በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከታሪክ ማኅደራችን

የሕዝብ ንግግሮች አየርላንድ ውስጥ ምሥራቹን አስፋፉ

የሕዝብ ንግግሮች አየርላንድ ውስጥ ምሥራቹን አስፋፉ

ወቅቱ ግንቦት 1910 ነው። መርከቧ ቤልፋስት ላክ የተባለውን ባሕረ ሰላጤ እየሰነጠቀች ወደ ወደቡ ስትጠጋ በማለዳዋ ፀሐይ ያሸበረቁ አረንጓዴ ኮረብቶች ከርቀት ይታዩ ጀመር። ከተሳፋሪዎቹ አንዱ የሆነው ቻርልስ ቴዝ ራስል ወደ አየርላንድ ለአምስተኛ ጊዜ መምጣቱ ነው። የባሕሩ ዳርቻ አካባቢ፣ ታይታኒክ እና ኦሎምፒክ * የተባሉት ግዙፍ መርከቦች ሲገነቡ ይታይ ነበር። መርከቦቹ ከሚሠሩበት ቦታ ባሻገር የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የወንድም ራስልን መምጣት እየተጠባበቁ ቆመዋል።

ወንድም ራስል ይህን ጉዞ ከማድረጉ ከ20 ዓመታት በፊት፣ ምሥራቹን በዓለም ዙሪያ ለማሰራጨት ሲል ከአሜሪካ ውጭ ወደተለያዩ የዓለም ክፍሎች ጉዞዎችን ለማድረግ ወስኖ ነበር። የመጀመሪያ ጉዞውን ያደረገው ሐምሌ 1891 ሲሆን የሄደውም ወደ አየርላንድ ነው። ወንድም ራስል ሲቲ ኦቭ ቺካጎ በተባለችው መርከብ ተሳፍሮ ወደ ኩዊንስታውን ሲቃረብ እያሽቆለቆለች ያለችውን ጀምበር ተመለከተ፤ በዚህ ወቅት ወላጆቹ ስለ ትውልድ አገራቸው ያወሩለትን ነገር ሳያስታውስ አልቀረም። ራስልና በጉዞው ላይ አብረውት የነበሩት ወንድሞች፣ ንጹሕ በሆኑት የከተማ ጎዳናዎችና ውብ በሆኑት የገጠር መንደሮች ሲዘዋወሩ “ለመሰብሰብ የደረሰ አዝመራ” እንዳለ ማስተዋል ችለው ነበር።

ወንድም ራስል ወደ አየርላንድ በአጠቃላይ ሰባት ጊዜ ሄዷል። በመጀመሪያ ጉዞው ወቅት ያቀረበው ንግግር የሕዝቡን የማወቅ ፍላጎት ስለቀሰቀሰው ከዚያ በኋላ በሄደባቸው ጊዜያት ንግግሩን ለማዳመጥ በመቶዎች፣ አንዳንድ ጊዜም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይገኙ ነበር። ግንቦት 1903 ባደረገው በሁለተኛው ጉዞው ወቅት፣ በቤልፋስትና በደብሊን ስለሚካሄዱት የሕዝብ ስብሰባዎች በአካባቢው ጋዜጦች ላይ ማስታወቂያ ወጥቶ ነበር። “በመሐላ የተረጋገጠው የተስፋ ቃል” በሚል ርዕስ ስለ አብርሃም እምነትና የሰው ዘር ወደፊት ስለሚያገኛቸው በረከቶች የቀረበውን ንግግር “የተሰበሰበው ሕዝብ በተመስጦ ያዳምጥ እንደነበረ” ራስል ተናግሯል።

በአየርላንድ ብዙዎች ለመልእክቱ ከፍተኛ ፍላጎት በማሳየታቸው ራስል ወደ አውሮፓ ሦስተኛው ጉዞውን ሲያደርግ ወደ አየርላንድም ሄዶ ነበር። ሚያዝያ 1908 ማለዳ ላይ ቤልፋስት ወደብ ሲደርስ አምስት ወንድሞች ተቀበሉት። “የሰይጣን አገዛዝ መውደቅ” በሚል ርዕስ የሕዝብ ንግግር እንደሚቀርብ ማስታወቂያ ተነግሮ ነበር፤ ራስል በዚያ ምሽት ንግግሩን ሲያቀርብ 300 ገደማ የሚሆኑ ተሰብሳቢዎች ተገኝተው ነበር። በመካከላቸው ለነበረ አንድ ተቃዋሚ ከቅዱሳን መጻሕፍት ጥሩ መልስ ተሰጥቶታል። ደብሊን ውስጥ ደግሞ ሚስተር ኦካነር የተባለ የወወክማ (የወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር) ጸሐፊ፣ ከ1,000 የሚበልጡትን ተሰብሳቢዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ላይ ለማሳመፅ ቆርጦ ተነስቶ ነበር። በወቅቱ የነበረው ሁኔታ ምን ይመስል ነበር?

በዚያ ወቅት ተፈጽሞ ሊሆን የሚችለውን ነገር በዓይነ ሕሊናችን ለመሳል እስቲ እንሞክር። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የማግኘት ፍላጎት ያለው አንድ ሰው ዚ አይሪሽ ታይምስ ላይ ስለ አንድ የሕዝብ ስብሰባ የወጣውን ማስታወቂያ ይመለከታል፤ ከዚያም ንግግሩን ለማዳመጥ ይወስናል። የስብሰባው አዳራሽ ጢም ብሎ ስለሞላ ወንበር ለማግኘት ተቸግሮ ነበር። መቀመጫ ካገኘ በኋላ፣ ረጅም ጥቁር ኮት የለበሰውና ሸበቶ የሆነው ተናጋሪ የሚያቀርበውን ንግግር በተመስጦ ያዳምጣል። ተናጋሪው አካላዊ መግለጫዎችን እየተጠቀመና በመድረኩ ላይ ከአንዱ ጫፍ ወደ ሌላው ጫፍ እየተዘዋወረ ንግግሩን ሲያቀርብ ለትምህርቱ ድጋፍ የሚሆኑ ጥቅሶችን ጥሩ አድርጎ ይጠቅሳል፤ በመሆኑም ሰውየው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ማስተዋል ቻለ። ተናጋሪው የድምፅ ማጉያ መሣሪያ ባይጠቀምም ድምፁ በአዳራሹ ውስጥ ከዳር እስከ ዳር ስለሚሰማ አንድ ሰዓት ተኩል የወሰደውን ንግግሩን አድማጮቹ በትኩረት ተከታተሉት። ከዚያም በጥያቄና መልስ ክፍለ ጊዜ ላይ ኦካነርና ጓደኞቹ ተናጋሪውን በጥያቄ ለማፋጠጥ ሞከሩ፤ ተናጋሪው ግን መጽሐፍ ቅዱስን በመጠቀም አጥጋቢ መልስ ሰጣቸው። በዚህ ጊዜ አድማጮቹ አድናቆታቸውን በጭብጨባ ገለጹ። ሁኔታው ሲረጋጋ፣ ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ፍላጎት ያሳየው ሰው ተጨማሪ ነገር ለመማር ወደ ወንድሞች ቀርቦ አነጋገራቸው። በወቅቱ የነበሩ ሰዎች እንደሚናገሩት ብዙዎች እውነትን የተማሩት በዚህ መንገድ ነበር።

ወንድም ራስል ግንቦት 1909 ወደ አየርላንድ ለአራተኛ ጊዜ ለመጓዝ ሞሪቴኒያ በተባለችው መርከብ ተሳፍሮ ከኒው ዮርክ ተነሳ፤ በዚህ ጉዞው ላይ የአጭር ጽሕፈት ባለሙያ የሆነው ወንድም ሀንትሲንገር አብሮት ነበረ፤ ራስል ይህ ወንድም አብሮት እንዲሄድ ያደረገው ውቅያኖሱን አቋርጠው በሚጓዙበት ወቅት፣ መጠበቂያ ግንብ ላይ የሚወጡ ርዕሶችን ለወንድም ሀንትሲንገር እየነገረ ሊያስጽፈው ስላሰበ ነው። ወንድም ራስል በቤልፋስት ያቀረበውን የሕዝብ ንግግር ለማዳመጥ 450 የአካባቢው ሰዎች ተሰብስበው ነበር፤ ከእነሱ መካከል 100 የሚሆኑት አዳራሹ በመሙላቱ ምክንያት ቆመው ለማዳመጥ ተገድደዋል።

ወንድም ቻርልስ ቴዝ ራስል ሉሲቴኒያ ላይ ተሳፍሮ

ወንድም ራስል በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ በተጠቀሰው በአምስተኛው ጉዞው ወቅትም ለተቃዋሚዎቹ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መልስ ሰጥቷል። በደብሊን የሕዝብ ንግግር ከቀረበ በኋላ፣ ከኦካነር ጋር የመጣ አንድ የታወቀ የሃይማኖት ምሁር ላነሳቸው ጥያቄዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ መልሶች ተሰጡት፤ በቦታው የነበሩት አድማጮች ይህን ማየታቸው አስደስቷቸዋል። በቀጣዩ ቀን ተጓዦቹ በፈጣን የፖስታ አመላላሽ ጀልባ ወደ ሊቨርፑል ሄዱ፤ ከዚያም ሉሲቴኒያ በተባለችው ዝነኛ መርከብ ላይ ተሳፍረው ወደ ኒው ዮርክ አቀኑ። *

የግንቦት 20, 1910 ዚ አይሪሽ ታይምስ ላይ የወጣ የሕዝብ ንግግር ማስታወቂያ

ወንድም ራስል በ1911 ባደረጋቸው በስድስተኛውና በሰባተኛው ጉዞዎቹ ወቅትም ስለሚያቀርባቸው የሕዝብ ንግግሮች በጋዜጦች ማስታወቂያ ወጥቶ ነበር። ሚያዝያ ላይ በቤልፋስት የሚገኙ 20 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች “ከሞት በኋላ” የተሰኘውን ንግግር ለማዳመጥ የመጡ 2,000 ሰዎችን አስተናግደዋል። በደብሊን፣ ኦካነር ሌላ ቄስ ይዞ በመምጣት ጥያቄዎች ያነሱ ሲሆን ቅዱስ ጽሑፋዊ መልሶች ተሰጥቷቸዋል፤ አድማጮቹም አድናቆታቸውን በጭብጨባ ገልጸዋል። ወንድም ራስል በዚያው ዓመት ጥቅምትና ኅዳር ላይ ሌሎች ከተሞችንም ጎበኘ፤ በስብሰባዎቹም ላይ በርካታ አድማጮች ተገኝተው ነበር። ኦካነርና አብረውት የመጡት 100 ሥርዓት አልበኞች የደብሊኑን ስብሰባ ለመረበሽ በድጋሚ ሙከራ ቢያደርጉም ተሰብሳቢዎቹ ተናጋሪውን እንደሚደግፉ አሳይተዋል።

በዚያ ወቅት በዋነኝነት የሕዝብ ንግግሮቹን ያቀርብ የነበረው ወንድም ራስል ነበር፤ ያም ቢሆን ራስል “ምትክ የሌለው የሚባል ሰው እንደሌለ” ተገንዝቦ ነበር፤ ምክንያቱም “ይህ የአምላክ እንጂ የሰው ሥራ አይደለም።” በዛሬው ጊዜ ላለው ሕዝባዊ ስብሰባ ፈር ቀዳጅ የሆኑት በጋዜጦች የሚተዋወቁ የሕዝብ ንግግሮች፣ ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነቶችን ለማስተማር ግሩም አጋጣሚ ፈጥረዋል። ውጤቱስ ምን ነበር? የሕዝብ ንግግሮች ምሥራቹን ለማሰራጨት ስላስቻሉ በመላው አየርላንድ ባሉ በርካታ ከተሞች ውስጥ ጉባኤዎች ተቋቁመዋል።—በብሪታንያ ካለው የታሪክ ማኅደራችን

^ አን.3 ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ታይታኒክ ሰጥማለች።

^ አን.9 ሉሲቴኒያ ግንቦት 1915 በአየርላንድ ደቡባዊ የባሕር ዳርቻ አቅራቢያ በባሕር ሰርጓጅ መርከብ ተመትታ ሰጥማለች።