በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 36

የይሖዋ ሕዝቦች ጽድቅን ይወዳሉ

የይሖዋ ሕዝቦች ጽድቅን ይወዳሉ

“ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ደስተኞች ናቸው።”—ማቴ. 5:6

መዝሙር 9 ይሖዋ ንጉሣችን ነው!

ማስተዋወቂያ *

1. ዮሴፍ ምን ፈተና አጋጠመው? እሱስ ምን ምላሽ ሰጠ?

 የያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ ከባድ ፈተና አጋጥሞት ነበር። አንዲት ሴት “ከእኔ ጋር ተኛ” አለችው። ሴትየዋ የጌታው የጶጢፋር ሚስት ነበረች። ዮሴፍ ግን ጥያቄዋን ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆነም። አንዳንዶች ‘ዮሴፍ ይህን ፈተና መቋቋም ያስፈለገው ለምንድን ነው?’ የሚል ጥያቄ ያነሱ ይሆናል። ጶጢፋር በቦታው አልነበረም። በዚያ ላይ ዮሴፍ ባሪያ ነው፤ ሴትየዋን እንቢ ካላት ሕይወቱን መራራ እንደምታደርግበት ጥያቄ የለውም። ያም ቢሆን ሴትየዋ በተደጋጋሚ ብትወተውተውም ዮሴፍ ፈቃደኛ አልሆነም። ለምን? ዮሴፍ “እንዲህ ያለውን እጅግ መጥፎ ድርጊት በመፈጸም በአምላክ ላይ እንዴት ኃጢአት እሠራለሁ?” ብሏል።—ዘፍ. 39:7-12

2. ዮሴፍ ምንዝር በአምላክ ዓይን ኃጢአት እንደሆነ ያወቀው እንዴት ነው?

2 ዮሴፍ፣ አምላኩ ምንዝርን “እጅግ መጥፎ ድርጊት” አድርጎ እንደሚመለከተው ያወቀው እንዴት ነው? “አታመንዝር” የሚል ግልጽ ትእዛዝ የያዘው የሙሴ ሕግ የተጻፈው ከሁለት መቶ ዓመት በኋላ ነው። (ዘፀ. 20:14) ያም ቢሆን ዮሴፍ ይሖዋን በደንብ ስለሚያውቀው ስለ ምንዝር ምን እንደሚሰማው ተገንዝቦ ነበር። ለምሳሌ ይሖዋ የጋብቻን ዝግጅት ያቋቋመው በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል የሚመሠረት ጥምረት አድርጎ እንደሆነ ዮሴፍ እንደሚያውቅ ጥያቄ የለውም። በተጨማሪም ቅድመ አያቱን ሣራን ሌሎች ወንዶች ሊወስዷት ሲሉ ይሖዋ ሁለት ጊዜ ጣልቃ ገብቶ እንደጠበቃት ዮሴፍ ሰምቶ መሆን አለበት። አምላክ የይስሐቅ ሚስት ለሆነችው ለርብቃም ተመሳሳይ ጥበቃ አድርጎላታል። (ዘፍ. 2:24፤ 12:14-20፤ 20:2-7፤ 26:6-11) ዮሴፍ እንዲህ ባሉ ጉዳዮች ላይ በማሰላሰል በአምላክ ዓይን ትክክልና ስህተት የሆኑትን ነገሮች ማስተዋል ችሏል። ዮሴፍ አምላኩን ይወድ ስለነበር ለይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ፍቅር ነበረው፤ እንዲሁም በእነዚህ መሥፈርቶች ለመመራት ቆርጦ ነበር።

3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

3 አንተስ ጽድቅን ትወዳለህ? እንደምትወድ ጥያቄ የለውም። ሆኖም ሁላችንም ፍጹማን አይደለንም። በመሆኑም ካልተጠነቀቅን ዓለም ለጽድቅ ያለው አመለካከት በቀላሉ ተጽዕኖ ሊያሳድርብን ይችላል። (ኢሳ. 5:20፤ ሮም 12:2) እንግዲያው ጽድቅ ምን እንደሆነ እንዲሁም ጽድቅን መውደዳችን ምን ጥቅም እንደሚያስገኝልን እንመልከት። ከዚያም ለይሖዋ መሥፈርቶች ያለንን ፍቅር ለማጠናከር የትኞቹን ሦስት እርምጃዎች መውሰድ እንደምንችል እንመለከታለን።

ጽድቅ ምንድን ነው?

4. ብዙዎች ስለ ጽድቅ ምን የተሳሳተ አመለካከት አላቸው?

4 ብዙዎች ‘ጻድቅ ሰው’ ሲባል ወደ አእምሯቸው የሚመጣው ኩሩ፣ ተቺና ተመጻዳቂ ሰው ነው። ሆኖም አምላክ እነዚህን ባሕርያት ፈጽሞ አይወዳቸውም። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት በዘመኑ የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች የራሳቸውን የጽድቅ መሥፈርቶች በማውጣታቸው አጥብቆ አውግዟቸዋል። (መክ. 7:16፤ ሉቃስ 16:15) እውነተኛ ጽድቅ ራስን ከማመጻደቅ ፈጽሞ የተለየ ነው።

5. በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ጽድቅ ምንድን ነው? ምሳሌ ስጥ።

5 ጽድቅ ማራኪ ባሕርይ ነው። በአጭር አነጋገር ጽድቅ ማለት በይሖዋ አምላክ ዓይን ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ማለት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ጽድቅ” ተብለው የተተረጎሙት ቃላት ከሁሉ በላቁት የይሖዋ መሥፈርቶች መመራትን ያመለክታሉ። ለምሳሌ ይሖዋ፣ ነጋዴዎች “ሐቀኛ ሚዛን” እንዲጠቀሙ አዝዞ ነበር። (ዘዳ. 25:15) እዚህ ላይ “ሐቀኛ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “ጻድቅ” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። በመሆኑም በአምላክ ዓይን ጻድቅ መሆን የሚፈልግ ክርስቲያን በንግድ ጉዳዮች ረገድ ሙሉ በሙሉ ሐቀኛ ይሆናል። በተጨማሪም ጻድቅ ሰው ፍትሕን ይወዳል፤ ማንም ላይ ግፍ ሲደርስ ማየት አይፈልግም። ከዚህም ሌላ ጻድቅ ሰው ‘ይሖዋን ሙሉ በሙሉ ማስደሰት’ ስለሚፈልግ ከሚያደርጋቸው ውሳኔዎች ጋር በተያያዘ የአምላክን አመለካከት ግምት ውስጥ ያስገባል።—ቆላ. 1:10

6. ይሖዋ ትክክልና ስህተት ስለሆኑት ነገሮች ባወጣው መሥፈርት መተማመን የምንችለው ለምንድን ነው? (ኢሳይያስ 55:8, 9)

6 መጽሐፍ ቅዱስ የጽድቅ ምንጭ ይሖዋ እንደሆነ ይናገራል። ይሖዋ “የጽድቅ መኖሪያ” ተብሎ የተጠራው ለዚህ ነው። (ኤር. 50:7) ይሖዋ ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን ትክክልና ስህተት ስለሆኑት ነገሮች መሥፈርት የማውጣት መብት ያለው እሱ ብቻ ነው። ይሖዋ ፍጹም ስለሆነ የትኞቹ ነገሮች ትክክል፣ የትኞቹ ነገሮች ደግሞ ስህተት እንደሆኑ በትክክል ያውቃል፤ እኛ ግን ፍጽምና የጎደለንና ኃጢአተኞች ስለሆንን ትክክልና ስህተት ስለሆኑ ነገሮች ያለን ግንዛቤ የተዛባ ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 14:12፤ ኢሳይያስ 55:8, 9ን አንብብ።) ያም ቢሆን የተሠራነው በአምላክ አምሳል ስለሆነ በእሱ የጽድቅ መሥፈርቶች መመራት እንችላለን። (ዘፍ. 1:27) እንዲህ ማድረግም ያስደስተናል። ለአባታችን ያለን ፍቅር አቅማችን በፈቀደ መጠን እሱን እንድንመስል ያነሳሳናል።—ኤፌ. 5:1

7. እምነት የሚጣልባቸው መሥፈርቶች የሚያስፈልጉን ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።

7 ትክክልና ስህተት የሆኑትን ነገሮች በተመለከተ ይሖዋ ባወጣቸው መሥፈርቶች መመራታችን ይጠቅመናል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? እያንዳንዱ ባንክ የገንዘብን ዋጋ በተመለከተ የራሱን መሥፈርት ቢያወጣ ወይም እያንዳንዱ የሕንፃ ተቋራጭ የራሱን የልኬት መሥፈርቶች ቢያወጣ ምን ሊፈጠር እንደሚችል እስቲ አስበው! ትርምስ ይፈጠር ነበር። ወይም ደግሞ የሕክምና ባለሙያዎች ከሕክምና አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ተገቢውን መሥፈርት የማይከተሉ ከሆነ አንዳንድ ታካሚዎች ሕይወታቸውን ሊያጡ ይችላሉ። በእርግጥም እምነት የሚጣልባቸው መሥፈርቶች መኖራቸው ጥበቃ ያስገኝልናል። በተመሳሳይም ትክክልና ስህተት የሆኑትን ነገሮች በተመለከተ አምላክ ያወጣቸው መሥፈርቶች ጥበቃ ያስገኙልናል።

8. ጽድቅን የሚወዱ ሰዎች የትኞቹ በረከቶች ይጠብቋቸዋል?

8 ይሖዋ በእሱ መሥፈርቶች ለመመራት ጥረት የሚያደርጉ ሰዎችን ይባርካል። “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእሷም ላይ ለዘላለም ይኖራሉ” በማለት ቃል ገብቷል። (መዝ. 37:29) ሁሉም ሰው የይሖዋን መሥፈርቶች በሚከተልበት ጊዜ የሰው ዘር ምን ያህል አንድነት ያለው፣ ሰላማዊና ደስተኛ እንደሚሆን እስቲ አስበው! ይሖዋ እንዲህ ያለውን ሕይወት እንድታጣጥም ይፈልጋል። በእርግጥም እያንዳንዳችን ጽድቅን የምንወድበት አጥጋቢ ምክንያት አለን! ታዲያ ለዚህ ባሕርይ ያለንን ፍቅር ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው? መውሰድ የምንችላቸውን ሦስት እርምጃዎች እስቲ እንመልከት።

ለይሖዋ መሥፈርቶች ያለህን ፍቅር አጠናክር

9. ጽድቅን ለመውደድ ምን ይረዳናል?

9 አንደኛ፦ መሥፈርቶቹን ላወጣው አምላክ ፍቅር ይኑርህ። ጽድቅን ለመውደድ ትክክልና ስህተት የሆኑትን ነገሮች በተመለከተ መሥፈርቱን ለሚያወጣው ለይሖዋ ያለንን ፍቅር ማጠናከር ይኖርብናል። ይሖዋን ይበልጥ በወደድነው መጠን በእሱ የጽድቅ መሥፈርቶች ለመመራት ያለን ፍላጎት ይጨምራል። ለምሳሌ አዳምና ሔዋን ለይሖዋ ፍቅር ቢኖራቸው ኖሮ ፍትሕ የሚንጸባረቅበትን ሕጉን አይጥሱም ነበር።—ዘፍ. 3:1-6, 16-19

10. አብርሃም የይሖዋን አስተሳሰብ ይበልጥ መረዳት የቻለው እንዴት ነው?

10 አዳምና ሔዋን የሠሩትን ዓይነት ስህተት መሥራት እንደማንፈልግ የታወቀ ነው። ስለ ይሖዋ መማራችንን፣ ባሕርያቱን ማድነቃችንን እንዲሁም አስተሳሰቡን ለመረዳት ጥረት ማድረጋችንን ከቀጠልን እንዲህ ያለውን ስህተት ከመሥራት እንጠበቃለን። እንዲህ ስናደርግ ለይሖዋ ያለን ፍቅር ያድጋል። የአብርሃምን ምሳሌ እንመልከት። አብርሃም ይሖዋን በጣም ይወደው ነበር። ይሖዋ ያደረጋቸውን አንዳንድ ውሳኔዎች መረዳት በከበደው ጊዜም እንኳ አብርሃም አላመፀም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋን ይበልጥ ለማወቅ ጥረት አድርጓል። ለምሳሌ ይሖዋ ሰዶምንና ገሞራን ለማጥፋት መወሰኑን ሲያውቅ አብርሃም መጀመሪያ ላይ “የምድር ሁሉ ዳኛ” ጻድቁን ከኃጢአተኛው ጋር አብሮ እንዳያጠፋ ሰግቶ ነበር። አብርሃም ይህ ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር እንደሆነ ተሰምቶት ነበር፤ በመሆኑም ይሖዋን በትሕትና የተለያዩ ጥያቄዎችን ጠየቀው። ይሖዋም በትዕግሥት መለሰለት። በመጨረሻም አብርሃም፣ ይሖዋ የሁሉንም ሰው ልብ እንደሚመረምርና መቼም ቢሆን ጻድቁን ከኃጢአተኛው ጋር አብሮ እንደማይቀጣ ተገነዘበ።—ዘፍ. 18:20-32

11. አብርሃም ይሖዋን እንደሚወደውና እንደሚተማመንበት ያሳየው እንዴት ነው?

11 አብርሃም ሰዶምንና ገሞራን በተመለከተ ከይሖዋ ጋር ያደረገው ውይይት በእጅጉ ጠቅሞታል። ለአባቱ ያለው ፍቅርና አክብሮት ከበፊቱ እንደጨመረ ምንም ጥያቄ የለውም። ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ አብርሃም በይሖዋ ላይ ያለው እምነት በከባዱ ተፈተነ። ይሖዋ አብርሃም የሚወደውን ልጁን ይስሐቅን መሥዋዕት እንዲያደርግ ጠየቀው። ሆኖም አብርሃም አሁን ስለ አምላኩ ያለው እውቀት ጨምሯል፤ በመሆኑም በዚህ ወቅት ምንም ጥያቄ አላነሳም። አብርሃም ወዲያውኑ ይሖዋ የጠየቀውን ነገር ለማድረግ ተነሳ። ያም ቢሆን አብርሃም ይስሐቅን መሥዋዕት ለማድረግ ሲዘጋጅ ምን ያህል ልቡ ተሰብሮ እንደሚሆን እስቲ አስበው! አብርሃም ስለ ይሖዋ በሚያውቀው ነገር ላይ በጥልቀት አስቦ መሆን አለበት። ይሖዋ መቼም ቢሆን ጽድቅ ወይም ፍቅር የጎደለው ነገር እንደማያደርግ ያውቅ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደገለጸው አብርሃም፣ ይሖዋ የሚወደውን ልጁን ይስሐቅን ከሞት እንኳ ሳይቀር ሊያስነሳው እንደሚችል ተገንዝቦ ነበር። (ዕብ. 11:17-19) ደግሞም ይሖዋ ከይስሐቅ አንድ ብሔር እንደሚገኝ ቃል ገብቶ ነበር፤ ሆኖም በዚያ ወቅት ይስሐቅ ገና ልጅ አልወለደም። አብርሃም ይሖዋን ይወደው ነበር፤ በመሆኑም አባቱ ጽድቅ የሆነውን ነገር እንደሚያደርግ ተማምኗል። በጣም ከባድ ቢሆንም በእምነት ታዘዘ።—ዘፍ. 22:1-12

12. የአብርሃምን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? (መዝሙር 73:28)

12 የአብርሃምን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? እኛም እንደ እሱ ስለ ይሖዋ መማራችንን መቀጠል ይኖርብናል። እንዲህ ስናደርግ ወደ እሱ ይበልጥ እንቀርባለን፤ ለእሱ ያለን ፍቅርም ያድጋል። (መዝሙር 73:28ን አንብብ።) ሕሊናችን ስለሚሠለጥን የአምላክን አስተሳሰብ ማንጸባረቅ ይጀምራል። (ዕብ. 5:14) በውጤቱም፣ አንድ ሰው መጥፎ ነገር እንድናደርግ ሲፈትነን ፈቃደኛ አንሆንም። አባታችንን የሚያሳዝንና ከእሱ ጋር ያለንን ዝምድና የሚያበላሽ ማንኛውንም ነገር ማድረግ ስናስበው እንኳ ይዘገንነናል። ይሁንና ጽድቅን እንደምንወድ ማሳየት የምንችልበት ሌላው መንገድ ምንድን ነው?

13. ጽድቅን መከታተል የምንችለው እንዴት ነው? (ምሳሌ 15:9)

13 ሁለተኛ፦ ለጽድቅ ያለህን ፍቅር ለማሳደግ በየቀኑ ጥረት አድርግ። ጡንቻችንን ማጎልበት ከፈለግን አዘውትረን ልናሠራው ይገባል፤ በተመሳሳይም ለይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ያለንን ፍቅር ለማሳደግ አዘውትረን ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። በየዕለቱ እንዲህ ያለውን ጥረት ማድረግ ከአቅማችን በላይ አይደለም። ይሖዋ ምክንያታዊ ነው፤ ደግሞም መቼም ቢሆን ከአቅማችን በላይ አይጠብቅብንም። (መዝ. 103:14) ‘ጽድቅን የሚከታተለውን እንደሚወድ’ ዋስትና ሰጥቶናል። (ምሳሌ 15:9ን አንብብ።) ለምሳሌ በይሖዋ አገልግሎት አንድን ግብ እንከታተላለን ሲባል እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እናደርጋለን ማለት ነው። ጽድቅን ከመከታተል ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ይሖዋም እድገት እንድናደርግና በጊዜ ሂደት እያሻሻልን እንድንሄድ ይረዳናል።—መዝ. 84:5, 7

14. ‘የጽድቅ ጥሩር’ ምንድን ነው? የሚያስፈልገንስ ለምንድን ነው?

14 ይሖዋ ጽድቅን መከታተል ከባድ ሸክም እንዳልሆነ የሚገልጽ ፍቅራዊ ማሳሰቢያ ሰጥቶናል። (1 ዮሐ. 5:3) እንዲያውም ጥበቃ ያስገኝልናል፤ እንዲህ ያለው ጥበቃ ደግሞ በየዕለቱ ያስፈልገናል። ሐዋርያው ጳውሎስ የጠቀሰውን መንፈሳዊ የጦር ትጥቅ ወደ አእምሮህ አምጣ። (ኤፌ. 6:14-18) የወታደሩን ልብ የሚጠብቅለት የትኛው የትጥቁ ክፍል ነው? የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶች የሚያመለክተው ‘የጽድቅ ጥሩር’ ነው። ጥሩር የወታደሩን ልብ እንደሚጠብቅለት ሁሉ የይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶችም ምሳሌያዊ ልባችንን ማለትም ውስጣዊ ማንነታችንን ይጠብቁልናል። እንግዲያው በጦር ትጥቅህ ውስጥ የጽድቅ ጥሩር መካተቱን ምንጊዜም አረጋግጥ!—ምሳሌ 4:23

15. የጽድቅን ጥሩር መልበስ የምትችለው እንዴት ነው?

15 የጽድቅን ጥሩር መልበስ የምትችለው እንዴት ነው? በየዕለቱ በምታደርጋቸው ምርጫዎች ረገድ የአምላክን መሥፈርት ከግምት በማስገባት ነው። ስለ ምን እንደምታወራ፣ የትኛውን ሙዚቃ እንደምትሰማ፣ የትኛውን መዝናኛ እንደምታይ ወይም የትኞቹን መጻሕፍት እንደምታነብ ከመወሰንህ በፊት ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ልቤን ምን ዓይነት ምግብ ልመግበው ነው? ይህን ነገር ይሖዋ በጥሩ ዓይን ይመለከተዋል? ወይስ ከይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር የሚጋጩትን የፆታ ብልግናን፣ ዓመፅን፣ ስግብግብነትንና ራስ ወዳድነትን ያበረታታል?’ (ፊልጵ. 4:8) የምታደርገው ውሳኔ ከይሖዋ ፈቃድ ጋር የሚስማማ ከሆነ የይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ልብህን ይጠብቁልሃል።

ጽድቅህ “እንደ ባሕር ሞገድ” ሊሆን ይችላል (ከአንቀጽ 16-17⁠ን ተመልከት)

16-17. ኢሳይያስ 48:18 ለዘላለም በይሖዋ መሥፈርቶች መመላለስ እንደምንችል ዋስትና የሚሰጠን እንዴት ነው?

16 ከዕለት ዕለት፣ ከዓመት ዓመት በይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች መመላለስ መቻልህን የምትጠራጠርበት ጊዜ አለ? ይሖዋ በኢሳይያስ 48:18 ላይ የተጠቀመበትን ምሳሌ ልብ በል። (ጥቅሱን አንብብ።) ይሖዋ ጽድቃችን “እንደ ባሕር ሞገድ” እንደሚሆን ቃል ገብቷል። በተንጣለለ ባሕር ዳርቻ ላይ ቆመህ የባሕሩ ሞገድ ያለማቋረጥ ተከታትሎ ሲመጣ እያየህ ነው እንበል። በዚህ የተረጋጋ ቦታ ሆነህ ‘እነዚህ ሞገዶች አንድ ቀን መምጣታቸውን ቢያቆሙስ?’ የሚል ስጋት ይፈጠርብሃል? በጭራሽ! ሞገዶቹ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ያለማቋረጥ እንደመጡ፣ ወደፊትም መምጣታቸውን እንደሚቀጥሉ እርግጠኛ ነህ።

17 የአንተም ጽድቅ ልክ እንደ ባሕር ሞገድ ሊሆን ይችላል! እንዴት? ውሳኔ ከማድረግህ በፊት ይሖዋ ምን እንድታደርግ እንደሚፈልግ ቆም ብለህ አስብ። ከዚያም ውሳኔውን ተግባራዊ አድርግ። ውሳኔው ምንም ያህል ከባድ ቢሆን፣ የሚወድህ አባትህ ዕለት ዕለት ያለማቋረጥ ከእሱ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ እንድትመላለስ ከጎንህ ሆኖ ይረዳሃል።—ኢሳ. 40:29-31

18. በራሳችን መሥፈርት በሌሎች ላይ ከመፍረድ መቆጠብ ያለብን ለምንድን ነው?

18 ሦስተኛ፦ ፍርዱን ለይሖዋ ተው። በይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ለመመራት አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ብናደርግም በሌሎች ላይ ከመፍረድና ራሳችንን ከማመጻደቅ መቆጠብ ይኖርብናል። ማናችንም ብንሆን በራሳችን መሥፈርቶች መሠረት በሌሎች ላይ የመፍረድ ሥልጣን የለንም፤ በመሆኑም ሌሎችን ከመናቅ ይልቅ ይሖዋ “የምድር ሁሉ ዳኛ” መሆኑን ማስታወስ ይኖርብናል። (ዘፍ. 18:25) ይሖዋ የመፍረድ ሥልጣኑን ለእኛ አሳልፎ አልሰጠንም። እንዲያውም ኢየሱስ “እንዳይፈረድባችሁ በሌሎች ላይ አትፍረዱ” በማለት አዞናል።—ማቴ. 7:1 *

19. ዮሴፍ በይሖዋ ፍርድ እንደሚተማመን ያሳየው እንዴት ነው?

19 የጻድቁን ዮሴፍን ምሳሌ በድጋሚ እንመልከት። ዮሴፍ የበደሉትን ሰዎች ጨምሮ በሌሎች ላይ ከመፍረድ ተቆጥቧል። የገዛ ወንድሞቹ አንገላተውታል፤ ለባርነት ሸጠውታል፤ አልፎ ተርፎም ‘ዮሴፍ ሞቷል’ ብለው ለአባታቸው ነግረውታል። ከበርካታ ዓመታት በኋላ ዮሴፍ ከቤተሰቡ ጋር መልሶ ተገናኘ። በወቅቱ ዮሴፍ ከፍተኛ ባለሥልጣን ስለነበር በወንድሞቹ ላይ በጭካኔ ሊፈርድባቸውና ሊበቀላቸው ይችል ነበር። የዮሴፍ ወንድሞች ለሠሩት በደል ከልባቸው የተጸጸቱ ቢሆንም ዮሴፍ ሊበቀላቸው እንደሚችል ፈርተው ነበር። ሆኖም ዮሴፍ “አይዟችሁ አትፍሩ። ለመሆኑ እኔን በአምላክ ቦታ ያስቀመጠኝ ማን ነው?” በማለት አረጋጋቸው። (ዘፍ. 37:18-20, 27, 28, 31-35፤ 50:15-21) ዮሴፍ በትሕትና ፍርዱን ለይሖዋ ትቷል።

20-21. ራሳችንን ከማመጻደቅ መቆጠብ የምንችለው እንዴት ነው?

20 እኛም እንደ ዮሴፍ ፍርዱን ለይሖዋ እንተዋለን። ለምሳሌ ያህል፣ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አንድን ነገር ለማድረግ የተነሳሱበት ውስጣዊ ዓላማ ምን እንደሆነ እናውቃለን ብለን አናስብም። እኛ የሰዎችን ልብ ማንበብ አንችልም፤ ‘ውስጣዊ ዓላማን የሚመረምረው’ ይሖዋ ብቻ ነው። (ምሳሌ 16:2) እሱ ባሕልና አስተዳደግ ሳይለይ ሁሉንም ዓይነት ሰዎች ይወዳል። በተጨማሪም ይሖዋ ‘ልባችንን ወለል አድርገን እንድንከፍት’ አበረታቶናል። (2 ቆሮ. 6:13) የመንፈሳዊ ቤተሰባችንን አባላት በሙሉ መውደድ እንጂ በእነሱ ላይ መፍረድ አንፈልግም።

21 ከጉባኤው ውጭ ባሉ ሰዎችም ላይ መፍረድ አይኖርብንም። (1 ጢሞ. 2:3, 4) እምነትህን የማይጋራ አንድ ዘመድህን በተመለከተ “እሱማ መቼም ወደ እውነት አይመጣም” ብለህ ትፈርድበታለህ? ይህ እብሪተኝነትና ተመጻዳቂነት ይሆናል። ይሖዋ “በየቦታው ያሉ ሰዎች ሁሉ ንስሐ እንዲገቡ” አሁንም አጋጣሚ ሰጥቷል። (ሥራ 17:30) ራስን ማመጻደቅ በራሱ ጽድቅ የጎደለው ድርጊት እንደሆነ አትዘንጋ።

22. ጽድቅን ለመውደድ ቁርጥ ውሳኔ ያደረግከው ለምንድን ነው፧

22 ለይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ያለን ፍቅር ደስተኛ ያደርገናል፤ እንዲሁም ሌሎች ሰዎች ወደ እኛም ሆነ ወደ አምላካችን እንዲቀርቡ ያነሳሳቸዋል። ‘ጽድቅን መራብህንና መጠማትህን’ ፈጽሞ አታቁም። (ማቴ. 5:6) ይሖዋ የምታደርገውን ጥረት እንደሚመለከትና በምታደርገው እድገት እንደሚደሰት አትጠራጠር። ይህ ዓለም ከጽድቅ እየራቀ ቢሄድም አይዞህ! ‘ይሖዋ ጻድቃንን እንደሚወድ’ ምንጊዜም አስታውስ።—መዝ. 146:8

መዝሙር 139 በአዲሱ ዓለም ስትኖር ይታይህ

^ በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ ጻድቅ ሰው ማግኘት አስቸጋሪ ነው። ያም ቢሆን በዛሬው ጊዜ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የጽድቅ ጎዳና ይከተላሉ። አንተም ከእነሱ አንዱ እንደሆንክ ምንም ጥያቄ የለውም። የጽድቅ ጎዳና የምትከተለው ይሖዋን ስለምትወደው ነው፤ ይሖዋ ደግሞ ጽድቅን ይወዳል። ለዚህ ግሩም ባሕርይ ያለንን ፍቅር ማሳደግ የምንችለው እንዴት ነው? ጽድቅ ምን እንደሆነ እንዲሁም ጽድቅን መውደዳችን ምን ጥቅም እንደሚያስገኝልን በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን። በተጨማሪም ለዚህ ባሕርይ ያለንን ፍቅር ለማሳደግ የትኞቹን እርምጃዎች መውሰድ እንደምንችል እንመለከታለን።

^ የጉባኤ ሽማግሌዎች አንዳንድ ጊዜ ከከባድ ኃጢአትና ከንስሐ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ፍርድ መስጠት ይጠበቅባቸዋል። (1 ቆሮ. 5:11፤ 6:5፤ ያዕ. 5:14, 15) ሆኖም ልብን ማንበብ እንደማይችሉ እንዲሁም የሚፈርዱት ለይሖዋ እንደሆነ በትሕትና አምነው ይቀበላሉ። (ከ2 ዜና መዋዕል 19:6 ጋር አወዳድር።) በሚፈርዱበት ጊዜም ሚዛናዊ የሆኑትንና ምሕረት የሚንጸባረቅባቸውን የይሖዋ የፍትሕ መሥፈርቶች በጥንቃቄ ይከተላሉ።