በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 33

መዝሙር 130 ይቅር ባይ ሁኑ

ጉባኤው ይሖዋ ለኃጢአተኞች ያለውን አመለካከት የሚያንጸባርቀው እንዴት ነው?

ጉባኤው ይሖዋ ለኃጢአተኞች ያለውን አመለካከት የሚያንጸባርቀው እንዴት ነው?

“ማንም ኃጢአት ቢሠራ . . . ረዳት አለን።”1 ዮሐ. 2:1

ዓላማ

በመጀመሪያው መቶ ዘመን በቆሮንቶስ በነበረው ጉባኤ ውስጥ ከባድ ጥፋት በተፈጸመበት ወቅት ጉዳዩ የተያዘበትን መንገድ በመመርመር ምን ትምህርት እናገኛለን?

1. ይሖዋ ሁሉም ሰዎች ምን እንዲያገኙ ይፈልጋል?

 ይሖዋ ሰዎችን ሲፈጥር የመምረጥ ነፃነት ሰጥቷቸዋል። ውሳኔዎችን ስናደርግ ይህን ስጦታ እንጠቀምበታለን። አንድ ሰው በሕይወቱ ውስጥ የሚያደርገው ትልቁ ውሳኔ ራሱን ለይሖዋ ወስኖ የይሖዋን አገልጋዮች ያቀፈውን ቤተሰብ መቀላቀል ነው። ይሖዋ ሁሉም ሰው ይህን ውሳኔ እንዲያደርግ ይፈልጋል። ለምን? ሰዎችን ስለሚወድና ከሁሉ የተሻለውን ነገር እንዲያገኙ ስለሚፈልግ ነው። የእሱ ወዳጆች እንዲሆኑና ለዘላለም እንዲኖሩ ይፈልጋል።—ዘዳ. 30:19, 20፤ ገላ. 6:7, 8

2. ይሖዋ ንስሐ ስለማይገቡ ጥፋተኞች ምን ይሰማዋል? (1 ዮሐንስ 2:1)

2 ያም ቢሆን ይሖዋ ማንንም ሰው እንዲያገለግለው አያስገድድም። እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱን ውሳኔ እንዲያደርግ ፈቅዷል። አንድ የተጠመቀ ክርስቲያን የአምላክን ሕግ በመጣስ ከባድ ኃጢአት ቢፈጽምስ? ንስሐ ካልገባ ከጉባኤው መወገድ ይኖርበታል። (1 ቆሮ. 5:13) ያም ሆኖ እንኳ ይሖዋ ጥፋተኛው ግለሰብ ወደ እሱ እንደሚመለስ ተስፋ ያደርጋል። እንዲያውም ቤዛውን ያዘጋጀበት አንዱ ወሳኝ ምክንያት ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞች ይቅርታ እንዲያገኙ ሲል ነው። (1 ዮሐንስ 2:1ን አንብብ።) አምላካችን ጥፋት የሠሩ ግለሰቦች ንስሐ እንዲገቡ ፍቅራዊ ግብዣ አቅርቦላቸዋል።—ዘካ. 1:3፤ ሮም 2:4፤ ያዕ. 4:8

3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

3 ይሖዋ ጉባኤ ውስጥ ከሚፈጸም ጥፋትም ሆነ ከጥፋተኞች ጋር በተያያዘ የእሱን አመለካከት እንድናዳብር ይፈልጋል። ይህ ርዕስ እንዲህ ማድረግ የምንችልበትን መንገድ ያብራራል። ይህን ርዕስ ስታነብ የሚከተሉትን ነጥቦች ለማስተዋል ሞክር፦ (1) በመጀመሪያው መቶ ዘመን በቆሮንቶስ በነበረው ጉባኤ ውስጥ ከባድ ጥፋት በተፈጸመበት ወቅት ጉዳዩ የተያዘው እንዴት ነው? (2) ጥፋት የፈጸመው ግለሰብ ንስሐ ሲገባ ሐዋርያው ጳውሎስ ምን መመሪያ ሰጠ? (3) ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ይሖዋ ከባድ ኃጢአት ለፈጸሙ ክርስቲያኖች ስላለው አመለካከት ምን ያስተምረናል?

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከባድ ጥፋት የተያዘበት መንገድ

4. በመጀመሪያው መቶ ዘመን በቆሮንቶስ በነበረው ጉባኤ ውስጥ ምን ሁኔታ ተፈጠረ? (1 ቆሮንቶስ 5:1, 2)

4 አንደኛ ቆሮንቶስ 5:1, 2ን አንብብ። ጳውሎስ በሦስተኛ ሚስዮናዊ ጉዞው ወቅት፣ አዲስ ስለተቋቋመው የቆሮንቶስ ጉባኤ የሚረብሽ ዜና ሰማ። በዚያ ጉባኤ ውስጥ የነበረ አንድ ወንድም ከእንጀራ እናቱ ጋር የፆታ ብልግና ይፈጽም ነበር። እንዲህ ያለው ምግባር ዘግናኝና ‘በአሕዛብ መካከል እንኳ ታይቶ የማይታወቅ’ ነው። ጉባኤው ይህን ምግባር ችላ ብሎ ማለፉ ሳያንስ በምግባሩ ተኩራርቶ የነበረ ይመስላል። ምናልባትም አንዳንዶች ይህን ሁኔታ ይሖዋ ፍጽምና የጎደላቸውን ሰዎች በምሕረት እንደሚይዝ የሚያሳይ ማስረጃ አድርገው ተመልክተውት ይሆናል። ይሁንና ይሖዋ በሕዝቦቹ መካከል የሚፈጸምን ጥፋት ችላ ብሎ አያልፍም። ግለሰቡ እንዲህ ያለ ልቅ ምግባር መከተሉ የጉባኤውን መልካም ስም የሚያበላሽ ነበር። ከእሱ ጋር ጊዜ በሚያሳልፉ ሌሎች ክርስቲያኖችም ላይ ተጽዕኖ አሳድሮ ሊሆን ይችላል። ታዲያ ጳውሎስ ለጉባኤው ምን መመሪያ ሰጠ?

5. ጳውሎስ ለጉባኤው ምን መመሪያ ሰጠ? ምን ማለቱስ ነበር? (1 ቆሮንቶስ 5:13) (ሥዕሉንም ተመልከት።)

5 አንደኛ ቆሮንቶስ 5:13ን አንብብ። ጳውሎስ ንስሐ ያልገባው ኃጢአተኛ ከጉባኤው መወገድ እንዳለበት የሚገልጽ ደብዳቤ በመንፈስ መሪነት ጻፈ። ታማኝ ክርስቲያኖች ከዚህ ግለሰብ ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት ሊኖራቸው ይገባል? ጳውሎስ ከዚህ ሰው ጋር ‘መግጠማቸውን እንዲተዉ’ ነግሯቸዋል። ምን ማለቱ ነበር? ጳውሎስ ይህ መመሪያ ‘እንዲህ ካለው ሰው ጋር ምግብ እንኳ አለመብላትን’ እንደሚያካትት ገልጿል። (1 ቆሮ. 5:11) ከአንድ ሰው ጋር ተቀምጦ ምግብ መብላት ከእሱ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት በር ይከፍታል። ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው፣ ጳውሎስ ጉባኤው ከግለሰቡ ጋር መቀራረብ እንደሌለበት መመሪያ መስጠቱ ነበር። ይህም ጉባኤው ግለሰቡ ከሚያሳድረው በካይ ተጽዕኖ እንዲጠበቅ ያስችላል። (1 ቆሮ. 5:5-7) በተጨማሪም በጉባኤው ውስጥ ያሉ ወንድሞችና እህቶች ከግለሰቡ ጋር አለመቀራረባቸው ግለሰቡ ከይሖዋ መንገዶች ምን ያህል እንደራቀ እንዲገነዘብና ኀፍረት ተሰምቶት ንስሐ እንዲገባ ሊያነሳሳው ይችላል።

ጳውሎስ ንስሐ ያልገባው ኃጢአተኛ ከጉባኤው መወገድ እንዳለበት የሚገልጽ ደብዳቤ በመንፈስ መሪነት ጽፏል (አንቀጽ 5⁠ን ተመልከት)


6. የጳውሎስ ደብዳቤ በጉባኤውና በጥፋተኛው ግለሰብ ላይ ምን ውጤት አምጥቷል?

6 ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለሚገኙ ክርስቲያኖች ደብዳቤ ከጻፈላቸው በኋላ ምን ምላሽ እንደሚሰጡ ማሰብ ጀመረ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ቲቶ አስደሳች ዜና ይዞለት መጣ። ጉባኤው ለጳውሎስ ደብዳቤ ጥሩ ምላሽ ሰጥቷል። (2 ቆሮ. 7:6, 7) ወንድሞች የሰጠውን መመሪያ ተከትለዋል። ከዚህም ሌላ፣ ጳውሎስ ደብዳቤውን በጻፈ በተወሰኑ ወራት ውስጥ ጥፋተኛው ግለሰብ ለኃጢአቱ ንስሐ ገብቷል። አመለካከቱንና ምግባሩን አስተካክሎ የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶች መከተል ጀምሯል። (2 ቆሮ. 7:8-11) ታዲያ ጳውሎስ ለጉባኤው ምን ተጨማሪ መመሪያ ይሰጥ ይሆን?

ጉባኤው ንስሐ የገባውን ኃጢአተኛ እንዴት ሊይዘው ይገባል?

7. ጥፋተኛው ግለሰብ ከጉባኤው መወገዱ ምን መልካም ውጤት አስገኝቷል? (2 ቆሮንቶስ 2:5-8)

7 ሁለተኛ ቆሮንቶስ 2:5-8ን አንብብ። ጳውሎስ “እንዲህ ዓይነቱ ሰው ከእናንተ አብዛኞቻችሁ የሰጣችሁት ተግሣጽ ይበቃዋል” ብሏል። በሌላ አባባል፣ ተግሣጹ ዓላማውን አከናውኗል። ዓላማው ምን ነበር? ግለሰቡን ወደ ንስሐ መምራት ነው።—ዕብ. 12:11

8. ጳውሎስ ቀጥሎ ለጉባኤው ምን መመሪያ ሰጠ?

8 በመሆኑም ጳውሎስ፣ ኃጢአት የሠራውን ወንድም ‘በደግነት ይቅር እንዲሉትና እንዲያጽናኑት’ እንዲሁም ‘ለእሱ ያላቸውን ፍቅር እንዲያረጋግጡለት’ መመሪያ ሰጠ። ጳውሎስ የፈለገው ወንድሞች ግለሰቡን ወደ ጉባኤው እንዲመልሱት ብቻ አይደለም። ወንድሞች ንስሐ የገባውን ግለሰብ ከልባቸው ይቅር እንዳሉትና እንደሚወዱት በቃላቸውና በተግባራቸው እንዲያረጋግጡለት ፈልጎ ነበር። በዚህ መንገድ፣ ወንድም በመመለሱ በጣም እንደተደሰቱ በግልጽ ያሳያሉ።

9. ምናልባት አንዳንዶች ንስሐ የገባውን ጥፋተኛ ይቅር ለማለት የከበዳቸው ለምን ሊሆን ይችላል?

9 በዚያ ጉባኤ ውስጥ ያሉ አንዳንዶች፣ ንስሐ የገባውን ኃጢአተኛ መልሰው መቀበል ከብዷቸው ይሆን? ዘገባው አይነግረንም፤ ሆኖም እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞ ሊሆን ይችላል። ደግሞም ምግባሩ በመላው ጉባኤ ላይ ችግር አስከትሏል፤ አንዳንድ ግለሰቦችንም ለኀፍረት ዳርጓቸው ሊሆን ይችላል። አንዳንዶች፣ ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናቸውን ለመጠበቅ እየታገሉ ያሉት እነሱ ሆነው ሳለ ይህ ግለሰብ እንዲህ ያለ ሞቅ ያለ አቀባበል ማግኘቱ ምክንያታዊ እንዳልሆነ ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። (ከሉቃስ 15:28-30 ጋር አወዳድር።) ይሁንና ጉባኤው ለተመለሰው ወንድም እውነተኛ ፍቅር ማሳየቱ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

10-11. ሽማግሌዎች ንስሐ የገባውን ኃጢአተኛ ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ካልሆኑ ምን ሊፈጠር ይችላል?

10 ግለሰቡ እውነተኛ ንስሐ ከገባ በኋላ ሽማግሌዎቹ ወደ ጉባኤው እንዳይመለስ ቢከለክሉት ወይም ደግሞ ከተመለሰ በኋላ ጉባኤው ለእሱ ፍቅር ለማሳየት ፈቃደኛ ባይሆን ምን እንደሚከሰት ለማሰብ ሞክር። ግለሰቡ “ከልክ በላይ በሐዘን” ይዋጣል። ምንም ተስፋ እንደሌለው ሊሰማው ይችላል። ከአምላክ ጋር ያለውን ዝምድና ለማደስ ጥረት ማድረጉን ሊያቆምም ይችላል።

11 ይህ ብቻ ሳይሆን፣ በጉባኤው ውስጥ ያሉ ሌሎች ወንድሞችና እህቶች ንስሐ የገባውን ኃጢአተኛ ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ካልሆኑ እነሱ ራሳቸው ከአምላክ ጋር ያላቸውን ወዳጅነት ሊያበላሹ ይችላሉ። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ንስሐ ለገቡ ኃጢአተኞች ምሕረት የሚያሳየውን ይሖዋን ሳይሆን ጨካኝና ምሕረት የለሽ የሆነውን ሰይጣንን መምሰል ይሆንባቸዋል። እንዲህ ካደረጉ፣ ዲያብሎስ ግለሰቡን በመንፈሳዊ ለማጥፋት የሚጠቀምበት መሣሪያ ሊሆኑ ይችላሉ።—2 ቆሮ. 2:10, 11፤ ኤፌ. 4:27

12. ጉባኤው ይሖዋን መምሰል የሚችለው እንዴት ነው?

12 ታዲያ በቆሮንቶስ የነበረው ጉባኤ ሰይጣንን ሳይሆን ይሖዋን መምሰል የሚችለው እንዴት ነው? ይሖዋ ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞችን የሚይዝበትን መንገድ በመኮረጅ ነው። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ስለ ይሖዋ ምን እንዳሉ ልብ በል። ዳዊት “አንተ ጥሩ ነህና፤ ይቅር ለማለትም ዝግጁ ነህ” ብሏል። (መዝ. 86:5) ሚክያስ ደግሞ “[ኃጢአትን] ይቅር የሚል፣ በደላቸውንም የሚያልፍ እንደ አንተ ያለ አምላክ ማን ነው?” በማለት ጽፏል። (ሚክ. 7:18) ኢሳይያስም እንዲህ ብሏል፦ “ክፉ ሰው መንገዱን፣ መጥፎ ሰውም ሐሳቡን ይተው፤ ምሕረት ወደሚያሳየው አምላካችን ወደ ይሖዋ ይመለስ፤ ይቅርታው ብዙ ነውና።”—ኢሳ. 55:7

13. ንስሐ የገባውን ኃጢአተኛ ወደ ጉባኤው መመለስ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው? (“ በቆሮንቶስ የነበረው ሰው ወደ ጉባኤው የተመለሰው መቼ ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

13 በቆሮንቶስ ጉባኤ ውስጥ የነበሩ ወንድሞችና እህቶች ይሖዋን መምሰል ከፈለጉ ንስሐ የገባውን ግለሰብ መቀበልና ለእሱ ያላቸውን ፍቅር ማረጋገጥ ነበረባቸው። የጉባኤው ወንድሞችና እህቶች፣ ጳውሎስ ንስሐ የገባውን ኃጢአተኛ እንዲቀበሉት የሰጠውን መመሪያ በመከተል ‘በሁሉም ነገር ታዛዥ መሆናቸውን አሳይተዋል።’ (2 ቆሮ. 2:9) እውነት ነው፣ ግለሰቡ ከተወገደ በኋላ ያለፉት ጥቂት ወራት ብቻ ናቸው። ሆኖም የተሰጠው ተግሣጽ ወደ ንስሐ መርቶታል። በመሆኑም ወደ ጉባኤው የሚመለስበትን ጊዜ ማዘግየት ምንም ትርጉም የለውም።

የይሖዋን ፍትሕና ምሕረት ማንጸባረቅ

14-15. በጥንቷ ቆሮንቶስ የነበረው ጉዳይ ከተያዘበት መንገድ ምን እንማራለን? (2 ጴጥሮስ 3:9) (ሥዕሉንም ተመልከት።)

14 በጥንቷ ቆሮንቶስ ይህ ጉዳይ ስለተያዘበት መንገድ የሚገልጸው ዘገባ የተጻፈውና ተጠብቆ የቆየው “ለእኛ ትምህርት እንዲሆን” ነው። (ሮም 15:4) ይህ ዘገባ ይሖዋ በሕዝቦቹ መካከል የሚፈጸምን ከባድ ጥፋት በቸልታ እንደማያልፍ ያስተምረናል። ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞች “በምሕረት” ታልፈው ከታማኝ አገልጋዮቹ ጋር መቀራረባቸውን እንዲቀጥሉ አይፈቅድላቸውም። ይሖዋ መሐሪ ቢሆንም ልል አይደለም፤ መሥፈርቱንም ዝቅ አያደርግም። (ይሁዳ 4) ደግሞም እንዲህ ማድረግ ምሕረት ሊባል አይችልም፤ ምክንያቱም በጉባኤው ውስጥ ያሉትን ሁሉ አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል።—ምሳሌ 13:20፤ 1 ቆሮ. 15:33

15 ያም ቢሆን ይሖዋ ማንም እንዲጠፋ እንደማይፈልግ እንማራለን። የሚቻል እስከሆነ ድረስ ሰዎች እንዲድኑ ይፈልጋል። ንስሐ ገብተው ከእሱ ጋር ያላቸውን ዝምድና ማደስ ለሚፈልጉ ሁሉ ምሕረት ያሳያል። (ሕዝ. 33:11፤ 2 ጴጥሮስ 3:9ን አንብብ።) በመሆኑም ይሖዋ በቆሮንቶስ የነበረው ወንድም ንስሐ ገብቶ ከኃጢአት ጎዳናው በተመለሰ ጊዜ ጉባኤው ይቅር ሊለውና መልሶ ሊቀበለው እንደሚገባ በጳውሎስ አማካኝነት ገልጿል።

ጉባኤው ከውገዳ የተመለሱ ክርስቲያኖችን ሞቅ ባለ መንፈስ በመቀበል የይሖዋን ፍቅርና ምሕረት ያንጸባርቃል (አንቀጽ 14-15⁠ን ተመልከት)


16. በቆሮንቶስ የነበረው ጉዳይ ስለተያዘበት መንገድ ምን ይሰማሃል?

16 በቆሮንቶስ የነበረው ጉዳይ የተያዘበትን መንገድ መመርመራችን የይሖዋን ፍቅር፣ ጽድቅና ፍትሕ በግልጽ ለማየት አስችሎናል። (መዝ. 33:5) ይህ አምላካችንን ይበልጥ ለማወደስ አያነሳሳህም? ደግሞም ሁላችንም ኃጢአተኞች ስለሆንን የእሱ ይቅርታ ያስፈልገናል። ይሖዋ ከኃጢአት ይቅርታ የምናገኝበትን ቤዛ ስላዘጋጀልን ሁላችንም አመስጋኝ ልንሆን ይገባል። ይሖዋ ሕዝቡን ከልቡ እንደሚወዳቸውና ከሁሉ የተሻለውን ነገር እንደሚመኝላቸው ማወቃችን ምንኛ ያጽናናናል!

17. በቀጣዮቹ ርዕሶች ውስጥ ምን እንመረምራለን?

17 በዛሬው ጊዜስ ከባድ ጥፋት ሲፈጸም ጉዳዩ እንዴት ሊያዝ ይገባል? የጉባኤ ሽማግሌዎች፣ ይሖዋ ጥፋት የሠሩ ግለሰቦችን ወደ ንስሐ ለመምራት ያለውን ፍላጎት ማንጸባረቅ የሚችሉት እንዴት ነው? ሽማግሌዎች አንድን ግለሰብ ለማስወገድ ወይም ለመመለስ በሚወስኑበት ጊዜ ጉባኤው ምን ምላሽ ሊሰጥ ይገባል? እነዚህ ጥያቄዎች በቀጣዮቹ ርዕሶች ውስጥ ይብራራሉ።

መዝሙር 109 አጥብቃችሁ ከልብ ተዋደዱ