ሁለት አዳዲስ የበላይ አካል አባላት
ረቡዕ፣ ጥር 18, 2023 ወንድም ጌጅ ፍሊግል እና ወንድም ጄፍሪ ዊንደር የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባላት ሆነው እንደተሾሙ የሚገልጽ ልዩ ማስታወቂያ jw.org ላይ ወጥቶ ነበር። ሁለቱም ወንድሞች ይሖዋን ለረጅም ጊዜ በታማኝነት አገልግለዋል።
ወንድም ፍሊግል ያደገው በምዕራባዊ ፔንስልቬንያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ሲሆን ወላጆቹ እውነት ውስጥ አሳድገውታል። ወንድም ፍሊግል በአሥራዎቹ ዕድሜ ሳለ ቤተሰባቸው ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አንድ አነስተኛ የገጠር ከተማ ተዛወረ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ኅዳር 20, 1988 ተጠመቀ።
የወንድም ፍሊግል ወላጆች ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንዲገባ ሁልጊዜ ያበረታቱት ነበር። ወላጆቹ የወረዳ የበላይ ተመልካቾችንና ቤቴላውያንን ብዙ ጊዜ ቤታቸው ይጋብዙ ነበር። ወንድም ፍሊግል እነዚህ ወንድሞችና እህቶች ምን ያህል ደስተኛ እንደሆኑ ማስተዋል ችሏል። ከተጠመቀ ብዙም ሳይቆይ መስከረም 1, 1989 በዘወትር አቅኚነት ማገልገል ጀመረ። ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ ቤቴል የመግባት ግቡ ላይ ደረሰ፤ ይህን ግብ ያወጣው በ12 ዓመቱ ነበር። ጥቅምት 1991 በብሩክሊን ቤቴል ማገልገል ጀመረ።
ወንድም ፍሊግል ቤቴል ውስጥ በመጻሕፍት መጠረዣ ክፍል ለስምንት ዓመታት ካገለገለ በኋላ ወደ አገልግሎት ዘርፍ ተዛወረ። በዚያ ወቅት ለተወሰኑ ዓመታት በሩሲያኛ ጉባኤ ውስጥ አገልግሏል። በ2006 ከናዲያ ጋር ትዳር መሠረተ፤ እሷም በቤቴል አብራው ማገልገል ጀመረች። አንድ ላይ ሆነው በፖርቱጋልኛ ጉባኤ እንዲሁም ከአሥር ዓመት በላይ በስፓንኛ ጉባኤ አገልግለዋል። ወንድም ፍሊግል በአገልግሎት ዘርፍ ለበርካታ ዓመታት ከሠራ በኋላ በትምህርት ኮሚቴ ቢሮ እንዲያገለግል ተመደበ፤ በኋላ ደግሞ በአገልግሎት ኮሚቴ ቢሮ ውስጥ ማገልገል ጀመረ። መጋቢት 2022 የበላይ አካሉ የአገልግሎት ኮሚቴ ረዳት ሆኖ ተሾመ።
ወንድም ዊንደር ያደገው በሙሪየታ፣ ካሊፎርኒያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ነው። ወላጆቹ እውነት ውስጥ ያሳደጉት ሲሆን መጋቢት 29, 1986 ተጠመቀ። በቀጣዩ ወር በረዳት አቅኚነት ማገልገል ጀመረ። አገልግሎቱን በጣም ስለወደደው በዚያው ቀጠለ። ለበርካታ ወራት በረዳት አቅኚነት ካገለገለ በኋላ ጥቅምት 1, 1986 የዘወትር አቅኚ ሆነ።
ወንድም ዊንደር በአሥራዎቹ ዕድሜ ሳለ በወቅቱ በቤቴል ያገለግሉ የነበሩትን ሁለት ታላላቅ ወንድሞቹን ሊጠይቅ ሄደ። ያ ጉብኝት ዕድሜው ሲደርስ በቤቴል ለማገልገል እንዲነሳሳ አደረገው። ግንቦት 1990 በዎልኪል ቤቴል እንዲያገለግል ተጋበዘ።
ወንድም ዊንደር ቤቴል ውስጥ በተለያዩ የሥራ ክፍሎች አገልግሏል፤ ከእነዚህ መካከል የጽዳት ክፍል፣ የግብርና ክፍል እና የቤቴል ቢሮ ይገኙበታል። በ1997 ከአንጄላ ጋር ትዳር የመሠረተ ሲሆን ከዚያን ጊዜ አንስቶ በቤቴል አብረው እያገለገሉ ነው። በ2014 ወደ ዎርዊክ ተዛወሩ፤ በዚያም ወንድም ዊንደር በዋናው መሥሪያ ቤት ግንባታ ላይ ተካፍሏል። በ2016 በፓተርሰን ወደሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ የትምህርት ማዕከል የተዛወሩ ሲሆን ወንድም ዊንደር በኦዲዮ/ቪዲዮ አገልግሎት ውስጥ መሥራት ጀመረ። ከአራት ዓመታት በኋላ ወደ ዎርዊክ ተመለሱ፤ ወንድም ዊንደርም በፐርሶኔል ኮሚቴ ቢሮ ውስጥ እንዲያገለግል ተመደበ። መጋቢት 2022 የበላይ አካሉ የፐርሶኔል ኮሚቴ ረዳት ሆኖ ተሾመ።
እነዚህ ‘ስጦታ የሆኑ ሰዎች’ የመንግሥቱን ጉዳዮች ለማራመድ በትጋት ሲሠሩ ይሖዋ አብዝቶ እንዲባርካቸው እንጸልያለን።—ኤፌ. 4:8