የጥናት ርዕስ 36
አስፈላጊ ሸክሞችን ተሸከሙ፤ የቀረውን ጣሉ
“ማንኛውንም ሸክም . . . ከላያችን አንስተን እንጣል፤ ከፊታችን የሚጠብቀንን ሩጫም በጽናት እንሩጥ።”—ዕብ. 12:1
መዝሙር 33 ሸክማችሁን በይሖዋ ላይ ጣሉ
ማስተዋወቂያ a
1. በዕብራውያን 12:1 መሠረት የሕይወት ሩጫችንን ለማጠናቀቅ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
መጽሐፍ ቅዱስ የክርስቲያኖችን ሕይወት ከሩጫ ውድድር ጋር ያመሳስለዋል። ሩጫውን የሚያጠናቅቁ ሰዎች የዘላለም ሕይወት ሽልማት ያገኛሉ። (2 ጢሞ. 4:7, 8) ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ወደ መጨረሻው መስመር እየተጠጋን ስለሆነ በሩጫው ለመቀጠል የቻልነውን ሁሉ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። የሕይወትን ሩጫ በተሳካ ሁኔታ ያጠናቀቀው ሐዋርያው ጳውሎስ ውድድሩን ለማሸነፍ ምን ማድረግ እንዳለብን ነግሮናል። “ማንኛውንም ሸክም . . . ከላያችን አንስተን እንጣል፤ ከፊታችን የሚጠብቀንን ሩጫም በጽናት እንሩጥ” የሚል መመሪያ ሰጥቶናል።—ዕብራውያን 12:1ን አንብብ።
2. ‘ማንኛውንም ሸክም መጣል’ ሲባል ምን ማለት ነው?
2 ጳውሎስ “ማንኛውንም ሸክም . . . ከላያችን አንስተን እንጣል” ሲል አንድ ክርስቲያን መሸከም ያለበት ምንም ዓይነት ሸክም እንደሌለ መግለጹ ነበር? በፍጹም፣ እንደዚያ ማለቱ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ማንኛውንም አላስፈላጊ ሸክም ማስወገድ እንዳለብን መግለጹ ነበር። እንዲህ ያለው ሸክም ፍጥነታችንን ሊቀንሰውና ሊያደክመን ይችላል። በሩጫው መጽናት ከፈለግን ፍጥነታችንን ሊቀንስ የሚችልን ማንኛውንም አላስፈላጊ ሸክም ለይተን ማወቅና ማስወገድ ይኖርብናል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ መሸከም ያለብንን ሸክም ችላ ልንል አይገባም። አለዚያ ከውድድሩ ልንባረር እንችላለን። (2 ጢሞ. 2:5) ለመሆኑ መሸከም ያለብን የትኞቹን ሸክሞች ነው?
3. (ሀ) በገላትያ 6:5 መሠረት ምን መሸከም ይኖርብናል? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን? ለምንስ?
3 ገላትያ 6:5ን አንብብ። ጳውሎስ መሸከም ያለብንን አንድ ነገር ጠቅሷል። “እያንዳንዱ የራሱን የኃላፊነት ሸክም ይሸከማል” ሲል ጽፏል። እዚህ ላይ ጳውሎስ፣ በግለሰብ ደረጃ በአምላክ ፊት ስላለን ኃላፊነት እየተናገረ ነው፤ ይህን ሸክም ሌላ ሰው ሊሸከምልን አይችልም። በዚህ ርዕስ ውስጥ ‘የራሳችን የኃላፊነት ሸክም’ የትኞቹን ነገሮች እንደሚያካትት እንዲሁም እንዴት አድርገን እንደምንሸከመው እንመረምራለን። በተጨማሪም የትኞቹን አላስፈላጊ ሸክሞች ተሸክመን ሊሆን እንደሚችል እንዲሁም እነዚህን ሸክሞች እንዴት አድርገን መጣል እንደምንችል እንመለከታለን። የራሳችንን የኃላፊነት ሸክም መሸከምና አላስፈላጊ ሸክሞችን ማስወገድ የሕይወት ሩጫችንን በተሳካ ሁኔታ ለማጠናቀቅ ይረዳናል።
መሸከም ያለብን ሸክሞች
4. ራሳችንን ስንወስን የገባነው ቃል ከባድ ሸክም ያልሆነው ለምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
4 ራሳችንን ስንወስን የገባነው ቃል። ለይሖዋ ራሳችንን ስንወስን እሱን ለማምለክና ፈቃዱን ለማድረግ ቃል ገብተናል። ይህን ቃላችንን ልንጠብቅ ይገባል። ራሳችንን ስንወስን የገባነውን ቃል ጠብቀን መኖር በቁም ነገር ሊታይ የሚገባው ኃላፊነት ነው፤ ከባድ ሸክም ግን አይደለም። ምክንያቱም ይሖዋ የፈጠረን ፈቃዱን እንድናደርግ ነው። (ራእይ 4:11) በውስጣችን መንፈሳዊ ፍላጎት አኑሯል፤ የፈጠረንም በራሱ መልክ ነው። በዚህም የተነሳ ወደ እሱ መቅረብና የእሱን ፈቃድ በማድረግ ደስታ ማግኘት እንችላለን። (መዝ. 40:8) በተጨማሪም የአምላክን ፈቃድ ስናደርግና ልጁን ስንከተል ‘ለራሳችን እረፍት እናገኛለን።’—ማቴ. 11:28-30
5. ራስህን ስትወስን የገባኸውን ቃል ለመጠበቅ ምን ሊረዳህ ይችላል? (1 ዮሐንስ 5:3)
5 ይህን ሸክም መሸከም የምትችለው እንዴት ነው? ሁለት ነገሮች ሊረዱህ ይችላሉ። አንደኛ፣ ለይሖዋ ያለህን ፍቅር ማጠናከርህን ቀጥል። ይህን ማድረግ የምትችለው እሱ ባደረገልህ መልካም ነገሮችና ለወደፊቱ ባዘጋጀልህ በረከቶች ላይ በማሰላሰል ነው። ለአምላክ ያለህ ፍቅር እያደገ ሲሄድ እሱን መታዘዝ ይበልጥ ቀላል ይሆንልሃል። (1 ዮሐንስ 5:3ን አንብብ።) ሁለተኛ፣ ኢየሱስን ምሰል። ኢየሱስ የአምላክን ፈቃድ በመፈጸም ረገድ የተሳካለት ይሖዋ እንዲረዳው ስለጸለየና በሽልማቱ ላይ ስላተኮረ ነው። (ዕብ. 5:7፤ 12:2) አንተም እንደ ኢየሱስ፣ ይሖዋ እንዲረዳህ ጸልይ፤ እንዲሁም አእምሮህ በዘላለም ሕይወት ተስፋህ ላይ ያተኮረ ይሁን። ለአምላክ ያለህን ፍቅር ማሳደግህና ልጁን መምሰልህ ራስህን ስትወስን የገባኸውን ቃል ለመጠበቅ ይረዳሃል።
6. የቤተሰብ ኃላፊነታችንን መወጣት ያለብን ለምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
6 የቤተሰብ ኃላፊነታችን። በሕይወት ሩጫ ስንካፈል ከቤተሰቦቻችን ይልቅ ይሖዋንና ኢየሱስን መውደድ እንዳለብን ማስታወስ ይኖርብናል። (ማቴ. 10:37) ይህ ሲባል ግን የቤተሰብ ኃላፊነታችንን ችላ እንላለን ማለት አይደለም። እንዲያውም በአምላክና በክርስቶስ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረን የቤተሰብ ኃላፊነታችንን መወጣት ይኖርብናል። (1 ጢሞ. 5:4, 8) እንዲህ ስናደርግ ይበልጥ ደስተኞች እንሆናለን። ደግሞም ይሖዋ ባልና ሚስት እርስ በርስ ሲዋደዱና ሲከባበሩ፣ ወላጆች ልጆቻቸውን ሲወዱና ሲያሠለጥኑ እንዲሁም ልጆች ወላጆቻቸውን ሲታዘዙ ቤተሰቦች ደስተኛ እንደሚሆኑ ያውቃል።—ኤፌ. 5:33፤ 6:1, 4
7. በቤተሰብ ውስጥ ያለህን ኃላፊነት መወጣት የምትችለው እንዴት ነው?
7 ይህን ሸክም መሸከም የምትችለው እንዴት ነው? በቤተሰብ ውስጥ ያለህ ሚና ምንም ይሁን ምን በስሜት፣ በባሕል ወይም ባለሙያዎች በሚሰጡት ምክር ከመመራት ይልቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ጥበብ የሚንጸባረቅበት ምክር ተከተል። (ምሳሌ 24:3, 4) መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችንን ጥሩ አድርገህ ተጠቀምባቸው። ጽሑፎቻችን የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል የሚያሳይ ጠቃሚ ምክር ይዘዋል። ለምሳሌ “ለቤተሰብ” የሚለው ዓምድ ባለትዳሮች፣ ወላጆች እንዲሁም ወጣቶች በአሁኑ ጊዜ የሚያጋጥሟቸውን የተለያዩ ተፈታታኝ ሁኔታዎች መወጣት እንዲችሉ የሚረዳ ጠቃሚ መረጃ ይዟል። b ሌሎቹ የቤተሰብህ አባላት ይህን ባያደርጉ እንኳ የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በሥራ ላይ ለማዋል ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። ይህን ስታደርግ ቤተሰብህ ይጠቀማል፤ የይሖዋን በረከትም ታገኛለህ።—1 ጴጥ. 3:1, 2
8. ውሳኔዎቻችን ምን ዓይነት ውጤት ሊያስከትሉብን ይችላሉ?
8 የምናደርጋቸው ውሳኔዎች የሚያስከትሉት ውጤት። ይሖዋ ልዩ ስጦታ የሆነውን የመምረጥ ነፃነት ሰጥቶናል፤ ጥሩ ውሳኔዎችን ማድረግ የሚያስገኘውን ደስታ እንድናጣጥምም ይፈልጋል። ሆኖም መጥፎ ውሳኔዎች ከሚያስከትሉት መዘዝ ከለላ አያደርግልንም። (ገላ. 6:7, 8) በዚህም የተነሳ መጥፎ ምርጫ ስናደርግ፣ ያልታሰበበት ቃል ስንናገር እንዲሁም የችኮላ እርምጃ ስንወስድ መዘዙን እንቀበላለን። አንዳንድ ጊዜ ባደረግነው ነገር የተነሳ ሕሊናችን ይረብሸን ይሆናል። ሆኖም ለውሳኔዎቻችን ኃላፊነት መውሰዳችን ኃጢአታችንን እንድንናዘዝ፣ ስህተታችንን እንድናርም እንዲሁም ጥፋቱን ላለመድገም እንድንጠነቀቅ ያነሳሳናል። እንዲህ ያሉ እርምጃዎችን መውሰዳችን በሕይወት ሩጫ ላይ እንድንቀጥል ይረዳናል።
9. መጥፎ ውሳኔ አድርገህ ከሆነ ምን ዓይነት እርምጃ መውሰድ ትችላለህ? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
9 ይህን ሸክም መሸከም የምትችለው እንዴት ነው? ያደረግከውን መጥፎ ውሳኔ መቀልበስ ካልቻልክ፣ ያለህበትን ሁኔታ አምነህ ተቀበል። የፈሰሰ ውኃ እንደማይታፈስ አስታውስ። ሰበብ በማቅረብ ወይም ላደረግከው ውሳኔ ራስህንም ሆነ ሌሎችን በመኮነን ጉልበት አታጥፋ። ከዚህ ይልቅ ስህተትህን አምነህ ተቀበል፤ እንዲሁም አሁን ማድረግ በምትችለው ነገር ላይ አተኩር። በሠራኸው ስህተት የተነሳ ሕሊናህ የሚወቅስህ ከሆነ በትሕትና ወደ ይሖዋ ጸልይ፤ ጥፋትህን እመን፤ እንዲሁም ይቅር እንዲልህ ጠይቀው። (መዝ. 25:11፤ 51:3, 4) የበደልካቸው ሰዎች ካሉ ይቅርታ ጠይቅ፤ አስፈላጊ ከሆነ ደግሞ የሽማግሌዎችን እርዳታ ለማግኘት ጥረት አድርግ። (ያዕ. 5:14, 15) ከስህተትህ ተማር፤ ጥፋትህን ላለመድገምም ተጠንቀቅ። እንዲህ ካደረግክ ይሖዋ ምሕረቱን እንደሚያሳይህና የሚያስፈልግህን እርዳታ እንደሚሰጥህ መተማመን ትችላለህ።—መዝ. 103:8-13
‘መጣል’ ያለብን ሸክሞች
10. ከራሳችን በምንጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ አለመሆናችን ከባድ ሸክም የሚሆንብን ለምንድን ነው? (ገላትያ 6:4)
10 ከራሳችን በምንጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ አለመሆን። ራሳችንን ከሌሎች ጋር የምናወዳድር ከሆነ ይህ ሸክም ሊሆንብን ይችላል። (ገላትያ 6:4ን አንብብ።) ሁልጊዜ ራሳችንን ከሌሎች ጋር የምናወዳድር ከሆነ የምቀኝነትና የፉክክር ስሜት ሊጠናወተን ይችላል። (ገላ. 5:26) የሌሎችን ያህል ለመሥራት ስንል አቅማችንና ሁኔታችን ከሚፈቅድልን በላይ ልንጣጣር እንችላለን። “የዘገየ ተስፋ ልብን ያሳምማል” ከተባለ ጨርሶ ሊደረስበት የማይችል ግብ ማውጣትማ ምንኛ ልብ የሚያሳምም ይሆናል! (ምሳሌ 13:12) እንዲህ ማድረግ ጉልበታችንን ሊያሟጥጠውና ለሕይወት በምናደርገው ሩጫ ፍጥነታችንን ሊቀንሰው ይችላል።—ምሳሌ 24:10
11. ከራስህ በምትጠብቀው ነገር ረገድ ሚዛናዊ ለመሆን ምን ሊረዳህ ይችላል?
11 ይህን ሸክም መጣል የምትችለው እንዴት ነው? ይሖዋ ከሚጠብቅብህ በላይ ከራስህ አትጠብቅ። ይሖዋ በሌለህ መጠን እንድትሰጥ አይጠብቅብህም። (2 ቆሮ. 8:12) ይሖዋ የምታከናውነውን ነገር ከሌሎች ጋር እንደማያወዳድር ተማመን። (ማቴ. 25:20-23) በሙሉ ልብ የምታቀርበውን አገልግሎት፣ ታማኝነትህንና ጽናትህን ከፍ አድርጎ ይመለከታል። ልክህን የምታውቅ ሁን፤ ጤናህና ያለህበት ሁኔታ በአሁኑ ጊዜ ማከናወን የምትችለውን ነገር ሊገድብብህ እንደሚችል አምነህ ተቀበል። ዕድሜህ ወይም የጤንነትህ ሁኔታ የሚገድብህ ከሆነ ልክ እንደ ቤርዜሊ አንዳንድ ኃላፊነቶችን ‘አልችልም’ ለማለት ፈቃደኛ ሁን። (2 ሳሙ. 19:35, 36) እንደ ሙሴ የሌሎችን እርዳታ ተቀበል፤ እንዲሁም አስፈላጊ ከሆነ ሥራህን ለሌሎች አካፍል። (ዘፀ. 18:21, 22) በዚህ መልኩ ልክህን እንደምታውቅ ማሳየትህ ምክንያታዊ ያልሆነ ግብ በማውጣት በሕይወት ሩጫ ላይ ራስህን እንዳታደክም ይረዳሃል።
12. ሌሎች ለሚያደርጉት መጥፎ ውሳኔ ተጠያቂ ነን? አብራራ።
12 ሌሎች ለሚያደርጉት መጥፎ ውሳኔ ኃላፊነት መውሰድ። ለሌሎች ውሳኔ ማድረግ አንችልም፤ እንዲሁም የሚያደርጉት መጥፎ ውሳኔ ከሚያስከትልባቸው መዘዝ ሁልጊዜ ልንከልላቸው አንችልም። ለምሳሌ አንድ ልጅ ይሖዋን ማገልገሉን ለማቆም ሊወስን ይችላል። ይህ ውሳኔው ወላጆቹን በጣም እንደሚጎዳቸው ጥያቄ የለውም። ሆኖም ልጃቸው ባደረገው መጥፎ ውሳኔ ራሳቸውን የሚወቅሱ ወላጆች ላያቸው ላይ ከባድ ሸክም እየጫኑ ነው። ይሖዋ ይህን ሸክም እንዲሸከሙ አይጠብቅባቸውም።—ሮም 14:12
13. ወላጆች ልጆቻቸው መጥፎ ውሳኔ ካደረጉ ምን ማድረግ ይችላሉ?
13 ይህን ሸክም መጣል የምትችለው እንዴት ነው? ይሖዋ ለሁላችንም የመምረጥ ነፃነት እንደሰጠን አትዘንጋ። ሁሉም ሰው የራሱን ምርጫ እንዲያደርግ ነፃነት ሰጥቷል። ይህም እሱን ለማገልገል ወይም ላለማገልገል መምረጥን ይጨምራል። ይሖዋ ፍጹም ወላጅ እንዳልሆንክ ያውቃል፤ እሱ የሚጠብቅብህ የምትችለውን እንድታደርግ ብቻ ነው። ልጅህ የሚያደርገው ምርጫ የእሱ እንጂ የአንተ ኃላፊነት አይደለም። (ምሳሌ 20:11) ያም ቢሆን፣ ልጆችህን ስታሳድግ ያደረግካቸውን ስህተቶች እያስታወስክ ትቆጭ ይሆናል። ከሆነ የሚሰማህን ነገር ለይሖዋ ንገረው፤ ይቅር እንዲልህም ጠይቀው። ይሖዋ ወደ ኋላ ተመልሰህ ያለፈውን ነገር መቀየር እንደማትችል ያውቃል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ልጅህ የዘራውን እንዳያጭድ እንድትከላከልለት አይጠብቅብህም። ልጅህ ወደ ይሖዋ ለመመለስ ጥረት ካደረገ ይሖዋ በደስታ እንደሚቀበለው አስታውስ።—ሉቃስ 15:18-20
14. ከመጠን ያለፈ የበደለኝነት ስሜት ልናስወግደው የሚገባ ሸክም የሆነው ለምንድን ነው?
14 ከመጠን ያለፈ የበደለኝነት ስሜት። ኃጢአት ስንፈጽም የበደለኝነት ስሜት ቢሰማን የሚያስገርም አይደለም። ሆኖም ይሖዋ ከመጠን ያለፈ የበደለኝነት ስሜት እንዲሰማን አይፈልግም። ይህ ልንጥለው የሚገባ ሸክም ነው። ይሁንና የሚሰማን የበደለኝነት ስሜት ከመጠን ያለፈ መሆን አለመሆኑን እንዴት እናውቃለን? ኃጢአታችንን ከተናዘዝን፣ ንስሐ ከገባንና ጥፋታችንን ላለመድገም ተገቢውን እርምጃ ከወሰድን ይሖዋ ይቅር እንዳለን መተማመን እንችላለን። (ሥራ 3:19) እነዚህን እርምጃዎች ከወሰድን በኋላ ይሖዋ የበደለኝነት ስሜት እንዲሰማን አይፈልግም። ከመጠን ያለፈ የበደለኝነት ስሜት ምን ያህል ጎጂ እንደሆነ ያውቃል። (መዝ. 31:10) በሐዘን ከተዋጥን ተስፋ ቆርጠን ለሕይወት የምናደርገውን ሩጫ ልናቋርጥ እንችላለን።—2 ቆሮ. 2:7
15. ከመጠን ያለፈ የበደለኝነት ስሜትን ለማስወገድ ምን ሊረዳህ ይችላል? (1 ዮሐንስ 3:19, 20) (ሥዕሉንም ተመልከት።)
15 ይህን ሸክም መጣል የምትችለው እንዴት ነው? ከመጠን ባለፈ የበደለኝነት ስሜት ከተደቆስክ ይሖዋ በሚሰጠው እውነተኛ ይቅርታ ላይ አተኩር። (መዝ. 130:4) ይሖዋ፣ ከልባቸው ንስሐ የገቡ ሰዎችን ይቅር ስለሚልበት ሁኔታ ሲናገር “ኃጢአታቸውንም ከእንግዲህ አላስታውስም” ብሏል። (ኤር. 31:34) ይህም ማለት ይሖዋ አንዴ ኃጢአትህን ይቅር ካለ በኋላ በዚያ ኃጢአት መልሶ አይጠይቅህም ማለት ነው። በመሆኑም የኃጢአትህን መዘዝ መቀበልህ ይሖዋ ይቅር እንዳላለህ የሚያሳይ ማስረጃ እንደሆነ አድርገህ አታስብ። በተጨማሪም ቀደም ሲል የሠራኸው ስህተት በአሁኑ ጊዜ በእሱ አገልግሎት ማከናወን የምትችለውን ነገር ቢገድበው ራስህን አትውቀስ። ይሖዋ የፈጸምከውን ኃጢአት እያስታወሰ አይኖርም፤ አንተም እንዲህ ልታደርግ አይገባም።—1 ዮሐንስ 3:19, 20ን አንብብ።
ውድድሩን ለማሸነፍ ሩጥ
16. ሯጮች እንደመሆናችን መጠን ምን መገንዘብ ይኖርብናል?
16 የሕይወትን ሩጫ ስንሮጥ ‘ሽልማቱን በሚያስገኝ ሁኔታ መሮጥ’ ይኖርብናል። (1 ቆሮ. 9:24) መሸከም ባለብን ሸክምና ማስወገድ ባለብን ሸክም መካከል ያለውን ልዩነት ከተገነዘብን ይህን ማድረግ እንችላለን። በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ መሸከም ካለብንና ማስወገድ ካለብን ሸክሞች መካከል አንዳንዶቹን ተመልክተናል። ግን ሌሎችም አሉ። ኢየሱስ “ከልክ በላይ በመብላትና በመጠጣት እንዲሁም ስለ ኑሮ በመጨነቅ” ሸክም ሊበዛብን እንደሚችል ተናግሯል። (ሉቃስ 21:34) ይህም ሆነ ሌሎች ጥቅሶች የሕይወትን ሩጫ ስንሮጥ ማድረግ ያለብንን አንዳንድ ማስተካከያዎች ለማወቅ ያስችሉናል።
17. የሕይወትን ሩጫ እንደምናሸንፍ መተማመን የምንችለው ለምንድን ነው?
17 ይሖዋ የሚያስፈልገንን ብርታት ስለሚሰጠን የሕይወትን ሩጫ እንደምናሸንፍ መተማመን እንችላለን። (ኢሳ. 40:29-31) በመሆኑም ፍጥነትህን አትቀንስ! ከፊቱ የሚጠብቀውን ሽልማት ለማግኘት አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ ያደረገውን የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ ተከተል። (ፊልጵ. 3:13, 14) ይህን ሩጫ ማንም ሊሮጥልህ አይችልም፤ ግን በይሖዋ እርዳታ ሊሳካልህ ይችላል። ይሖዋ የኃላፊነት ሸክምህን እንድትሸከምና አላስፈላጊ ሸክሞችን እንድታስወግድ ሊረዳህ ይችላል። (መዝ. 68:19) እሱ ከጎንህ ስለሆነ ሩጫውን በጽናት መሮጥና ማሸነፍ ትችላለህ!
መዝሙር 65 ወደፊት ግፋ!
a ይህ ርዕስ የሕይወትን ሩጫ ለመሮጥ ይረዳናል። ሯጮች እንደመሆናችን መጠን አንዳንድ ሸክሞችን መሸከም አለብን። ከእነዚህ መካከል ራሳችንን ስንወስን የገባነው ቃል፣ የቤተሰብ ኃላፊነታችን እንዲሁም ውሳኔዎቻችን የሚያስከትሉት ውጤት ይገኙበታል። ሆኖም ፍጥነታችን እንዲቀንስ የሚያደርግን ማንኛውንም አላስፈላጊ ሸክም ከላያችን አንስተን መጣል ይኖርብናል። እንዲህ ያለው ሸክም የትኞቹን ነገሮች ያካትታል? ይህ ርዕስ ይህን ጥያቄ ይመልስልናል።
b “ለቤተሰብ” የሚለውን ዓምድ jw.org ላይ ማግኘት ትችላለህ። እዚያ ላይ ከወጡት ርዕሶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦ ለባለትዳሮች፣ “አክብሮት ማሳየት የሚቻለው እንዴት ነው?” እና “አድናቆት ማሳየት የሚቻለው እንዴት ነው?”፤ ለወላጆች፣ “ልጆች ዘመናዊ ስልክን በጥበብ እንዲጠቀሙ ማስተማር” እና “በአሥራዎቹ ዕድሜ ከሚገኝ ልጃችሁ ጋር የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ”፤ ለወጣቶች፣ “የእኩዮችን ተጽዕኖ መቋቋም የሚቻልበት መንገድ” እና “ብቸኝነትን መቋቋም የሚቻለው እንዴት ነው?”