በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 34

መዝሙር 107 መለኮታዊው የፍቅር መንገድ

ለኃጢአተኞች ፍቅርና ምሕረት ማሳየት

ለኃጢአተኞች ፍቅርና ምሕረት ማሳየት

“አምላክ በደግነቱ ወደ ንስሐ ሊመራህ እየሞከረ [ነው]።”—ሮም 2:4

ዓላማ

ሽማግሌዎች ከባድ ኃጢአት የፈጸሙ ክርስቲያኖችን ለመርዳት የሚሞክሩት እንዴት ነው?

1. ከባድ ኃጢአት የፈጸሙ አንዳንድ ክርስቲያኖች ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?

 በቆሮንቶስ ባለው ጉባኤ ውስጥ ከባድ ጥፋት በተፈጸመበት ወቅት ጳውሎስ ጉዳዩን የያዘው እንዴት እንደሆነ ባለፈው ርዕስ ውስጥ ተመልክተናል። ኃጢአተኛው ንስሐ ባለመግባቱ ከጉባኤው መወገድ ነበረበት። ይሁንና የጭብጡ ጥቅስ እንደሚያሳየው፣ ከባድ ኃጢአት የፈጸሙ አንዳንድ ክርስቲያኖች የተደረገላቸውን እርዳታ ተቀብለው ንስሐ ሊገቡ ይችላሉ። (ሮም 2:4) ታዲያ ሽማግሌዎች ንስሐ እንዲገቡ ሊረዷቸው የሚችሉት እንዴት ነው?

2-3. አንድ የእምነት አጋራችን ከባድ ኃጢአት እንደፈጸመ ብናውቅ ምን ማድረግ ይኖርብናል? ለምንስ?

2 ሽማግሌዎች እርዳታ ማበርከት እንዲችሉ ስለ ጉዳዩ ማወቅ አለባቸው። ስለዚህ አንድ የእምነት አጋራችን ከጉባኤው ሊያስወግድ የሚችል ከባድ ኃጢአት እንደፈጸመ ብናውቅ ምን ማድረግ ይኖርብናል? ጥፋት የሠራው ግለሰብ የሽማግሌዎችን እርዳታ እንዲጠይቅ ልናበረታታው ይገባል።—ኢሳ. 1:18፤ ሥራ 20:28፤ 1 ጴጥ. 5:2

3 ይሁንና ጥፋት የሠራው ግለሰብ ሽማግሌዎችን ለማነጋገር ፈቃደኛ ባይሆንስ? ሁኔታው እንደዚያ ከሆነ እኛ ራሳችን ሽማግሌዎችን በማነጋገር ግለሰቡ የሚያስፈልገውን እርዳታ እንዲያገኝ ማድረግ ይኖርብናል። ይህ ፍቅር የሚንጸባረቅበት እርምጃ ነው። ምክንያቱም ወንድማችንን ወይም እህታችንን ማጣት አንፈልግም። ግለሰቡ ኃጢአት መፈጸሙን ከቀጠለ ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና የባሰ ያበላሻል። በተጨማሪም የጉባኤውን መልካም ስም ሊያጎድፍ ይችላል። በመሆኑም ለይሖዋና ጥፋት ለሠራው ግለሰብ ባለን ፍቅር ተነሳስተን በድፍረት እርምጃ እንወስዳለን።—መዝ. 27:14

ሽማግሌዎች ከባድ ኃጢአት የፈጸሙ ክርስቲያኖችን የሚረዱት እንዴት ነው?

4. ሽማግሌዎች ከባድ ኃጢአት ከፈጸመ ክርስቲያን ጋር በሚነጋገሩበት ወቅት ግባቸው ምንድን ነው?

4 በጉባኤ ውስጥ ያለ አንድ ክርስቲያን ከባድ ኃጢአት በሚፈጽምበት ጊዜ የሽማግሌዎች አካል ብቃት ያላቸውን ሦስት ሽማግሌዎች በመምረጥ ኮሚቴ ያቋቁማል። a እነዚህ ወንድሞች ትሑትና ልካቸውን የሚያውቁ መሆን አለባቸው። ኃጢአተኛው ንስሐ እንዲገባ ለመርዳት ቢሞክሩም ግለሰቡ ለውጥ እንዲያደርግ ማስገደድ እንደማይችሉ አምነው ይቀበላሉ። (ዘዳ. 30:19) ሽማግሌዎች፣ እንደ ንጉሥ ዳዊት በጎ ምላሽ የሚሰጡት ሁሉም ኃጢአተኞች እንዳልሆኑ ይገነዘባሉ። (2 ሳሙ. 12:13) ጥፋት የሠሩ አንዳንድ ሰዎች የይሖዋን ምክር ችላ ለማለት ሊመርጡ ይችላሉ። (ዘፍ. 4:6-8) ያም ቢሆን የሽማግሌዎቹ ግብ፣ የሚቻል እስከሆነ ድረስ ኃጢአተኛውን ወደ ንስሐ መምራት ነው። ታዲያ ጥፋት የሠራውን ግለሰብ በሚያነጋግሩበት ወቅት የትኞቹ መሠረታዊ ሥርዓቶች ሊረዷቸው ይችላሉ?

5. ሽማግሌዎች ኃጢአተኛውን በሚያነጋግሩበት ወቅት የትኛውን ምክር በአእምሯቸው ይይዛሉ? (2 ጢሞቴዎስ 2:24-26) (ሥዕሉንም ተመልከት።)

5 ሽማግሌዎች ኃጢአተኛውን ከመንጋው እንደጠፋ ውድ በግ አድርገው ይመለከቱታል። (ሉቃስ 15:4, 6) በመሆኑም ግለሰቡን በሚያነጋግሩበት ወቅት በአነጋገራቸው፣ በአመለካከታቸውም ሆነ በአቀራረባቸው ሻካራ አይሆኑበትም። በተጨማሪም ይህን ውይይት እንዲሁ መመሪያ ለመከተል ወይም መረጃ ለማጣራት ያህል እንደሚከተሉት ሂደት አድርገው አይቆጥሩትም። ከዚህ ይልቅ በ2 ጢሞቴዎስ 2:24-26 ላይ የተጠቀሱትን ባሕርያት ያንጸባርቃሉ። (ጥቅሱን አንብብ።) ሽማግሌዎች የኃጢአተኛውን ልብ ለመንካት ጥረት በሚያደርጉበት ወቅት ደግነትና ገርነት ያሳያሉ።

በጥንት ዘመን እንደነበሩት እረኞች ሁሉ ሽማግሌዎች የጠፋውን በግ ለመርዳት ጥረት ያደርጋሉ (አንቀጽ 5⁠ን ተመልከት)


6. ሽማግሌዎች ጥፋት የሠራውን ግለሰብ ከማነጋገራቸው በፊት የራሳቸውን ልብ የሚያዘጋጁት እንዴት ነው? (ሮም 2:4)

6 ሽማግሌዎች የራሳቸውን ልብ ያዘጋጃሉ። ኃጢአተኛውን በሚይዙበት መንገድ በሙሉ ይሖዋን ለመምሰል ጥረት ያደርጋሉ። ጳውሎስ “አምላክ በደግነቱ ወደ ንስሐ ሊመራህ እየሞከረ [ነው]” በማለት የተናገረውን ሐሳብ በአእምሯቸው ይይዛሉ። (ሮም 2:4ን አንብብ።) ሽማግሌዎች ዋነኛ ሥራቸው እረኝነት እንደሆነ እንዲሁም የክርስቶስን አመራር መከተል እንደሚጠበቅባቸው ማስታወስ ይኖርባቸዋል። (ኢሳ. 11:3, 4፤ ማቴ. 18:18-20) የኮሚቴው አባላት ጥፋት የሠራውን ግለሰብ ከማነጋገራቸው በፊት ግባቸውን በአእምሯቸው ይዘው ይጸልያሉ፤ ግባቸው ኃጢአተኛውን ወደ ንስሐ መምራት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስና በጽሑፎቻችን ላይ ምርምር ያደርጋሉ፤ ማስተዋል ለማግኘትም ይጸልያሉ። በግለሰቡ አስተሳሰብ፣ ዝንባሌ ወይም ምግባር ላይ ተጽዕኖ ያሳደሩት የትኞቹ ነገሮች እንደሆኑ ከግምት ለማስገባት ይሞክራሉ።—ምሳሌ 20:5

7-8. ሽማግሌዎች ኃጢአት ከሠራው ግለሰብ ጋር በሚነጋገሩበት ወቅት የይሖዋን ትዕግሥት መኮረጅ የሚችሉት እንዴት ነው?

7 ሽማግሌዎች የይሖዋን ትዕግሥት ይኮርጃሉ። ይሖዋ በጥንት ዘመን ኃጢአት የሠሩ ሰዎችን የያዘበትን መንገድ ከግምት ያስገባሉ። ለምሳሌ ይሖዋ ቃየንን በትዕግሥት አነጋግሮታል፤ ኃጢአት ስለሚያስከትለው ውጤት አስጠንቅቆታል፤ እንዲሁም መልካም ካደረገ የእሱን ሞገስ ማግኘት እንደሚችል ነግሮታል። (ዘፍ. 4:6, 7) ይሖዋ በነቢዩ ናታን አማካኝነት ለዳዊት እርማት ሰጥቶታል፤ ናታንም የንጉሡን ልብ የሚነካ ምሳሌ ተጠቅሟል። (2 ሳሙ. 12:1-7) በተጨማሪም ይሖዋ ለዓመፀኞቹ እስራኤላውያን ‘ደግሞ ደጋግሞ’ ነቢያትን ‘መላኩን ቀጥሏል።’ (ኤር. 7:24, 25) ለሕዝቦቹ የእርዳታ እጁን የዘረጋላቸው ንስሐ ከገቡ በኋላ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ቅድሚያውን ወስዶ ንስሐ እንዲገቡ አበረታቷቸዋል።

8 ሽማግሌዎች ከባድ ኃጢአት የፈጸሙ ክርስቲያኖችን ለመርዳት በሚሞክሩበት ወቅት የይሖዋን ምሳሌ ይከተላሉ። ሁለተኛ ጢሞቴዎስ 4:2 እንደሚለው ችግር ውስጥ የገቡ የእምነት አጋሮቻቸውን በሚያነጋግሩበት ጊዜ “ብዙ ትዕግሥት” ያሳያሉ። ለዚህ ጥቅስ የተዘጋጀው ለጥናት የሚረዳ መረጃ እንዲህ ስላለው ሽማግሌ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “ምንጊዜም ራሱን መቆጣጠር እንዲሁም [ኃጢአተኛው] ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ እንዲነሳሳ በትዕግሥት መርዳት ይኖርበታል። [ሽማግሌው] ከተማረረ ወይም ከተበሳጨ [ኃጢአተኛውን] የባሰ ሊያርቀው አልፎ ተርፎም ሊያሰናክለው ይችላል።”

9-10. ሽማግሌዎች ኃጢአተኛው አካሄዱን መለስ ብሎ እንዲመረምር ሊረዱት የሚችሉት እንዴት ነው?

9 ሽማግሌዎች ግለሰቡን ወደ ኃጢአት የመራው ምን እንደሆነ ለማወቅ ጥረት ያደርጋሉ። ለምሳሌ ግለሰቡ የግል ጥናቱን ወይም አገልግሎቱን ችላ በማለቱ የተነሳ ቀስ በቀስ መንፈሳዊነቱ ተዳክሞ ይሆን? አዘውትሮ መጸለዩን አቁሞ ወይም የጸሎቱን ጥልቀት ቀንሶ ይሆን? መጥፎ ምኞቶችን ለማሸነፍ መታገሉን አቁሞ ይሆን? በጓደኛ ወይም በመዝናኛ ረገድ ጥበብ የጎደለው ምርጫ አድርጎ ይሆን? እንዲህ ያለ ምርጫ ማድረጉ በልቡ ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሯል? ውሳኔዎቹና ድርጊቶቹ በአባቱ በይሖዋ ላይ ምን ስሜት እንደፈጠሩበት ገብቶታል?

10 ሽማግሌዎች ሳያስፈልግ በግለሰቡ የግል ሕይወት ውስጥ ሳይገቡ አስፈላጊ ጥያቄዎችን በደግነት በመጠየቅ ስሜቱን አውጥቶ እንዲናገርና አካሄዱን መለስ ብሎ እንዲመረምር ሊረዱት ይችላሉ። (ምሳሌ 20:5) በተጨማሪም ግለሰቡ የፈጸመው ድርጊት ምን ያህል ስህተት እንደሆነ እንዲገነዘብ ለመርዳት እንደ ነቢዩ ናታን ጥሩ ምሳሌዎችን መጠቀም ይችላሉ። ምናልባት በመጀመሪያ ውይይታቸው ወቅት ግለሰቡ በድርጊቱ ከልቡ ማዘን ሊጀምር ይችላል። እንዲያውም ንስሐ ሊገባ ይችላል።

11. ኢየሱስ ኃጢአተኞችን የያዘው እንዴት ነው?

11 ሽማግሌዎች ኢየሱስን ለመምሰል ጥረት ያደርጋሉ። ኢየሱስ የጠርሴሱን ሳኦልን “ሳኦል፣ ሳኦል ለምን ታሳድደኛለህ?” በማለት ራሱን እንዲመረምር የሚያደርግ ጥያቄ ጠይቆታል። በዚህ መንገድ አካሄዱ የተሳሳተ መሆኑን እንዲገነዘብ ረድቶታል። (ሥራ 9:3-6) በተጨማሪም ኢየሱስ “ያቺን ሴት ኤልዛቤልን” አስመልክቶ ሲናገር “ንስሐ እንድትገባ ጊዜ ሰጠኋት” ብሏል።—ራእይ 2:20, 21

12-13. ሽማግሌዎች ለኃጢአተኛው ንስሐ የሚገባበት ጊዜ ሊሰጡት የሚችሉት እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

12 ሽማግሌዎች የኢየሱስን ምሳሌ ስለሚከተሉ ጥፋት የሠራው ግለሰብ ንስሐ አይገባም ብለው ለመደምደም አይቸኩሉም። አንዳንዶች ኮሚቴው ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያነጋግራቸው ንስሐ ሊገቡ ይችላሉ፤ ሌሎች ግን ተጨማሪ ጊዜ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። በመሆኑም ሽማግሌዎች ኃጢአተኛውን ከአንድ ጊዜ በላይ ለማነጋገር ዝግጅት ሊያደርጉ ይችላሉ። ኃጢአተኛው ከኮሚቴው ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ከተነጋገረ በኋላ የተባለውን ነገር አስመልክቶ በቁም ነገር ማሰብ ሊጀምር ይችላል። በትሕትና ወደ ይሖዋ ሊጸልይ ይችላል። (መዝ. 32:5፤ 38:18) በዚህም የተነሳ በቀጣዩ ጊዜ ሲያነጋግሩት በመጀመሪያው ውይይታቸው ወቅት ካሳየው የተለየ መንፈስ ሊያሳይ ይችላል።

13 ሽማግሌዎች ኃጢአተኛውን ወደ ንስሐ ለመምራት ጥረት በሚያደርጉበት ጊዜ ስሜቱን ይረዱለታል፤ ደግነትም ያሳዩታል። ይሖዋ ጥረታቸውን እንዲባርክላቸው ይጸልያሉ፤ እንዲሁም ኃጢአተኛው ክርስቲያን ወደ ልቦናው እንደሚመለስና ንስሐ እንደሚገባ ተስፋ ያደርጋሉ።—2 ጢሞ. 2:25, 26

ሽማግሌዎች ኃጢአት የፈጸመው ክርስቲያን ንስሐ እንዲገባ ጊዜ ለመስጠት ከአንድ ጊዜ በላይ ሊያነጋግሩት ይችላሉ (አንቀጽ 12⁠ን ተመልከት)


14. አንድ ኃጢአተኛ ንስሐ በሚገባበት ጊዜ ለዚህ ሊመሰገን የሚገባው ማን ነው? ለምንስ?

14 ኃጢአተኛው ንስሐ ከገባ ይህ በጣም የሚያስደስት ነገር ነው! (ሉቃስ 15:7, 10) ይሁንና ለዚህ ሊመሰገን የሚገባው ማን ነው? ሽማግሌዎች ናቸው? ጳውሎስ ስለ ኃጢአተኞች ሲናገር “ምናልባትም አምላክ . . . ለንስሐ ያበቃቸው ይሆናል” እንዳለ ልብ በል። (2 ጢሞ. 2:25) ለዚህ ጥቅስ የተዘጋጀው ለጥናት የሚረዳ መረጃ እንዲህ ይላል፦ “እንዲህ ላለው የአስተሳሰብ ለውጥ ሊመሰገን የሚገባው ሰው ሳይሆን መንገድ ስቶ የወጣው ክርስቲያን ይህን ወሳኝ ለውጥ እንዲያደርግ የረዳው ይሖዋ ነው። ቀጥሎ ጳውሎስ እንዲህ ያለው ንስሐ የሚያስገኛቸውን አንዳንድ ግሩም ውጤቶች ጠቅሷል፦ ኃጢአተኛው ይበልጥ ትክክለኛ የሆነ የእውነት እውቀት እንዲያገኝ፣ ወደ ልቦናው እንዲመለስ እንዲሁም ከሰይጣን ወጥመድ እንዲያመልጥ ይረዳዋል።—2ጢሞ 2:26

15. ሽማግሌዎች ንስሐ የገባውን ኃጢአተኛ በቀጣይነት መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?

15 ጥፋት የሠራ ሰው ንስሐ ከገባ በኋላ ኮሚቴው እረኝነት እንዲደረግለት ዝግጅት ያደርጋል፤ ይህም ግለሰቡ ከሰይጣን ወጥመዶች ጋር መታገሉን እንዲቀጥል እንዲሁም ‘እግሩ ዘወትር ቀና በሆነ መንገድ እንዲጓዝ’ ይረዳዋል። (ዕብ. 12:12, 13) እርግጥ ነው፣ ሽማግሌዎች ግለሰቡ የሠራውን ኃጢአት ለማንም በዝርዝር አይናገሩም። ይሁንና ለጉባኤው ምን ዓይነት መረጃ መስጠት ሊያስፈልግ ይችላል?

“በሁሉ ፊት ውቀሳቸው”

16. በ1 ጢሞቴዎስ 5:20 ላይ ጳውሎስ “በሁሉ ፊት” ሲል ምን ማለቱ ነበር?

16 አንደኛ ጢሞቴዎስ 5:20ን አንብብ። ጳውሎስ በሽምግልና ለሚያገለግለው ለጢሞቴዎስ “ኃጢአት የመሥራት ልማድ ያላቸውን ሰዎች” በተመለከተ እነዚህን ቃላት ጽፎለታል። ይሁንና ይህን ሲል ምን ማለቱ ነበር? “በሁሉ ፊት” ሲል መላውን ጉባኤ ማመልከቱ ላይሆን ይችላል። ከዚህ ይልቅ ስለ ኃጢአቱ የሚያውቁትን የተወሰኑ ክርስቲያኖች ማመልከቱ ነው። የዓይን ምሥክሮች ወይም ግለሰቡ ስለ ኃጢአቱ የነገራቸው ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ሽማግሌዎች ጉዳዩ እንደታየ እንዲሁም ኃጢአተኛው እርማት እንደተሰጠው ለእነሱ ብቻ ይነግሯቸዋል።

17. አንድ ከባድ ኃጢአት በጉባኤው ውስጥ በስፋት የሚታወቅ ወይም መታወቁ የማይቀር ከሆነ ምን ማስታወቂያ ይነገራል? ለምንስ?

17 አንዳንድ ጊዜ የተፈጸመው ኃጢአት በጉባኤው ውስጥ በስፋት የሚታወቅ ወይም መታወቁ የማይቀር ሊሆን ይችላል። ሁኔታው እንደዚያ ከሆነ “በሁሉ ፊት” የሚለው መላውን ጉባኤ ያካትታል። ስለዚህ አንድ ሽማግሌ፣ ያ ወንድም ወይም ያቺ እህት ወቀሳ እንደተሰጣቸው የሚገልጽ ማስታወቂያ ለጉባኤው ይናገራል። ለምን? ጳውሎስ እንዳለው በኃጢአት እንዳይወድቁ “ለሌሎቹ ማስጠንቀቂያ እንዲሆን” ነው።

18. ለአካለ መጠን ካልደረሱ የተጠመቁ ልጆች ጋር በተያያዘ ሽማግሌዎች ጉዳዩን የሚይዙት እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

18 ከ18 ዓመት በታች የሆነ የተጠመቀ ልጅ ከባድ ኃጢአት ቢፈጽምስ? የሽማግሌዎች አካል፣ ሁለት ሽማግሌዎች ልጁን ከክርስቲያን ወላጆቹ b ጋር እንዲያነጋግሩት ዝግጅት ያደርጋል። ሽማግሌዎቹ፣ ወላጆቹ ልጁን ወደ ንስሐ ለመምራት የትኞቹን እርምጃዎች እንደወሰዱ ለማወቅ ጥረት ያደርጋሉ። ልጁ ጥሩ ዝንባሌ ካለውና የወላጆቹን እርዳታ እየተቀበለ ከሆነ ሁለቱ ሽማግሌዎች ሌላ ተጨማሪ እርምጃ መውሰድ እንደማያስፈልግ ሊወስኑ ይችላሉ። ደግሞም ለልጆች ፍቅራዊ እርማት መስጠት አምላክ ለወላጆች የሰጠው ኃላፊነት ነው። (ዘዳ. 6:6, 7፤ ምሳሌ 6:20፤ 22:6፤ ኤፌ. 6:2-4) ከዚያ በኋላ ሽማግሌዎቹ ለአካለ መጠን ያልደረሰው ልጅ አስፈላጊውን እርዳታ እያገኘ መሆኑን ለማረጋገጥ አልፎ አልፎ ወላጆቹን በመጠየቅ ያጣራሉ። ይሁንና አንድ የተጠመቀ ልጅ ንስሐ ባይገባና የኃጢአት ጎዳና መከተሉን ቢቀጥልስ? ሁኔታው እንደዚያ ከሆነ፣ የሽማግሌዎች ኮሚቴ ከክርስቲያን ወላጆቹ ጋር አብሮ ያነጋግረዋል።

ለአካለ መጠን ያልደረሰ ልጅ ከባድ ኃጢአት በሚፈጽምበት ጊዜ ሁለት ሽማግሌዎች ልጁን ከክርስቲያን ወላጆቹ ጋር ያነጋግሩታል (አንቀጽ 18⁠ን ተመልከት)


‘ይሖዋ እጅግ አፍቃሪና መሐሪ ነው’

19. ሽማግሌዎች ጥፋት የሠሩ ሰዎችን በሚይዙበት መንገድ ይሖዋን ለመምሰል ጥረት የሚያደርጉት እንዴት ነው?

19 በኮሚቴ ውስጥ የሚያገለግሉ ሽማግሌዎች የጉባኤውን ንጽሕና እንዲያስጠብቁ ይሖዋ ይጠብቅባቸዋል። (1 ቆሮ. 5:7) የሚቻል ከሆነ ደግሞ ጥፋት የሠሩት ሰዎች ንስሐ እንዲገቡ ይፈልጋሉ። ለዚህም ሲባል ሽማግሌዎች አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ ጥረት ያደርጋሉ። ለምን? “እጅግ አፍቃሪና መሐሪ” የሆነውን ይሖዋን መምሰል ስለሚፈልጉ ነው። (ያዕ. 5:11) ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ያለውን መንፈስ ያሳየው እንዴት እንደሆነ ልብ በል። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የተወደዳችሁ ልጆቼ፣ እነዚህን ነገሮች የምጽፍላችሁ ኃጢአት እንዳትሠሩ ነው። ማንም ኃጢአት ቢሠራ ግን በአብ ዘንድ ረዳት አለን፤ እሱም ጻድቅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።”—1 ዮሐ. 2:1

20. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

20 የሚያሳዝነው፣ አንዳንድ ጊዜ ኃጢአት የፈጸመው ክርስቲያን ንስሐ ለመግባት ፈቃደኛ ላይሆን ይችላል። ሁኔታው እንደዚያ ከሆነ፣ ከጉባኤው መወገድ ይኖርበታል። ሽማግሌዎች እንዲህ ያሉትን ከባድ ጉዳዮች የሚይዙት እንዴት ነው? ከእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች መካከል የመጨረሻ በሆነው በቀጣዩ ርዕስ ላይ ይህን ጉዳይ እንመለከታለን።

መዝሙር 103 እረኞች—ስጦታ የሆኑ ወንዶች

a ቀደም ሲል እነዚህ ሽማግሌዎች የፍርድ ኮሚቴ ተብለው ይጠሩ ነበር። ይሁን እንጂ ፍርድ መስጠት የሥራቸው አንድ ገጽታ ብቻ ከመሆኑ አንጻር ይህን አገላለጽ መጠቀማችንን እናቆማለን። ከዚህ ይልቅ ይህን ቡድን የሽማግሌዎች ኮሚቴ ብለን እንጠራዋለን።

b ወላጆች ሲባል ሕጋዊ ሞግዚቶችን ወይም ልጁን እንደ ወላጅ ሆነው የሚያሳድጉ ሰዎችንም ያካትታል።