የጥናት ርዕስ 31
መዝሙር 12 ታላቁ አምላክ ይሖዋ
ይሖዋ ኃጢአተኛ የሰው ልጆችን ለማዳን ምን አድርጓል?
“አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ . . . አንድያ ልጁን ሰጥቷል።”—ዮሐ. 3:16
ዓላማ
ይሖዋ ከኃጢአት ጋር በምናደርገው ውጊያ ቅድሚያውን ወስዶ የረዳን እንዴት ነው? ከኃጢአት ነፃ ወጥተን የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንድንችል ያደረገውስ እንዴት ነው?
1-2. (ሀ) ኃጢአት ምንድን ነው? ከኃጢአት ጋር በምናደርገው ውጊያ አሸናፊዎች መሆን የምንችለውስ እንዴት ነው? (“ተጨማሪ ማብራሪያ” የሚለውንም ተመልከት።) (ለ) በዚህ ርዕስና በዚህ መጠበቂያ ግንብ ውስጥ በሚገኙት ሌሎች ርዕሶች ላይ ምን እንመለከታለን? (በዚህ መጽሔት ላይ የሚገኘውን “ለአንባቢያን የተዘጋጀ ማስታወሻ” የሚለውን ርዕስም ተመልከት።)
ይሖዋ አምላክ ምን ያህል እንደሚወድህ ማወቅ ትፈልጋለህ? ይህን ማወቅ የምትችልበት ቀላል መንገድ አለ። አንተን ከኃጢአትና ከሞት ለማዳን ሲል ምን እንዳደረገ አጥና። ኃጢአት a በራስህ ልታሸንፈው የማትችለው ክፉ ጠላት ነው። ሁላችንም በየዕለቱ ኃጢአት እንሠራለን፤ በኃጢአታችን ምክንያትም እንሞታለን። (ሮም 5:12) ይሁንና አንድ መልካም ዜና አለ። በይሖዋ እርዳታ ኃጢአትን ማሸነፍ እንችላለን። እንዲያውም ድል መቀዳጀታችን የተረጋገጠ ነው!
2 ይሖዋ አምላክ ወደ 6,000 ለሚጠጉ ዓመታት የሰው ልጆች ከኃጢአት ጋር በሚያደርጉት ውጊያ ሲረዳቸው ቆይቷል። ለምን? ስለሚወደን ነው። ከመጀመሪያው አንስቶ የሰው ልጆችን በጣም ስለሚወድ በዚህ ውጊያ እነሱን ለመርዳት ብዙ ነገር አድርጓል። አምላክ ኃጢአት ወደ ሞት እንደሚመራን ያውቃል፤ እሱ ደግሞ እንድንሞት አይፈልግም። ከዚህ ይልቅ ለዘላለም እንድንኖር ይፈልጋል። (ሮም 6:23) ለአንተም ቢሆን የሚመኝልህ ይህንኑ ነው። በዚህ ርዕስ ውስጥ ሦስት ጥያቄዎችን እንመልሳለን፦ (1) ይሖዋ ኃጢአተኛ ለሆኑ የሰው ልጆች ምን ተስፋ ሰጥቷል? (2) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩ ኃጢአተኛ ሰዎች የይሖዋን ሞገስ ማግኘት የቻሉት እንዴት ነው? (3) ኢየሱስ ኃጢአተኛ የሆኑ የሰው ልጆችን ለማዳን ምን አድርጓል?
ይሖዋ ኃጢአተኛ ለሆኑ የሰው ልጆች ምን ተስፋ ሰጥቷል?
3. የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ኃጢአተኞች የሆኑት እንዴት ነው?
3 ይሖዋ የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት ሲፈጥር ደስተኛ እንዲሆኑ ፈልጎ ነበር። የሚያምር የመኖሪያ ቦታ፣ የጋብቻን ስጦታ እንዲሁም አስደሳች ሥራ ሰጥቷቸዋል። ምድርን በዘሮቻቸው የመሙላት እንዲሁም መላዋን ምድር ልክ እንደ ኤደን ገነት ውብ የማድረግ ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል። የተከለከሉት አንድ ቀላል ነገር ብቻ ነበር። ደግሞም ይህን ትእዛዝ በመተላለፍ ሆን ብለው በእሱ ላይ ካመፁ ኃጢአታቸው ወደ ሞት እንደሚመራቸው ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸዋል። ቀጥሎ ምን እንደሆነ እናውቃለን። ለአምላክም ሆነ ለእነሱ ምንም ፍቅር የሌለው አንድ መንፈሳዊ ፍጡር ያንን ኃጢአት እንዲፈጽሙ ፈተናቸው። አዳምና ሔዋን በፈተናው ወደቁ። በሚወዳቸው አባታቸው ከመታመን ይልቅ ኃጢአት ሠሩ። እንደምናውቀው የይሖዋ ቃል ተፈጽሟል። ከዚያች ዕለት አንስቶ የኃጢአታቸውን መዘዝ መቀበል ጀመሩ፤ እያረጁ ሄዱ፤ በመጨረሻም ለሞት ተዳረጉ።—ዘፍ. 1:28, 29፤ 2:8, 9, 16-18፤ 3:1-6, 17-19, 24፤ 5:5
4. ይሖዋ ኃጢአትን የሚጠላውና ከኃጢአት ጋር በምናደርገው ውጊያ የሚረዳን ለምንድን ነው? (ሮም 8:20, 21)
4 ይሖዋ ይህ አሳዛኝ ታሪክ እንዲጻፍ ያደረገው ለእኛ ጥቅም ነው። ይህ ታሪክ፣ ይሖዋ ኃጢአትን በጣም የሚጠላው ለምን እንደሆነ እንድንገነዘብ ይረዳናል። ኃጢአት ከአባታችን ይነጥለናል፤ እንዲሁም ወደ ሞት ይመራናል። (ኢሳ. 59:2) የዚህ ሁሉ ችግር ጠንሳሽ የሆነው ዓመፀኛው ሰይጣን ኃጢአትን የሚወደውና ለማስፋፋት ጥረት የሚያደርገው ለዚህ ነው። ሰይጣን በኤደን ትልቅ ድል እንደተቀዳጀ ተሰምቶት ሊሆን ይችላል። ይሁንና ይሖዋ ምን ያህል አፍቃሪ እንደሆነ አልገባውም። አምላክ ለአዳምና ለሔዋን ዘሮች ያወጣውን ዓላማ አልቀየረም። እሱ ሰዎችን በጣም ስለሚወድ ወዲያውኑ ለሁሉም የሰው ልጆች ተስፋ ሰጠ። (ሮም 8:20, 21ን አንብብ።) ይሖዋ ከአዳምና ከሔዋን ዘሮች መካከል አንዳንዶቹ እሱን ለመውደድ እንደሚመርጡ እንዲሁም ከኃጢአት ጋር በሚያደርጉት ውጊያ የእሱን እርዳታ እንደሚፈልጉ ያውቅ ነበር። እሱም አባታቸውና ፈጣሪያቸው እንደመሆኑ መጠን ከኃጢአት ነፃ የሚወጡበትንና ወደ እሱ መቅረብ የሚችሉበትን መንገድ ያዘጋጅላቸዋል። ይሖዋ ይህን ያደረገው እንዴት ነው?
5. ይሖዋ ለኃጢአተኛ የሰው ልጆች የመጀመሪያውን የተስፋ ጭላንጭል የፈነጠቀው መቼ ነው? አብራራ። (ዘፍጥረት 3:15)
5 ዘፍጥረት 3:15ን አንብብ። የመጀመሪያው የተስፋ ጭላንጭል የታየው ይሖዋ በሰይጣን ላይ ፍርድ ባስተላለፈበት ወቅት ነው። አምላክ የሰው ልጆችን የሚያድን “ዘር” እንደሚመጣ ገለጸ። ይህ ዘር በስተ መጨረሻ ሰይጣንን በመጨፍለቅ በኤደን ያደረሰውን ጉዳት በሙሉ ያስተካክላል። (1 ዮሐ. 3:8) ይሁንና በዚህ ሂደት መሃል ይህ ዘር መከራ ይደርስበታል። ሰይጣን ተረከዙን ያቆስለዋል፤ ማለትም እንዲሞት ያደርገዋል። ይህም ይሖዋን በእጅጉ ያሳዝነዋል። ይሁንና ይህ ሁሉ መሥዋዕት መከፈሉ አያስቆጭም፤ ምክንያቱም ስፍር ቁጥር የሌላቸው የሰው ልጆች ከኃጢአትና ከሞት ይድናሉ!
በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩ ኃጢአተኛ ሰዎች የይሖዋን ሞገስ ማግኘት የቻሉት እንዴት ነው?
6. እንደ አቤልና እንደ ኖኅ ያሉ የእምነት ሰዎች ወደ ይሖዋ ለመቅረብ ሲሉ ምን አድርገዋል?
6 ከዚያ በኋላ በነበሩት መቶ ዘመናት ይሖዋ ኃጢአተኛ የሆኑ የሰው ልጆች ወደ እሱ መቅረብ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ደረጃ በደረጃ ግልጽ አድርጓል። በኤደን ዓመፅ ከተቀሰቀሰ በኋላ በይሖዋ ላይ እምነት የጣለው የመጀመሪያው ሰው የአዳምና የሔዋን ሁለተኛ ልጅ የሆነው አቤል ነው። አቤል ይሖዋን ስለሚወደው እንዲሁም እሱን ማስደሰትና ወደ እሱ መቅረብ ስለሚፈልግ መሥዋዕት አቀረበ። አቤል እረኛ ስለነበር ከጠቦቶቹ የተወሰኑትን አርዶ ለይሖዋ አቀረበ። በዚህ ጊዜ ይሖዋ ምን ተሰማው? “አቤልንና ያቀረበውን መባ በጥሩ ፊት [ተመለከተ]።” (ዘፍ. 4:4) ይሖዋ እሱን የሚወዱና በእሱ የሚታመኑ ሰዎች ያቀረቧቸውን ሌሎች መሥዋዕቶችም በሞገስ ዓይን ተመልክቷል፤ ለምሳሌ ኖኅ ያቀረበውን መሥዋዕት ተቀብሏል። (ዘፍ. 8:20, 21) ይሖዋ እንዲህ ያሉ መሥዋዕቶችን በመቀበል ኃጢአተኛ የሆኑ የሰው ልጆች የእሱን ሞገስ ማግኘትና ወደ እሱ መቅረብ እንደሚችሉ አሳይቷል። b
7. አብርሃም የገዛ ልጁን መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ፈቃደኛ መሆኑ ምን ያስተምረናል?
7 ይሖዋ አስደናቂ እምነት የነበረውን አብርሃምን በጣም ከባድ ነገር እንዲያደርግ ይኸውም ልጁን ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብ ጠየቀው። ይህ ትእዛዝ አብርሃምን በጣም አስጨንቆት እንደሚሆን ምንም ጥያቄ የለውም። ያም ቢሆን አብርሃም ይሖዋን ታዘዘ። ሆኖም ልጁን መሥዋዕት ከማድረጉ በፊት አምላክ አስቆመው። ይሁንና ይህ ምሳሌ ለሁሉም የእምነት ሰዎች ወሳኝ ትምህርት ይዟል። ይሖዋ የሚወደውን ልጁን መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ፈቃደኛ ሆኗል። ይሖዋ ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር ያን ያህል ታላቅ ነው።—ዘፍ. 22:1-18
8. በሕጉ ሥር ይቀርቡ የነበሩት መሥዋዕቶች ለምን ነገር ጥላ ነበሩ? (ዘሌዋውያን 4:27-29፤ 17:11)
8 በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ለእስራኤል ብሔር የተሰጠው ሕግ የአምላክ ሕዝቦች ኃጢአታቸውን ለማስተሰረይ ብዙ መሥዋዕቶችን እንዲያቀርቡ ያዝዝ ነበር። (ዘሌዋውያን 4:27-29፤ 17:11ን አንብብ።) እነዚህ መሥዋዕቶች የሰው ልጆችን ከኃጢአት ሙሉ በሙሉ ለሚያድነው የላቀ መሥዋዕት ጥላ ነበሩ። የአምላክ ነቢያት፣ ተስፋ የተሰጠበት ዘር መከራ እንደሚቀበልና እንደሚገደል በመንፈስ ተመርተው ተናግረዋል። መሥዋዕት ሆኖ እንደሚቀርብ በግ እንደሚታረድ ገልጸዋል። (ኢሳ. 53:1-12) ይህ ዘር የአምላክ አንድያ ልጅ ሆኖ ተገኝቷል። እስቲ አስበው፣ ይሖዋ አንተን ጨምሮ የሰው ልጆችን ከኃጢአትና ከሞት ለማዳን ሲል የሚወደው ልጁ መሥዋዕት ሆኖ እንዲቀርብ ያደርጋል!
ኢየሱስ ሰዎችን ከኃጢአት ለማዳን ምን አድርጓል?
9. መጥምቁ ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ ምን ተናግሯል? (ዕብራውያን 9:22፤ 10:1-4, 12)
9 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. የአምላክ አገልጋይ የሆነው መጥምቁ ዮሐንስ የናዝሬቱ ኢየሱስ ወደ እሱ ሲመጣ ሲያይ “የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግደው የአምላክ በግ ይኸውላችሁ!” ብሎ ነበር። (ዮሐ. 1:29) በመንፈስ መሪነት የተነገሩት እነዚህ ቃላት ኢየሱስ ለረጅም ጊዜ በተስፋ ሲጠበቅ የነበረው ዘር መሆኑን ያሳያሉ። መሥዋዕት ሆኖ የሚቀርበው እሱ ነው። አሁን ኃጢአተኛ የሆኑ የሰው ልጆች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አስተማማኝ የሆነ ተስፋ ፈነጠቀላቸው፤ ኃጢአት ሙሉ በሙሉ ድል ሊደረግ ነው!—ዕብራውያን 9:22፤ 10:1-4, 12ን አንብብ።
10. ኢየሱስ ኃጢአተኞችን ሊጠራ እንደመጣ ያሳየው እንዴት ነው?
10 ኢየሱስ የኃጢአት ሸክም ለተጫናቸው ሰዎች ለየት ያለ ትኩረት ይሰጥ ነበር፤ ተከታዮቹ እንዲሆኑም ጋብዟቸዋል። በሰው ልጆች ላይ ለሚደርሰው መከራ ሁሉ ዋነኛው መንስኤ ኃጢአት እንደሆነ ያውቅ ነበር። በመሆኑም በኃጢአተኝነታቸው የሚታወቁ ሰዎችን ለመርዳት ጥረት አድርጓል። ሁኔታውን በምሳሌ ሲያስረዳ “ሐኪም የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች አይደሉም” ብሏል። አክሎም እንዲህ አለ፦ “እኔ የመጣሁት ጻድቃንን ሳይሆን ኃጢአተኞችን ልጠራ ነው።” (ማቴ. 9:12, 13) ደግሞም ያደረገው ይህንኑ ነው። እግሩን በእንባዋ ያጠበችውን ሴት በርኅራኄ አነጋግሯታል፤ ኃጢአቷንም ይቅር ብሎላታል። (ሉቃስ 7:37-50) በውኃ ጉድጓዱ አጠገብ የነበረችው ሳምራዊት ሴት ሥነ ምግባር የጎደለው ሕይወት እንደምትመራ ቢያውቅም እንኳ ወሳኝ እውነቶችን አስተምሯታል። (ዮሐ. 4:7, 17-19, 25, 26) እንዲያውም አምላክ የኃጢአት የመጨረሻ ውጤት የሆነውን ሞትን እንዲቀለብስ ለኢየሱስ ኃይል ሰጥቶታል። እንዴት? ኢየሱስ ልጅ አዋቂ፣ ወንድ ሴት ሳይል ሰዎችን ከሞት አስነስቷል።—ማቴ. 11:5
11. ኃጢአተኛ የሆኑ ሰዎች ወደ ኢየሱስ ለመቅረብ የተነሳሱት ለምንድን ነው?
11 በኃጢአት የተዘፈቁ ሰዎችም እንኳ ወደ ኢየሱስ ለመቅረብ መነሳሳታቸው አያስገርምም። ስሜታቸውን ይረዳላቸው ነበር፤ በርኅራኄም ይዟቸዋል። በመሆኑም ወደ እሱ መቅረብ አልከበዳቸውም። (ሉቃስ 15:1, 2) ኢየሱስም እንዲህ ያሉት ሰዎች በእሱ ላይ እምነት በማሳየታቸው አመስግኗቸዋል። (ሉቃስ 19:1-10) የአባቱን ምሕረት ፍጹምና ሕያው በሆነ መንገድ አንጸባርቋል። (ዮሐ. 14:9) መሐሪና ሩኅሩኅ የሆነው አባቱ ሰዎችን እንደሚወድ እንዲሁም ከኃጢአት ጋር በሚያደርጉት ውጊያ አሸናፊዎች እንዲሆኑ ሊረዳቸው እንደሚፈልግ በንግግሩም ሆነ በተግባሩ አሳይቷል። ኢየሱስ ኃጢአተኛ የሆኑ ሰዎች መንገዳቸውን ለማስተካከልና እሱን ለመከተል እንዲነሳሱ ረድቷቸዋል።—ሉቃስ 5:27, 28
12. ኢየሱስ ሞቱን አስመልክቶ ምን ብሏል?
12 ኢየሱስ ከፊቱ ምን እንደሚጠብቀው ያውቅ ነበር። አልፎ እንደሚሰጥና በእንጨት ላይ እንደሚሰቀል ለተከታዮቹ በተደጋጋሚ ነግሯቸዋል። (ማቴ. 17:22፤ 20:18, 19) ዮሐንስም ሆነ ነቢያት እንደተናገሩት የእሱ መሥዋዕት የዓለምን ኃጢአት እንደሚያስወግድ ያውቅ ነበር። በተጨማሪም ኢየሱስ ሕይወቱን አሳልፎ ከሰጠ በኋላ “ሁሉንም ዓይነት ሰዎች” ወደ ራሱ እንደሚስብ ተናግሯል። (ዮሐ. 12:32) ኃጢአተኛ የሆኑ የሰው ልጆች ኢየሱስን እንደ ጌታቸው አድርገው በመቀበልና የእሱን ፈለግ በመከተል ይሖዋን ማስደሰት ይችላሉ። እንዲህ ካደረጉ “ከኃጢአት ነፃ” ይወጣሉ። (ሮም 6:14, 18, 22፤ ዮሐ. 8:32) በመሆኑም ኢየሱስ ይህን አሰቃቂ ሞት በድፍረትና በፈቃደኝነት ተጋፍጧል።—ዮሐ. 10:17, 18
13. ኢየሱስ የሞተው እንዴት ነው? የእሱ ሞትስ ስለ ይሖዋ አምላክ ምን ያስተምረናል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
13 ኢየሱስ ተከድቷል፣ ታስሯል፣ ተሰድቧል፣ ስሙ ጠፍቷል፣ ተፈርዶበታል እንዲሁም ተገርፏል። ከዚያም ወታደሮች ወደሚገደልበት ቦታ ወስደው በእንጨት ላይ በምስማር ቸነከሩት። ኢየሱስ ይህን ሁሉ ሥቃይ በታማኝነት የተቋቋመ ቢሆንም በዚያ ሰዓት ከእሱ ይበልጥ የተሠቃየ ሌላ አካል አለ። እሱም ይሖዋ አምላክ ነው። ገደብ የለሽ ኃይል ቢኖረውም ጣልቃ ከመግባት ራሱን ገቷል። ለምን? አንድን አፍቃሪ አባት እንዲህ ያለ ነገር እንዲያደርግ ሊያነሳሳው የሚችለው ምንድን ነው? በአጭር አነጋገር ፍቅር ነው። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።”—ዮሐ. 3:16
14. የኢየሱስ መሥዋዕት ምን ያስተምርሃል?
14 የኢየሱስ መሥዋዕት ይሖዋ የአዳምና የሔዋንን ዘሮች ምን ያህል እንደሚወዳቸው የሚያሳይ ከሁሉ የላቀ ማስረጃ ነው። ይህ መሥዋዕት ይሖዋ አንተን ምን ያህል እንደሚወድህ ያሳያል። አንተን ከኃጢአትና ከሞት ለማዳን ሲል በራሱ ላይ እጅግ ከፍተኛ ሥቃይ እንዲደርስ ፈቅዷል። (1 ዮሐ. 4:9, 10) በእርግጥም እያንዳንዳችን ከኃጢአት ጋር እንድንዋጋ አልፎ ተርፎም እንድናሸንፍ ይፈልጋል!
15. የአምላክ ስጦታ ከሆነው ከኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ለመጠቀም ምን ማድረግ ይኖርብናል?
15 የአምላክ ስጦታ ማለትም የአንድያ ልጁ ቤዛዊ መሥዋዕት ኃጢአታችን ይቅር እንዲባል መሠረት ይሆናል። ይሁንና የአምላክን ይቅርታ ለማግኘት ከእኛ የሚጠበቅ ነገር አለ። ምንድን ነው? መጥምቁ ዮሐንስና ኢየሱስ ክርስቶስ መልሱን ይሰጡናል፦ “መንግሥተ ሰማያት ስለቀረበ ንስሐ ግቡ” ብለዋል። (ማቴ. 3:1, 2፤ 4:17) ስለዚህ ከኃጢአት ጋር መዋጋትና ወደ አፍቃሪው አባታችን መቅረብ የምንፈልግ ከሆነ ንስሐ መግባታችን የግድ አስፈላጊ ነው። ይሁንና ንስሐ መግባት ምን ያካትታል? ኃጢአትን ለማሸነፍ የሚረዳንስ እንዴት ነው? ቀጣዩ የጥናት ርዕስ መልሱን ይሰጠናል።
መዝሙር 18 ለቤዛው አመስጋኝ መሆን
a ተጨማሪ ማብራሪያ፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ኃጢአት” የሚለው ቃል የተሳሳተ ድርጊትን ወይም ከይሖዋ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጋር የሚጋጭ ነገር ማድረግን ሊያመለክት ይችላል። ይሁንና “ኃጢአት” የሚለው ቃል ከአዳም የወረስነውን አለፍጽምና ወይም የኃጢአት ዝንባሌም ሊያመለክት ይችላል። ሁላችንም የምንሞተው በዘር በወረስነው ኃጢአት የተነሳ ነው።