የጥናት ርዕስ 7
የዋህነትን በመፈለግ ይሖዋን ደስ አሰኙ
“በምድር ላይ የምትኖሩ የዋሆች ሁሉ ይሖዋን ፈልጉ። . . . የዋህነትን ፈልጉ።”—ሶፎ. 2:3
መዝሙር 80 “ይሖዋ ጥሩ መሆኑን ቅመሱ፤ እዩም”
የትምህርቱ ዓላማ *
1-2. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ሙሴን የሚገልጸው እንዴት ነው? ሙሴስ ምን ነገሮችን አድርጓል? (ለ) የዋህ ለመሆን የሚያነሳሳ ምን ምክንያት አለን?
መጽሐፍ ቅዱስ “ሙሴ በምድር ላይ ከነበሩ ሰዎች ሁሉ ይልቅ በጣም የዋህ” እንደነበር ይገልጻል። (ዘኁ. 12:3) ይህ ሲባል ታዲያ ሙሴ ደካማ፣ ወላዋይና የሚያጋጥመውን ተቃውሞ ፊት ለፊት መጋፈጥ የሚፈራ ሰው ነበር ማለት ነው? አንዳንዶች የዋህ የሚለውን ቃል ሲሰሙ ወደ አእምሯቸው የሚመጣው እንዲህ ዓይነት ሰው ሊሆን ይችላል። ሆኖም ይህ ከእውነታው ፈጽሞ የራቀ ነው። ሙሴ ጠንካራ፣ ውሳኔ ማድረግ የማይፈራና ደፋር የአምላክ አገልጋይ ነበር። በይሖዋ እርዳታ፣ ኃያል ከሆነው የግብፅ ገዢ ጋር ፊት ለፊት ተጋፍጧል፤ ሦስት ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎችን በምድረ በዳ መርቷል፤ እንዲሁም እስራኤላውያን ጠላቶቻቸውን ድል እንዲያደርጉ ረድቷል።
2 እርግጥ ነው፣ እኛ ሙሴን ያጋጠሙት ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታዎች አያጋጥሙን ይሆናል፤ ሆኖም በዕለት ተዕለት ሕይወታችን፣ የዋህ መሆን ከባድ እንዲሆንብን የሚያደርጉ ሰዎች ወይም ሁኔታዎች ያጋጥሙናል። ይሁንና ይህን ባሕርይ እንድናዳብር የሚያነሳሳ አጥጋቢ ምክንያት አለን። ይሖዋ “የዋሆች . . . ምድርን ይወርሳሉ” በማለት ቃል ገብቷል። (መዝ. 37:11) የዋህ እንደሆንክ ይሰማሃል? ሌሎችስ ስለ አንተ እንደዚያ ይሰማቸዋል? እነዚህን አስፈላጊ ጥያቄዎች ከመመለሳችን በፊት የዋህነት ምን ማለት እንደሆነ ማወቅ ያስፈልገናል።
የዋህነት ምንድን ነው?
3-4. (ሀ) የዋህነት ከምን ጋር ሊመሳሰል ይችላል? (ለ) የዋህ ለመሆን የትኞቹ አራት ባሕርያት ያስፈልጉናል? ለምንስ?
3 የዋህነት * ልክ እንደ አንድ የሚያምር ሥዕል ነው ሊባል ይችላል። በምን መንገድ? አንድ ሠዓሊ የተለያዩ ማራኪ ቀለሞችን ተጠቅሞ አንድ ሥዕል እንደሚሥል ሁሉ እኛም የዋህ ለመሆን የተለያዩ ማራኪ ባሕርያትን ማዳበር ይኖርብናል። ከእነዚህ ባሕርያት መካከል ዋና ዋናዎቹ ትሕትና፣ ታዛዥነት፣ ገርነትና ድፍረት ናቸው። ይሖዋን ለማስደሰት እነዚህን ባሕርያት ማዳበር የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
4 የአምላክን ፈቃድ ለመታዘዝ የሚፈልጉት ትሑት የሆኑ ሰዎች ብቻ ናቸው። ከአምላክ ፈቃድ መካከል አንዱ ደግሞ ገር እንድንሆን ነው። (ማቴ. 5:5፤ ገላ. 5:23) የአምላክን ፈቃድ ማድረጋችን ሰይጣንን ያስቆጣዋል። ስለዚህ ትሑትና ገር ብንሆንም በሰይጣን ዓለም ውስጥ ያሉ በርካታ ሰዎች ይጠሉናል። (ዮሐ. 15:18, 19) በመሆኑም ሰይጣንን ለመቋቋም ድፍረት ያስፈልገናል።
5-6. (ሀ) ሰይጣን የዋህ የሆኑ ሰዎችን የሚጠላው ለምንድን ነው? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
5 የየዋህነት ተቃራኒ ኩራት፣ ቁጣን አለመቆጣጠርና ይሖዋን አለመታዘዝ ነው። እነዚህ ባሕርያት ሰይጣንን ጥሩ አድርገው ይገልጹታል። በእርግጥም ሰይጣን የዋህ የሆኑ ሰዎችን የሚጠላ መሆኑ ምንም አያስገርምም! እነዚህ ሰዎች ሰይጣን የሌሉትን ግሩም ባሕርያት ስለሚያንጸባርቁ የእሱ ክፋት በግልጽ እንዲታይ ያደርጋሉ። ከዚህም በላይ ውሸታም እንደሆነ ያጋልጣሉ። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ሰይጣን ምንም ነገር ቢናገር ወይም ቢያደርግ፣ የዋህ የሆኑ ሰዎች ይሖዋን ማገልገላቸውን እንዲያቆሙ ማድረግ አይችልም!—ኢዮብ 2:3-5
6 የዋህ መሆን ተፈታታኝ የሚሆንብን መቼ ነው? የዋህነትን መፈለጋችንን መቀጠል ያለብንስ ለምንድን ነው? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ሙሴ፣ በባቢሎን በግዞት የነበሩት ሦስት ዕብራውያንና ኢየሱስ የተዉትን ምሳሌ እንመልከት።
የዋህ መሆን ተፈታታኝ የሚሆንብን መቼ ነው?
7-8. ሙሴ ሌሎች ለእሱ አክብሮት እንደሌላቸው የሚያሳይ ነገር ባደረጉበት ወቅት ምን ምላሽ ሰጠ?
7 ኃላፊነት ሲኖረን፦ ኃላፊነት ያላቸው ሰዎች የዋህ መሆን ተፈታታኝ ሊሆንባቸው ይችላል፤ በተለይ በእነሱ ሥልጣን ሥር ያለ ሰው ለእነሱ አክብሮት እንደሌለው የሚያሳይ ነገር በሚያደርግበት ወይም ውሳኔያቸው ትክክል መሆኑን በሚጠራጠርበት ጊዜ የዋህነት ማሳየት ከባድ ይሆንባቸዋል። አንተስ እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞህ ያውቃል? የቤተሰብህ አባል የሆነ ሰው እንዲህ ቢያደርግ ምን ይሰማሃል? ምን ምላሽስ ትሰጣለህ? እስቲ ሙሴ እንዲህ ያለ ሁኔታ ባጋጠመው ጊዜ ምን ምላሽ እንደሰጠ ተመልከት።
8 ይሖዋ ሙሴን የእስራኤል ብሔር መሪ አድርጎ የሾመው ከመሆኑም ሌላ ብሔሩ የሚተዳደርበትን ሕግ የመጻፍ መብት ሰጥቶታል። ሙሴ የይሖዋ ድጋፍ ዘኁ. 12:1-13) ሙሴ እንዲህ ያለ ምላሽ የሰጠው ለምንድን ነው?
እንዳልተለየው ግልጽ ነበር። ያም ሆኖ የሥጋ እህቱና ወንድሙ የሆኑት ሚርያምና አሮን በትዳር ጓደኛ ምርጫው ምክንያት ነቀፋ ይሰነዝሩበት ጀመር። እንደ ሙሴ ዓይነት ኃላፊነት ያላቸው አንዳንድ ሰዎች እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥማቸው ሊቆጡና የበቀል እርምጃ ለመውሰድ ሊነሳሱ ቢችሉም ሙሴ ግን እንዲህ ከማድረግ ተቆጥቧል። ሙሴ በቀላሉ አልተበሳጨም። አልፎ ተርፎም ሚርያም በጥፋቷ ምክንያት ከያዛት የሥጋ ደዌ እንድትፈወስ ይሖዋን ተማጽኗል። (9-10. (ሀ) ይሖዋ ሙሴን ምን ነገር እንዲገነዘብ ረድቶታል? (ለ) የቤተሰብ ራሶችና የጉባኤ ሽማግሌዎች ከሙሴ ምን ይማራሉ?
9 ሙሴ ይሖዋ እንዲያሠለጥነው ፈቅዶ ነበር። ከ40 ዓመት ገደማ በፊት የግብፅ ንጉሣዊ ቤተሰብ አባል ሳለ የዋህ አልነበረም። እንዲያውም በአንድ ወቅት በጣም ከመበሳጨቱ የተነሳ ኢፍትሐዊ ድርጊት እንደፈጸመ የተሰማውን ሰው ገድሎታል። ሙሴ፣ ይሖዋ ይህን ድርጊቱን እንደሚደግፍለት እርግጠኛ ሆኖ ነበር። ይሖዋ እስራኤላውያንን ለመምራት ድፍረት ብቻ ሳይሆን የዋህነትም እንደሚያስፈልግ ለማስተማር ሙሴን ለ40 ዓመታት ያህል አሠልጥኖታል። የዋህ ለመሆን ደግሞ ሙሴ ትሑት፣ ታዛዥና ገር መሆንም ያስፈልገዋል። ሙሴ ከይሖዋ ያገኘውን ሥልጠና በሚገባ ስለተቀበለ ጥሩ መሪ ሊሆን ችሏል።—ዘፀ. 2:11, 12፤ ሥራ 7:21-30, 36
10 እናንት የቤተሰብ ራሶችና የጉባኤ ሽማግሌዎች፣ የሙሴን ምሳሌ ተከተሉ። ሌሎች ለእናንተ አክብሮት እንደሌላቸው የሚያሳይ ነገር ሲያደርጉባችሁ በቀላሉ አትበሳጩ። ያሉባችሁን ድክመቶች በትሕትና አምናችሁ ተቀበሉ። (መክ. 7:9, 20) ችግሮችን ለመፍታት ይሖዋ የሰጣቸውን መመሪያዎች በታዛዥነት ተከተሉ። በተጨማሪም ምንጊዜም ገርነት በሚንጸባረቅበት ወይም በለዘበ መንገድ መልስ ስጡ። (ምሳሌ 15:1) እንዲህ የሚያደርጉ የቤተሰብ ራሶችና የበላይ ተመልካቾች ይሖዋን ደስ ያሰኛሉ፣ ሰላም እንዲሰፍን ያደርጋሉ እንዲሁም የዋህነት በማሳየት ረገድ ለሌሎች ግሩም ምሳሌ ይተዋሉ።
11-13. ሦስቱ ዕብራውያን ምን ምሳሌ ትተውልናል?
11 ስደት ሲደርስብን፦ በታሪክ ዘመናት ሁሉ ሰብዓዊ ገዢዎች በይሖዋ ሕዝቦች ላይ ስደት አድርሰዋል። እነዚህ ሰዎች በተለያዩ የሐሰት ክሶች ቢወነጅሉንም በእኛ ላይ ስደት የሚያደርሱበት እውነተኛው ምክንያት ግን “ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዢያችን አድርገን [ለመታዘዝ]” መምረጣችን ነው። (ሥራ 5:29) በዚህ አቋማችን ምክንያት ሊሾፍብን፣ ለእስር ልንዳረግ አልፎ ተርፎም አካላዊ ጥቃት ሊሰነዘርብን ይችላል። ሆኖም ይሖዋ ስለሚረዳን፣ ስደት ሲደርስብን አጸፋውን ከመመለስ ይልቅ ገርነት ማሳየታችንን እንቀጥላለን።
12 በግዞት ወደ ባቢሎን የተወሰዱት ሃናንያህ፣ ሚሳኤልና አዛርያስ የተባሉ ሦስት ዕብራውያን የተዉትን ምሳሌ እንመልከት። * የባቢሎን ንጉሥ እሱ ላሠራው ግዙፍ የወርቅ ምስል እንዲሰግዱ አዘዛቸው። በዚህ ጊዜ ለምስሉ አምልኮ የማያቀርቡበትን ምክንያት ለንጉሡ በገርነት ነገሩት። ንጉሡ ወደሚንበለበለው የእቶን እሳት እንደሚጣሉ በመግለጽ ቢያስፈራራቸውም ይሖዋን ከመታዘዝ ወደኋላ አላሉም። ይሖዋም ወዲያውኑ ጣልቃ በመግባት እነዚህን ወጣቶች አድኗቸዋል። እርግጥ ነው፣ እነሱ ይሖዋ የግድ ሊያድናቸው እንደሚገባ አልተሰማቸውም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ የፈቀደውን ማንኛውንም ነገር ለመቀበል ፈቃደኞች ነበሩ። (ዳን. 3:1, 8-28) እነዚህ ወጣቶች የዋህ የሆኑ ሰዎች እውነተኛ ድፍረት እንዳላቸው አስመሥክረዋል፤ የትኛውም ንጉሥ አሊያም ምንም ዓይነት ማስፈራሪያ ወይም ቅጣት ይሖዋን ብቻ ለማምለክ ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ሊያስለውጠን አይችልም።—ዘፀ. 20:4, 5
13 ለአምላክ ያለንን ታማኝነት የሚፈትን ሁኔታ ሲያጋጥመን የእነዚህን ሦስት ዕብራውያን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? ትሑት በመሆን ይሖዋ እንደሚረዳን እንተማመናለን። (መዝ. 118:6, 7) የሐሰት ክስ ለሚሰነዝሩብን ሰዎች ገርነትና አክብሮት በሚንጸባረቅበት መንገድ መልስ እንሰጣለን። (1 ጴጥ. 3:15) በተጨማሪም ከአፍቃሪው አባታችን ጋር ያለንን ወዳጅነት ፈጽሞ ለድርድር አናቀርብም።
14-15. (ሀ) ውጥረት ውስጥ ስንሆን ምን ሊያጋጥመን ይችላል? (ለ) በኢሳይያስ 53:7, 10 መሠረት ኢየሱስ ውጥረት በሚፈጥሩ ሁኔታዎች ሥር የዋህ በመሆን ረገድ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ ትቶልናል የምንለው ለምንድን ነው?
14 ውጥረት ውስጥ ስንሆን፦ ሁላችንም በተለያዩ ምክንያቶች ውጥረት ውስጥ ልንገባ እንችላለን። ትምህርት ቤት ውስጥ ፈተና ልንፈተን ስንል ወይም በሥራ ቦታ አንድ ለየት ያለ ሥራ ከማከናወናችን በፊት ውጥረት ሊሰማን ይችላል። አሊያም አንድ ዓይነት ሕክምና ወይም ምርመራ ለማድረግ ማሰባችን ብቻ እንኳ ውጥረት ሊፈጥርብን ይችላል። እንዲህ ባሉ ሁኔታዎች ሥር የዋህ መሆን ይከብደናል። ሌላ ጊዜ ቢሆን ችላ ብለን የምናልፋቸው ነገሮች በቀላሉ ሊያበሳጩን ይችላሉ። በተጨማሪም ደግነት በጎደለውና ሌሎችን ቅር በሚያሰኝ መንገድ ልንናገር እንችላለን። አንተም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞህ የሚያውቅ ከሆነ የኢየሱስን ምሳሌ መመርመርህ ይጠቅምሃል።
15 ኢየሱስ ምድር ላይ ባሳለፋቸው የመጨረሻ ወራት ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ እንደሚገደልና ብዙ መከራ እንደሚደርስበት ያውቃል። (ዮሐ. 3:14, 15፤ ገላ. 3:13) ከመሞቱ ከተወሰኑ ወራት በፊት፣ በጣም እንደተጨነቀ ተናግሯል። (ሉቃስ 12:50) ሊሞት ጥቂት ቀናት ሲቀረውም “ተጨንቄአለሁ” ብሏል። ኢየሱስ ስሜቱን አውጥቶ ወደ አምላክ ያቀረበው የሚከተለው ጸሎት ምን ያህል ትሑትና ታዛዥ እንደሆነ ያሳያል፦ “አባት ሆይ፣ ከዚህ ሰዓት አድነኝ። ይሁንና የመጣሁት ለዚህ ሰዓት ነው። አባት ሆይ፣ ስምህን አክብረው።” (ዮሐ. 12:27, 28) ጊዜው ሲደርስ፣ ኢየሱስ ራሱን ለአምላክ ጠላቶች አሳልፎ የሰጠ ሲሆን እነዚህ ሰዎች እጅግ አሰቃቂ በሆነና በሚያዋርድ መንገድ ገድለውታል። ኢየሱስ ከፍተኛ ውጥረትና ከባድ መከራ ቢያጋጥመውም የዋህ በመሆን የአምላክን ፈቃድ አድርጓል። በእርግጥም ውጥረት በሚፈጥሩ ሁኔታዎች ሥር የዋህ በመሆን ረገድ ኢየሱስ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ ትቶልናል ቢባል ማጋነን አይሆንም!—ኢሳይያስ 53:7, 10ን አንብብ።
16-17. (ሀ) የኢየሱስ ወዳጆች የኢየሱስን የዋህነት የሚፈታተን ምን ነገር አድርገው ነበር? (ለ) ኢየሱስን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?
16 ኢየሱስ ምድር ላይ ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት፣ የቅርብ ወዳጆቹ የዋህነቱን የሚፈታተን ነገር አድርገው ነበር። በዚያ ምሽት ኢየሱስ ምን ያህል ውጥረት ውስጥ ገብቶ እንደሚሆን ለማሰብ ሞክሩ። እስከ ሞት ድረስ ፍጹም ታማኝነቱን የመጠበቁ ጉዳይ አሳስቦት እንደሚሆን የታወቀ ነው። ደግሞም እሱ የሚወስደው እርምጃ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። (ሮም 5:18, 19) ከሁሉ በላይ ደግሞ የአባቱን መልካም ስም ይነካል። (ኢዮብ 2:4) ሆኖም የቅርብ ወዳጆቹ ከሆኑት ሐዋርያቱ ጋር በተመገበው የመጨረሻ ማዕድ ላይ “ከመካከላችን ታላቅ የሆነው ማን ነው?” በሚል በሐዋርያቱ መካከል “የጦፈ ክርክር” ተነሳ። ኢየሱስ በዚህ ጉዳይ ላይ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ምክር ሰጥቷቸው ነበር! ሌላው ቀርቶ በዚያው ምሽት እንኳ ይህንኑ ምክር ሰጥቷቸዋል። የሚገርመው ግን ኢየሱስ በሐዋርያቱ ላይ አልተበሳጨም። ከዚህ ይልቅ ገርነት በሚንጸባረቅበት መንገድ አነጋገራቸው። በደግነት ሆኖም ጠንከር ባለ መንገድ በድጋሚ ምክር ሰጣቸው። ምን ዓይነት ዝንባሌ ሊኖራቸው እንደሚገባ ነገራቸው። ከዚያም እስከ መጨረሻው ከጎኑ ስላልተለዩ አመሰገናቸው።—ሉቃስ 22:24-28፤ ዮሐ. 13:1-5, 12-15
17 አንተ ብትሆን ኖር ምን ታደርግ ነበር? ውጥረት ውስጥ በምንሆንበት ጊዜም እንኳ ገርነት በማሳየት ኢየሱስን መምሰል እንችላለን። ይሖዋ “እርስ በርስ መቻቻላችሁን . . . ቀጥሉ” በማለት የሰጠንን መመሪያ በፈቃደኝነት እንታዘዝ። (ቆላ. 3:13) ሁላችንም ሌሎችን የሚያበሳጭ ነገር እንደምንናገርና እንደምናደርግ ካስታወስን ይህን ትእዛዝ ከመከተል ወደኋላ አንልም። (ምሳሌ 12:18፤ ያዕ. 3:2, 5) በተጨማሪም ሌሎች ያላቸውን መልካም ነገር ጠቅሰን ለማመስገን ጥረት እናድርግ።—ኤፌ. 4:29
የዋህነትን መፈለጋችንን መቀጠል ያለብን ለምንድን ነው?
18. ይሖዋ የዋሆችን ጥሩ ውሳኔ እንዲያደርጉ የሚረዳቸው እንዴት ነው? ሆኖም እነሱ ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል?
18 የዋህነትን መፈለጋችን ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ ይረዳናል። ይሖዋ በሕይወታችን ውስጥ ምርጫ ማድረግ የሚጠይቁ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ጥሩ ውሳኔ ማድረግ እንድንችል ይረዳናል፤ ሆኖም ይሖዋ የሚረዳን የዋህ ከሆንን ብቻ ነው። ይሖዋ “የዋሆች የሚያቀርቡትን ልመና” እንደሚሰማ ቃል ገብቷል። (መዝ. 10:17) አምላክ ልመናችንን በመስማት ብቻ አይወሰንም። መጽሐፍ ቅዱስ “የዋሆችን በትክክለኛ መንገድ ይመራቸዋል፤ እንዲሁም ለየዋሆች መንገዱን ያስተምራል” የሚል ተስፋ ይዟል። (መዝ. 25:9) ይሖዋ የሚመራን በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በጽሑፎቻችን * እንዲሁም “ታማኝና ልባም ባሪያ” በሚያዘጋጃቸው ፕሮግራሞች አማካኝነት ነው። (ማቴ. 24:45-47) እኛም የይሖዋ እርዳታ እንደሚያስፈልገን በትሕትና አምነን በመቀበል፣ የሚቀርቡልንን ጽሑፎች በትጋት በማጥናትና የተማርነውን ነገር በታዛዥነት ተግባራዊ በማድረግ የበኩላችንን ድርሻ መወጣት ይኖርብናል።
19-21. ሙሴ በቃዴስ ምን ስህተት ሠርቷል? እኛስ ከዚህ ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን?
19 የዋህነትን መፈለጋችን ስህተት ከመሥራት ይጠብቀናል። እስቲ የሙሴን ሁኔታ በድጋሚ እንመልከት። ሙሴ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት የዋህ በመሆን የይሖዋን ልብ ደስ አሰኝቷል። እስራኤላውያን በምድረ በዳ ለ40 ዓመት ያህል ያደረጉት አስቸጋሪ ጉዞ ሊደመደም ጥቂት ሲቀረው ግን የዋህነት ማሳየት ተስኖት ነበር። እህቱ ሞታ በቃዴስ ከተቀበረች ብዙ ጊዜ አላለፈም፤ በግብፅ ውስጥ ሕይወቱን ያተረፈችለት እሷ ሳትሆን አትቀርም። አሁን ደግሞ እስራኤላውያን፣ የሚያስፈልጓቸው ነገሮች እንዳልተሟሉላቸው በመናገር በድጋሚ ማጉረምረም ጀመሩ። ሕዝቡ የሚጠጣ ውኃ በማጣቱ “ከሙሴ ጋር ተጣላ።” ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት በርካታ ተአምራትን ዘኁ. 20:1-5, 9-11
ፈጽሟል፤ ሙሴም ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ እስራኤላውያንን ለረጅም ጊዜ ሲመራ ቆይቷል። ሕዝቡ ይህን ሁሉ ቢያውቅም ከማጉረምረም ወደኋላ አላለም። እስራኤላውያን ውኃ በማጣታቸው ብቻ ሳይሆን በሙሴ ምክንያት ውኃ ያጡ ይመስል በእሱ ላይ ጭምር አጉረምርመዋል።—20 ሙሴ በጣም ስለተበሳጨ እንደ ወትሮው ገር መሆን ሳይችል ቀረ። በይሖዋ በመታመን ልክ እንደታዘዘው ዓለቱን ከመናገር ይልቅ በምሬት ሕዝቡን የተቆጣ ከመሆኑም ሌላ ተአምሩን የሚፈጽመው እሱ ራሱ እንደሆነ በሚያስመስል መንገድ ተናገረ። ከዚያም ዓለቱን ሁለቴ ሲመታው ውኃው እየተንዶለዶለ ይወጣ ጀመር። ኩራትና ብስጭት፣ ሙሴን አሳዛኝ ስህተት እንዲሠራ አድርገውታል። (መዝ. 106:32, 33) ሙሴ ለተወሰነ ጊዜ ያህል የዋህነት ማሳየት ስላቃተው ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዳይገባ ተከልክሏል።—ዘኁ. 20:12
21 ከዚህ ታሪክ ትልቅ ትምህርት እናገኛለን። አንደኛ፣ ምንጊዜም የዋህ ሆነን ለመቀጠል ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ አለብን። ለአፍታ እንኳ ከተዘናጋን ወዲያውኑ ኩራት ሊጠናወተንና ሞኝነት የሚንጸባረቅበት ነገር ልንናገር ወይም ልናደርግ እንችላለን። ሁለተኛ፣ ውጥረት ውስጥ ስንሆን የዋህነት ማሳየት ከባድ ሊሆንብን ይችላል፤ ስለዚህ ውጥረት ውስጥ በምንሆንበት ጊዜም እንኳ የዋህነት ለማሳየት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል።
22-23. (ሀ) የዋህነትን መፈለጋችንን መቀጠል ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) በሶፎንያስ 2:3 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ምን ይጠቁማል?
22 የዋህነትን መፈለጋችን ጥበቃ ያስገኝልናል። በቅርቡ ይሖዋ ክፉዎችን በሙሉ ከምድር ላይ ጠራርጎ በማጥፋት የዋሆች ብቻ እንዲተርፉ ያደርጋል። ከዚያም በምድር ላይ እውነተኛ ሰላም ይሰፍናል። (መዝ. 37:10, 11) ታዲያ አንተ በሕይወት ከሚተርፉት የዋሆች መካከል ትገኝ ይሆን? ይሖዋ በነቢዩ ሶፎንያስ በኩል ያቀረበውን ፍቅራዊ ግብዣ ተቀብለህ እርምጃ የምትወስድ ከሆነ ከእነሱ መካከል መሆን ትችላለህ።—ሶፎንያስ 2:3ን አንብብ።
23 ይሁንና ሶፎንያስ 2:3 “ምናልባት . . . ትሰወሩ ይሆናል” የሚለው ለምንድን ነው? ይህ አገላለጽ ይሖዋ ለሚወዳቸውና እሱን ማስደሰት ለሚፈልጉ ሰዎች ጥበቃ ማድረግ እንደማይችል የሚጠቁም አይደለም። ከዚህ ይልቅ ጥበቃ ለማግኘት ከእኛም የሚጠበቅ ነገር እንዳለ የሚያሳይ ነው። በዛሬው ጊዜ የዋህነትን ለመፈለግና ይሖዋን ለማስደሰት ጥረት የምናደርግ ከሆነ ‘ከይሖዋ የቁጣ ቀን’ የመትረፍና ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ እናገኛለን።
መዝሙር 120 እንደ ክርስቶስ ገር መሆን
^ አን.5 በተፈጥሮው የዋህ የሆነ ሰው የለም። ሁላችንም ይህን ባሕርይ ለማዳበር ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ሰላማዊ ከሆኑ ሰዎች ጋር ስንሆን የዋህነት ማሳየት አይከብደን ይሆናል፤ ኩሩ የሆኑ ሰዎች ሲያጋጥሙን ግን የዋህ መሆን ተፈታታኝ ሊሆንብን ይችላል። ይህ ርዕስ ይህን ግሩም ባሕርይ ለማዳበር፣ የትኞቹን ተፈታታኝ ሁኔታዎች መወጣት እንዳለብን ያብራራል።
^ አን.3 ተጨማሪ ማብራሪያ፦ የዋህነት። የዋህ የሆኑ ሰዎች ሌሎችን በደግነት የሚይዙ ከመሆኑም ሌላ የሚያስቆጣ ነገር በሚያጋጥማቸው ጊዜም እንኳ ገርነት ያሳያሉ። ትሕትና። ትሑት የሆኑ ሰዎች ከኩራት ወይም ከትዕቢት የራቁ ናቸው፤ በተጨማሪም ሌሎች ከእነሱ እንደሚበልጡ አድርገው ያስባሉ። ትሕትና የሚለው ቃል ከይሖዋ ጋር በተያያዘ ሲሠራበት ፍጥረታቱ ከእሱ የሚያንሱ ቢሆኑም ፍቅርና ምሕረት በሚንጸባረቅበት መንገድ እንደሚይዛቸው ያሳያል።
^ አን.18 ለምሳሌ ያህል፣ በሚያዝያ 15, 2011 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “አምላክን የሚያስከብር ውሳኔ አድርጉ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
^ አን.59 የሥዕሉ መግለጫ፦ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ከመካከላቸው ማን ታላቅ እንደሆነ በተከራከሩ ጊዜ ኢየሱስ በገርነትና በተረጋጋ መንፈስ እርማት ሰጥቷቸዋል።