በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 5

መዝሙር 27 የአምላክ ልጆች መገለጥ

“በምንም ዓይነት አልጥልህም”!

“በምንም ዓይነት አልጥልህም”!

“[አምላክ] ‘ፈጽሞ አልተውህም፤ በምንም ዓይነት አልጥልህም’ ብሏል።”ዕብ. 13:5ለ

ዓላማ

ቅቡዓን ቀሪዎች በሙሉ ወደ ሰማይ ሲሄዱ አምላክ በምድር ላይ ያሉ አገልጋዮቹን እንደማይጥላቸው እንድንተማመን የሚያደርጉንን ምክንያቶች እንመለከታለን።

1. ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሙሉ ወደ ሰማይ ሄደው የሚያልቁት መቼ ነው?

 ከበርካታ ዓመታት በፊት የይሖዋ ሕዝቦች ‘ቅቡዓን ክርስቲያኖች ወደ ሰማይ ሄደው የሚያልቁት መቼ ነው?’ የሚለው ጥያቄ ያሳስባቸው ነበር። ቀደም ሲል፣ የአርማጌዶን ጦርነት ካበቃ በኋላ አንዳንድ ቅቡዓን ገነት በሆነችው ምድር ላይ ለተወሰነ ጊዜ ያህል ሊኖሩ እንደሚችሉ እናስብ ነበር። ሆኖም በሐምሌ 15, 2013 መጠበቂያ ግንብ ላይ በምድር ላይ የቀሩ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሙሉ የአርማጌዶን ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ወደ ሰማይ እንደሚሄዱ ተምረናል።—ማቴ. 24:31

2. ምን የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል? በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?

2 ይሁንና አንድ ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፦ ‘በታላቁ መከራ’ ወቅት በምድር ላይ ይሖዋን በታማኝነት የሚያገለግሉት የክርስቶስ “ሌሎች በጎች” ምን ዓይነት ሁኔታ ያጋጥማቸዋል? (ዮሐ. 10:16፤ ማቴ. 24:21) አንዳንዶች ‘ውድ ቅቡዓን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ወደ ሰማይ ከሄዱ በኋላ ግራ ልንጋባ እንችላለን፤ ወይም እንደተጣልን ሊሰማን ይችላል’ ብለው ይሰጋሉ። ወደ አእምሯቸው ሊመጡ የሚችሉ ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን እስቲ እንመልከት። ከዚያም የምንሰጋበት ምክንያት የለም የምንለው ለምን እንደሆነ እንመለከታለን።

ምን አያጋጥማቸውም?

3-4. አንዳንዶች ምን የሚል ስጋት ሊፈጠርባቸው ይችላል? ለምንስ?

3 አንዳንዶች፣ አመራር የሚሰጡት የበላይ አካል አባላት ከሌሉ ሌሎች በጎች ከእውነት ሊርቁ ይችላሉ የሚል ስጋት ሊፈጠርባቸው ይችላል። እዚህ መደምደሚያ ላይ እንዲደርሱ የሚያደርጓቸው አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ሁለት ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት። የመጀመሪያው ምሳሌ ከሊቀ ካህናቱ ዮዳሄ ጋር የተያያዘ ነው። ዮዳሄ ታማኝ የአምላክ አገልጋይ ነበር። እሱና ሚስቱ ዮሳቤት፣ ኢዮዓስ የተባለን ሕፃን ልጅ ሸሽገው አሳደጉ፤ እንዲሁም ጥሩና ታማኝ ንጉሥ እንዲሆን ረዱት። አረጋዊው ዮዳሄ በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ ኢዮዓስ ጥሩ ንጉሥ ነበር። ዮዳሄ ከሞተ በኋላ ግን ኢዮዓስ ወዲያውኑ መጥፎ ነገር መሥራት ጀመረ። ክፉ የሆኑትን መኳንንት በመስማት ይሖዋን ተወ።—2 ዜና 24:2, 15-19

4 ቀጣዩ ምሳሌ በሁለተኛው መቶ ዘመን ከነበሩት ክርስቲያኖች ጋር የተያያዘ ነው። በሕይወት የቀረው የመጨረሻ ሐዋርያ የሆነው ዮሐንስ በበርካታ ክርስቲያኖች ላይ በጎ ተጽዕኖ በማሳደር ይሖዋን በጽናት ማገልገላቸውን እንዲቀጥሉ ረድቷቸዋል። (3 ዮሐ. 4) ዮሐንስም ሆነ ሌሎቹ ታማኝ የኢየሱስ ሐዋርያት በወቅቱ መስፋፋት ከጀመረው ክህደት ጋር ለተወሰነ ጊዜ ያህል ሲታገሉ ቆይተዋል። (1 ዮሐ. 2:18፤ 2 ተሰ. 2:7) ዮሐንስ ከሞተ በኋላ ግን ክህደት እንደ ሰደድ እሳት ተዛመተ። በጥቂት አሥርተ ዓመታት ውስጥ የክርስቲያን ጉባኤ ሙሉ በሙሉ ተበከለ።

5. ከእነዚህ ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች በመነሳት ምን የሚል መደምደሚያ ላይ መድረስ አይኖርብንም?

5 እነዚህ ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ቅቡዓኑ ወደ ሰማይ ከሄዱ በኋላ የክርስቶስ ሌሎች በጎች ተመሳሳይ ነገር እንደሚያጋጥማቸው የሚጠቁሙ ናቸው? በዚያ ወቅት በምድር ላይ ያሉ ታማኝ ክርስቲያኖች እንደ ኢዮዓስ መጥፎ ጎዳና መከተል ይጀምሩ ይሆን? ወይም ደግሞ በሁለተኛው መቶ ዘመን እንደነበሩ በርካታ ክርስቲያኖች ወደ ክህደት ዞር ይሉ ይሆን? በጭራሽ! ቅቡዓኑ ወደ ሰማይ ከሄዱ በኋላ ሌሎች በጎች ተገቢውን እንክብካቤ እንደሚያገኙ እንዲሁም በመንፈሳዊ እንደሚጠናከሩ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

ንጹሕ አምልኮ አይበከልም

6. ስለ የትኞቹ ሦስት ዘመናት እንመረምራለን?

6 ከፊታችን በሚጠብቁን አስቸጋሪ ጊዜያትም እንኳ ንጹሕ አምልኮ እንደማይበከል እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ስለምንኖርበት ዘመን ከሚያስተምረው ነገር በመነሳት ነው። ይህ ዘመን የጥንቶቹ እስራኤላውያን ከኖሩበት ዘመንም ሆነ በሁለተኛው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ከኖሩበት ዘመን በእጅጉ የተለየ ነው። እንግዲያው እነዚህን ሦስት ዘመናት ቀረብ ብለን እንመርምር፦ (1) የጥንቶቹ እስራኤላውያን የኖሩበት ዘመን፣ (2) ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ የነበረው ዘመን እንዲሁም (3) እኛ የምንኖርበት ዘመን ማለትም “ነገሮች ሁሉ የሚታደሱበት ዘመን።”—ሥራ 3:21

7. በጥንቷ እስራኤል ዘመን ነገሥታቱና ሕዝቡ የክፋት አካሄድ ሲከተሉ ታማኝ የሆኑት እስራኤላውያን ተስፋ ያልቆረጡት ለምንድን ነው?

7 የጥንቶቹ እስራኤላውያን የኖሩበት ዘመን። ሙሴ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ እስራኤላውያንን እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “እኔ ከሞትኩ በኋላ ክፉ ድርጊት እንደምትፈጽሙና ካዘዝኳችሁ መንገድ ዞር እንደምትሉ በሚገባ አውቃለሁ።” (ዘዳ. 31:29) በተጨማሪም ሙሴ፣ እስራኤላውያን ካመፁ በግዞት እንደሚወሰዱ አስጠንቅቋቸዋል። (ዘዳ. 28:35, 36) ታዲያ እነዚህ ቃላት ተፈጽመዋል? አዎ። ከዚያ በኋላ ባሉት መቶ ዘመናት በርካታ ነገሥታት መጥፎ አካሄድ የተከተሉ ከመሆኑም ሌላ ሕዝቡ ከይሖዋ እንዲርቅ አድርገዋል። በዚህም የተነሳ ይሖዋ ክፉ የሆኑትን ሕዝቦቹን ተዋቸው፤ እንዲሁም የእስራኤል ነገሥታት መስመር እንዲቋረጥ አደረገ። (ሕዝ. 21:25-27) ሆኖም ታማኝ የሆኑ እስራኤላውያን አምላክ የተናገረው ቃል መፈጸሙን ማየታቸው እንዲበረታቱ አድርጓቸዋል።—ኢሳ. 55:10, 11

8. በሁለተኛው መቶ ዘመን የነበረው የክርስቲያን ጉባኤ መበከሉ ሊያስገርመን ይገባል? አብራራ።

8 ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ የነበረው ዘመን። በሁለተኛው መቶ ዘመን የነበረው የክርስቲያን ጉባኤ መበከሉ ሊያስገርመን ይገባል? በፍጹም። ኢየሱስ መጠነ ሰፊ ክህደት እንደሚከሰት አስቀድሞ ተናግሯል። (ማቴ. 7:21-23፤ 13:24-30, 36-43) ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ሐዋርያው ጴጥሮስና ሐዋርያው ዮሐንስም ኢየሱስ የተናገረው ትንቢት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. ፍጻሜውን ማግኘት እንደጀመረ መሥክረዋል። (2 ተሰ. 2:3, 7፤ 2 ጴጥ. 2:1፤ 1 ዮሐ. 2:18) በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. የክርስቲያን ጉባኤ ተበከለ። የክህደት ክርስትና በዓለም ላይ ያሉትን የሐሰት ሃይማኖቶች በሙሉ የምታመለክተው የታላቂቱ ባቢሎን ዋነኛ ክፍል ሆነ። አሁንም በመንፈስ መሪነት የተነገረው ትንቢት ፍጻሜውን አግኝቷል።

9. እኛ የምንኖርበት ዘመን ከጥንቷ እስራኤል ዘመንም ሆነ የሁለተኛው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ከኖሩበት ዘመን የሚለየው እንዴት ነው?

9 “ነገሮች ሁሉ የሚታደሱበት ዘመን።” እኛ የምንኖርበት ዘመን ከጥንቷ እስራኤል ዘመንም ሆነ በሁለተኛው መቶ ዘመን መጠነ ሰፊ ክህደት ከተከሰተበት ዘመን ይለያል። ይህ ዘመን ምን ተብሎ ይጠራል? ብዙውን ጊዜ፣ የዚህ ክፉ ሥርዓት ‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ ብለን እንጠራዋለን። (2 ጢሞ. 3:1) ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው በዚህ ወቅት ሌላ ረዘም ያለና ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ዘመንም ጀምሯል። ይህ ዘመን መሲሐዊው መንግሥት ሰዎችን ወደ ፍጽምና ደረጃ እስኪያደርስ እንዲሁም ምድርን ወደ ገነትነት እስኪለውጥ ድረስ ይቀጥላል። ይህ ዘመን “ነገሮች ሁሉ የሚታደሱበት ዘመን” ተብሎ ይጠራል። (ሥራ 3:21) ይህ ዘመን የጀመረው በ1914 ነው። በዚያ ዓመት የታደሰው ምንድን ነው? ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ በሰማይ ላይ መግዛት ጀመረ። ስለዚህ ይሖዋ እሱን የሚወክል ንጉሥ በድጋሚ ሾመ፤ ይህ ንጉሥ የታማኙ ንጉሥ የዳዊት ዘር ነው። ይሁንና ይሖዋ መልሶ ያቋቋመው ያንን ንግሥና ብቻ አይደለም። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ንጹሕ አምልኮ መልሶ መቋቋም ጀመረ። (ኢሳ. 2:2-4፤ ሕዝ. 11:17-20) ታዲያ ንጹሕ አምልኮ በድጋሚ ይበከል ይሆን?

10. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ በዘመናችን ስላለው ንጹሕ አምልኮ ምን ብሏል? (ኢሳይያስ 54:17) (ለ) እንዲህ ያሉት ትንቢቶች የሚያጽናኑን ለምንድን ነው?

10 ኢሳይያስ 54:17ን አንብብ። “አንቺን ለማጥቃት የተሠራ ማንኛውም መሣሪያ ይከሽፋል” የሚለውን ትንቢት ልብ በል። በመንፈስ መሪነት የተነገሩት እነዚህ ቃላት በዛሬው ጊዜ እየተፈጸሙ ነው። የሚከተለው የሚያጽናና ሐሳብም የሚናገረው ስለ ዘመናችን ነው፦ “ልጆችሽም ሁሉ ከይሖዋ የተማሩ ይሆናሉ፤ የልጆችሽም ሰላም ብዙ ይሆናል። በጽድቅ ጽኑ ሆነሽ ትመሠረቺያለሽ። . . . ምንም ነገር አትፈሪም፤ የሚያሸብርሽም ነገር አይኖርም፤ ወደ አንቺ አይቀርብምና።” (ኢሳ. 54:13, 14) “የዚህ ሥርዓት አምላክ” የሆነው ሰይጣንም እንኳ የይሖዋ ሕዝቦች እያካሄዱ ያሉትን የማስተማር ሥራ ሊያስቆመው አይችልም። (2 ቆሮ. 4:4) ንጹሕ አምልኮ መልሶ ተቋቁሟል፤ ደግሞም ከዚህ በኋላ ፈጽሞ አይበከልም። ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል። እኛን ለማጥቃት የተሠራ ማንኛውም መሣሪያ ይከሽፋል።

ምን ይከሰታል?

11. ቅቡዓኑ ወደ ሰማይ ሲሄዱ ሌሎች በጎች እንደማይተዉ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

11 ቅቡዓኑ ወደ ሰማይ ሲሄዱ ምን ይከሰታል? እረኛችን ኢየሱስ እንደሆነ አስታውስ። የክርስቲያን ጉባኤ ራስ እሱ ነው። ኢየሱስ “መሪያችሁ አንድ እሱም ክርስቶስ [ነው]” በማለት በግልጽ ተናግሯል። (ማቴ. 23:10) ንጉሣችን ምንጊዜም ሥራውን እንደሚያከናውን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። በምድር ላይ ያሉት የክርስቶስ ተከታዮች የሚመራቸው ክርስቶስ ራሱ ስለሆነ የሚፈሩበት ምክንያት አይኖርም። እርግጥ ነው፣ ክርስቶስ በዚያ ወቅት ሕዝቦቹን የሚመራቸው እንዴት እንደሆነ በእርግጠኝነት አናውቅም። ስለዚህ ሊያጽናኑን የሚችሉ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት።

12. (ሀ) ይሖዋ ሙሴ ከሞተ በኋላ ሕዝቦቹን የተንከባከባቸው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ኤልያስ ወደ ሌላ ምድብ ከተዛወረ በኋላ ሕዝቦቹን የተንከባከባቸው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

12 እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመግባታቸው በፊት ሙሴ ሞተ። ታዲያ በዚያ ወቅት የአምላክ ሕዝቦች ምን አጋጠማቸው? ይህ ታማኝ ሰው ስለሌለ ይሖዋ እነሱን መንከባከቡን አቁሟል? በፍጹም! ታማኝነታቸውን እስከጠበቁ ድረስ ይሖዋ ይንከባከባቸው ነበር። ሙሴ ከመሞቱ በፊት፣ ይሖዋ ኢያሱን የሕዝቡ መሪ አድርጎ እንዲሾመው አዞታል። ሙሴ ኢያሱን ለበርካታ አሥርተ ዓመታት አሠልጥኖታል። (ዘፀ. 33:11፤ ዘዳ. 34:9) በተጨማሪም አመራር የሚሰጡ ብቃት ያላቸው የሺህ አለቆች፣ የመቶ አለቆች፣ የሃምሳ አለቆችና የአሥር አለቆች ነበሩ። (ዘዳ. 1:15) የአምላክ ሕዝቦች የሚያስፈልጋቸውን እንክብካቤ አግኝተዋል። በኤልያስ ዘመንም ተመሳሳይ ሁኔታ አጋጥሞ ነበር። ኤልያስ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ግንባር ቀደም ሆኖ እስራኤላውያን በንጹሕ አምልኮ እንዲካፈሉ ይረዳቸው ነበር። ሆኖም ከጊዜ በኋላ ይሖዋ በደቡባዊው የይሁዳ መንግሥት ሌላ የአገልግሎት ምድብ ሰጠው። (2 ነገ. 2:1፤ 2 ዜና 21:12) ታዲያ አሥሩን ነገድ ባቀፈው የእስራኤል መንግሥት ውስጥ የነበሩ ታማኝ ሰዎች ተጥለዋል? በፍጹም! ኤልያስ ለተወሰኑ ዓመታት ኤልሳዕን ሲያሠለጥነው ቆይቷል። በተጨማሪም በሆነ መልኩ የተደራጁ የሠለጠኑ ‘የነቢያት ልጆች’ ነበሩ። (2 ነገ. 2:7) በመሆኑም ለአምላክ ሕዝቦች አመራር የሚሰጡ በርካታ ታማኝ ሰዎች ነበሩ። ይሖዋ ዓላማውን ማስፈጸሙን እንዲሁም ታማኝ አገልጋዮቹን መንከባከቡን ቀጥሏል።

ሙሴም (በስተ ግራ) ሆነ ኤልያስ (በስተ ቀኝ) ኃላፊነታቸውን የሚረከብ ሰው አሠልጥነዋል (አንቀጽ 12⁠ን ተመልከት)


13. በዕብራውያን 13:5ለ ላይ ምን ዋስትና እናገኛለን? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

13 ከእነዚህ ምሳሌዎች አንጻር፣ ቅቡዓኑ ወደ ሰማይ ሄደው ካለቁ በኋላ የአምላክ ሕዝቦች ምን የሚያጋጥማቸው ይመስልሃል? መልሱን መገመት አያስፈልገንም። መጽሐፍ ቅዱስ አጭርና የሚያጽናና መልስ ይሰጠናል፦ ይሖዋ በምድር ላይ ያሉትን ሕዝቦቹን በምንም ዓይነት አይጥላቸውም። (ዕብራውያን 13:5ለን አንብብ።) እንደ ሙሴ እና እንደ ኤልያስ ሁሉ በዛሬው ጊዜ አመራር የሚሰጡት ጥቂት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሌሎችን ማሠልጠን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ በሚገባ ይገነዘባሉ። የበላይ አካሉ አባላት የሌሎች በጎች አባላት የሆኑ ወንድሞች አመራር እንዲሰጡ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ሲያሠለጥኑ ቆይተዋል። ለምሳሌ የጉባኤ ሽማግሌዎችን፣ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችን፣ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላትን፣ በቤቴል ያሉ የበላይ ተመልካቾችን እንዲሁም ሌሎችን ለማሠልጠን በርካታ ትምህርት ቤቶችን አዘጋጅተዋል። የበላይ አካሉ በተለያዩ የበላይ አካሉ ኮሚቴዎች ውስጥ የሚያገለግሉ ረዳቶችን በግለሰብ ደረጃ ሲያሠለጥን ቆይቷል። እነዚህ ረዳቶች በአሁኑ ወቅት ከባድ ኃላፊነት እየተወጡ ነው። የክርስቶስን በጎች የመንከባከቡን ሥራ ለማስቀጠል ዝግጁ ናቸው።

የበላይ አካሉ፣ ረዳቶቹን ለማሠልጠን እንዲሁም በዓለም ዙሪያ ያሉ ሽማግሌዎችን፣ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችን፣ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላትን፣ በቤቴል ያሉ የበላይ ተመልካቾችንና ሚስዮናውያንን የሚያሠለጥኑ ትምህርት ቤቶችን ለማዘጋጀት ተግቶ እየሠራ ነው (አንቀጽ 13⁠ን ተመልከት)


14. የዚህ ውይይት ዋና ነጥብ ምንድን ነው?

14 የውይይታችን ዋና ነጥብ የሚከተለው ነው፦ በታላቁ መከራ መደምደሚያ አካባቢ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ወደ ሰማይ ሄደው ሲያልቁ ንጹሕ አምልኮ በምድር ላይ ይቀጥላል። ኢየሱስ ክርስቶስ አመራር ስለሚሰጣቸው የአምላክ ሕዝቦች ሥራቸው አይስተጓጎልም። እርግጥ ነው፣ በዚያ ወቅት የማጎጉ ጎግ ማለትም ግንባር የፈጠሩ ብሔራት ከባድ ጥቃት ይሰነዝሩብናል። (ሕዝ. 38:18-20) ሆኖም ይህ አጭር ጥቃት ይከሽፋል፤ የአምላክ ሕዝቦች ይሖዋን ማምለካቸውን እንዲያቆሙ አያደርጋቸውም። ይሖዋ ይታደጋቸዋል። ሐዋርያው ዮሐንስ፣ የክርስቶስን ሌሎች በጎች ያቀፈውን “እጅግ ብዙ ሕዝብ” በራእይ ተመልክቷል። ዮሐንስ እነዚህ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ‘ታላቁን መከራ አልፈው እንደመጡ’ ተነግሮታል። (ራእይ 7:9, 14) ስለዚህ ይሖዋ እንደሚያድናቸው እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

15-16. በራእይ 17:14 መሠረት የክርስቶስ ቅቡዓን በአርማጌዶን ጦርነት ወቅት ምን ያደርጋሉ? ይህስ የሚያበረታታን ለምንድን ነው?

15 ይሁንና አንዳንዶች ‘ቅቡዓኑስ ከምድር ከሄዱ በኋላ ምን ይሠራሉ?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ጥያቄ በቀጥታ ይመልስልናል። የዚህ ዓለም መንግሥታት ‘ከበጉ ጋር እንደሚዋጉ’ ይናገራል። እርግጥ መሸነፋቸው አይቀርም። ጥቅሱ “በጉ . . . ድል ይነሳቸዋል” ይላል። ከበጉ ጋር አብረው የሚሆኑትስ እነማን ናቸው? ጥቅሱ መልሱን ይሰጠናል። “የተጠሩት፣ የተመረጡትና የታመኑት” ናቸው። (ራእይ 17:14ን አንብብ።) እነዚህ እነማን ናቸው? ትንሣኤ ያገኙት ቅቡዓን ናቸው። ስለዚህ በታላቁ መከራ መገባደጃ አካባቢ ሁሉም ቅቡዓን ክርስቲያኖች ወደ ሰማይ ሄደው ካለቁ በኋላ ከሚሰጧቸው የመጀመሪያ ሥራዎች አንዱ መዋጋት ነው። እንዴት ያለ አስደናቂ ኃላፊነት ነው! አንዳንድ ቅቡዓን ክርስቲያኖች የይሖዋ ምሥክሮች ከመሆናቸው በፊት ተዋጊዎች ነበሩ። እንዲያውም አንዳንዶቹ ወታደር ሆነው ሠርተዋል። እውነተኛ ክርስቲያኖች ከሆኑ በኋላ ግን የሰላምን መንገድ ተማሩ። (ገላ. 5:22፤ 2 ተሰ. 3:16) ጦርነትን በሙሉ አስወገዱ። ወደ ሰማይ ከሄዱ በኋላ ግን ከክርስቶስና ከቅዱሳን መላእክቱ ጋር ሆነው ከአምላክ ጠላቶች ጋር በሚካሄደው የመጨረሻ ጦርነት ላይ ይዋጋሉ።

16 እስቲ አስበው። አንዳንድ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በምድር ላይ ሳሉ አረጋውያን፣ ምናልባትም አቅመ ደካሞች ነበሩ። ትንሣኤ አግኝተው ወደ ሰማይ ከሄዱ በኋላ ግን ኃያልና የማይሞቱ መንፈሳዊ ፍጥረታት ሆነው ከተዋጊው ንጉሣቸው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጎን ተሰልፈው ይዋጋሉ። የአርማጌዶን ጦርነት ካበቃ በኋላ የሰው ልጆችን ወደ ፍጽምና ደረጃ በማድረሱ ሥራ ይካፈላሉ። በእርግጥም ሰማይ ከሄዱ በኋላ በምድር ላይ ላሉት ውድ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ማከናወን የሚችሉት ነገር በምድር ላይ ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች ሆነው ሊያከናውኑ ከሚችሉት ነገር ጋር ጨርሶ አይወዳደርም!

17. በአርማጌዶን ጦርነት ወቅት ሁሉም የአምላክ አገልጋዮች ምንም ጉዳት እንደማይደርስባቸው እንዴት እናውቃለን?

17 የሌሎች በጎች አባል ነህ? ከሆንክ፣ ታላቁ የአርማጌዶን ጦርነት ሲጀምር ምን ማድረግ ይኖርብሃል? መልሱ ቀላል ነው፦ በይሖዋ ታመን፤ መመሪያውንም ተከተል። ይህ ምን ሊያካትት ይችላል? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ የሚል የሚያጽናና ሐሳብ ይዟል፦ “ወደ ውስጠኛው ክፍልህ ግባ፤ በርህንም ከኋላህ ዝጋ። ቁጣው እስኪያልፍ ድረስ ለጥቂት ጊዜ ተሸሸግ።” (ኢሳ. 26:20) በዚያ ወቅት በሰማይም ሆነ በምድር ላይ ያሉ የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች በሙሉ ምንም ጉዳት አይደርስባቸውም። እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ሁሉ እኛም “መንግሥታትም ቢሆኑ፣ አሁን ያሉት ነገሮችም ቢሆኑ፣ ወደፊት የሚመጡት ነገሮችም ቢሆኑ” ከአምላክ ፍቅር ሊለዩን እንደማይችሉ ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች ነን። (ሮም 8:38, 39) ይህን ምንጊዜም አትርሳ፦ ይሖዋ ይወድሃል፤ እንዲሁም በምንም ዓይነት አይጥልህም!

ቅቡዓን ክርስቲያኖች ወደ ሰማይ ሄደው ካለቁ በኋላ

  • በምድር ላይ ያሉ የአምላክ ሕዝቦች ምን አያጋጥማቸውም?

  • ንጹሕ አምልኮ እንደማይበከል እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

  • ይሖዋ ሕዝቡን እንደሚንከባከብ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

መዝሙር 8 ይሖዋ መጠጊያችን ነው