በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኖኅ፣ ዳንኤልና ኢዮብ የተዉትን የእምነትና የታዛዥነት ምሳሌ ተከተሉ

ኖኅ፣ ዳንኤልና ኢዮብ የተዉትን የእምነትና የታዛዥነት ምሳሌ ተከተሉ

“ኖኅ፣ ዳንኤልና ኢዮብ . . . በጽድቃቸው የሚያድኑት ራሳቸውን ብቻ ነው።”—ሕዝ. 14:14

መዝሙሮች፦ 89, 119

1, 2. (ሀ) ኖኅ፣ ዳንኤልና ኢዮብ የተዉት ምሳሌ የብርታት ምንጭ ይሆነናል የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ሕዝቅኤል 14:14 ላይ የሚገኘው ሐሳብ በተጻፈበት ወቅት የነበረውን ሁኔታ ግለጽ።

እንደ ጤና ማጣት፣ የገንዘብ ችግር ወይም ስደት ካሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ጋር እየታገልክ ነው? በይሖዋ አገልግሎት ደስተኛ ሆኖ መቀጠል ፈታኝ የሚሆንብህ ጊዜ አለ? ከሆነ ኖኅ፣ ዳንኤልና ኢዮብ የተዉት ምሳሌ የብርታት ምንጭ ይሆንሃል። እነዚህ ሰዎች ፍጹማን ያልነበሩ ከመሆናቸውም ሌላ ዛሬ በእኛ ላይ እየደረሱ ያሉትን አብዛኞቹን ፈተናዎች ተጋፍጠዋል፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ ፈተናዎች ለሕይወታቸው አስጊ ነበሩ። ያም ሆኖ እስከ መጨረሻው ንጹሕ አቋማቸውን በመጠበቅ በአምላክ ዘንድ የእምነትና የታዛዥነት ምሳሌ ሆነው ለመቆጠር በቅተዋል።—ሕዝቅኤል 14:12-14ን አንብብ።

2 ሕዝቅኤል ይህ የጥናት ርዕስ በተመሠረተበት ጥቅስ ላይ የሚገኘውን ሐሳብ የጻፈው በ612 ዓ.ዓ. በባቢሎን ሆኖ ነበር። * (ሕዝ. 1:1፤ 8:1) አስቀድሞ በተነገረው መሠረት ከሃዲዋ ኢየሩሳሌም የምትጠፋበት ወቅት ማለትም 607 ዓ.ዓ. በጣም ተቃርቦ ነበር። በዚያን ወቅት እንደ ኖኅ፣ ዳንኤልና ኢዮብ ያለ እምነትና ታዛዥነት የነበራቸው እንዲሁም ከጥፋቱ እንዲተርፉ ምልክት የተደረገባቸው ሰዎች ጥቂት ነበሩ። (ሕዝ. 9:1-5) ከእነዚህ መካከል ኤርምያስ፣ ባሮክ፣ ኤቤድሜሌክና ሬካባውያን ይገኙበታል።

3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?

3 ዛሬም ቢሆን ይህ ሥርዓት በሚጠፋበት ጊዜ ከጥፋቱ እንዲተርፉ ምልክት የሚደረግባቸው ይሖዋ ከነቀፋ ነፃ እንደሆኑ የሚቆጥራቸው እንደ ኖኅ፣ ዳንኤልና ኢዮብ ያሉ ሰዎች ብቻ ናቸው። (ራእይ 7:9, 14) በመሆኑም ይሖዋ እነዚህን ሰዎች የጽድቅ ምሳሌ አድርጎ የጠቀሳቸው ለምን እንደሆነ መመርመራችን ጠቃሚ ነው። ስለ እያንዳንዱ ግለሰብ በምንወያይበት ወቅት (1) ግለሰቡ ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንዳጋጠሙት (2) ግለሰቡ የተወውን የእምነትና የታዛዥነት ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን።

ኖኅ ከ900 ለሚበልጡ ዓመታት እምነት እንዳለውና ታዛዥ እንደሆነ አሳይቷል

4, 5. ኖኅ ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመውታል? ያሳየው ጽናት አስደናቂ የሆነውስ ለምንድን ነው?

4 ኖኅ ያጋጠሙት ተፈታታኝ ሁኔታዎች። የኖኅ ቅድመ አያት በሆነው በሄኖክ ዘመን የነበሩት ሰዎች ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ነበሩ። ሌላው ቀርቶ በይሖዋ ላይ “ክፉ ቃል” ይናገሩ ነበር። (ይሁዳ 14, 15) ዓመፅ ከዕለት ወደ ዕለት እየተስፋፋ ነበር። እንዲያውም በኖኅ ዘመን ምድር “በዓመፅ ተሞልታ ነበር።” ክፉ መላእክት ሥጋ ለብሰው ወደ ምድር በመምጣት የሰውን ሴቶች ልጆች ያገቡ ሲሆን ጨካኝ የሆኑ የሰውና የመላእክት ዲቃላዎችን ወለዱ። (ዘፍ. 6:2-4, 11, 12) ኖኅ ግን በዘመኑ ካሉት ሰዎች የተለየ አቋም ነበረው። “በይሖዋ ፊት ሞገስ [ያገኘ]” ከመሆኑም ሌላ “በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች መካከል እሱ እንከን የሌለበት ሰው ነበር። ኖኅ ከእውነተኛው አምላክ ጋር ይሄድ ነበር።”—ዘፍ. 6:8, 9

5 እስቲ ይህ ምን ማለት እንደሆነ ለማሰብ ሞክር። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ኖኅ ከጥፋት ውኃ በፊት በነበረው በዓመፅ የተሞላ ዓለም ውስጥ ከአምላክ ጋር የሄደው በዛሬው ጊዜ ያለውን የሰው ልጅ ዕድሜ ያህል ማለትም ለ70 ወይም ለ80 ዓመት ብቻ አልነበረም። በዚያ ዓለም ውስጥ ለ600 ዓመታት ያህል ኖሯል! (ዘፍ. 7:11) በተጨማሪም ኖኅ ልክ እንደ እኛ የሚደግፉትና የሚያበረታቱት የእምነት ባልንጀሮች አልነበሩትም፤ ከሁኔታዎች መረዳት እንደምንችለው የገዛ ወንድሞቹና እህቶቹም እንኳ መንፈሳዊ ድጋፍ አላደረጉለትም። *

6. ኖኅ ድፍረት እንደነበረው ያሳየው እንዴት ነው?

6 ኖኅ ጥሩ ሰው መሆኑ ብቻ በቂ እንደሆነ አልተሰማውም። ከዚህ ይልቅ ደፋር “የጽድቅ ሰባኪ” በመሆን በይሖዋ ላይ ያለውን እምነት በይፋ ይናገር ነበር። (2 ጴጥ. 2:5) ሐዋርያው ጳውሎስ ኖኅን አስመልክቶ ሲናገር “በዚህ እምነት አማካኝነትም ዓለምን ኮንኗል” በማለት ጽፏል። (ዕብ. 11:7) ኖኅ በዚህ አቋሙ የተነሳ ፌዝና ተቃውሞ አልፎ ተርፎም የኃይል ጥቃት አጋጥሞታል ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ ነው። ያም ሆኖ ‘በሰው ፍርሃት’ አልተሸነፈም። (ምሳሌ 29:25) ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ለታማኝ አገልጋዮቹ የሚሰጠው ድፍረት እንደነበረው አሳይቷል።

7. ኖኅ መርከቡን በሚሠራበት ወቅት ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመውታል?

7 ኖኅ ከ500 ለሚበልጡ ዓመታት ለአምላክ ታማኝ ሆኖ ከኖረ በኋላ ይሖዋ የሰዎችንና የእንስሳትን ሕይወት ለማትረፍ የሚያስችል መርከብ እንዲሠራ ትእዛዝ ሰጠው። (ዘፍ. 5:32፤ 6:14) ይህ ሥራ ለኖኅ ምን ያህል ከባድ እንደነበር መገመት እንችላለን! ሥራውን ተፈታታኝ የሚያደርግበት የግንባታው ክብደት ብቻ አልነበረም። ኖኅ ይህ ሥራ ለተጨማሪ ፌዝና ተቃውሞ እንደሚያጋልጠው ያውቅ ነበር። ያም ቢሆን በእምነት የይሖዋን ትእዛዝ ፈጽሟል። ዘገባው “ልክ እንደዚሁ አደረገ” ይላል።—ዘፍ. 6:22

8. ኖኅ የሚያስፈልገውን ነገር ይሖዋ እንደሚያሟላለት እምነት እንዳለው ያሳየው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

8 ኖኅ የነበረበት ሌላው ተፈታታኝ ነገር ደግሞ የሚስቱንና የልጆቹን ቁሳዊ ፍላጎት ማሟላት ነበር። ከጥፋት ውኃው በፊት ሰዎች የሚመገቡትን እህል ለማምረት ከፍተኛ ልፋት ይጠይቅባቸው ነበር፤ ለኖኅም ቢሆን ሁኔታው ከዚህ የተለየ አልነበረም። (ዘፍ. 5:28, 29) ያም ሆኖ ሕይወቱ በቁሳዊ ነገሮች ላይ ሳይሆን በአምላክ ላይ ያተኮረ ነበር። መርከቡን በመገንባት ባሳለፋቸው 40 ወይም 50 ዓመታትም እንኳ መንፈሳዊነቱን ጠብቆ ቆይቷል። ከጥፋት ውኃው በኋላም ለ350 ዓመታት ያህል በዚህ አቋሙ ቀጥሏል። (ዘፍ. 9:28) እንዴት ያለ የእምነትና የታዛዥነት ምሳሌ ነው!

9, 10. (ሀ) ኖኅ የተወውን የእምነትና የታዛዥነት ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶቹን ለሚጠብቁ ሰዎች ምን አመለካከት አለው?

9 ኖኅ የተወውን የእምነትና የታዛዥነት ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶች በመደገፍ፣ የሰይጣን ዓለም ክፍል ባለመሆንና ከመንግሥቱ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ቅድሚያ በመስጠት ነው። (ማቴ. 6:33፤ ዮሐ. 15:19) እርግጥ ነው፣ የመረጥነው የሕይወት ጎዳና በዓለም ዘንድ ተቀባይነት እንደማያስገኝልን የታወቀ ነው። እንዲያውም እንደ ጋብቻና የፆታ ሥነ ምግባር ካሉ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ አምላክ ያወጣቸውን ሕጎች ለመጠበቅ በወሰድነው ቁርጥ አቋም የተነሳ በአንዳንድ አገሮች ያሉ መገናኛ ብዙኃን መጥፎ ስም ሰጥተውናል። (ሚልክያስ 3:17, 18ን አንብብ።) ሆኖም እኛም ልክ እንደ ኖኅ ይሖዋን እንጂ ሰዎችን አንፈራም። የዘላለም ሕይወት ሊሰጠን የሚችለው እሱ ብቻ እንደሆነ እናውቃለን።—ሉቃስ 12:4, 5

10 አንተስ በግለሰብ ደረጃ የኖኅን ምሳሌ መከተል የምትችለው እንዴት ነው? ሌሎች በሚያሾፉብህ ወይም በሚነቅፉህ ጊዜም ‘ከአምላክ ጋር መሄድህን’ ትቀጥላለህ? የኢኮኖሚ ችግር ቢያጋጥምህም ይሖዋ የሚያስፈልግህን ነገር እንደሚያሟላልህ ትተማመናለህ? ኖኅ የተወውን የእምነትና የታዛዥነት ምሳሌ የምትከተል ከሆነ ይሖዋ እንደሚንከባከብህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።—ፊልጵ. 4:6, 7

ዳንኤል በክፋት በተሞላች ከተማ ውስጥ እምነት እንዳለውና ታዛዥ እንደሆነ አሳይቷል

11. ዳንኤልና ሦስቱ ጓደኞቹ በባቢሎን ምን ከባድ ፈተናዎች አጋጥመዋቸዋል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

11 ዳንኤል ያጋጠሙት ተፈታታኝ ሁኔታዎች። ዳንኤል በግዞት ይኖርባት የነበረችው የባቢሎን ከተማ በጣዖት አምልኮና በመናፍስታዊ ድርጊቶች የተሞላች ነበረች። በተጨማሪም ባቢሎናውያን አይሁዳውያንን ይንቋቸው የነበረ ከመሆኑም ሌላ በእነሱና በአምላካቸው በይሖዋ ላይ ይሳለቁ ነበር። (መዝ. 137:1, 3) ይህ እንደ ዳንኤል ያሉ ታማኝ አይሁዳውያንን ስሜት ምንኛ ጎድቶት ይሆን! ከዚህም ሌላ ዳንኤል እንዲሁም ሃናንያህ፣ ሚሳኤልና አዛርያስ የተባሉት ሦስት ጓደኞቹ ንጉሡን ለማገለገል እየሠለጠኑ ስለነበር የሰዉን ሁሉ ትኩረት ስበው መሆን አለበት። ሌላው ቀርቶ መመገብ የሚችሉት እንኳ የተመረጠላቸውን ምግብ ብቻ ነበር። ሆኖም ዳንኤል “በንጉሡ ምርጥ ምግብ ወይም በሚጠጣው የወይን ጠጅ ላለመርከስ” ወስኖ ነበር፤ በመሆኑም እነዚህ ወጣቶች ከምግብና ከመጠጥ ጋር በተያያዘም ተፈታታኝ ሁኔታ አጋጥሟቸዋል።—ዳን. 1:5-8, 14-17

12. (ሀ) ዳንኤል የትኞቹን ግሩም ባሕርያት አንጸባርቋል? (ለ) ይሖዋ ለዳንኤል ምን አመለካከት ነበረው?

12 ዳንኤል ስውር የሆነ ፈተናም አጋጥሞታል፤ ለየት ያለ ችሎታ ስለነበረው ከፍተኛ ኃላፊነት ተሰጥቶት ነበር። (ዳን. 1:19, 20) ሆኖም ዳንኤል ትዕቢተኛና ግትር ከመሆን ይልቅ ምንጊዜም ክብር የሚገባው ይሖዋ እንደሆነ በመናገር ትሑትና ልኩን የሚያውቅ ሰው እንደሆነ አሳይቷል። (ዳን. 2:30) የሚገርመው ነገር፣ ይሖዋ ዳንኤልን የጽድቅ ምሳሌ አድርጎ ከኖኅና ከኢዮብ ጋር የጠቀሰው ዳንኤል ገና ወጣት ሳለ ነበር። አምላክ በዳንኤል ላይ ይህን ያህል እምነት መጣሉ ተገቢ ነበር? እንዴታ! ዳንኤል እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ እምነት እንዳለውና ታዛዥ እንደሆነ አሳይቷል። የአምላክ መልአክ “እጅግ የተወደድክ ዳንኤል ሆይ” ብሎ ባነጋገረው ወቅት ዳንኤል በ90ዎቹ መጨረሻ አካባቢ የሚገኝ አረጋዊ ሳይሆን አይቀርም።—ዳን. 10:11

13. ዳንኤል ለአይሁዳውያን በረከት የሆነው በምን መንገድ ሊሆን ይችላል?

13 ዳንኤል የአምላክ ሞገስ ስላልተለየው በመጀመሪያ በባቢሎን ከዚያም በሜዶ ፋርስ ግዛት ውስጥ ከፍተኛ ባለሥልጣን ሆኖ ተሹሞ ነበር። (ዳን. 1:21፤ 6:1, 2) ምናልባትም በግብፅ እንደነበረው እንደ ዮሴፍ እንዲሁም በፋርስ እንደነበሩት እንደ አስቴርና እንደ መርዶክዮስ ሁሉ ዳንኤልንም እዚህ ቦታ ላይ በማስቀመጥ ለሕዝቡ በረከት እንዲሆን ሁኔታዎችን ያመቻቸው ይሖዋ ሊሆን ይችላል። * (ዳን. 2:48) ሕዝቅኤልን ጨምሮ በግዞት የነበሩት አይሁዳውያን በዚህ መንገድ የይሖዋን እጅ በማየታቸው ምንኛ ተጽናንተው ይሆን!

ይሖዋ ንጹሕ አቋማቸውን የሚጠብቁ ሰዎችን ውድ አድርጎ ይመለከታቸዋል (አንቀጽ 14, 15⁠ን ተመልከት)

14, 15. (ሀ) እኛ ያለንበት ሁኔታ ዳንኤል ከነበረበት ሁኔታ ጋር የሚመሳሰለው በየትኞቹ መንገዶች ነው? (ለ) በዛሬው ጊዜ ያሉ ወላጆች የዳንኤል ወላጆች ከተዉት ምሳሌ ትምህርት ማግኘት የሚችሉት እንዴት ነው?

14 ዳንኤል የተወውን የእምነትና የታዛዥነት ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? የምንኖርበት ዓለም “የአጋንንት መኖሪያ” የሆነችውና በዓለም ላይ ያሉ የሐሰት ሃይማኖቶችን በሙሉ የምትወክለው ታላቂቱ ባቢሎን በምታሳድረው ተጽዕኖ የተነሳ በሥነ ምግባራዊም ሆነ በመንፈሳዊ ሁኔታ የተበላሸ ነው፤ ከዚህ አንጻር እኛም የምንኖረው በባዕድ አገር ውስጥ ነው ሊባል ይችላል። (ራእይ 18:2) በመሆኑም ከሌሎች ለየት ብለን ልንታይ አልፎ ተርፎም ሰዎች ሊያፌዙብን ይችላሉ። (ማር. 13:13) ስለዚህ ልክ እንደ ዳንኤል አምላካችን ወደሆነው ወደ ይሖዋ መቅረባችን አስፈላጊ ነው። ትሑትና ታዛዥ በመሆን በእሱ የምንታመን ከሆነ ይሖዋ ልክ እንደ ዳንኤል ውድ አድርጎ ይመለከተናል።—ሐጌ 2:7 ግርጌ

15 በዛሬው ጊዜ ያሉ ወላጆችም የዳንኤል ወላጆች ከተዉት ምሳሌ ትምህርት ማግኘት ይችላሉ። እንዴት? ዳንኤል ልጅ በነበረበት ጊዜ በይሁዳ ውስጥ ክፋት ተስፋፍቶ የነበረ ቢሆንም ዳንኤል ከልጅነቱ ጀምሮ ለአምላክ ፍቅር አዳብሯል። ይህ እንዲሁ በአጋጣሚ የሆነ ነገር አይደለም። ወላጆቹ ጥሩ አድርገው እንዳሠለጠኑት የሚያሳይ ነው። (ምሳሌ 22:6) “አምላክ ፈራጄ ነው” የሚል ትርጉም ያለው የዳንኤል ስም ራሱ ወላጆቹ አምላክን የሚፈሩ ሰዎች እንደነበሩ ይጠቁማል። (ዳን. 1:6 ግርጌ) ስለዚህ ወላጆች፣ በልጆቻችሁ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ በትዕግሥት አስተምሯቸው። (ኤፌ. 6:4) በተጨማሪም አብራችኋቸው ጸልዩ፤ ለእነሱም ጸልዩላቸው። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች በልጆቻችሁ ልብ ውስጥ ለመቅረጽ ጥረት ስታደርጉ የይሖዋ የተትረፈረፈ በረከት እንደማይለያችሁ እርግጠኞች መሆን ትችላላችሁ።—መዝ. 37:5

ኢዮብ በጥሩውም ሆነ በመጥፎው ወቅት እምነት እንዳለውና ታዛዥ እንደሆነ አሳይቷል

16, 17. ኢዮብ በጥሩውም ሆነ በመጥፎው ወቅት ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመውታል?

16 ኢዮብ ያጋጠሙት ተፈታታኝ ሁኔታዎች። ኢዮብ በሕይወቱ ውስጥ ትልቅ ለውጥ አጋጥሞታል። ከፈተናው በፊት “በምሥራቅ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይበልጥ ታላቅ ሰው” ነበር። (ኢዮብ 1:3) እንዲሁም ባለጸጋ፣ የታወቀና እጅግ የተከበረ ሰው ነበር። (ኢዮብ 29:7-16) ኢዮብ ከፍ ያለ ቦታ የነበረው ቢሆንም ለራሱ የተጋነነ አመለካከት አልነበረውም፤ እንዲሁም አምላክ እንደማያስፈልገው አልተሰማውም። እንዲያውም ይሖዋ “አገልጋዬ” ብሎ የጠራው ሲሆን “በንጹሕ አቋም የሚመላለስ ቅን ሰው እንዲሁም አምላክን የሚፈራና ከክፋት የራቀ” በማለት መሥክሮለታል።—ኢዮብ 1:8

17 ይሁንና የኢዮብ ሕይወት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተለወጠ። በከባድ ድህነት ውስጥ የተዘፈቀ ከመሆኑም ሌላ በተስፋ መቁረጥ ስሜት ተዋጠ። እንደምናውቀው የዚህ ሁሉ መከራ መንስኤ ስም አጥፊ የሆነው ሰይጣን ነው፤ ሰይጣን፣ ኢዮብ አምላክን የሚያመልከው ለግል ጥቅሙ ሲል እንደሆነ በመናገር የሐሰት ክስ ሰንዝሮበታል። (ኢዮብ 1:9, 10ን አንብብ።) ይሖዋ ይህን ተንኮል ያዘለ ክስ በቸልታ አላለፈውም። ከዚህ ይልቅ ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን በመጠበቅ እሱን የሚያመልከው በንጹሕና ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ልብ ተነሳስቶ እንደሆነ ማረጋገጥ የሚችልበት አጋጣሚ ሰጥቶታል።

18. (ሀ) ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን መጠበቁ የሚያስደንቅህ ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ኢዮብን የያዘበት መንገድ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል?

18 ሰይጣን ጭካኔ የተሞላባቸው ጥቃቶች በኢዮብ ላይ በማዥጎድጎድ ኢዮብ መከራ የሚያደርስበት አምላክ እንደሆነ እንዲያስብ ለማድረግ ሞክሯል። (ኢዮብ 1:13-21) ከዚያም ሦስቱ የሐሰት አጽናኞች ወደ እሱ ቀርበው አምላክ የእጁን እየሰጠው እንዳለ በሚያስመስሉ ቅስም የሚሰብሩ ቃላት ጥቃት ሰነዘሩበት! (ኢዮብ 2:11፤ 22:1, 5-10) ይሁንና ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን ጠብቋል። እርግጥ ነው፣ ኢዮብ እንዳመጣለት የተናገረባቸው ጊዜያት ነበሩ፤ ሆኖም ይሖዋ፣ ኢዮብ በዚህ መንገድ የተናገረው ከደረሰበት ሥቃይና ከነበረበት ጭንቀት የተነሳ እንደሆነ ተረድቶለት ነበር። (ኢዮብ 6:1-3) ሰይጣን በኢዮብ ላይ ብዙ ችግሮች ማድረሱ አልበቃ ብሎት መርዘኛ በሆኑ ቃላት ስሜቱን ደቁሶታል፤ ይሖዋ ግን ኢዮብ ፈጽሞ ጀርባውን እንዳልሰጠው ተገንዝቧል። ፈተናው ካበቃ በኋላ ይሖዋ ለኢዮብ ከዚያ በፊት የነበረውን ሁሉ እጥፍ አድርጎ የሰጠው ሲሆን በዕድሜው ላይ 140 ዓመት ጨምሮለታል። (ያዕ. 5:11) በእነዚያ ዓመታት ሁሉ ኢዮብ ይሖዋን በሙሉ ልቡ ማምለኩን ቀጥሏል። ይህን እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን? ሕዝቅኤል ይህ የጥናት ርዕስ የተመሠረተበትን ጥቅስ የጻፈው ኢዮብ ከሞተ ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ መሆኑ ይህን ያሳያል።

19, 20. (ሀ) ኢዮብ የተወውን የእምነትና የታዛዥነት ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት እንደ አምላክ ሩኅሩኅ መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

19 ኢዮብ የተወውን የእምነትና የታዛዥነት ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን በሕይወታችን ውስጥ ከሁሉ የላቀውን ቦታ ለይሖዋ በመስጠት ነው፤ ምንጊዜም በእሱ መታመንና በሙሉ ልባችን እሱን መታዘዝ ይኖርብናል። ደግሞም እኛ ከኢዮብ አንጻር ሲታይ እንዲህ ለማድረግ የሚያነሳሱ ተጨማሪ ምክንያቶች አሉን! እስቲ አስቡት፦ ስለ ሰይጣንና እሱ ስለሚጠቀምባቸው ዘዴዎች ብዙ ነገር እናውቃለን። (2 ቆሮ. 2:11) መጽሐፍ ቅዱስ በተለይም የኢዮብ መጽሐፍ በእጃችን ስላለ አምላክ በሰዎች ላይ መከራ እንዲደርስ የፈቀደበትን ምክንያት መረዳት ችለናል። በተጨማሪም የአምላክ መንግሥት በክርስቶስ ኢየሱስ የሚመራ ዓለም አቀፋዊ መስተዳድር እንደሆነ ከዳንኤል ትንቢት ተገንዝበናል። (ዳን. 7:13, 14) ይህ መንግሥት የሚደርሱብንን መከራዎች ሁሉ በቅርቡ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚያስወግድም እናውቃለን።

20 የኢዮብ ታሪክ መከራ እየደረሰባቸው ላሉ የእምነት ባልንጀሮቻችን ርኅራኄ ልናሳያቸው እንደሚገባም ያጎላል። አንዳንዶች ልክ እንደ ኢዮብ እንዳመጣላቸው የሚናገሩበት ጊዜ ይኖራል። (መክ. 7:7) በዚህ ጊዜ በእነሱ ላይ ከመፍረድ ይልቅ አስተዋይ በመሆን ርኅራኄ ልናሳያቸው ይገባል። እንዲህ በማድረግ አፍቃሪና መሐሪ የሆነውን አባታችንን ይሖዋን መምሰል እንችላለን።—መዝ. 103:8

ይሖዋ “ያጠነክራችኋል”

21. በ1 ጴጥሮስ 5:10 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ከኖኅ፣ ከዳንኤልና ከኢዮብ ጋር በተያያዘ እውነት መሆኑ የታየው እንዴት ነው?

21 ኖኅ፣ ዳንኤልና ኢዮብ የኖሩበት ዘመንም ሆነ የነበሩበት ሁኔታ ፈጽሞ የተለያየ ቢሆንም ሁሉም የደረሰባቸውን ፈተና በጽናት ተቋቁመዋል። የእነዚህ ሰዎች ታሪክ ሐዋርያው ጴጥሮስ የጻፈውን የሚከተለውን ሐሳብ ያስታውሰናል፦ “የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራ ከተቀበላችሁ በኋላ እሱ ራሱ ሥልጠናችሁ እንዲጠናቀቅ ያደርጋል። ጽኑ እንድትሆኑ ያደርጋችኋል፤ ደግሞም ያጠነክራችኋል፤ አጽንቶም ያቆማችኋል።”—1 ጴጥ. 5:10

22. በቀጣዩ ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

22 ጴጥሮስ በመንፈስ መሪነት የጻፈው ሐሳብ ይሖዋ አገልጋዮቹን ጽኑና ጠንካራ እንደሚያደርጋቸው ማረጋገጫ ይሰጠናል። ይህ ጥቅስ በዛሬው ጊዜ ካሉ የአምላክ ሕዝቦች ጋር በተያያዘም ይሠራል። ሁላችንም ይሖዋ እንዲያጠነክረን እንፈልጋለን፤ እንዲሁም ምኞታችን ለእሱ በምናቀርበው አምልኮ እስከ መጨረሻው መጽናት ነው። እንግዲያው ኖኅ፣ ዳንኤልና ኢዮብ የተዉትን የእምነትና የታዛዥነት ምሳሌ ለመከተል ጥረት እናድርግ! በቀጣዩ ርዕስ ላይ እንደምንመለከተው እነዚህ ሰዎች ንጹሕ አቋማቸውን እንዲጠብቁ የረዳቸው ዋነኛው ነገር ይሖዋን በሚገባ ማወቃቸው ነው። ይሖዋ ከእነሱ የሚፈልገውን “[ሁሉንም] ነገር መረዳት” ችለዋል። (ምሳሌ 28:5) እኛም እንዲሁ ማድረግ እንችላለን።

^ አን.2 ሕዝቅኤል በግዞት ወደ ባቢሎን የተወሰደው በ617 ዓ.ዓ. ነበር። ሕዝቅኤል 8:1–19:14 የተጻፈው ሕዝቅኤል በግዞት በተወሰደ ‘በስድስተኛው ዓመት’ ማለትም በ612 ዓ.ዓ. ነው።

^ አን.5 የኖኅ አባት ላሜህ አምላክን ይፈራ የነበረ ሲሆን የሞተው ከጥፋት ውኃው አምስት ዓመት ቀደም ብሎ ነው። የኖኅ እናት እንዲሁም ወንድሞቹና እህቶቹ የጥፋት ውኃው በጀመረበት ወቅት በሕይወት ከነበሩ ከጥፋት ውኃው አልተረፉም ማለት ነው።

^ አን.13 ከፍተኛ ሥልጣን ከተሰጣቸው ከሦስቱ የዳንኤል ጓደኞች ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል።—ዳን. 2:49