ለጥናት የሚረዱ ሐሳቦች
በሥራ ላይ የምታውላቸውን መንፈሳዊ ዕንቁዎች ፈልግ
መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ ተጨማሪ ምርምር በማድረግ መንፈሳዊ ዕንቁዎችን መፈለግ እንችላለን። ይሁንና የተሟላ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
ጥልቀት ያለው ጥናት አድርግ። ከመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ጋር በተያያዙ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ምርምር አድርግ። ለምሳሌ ዘገባውን የጻፈው ማን ነው? የተጻፈው ለማን ነው? የተጻፈው መቼ ነው? በወቅቱ የነበረው ሁኔታ ምን ይመስላል? ከዚያ በፊት ምን ተከናውኗል? ከዚያ በኋላስ?
ትምህርቱን ለማስተዋል ሞክር። ይህን ለማድረግ እንደሚከተሉት ባሉ ጥያቄዎች ላይ ምርምር ማድረግ ትችላለህ፦ ‘በዘገባው ላይ የተጠቀሱት ሰዎች ምን ተሰምቷቸዋል? የትኞቹን ባሕርያት አንጸባርቀዋል? እነዚህን ባሕርያት ማዳበር ወይም ከማዳበር መቆጠብ ያለብኝ ለምንድን ነው?’
ትምህርቱን በሥራ ላይ አውል። የተማርከውን ነገር በአገልግሎት ላይ ወይም ከሌሎች ሰዎች ጋር ካለህ ግንኙነት ጋር በተያያዘ በሥራ ላይ አውል። እንዲህ በማድረግ አምላካዊ ጥበብ እንዳለህ ማሳየት ትችላለህ። መጽሐፍ ቅዱስ “ጥበበኛ የሆነ ሁሉ እነዚህን ነገሮች ልብ ይላል” በማለት ይናገራል።—መዝ. 107:43
-
ጠቃሚ ምክር፦ በሳምንቱ መሃል በምናደርገው ስብሰባ ላይ ያለው ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት የሚለው ክፍል በትምህርቱ ተግባራዊነት ላይ እንድናተኩር የሚረዳን እንዴት እንደሆነ ለማስተዋል ሞክር። ይህ ክፍል ራሳችንን ልንጠይቅ የምንችላቸውን ጥያቄዎች፣ ልናሰላስልባቸው የምንችላቸውን ነጥቦች እንዲሁም ትምህርቱን የሚያጎሉ ሥዕሎችን ይዞ ይወጣል።