በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 35

መዝሙር 123 ለቲኦክራሲያዊ ሥርዓት በታማኝነት መገዛት

ከጉባኤ ለተወገዱ ሰዎች የሚደረግ እርዳታ

ከጉባኤ ለተወገዱ ሰዎች የሚደረግ እርዳታ

“ንስሐ መግባት ከማያስፈልጋቸው 99 ጻድቃን ይልቅ ንስሐ በሚገባ አንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ታላቅ ደስታ ይሆናል።”ሉቃስ 15:7

ዓላማ

አንዳንድ ሰዎች ከጉባኤ መወገድ ያለባቸው ለምንድን ነው? የተወገዱ ሰዎች ንስሐ እንዲገቡና የይሖዋን ሞገስ መልሰው እንዲያገኙ ሽማግሌዎች ሊረዷቸው የሚችሉትስ እንዴት ነው?

1-2. (ሀ) ይሖዋ ሆን ተብሎ ለሚሠራ ኃጢአት ምን አመለካከት አለው? (ለ) ይሖዋ ጥፋት የሠሩ ሰዎች ምን እንዲያደርጉ ይፈልጋል?

 ይሖዋ ልል አምላክ አይደለም፤ ኃጢአትን በቸልታ አያልፍም። (መዝ. 5:4-6) በቃሉ ውስጥ ያስቀመጠልንን የጽድቅ መሥፈርቶች እንድንከተል ይጠብቅብናል። እርግጥ ይሖዋ ፍጹማን ካልሆኑ ሰዎች ፍጽምናን አይጠብቅም። (መዝ. 130:3, 4) ሆኖም “በአምላካችን ጸጋ እያሳበቡ ማንአለብኝነት የሚንጸባረቅበት ድርጊት የሚፈጽሙ” ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎችን አይታገሥም። (ይሁዳ 4) እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ‘ፈሪሃ አምላክ የሌላቸውን ሰዎች’ በአርማጌዶን ጦርነት እንደሚያጠፋ ይናገራል።—2 ጴጥ. 3:7፤ ራእይ 16:16

2 ያም ሆኖ ይሖዋ ማንም እንዲጠፋ አይፈልግም። ከዚህ በፊት በነበሩት ተከታታይ ርዕሶች ላይ እንዳየነው ይሖዋ “ሁሉ ለንስሐ እንዲበቃ” እንደሚፈልግ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል። (2 ጴጥ. 3:9) ክርስቲያን ሽማግሌዎች ይሖዋን በመምሰል፣ ጥፋት ያጠፉ ሰዎች አካሄዳቸውን እንዲያስተካክሉና የይሖዋን ሞገስ መልሰው እንዲያገኙ በትዕግሥት ለመርዳት ይሞክራሉ። ሆኖም አዎንታዊ ምላሽ የሚሰጡት ሁሉም ጥፋተኞች አይደሉም። (ኢሳ. 6:9) አንዳንዶች፣ ሽማግሌዎች ንስሐ እንዲገቡ በተደጋጋሚ ሊረዷቸው ቢሞክሩም የተሳሳተ ጎዳና መከተላቸውን ይቀጥላሉ። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥም ሽማግሌዎች ምን ማድረግ ይችላሉ?

‘ክፉውን ሰው አስወግዱት’

3. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞች ምን ሊደረጉ እንደሚገባ ይናገራል? (ለ) ጥፋተኛው ከጉባኤ ለመወገድ መርጧል ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

3 አንድ ጥፋተኛ ንስሐ የማይገባ ከሆነ ሽማግሌዎች በ1 ቆሮንቶስ 5:13 ላይ የሚገኘውን “ክፉውን ሰው ከመካከላችሁ አስወግዱት” የሚለውን መመሪያ ከመከተል ሌላ ምንም አማራጭ አይኖራቸውም። ደግሞም ጥፋተኛው ይህ እንዲደርስበት መርጧል ሊባል ይችላል፤ እሱ a ራሱ የዘራውን እያጨደ ነው። (ገላ. 6:7) እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ሽማግሌዎች እሱን ወደ ንስሐ ለመምራት በተደጋጋሚ ያደረጉትን ጥረት ሳይቀበል ቀርቷል። (2 ነገ. 17:12-15) የይሖዋን መሥፈርቶች ላለመታዘዝ እንደመረጠ በተግባሩ አሳይቷል።—ዘዳ. 30:19, 20

4. ንስሐ የማይገባ ኃጢአተኛ ከጉባኤው ሲወገድ ማስታወቂያ የሚነገረው ለምንድን ነው?

4 ንስሐ ያልገባ አንድ ኃጢአተኛ ከጉባኤ ሲወገድ ከእንግዲህ በኋላ የይሖዋ ምሥክር እንዳልሆነ የሚገልጽ ማስታወቂያ ለጉባኤው ይነገራል። የዚህ ማስታወቂያ ዓላማ ጥፋተኛውን ማሸማቀቅ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ዓላማው፣ ወንድሞችና እህቶች ከዚህ ሰው ጋር ‘መግጠማቸውን እንዲተዉ አልፎ ተርፎም እንዲህ ካለው ሰው ጋር ምግብ እንኳ እንዳይበሉ’ የሚያዘውን ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያ እንዲከተሉ መርዳት ነው። (1 ቆሮ. 5:9-11) ይህ መመሪያ የተሰጠበት አጥጋቢ ምክንያት አለ። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ ያቦካዋል’ ሲል ጽፏል። (1 ቆሮ. 5:6) ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞች በይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ለመመራት ጥረት የሚያደርጉ ሰዎችን ቁርጠኝነት ያዳክማሉ።—ምሳሌ 13:20፤ 1 ቆሮ. 15:33

5. ከጉባኤ ለተወገደ ሰው ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል? ለምንስ?

5 ታዲያ ከጉባኤ ለተወገደ የእምነት አጋራችን ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል? ምንም እንኳ ከእሱ ጋር መቀራረባችንን ብናቆምም ሁኔታው ተስፋ እንደሌለው ልናስብ አይገባም፤ ከዚህ ይልቅ እንደጠፋ በግ እንመለከተዋለን። ከመንጋው ተለይቶ የጠፋ በግ ተመልሶ ሊመጣ ይችላል። ይህ የጠፋ በግ ራሱን ለይሖዋ ወስኖ እንደነበር አስታውስ። የሚያሳዝነው፣ ከገባው ቃል ጋር በሚስማማ ሁኔታ እየኖረ አይደለም፤ ይህ ደግሞ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ከቶታል። (ሕዝ. 18:31) ሆኖም ይሖዋ ምሕረት የሚያሳይበት አጋጣሚ ክፍት እስከሆነ ድረስ ይህ ሰው ወደ ጉባኤው የመመለስ ተስፋ አለው። ታዲያ ሽማግሌዎች ይህን ከጉባኤ የተወገደ ሰው ሊረዱት የሚችሉት እንዴት ነው?

ሽማግሌዎች ለተወገዱ ሰዎች የሚያደርጉት እርዳታ

6. ሽማግሌዎች ከጉባኤ የተወገደውን ሰው ለመርዳት የትኞቹን እርምጃዎች ይወስዳሉ?

6 ታዲያ አንድ ሰው ከጉባኤው ተወግዷል ማለት ብቻውን ይተዋል ወይም ያለማንም እርዳታ ወደ ይሖዋ ለመመለስ እንዲፍጨረጨር ይጠበቅበታል ማለት ነው? በፍጹም! በኮሚቴው ውስጥ ያሉት ሽማግሌዎች ንስሐ ላልገባው ኃጢአተኛ ከጉባኤ መወገዱን ሲነግሩት ወደ ጉባኤው ለመመለስ የትኞቹን እርምጃዎች መውሰድ እንደሚችል ያስረዱታል። ሆኖም ሽማግሌዎቹ በዚህ ብቻ አይወሰኑም። በአብዛኛው፣ አመለካከቱን ቀይሮ እንደሆነ ለማየት ከጥቂት ወራት በኋላ በድጋሚ ሊያገኙት እንደሚፈልጉ ይገልጹለታል። ጥፋተኛው ከእነሱ ጋር በድጋሚ ለመገናኘት ፈቃደኛ ከሆነ ሽማግሌዎቹ በዚህ ጊዜ ሲያገኙት ንስሐ እንዲገባና አካሄዱን እንዲያስተካክል ፍቅራዊ ግብዣ ያቀርቡለታል። በዚያ ጊዜ አመለካከቱን አስተካክሎ ባይሆን እንኳ ሽማግሌዎቹ በየተወሰነ ጊዜው እሱን ለማነጋገር ጥረት ያደርጋሉ።

7. ሽማግሌዎች የተወገደን ሰው በሚይዙበት መንገድ የይሖዋን ርኅራኄ የሚኮርጁት እንዴት ነው? (ኤርምያስ 3:12)

7 ሽማግሌዎች ከጉባኤ የተወገደን ሰው የሚይዙበት መንገድ የይሖዋን ርኅራኄ የሚያንጸባርቅ እንዲሆን ጥረት ያደርጋሉ። ለምሳሌ ይሖዋ፣ በጥንቷ እስራኤል የነበሩት ዓመፀኛ ሕዝቦቹ ወደ እሱ ለመመለስ የመጀመሪያውን እርምጃ እንዲወስዱ አልጠበቀባቸውም። ከዚህ ይልቅ፣ እነሱ ምንም ዓይነት የንስሐ ምልክት ከማሳየታቸው በፊት ቅድሚያውን ወስዶ ረድቷቸዋል። ከእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች በሁለተኛው ላይ እንደተመለከትነው፣ ይሖዋ ለሕዝቡ የሚያሳየውን ርኅራኄ ሆሴዕን እንደ ምሳሌ በመጠቀም አሳይቷል። የሆሴዕ ሚስት ገና ኃጢአት መፈጸሟን ባታቆምም እንኳ ሆሴዕ ቅድሚያውን ወስዶ እንዲታረቃት ነግሮታል። (ሆሴዕ 3:1፤ ሚል. 3:7) ክርስቲያን ሽማግሌዎችም የይሖዋን ምሳሌ ስለሚከተሉ ጥፋተኛው እንዲመለስ ከልባቸው ይፈልጋሉ፤ እንዲሁም መመለስ ከባድ እንዲሆንበት አያደርጉም።—ኤርምያስ 3:12ን አንብብ።

8. ኢየሱስ ስለ አባካኙ ልጅ የተናገረው ምሳሌ ስለ ይሖዋ ርኅራኄና ምሕረት ይበልጥ እንድንረዳ የሚያግዘን እንዴት ነው? (ሉቃስ 15:7)

8 በሁለተኛው የጥናት ርዕስ ላይ የተመለከትነውን ኢየሱስ ስለ አባካኙ ልጅ የተናገረውን ምሳሌ አስታውስ። አባትየው ልጁ ወደ ቤት ሲመለስ እንዳየው “እየሮጠ [ሄዶ] አንገቱ ላይ ተጠምጥሞ ሳመው።” (ሉቃስ 15:20) አባትየው ልጁ ይቅርታ እስኪጠይቀው ድረስ እንዳልጠበቀ ልብ በል። ከዚህ ይልቅ ማንኛውም አፍቃሪ አባት እንደሚያደርገው ቀድሞ እርምጃ የወሰደው እሱ ነው። ሽማግሌዎችም ከጉባኤው ለወጡት እንዲህ ያለ አመለካከት ለማዳበር ጥረት ያደርጋሉ። እነዚህ የጠፉ በጎች ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ይፈልጋሉ። (ሉቃስ 15:22-24, 32) አንድ ኃጢአተኛ ሲመለስ በሰማይ ደስታ ይሆናል፤ በምድርም ላይ እንደዚያው።—ሉቃስ 15:7ን አንብብ።

9. ይሖዋ ለኃጢአተኞች ምን ፍቅራዊ ግብዣ አቅርቧል?

9 እስካሁን በግልጽ እንደተመለከትነው ይሖዋ ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞችን በቸልታ አያልፍም። ይህ ማለት ግን እርግፍ አድርጎ ይተዋቸዋል ማለት አይደለም። እንዲመለሱ ይፈልጋል። ይሖዋ ንስሐ ለሚገቡ ጥፋተኞች ያለው ስሜት በሆሴዕ 14:4 ላይ ተገልጿል፤ እንዲህ ብሏል፦ “እኔም ከዳተኛነታቸውን እፈውሳለሁ። በገዛ ፈቃዴ እወዳቸዋለሁ፤ ምክንያቱም ቁጣዬ . . . ተመልሷል።” ሽማግሌዎች ይህን ማወቃቸው የንስሐ ምልክቶችን በንቃት እንዲከታተሉ ያነሳሳቸዋል። ይሖዋን የተዉ ሰዎችም ይህን ማሰባቸው ጊዜ ሳያባክኑ ወደ እሱ እንዲመለሱ ያነሳሳቸዋል።

10-11. ሽማግሌዎች ቀደም ሲል ከጉባኤው ተወግደው የነበሩ ሰዎችን መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?

10 ቀደም ሲል ምናልባትም ከረጅም ዓመታት በፊት ከጉባኤ ተወግደው ስለነበሩ ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? እነዚህ ሰዎች እንዲወገዱ ያደረጋቸውን ኃጢአት መፈጸማቸውን አቁመው ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ፣ የተወገዱበትን ምክንያት እንኳ ላያስታውሱት ይችላሉ። ሁኔታው ምንም ይሁን ምን፣ ሽማግሌዎች እነዚህን ሰዎች አግኝተው ለማነጋገር ጥረት ያደርጋሉ። በዚህ ወቅት ሽማግሌዎቹ አብረዋቸው ሊጸልዩ ይችላሉ፤ እንዲሁም ወደ ጉባኤው እንዲመለሱ ሞቅ ያለ ግብዣ ያቀርቡላቸዋል። እርግጥ ግለሰቡ ከጉባኤው ርቆ ለረጅም ዓመታት ቆይቶ ከሆነ በመንፈሳዊ በጣም ተዳክሞ እንደሚሆን አያጠራጥርም። ግለሰቡ ወደ ጉባኤው የመመለስ ፍላጎት ካሳየ ውገዳው ገና ባይነሳለትም እንኳ ሽማግሌዎች አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያስጠናው ዝግጅት ሊያደርጉለት ይችላሉ። በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ እንዲህ ያሉ ግለሰቦች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ ዝግጅት ማድረግ የሚችሉት ሽማግሌዎች ብቻ ናቸው።

11 ሽማግሌዎች የይሖዋን ርኅራኄ በመኮረጅ በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎችን ማግኘትና ለመመለስ በሩ ክፍት እንደሆነ ማሳወቅ ይፈልጋሉ። አንድ ኃጢአተኛ የንስሐ ፍሬ ካፈራና የተሳሳተ ድርጊቱን እርግፍ አድርጎ ከተወ በፍጥነት ወደ ጉባኤው መመለስ ይችላል።—2 ቆሮ. 2:6-8

12. (ሀ) ሽማግሌዎች የተለየ ጥንቃቄ ማድረግ የሚኖርባቸው በየትኞቹ ሁኔታዎች ውስጥ ነው? (ለ) አንዳንድ ኃጢአተኞች የይሖዋን ምሕረት ፈጽሞ አያገኙም ብለን ማሰብ የሌለብን ለምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

12 በአንዳንድ ሁኔታዎች ውስጥ፣ ሽማግሌዎች አንድን ሰው ወደ ጉባኤው ከመመለሳቸው በፊት ለየት ያለ ጥንቃቄ ማድረግ ሊኖርባቸው ይችላል። ለምሳሌ አንድ ሰው የተወገደው በልጆች ጥቃት፣ በክህደት ወይም በተንኮል አሲሮ ትዳሩን በማፍረስ ከሆነ ሽማግሌዎች የእውነት ንስሐ መግባቱን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። (ሚል. 2:14፤ 2 ጢሞ. 3:6) መንጋውን ከአደጋ ሊጠብቁ ይገባል። በሌላ በኩል ግን ይሖዋ እውነተኛ ንስሐ የገባንና መጥፎ ድርጊት መፈጸሙን ያቆመን ማንኛውንም ኃጢአተኛ ይቅር እንደሚል ማስታወስ ይኖርብናል። ስለዚህ ሽማግሌዎች በሌሎች ላይ ክህደት ከፈጸሙ ሰዎች ጋር በተያያዘ ለየት ያለ ጥንቃቄ ማድረግ ቢኖርባቸውም አንዳንድ ኃጢአተኞች ፈጽሞ የይሖዋን ምሕረት አያገኙም የሚል መደምደሚያ ላይ ከመድረስ ሊቆጠቡ ይገባል። b1 ጴጥ. 2:10

ጉባኤው ምን ማድረግ ይችላል?

13. በሽማግሌዎች ወቀሳ የተሰጠውን ሰው በምንይዝበት መንገድና ከጉባኤ የተወገደን ሰው በምንይዝበት መንገድ መካከል ምን ልዩነት አለ?

13 ባለፈው የጥናት ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው፣ አንዳንድ ጊዜ አንድ ሰው ወቀሳ እንደተሰጠው ማስታወቂያ ሊነገር ይችላል። በዚህ ጊዜ ይህ ሰው ንስሐ እንደገባና መጥፎ ድርጊቱን እንደተወ ስለምንገነዘብ ከእሱ ጋር መወዳጀታችንን መቀጠል እንችላለን። (1 ጢሞ. 5:20) ይህ ሰው አሁንም የጉባኤው ክፍል ነው፤ ደግሞም ከእምነት አጋሮቹ ጋር ጊዜ በማሳለፍ ማበረታቻ ማግኘት ያስፈልገዋል። (ዕብ. 10:24, 25) አንድ ሰው ከጉባኤ ሲወገድ ግን ሁኔታው ከዚህ በጣም የተለየ ነው። እንዲህ ካለው ሰው ጋር ‘መግጠማችንን እንተዋለን፤ አብረነው ምግብ እንኳ አንበላም።’—1 ቆሮ. 5:11

14. ክርስቲያኖች ከጉባኤ ከተወገዱ ሰዎች ጋር በተያያዘ በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናቸውን መጠቀም የሚችሉት እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

14 እስካሁን ከተመለከትነው ሐሳብ አንጻር፣ አንድ ሰው ከጉባኤው ሲወገድ ጨርሶ አናነጋግረውም ማለት ነው? እንደዚያ ማለት ላይሆን ይችላል። ከእሱ ጋር ጊዜ እንደማናሳልፍ የታወቀ ነው። ሆኖም ክርስቲያኖች የተወገደውን ሰው ወደ ጉባኤ ስብሰባ ለመጋበዝ በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናቸውን ተጠቅመው ሊወስኑ ይችላሉ፤ ምናልባትም ግለሰቡ ዘመዳቸው ወይም ይቀርቡት የነበረ ሰው ሊሆን ይችላል። ይህ ሰው በስብሰባ ላይ ከተገኘስ? ከዚህ በፊት እንዲህ ያለውን ሰው ሰላም አንልም ነበር። ነገር ግን በዚህ ጉዳይ ረገድም እያንዳንዱ ክርስቲያን በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናውን ተጠቅሞ መወሰን ይኖርበታል። አንዳንዶች ለግለሰቡ ሰላምታ ለመስጠት ወይም ‘እንኳን ደህና መጣህ’ ለማለት ነፃነት ሊሰማቸው ይችላል። ይሁንና ከግለሰቡ ጋር ረዘም ያለ ጭውውት አናደርግም፤ ወይም በሌሎች እንቅስቃሴዎች ከእሱ ጋር ጊዜ አናሳልፍም።

ክርስቲያኖች አንድን የተወገደ ሰው ወደ ስብሰባ ለመጋበዝም ሆነ በስብሰባ ላይ ሲገኝ አጭር ሰላምታ ለመስጠት ሲወስኑ በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናቸውን መጠቀም ይችላሉ (አንቀጽ 14⁠ን ተመልከት)


15. ሁለተኛ ዮሐንስ 9-11 የሚናገረው ስለ ምን ዓይነት ኃጢአተኞች ነው? (“ ዮሐንስና ጳውሎስ የተናገሩት ስለ ተመሳሳይ ዓይነት ኃጢአት ነው?” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

15 አንዳንዶች ‘መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለውን ሰው ሰላም የሚል ክርስቲያን የክፉ ሥራው ተባባሪ እንደሚሆን ይናገር የለ እንዴ?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። (2 ዮሐንስ 9-11ን አንብብ።) የጥቅሱ አውድ እንደሚጠቁመው ይህ መመሪያ የሚመለከተው ከሃዲዎችንና መጥፎ ምግባርን የሚያስፋፉ ሌሎች ሰዎችን ነው። (ራእይ 2:20) ስለዚህ አንድ ሰው የክህደት ትምህርቶችንና መጥፎ ምግባርን የሚያስፋፋ ከሆነ ሽማግሌዎች ይህን ሰው ለማነጋገር ዝግጅት አያደርጉም። እርግጥ እንዲህ ያለውም ሰው ወደ ልቦናው ሊመለስ ይችላል። ሆኖም ይህ እስኪሆን ድረስ እንዲህ ያለውን ሰው ሰላም አንለውም፤ ወይም ወደ ስብሰባ እንዲመጣ አንጋብዘውም።

የይሖዋን ርኅራኄና ምሕረት መኮረጅ

16-17. (ሀ) ይሖዋ ኃጢአተኞች ምን እንዲያደርጉ ይፈልጋል? (ሕዝቅኤል 18:32) (ለ) ሽማግሌዎች ኃጢአተኞችን በሚረዱበት ጊዜ ከይሖዋ ጋር አብረው መሥራት የሚችሉት እንዴት ነው?

16 ከእነዚህ አምስት ተከታታይ ርዕሶች ምን ትምህርት አግኝተናል? ይሖዋ ማንም ሰው እንዲጠፋ አይፈልግም! (ሕዝቅኤል 18:32ን አንብብ።) ኃጢአተኞች ከእሱ ጋር እንዲታረቁ ይፈልጋል። (2 ቆሮ. 5:20) በታሪክ ዘመናት ሁሉ ይሖዋ ዓመፀኛ ሕዝቦቹንና ዓመፀኛ ግለሰቦችን ንስሐ እንዲገቡና ወደ እሱ እንዲመለሱ በተደጋጋሚ ሲያሳስብ የኖረው ለዚህ ነው። የጉባኤ ሽማግሌዎች፣ ኃጢአተኞች ንስሐ እንዲገቡ በመርዳት ከይሖዋ ጋር የመሥራት ትልቅ መብት አግኝተዋል።—ሮም 2:4፤ 1 ቆሮ. 3:9

17 ኃጢአተኞች ንስሐ ሲገቡ በሰማይ ምን ያህል ደስታ እንደሚኖር ለማሰብ ሞክር። አንድ የጠፋ በግ ወደ ጉባኤ በተመለሰ ቁጥር የሰማዩ አባታችን ይሖዋ ታላቅ ደስታ ይሰማዋል። በይሖዋ ርኅራኄ፣ ምሕረትና ጸጋ ላይ ባሰላሰልን ቁጥር ለእሱ ያለን ፍቅር እያደገ ይሄዳል።—ሉቃስ 1:78

መዝሙር 111 ለደስታችን ምክንያት የሆኑ ነገሮች

a በዚህ ርዕስ ውስጥ ጥፋተኛው በወንድ ፆታ የተገለጸ ቢሆንም ሐሳቡ ለሴቶችም ይሠራል።

b በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፣ ‘ይቅር የማይባል ኃጢአት’ የሚለው አገላለጽ የሚያመለክተው አንድን የተለየ ኃጢአት ሳይሆን በደነደነ ልብ የሚፈጸምን ኃጢአት ነው፤ እንዲህ ያለ ኃጢአት የሚፈጽም ሰው በዘላቂነት አምላክን ለመቃወም ወስኗል። አንድ ሰው የሠራው ኃጢአት ይቅር የማይባል መሆኑን መወሰን የእኛ ቦታ አይደለም።—ማር. 3:29፤ ዕብ. 10:26, 27