በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 8

መዝሙር 123 ለቲኦክራሲያዊ ሥርዓት በታማኝነት መገዛት

ምንጊዜም የይሖዋን አመራር ተከተሉ

ምንጊዜም የይሖዋን አመራር ተከተሉ

“የምመራህ እኔ ይሖዋ አምላክህ ነኝ።”ኢሳ. 48:17

ዓላማ

በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ሕዝቦቹን እየመራቸው ያለው እንዴት እንደሆነ እንዲሁም የእሱን አመራር መከተላችን ምን በረከት እንደሚያስገኝልን እንመለከታለን።

1. የይሖዋ አመራር የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።

 ጫካ ውስጥ መንገድ ጠፍቶብሃል እንበል። በዙሪያህ ብዙ አደገኛ ነገሮች አሉ፤ የዱር አራዊት፣ ተናዳፊ ነፍሳት፣ መርዛማ ተክሎች እንዲሁም እንቅፋቶች አሉ። አካባቢውን በደንብ የሚያውቅ ሰው መንገዱን ቢመራህ እንዲሁም ከአደገኛዎቹ ሁኔታዎች እንድትርቅ ቢረዳህ በጣም እንደምትደሰት ምንም ጥያቄ የለውም። የምንኖርበት ዓለም እንደዚህ ጫካ ነው። መንፈሳዊ ጤንነታችንን በሚጎዱ አደገኛ ሁኔታዎች የተሞላ ነው። ሆኖም ፍጹም የሆነ መሪ አለን፤ እሱም ይሖዋ ነው። ይሖዋ ከአደጋዎቹ ተጠብቀን ወደ መዳረሻችን ማለትም የዘላለም ሕይወት ወደምናገኝበት አዲስ ዓለም እንድንደርስ ይረዳናል።

2. ይሖዋ የሚመራን እንዴት ነው?

2 ይሖዋ የሚመራን እንዴት ነው? በዋነኝነት የሚመራን በጽሑፍ በሰፈረው ቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ነው። ሆኖም ይሖዋ ሰብዓዊ ወኪሎቹንም ይጠቀማል። ለምሳሌ ‘ታማኝና ልባም ባሪያን’ ተጠቅሞ ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዳንን መንፈሳዊ ምግብ ያቀርብልናል። (ማቴ. 24:45) ይሖዋ እኛን ለመምራት፣ ብቃት ያላቸውን ሌሎች ወንዶችም ይጠቀማል። ለምሳሌ የወረዳ የበላይ ተመልካቾችና የጉባኤ ሽማግሌዎች አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ለመቋቋም የሚረዳ ማበረታቻና መመሪያ ይሰጡናል። በእነዚህ አስጨናቂ የመጨረሻ ቀናት አስተማማኝ መመሪያ ማግኘት በመቻላችን ምንኛ አመስጋኞች ነን! ይህ መመሪያ የይሖዋ ወዳጆች ሆነን እንድንቀጥል እንዲሁም ከሕይወት መንገድ እንዳንወጣ ይረዳናል።

3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?

3 ይሁንና አንዳንድ ጊዜ የይሖዋን አመራር መከተል ተፈታታኝ ሊሆንብን ይችላል፤ በተለይ መመሪያው የመጣው ፍጹማን ባልሆኑ ሰዎች አማካኝነት ከሆነ ታዛዥ መሆን ይበልጥ ሊከብደን ይችላል። ለምን? የተሰጠን ምክር ከእኛ ፍላጎት ጋር አይጣጣም ይሆናል። ወይም ደግሞ የተሰጠን መመሪያ ጥበብ የሚንጸባረቅበት እንደሆነ ስላልተሰማን መመሪያው የመጣው ከይሖዋ መሆኑን ልንጠራጠር እንችላለን። በተለይ እንዲህ ባሉት ጊዜያት፣ ሕዝቦቹን እየመራ ያለው ይሖዋ እንደሆነ እንዲሁም የእሱን አመራር መከተል በረከት እንደሚያስገኝ መተማመን ይኖርብናል። በዚህ ረገድ እምነታችንን ማጠናከር እንድንችል በዚህ ርዕስ ውስጥ ሦስት ጥያቄዎችን እንመልሳለን፦ (1) ይሖዋ በጥንት ዘመን ሕዝቦቹን የመራቸው እንዴት ነው? (2) ይሖዋ በዛሬው ጊዜ እየመራን ያለው እንዴት ነው? እንዲሁም (3) ምንጊዜም የይሖዋን አመራር መከተላችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

ከጥንት ዘመን አንስቶ እስካሁን ድረስ ይሖዋ ሕዝቦቹን ለመምራት ሰብዓዊ ወኪሎቹን ሲጠቀም ቆይቷል (አንቀጽ 3⁠ን ተመልከት)


ይሖዋ እስራኤላውያንን የመራቸው እንዴት ነው?

4-5. ይሖዋ እስራኤላውያንን ለመምራት በሙሴ እየተጠቀመ እንዳለ ያሳየው እንዴት ነው? (የሽፋኑን ሥዕል ተመልከት።)

4 ይሖዋ እስራኤላውያንን እየመራ ከግብፅ እንዲያወጣ ሙሴን ሾሞት ነበር። በተጨማሪም እስራኤላውያን በሙሴ አማካኝነት እየመራቸው ያለው እሱ መሆኑን እንዲያስተውሉ በዓይን የሚታይ ማስረጃ ሰጥቷቸዋል። ለምሳሌ ቀን ቀን የደመና ዓምድ፣ ሌሊት ሌሊት ደግሞ የእሳት ዓምድ ያሳያቸው ነበር። (ዘፀ. 13:21) ሙሴ ዓምዱን ተከትሏል፤ ሆኖም ዓምዱ እሱንና እስራኤላውያንን ወደ ቀይ ባሕር መራቸው። ሕዝቡ በቀይ ባሕርና በሚያሳድዳቸው የግብፅ ሠራዊት መካከል አጣብቂኝ ውስጥ እንደገቡ ስለተሰማቸው በፍርሃት ተዋጡ። በመሆኑም ሙሴ እነሱን እየመራ ወደ ቀይ ባሕር መሄዱ ስህተት እንደሆነ ተሰማቸው። ሆኖም ይህ ስህተት አልነበረም። ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት ሕዝቦቹን ወደዚያ የመራቸው በዓላማ ነው። (ዘፀ. 14:2) አምላክ እስራኤላውያንን እጅግ አስደናቂ በሆነ መንገድ ታደጋቸው።—ዘፀ. 14:26-28

ሙሴ የደመናውን ዓምድ በመከተል የአምላክን ሕዝቦች በምድረ በዳው ውስጥ መርቷቸዋል (ከአንቀጽ 4-5⁠ን ተመልከት)


5 ከዚያ በኋላ ላሉት 40 ዓመታት ሙሴ የደመናውን ዓምድ እየተከተለ የአምላክን ሕዝቦች በምድረ በዳው ውስጥ መምራቱን ቀጥሏል። a ለተወሰነ ጊዜ ያህል ይሖዋ የደመናውን ዓምድ በሙሴ ድንኳን ላይ ያቆመው ነበር፤ ይህንንም ሁሉም እስራኤላውያን ማየት ይችላሉ። (ዘፀ. 33:7, 9, 10) ይሖዋ ከደመናው ዓምድ ሙሴን ያነጋግረዋል፤ ሙሴ ደግሞ መመሪያውን ለሕዝቡ ያስተላልፋል። (መዝ. 99:7) እስራኤላውያን በሙሴ አማካኝነት እየመራቸው ያለው ይሖዋ መሆኑን መገንዘብ የሚችሉበት አጥጋቢ ማስረጃ ነበራቸው።

ሙሴ እና በእሱ ምትክ የተሾመው ኢያሱ (አንቀጽ 5, 7⁠ን ተመልከት)


6. እስራኤላውያን ለይሖዋ አመራር ምን ምላሽ ሰጡ? (ዘኁልቁ 14:2, 10, 11)

6 የሚያሳዝነው፣ አብዛኞቹ እስራኤላውያን ይሖዋ በሙሴ እየተጠቀመ እንዳለ የሚያሳየውን ግልጽ ማስረጃ ለመቀበል አሻፈረን ብለዋል። (ዘኁልቁ 14:2, 10, 11ን አንብብ።) የሙሴን ሚና ለመቀበል በተደጋጋሚ እንቢተኞች ሆነዋል። በዚህም የተነሳ ያ የእስራኤላውያን ትውልድ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዲገባ አልተፈቀደለትም።—ዘኁ. 14:30

7. የይሖዋን አመራር የተከተሉ ሰዎችን ምሳሌ ጥቀስ። (ዘኁልቁ 14:24) (ሥዕሉንም ተመልከት።)

7 ይሁንና የይሖዋን አመራር የተከተሉ አንዳንድ እስራኤላውያን ነበሩ። ለምሳሌ ይሖዋ ‘ካሌብ በሙሉ ልቡ ተከትሎኛል’ በማለት ተናግሯል። (ዘኁልቁ 14:24ን አንብብ።) አምላክ ለካሌብ ወሮታውን ከፍሎታል፤ እንዲያውም በከነአን ምድር የፈለገውን መሬት ሰጥቶታል። (ኢያሱ 14:12-14) ቀጣዩ የእስራኤላውያን ትውልድም የይሖዋን አመራር በመከተል ረገድ ጥሩ ምሳሌ ትቷል። ኢያሱ በሙሴ ምትክ የእስራኤላውያን መሪ ሆኖ በተሾመበት ወቅት እነዚህ እስራኤላውያን ‘በሕይወት ዘመኑ ሁሉ በጥልቅ አክብረውታል።’ (ኢያሱ 4:14) በዚህም የተነሳ ይሖዋ፣ ቃል ወደገባላቸው ምድር በማስገባት ባርኳቸዋል።—ኢያሱ 21:43, 44

8. ይሖዋ በነገሥታት ዘመን ሕዝቦቹን የመራቸው እንዴት እንደሆነ አብራራ። (ሥዕሉንም ተመልከት።)

8 ከበርካታ ዓመታት በኋላ ይሖዋ ሕዝቡን ለመምራት መሳፍንትን አስነሳላቸው። ከዚያ በኋላ ደግሞ በነገሥታት ዘመን ይሖዋ ሕዝቡን ለመምራት ነቢያትን ሾሞላቸዋል። ታማኝ የሆኑ ነገሥታት የነቢያቱን ምክር ይከተሉ ነበር። ለምሳሌ ንጉሥ ዳዊት፣ ነቢዩ ናታን የሰጠውን እርማት በትሕትና ተቀብሏል። (2 ሳሙ. 12:7, 13፤ 1 ዜና 17:3, 4) ንጉሥ ኢዮሳፍጥ፣ ነቢዩ ያሃዚኤል የሰጠውን መመሪያ ተከትሏል፤ በተጨማሪም ‘በአምላክ ነቢያት እንዲያምኑ’ የይሁዳን ሕዝብ አበረታቷቸዋል። (2 ዜና 20:14, 15, 20) ንጉሥ ሕዝቅያስ በጭንቀት በተዋጠበት ወቅት ከነቢዩ ኢሳይያስ ምክር ጠይቋል። (ኢሳ. 37:1-6) ነገሥታቱ የይሖዋን አመራር በተከተሉበት ዘመን ሁሉ በረከት ያገኙ ነበር፤ ብሔሩም ጥበቃ አግኝቷል። (2 ዜና 20:29, 30፤ 32:22) ይሖዋ ሕዝቦቹን ለመምራት ነቢያቱን እየተጠቀመ እንዳለ ሁሉም ሊገነዘቡ ይገባ ነበር። ያም ቢሆን አብዛኞቹ ነገሥታት እንዲሁም ሕዝቡ የይሖዋን ነቢያት ለመስማት አሻፈረን ብለዋል።—ኤር. 35:12-15

ንጉሥ ሕዝቅያስ እና ነቢዩ ኢሳይያስ (አንቀጽ 8⁠ን ተመልከት)


ይሖዋ የጥንቶቹን ክርስቲያኖች የመራቸው እንዴት ነው?

9. ይሖዋ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን ክርስቲያኖች ለመምራት በማን ተጠቅሟል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

9 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. ይሖዋ የክርስቲያን ጉባኤን አቋቋመ። ታዲያ እነዚያን ክርስቲያኖች የመራቸው እንዴት ነው? ኢየሱስን የጉባኤው ራስ አድርጎ ሾሞታል። (ኤፌ. 5:23) ሆኖም ኢየሱስ ለእያንዳንዱ ደቀ መዝሙር በግለሰብ ደረጃ አመራር አልሰጠም። ከዚህ ይልቅ ሐዋርያትንና በኢየሩሳሌም የነበሩትን ሽማግሌዎች አመራር እንዲሰጡ ተጠቅሞባቸዋል። (ሥራ 15:1, 2) ከዚህም ሌላ ለጉባኤዎቹ አመራር የሚሰጡ ሽማግሌዎች ተሹመው ነበር።—1 ተሰ. 5:12፤ ቲቶ 1:5

ሐዋርያትና በኢየሩሳሌም የነበሩት ሽማግሌዎች (አንቀጽ 9⁠ን ተመልከት)


10. (ሀ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ለተሰጣቸው አመራር ምን ምላሽ ሰጥተዋል? (የሐዋርያት ሥራ 15:30, 31) (ለ) በጥንት ዘመን የነበሩ አንዳንድ ሰዎች የይሖዋን ወኪሎች ለመቀበል ፈቃደኛ ያልነበሩት ለምንድን ነው? (“ አንዳንዶች በግልጽ የሚታየውን ማስረጃ ያልተቀበሉት ለምንድን ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

10 የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ለሚሰጣቸው አመራር ምን ምላሽ ሰጡ? አብዛኞቹ የተሰጣቸውን መመሪያ ለመከተል ፈቃደኞች ነበሩ። እንዲያውም ‘ባገኙት ማበረታቻ እጅግ ተደስተዋል።’ (የሐዋርያት ሥራ 15:30, 31ን አንብብ።) በዘመናችንስ ይሖዋ ሕዝቦቹን እየመራ ያለው እንዴት ነው?

ይሖዋ በዛሬው ጊዜ እየመራን ያለው እንዴት ነው?

11. ይሖዋ በዘመናችን ኃላፊነት ያላቸውን ወንድሞች እንደመራቸው የሚያሳይ ምሳሌ ስጥ።

11 ይሖዋ በዛሬው ጊዜም ሕዝቡን መምራቱን ቀጥሏል። ይህን የሚያደርገው በቃሉ እንዲሁም የጉባኤው ራስ በሆነው በልጁ አማካኝነት ነው። ይሁንና አምላክ ሰብዓዊ ወኪሎችንም መጠቀሙን እንደቀጠለ የሚያሳይ ማስረጃ አለ? በሚገባ። በ19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ አካባቢ የተፈጸሙ አንዳንድ ክንውኖችን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ቻርልስ ቴዝ ራስልና ጓደኞቹ 1914 ከአምላክ መንግሥት መቋቋም ጋር በተያያዘ ወሳኝ ዓመት እንደሚሆን ማስተዋል ጀምረው ነበር። (ዳን. 4:25, 26) እዚህ መደምደሚያ ላይ የደረሱት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን መሠረት አድርገው ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ምርምር ሲያደርጉ ይሖዋ እንደመራቸው ምንም ጥያቄ የለውም። በ1914 በዓለም ላይ የተፈጸሙት ክንውኖች የአምላክ መንግሥት መግዛት እንደጀመረ አረጋገጡ። የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ፈነዳ፤ ከዚያም ቸነፈር፣ የምድር ነውጥና የምግብ እጥረት ተከሰተ። (ሉቃስ 21:10, 11) ይሖዋ ሕዝቡን ለመርዳት ቅን ልብ ያላቸውን እነዚያን ክርስቲያን ወንዶች እንደተጠቀመ በግልጽ ማየት ይቻላል።

12-13. በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የስብከቱንና የማስተማሩን ሥራ ለማጧጧፍ የትኞቹ ዝግጅቶች ተደረጉ?

12 በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የተከናወነውን ነገርም እንመልከት። በዋናው መሥሪያ ቤት የነበሩ ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች በራእይ 17:8 ላይ ምርምር ካደረጉ በኋላ ጦርነቱ የሚያመራው ወደ አርማጌዶን ሳይሆን የስብከት እንቅስቃሴያችንን ለማጧጧፍ ወደሚያስችል አንጻራዊ ሰላም ያለበት ጊዜ እንደሆነ ተገነዘቡ። በመሆኑም በወቅቱ ምክንያታዊ የማይመስል እርምጃ ወሰዱ። እነዚህ ወንድሞች በዓለም ዙሪያ በተለያዩ አገሮች የሚሰብኩና የሚያስተምሩ ሚስዮናውያንን ለማሠልጠን የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤትን አቋቋሙ። በጦርነቱ ወቅትም ጭምር ሚስዮናውያን ይላኩ ነበር። በተጨማሪም ታማኙ ባሪያ ሁሉም የጉባኤ አስፋፊዎች የመስበክና የማስተማር ችሎታቸውን እንዲያሻሽሉ ለማሠልጠን የቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ኮርስ b እንዲጀመር አደረገ። በዚህ መንገድ የአምላክ ሕዝቦች ከፊታቸው ለሚጠብቃቸው ሥራ ተዘጋጁ።

13 ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንመለከት፣ ይሖዋ በዚያ አስቸጋሪ ጊዜ ሕዝቦቹን እየመራቸው እንደነበር በግልጽ ማየት እንችላለን። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በበርካታ አገሮች ያሉ የይሖዋ ሕዝቦች የስብከቱን ሥራ ለማከናወን የሚያስችል መጠነኛ ሰላምና ነፃነት አግኝተዋል። እንዲያውም ሥራው በእጅጉ ተስፋፍቷል።

14. ከይሖዋ ድርጅትና ከሽማግሌዎች በምናገኘው መመሪያ ላይ መተማመን የምንችለው ለምንድን ነው? (ራእይ 2:1) (ሥዕሉንም ተመልከት።)

14 በዛሬው ጊዜ የበላይ አካል አባላት የክርስቶስን አመራር ለማግኘት ጥረት ማድረጋቸውን ቀጥለዋል። ለወንድሞች የሚሰጡት መመሪያ የይሖዋንና የኢየሱስን አመለካከት የሚያንጸባርቅ እንዲሆን ይፈልጋሉ። የወረዳ የበላይ ተመልካቾችና ሽማግሌዎች ደግሞ ለጉባኤዎች መመሪያ ይሰጣሉ። c ቅቡዓን ሽማግሌዎች በክርስቶስ ‘ቀኝ እጅ’ ውስጥ ናቸው። (ራእይ 2:1ን አንብብ።) እርግጥ ነው፣ እነዚህ ሽማግሌዎች ፍጹማን ስላልሆኑ ስህተት መሥራታቸው አይቀርም። ሙሴና ኢያሱ ስህተት የሠሩባቸው ጊዜያት ነበሩ፤ ሐዋርያትም እንደዚያው። (ዘኁ. 20:12፤ ኢያሱ 9:14, 15፤ ሮም 3:23) ያም ቢሆን፣ ክርስቶስ ታማኙን ባሪያና የተሾሙ ሽማግሌዎችን በጥንቃቄ እየመራቸው ነው። ደግሞም “እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ” እንዲህ ማድረጉን ይቀጥላል። (ማቴ. 28:20) በመሆኑም ኃላፊነት ባላቸው ወንድሞች አማካኝነት በሚሰጠን አመራር ላይ ለመተማመን የሚያበቃ አጥጋቢ ምክንያት አለን።

በዛሬው ጊዜ ያለው የበላይ አካል (አንቀጽ 14⁠ን ተመልከት)


የይሖዋን መመሪያ ምንጊዜም ከተከተልን እንጠቀማለን

15-16. የይሖዋን መመሪያዎች ስለተከተሉት ክርስቲያኖች ከሚገልጹት ተሞክሮዎች ምን ትምህርት አግኝተሃል?

15 የይሖዋን አመራር ምንጊዜም ከተከተልን በአሁኑ ጊዜም እንኳ በረከት እናገኛለን። ለምሳሌ አንዲ እና ሮቢን፣ ታማኙ ባሪያ አኗኗራችንን ቀላል እንድናደርግ የሰጠውን ምክር ለመከተል ወሰኑ። (ማቴ. 6:22) በዚህም የተነሳ በቲኦክራሲያዊ የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ ለመካፈል ራሳቸውን ማቅረብ ችለዋል። ሮቢን እንዲህ ብላለች፦ “በጣም ትናንሽ ቤቶች ውስጥ ኖረናል፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ ቤቶች ኩሽና የላቸውም። ቀደም ሲል በትርፍ ጊዜዬ ፎቶግራፍ ማንሳት በጣም እወድ ነበር፤ ሆኖም ፎቶ ለማንሳት የምጠቀምባቸውን አብዛኞቹን መሣሪያዎች መሸጥ ነበረብኝ። ይህን ያደረግኩት እያለቀስኩ ነው። ሆኖም የአብርሃምን ሚስት የሣራን ምሳሌ በመከተል ወደ ኋላ ሳይሆን ወደ ፊት ለመመልከት ቆርጬ ነበር።” (ዕብ. 11:15) እነዚህ ባልና ሚስት ያደረጉት ውሳኔ ምን ጥቅም አስገኝቶላቸዋል? ሮቢን እንዲህ ብላለች፦ “ያለንን ነገር ሁሉ ለይሖዋ እንደሰጠነው ስለምናውቅ ጥልቅ እርካታ አለን። በቲኦክራሲያዊ ፕሮጀክቶች ላይ ስንካፈል በአዲሱ ዓለም ውስጥ የሚኖረን ሕይወት ምን እንደሚመስል በትንሹም ቢሆን እናጣጥማለን።” አንዲም በሐሳቧ ይስማማል፤ እንዲህ ብሏል፦ “ጊዜያችንንና ጉልበታችንን በሙሉ መንግሥቱን ለመደገፍ እንዳዋልነው ስለምናውቅ እርካታ ይሰማናል።”

16 የይሖዋን አመራር ምንጊዜም የምንከተል ከሆነ ሌላስ ምን ጥቅም እናገኛለን? ማርሲያ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ግብ እንድናደርግ የሚሰጠንን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ወሰነች። (ማቴ. 6:33፤ ሮም 12:11) እንዲህ ብላለች፦ “በአንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የአራት ዓመት ነፃ የትምህርት ዕድል አግኝቼ ነበር። ሆኖም መንፈሳዊ ግቦችን መከታተል ፈለግኩ። በመሆኑም አገልግሎቴን እያከናወንኩ ራሴን ለማስተዳደር የሚያስችለኝ ሙያ ለመማር ወደ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት ገባሁ። በሕይወቴ ውስጥ ካደረግኳቸው በጣም ጥሩ ውሳኔዎች አንዱ ይህ ነው። አሁን በዘወትር አቅኚነት በደስታ እያገለገልኩ ነው። በተጨማሪም የሥራ ፕሮግራሜ አመቺ ስለሆነ በቤቴል ተመላላሽ ሆኜ ማገልገል እንዲሁም ሌሎች ልዩ መብቶችን ማግኘት ችያለሁ።”

17. የይሖዋን አመራር ምንጊዜም ከተከተልን ምን ሌሎች በረከቶች እናገኛለን? (ኢሳይያስ 48:17, 18)

17 ከድርጅቱ የምናገኘው ምክር ጥበቃም ያስገኝልናል። ለምሳሌ ከፍቅረ ነዋይ እንዲሁም የይሖዋን ሕጎች እንድንጥስ ሊያደርጉን ከሚችሉ አንዳንድ ድርጊቶች እንድንርቅ ምክር ይሰጠናል። በእነዚህ ጉዳዮች ረገድም የይሖዋን መመሪያ መከተላችን ይጠቅመናል። ንጹሕ ሕሊና ይኖረናል፤ እንዲሁም ከአላስፈላጊ ጭንቀት ራሳችንን እናድናለን። (1 ጢሞ. 6:9, 10) ይህም በሙሉ ልባችን ይሖዋን ለማምለክ ያስችለናል፤ በውጤቱም ወደር የሌለው ደስታ፣ ሰላምና እርካታ እናገኛለን።—ኢሳይያስ 48:17, 18ን አንብብ።

18. ምንጊዜም የይሖዋን አመራር ለመከተል ቁርጥ ውሳኔ ያደረግከው ለምንድን ነው?

18 ይሖዋ በታላቁ መከራም ሆነ በሺህ ዓመቱ ግዛት ወቅት እኛን ለመምራት ሰብዓዊ ወኪሎቹን መጠቀሙን እንደሚቀጥል ምንም ጥያቄ የለውም። (መዝ. 45:16) የግል ምርጫችንን መሥዋዕት ማድረግ ቢጠይቅብንም እንኳ ይህን መመሪያ መከተላችንን እንቀጥላለን? ይህ በዋነኝነት የተመካው በአሁኑ ጊዜ ለይሖዋ አመራር በምንሰጠው ምላሽ ላይ ነው። እንግዲያው ተግተው እንዲጠብቁን በተሾሙ ወንድሞች አማካኝነት የምናገኘውን መመሪያ ጨምሮ የይሖዋን አመራር ምንጊዜም እንከተል። (ኢሳ. 32:1, 2፤ ዕብ. 13:17) እንዲህ ካደረግን፣ መሪያችን ይሖዋ ከመንፈሳዊ አደጋዎች ጠብቆ ወደ መዳረሻችን ማለትም የዘላለም ሕይወት ወደምናገኝበት አዲስ ዓለም እንደሚመራን ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • ይሖዋ እስራኤላውያንን የመራቸው እንዴት ነው?

  • ይሖዋ የጥንቶቹን ክርስቲያኖች የመራቸው እንዴት ነው?

  • በአሁኑ ጊዜ የይሖዋን አመራር መከተላችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

መዝሙር 48 በየዕለቱ ከይሖዋ ጋር መሄድ

a ይሖዋ እስራኤላውያንን ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመምራት ‘ከሕዝቡ ፊት ፊት ይሄድ የነበረ’ መልአክም ሾሞላቸው ነበር። ይህ መልአክ ሚካኤል እንደሆነ ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል፤ “ሚካኤል” ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት የሚጠራበት ስም ነው።—ዘፀ. 14:19፤ 32:34

b ከጊዜ በኋላ ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ተብሎ መጠራት ጀመረ። በዛሬው ጊዜ ይህ ሥልጠና የሳምንቱ መሃል ስብሰባችን ክፍል ነው።

c በየካቲት 2021 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 18 ላይ የሚገኘውን “የበላይ አካሉ ሚና” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።