በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 33

ከዳንኤል ምሳሌ ተማሩ

ከዳንኤል ምሳሌ ተማሩ

“አንተ እጅግ የተወደድክ ነህ።”—ዳን. 9:23

መዝሙር 73 ድፍረት ስጠን

ማስተዋወቂያ a

1. ባቢሎናውያን በነቢዩ ዳንኤል የተደመሙት ለምንድን ነው?

 ነቢዩ ዳንኤል በባቢሎናውያን ተማርኮ ወደ ሩቅ አገር በተወሰደበት ወቅት ገና ወጣት ነበር። ዳንኤል ልጅ ቢሆንም የባቢሎን ባለሥልጣናት በጣም ተደመሙበት። እነሱ ያዩት ‘ውጫዊ ገጽታውን’ ማለትም ‘እንከን የሌለበት፣ መልከ መልካም’ እና ከታዋቂ ቤተሰብ የመጣ መሆኑን ነው። (1 ሳሙ. 16:7) በመሆኑም ባቢሎናውያን በቤተ መንግሥቱ ውስጥ እንዲያገለግል አሠለጠኑት።—ዳን. 1:3, 4, 6

2. ይሖዋ ለዳንኤል ምን አመለካከት ነበረው? (ሕዝቅኤል 14:14)

2 ይሖዋ ዳንኤልን ይወደው ነበር፤ ሆኖም የወደደው በመልኩ ወይም ባለው ሥልጣን የተነሳ ሳይሆን ይህ ወጣት ምን ዓይነት ሰው ለመሆን እንደመረጠ ስላየ ነው። እንዲያውም ይሖዋ ዳንኤልን ለበርካታ አሥርተ ዓመታት እሱን በታማኝነት ካገለገሉት ከኖኅና ከኢዮብ ጋር አብሮ የጠቀሰው ዳንኤል ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ወይም በሃያዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ሳለ ሊሆን ይችላል። (ዘፍ. 5:32፤ 6:9, 10፤ ኢዮብ 42:16, 17፤ ሕዝቅኤል 14:14ን አንብብ።) ደግሞም ዳንኤል ባሳለፈው ረጅምና አስደናቂ ሕይወት በሙሉ ይሖዋ ይወደው ነበር።—ዳን. 10:11, 19

3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

3 ዳንኤልን በይሖዋ ዓይን ተወዳጅ እንዲሆን ካደረጉት ባሕርያት መካከል ሁለቱን በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን። በመጀመሪያ የእያንዳንዱን ባሕርይ ምንነት እንዲሁም ዳንኤል እነዚህን ባሕርያት ያንጸባረቀው እንዴት እንደሆነ እናያለን። ከዚያም ዳንኤል እነዚህን ባሕርያት እንዲያዳብር የረዳው ምን እንደሆነ እንመረምራለን። በመጨረሻም የእሱን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንወያያለን። ይህ ርዕስ በዋነኝነት የተዘጋጀው ለወጣቶች ቢሆንም ሁላችንም ከዳንኤል ምሳሌ ትምህርት ማግኘት እንችላለን።

የዳንኤልን ድፍረት ኮርጁ

4. ዳንኤል ድፍረት ያሳየው እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።

4 ደፋር የሆኑ ሰዎች ፍርሃት ሊሰማቸው ይችላል፤ ሆኖም በፍርሃት ተሽመድምደው ትክክል የሆነውን ነገር ከማድረግ ወደኋላ አይሉም። ዳንኤል በጣም ደፋር ወጣት ነበር። ድፍረት ያሳየባቸውን ሁለት አጋጣሚዎች እስቲ እንመልከት። የመጀመሪያው ታሪክ የተፈጸመው ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን ካጠፉ ከሁለት ዓመት ገደማ በኋላ ሳይሆን አይቀርም። የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር አንድን ግዙፍ ምስል የሚያሳይ አስፈሪ ሕልም ተመለከተ። ሕልሙን ከነትርጉሙ ካልነገሩት ዳንኤልን ጨምሮ ሁሉንም ጠቢባን እንደሚገድል ዛተ። (ዳን. 2:3-5) ዳንኤል አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ነበረበት፤ አለዚያ ብዙዎች ሕይወታቸውን ያጣሉ። ስለዚህ “ወደ ንጉሡ ገብቶ የሕልሙን ትርጉም ለእሱ የሚያስታውቅበት ጊዜ እንዲሰጠው ንጉሡን ጠየቀው።” (ዳን. 2:16) ይህን ለማድረግ ድፍረትና እምነት ጠይቆበታል። ምክንያቱም ዳንኤል ከዚያ በፊት ሕልም እንደተረጎመ የሚገልጽ ዘገባ የለም። ዳንኤል፣ ባቢሎናውያን ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ብለው የሰየሟቸውን ጓደኞቹን “የሰማይ አምላክ ምሕረት እንዲያሳያቸውና ሚስጥሩን እንዲገልጥላቸው ይጸልዩ ዘንድ ነገራቸው።” (ዳን. 2:18) ይሖዋ ጸሎታቸውን መልሶላቸዋል። ዳንኤል በአምላክ እርዳታ የናቡከደነጾርን ሕልም ተረጎመለት። የዳንኤልና የጓደኞቹ ሕይወትም ተረፈ።

5. የዳንኤል ድፍረት በድጋሚ የተፈተነው እንዴት ነው?

5 ዳንኤል ስለ ግዙፉ ምስል የሚገልጸውን ሕልም ከተረጎመ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ድፍረቱ በድጋሚ ተፈተነ። ናቡከደነጾር ሌላ አስፈሪ ሕልም አየ። ይህ ሕልም ደግሞ አንድን ግዙፍ ዛፍ የሚያሳይ ነው። ዳንኤል የሕልሙን ትርጉም ለንጉሡ በድፍረት ነገረው፤ እንዲያውም ንጉሡ አእምሮውን እንደሚስትና ለተወሰነ ጊዜ ያህል ከዙፋኑ እንደሚነሳ ገለጸለት። (ዳን. 4:25) ንጉሡ ይህን መልእክት እንደ ዓመፅ ሊቆጥረውና ዳንኤልን ሊያስገድለው ይችል ነበር። ያም ቢሆን ዳንኤል በድፍረት መልእክቱን አድርሷል።

6. ዳንኤል ደፋር እንዲሆን የረዳው ምን ሊሆን ይችላል?

6 ዳንኤል በመላ ሕይወቱ ደፋር እንዲሆን የረዳው ምን ሊሆን ይችላል? በልጅነቱ ከእናቱና ከአባቱ ምሳሌ እንደተማረ ምንም ጥያቄ የለውም። እናቱና አባቱ፣ ይሖዋ ለእስራኤላውያን ወላጆች የሰጠውን መመሪያ በመከተል ለልጃቸው የአምላክን ሕግ አስተምረውት መሆን አለበት። (ዘዳ. 6:6-9) ዳንኤል እንደ አሥርቱ ትእዛዛት ያሉትን የሕጉን መሠረታዊ ክፍሎች ብቻ ሳይሆን ዝርዝር ነገሮችንም ያውቅ ነበር፤ ለምሳሌ እስራኤላውያን መብላት የሚፈቀድላቸውንና የማይፈቀድላቸውን ምግብ ለይቶ ያውቃል። b (ዘሌ. 11:4-8፤ ዳን. 1:8, 11-13) በተጨማሪም ዳንኤል የአምላክን ሕዝቦች ታሪክ ተምሯል፤ እስራኤላውያን የይሖዋን መሥፈርቶች ሳይከተሉ በቀሩበት ወቅት ምን እንደደረሰባቸው ያውቃል። (ዳን. 9:10, 11) ከዚህም ሌላ በሕይወት ዘመኑ ያጋጠሙት ተሞክሮዎች ይሖዋና ኃያላን መላእክቱ እንደሚደግፉት እርግጠኛ እንዲሆን አድርገውታል።—ዳን. 2:19-24፤ 10:12, 18, 19

ዳንኤል በማጥናት፣ በመጸለይ እንዲሁም በይሖዋ በመታመን ድፍረት ማዳበር ችሏል (አንቀጽ 7⁠ን ተመልከት)

7. ዳንኤል ደፋር እንዲሆን የረዳው ሌላው ነገር ምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

7 ዳንኤል የኤርምያስን ትንቢቶች ጨምሮ የአምላክ ነቢያት የጻፏቸውን መልእክቶች ያጠና ነበር። ትንቢቶችን ማጥናቱ አይሁዳውያን በባቢሎን የሚያሳልፉት ረጅም የግዞት ዘመን በቅርቡ እንደሚያበቃ እንዲገነዘብ ረድቶታል። (ዳን. 9:2) ዳንኤል፣ አምላክ የተናገራቸው ትንቢቶች ሲፈጸሙ ማየቱ በይሖዋ ላይ ያለውን እምነት እንዳጠናከረለት ምንም ጥያቄ የለውም። በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት ያላቸው ሰዎች ደግሞ አስደናቂ ድፍረት ማሳየት ይችላሉ። (ከሮም 8:31, 32, 37-39 ጋር አወዳድር።) ከሁሉ በላይ ደግሞ ዳንኤል ወደ ሰማዩ አባቱ አዘውትሮ ይጸልይ ነበር። (ዳን. 6:10) ኃጢአቱን ለይሖዋ ተናዟል፤ እንዲሁም ስሜቱን አውጥቶ ነግሮታል። በተጨማሪም ዳንኤል የይሖዋን እርዳታ ጠይቋል። (ዳን. 9:4, 5, 19) እንደ ማናችንም ሁሉ ዳንኤልም ሰው እንደመሆኑ መጠን ሲወለድ ጀምሮ ደፋር አልነበረም። ከዚህ ይልቅ በማጥናት፣ በመጸለይ እንዲሁም በይሖዋ በመታመን ይህን ባሕርይ ማዳበር ችሏል።

8. ድፍረት ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?

8 ድፍረት ለማዳበር ምን ማድረግ ያስፈልገናል? ወላጆቻችን ደፋር እንድንሆን ሊያበረታቱን ይችሉ ይሆናል፤ ሆኖም ይህን ባሕርይ እንደ ንብረት ሊያወርሱን አይችሉም። ድፍረት ማዳበር አዲስ ክህሎት ከመማር ጋር ይመሳሰላል። አዲስ ክህሎት ማዳበር የሚቻልበት አንዱ መንገድ አስተማሪው የሚያደርገውን ነገር በጥንቃቄ ማየትና ምሳሌውን መኮረጅ ነው። በተመሳሳይም ሌሎች ድፍረት የሚያሳዩት እንዴት እንደሆነ በጥንቃቄ በማየትና የእነሱን ምሳሌ በመኮረጅ ይህን ባሕርይ ማዳበር እንችላለን። ታዲያ ከዳንኤል ምን ትምህርት እናገኛለን? እኛም እንደ እሱ የአምላክን ቃል በደንብ ማወቅ ይኖርብናል። ስሜታችንን አውጥተን ከይሖዋ ጋር አዘውትረን በመነጋገር ከእሱ ጋር የቀረበ ወዳጅነት መመሥረት ያስፈልገናል። በተጨማሪም ይሖዋ እንደሚደግፈን እርግጠኛ በመሆን ሙሉ በሙሉ ልንታመንበት ይገባል። እንዲህ ካደረግን እምነታችን በሚፈተንበት ወቅት ድፍረት ማሳየት እንችላለን።

9. ደፋር መሆናችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

9 ደፋር መሆናችን በተለያዩ መንገዶች ይጠቅመናል። የቤንን ተሞክሮ እስቲ እንመልከት። በጀርመን የሚኖረው ቤን በትምህርት ቤቱ ውስጥ ያሉት ተማሪዎች በሙሉ በዝግመተ ለውጥ የሚያምኑ ከመሆኑም ሌላ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የፍጥረት ዘገባ አፈ ታሪክ እንደሆነ ይሰማቸው ነበር። አንድ ቀን ቤን በክፍሉ ተማሪዎች ፊት ቆሞ ሕይወት የተገኘው በፍጥረት እንደሆነ የሚያምንበትን ምክንያት እንዲያብራራ ተጋበዘ። ቤን ስለ እምነቱ በድፍረት አብራራ። ውጤቱስ ምን ሆነ? ቤን እንዲህ ብሏል፦ “አስተማሪዬ በጥሞና አዳመጠኝ። እንዲሁም ሐሳቡን ለማብራራት ያዘጋጀሁትን ጽሑፍ ኮፒ አድርጎ በክፍሉ ውስጥ ላሉት ተማሪዎች በሙሉ ሰጣቸው።” በቤን ክፍል ውስጥ ያሉት ተማሪዎች ምን ምላሽ ሰጡ? ቤን “ብዙዎቹ በደንብ አዳመጡኝ፤ እንዲሁም እንደሚያደንቁኝ ነገሩኝ” ብሏል። የቤን ተሞክሮ እንደሚያሳየው፣ ደፋር የሆኑ ሰዎች ብዙውን ጊዜ የሌሎችን አክብሮት ያተርፋሉ። በተጨማሪም ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ወደ ይሖዋ እንዲሳቡ ሊረዱ ይችላሉ። በእርግጥም ድፍረት ለማዳበር የሚያነሳሳ በቂ ምክንያት አለን።

የዳንኤልን ታማኝነት ኮርጁ

10. ታማኝነት ምንድን ነው?

10 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ታማኝነት” ወይም “ታማኝ ፍቅር” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል አብዛኛውን ጊዜ የተሠራበት አምላክ ከአገልጋዮቹ ጋር ያለውን ፍቅራዊ ቁርኝት ለማመልከት ነው። ይኸው ቃል በአምላክ አገልጋዮች መካከል ያለውን ፍቅር ለማመልከትም ተሠርቶበታል። (2 ሳሙ. 9:6, 7) ታማኝነታችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠነከረ ሊሄድ ይችላል። የዳንኤል ታማኝነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ የሄደው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

ይሖዋ መልአክ ልኮ የአንበሶቹን አፍ በመዝጋት ዳንኤልን ለታማኝነቱ ክሶታል (አንቀጽ 11⁠ን ተመልከት)

11. ዳንኤል በስተርጅናው ምን ዓይነት የታማኝነት ፈተና አጋጥሞታል? (የሽፋኑን ሥዕል ተመልከት።)

11 ዳንኤል በመላ ሕይወቱ ለይሖዋ ያለው ታማኝነት ተፈትኗል። ሆኖም ከደረሱበት ትላልቅ ፈተናዎች አንዱ ያጋጠመው በ90ዎቹ ዕድሜ ሳለ ነው። በዚህ ወቅት ባቢሎን በሜዶናውያንና በፋርሳውያን ድል ተደርጋ በንጉሥ ዳርዮስ ትተዳደር ነበር። የቤተ መንግሥቱ ባለሥልጣናት ዳንኤልን ይጠሉት ነበር፤ ለሚያመልከው አምላክም አክብሮት አልነበራቸውም። በመሆኑም ዳንኤልን ለማስገደል ሴራ ጠነሰሱ። ‘ዳንኤል ታማኝ የሚሆነው ለአምላኩ ነው ወይስ ለንጉሡ’ የሚለውን ለመፈተን አንድ አዋጅ እንዲታወጅ አደረጉ። ዳንኤል ለንጉሡ ያለውን ታማኝነት ለማረጋገጥና ከሌሎቹ ሰዎች ጋር ለመመሳሰል ማድረግ የሚጠበቅበት ለ30 ቀናት ያህል ወደ ይሖዋ መጸለዩን ማቆም ብቻ ነበር። ዳንኤል አቋሙን ለማላላት ፈቃደኛ አልሆነም። በመሆኑም ወደ አንበሶች ጉድጓድ ተጣለ። ሆኖም ይሖዋ ዳንኤልን ከአንበሶቹ አፍ በመታደግ ለታማኝነቱ ክሶታል። (ዳን. 6:12-15, 20-22) እኛስ ዳንኤል ያሳየውን ዓይነት የማይናወጥ ታማኝነት ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?

12. ዳንኤል ለይሖዋ የማይናወጥ ታማኝነት ያዳበረው እንዴት ነው?

12 ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ታማኝነት የሚመነጨው ከጠንካራ ፍቅር ነው። ዳንኤል ለይሖዋ የማይናወጥ ታማኝነት ሊያዳብር የቻለው በሰማይ ላለው አባቱ ጥልቅ ፍቅር ስለነበረው ነው። ዳንኤል እንዲህ ያለ ፍቅር እንዲያዳብር የረዳው ስለ ይሖዋ ባሕርያትና እነዚህን ባሕርያት ስላሳየበት መንገድ ጊዜ ወስዶ ማሰላሰሉ እንደሆነ ጥያቄ የለውም። (ዳን. 9:4) በተጨማሪም ዳንኤል፣ ይሖዋ ለእሱም ሆነ ለሕዝቡ ስላደረጋቸው መልካም ነገሮች በአመስጋኝነት ያሰላስል ነበር።—ዳን. 2:20-23፤ 9:15, 16

እንደ ዳንኤል ይሖዋን በጥልቅ በመውደድ ለእሱ የማይናወጥ ታማኝነት ማዳበር ትችላለህ (አንቀጽ 13⁠ን ተመልከት)

13. (ሀ) በዛሬው ጊዜ ያሉ ወጣቶች ምን ዓይነት የታማኝነት ፈተና ያጋጥማቸዋል? ምሳሌ ስጥ። (ሥዕሉንም ተመልከት።) (ለ) በቪዲዮው ላይ እንደሚታየው፣ አንድ ሰው ‘የይሖዋ ምሥክሮች ግብረ ሰዶማውያንን ይደግፋሉ?’ ብሎ ቢጠይቀን ምን ዓይነት ምላሽ መስጠት እንችላለን?

13 እንደ ዳንኤል ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ ወጣቶችም ለይሖዋና ለመሥፈርቶቹ ምንም አክብሮት በሌላቸው ሰዎች ተከበዋል። እንዲህ ያሉት ሰዎች ከእነሱ የተለየ አመለካከት ወይም እምነት ያለውን ማንኛውንም ሰው ይጠሉ ይሆናል። እንዲያውም አንዳንዶቹ፣ ወጣቶቻችን ለይሖዋ ያላቸውን ታማኝነት እንዲያላሉ ለማድረግ ከፍተኛ ጫና ያሳድሩባቸው ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ ግራም የተባለ በአውስትራሊያ የሚኖር ወጣት ምን እንዳጋጠመው እንመልከት። ግራም የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ ፈታኝ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር። አስተማሪያቸው ‘አንድ ጓደኛችሁ ግብረ ሰዶማዊ እንደሆነ ቢነግራችሁ ምን ታደርጋላችሁ?’ የሚል ጥያቄ ለተማሪዎቹ አቀረበች። ከዚያም አስተማሪዋ፣ ጓደኛቸው ግብረ ሰዶማዊ መሆኑ ምንም ችግር እንደሌለው የሚሰማቸው ተማሪዎች በክፍሉ አንድ ጎን እንዲቆሙ፣ ሌሎቹ ደግሞ በሌላኛው ጎን እንዲቆሙ ጠየቀች። ግራም እንዲህ ብሏል፦ “ከእኔና ከአንድ ሌላ የይሖዋ ምሥክር በስተቀር የክፍሉ ተማሪዎች በሙሉ ግብረ ሰዶማዊነትን በሚደግፈው ወገን ቆሙ።” ቀጥሎ የተፈጠረው ነገር ግራም ለይሖዋ ያለውን ታማኝነት በእጅጉ ፈትኖታል። እንዲህ ብሏል፦ “አንድ ሰዓት የሚፈጀው ክፍለ ጊዜ እስኪጠናቀቅ ድረስ አስተማሪዋን ጨምሮ ተማሪዎቹ በሙሉ ሰደቡን። በተረጋጋና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ስለ እምነቴ ለማስረዳት ሞከርኩ፤ እነሱ ግን የምናገረውን ለመስማት ፈቃደኞች አልነበሩም።” ግራም እንዲህ ያለ የታማኝነት ፈተና ሲደርስበት ምን ተሰማው? እንዲህ ብሏል፦ “የክፍሌ ተማሪዎች የሰደቡኝ መሆኑ አላስደሰተኝም። ሆኖም ለእምነቴ ጥብቅና በመቆሜና አቋሜን ባለማላላቴ በጣም ተደሰትኩ።” c

14. ለይሖዋ የማይናወጥ ታማኝነት ማዳበር የምንችልበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?

14 እኛም እንደ ዳንኤል ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅር ካዳበርን ለእሱ የማይናወጥ ታማኝነት ሊኖረን ይችላል። ስለ ይሖዋ ባሕርያት በመማር እንዲህ ያለውን ፍቅር ማዳበር እንችላለን። ለምሳሌ እሱ ስለፈጠራቸው ነገሮች ማጥናት እንችላለን። (ሮም 1:20) ለይሖዋ ያለህን ፍቅርና አክብሮት ማሳደግ የምትፈልግ ከሆነ “ንድፍ አውጪ አለው?” በሚለው ዓምድ ሥር የሚወጡትን አጫጭር ርዕሶች ማንበብ ወይም ቪዲዮዎቹን መመልከት ትችላለህ። በተጨማሪም ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው? እንዲሁም የሕይወት አመጣጥ—መልስ የሚያሻቸው አምስት ጥያቄዎች የሚሉትን ብሮሹሮች ማንበብ ትችላለህ። በዴንማርክ የምትኖር ኤስተር የተባለች እህት እነዚህን ጽሑፎች አስመልክቶ እንዲህ ብላለች፦ “ማብራሪያው የሚያረካ ነው። ብሮሹሮቹ ምን ማመን እንዳለባችሁ አይነግሯችሁም። ከዚህ ይልቅ መረጃውን ያስቀምጣሉ፤ ከዚያም የራሳችሁ መደምደሚያ ላይ እንድትደርሱ ይረዷችኋል።” ቀደም ሲል የተጠቀሰው ቤን እንዲህ ብሏል፦ “እነዚህ ጽሑፎች እምነቴን በእጅጉ አጠናክረውልኛል። ሕይወት የተገኘው በፍጥረት እንደሆነ አሳምነውኛል።” እነዚህን ጽሑፎች ካጠናችሁ በኋላ በሚከተለው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ እንደምትስማሙ ምንም ጥያቄ የለውም፦ “ይሖዋ አምላካችን፣ ሁሉንም ነገሮች ስለፈጠርክ . . . ግርማ፣ ክብርና ኃይል ልትቀበል ይገባሃል።”—ራእይ 4:11 d

15. ከይሖዋ ጋር የቀረበ ወዳጅነት መመሥረት የምንችልበት ሌላው መንገድ ምንድን ነው?

15 ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅር ማዳበር የምንችልበት ሌላው መንገድ የልጁን የኢየሱስን ሕይወት መመርመር ነው። በጀርመን የምትኖር ሰሚራ የምትባል ወጣት እህት ይህን አድርጋለች። እንዲህ ብላለች፦ “ስለ ይሖዋ ይበልጥ ማወቅ የቻልኩት በኢየሱስ አማካኝነት ነው።” ሰሚራ ልጅ ሳለች ይሖዋ ስሜት ያለው መሆኑን መረዳት ይከብዳት ነበር። ኢየሱስ ስሜት እንዳለው መረዳት ግን አይከብዳትም። እንዲህ ብላለች፦ “ኢየሱስ በቀላሉ ስለሚቀረብና ልጆችን ስለሚወድ እወደው ነበር።” ስለ ኢየሱስ ይበልጥ በተማረች መጠን ከይሖዋ ጋር ያላት ወዳጅነት እየተጠናከረ መጣ። እንዴት? እንዲህ ብላለች፦ “ኢየሱስ አባቱን ሙሉ በሙሉ እንደሚመስል ቀስ በቀስ እየገባኝ መጣ። ሁለቱ በጣም ይመሳሰላሉ። ይሖዋ ኢየሱስን ወደ ምድር የላከበት አንዱ ምክንያት የሰው ልጆች እሱን ይበልጥ እንዲያውቁት ስለሚፈልግ እንደሆነ ገባኝ።” (ዮሐ. 14:9) ከይሖዋ ጋር ያለህን ወዳጅነት ማጠናከር የምትፈልግ ከሆነ ጊዜ መድበህ ስለ ኢየሱስ የቻልከውን ያህል ለመማር ለምን አትሞክርም? እንዲህ ካደረግክ ለይሖዋ ያለህ ፍቅርና ታማኝነት ያድጋል።

16. ታማኝ መሆናችን የሚጠቅመን እንዴት ነው? (መዝሙር 18:25፤ ሚክያስ 6:8)

16 ታማኝ የሆኑ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ከሌሎች ጋር የቀረበና ዘላቂ ወዳጅነት መመሥረት ይችላሉ። (ሩት 1:14-17) በተጨማሪም ለይሖዋ ታማኝ የሆኑ ሰዎች ውስጣዊ ሰላም ይኖራቸዋል። ለምን? ምክንያቱም ይሖዋ ለእሱ ታማኝ ለሚሆኑ ሰዎች ታማኝ እንደሚሆን ቃል ገብቷል። (መዝሙር 18:25፤ ሚክያስ 6:8ን አንብብ።) እስቲ አስበው፣ ሁሉን ቻይ የሆነው ፈጣሪ እዚህ ግቡ ከማንባለው ከእኛ ጋር ጠንካራ ወዳጅነት ለመመሥረት ፈቃደኛ ነው! ደግሞም ፈተናም ሆነ ተቃውሞ አልፎ ተርፎም ሞት ይህን ወዳጅነት ሊበጥሰው አይችልም። (ዳን. 12:13፤ ሉቃስ 20:37, 38፤ ሮም 8:38, 39) የዳንኤልን ምሳሌ በመከተል ምንጊዜም ለይሖዋ ታማኝ መሆናችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!

ከዳንኤል መማራችሁን ቀጥሉ

17-18. ከዳንኤል ሌላስ ምን ትምህርት እናገኛለን?

17 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተመለከትነው ከዳንኤል ባሕርያት መካከል ሁለቱን ብቻ ነው። ሆኖም ከዳንኤል የምናገኛቸው ሌሎች ብዙ ትምህርቶች አሉ። ለምሳሌ ይሖዋ ለዳንኤል ራእዮችንና ሕልሞችን አሳይቶታል፤ እንዲሁም ትንቢታዊ መልእክቶችን የመተርጎም ችሎታ ሰጥቶታል። ከእነዚህ ትንቢቶች ብዙዎቹ ተፈጽመዋል። ሌሎቹ ትንቢቶች ደግሞ በምድር ላይ የሚኖረውን እያንዳንዱን ሰው የሚነኩ ወደፊት የሚፈጸሙ ክንውኖችን በተመለከተ ጠቃሚ መረጃ ይሰጡናል።

18 በሚቀጥለው ርዕስ ላይ፣ ዳንኤል ከጻፋቸው ትንቢቶች መካከል ሁለቱን እንመረምራለን። ወጣቶችም ሆንን አረጋውያን እነዚህን ትንቢቶች መረዳታችን በአሁኑ ጊዜ የጥበብ ውሳኔዎችን ለማድረግ ይረዳናል። በተጨማሪም እነዚህ ትንቢቶች ከፊታችን የሚጠብቁንን ፈተናዎች ለመቋቋም ዝግጁ እንድንሆን ድፍረታችንን እና ታማኝነታችንን ያጠናክሩልናል።

መዝሙር 119 ጠንካራ እምነት ሊኖረን ይገባል

a በዛሬው ጊዜ ያሉ ወጣት የይሖዋ አገልጋዮች ድፍረታቸውንና ለይሖዋ ያላቸውን ታማኝነት የሚፈትኑ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል። በፍጥረት በማመናቸው የተነሳ አብረዋቸው የሚማሩ ልጆች ያሾፉባቸው ይሆናል። ወይም ደግሞ አምላክን በማገልገላቸውና በእሱ መሥፈርቶች በመመራታቸው የተነሳ እኩዮቻቸው ይሳለቁባቸው ይሆናል። ያም ቢሆን፣ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንደምንመለከተው የነቢዩ ዳንኤልን ምሳሌ በመከተል ይሖዋን በድፍረትና በታማኝነት የሚያገለግሉ ሁሉ እውነተኛ ጥበብ አላቸው።

b ዳንኤል የባቢሎናውያንን ምግብ ለመብላት ፈቃደኛ ያልሆነው በሚከተሉት ሦስት ምክንያቶች የተነሳ ሊሆን ይችላል፦ (1) የሚበሉት በሕጉ የተከለከሉትን እንስሳት ሥጋ ሊሆን ይችላል። (ዘዳ. 14:7, 8) (2) ሥጋው በተገቢው መንገድ ደሙ ያልፈሰሰ ሊሆን ይችላል። (ዘሌ. 17:10-12) (3) ምግቡን መብላቱ የጣዖት አምልኮ ተካፋይ እንደሆነ ሊያስቆጥረው ይችላል።—ከዘሌዋውያን 7:15፤ 1 ቆሮንቶስ 10:18, 21, 22 ጋር አወዳድር።

c የእውነተኛ ጽድቅ ውጤት ሰላም . . . ይሆናል የሚለውን ቪዲዮ ከ​jw.org ላይ ተመልከት።

d ለይሖዋ ያለህን ፍቅር ለማጠናከር ስለ ይሖዋ ባሕርያትና ስለ ማንነቱ በጥልቀት የሚያብራራውን ወደ ይሖዋ ቅረብ የተባለውን መጽሐፍ ማጥናትም ትችላለህ።