሕይወታችን ውስጥ ያደረግነውን ለውጥ መቀበል ሊከብዳቸው ይችላል። ብዙውን ጊዜ መጀመሪያ ላይ የሚያስተውሉት ነገር አብረናቸው ሃይማኖታዊ በዓላትን ማክበር እንደተውንና በፖለቲካ ጉዳዮች እንደማንሳተፍ ነው። አንዳንድ የቤተሰባችን አባላት መጀመሪያ ላይ ይበሳጩብን ይሆናል። (ማቴ. 10:35, 36) ሆኖም አመለካከታቸውን ፈጽሞ እንደማይለውጡ ልናስብ አይገባም። የምናምንባቸውን ነገሮች እንዲረዱ ለማድረግ መጣራችንን ካቆምን፣ የዘላለም ሕይወት የማይገባቸው ሰዎች እንደሆኑ አድርገን የፈረድንባቸው ያህል ነው። ይሖዋ የመፍረድ ሥልጣን የሰጠው ለእኛ ሳይሆን ለኢየሱስ ነው። (ዮሐ. 5:22) ትዕግሥተኛ ከሆንን የቤተሰባችን አባላት ከጊዜ በኋላ መልእክታችንን ለማዳመጥ ፈቃደኛ ሊሆኑ ይችላሉ።—“ በድረ ገጻችን ተጠቅማችሁ አስተምሩ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

11-13. አሊስ ወላጆቿን ከያዘችበት መንገድ ምን ትምህርት እናገኛለን?

11 ቆራጥ ሆኖም ዘዴኛ ሁኑ። (ምሳሌ 15:2) የአሊስን ተሞክሮ እንመልከት። አሊስ ስለ ይሖዋ የተማረችው ከወላጆቿ ርቃ እየኖረች ባለበት ወቅት ነው፤ ወላጆቿ ፖለቲከኞችና በአምላክ መኖር የማያምኑ ሰዎች ነበሩ። አሊስ እየተማረች ያለችውን አስደሳች ነገር በተቻለ መጠን ወዲያውኑ ለወላጆቿ መናገር እንዳለባት ተገንዝባ ነበር። “ስለ አዲሱ እምነታችሁ ለመናገር የምትዘገዩ ከሆነ ቤተሰቦቻችሁ ጉዳዩን በሚያውቁበት ጊዜ ይበልጥ ይደናገጣሉ” ብላለች። አሊስ ለወላጆቿ ደብዳቤ የጻፈች ሲሆን የእነሱን ትኩረት ሊስቡ የሚችሉ እንደ ፍቅር ያሉ ርዕሰ ጉዳዮችን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚያስተምር ነገረቻቸው፤ ከዚያም አመለካከታቸውን ጠየቀቻቸው። (1 ቆሮ. 13:1-13) በተጨማሪም ወላጆቿ ተንከባክበው ስላሳደጓት ምስጋናዋን በመግለጽ ስጦታ ላከችላቸው። ወላጆቿን ለመጠየቅ በሄደችባቸው ጊዜያት ደግሞ ቤት ውስጥ እናቷን ሥራ ለማገዝ ለየት ያለ ጥረት ታደርግ ነበር። በእርግጥ አሊስ ስለ አዲሱ እምነቷ ለወላጆቿ ስትነግራቸው መጀመሪያ ላይ አልተደሰቱም።

12 አሊስ፣ ወላጆቿ ቤት በምትቆይበት ጊዜም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራሟን በጥብቅ ትከተል ነበር። አሊስ “ይህን ማድረጌ እናቴ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ምን ያህል ከፍ አድርጌ እንደምመለከት እንድትገነዘብ አስችሏታል” ብላለች። የአሊስ አባት ደግሞ የልጁን አመለካከት የቀየረው ምን እንደሆነ ለመረዳት ሲል ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የተወሰነ ነገር ለማወቅ ወሰነ፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስህተት ማግኘትም ፈልጎ ነበር። “ለአባቴ መጽሐፍ ቅዱስ የሰጠሁት ሲሆን ላዩ ላይ አጭር ማስታወሻ ጽፌለት ነበር” ብላለች። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? የአሊስ አባት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስህተት አላገኘም፤ እንዲያውም በአምላክ ቃል ላይ ያነበበው ነገር ልቡን በጥልቅ ነካው።

13 ተቃውሞን መቋቋም ቢያስፈልገንም እንኳ ዘዴኛ ሆኖም ቆራጥ ልንሆን ይገባል። (1 ቆሮ. 4:12ለ) ለምሳሌ ያህል፣ አሊስ የእናቷን ተቃውሞ መቋቋም ነበረባት። አሊስ ስለ ሁኔታው ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “ስጠመቅ እናቴ ‘መጥፎ ልጅ ነሽ’ አለችኝ።” ታዲያ ምን አደረገች? “ጉዳዩን ለማረሳሳት ከመሞከር ይልቅ የይሖዋ ምሥክር ለመሆን እንደቆረጥኩና በዚህ ውሳኔዬ እንደምጸና በአክብሮት አስረዳኋት። እናቴን ከልቤ እንደምወዳት አረጋገጥኩላት። ይህን ስናወራ ሁለታችንም አለቀስን፤ በኋላ ላይ የሚጣፍጥ ምግብ ሠራሁላት። ከዚያ ጊዜ ወዲህ እናቴ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የተሻልኩ ሰው ለመሆን እንደረዳኝ መግለጽ ጀመረች።”

14. አቋማችንን እንድናላላ ለሚደርስብን ጫና ፈጽሞ እጅ መስጠት የሌለብን ለምንድን ነው?

14 የቤተሰባችን አባላት፣ ይሖዋን ለማገልገል ያደረግነው ውሳኔ በቁም ነገር ያሰብንበት ጉዳይ እንደሆነ እስኪገነዘቡ ጊዜ ሊወስድ ይችላል። ለምሳሌ አሊስ፣ ወላጆቿ እንደሚፈልጉት ከፍተኛ ትምህርት መከታተሏን ከመቀጠል ይልቅ አቅኚ ለመሆን ስትወስን እናቷ እንደገና አለቀሰች። አሊስ ግን በአቋሟ ጸናች። እንዲህ ብላለች፦ “ቤተሰቦቻችሁ በአንድ ጉዳይ ላይ ጫና ሲያደርጉባችሁ እጅ ከሰጣችሁ በሌሎች ጉዳዮች ላይም ጫና ሊያሳድሩባችሁ መሞከራቸው አይቀርም። ሆኖም አቋማችሁን እንደማታላሉ በደግነት ከገለጻችሁላቸው፣ አንዳንዶቹ የቤተሰባችሁ አባላት ሐሳባችሁን ይቀበሏችሁ ይሆናል።” አሊስ ይህን በራሷ ሕይወት አይታዋለች። በአሁኑ ወቅት ወላጆቿ አቅኚ ሆነው የሚያገለግሉ ሲሆን አባቷም የጉባኤ ሽማግሌ ነው።

የጉባኤው አባላት አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?

ጉባኤው፣ የማያምን የቤተሰባችንን አባል መርዳት የሚችለው እንዴት ነው? (ከአንቀጽ 15-16⁠ን ተመልከት) *

15. በማቴዎስ 5:14-16 እና በ1 ጴጥሮስ 2:12 ላይ እንደተገለጸው የሌሎች “መልካም ሥራ” የቤተሰባችንን አባላት የሚረዳቸው እንዴት ነው?

15 ይሖዋ የክርስቲያን ጉባኤ አባላት በሚያከናውኑት “መልካም ሥራ” አማካኝነት ሰዎችን ወደ ራሱ ይስባል። (ማቴዎስ 5:14-16ን እና 1 ጴጥሮስ 2:12ን አንብብ።) የትዳር ጓደኛሽ የይሖዋ ምሥክር ካልሆነ፣ ከጉባኤሽ አባላት ጋር ተገናኝቶ ያውቃል? ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ፖሊን፣ ባለቤቷ ዌን ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር እንዲተዋወቅ ስትል ቤቷ ትጋብዛቸው ነበር። ዌን የነበረውን የተሳሳተ አመለካከት ለማስተካከል አንድ ወንድም እንዴት እንደረዳው ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ከእኔ ጋር የስፖርት ጨዋታ ለማየት ሲል ከሥራው እረፍት ወሰደ። ይህን ሳይ ‘ለካስ እንደማንኛውም ሰው ነው!’ ብዬ አሰብኩ።”

16. የቤተሰባችን አባላት በስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ መጋበዝ ያለብን ለምንድን ነው?

16 የቤተሰባችንን አባላት ለመርዳት የሚያስችለን አንዱ ግሩም መንገድ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ መጋበዝ ነው። (1 ቆሮ. 14:24, 25) ዌን ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘበት ስብሰባ የመታሰቢያው በዓል ነበር፤ በዓሉ የሚከበረው ከሥራ ሰዓት በኋላ መሆኑና ፕሮግራሙ አጠር ማለቱ በስብሰባው ላይ መገኘት ቀላል እንዲሆንለት አድርጓል። ዌን እንዲህ ብሏል፦ “ንግግሩ በደንብ ባይገባኝም ሰዎቹን ግን አልረሳቸውም። ወደ እኔ መጥተው እጄን እየጨበጡ ሞቅ ያለ ሰላምታ ሰጡኝ። ጥሩ ሰዎች እንደሆኑ ማስተዋል ቻልኩ።” በተለይ አንድ ባልና ሚስት ለፖሊን ልዩ ደግነት ያሳዩዋት ነበር፤ በስብሰባዎችና በአገልግሎት ላይ ልጇን በመያዝ ፖሊንን ያግዟት ነበር። ከጊዜ በኋላ ዌን፣ ፖሊን ስለምታምንባቸው ነገሮች ለመመርመር ሲወስን መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያስጠናው የጠየቀው ባልየውን ነው።

17. ስለ ምን ጉዳይ ራሳችንን መውቀስ የለብንም? የቤተሰባችንን አባላት ለመርዳት የምናደርገውን ጥረት ማቋረጥ የሌለብን ግን ለምንድን ነው?

17 የቤተሰባችን አባላት በሙሉ አብረውን ይሖዋን ቢያገለግሉ ደስ ይለናል። ይሁንና የቤተሰባችን አባላት የአምላክ አገልጋዮች እንዲሆኑ ምንም ያህል ጥረት ብናደርግ ወደ እውነት ላይመጡ ይችላሉ። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ካጋጠመን በእነሱ ውሳኔ ራሳችንን ልንወቅስ አይገባም። ደግሞም የምናምንበትን ነገር እንዲቀበል ማንንም ሰው ማስገደድ አንችልም። ይሁን እንጂ የቤተሰባችሁ አባላት፣ ይሖዋን ማገልገላችሁ ምን ያህል ደስታ እንዳስገኘላችሁ መመልከታቸው ሊያሳድርባቸው የሚችለውን በጎ ተጽዕኖ አቅልላችሁ አትመልከቱት። ስለ እነሱ ጸልዩ። በዘዴ መሥክሩላቸው። እነሱን ከመርዳት ወደኋላ አትበሉ! (ሥራ 20:20) ይሖዋ ጥረታችሁን እንደሚባርክላችሁ እርግጠኛ ሁኑ። የቤተሰባችሁ አባላት መልእክታችሁን ለመስማት ፈቃደኛ ከሆኑ ደግሞ መዳን ያገኛሉ!

መዝሙር 57 ለሁሉም ዓይነት ሰዎች መስበክ

^ አን.5 የቤተሰባችን አባላት ይሖዋን እንዲያውቁ እንፈልጋለን፤ ሆኖም እሱን ማገልገል፣ እነሱ ራሳቸው ሊያደርጉት የሚገባ ውሳኔ ነው። የቤተሰባችን አባላት የምንነግራቸውን መልእክት መስማት ቀላል እንዲሆንላቸው ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ በዚህ ርዕስ ላይ እንመለከታለን።

^ አን.1 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል። ይህ ርዕስ የሚያተኩረው ይሖዋን ማገልገል ባልጀመሩ የቅርብ ቤተሰባችን አባላት ላይ ቢሆንም ትምህርቱ ከሌሎች ዘመዶቻችን ጋር በተያያዘም ይሠራል።

^ አን.53 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ወጣት ወንድም አባቱ መኪና ሲጠግን እያገዘው። አመቺ አጋጣሚ ሲያገኝ በjw.org® ላይ የሚገኝ ቪዲዮ ለአባቱ አሳየው።

^ አን.55 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንዲት እህት የማያምን ባሏ ስለ ውሎው ሲነግራት በጥሞና እያዳመጠች ነው። በኋላ ላይ ከቤተሰቧ ጋር ሲዝናኑ ይታያል።

^ አን.57 የሥዕሉ መግለጫ፦ ይህች እህት አንዳንድ የጉባኤዋን አባላት ቤቷ ጋብዛለች። ወንድሞች ባልየውን ለማጫወት ጥረት ያደርጋሉ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ባልየው በመታሰቢያው በዓል ላይ ይገኛል።