በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

በ2 ተሰሎንቄ 3:14 ላይ የተጠቀሰው ምልክት ማድረግ ጉባኤው የሚወስደው እርምጃ ነው ወይስ ክርስቲያኖች በግለሰብ ደረጃ የሚወስዱት እርምጃ?

ሐዋርያው ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች “በዚህ ደብዳቤ አማካኝነት ላስተላለፍነው ቃል የማይታዘዝ ሰው ቢኖር ይህን ሰው ምልክት አድርጉበት” የሚል መመሪያ ጽፎላቸዋል። (2 ተሰ. 3:14) ቀደም ሲል፣ ይህ መመሪያ ለሽማግሌዎች የተሰጠ እንደሆነ እንገልጽ ነበር። አንድ ሰው በተደጋጋሚ ምክር ቢሰጠውም እንኳ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ችላ ማለቱን ከገፋበት ሽማግሌዎች የማስጠንቀቂያ ንግግር ለጉባኤው ሊያቀርቡ ይችላሉ። ከዚያ በኋላ አስፋፊዎች ምልክት ከተደረገበት ግለሰብ ጋር ቅርርብ ከመፍጠር ይቆጠባሉ።

ይሁንና በዚህ አሠራር ላይ ማስተካከያ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው ጳውሎስ ይህን ምክር የሰጠው ክርስቲያኖች በአንዳንድ ሁኔታዎች ውስጥ በግለሰብ ደረጃ ምን ዓይነት እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው ለማመልከት ነው። ስለዚህ ሽማግሌዎች ለጉባኤው የማስጠንቀቂያ ንግግር ማቅረብ አያስፈልጋቸውም። እንዲህ ያለ ማስተካከያ ማድረግ ያስፈለገው ለምንድን ነው? ጳውሎስ እዚህ ጥቅስ ላይ የሰጠውን ምክር ከአውዱ አንጻር እንመልከት።

ጳውሎስ በዚያ ጉባኤ ውስጥ ያሉ አንዳንዶች ‘ሥርዓት በጎደለው መንገድ እንደሚመላለሱ’ ተናግሯል። የተሰጣቸውን በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ ምክር ችላ ብለዋል። ባለፈው ጉብኝቱ ወቅት “መሥራት የማይፈልግ ሁሉ አይብላ” የሚል ትእዛዝ ሰጥቷቸው ነበር። ያም ቢሆን አንዳንዶች አቅማቸው ቢፈቅድላቸውም እንኳ እየሠሩ ራሳቸውን ለማስተዳደር ፈቃደኛ አልሆኑም። በተጨማሪም በሌሎች ሰዎች ጉዳይ ጣልቃ ይገቡ ነበር። ክርስቲያኖች ሥርዓት በጎደለው መንገድ የሚመላለሱትን እነዚህን ሰዎች እንዴት ሊይዟቸው ይገባል?—2 ተሰ. 3:6, 10-12

ጳውሎስ “ይህን ሰው ምልክት አድርጉበት” ብሏል። እዚህ ላይ ያለው የግሪክኛ ቃል እንዲህ ያለውን ሰው በትኩረት መከታተልን ያመለክታል። ጳውሎስ ይህን መመሪያ የሰጠው ለሽማግሌዎች ብቻ ሳይሆን ለመላው ጉባኤ ነው። (2 ተሰ. 1:1፤ 3:6) ስለዚህ ክርስቲያኖች አንድ የእምነት አጋራቸው አንድን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር አልታዘዝም እንዳለ ሲያስተውሉ ሥርዓት በጎደለው መንገድ ከሚመላለሰው ከዚህ ሰው ጋር ‘መግጠማቸውን ለመተው’ በግለሰብ ደረጃ ይወስናሉ።

ታዲያ ይህ ሰው ሊያዝ የሚገባው ከጉባኤ እንደተወገደ ሰው ነው ማለት ነው? አይደለም፣ ምክንያቱም ጳውሎስ “እንደ ወንድም አጥብቃችሁ መምከራችሁን ቀጥሉ” ብሏል። ስለዚህ ክርስቲያኖች፣ ምልክት ካደረጉበት ሰው ጋር በጉባኤ ስብሰባዎችና በአገልግሎት ቢካፈሉም በመዝናኛ ወይም በሌሎች ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች አብረውት ጊዜ ላለማሳለፍ ይመርጣሉ። ለምን? ጳውሎስ፣ ‘ያፍር ዘንድ’ ብሏል። ሥርዓት በጎደለው መንገድ የሚመላለሰው ክርስቲያን ምልክት ስለተደረገበት በምግባሩ አፍሮ አካሄዱን ሊያስተካክል ይችላል።—2 ተሰ. 3:14, 15

በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች ይህን ምክር በሥራ ላይ ማዋል የሚችሉት እንዴት ነው? በመጀመሪያ፣ የግለሰቡ ምግባር ጳውሎስ እንደገለጸው ‘ሥርዓት የጎደለው’ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርብናል። ጳውሎስ እየተናገረ የነበረው በሕሊና ጉዳይ ወይም በግል ምርጫ ከእኛ ስለሚለዩ ሰዎች አይደለም። ወይም ደግሞ ስሜታችንን ስለጎዱት ሰዎች መናገሩ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ጳውሎስ እየተናገረ የነበረው ግልጽ የሆነን አምላካዊ ምክር ሆን ብለው ለመጣስ ስለመረጡ ሰዎች ነው።

በዛሬው ጊዜ አንድ የእምነት አጋራችን እንዲህ ያለ ያለመታዘዝ መንፈስ a እያሳየ እንደሆነ ካስተዋልን በመዝናኛም ሆነ በሌሎች ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች አብረነው ጊዜ ላለማሳለፍ የግላችንን ውሳኔ እናደርጋለን። ይህ የግል ውሳኔ ስለሆነ፣ አብረውን ከሚኖሩት የቤተሰባችን አባላት በቀር ስለዚህ ጉዳይ ከሌላ ሰው ጋር መነጋገር አይኖርብንም። በተጨማሪም ከግለሰቡ ጋር በጉባኤ ስብሰባዎችና በአገልግሎት አብረን መካፈላችንን እንቀጥላለን። ግለሰቡ አካሄዱን ካስተካከለ ደግሞ እንደ ቀድሞው ከእሱ ጋር መቀራረባችንን እንቀጥላለን።

a ለምሳሌ አንድ የእምነት አጋራችን አቅሙ ቢፈቅድለትም እንኳ እየሠራ ራሱን ለማስተዳደር ፈቃደኛ ላይሆን፣ ከማያምን ሰው ጋር መጠናናቱን ለማቆም ፈቃደኛ ላይሆን፣ በጉባኤ ውስጥ ክፍፍል የሚፈጥር ሐሳብ ሊያስፋፋ ወይም ጎጂ ሐሜት ሊያሰራጭ ይችላል። (1 ቆሮ. 7:39፤ 2 ቆሮ. 6:14፤ 2 ተሰ. 3:11, 12፤ 1 ጢሞ. 5:13) እንዲህ ባለው አካሄድ የሚገፉ ሰዎች ‘ሥርዓት በጎደለው መንገድ ይመላለሳሉ’ ሊባል ይችላል።