በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 33

ይሖዋ ሕዝቡን በትኩረት ይመለከታል

ይሖዋ ሕዝቡን በትኩረት ይመለከታል

“የይሖዋ ዓይን የሚፈሩትን . . . በትኩረት ይመለከታል።”—መዝ. 33:18

መዝሙር 4 “ይሖዋ እረኛዬ ነው”

ማስተዋወቂያ *

1. ኢየሱስ ተከታዮቹን እንዲጠብቃቸው ይሖዋን የጠየቀው ለምንድን ነው?

 ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይ ለሰማዩ አባቱ ልዩ ልመና አቅርቧል። ተከታዮቹን እንዲጠብቃቸው ይሖዋን ጠይቆታል። (ዮሐ. 17:15, 20) እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ከጥንትም ጀምሮ ሕዝቡን በትኩረት ሲመለከት፣ ሲንከባከብና ሲጠብቅ ቆይቷል። ሆኖም ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ ከሰይጣን ይህ ነው የማይባል ተቃውሞ እንደሚደርስባቸው ጠብቆ ነበር። በተጨማሪም ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ የዲያብሎስን መሠሪ ዘዴዎች እንዲቋቋሙ የይሖዋ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተገንዝቦ ነበር።

2. በመዝሙር 33:18-20 መሠረት መከራን መፍራት የሌለብን ለምንድን ነው?

2 በዛሬው ጊዜ የሰይጣን ሥርዓት በእውነተኛ ክርስቲያኖች ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድራል። ተስፋ ሊያስቆርጡን አልፎ ተርፎም ለይሖዋ ያለንን ታማኝነት ሊፈትኑ የሚችሉ መከራዎች ያጋጥሙናል። ሆኖም በዚህ ርዕስ ውስጥ እንደምንመለከተው፣ የምንፈራበት ምንም ምክንያት የለም። ይሖዋ በትኩረት ይመለከተናል። የሚያጋጥሙንን ችግሮች ያያል፤ እንዲሁም ችግሮቹን እንድንቋቋም ለመርዳት ምንጊዜም ዝግጁ ነው። ይሖዋ ‘የሚፈሩትን በትኩረት እንደሚመለከት’ የሚያሳዩ ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችን እንመርምር።—መዝሙር 33:18-20ን አንብብ።

ብቻችንን እንደሆንን ሲሰማን

3. ብቻችንን እንደሆንን የሚሰማን መቼ ሊሆን ይችላል?

3 የይሖዋን አገልጋዮች ያቀፈው ትልቅ ቤተሰብ ክፍል ብንሆንም አልፎ አልፎ ብቻችንን እንደሆንን ሊሰማን ይችላል። ለምሳሌ ወጣቶች በክፍላቸው ልጆች ፊት ቀርበው ስለ እምነታቸው ሲናገሩ ወይም ወደ አዲስ ጉባኤ ሲዛወሩ ብቻቸውን እንደሆኑ ሊሰማቸው ይችላል። አንዳንዶቻችን ከሐዘን ወይም ከአሉታዊ ስሜቶች ጋር እንታገል ይሆናል፤ ከእነዚህ ስሜቶች ጋር የምንታገለው ብቻችንን እንደሆነ ሊሰማን ይችላል። ሌሎች ስሜታችንን ሊረዱልን እንደማይችሉ በማሰብ ስሜታችንን ለሌሎች ከማካፈል ወደኋላ እንል ይሆናል። አንዳንድ ጊዜም የሚያስብልን ማንም እንደሌለ ሊሰማን ይችላል። ብቻችንን እንደሆንን እንዲሰማን ያደረገው ነገር ምንም ይሁን ምን፣ ይህ ስሜት አቅመ ቢስ እንደሆንን እንዲሰማን እንዲሁም እንድንጨነቅ ሊያደርገን ይችላል። ይሖዋ እንዲህ ዓይነት ስሜት እንዲያድርብን በፍጹም አይፈልግም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

4. ነቢዩ ኤልያስ “የቀረሁት እኔ ብቻ ነኝ” ያለው ለምንድን ነው?

4 ታማኝ ሰው የነበረውን ኤልያስን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ኤልዛቤል እንደምትገድለው ስለዛተችበት ኤልያስ ሕይወቱን ለማትረፍ ከ40 ቀናት በላይ ሲሸሽ ቆይቷል። (1 ነገ. 19:1-9) በመጨረሻም ብቻውን ዋሻ ውስጥ ሆኖ “የቀረሁት [ነቢይ] እኔ ብቻ ነኝ” በማለት ወደ ይሖዋ ጮኸ። (1 ነገ. 19:10) እርግጥ በምድሪቱ ላይ ሌሎች ነቢያት ነበሩ፤ ለምሳሌ አብድዩ 100 ነቢያትን ከኤልዛቤል እጅ ማስጣል ችሏል። (1 ነገ. 18:7, 13) ታዲያ ኤልያስ ብቻውን እንደሆነ የተሰማው ለምንድን ነው? አብድዩ ያተረፋቸው ነቢያት በሙሉ እንደሞቱ አስቦ ይሆን? ብቻውን እንደሆነ የተሰማው፣ ባአል እውነተኛ አምላክ እንዳልሆነ በቀርሜሎስ ተራራ ላይ ከተረጋገጠ በኋላም ሌሎች አብረውት ይሖዋን ማምለክ ስላልጀመሩ ይሆን? ወይስ ምን ዓይነት አደጋ ውስጥ እንደሆነ የሚያውቅ ማንም ሰው እንደሌለ ወይም ማንም እንደማያስብለት ተሰምቶት ይሆን? ዘገባው ኤልያስ እንዲህ የተሰማው ለምን እንደሆነ በዝርዝር አይገልጽልንም። ሆኖም በእርግጠኝነት የምናውቀው አንድ ነገር አለ፤ ይሖዋ ኤልያስ ብቻውን እንደሆነ የተሰማው ለምን እንደሆነ እንዲሁም እሱን መርዳት የሚችለው እንዴት እንደሆነ በትክክል ያውቅ ነበር።

ብቻችንን እንደሆንን ሲሰማን ይሖዋ ኤልያስን ከረዳበት መንገድ ምን የሚያጽናና ትምህርት እናገኛለን? (ከአንቀጽ 5-6⁠ን ተመልከት)

5. ይሖዋ ለኤልያስ ብቻውን እንዳልሆነ ያረጋገጠለት እንዴት ነው?

5 ይሖዋ ኤልያስን በተለያዩ መንገዶች ረድቶታል። ኤልያስ ስሜቱን አውጥቶ እንዲናገር አበረታቶታል። “ኤልያስ፣ እዚህ ምን ታደርጋለህ?” በማለት ሁለት ጊዜ ጠይቆታል። (1 ነገ. 19:9, 13) በሁለቱም ጊዜያት ኤልያስ ስሜቱን ሲገልጽ ይሖዋ አዳምጦታል። ይሖዋ ከኤልያስ ጋር አብሮት እንዳለ በማሳየትና ኃይሉን በመግለጥ ለኤልያስ ምላሽ ሰጥቶታል። በተጨማሪም ይሖዋ፣ ኤልያስ አሁንም በርካታ የእምነት አጋሮች እንዳሉት አረጋግጦለታል። (1 ነገ. 19:11, 12, 18) ኤልያስ ልቡን በይሖዋ ፊት ማፍሰሱ እንዲሁም የይሖዋን ምላሽ መስማቱ እፎይታ እንዳስገኘለት ምንም ጥያቄ የለውም። ይሖዋ ለኤልያስ የተለያዩ ወሳኝ ኃላፊነቶችን ሰጥቶታል። ሃዛኤልን የሶርያ ንጉሥ፣ ኢዩን የእስራኤል ንጉሥ እንዲሁም ኤልሳዕን ነቢይ አድርጎ እንዲቀባ አዘዘው። (1 ነገ. 19:15, 16) ይሖዋ ለኤልያስ እነዚህን ኃላፊነቶች በመስጠት በአዎንታዊ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ረድቶታል። በተጨማሪም አምላክ፣ ለኤልያስ የቅርብ ወዳጅ እንዲሆነው ኤልሳዕን ሰጥቶታል። አንተስ ብቻህን እንደሆንክ ሲሰማህ የይሖዋን እርዳታ ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?

6. ብቻህን እንደሆንክ ሲሰማህ ምን ብለህ መጸለይ ትችላለህ? (መዝሙር 62:8)

6 ይሖዋ ወደ እሱ እንድትጸልይ ጋብዞሃል። የሚያጋጥሙህን ችግሮች ያያል፤ እንዲሁም በማንኛውም ጊዜ ጸሎትህን እንደሚሰማ ዋስትና ሰጥቶሃል። (1 ተሰ. 5:17) ይሖዋ አገልጋዮቹን መስማት ደስ ያሰኘዋል። (ምሳሌ 15:8) ይሁንና ብቻህን እንደሆንክ ሲሰማህ ምን ብለህ መጸለይ ትችላለህ? እንደ ኤልያስ ልብህን በይሖዋ ፊት አፍስስ። (መዝሙር 62:8ን አንብብ።) ስለሚያሳስቡህ ነገሮች እንዲሁም እነዚህ ነገሮች ስለፈጠሩብህ ስሜት ንገረው። ይሖዋ አሉታዊ ስሜቶችን ለማሸነፍ እንዲረዳህ ለምነው። ለምሳሌ በትምህርት ቤት ስትመሠክር ብቻህን እንደሆንክ ከተሰማህ ወይም ከፈራህ፣ እምነትህን ለመግለጽ የሚያስችል ድፍረት እንዲሰጥህ ይሖዋን ጠይቀው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ስለ እምነትህ በዘዴ ለማስረዳት የሚያስችል ጥበብ እንዲሰጥህ መጠየቅ ትችላለህ። (ሉቃስ 21:14, 15) ከአሉታዊ ስሜቶች ጋር እየታገልክ ከሆነ ከአንድ ጎልማሳ ክርስቲያን ጋር ስለ ጉዳዩ ለመነጋገር እንዲረዳህ ይሖዋን ጠይቀው። የምታነጋግረው ሰው ስሜትህን መረዳት እንዲችል እንዲያግዘውም ይሖዋን መጠየቅ ትችላለህ። ልብህን በይሖዋ ፊት አፍስስ፤ ይሖዋ ለጸሎትህ የሚሰጠውን ምላሽ ተመልከት፤ እንዲሁም የሌሎችን እርዳታ ተቀበል። እንዲህ ካደረግክ የሚሰማህ የብቸኝነት ስሜት ይቀንሳል።

አገልግሎትህን ማስፋትና ከሌሎች ጋር በአገልግሎት መካፈል የምትችልባቸውን መንገዶች ትፈልጋለህ? (አንቀጽ 7⁠ን ተመልከት)

7. ከማውሪሲዮ ምሳሌ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

7 ይሖዋ ለሁላችንም ትርጉም ያለው ሥራ ሰጥቶናል። ይሖዋ በጉባኤና በአገልግሎት ያለህን ኃላፊነት ለመወጣት የምታደርገውን ጥረት በሙሉ እንደሚመለከትና እንደሚያደንቅ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። (መዝ. 110:3) በዚህ ሥራ መጠመድህ ብቻህን እንደሆንክ ሲሰማህ የሚረዳህ እንዴት ነው? ማውሪሲዮ * የተባለን ወጣት ወንድም እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ማውሪሲዮ ከተጠመቀ ብዙም ሳይቆይ አንድ የቅርብ ጓደኛው ቀስ በቀስ ከእውነት መራቅ ጀመረ። ማውሪሲዮ እንዲህ ብሏል፦ “ጓደኛዬ ከእውነት ሲርቅ ማየቴ በራስ የመተማመን ስሜቴን አሳጣኝ። ራሴን ስወስን የገባሁትን ቃል መፈጸም እንዲሁም የይሖዋ ቤተሰብ አባል ሆኜ መቀጠል መቻሌን ተጠራጥሬ ነበር። ብቻዬን እንደሆንኩና ስሜቴን ሊረዳልኝ የሚችል ማንም እንደሌለ ተሰማኝ።” ታዲያ ማውሪሲዮን የረዳው ምንድን ነው? እንዲህ ብሏል፦ “አገልግሎቴን አሰፋሁ። ይህም በራሴ ላይ እንዳላተኩርና በአሉታዊ ስሜቶች ላይ እንዳላውጠነጥን ረድቶኛል። ከሌሎች ጋር አብሬ ሳገለግል ደስታ አገኘሁ፤ እንዲሁም የሚሰማኝ የብቸኝነት ስሜት ቀነሰ።” እኛም ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር በአካል አብረን መስበክ ባንችልም እንኳ አብረን ሆነን በደብዳቤና በስልክ ምሥክርነት መካፈላችን ያበረታታናል። ማውሪሲዮን የረዳው ሌላም ነገር አለ። እንዲህ ብሏል፦ “በጉባኤ እንቅስቃሴዎችም ተጠመድኩ። የተማሪ ክፍሎችን በደንብ ተዘጋጅቼ ለማቅረብ ልባዊ ጥረት አደርግ ነበር። በእነዚህ ሥራዎች መጠመዴ በይሖዋና በሌሎች ዘንድ ዋጋ እንዳለኝ እንዲሰማኝ አድርጎኛል።”

የሚደርሱብን ፈተናዎች ከአቅማችን በላይ እንደሆኑብን ሲሰማን

8. ከባድ ፈተናዎች ሲደርሱብን ምን ሊሰማን ይችላል?

8 በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት የተለያዩ ፈተናዎች እንደሚያጋጥሙን እንጠብቃለን። (2 ጢሞ. 3:1) ያም ቢሆን፣ ፈተናው የደረሰበት ጊዜ ወይም የፈተናው ዓይነት ዱብ ዕዳ ሊሆንብን ይችላል። ድንገተኛ የኢኮኖሚ ችግር ሊያጋጥመን፣ በከባድ ሕመም ልንያዝ ወይም የምንወደውን ሰው በሞት ልናጣ እንችላለን። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን በጭንቀት ልንዋጥና ሁኔታው ከአቅማችን በላይ እንደሆነብን ሊሰማን ይችላል። በተለይም ፈተናዎቹ ከተከታተሉብን ወይም በአንድ ጊዜ ተደራርበው ከመጡብን ሁኔታው ይበልጥ ሊከብደን ይችላል። ያም ቢሆን፣ ይሖዋ በትኩረት እንደሚመለከተን እንዲሁም በእሱ እርዳታ የትኛውንም ፈተና በልበ ሙሉነት መጋፈጥ እንደምንችል አትዘንጋ።

9. በኢዮብ ላይ የደረሱትን አንዳንድ ፈተናዎች ግለጽ።

9 ይሖዋ ታማኝ ሰው የሆነውን ኢዮብን እንዴት እንደረዳው እንመልከት። ኢዮብ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተለያዩ ከባባድ ፈተናዎች ደርሰውበታል። ኢዮብ ከብቶቹ እንዳለቁ፣ አገልጋዮቹ እንደተገደሉ፣ ይባስ ብሎም የሚወዳቸው ልጆቹ በሙሉ እንደሞቱ በአንድ ቀን ውስጥ ሰማ። (ኢዮብ 1:13-19) ኢዮብ ከደረሰበት መሪር ሐዘን ገና ሳያገግም ከፍተኛ ሥቃይ የሚያስከትልና አካላዊ ገጽታውን የሚያበላሽ ከባድ ሕመም ያዘው። (ኢዮብ 2:7) ኢዮብ የነበረበት ሁኔታ በጣም አስከፊ ከመሆኑ የተነሳ “ሕይወቴን ተጸየፍኳት፤ በሕይወት መቀጠል አልፈልግም” በማለት ተናግሯል።—ኢዮብ 7:16

ይሖዋ ኢዮብን እንደሚወደውና እንደሚንከባከበው ለማስረዳት ፍጥረታቱን ስለሚንከባከብባቸው የተለያዩ መንገዶች ነግሮታል (አንቀጽ 10⁠ን ተመልከት)

10. ይሖዋ፣ ኢዮብ ያጋጠሙትን ፈተናዎች በጽናት ለመቋቋም የሚያስችል እርዳታ የሰጠው እንዴት ነው? (የሽፋኑን ሥዕል ተመልከት።)

10 ይሖዋ ኢዮብን በትኩረት ይመለከተው ነበር። ይሖዋ ኢዮብን ስለሚወደው ያጋጠሙትን ፈተናዎች በጽናት ለመቋቋም የሚያስችል እርዳታ ሰጥቶታል። ይሖዋ ኢዮብን በማነጋገር፣ ወደር ስለሌለው ጥበቡ እንዲሁም ለፍጥረታቱ ስለሚያሳየው ፍቅርና አሳቢነት አስታወሰው። ስለተለያዩ አስደናቂ እንስሳት ነገረው። (ኢዮብ 38:1, 2፤ 39:9, 13, 19, 27፤ 40:15፤ 41:1, 2) በተጨማሪም ይሖዋ፣ ኤሊሁ የተባለ አንድ ታማኝ ወጣት ኢዮብን እንዲያጽናናውና እንዲያበረታታው አደረገ። ኤሊሁ፣ ይሖዋ ምንጊዜም አገልጋዮቹን ለጽናታቸው ወሮታ እንደሚከፍላቸው ለኢዮብ አረጋገጠለት። ሆኖም ይሖዋ፣ ኤሊሁ ለኢዮብ ፍቅር የሚንጸባረቅበት እርማት እንዲሰጠውም አነሳስቶታል። ኤሊሁ፣ ኢዮብ የጽንፈ ዓለሙ ፈጣሪ ከሆነው ከይሖዋ አንጻር ያለውን ቦታ እንዲያስታውስ በማድረግ እይታውን እንዲያሰፋ ረድቶታል። (ኢዮብ 37:14) ከዚህም ሌላ ይሖዋ ለኢዮብ ኃላፊነት ሰጠው፤ ኃጢአት ለሠሩት ሦስት ጓደኞቹ እንዲጸልይ አዘዘው። (ኢዮብ 42:8-10) በዛሬው ጊዜስ ከባድ ፈተናዎች ሲያጋጥሙን ይሖዋ የሚደግፈን እንዴት ነው?

11. መከራ ሲያጋጥመን መጽሐፍ ቅዱስ ምን ማጽናኛ ይሰጠናል?

11 ይሖዋ ለኢዮብ እንዳደረገው እኛን በቀጥታ አያነጋግረንም፤ ሆኖም በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ያነጋግረናል። (ሮም 15:4) ለወደፊቱ ጊዜ ተስፋ በመስጠት ያጽናናናል። መከራ ሲያጋጥመን ሊያጽናኑን የሚችሉ ጥቂት የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳቦችን እስቲ እንመልከት። ይሖዋ ከባድ መከራን ጨምሮ ማንኛውም ነገር “[ከእሱ] ፍቅር ሊለየን እንደማይችል” በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ዋስትና ሰጥቶናል። (ሮም 8:38, 39) በተጨማሪም በጸሎት “ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ” እንደሆነ ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (መዝ. 145:18) ይሖዋ በእሱ እስከታመንን ድረስ ማንኛውንም ፈተና በጽናት መወጣት፣ አልፎ ተርፎም በመከራ ውስጥ ሆነንም ደስታ ማግኘት እንደምንችል ነግሮናል። (1 ቆሮ. 10:13፤ ያዕ. 1:2, 12) ከዚህም ሌላ የአምላክ ቃል፣ በአሁኑ ጊዜ የሚያጋጥሙን ፈተናዎች አምላክ ወደፊት ከሚሰጠን ዘላለማዊ በረከቶች ጋር ሲወዳደሩ ጊዜያዊና አጭር እንደሆኑ ያስታውሰናል። (2 ቆሮ. 4:16-18) ይሖዋ የችግሮቻችንን ዋነኛ መንስኤ እንደሚያስወግድ፣ ማለትም ሰይጣን ዲያብሎስንና የእሱን የክፋት ጎዳና የሚከተሉትን በሙሉ እንደሚያጠፋ አስተማማኝ ተስፋ ሰጥቶናል። (መዝ. 37:10) ወደፊት የሚያጋጥሙህን ፈተናዎች በጽናት ለመወጣት የሚረዱ አንዳንድ የሚያጽናኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በቃልህ ይዘሃል?

12. ይሖዋ ከቃሉ የተሟላ ጥቅም ማግኘት ከፈለግን ምን እንድናደርግ ይጠብቅብናል?

12 ይሖዋ መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረን ለማንበብና ባነበብነው ነገር ላይ በጥልቀት ለማሰብ ጊዜ እንድንመድብ ይጠብቅብናል። የተማርነውን ነገር በሥራ ላይ ስናውል እምነታችን ይጠናከራል፤ ወደ ሰማዩ አባታችንም ይበልጥ እንቀርባለን። ይህ ደግሞ የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች በጽናት ለመቋቋም ብርታት ይሰጠናል። በተጨማሪም ይሖዋ በቃሉ ለሚመሩ ሰዎች ቅዱስ መንፈሱን ይሰጣቸዋል። ይህ መንፈስ ደግሞ የትኛውንም ፈተና በጽናት መቋቋም እንድንችል “ከሰብዓዊ ኃይል በላይ [የሆነ] ኃይል” ይሰጠናል።—2 ቆሮ. 4:7-10

13. “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚያቀርብልን መንፈሳዊ ምግብ የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች በጽናት ለመቋቋም የሚረዳን እንዴት ነው?

13 በይሖዋ እርዳታ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ጠንካራ እምነት ለመገንባትና በመንፈሳዊ ንቁ ሆነን ለመኖር የሚረዱ ጽሑፎችን፣ ቪዲዮዎችንና ሙዚቃዎችን አትረፍርፎ ያዘጋጅልናል። (ማቴ. 24:45) ወቅቱን ጠብቆ የሚቀርብልንን ይህን መንፈሳዊ ምግብ በተሟላ ሁኔታ ልንጠቀምበት ይገባል። በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር አንዲት እህት ለዚህ ሁሉ መንፈሳዊ ምግብ ያላትን አድናቆት በቅርቡ ገልጻ ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “በይሖዋ አገልግሎት ባሳለፍኳቸው 40 ዓመታት ውስጥ ንጹሕ አቋሜ በተደጋጋሚ ተፈትኗል።” እህታችን የተለያዩ ከባባድ ፈተናዎች አጋጥመዋታል። ለምሳሌ አያቷ፣ ጠጥቶ በሚያሽከረክር ሹፌር ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ ወላጆቿ በከባድ ሕመም ሲሠቃዩ ከቆዩ በኋላ ሞተዋል፤ እሷም ሁለት ጊዜ በካንሰር በሽታ ተይዛ ነበር። ታዲያ ለመጽናት የረዳት ምንድን ነው? እንዲህ ብላለች፦ “የይሖዋ እንክብካቤ ተለይቶኝ አያውቅም። በታማኝና ልባም ባሪያ አማካኝነት ያቀረበልኝ መንፈሳዊ ምግብ ለመጽናት ረድቶኛል። ይህን መንፈሳዊ ምግብ በማግኘቴ እንደ ኢዮብ ‘እስክሞት ድረስ ንጹሕ አቋሜን አላጎድፍም!’ ማለት እችላለሁ።”—ኢዮብ 27:5

በጉባኤ ውስጥ ላሉ ወንድሞችና እህቶች በረከት መሆን የምንችለው እንዴት ነው? (አንቀጽ 14⁠ን ተመልከት)

14. ይሖዋ ፈተና ሲያጋጥመን እኛን ለመደገፍ በእምነት ባልንጀሮቻችን የሚጠቀመው እንዴት ነው? (1 ተሰሎንቄ 4:9)

14 ይሖዋ በአስጨናቂ ጊዜያት ሕዝቦቹ እርስ በርስ እንዲዋደዱና አንዳቸው ሌላውን እንዲያጽናኑ አሠልጥኗቸዋል። (2 ቆሮ. 1:3, 4፤ 1 ተሰሎንቄ 4:9 አንብብ።) ልክ እንደ ኤሊሁ፣ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጋጥመን በታማኝነት እንድንጸና እኛን ለመርዳት ዝግጁ ናቸው። (ሥራ 14:22) ዳያን የተባለችን እህት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ባለቤቷ ከባድ የጤና እክል ካጋጠመው በኋላ ጉባኤያቸው ያበረታታትና በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆና እንድትቀጥል የረዳት እንዴት እንደሆነ እንመልከት። እንዲህ ብላለች፦ “ሁኔታው ከባድ ነበር። ሆኖም በእነዚያ አስቸጋሪ ወራት አፍቃሪ የሆነውን አምላካችንን ኃያል እጅ ተመልክተናል። የጉባኤያችን ወንድሞችና እህቶች በተለያዩ መንገዶች ረድተውናል። መጥተው ሲጠይቁን፣ ሲደውሉልን እንዲሁም እቅፍ ሲያደርጉን ለመጽናት የሚያስፈልገንን ብርታት አግኝተናል። እኔ መኪና መንዳት ስለማልችል ወንድሞችና እህቶች በስብሰባዎች ላይ እንድገኝ እንዲሁም ሁኔታዬ ሲፈቅድ አገልግሎት እንድወጣ ረድተውኛል።” እንዲህ ባለ አፍቃሪ መንፈሳዊ ቤተሰብ ውስጥ መታቀፍ ምንኛ የሚያስደስት ነው!

ለይሖዋ ፍቅራዊ እንክብካቤ አመስጋኞች ነን

15. የሚያጋጥመንን ማንኛውም መከራ መቋቋም እንደምንችል እርግጠኞች የሆንነው ለምንድን ነው?

15 ሁላችንም በተለያየ መልኩ ፈተና ያጋጥመናል። ይሁንና እስካሁን እንደተመለከትነው፣ መቼም ቢሆን ፈተናውን ብቻችንን መጋፈጥ አያስፈልገንም። ይሖዋ ልክ እንደ አንድ አፍቃሪ አባት ሁልጊዜ በትኩረት ይመለከተናል። እሱ ከጎናችን ነው፤ እርዳታ ለማግኘት የምናሰማውን ጩኸት ለማዳመጥ እንዲሁም እኛን ለመደገፍ ሁሌም ዝግጁ ነው። (ኢሳ. 43:2) ለመጽናት የሚያስፈልጉንን ነገሮች በሙሉ አትረፍርፎ ስለሰጠን ማንኛውንም መከራ መቋቋም እንደምንችል እርግጠኞች ነን። የጸሎት መብት፣ መጽሐፍ ቅዱስ፣ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ እንዲሁም እርዳታ ሲያስፈልገን የሚደርስልን አፍቃሪ የወንድማማች ማኅበር ሰጥቶናል።

16. በይሖዋ ፍቅራዊ እንክብካቤ ውስጥ መኖር የምንችለው እንዴት ነው?

16 በትኩረት የሚመለከተን ሰማያዊ አባት ስላለን ምንኛ አመስጋኞች ነን! “ልባችን በእሱ ሐሴት ያደርጋል።” (መዝ. 33:21) ይሖዋ እኛን ለመርዳት ባደረጋቸው ዝግጅቶች በሙሉ በመጠቀም የእሱን ፍቅራዊ እንክብካቤ እንደምናደንቅ እናሳያለን። በተጨማሪም በአምላክ እንክብካቤ ውስጥ ለመኖር የበኩላችንን ድርሻ መወጣት ያስፈልገናል። በሌላ አነጋገር፣ ይሖዋን ለመታዘዝና በእሱ ዓይን ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ማድረጋችንን ከቀጠልን እሱ ለዘላለም በትኩረት ይመለከተናል!—1 ጴጥ. 3:12

መዝሙር 30 አባቴ፣ አምላኬና ወዳጄ

^ በዛሬው ጊዜ የሚያጋጥሙንን መከራዎች ለመወጣት የይሖዋ እርዳታ ያስፈልገናል። ይህ ርዕስ፣ ይሖዋ ሕዝቡን በትኩረት እንደሚመለከት ዋስትና ይሰጠናል። ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ የሚያጋጥሙንን ችግሮች ይመለከታል፤ እንዲሁም እነዚህን ችግሮች ለመወጣት የሚያስፈልገንን እርዳታ ይሰጠናል።

^ አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።