የአንባቢያን ጥያቄዎች
በሰኔ 2020 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣው “ስምህ ይቀደስ” የሚለው ርዕስ የይሖዋን ስምና ሉዓላዊነቱን አስመልክቶ በነበረን ግንዛቤ ላይ የተደረገውን ማስተካከያ የሚያብራራው እንዴት ነው?
በዚያ ርዕስ ላይ፣ ማሰብ የሚችሉ ፍጥረታትን በሙሉ የሚመለከተው ጉዳይ አንድ ብቻ ይኸውም የይሖዋ ታላቅ ስም መቀደስ እንደሆነ ተመልክተን ነበር። የይሖዋን ሉዓላዊነት ማለትም አገዛዙ ከሁሉ የተሻለ መሆኑን በተመለከተ የተነሳው ጥያቄ የዚህ ወሳኝ ጉዳይ አንድ ገጽታ ነው። የሰዎችን ንጹሕ አቋም ጠባቂነት በተመለከተ የተነሳው ጥያቄም የዚህ ወሳኝ ጉዳይ ሌላ ገጽታ ነው።
ሁላችንንም የሚያሳስበን ዋነኛው ጉዳይ የይሖዋ ስምና የስሙ መቀደስ እንደሆነ ጎላ አድርገን መግለጽ የጀመርነው ለምንድን ነው? ሦስት ምክንያቶችን እስቲ እንመልከት።
አንደኛ፣ በኤደን ገነት ውስጥ ሰይጣን ጥቃት የሰነዘረው በይሖዋ ስም ላይ ነው። ሰይጣን ለሔዋን ያቀረበላት መሠሪ ጥያቄ ይሖዋ በተገዢዎቹ ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ ገደብ የሚጥል ንፉግ አምላክ ነው የሚል አንድምታ አለው። ከዚያም ሰይጣን ከይሖዋ ቃል ጋር በቀጥታ የሚቃረን ነገር ተናገረ፤ እንዲህ ማድረጉ አምላክን ‘ውሸታም’ እንዳለው ሊቆጠር ይችላል። በዚህ መንገድ የይሖዋን ስም አጥፍቷል። በመሆኑም “ዲያብሎስ” ማለትም “ስም አጥፊ” ሆነ። (ዮሐ. 8:44) ሔዋን የሰይጣንን ውሸቶች ስላመነች የአምላክን ትእዛዝ በመጣስ በሉዓላዊነቱ ላይ ዓመፀች። (ዘፍ. 3:1-6) እስካሁን ድረስ ሰይጣን የይሖዋን ማንነት አስመልክቶ የተለያዩ ውሸቶችን በማስፋፋት ስሙን እያጠፋው ነው። እንዲህ ያሉ ውሸቶችን የሚያምኑ ሰዎች የይሖዋን ትእዛዝ የመጣሳቸው አጋጣሚ ሰፊ ነው። በመሆኑም በይሖዋ ሕዝቦች ዓይን ከሁሉ የከፋው ግፍ በይሖዋ ስም ላይ የተሰነዘረው ነቀፋ ነው። በዓለም ላይ ላለው መከራና ክፋት ዋነኛው መንስኤም እሱ ነው።
ሁለተኛ፣ ፍጥረታቱን ሁሉ ለመጥቀም ሲል ይሖዋ ስሙን ከነቀፋ ነፃ ያደርጋል። ይሖዋ ከምንም በላይ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ይህ ነው። “ታላቅ ስሜን በእርግጥ እቀድሰዋለሁ” ያለው ለዚህ ነው። (ሕዝ. 36:23) በተጨማሪም ኢየሱስ “ስምህ ይቀደስ” በማለት ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች በሙሉ በጸሎታቸው ውስጥ ቅድሚያ ሊሰጡት የሚገባው ነገር ምን እንደሆነ ግልጽ አድርጓል። (ማቴ. 6:9) መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋን ስም የማክበርን አስፈላጊነት በተደጋጋሚ ጎላ አድርጎ ይገልጻል። ጥቂት ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት፦ “ለስሙ የሚገባውን ክብር ለይሖዋ ስጡ።” (1 ዜና 16:29፤ መዝ. 96:8) “ለክብራማ ስሙ የውዳሴ መዝሙር ዘምሩ።” (መዝ. 66:2) “ስምህን . . . ለዘላለም ከፍ ከፍ አደርጋለሁ።” (መዝ. 86:12) ይሖዋ ከሰማይ በቀጥታ ከተናገረባቸው ጊዜያት አንዱ፣ ኢየሱስ በኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ውስጥ “አባት ሆይ፣ ስምህን አክብረው” ባለበት ወቅት ነው። ይሖዋም “ስሜን አክብሬዋለሁ፤ ደግሞም አከብረዋለሁ” በማለት መለሰ።—ዮሐ. 12:28 a
ሦስተኛ፣ የይሖዋ ዘላለማዊ ዓላማ ከስሙ ጋር የተያያዘ ነው። እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ሲጠናቀቅ ከሚኖረው የመጨረሻ ፈተና በኋላ ምን ይከሰታል? ወሳኝ ጉዳይ ከሆነው ከይሖዋ ስም መቀደስ ጋር በተያያዘ የማሰብ ችሎታ ባላቸው ፍጥረታት መካከል ክፍፍል ይኖራል? ይህን ጥያቄ ለመመለስ የዚህን ጉዳይ ሁለት ተያያዥ ገጽታዎች ማለትም ከሰው ልጆች ንጹሕ አቋም ጠባቂነት እና ከጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት ጋር በተያያዘ የተነሱትን ጥያቄዎች መለስ ብለን እንመልከት። ታማኝነታቸውን ያስመሠከሩ ሰዎች ንጹሕ አቋማቸው ከዚያ በኋላ ይፈተናል? በጭራሽ። ሙሉ በሙሉ ተፈትነው
ፍጹም ሆነዋል። ከፊታቸው የዘላለም ሕይወት ይጠብቃቸዋል። ጽንፈ ዓለማዊው የሉዓላዊነት ጥያቄ የማሰብ ችሎታ ባላቸው ፍጥረታት መካከል የውይይት ርዕሰ ጉዳይ አልፎ ተርፎም የክፍፍል መንስኤ ይሆናል? በፍጹም። በዚህ ወቅት የይሖዋ አገዛዝ ትክክለኛና ከሁሉ የተሻለ መሆኑ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተረጋግጧል። የይሖዋን ስም በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል?በዚያ ወቅት የይሖዋ ስም ሙሉ በሙሉ ይቀደሳል፤ ሙሉ በሙሉ ከነቀፋ ነፃ ይሆናል። ያም ቢሆን በሰማይም ሆነ በምድር ያሉ ታማኝ ፍጥረታት በሙሉ ለይሖዋ ስም ትኩረት መስጠታቸውን ይቀጥላሉ። ለምን? ይሖዋ የሚያከናውናቸውን አስደናቂ ነገሮች ማየታቸውን ስለሚቀጥሉ ነው። እስቲ አስበው፦ ኢየሱስ ሥልጣንን ሁሉ በትሕትና ለይሖዋ ስለሚያስረክብ አምላክ “ለሁሉም ሁሉንም ነገር” ይሆናል። (1 ቆሮ. 15:28) ከዚያ በኋላ በምድር ላይ ያሉ ሰዎች “የአምላክ ልጆች የሚያገኙት ዓይነት ክብራማ ነፃነት” ያገኛሉ። (ሮም 8:21) ይሖዋም በሰማይም ሆነ በምድር ያሉ የማሰብ ችሎታ ያላቸውን ፍጥረታት በሙሉ አንድነት ባለው ትልቅ ቤተሰብ ውስጥ ለመሰብሰብ ያለውን ዘላለማዊ ዓላማ በስተ መጨረሻ ያሳካል።—ኤፌ. 1:10
በሰማይም ሆነ በምድር ያሉት የይሖዋ ቤተሰብ አባላት እነዚህን ክንውኖች ሲመለከቱ ምን ይሰማቸዋል? ልባችን ፈንቅሎን የይሖዋን ክብራማ ስም ለማወደስ እንደምንነሳሳ ምንም ጥያቄ የለውም። መዝሙራዊው ዳዊት በመንፈስ ተመርቶ “ይሖዋ ይወደስ። ክብራማ ስሙ ለዘላለም ይወደስ” በማለት ጽፏል። (መዝ. 72:18, 19) ይህን ለማድረግ የሚያነሳሱ አዳዲስና አስደሳች ምክንያቶችን ለዘላለም ማግኘታችንን እንቀጥላለን።
የይሖዋ ስም መላውን ማንነቱን ይወክላል። በመሆኑም ስሙ በዋነኝነት የሚያስታውሰን ፍቅሩን ነው። (1 ዮሐ. 4:8) ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ እንደፈጠረን፣ በፍቅር ተነሳስቶ ቤዛዊ መሥዋዕቱን እንዳዘጋጀልን እንዲሁም በፍቅር ተነሳስቶ አገዛዙ ከሁሉ የተሻለ መሆኑን እንዳሳየን ምንጊዜም እናስታውሳለን። ግን ይህ ብቻ ሳይሆን የይሖዋን ወደር የለሽ ፍቅር ማጣጣማችንን እንቀጥላለን። ለዘላለም ወደ አባታችን ይበልጥ ለመቅረብ እንዲሁም ለክብራማው ስሙ የውዳሴ መዝሙር ለመዘመር እንነሳሳለን።—መዝ. 73:28