በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 34

‘በእውነት ውስጥ ተመላለሱ’

‘በእውነት ውስጥ ተመላለሱ’

‘በእውነት ውስጥ ተመላለሱ።’—3 ዮሐ. 4

መዝሙር 111 ለደስታችን ምክንያት የሆኑ ነገሮች

ማስተዋወቂያ *

1. ‘እውነትን’ ስለሰማንበት መንገድ መነጋገራችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

 “እውነትን የሰማኸው እንዴት ነው?” ይህን ጥያቄ ብዙ ጊዜ መልሰህ እንደምታውቅ ጥርጥር የለውም። ከአንድ የይሖዋ ምሥክር ጋር ስንተዋወቅ ከምናነሳቸው የመጀመሪያ ጥያቄዎች መካከል አንዱ ይህ ነው። ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ይሖዋን ማወቅና መውደድ የቻሉት እንዴት እንደሆነ መስማት እንዲሁም ለእውነት ምን ያህል ፍቅር እንዳለን መናገር ያስደስተናል። (ሮም 1:11) እንዲህ ያሉ ጭውውቶችን ማድረጋችን እውነት ምን ያህል ውድ እንደሆነ ያስታውሰናል። በተጨማሪም ‘በእውነት ውስጥ ለመመላለስ’ ማለትም የይሖዋን በረከትና ሞገስ በሚያስገኝ መንገድ መኖራችንን ለመቀጠል ያለንን ቁርጠኝነት ያጠናክረዋል።—3 ዮሐ. 4

2. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

2 እውነትን እንድንወደው ያደረጉንን አንዳንድ ምክንያቶች በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን። ከዚያም ለዚህ ውድ ስጦታ ያለንን ፍቅር ማሳየታችንን መቀጠል የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን። ስለዚህ ጉዳይ መወያየታችን ይሖዋ እኛን ወደ እውነት በመሳብ ላደረገልን ዝግጅት ያለንን አድናቆት እንደሚጨምረው ጥያቄ የለውም። (ዮሐ. 6:44) በተጨማሪም እውነትን ለሌሎች ለማካፈል ያለንን ፍላጎት ያጠናክርልናል።

‘እውነትን’ የምንወደው ለምንድን ነው?

3. እውነትን የምንወድበት ዋነኛ ምክንያት ምንድን ነው?

3 እውነትን ለመውደድ የሚያነሳሱን ብዙ ምክንያቶች አሉ። ዋነኛው ምክንያት የእውነት ምንጭ የሆነውን ይሖዋ አምላክን ስለምንወደው ነው። ይሖዋ ሰማይንና ምድርን የፈጠረ ሁሉን ቻይ አምላክ መሆኑን ብቻ ሳይሆን በርኅራኄ የሚንከባከበን አፍቃሪ የሰማዩ አባታችን መሆኑንም በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ተምረናል። (1 ጴጥ. 5:7) አምላካችን “መሐሪና ሩኅሩኅ . . . ለቁጣ የዘገየ፣ ታማኝ ፍቅሩና እውነቱ እጅግ ብዙ የሆነ” አምላክ እንደሆነ እናውቃለን። (ዘፀ. 34:6) ይሖዋ ፍትሕን ይወዳል። (ኢሳ. 61:8) ስንሠቃይ ሲያይ ልቡ በጣም ያዝናል፤ በወሰነው ጊዜም መከራንና ሥቃይን በሙሉ ለማስወገድ ዝግጁ ነው፤ አልፎ ተርፎም ይጓጓል። (ኤር. 29:11) እንዴት ደስ ይላል! ይሖዋን በጣም የምንወደው ለዚህ ነው!

የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በምን ተመስሏል?⁠—⁠በመልሕቅ

መልሕቅ አንድ መርከብ እንዳይናወጥ አጥብቆ እንደሚይዘው ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተው ተስፋችንም ፈተናዎች ሲያጋጥሙን ያረጋጋናል። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የወደፊት ተስፋችንን ለሌሎች እንድናካፍል ያነሳሳናል (ከአንቀጽ 4-7⁠ን ተመልከት)

4-5. ሐዋርያው ጳውሎስ ተስፋችንን ከመልሕቅ ጋር ያመሳሰለው ለምንድን ነው?

4 እውነትን ለመውደድ የሚያነሳሳን ሌላው ምክንያት ምንድን ነው? እውነት ብዙ ጥቅሞችን ያስገኝልናል። አንድ ምሳሌ እናንሳ። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ስለ ወደፊቱ ጊዜ ያለንን ተስፋ ያካትታል። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህ ተስፋ ያለውን ዋጋ በምሳሌ ለማስረዳት እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “እኛ ለነፍሳችን እንደ መልሕቅ አስተማማኝና ጽኑ የሆነ ይህ ተስፋ አለን።” (ዕብ. 6:19) መልሕቅ አንድ መርከብ እንዳይናወጥ አጥብቆ እንደሚይዘው ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተው ተስፋችንም በሕይወታችን ውስጥ ፈተናዎች ሲያጋጥሙን እንድንረጋጋ ይረዳናል።

5 ጳውሎስ እዚህ ጥቅስ ላይ እየተናገረ ያለው ቅቡዓን ክርስቲያኖች ስላላቸው ሰማያዊ ተስፋ ነው። ሆኖም የተናገረው ሐሳብ ገነት በሆነችው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ላላቸው ክርስቲያኖችም ይሠራል። (ዮሐ. 3:16) ስለ ዘላለም ሕይወት ተስፋ መማራችን ሕይወታችን ትርጉም እንዲኖረው እንደረዳን ምንም ጥያቄ የለውም።

6-7. ኢቮን ስለ ወደፊቱ ጊዜ እውነቱን መማሯ የጠቀማት እንዴት ነው?

6 ኢቮን የተባለችን አንዲት እህት ተሞክሮ እንመልከት። ኢቮን ያደገችው እውነት ውስጥ አይደለም። በልጅነቷ ሞትን በጣም ትፈራ ነበር። በአንድ ወቅት ያነበበችው “ነገ የማይኖርበት ቀን ይመጣል” የሚል አባባል ከአእምሮዋ ሊወጣ አልቻለም። እንዲህ ብላለች፦ “በእነዚህ ቃላት የተነሳ ስለ ወደፊቱ ጊዜ እያሰብኩ እንቅልፍ አጥቼ አድር ነበር። ‘መቼም ሕይወት ይህ ብቻ ሊሆን አይችልም። ወደዚህ ዓለም የመጣሁት ለምንድን ነው?’ ብዬ አስብ ነበር። መሞት አልፈልግም ነበር!”

7 በኋላም ኢቮን በአሥራዎቹ ዕድሜ እያለች ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘች። እንዲህ ብላለች፦ “በምድር ላይ በገነት ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋ እንዳለኝ ማመን ጀመርኩ።” እህታችን እውነትን ማወቋ የጠቀማት እንዴት ነው? “አሁን ስለ ወደፊቱ ጊዜ ወይም ስለ ሞት እየተጨነቅኩ እንቅልፍ አጥቼ አላድርም” ብላለች። ኢቮን እውነትን በጣም ከፍ አድርጋ እንደምትመለከተው ምንም ጥያቄ የለውም። ስለ ወደፊቱ ጊዜ ያላትን ተስፋ ለሌሎች ማካፈልም ከፍተኛ እርካታ ይሰጣታል።

የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በምን ተመስሏል?⁠—⁠በውድ ሀብት

በአሁኑ ወቅት እንዲሁም ወደፊት በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ለዘላለም ይሖዋን የማገልገል መብት እንደ ውድ ሀብት ነው። የትኛውም መሥዋዕት ቢከፈልለት አያስቆጭም (ከአንቀጽ 8-11⁠ን ተመልከት)

8-9. (ሀ) ኢየሱስ በጠቀሰው ምሳሌ ላይ ሰውየው ያገኘውን ውድ ሀብት ምን ያህል ከፍ አድርጎ ተመልክቶታል? (ለ) ለእውነት ምን አመለካከት አለህ?

8 የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸውን ምሥራችም ያካትታል። ኢየሱስ ስለ መንግሥቱ የሚናገረውን እውነት ከተደበቀ ሀብት ጋር አመሳስሎታል። በማቴዎስ 13:44 ላይ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “መንግሥተ ሰማያት በእርሻ ውስጥ ከተደበቀ ውድ ሀብት ጋር ይመሳሰላል፤ አንድ ሰው ባገኘው ጊዜ ሸሸገው፤ ከመደሰቱም የተነሳ ሄዶ ያለውን ሁሉ በመሸጥ እርሻውን ገዛው።” ሰውየው በወቅቱ ያንን ውድ ሀብት እየፈለገ እንዳልነበር ልብ በል። ሆኖም ሲያገኘው ያንን ውድ ሀብት እጁ ለማስገባት ሲል ትልቅ መሥዋዕት ከፍሏል። እንዲያውም ያለውን ሁሉ ሸጧል። ለምን? ያ ሀብት ምን ያህል ውድ እንደሆነ ስለተገነዘበ ነው። መሥዋዕት ካደረገው ነገር ሁሉ የሚበልጥ ዋጋ አለው።

9 አንተስ ስለ እውነት እንደዚያ ይሰማሃል? እንደሚሰማህ ጥያቄ የለውም! ይህ ዓለም የሚያቀርብልን ማንኛውም ነገር በአሁኑ ጊዜ ይሖዋን በማገልገል ከምናገኘው ደስታ እንዲሁም ወደፊት በመንግሥቱ አገዛዝ ሥር የዘላለም ሕይወት ከማግኘት ተስፋችን ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና የመመሥረት መብት ምንም ዓይነት መሥዋዕት ቢከፈልለት የሚያስቆጭ አይደለም። ‘እሱን ሙሉ በሙሉ ማስደሰት’ ከምንም በላይ ያስደስተናል።—ቆላ. 1:10

10-11. ማይክል የሕይወቱን አቅጣጫ እንዲቀይር ያነሳሳው ምንድን ነው?

10 ብዙዎቻችን የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት ስንል ትላልቅ መሥዋዕቶችን ከፍለናል። አንዳንዶች በዓለም ላይ አንቱ የሚያስብል ሥራቸውን ትተዋል። ሌሎች ሀብትን ማሳደዳቸውን አቁመዋል። ሌሎች ደግሞ ስለ ይሖዋ ሲማሩ የሕይወት አቅጣጫቸውን ሙሉ በሙሉ ቀይረዋል። ማይክልም ያደረገው ይህንን ነው። ያደገው እውነት ቤት አይደለም። በወጣትነቱ የካራቴ ሥልጠና ወስዶ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “ጥሩ ተክለ ሰውነት ያለኝ መሆኑ ያኮራኝ ነበር። እንዲያውም አንዳንዴ የማልበገር እንደሆንኩ ይሰማኝ ነበር።” ማይክል መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ሲጀምር ግን ይሖዋ ለዓመፅ ያለውን አመለካከት ተማረ። (መዝ. 11:5) ማይክል ያስጠኑትን ባልና ሚስት አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ካራቴ ማቆም እንዳለብኝ ነግረውኝ አያውቁም። ዝም ብለው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት አስተማሩኝ።”

11 ማይክል ስለ ይሖዋ ይበልጥ በተማረ መጠን ለእሱ ያለው ፍቅር እያደገ ሄደ። በተለይም ይሖዋ ለአገልጋዮቹ የሚያሳየው ርኅራኄ ልቡን ነካው። ውሎ አድሮ ማይክል ሕይወቱን የሚቀይር ውሳኔ ማድረግ እንዳለበት ተገነዘበ። እንዲህ ብሏል፦ “ካራቴ ማቆም እስካሁን በሕይወቴ ካደረግኳቸው ውሳኔዎች ሁሉ ከባዱ እንደሚሆን አውቄ ነበር። ሆኖም እንዲህ ማድረጌ ይሖዋን እንደሚያስደስተውም ተገንዝቤያለሁ። ደግሞም ይሖዋን ማገልገል የትኛውም መሥዋዕትነት ቢከፈልለት እንደማያስቆጭ እርግጠኛ ነበርኩ።” ማይክል፣ ያገኘው እውነት ያለውን ውድ ዋጋ ተገንዝቧል። ይህም በሕይወቱ ውስጥ ትላልቅ ለውጦችን እንዲያደርግ አነሳስቶታል።—ያዕ. 1:25

የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በምን ተመስሏል?⁠—⁠በመብራት

ኃይለኛ መብራት በጨለማ ውስጥ መንገዳችንን እንድናገኝ ይረዳናል። በተመሳሳይም የአምላክ ቃል በጨለማ በተዋጠው የሰይጣን ዓለም ውስጥ መንገድ ይመራናል (ከአንቀጽ 12-13⁠ን ተመልከት)

12-13. የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ማይሊን የረዳት እንዴት ነው?

12 መጽሐፍ ቅዱስ የእውነትን ዋጋ ለማሳየት፣ እውነትን በጨለማ ውስጥ ከሚያበራ መብራት ጋር ያመሳስለዋል። (መዝ. 119:105፤ ኤፌ. 5:8) በአዘርባጃን የምትኖረው ማይሊ ከአምላክ ቃል ላገኘችው ብርሃን ከፍተኛ አድናቆት አላት። ያደገችው በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ ነው። አባቷ ሙስሊም፣ እናቷ ደግሞ የአይሁድ እምነት ተከታይ ነበሩ። እንዲህ ብላለች፦ “የአምላክን መኖር ተጠራጥሬ ባላውቅም ብዙ ጥያቄዎች አእምሮዬ ውስጥ ይመላለሱ ነበር። ‘አምላክ ሰዎችን የፈጠረው ለምንድን ነው? አንድ ሰው ዕድሜ ልኩን በመከራ ውስጥ ኖሮ ከዚያ ደግሞ ለዘላለም ሲኦል ውስጥ የሚሠቃይበት ምን ምክንያት አለ?’ ብዬ አስብ ነበር። ሰዎች ሁሉም ነገር የሚሆነው በአምላክ ፈቃድ መሠረት እንደሆነ ስለሚናገሩ ‘አምላክ የሰዎችን ሕይወት እየተቆጣጠረ እነሱ ሲሠቃዩ ማየት ያስደስተዋል ማለት ነው?’ ብዬ አስብ ነበር።”

13 ማይሊ ለጥያቄዎቿ መልስ መፈለጓን ቀጠለች። ከጊዜ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን አጥንታ ወደ እውነት መጣች። እንዲህ ብላለች፦ “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው አሳማኝ ማስረጃ ለሕይወት ያለኝን አመለካከት ሙሉ በሙሉ ቀየረው። በአምላክ ቃል ውስጥ ያገኘሁት ምክንያታዊ ማብራሪያ ውስጣዊ ሰላም እንዳገኝ ረዳኝ።” እኛም እንደ ማይሊ ‘ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ የጠራንን’ ይሖዋን እናወድሳለን።—1 ጴጥ. 2:9

14. ለእውነት ያለንን ፍቅር ማሳደግ የምንችለው እንዴት ነው? (“ ሌላስ በምን ተመስሏል?” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

14 እስካሁን የተመለከትነው የእውነትን ዋጋ የሚያሳዩ ጥቂት ምሳሌዎችን ብቻ ነው። ሌሎች ብዙ ምሳሌዎችንም እንደምታስታውስ ምንም ጥያቄ የለውም። እውነትን ለመውደድ የሚያነሳሱንን ሌሎች ምክንያቶች በግል ጥናትህ ላይ ለማግኘት ለምን ጥረት አታደርግም? እውነትን ይበልጥ በወደድን መጠን ለእውነት ያለንን ፍቅር ለማሳየት የሚያስችሉ ብዙ መንገዶችን እናገኛለን።

እውነትን እንደምንወድ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

15. እውነትን እንደምንወድ ማሳየት የምንችልበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?

15 መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን አዘውትረን በማጥናት እውነትን እንደምንወድ ማሳየት እንችላለን። ደግሞም እውነት ውስጥ የቆየንበት ጊዜ ምንም ያህል ረጅም ቢሆን ሁሌም የምንማረው ነገር አለ። የዚህ መጽሔት የመጀመሪያ እትም እንዲህ የሚል ሐሳብ ይዞ ወጥቶ ነበር፦ “እውነት በጣም ተንሰራፍቶ በሚገኝ የሐሰት አረም ልትዋጥ ምንም ያህል እንዳልቀራት በሕይወት ጫካ ውስጥ እንደምትገኝ ትንሽ አበባ ናት። ልታገኛት የምትሻ ከሆነ በትጋት ልትፈልጋት ይገባል። . . . የራስህ ልታደርጋት ከፈለግክ ደግሞ ጎንበስ ብለህ ማንሳት ይኖርብሃል። አንድ የእውነት አበባ ስላገኘህ ብቻ አትርካ። . . . መሰብሰብህን አታቋርጥ፤ ፍለጋህን ቀጥል።” ጥናት ጥረት እንደሚጠይቅ የታወቀ ነው፤ ሆኖም የምናደርገው ጥረት የሚክስ ነው።

16. ውጤታማ ሆኖ ያገኘኸው የጥናት ዘዴ የትኛው ነው? (ምሳሌ 2:4-6)

16 እርግጥ ማንበብና ማጥናት የምንወደው ሁላችንም አይደለንም። ሆኖም ይሖዋ ስለ እውነት ጥልቅ ግንዛቤ ለማግኘት ‘ተግተን እንድንፈልግ’ እንዲሁም ‘አጥብቀን እንድንሻ’ ጋብዞናል። (ምሳሌ 2:4-6ን አንብብ።) እንዲህ ያለውን ጥረት ስናደርግ ሁሌም እንጠቀማለን። ኮሪ መጽሐፍ ቅዱስን ስለሚያነብበት መንገድ ሲናገር በእያንዳንዷ ጥቅስ ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ተናግሯል። እንዲህ ብሏል፦ “ሁሉንም የግርጌ ማስታወሻዎች አነብባለሁ፤ ሁሉንም የኅዳግ ማጣቀሻዎች እመለከታለሁ፤ እንዲሁም ተጨማሪ ምርምር አደርጋለሁ። . . . ይህን ዘዴ በመጠቀሜ ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባቤ ብዙ ጥቅም አግኝቻለሁ!” እኛም የምንጠቀመው ዘዴ ይህም ሆነ ሌላ፣ እውነትን ለማጥናት ጊዜና ጥረት የምናውል ከሆነ ለእውነት ያለንን አድናቆት እናሳያለን።—መዝ. 1:1-3

17. በእውነት ውስጥ መመላለስ ሲባል ምን ማለት ነው? (ያዕቆብ 1:25)

17 እርግጥ ነው፣ እውነትን ማጥናታችን ብቻውን በቂ እንዳልሆነ እናውቃለን። የተሟላ ጥቅም ለማግኘት በእውነት ውስጥ መመላለስ፣ ማለትም የተማርነውን ነገር በሕይወታችን ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልገናል። እውነት እውነተኛ ደስታ የሚያስገኝልን እንዲህ ካደረግን ብቻ ነው። (ያዕቆብ 1:25ን አንብብ።) በእውነት ውስጥ እየተመላለስን መሆኑን ማረጋገጥ የምንችለው እንዴት ነው? አንድ ወንድም፣ ራሳችንን በሐቀኝነት በመመርመር በየትኞቹ አቅጣጫዎች ጥሩ እየሠራን እንደሆነ፣ በየትኞቹ አቅጣጫዎች ደግሞ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚያስፈልገን መገምገም እንደምንችል ሐሳብ ሰጥቷል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “ምንም ያህል እድገት ያደረግን ብንሆን በዚሁ መንገድ በአግባቡ ወደፊት መጓዛችንን እንቀጥል።”—ፊልጵ. 3:16

18. ‘በእውነት ውስጥ ለመመላለስ’ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ የምናደርገው ለምንድን ነው?

18 ‘በእውነት ውስጥ ለመመላለስ’ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ማድረጋችን የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች እስቲ ለማሰብ ሞክር! ሕይወታችን ይሻሻላል፤ ይህ ብቻ ሳይሆን ለይሖዋም ሆነ ለእምነት ባልንጀሮቻችን የደስታ ምንጭ እንሆናለን። (ምሳሌ 27:11፤ 3 ዮሐ. 4) እውነትን ለመውደድና በእውነት ውስጥ ለመመላለስ የሚያነሳሳ ከዚህ የበለጠ ምን ምክንያት ሊኖር ይችላል?

መዝሙር 144 ዓይንህ ሽልማቱ ላይ ያተኩር!

^ ብዙውን ጊዜ ስለ እምነታችን እንዲሁም ሕይወታችንን ስለምንመራበት መንገድ ስንናገር “እውነት” የሚለውን ቃል እንጠቀማለን። አዲሶችም እንሁን ለረጅም ዘመን እውነት ውስጥ የቆየን ክርስቲያኖች፣ እውነትን የምንወደው ለምን እንደሆነ መመርመራችን በእጅጉ ይጠቅመናል። እንዲህ ማድረጋችን የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት ያለንን ቁርጠኝነት ያጠናክረዋል።