“የባዕድ አገር ሰዎች” ይሖዋን ‘በደስታ እንዲያገለግሉት’ መርዳት
“ይሖዋ የባዕድ አገር ሰዎችን ይጠብቃል።”—መዝ. 146:9
1, 2. (ሀ) አንዳንድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ምን ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመዋቸዋል? (ለ) የትኞቹ ጥያቄዎች ይነሳሉ?
“በቡሩንዲ የእርስ በርስ ጦርነት ሲጀምር ቤተሰባችን አንድ ትልቅ ስብሰባ እየተካፈለ ነበር” በማለት ሊጄ የተባለ ወንድም ተናግሯል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ሰዎች ሲሯሯጡና ሲታኮሱ ተመለከትን። ወላጆቼ ሕይወታችንን ለማትረፍ ሲሉ እኔን እንዲሁም 10 ወንድሞቼንና እህቶቼን ይዘው መሸሽ ጀመሩ፤ ከለበስነው ሌላ የያዝነው ነገር በጣም ጥቂት ነበር። ከጊዜ በኋላ ከቤተሰቤ አባላት አንዳንዶቹ 1,600 ኪሎ ሜትር ርቆ በማላዊ ወደሚገኝ የስደተኞች መጠለያ ደረሱ። ሌሎቻችን ግን ተበታተንን።”
2 በዓለም ዙሪያ በጦርነት አሊያም በሌሎች አስቸጋሪ ሁኔታዎች የተነሳ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ከ65,000,000 በላይ ስደተኞች አሉ፤ ይህም እስከ ዛሬ ከተመዘገበው ሁሉ ከፍተኛው ቁጥር ነው። * ከእነዚህ መካከል በሺዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ይገኙበታል። ብዙዎች የሚወዷቸውን ሰዎችና ንብረታቸውን አጥተዋል። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች፣ ምን ሌሎች ችግሮች አጋጥመዋቸዋል? ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሟቸውም ‘ይሖዋን በደስታ እንዲያገለግሉት’ እኛ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው? (መዝ. 100:2) ይሖዋን ለማያውቁ ስደተኞችስ ምሥራቹን ውጤታማ በሆነ መንገድ ማካፈል የምንችለው እንዴት ነው?
የስደተኞች ሕይወት
3. ኢየሱስም ሆነ በርካታ ደቀ መዛሙርቱ ለስደት ሕይወት የተጋለጡት ለምን ነበር?
3 የይሖዋ መልአክ፣ ንጉሥ ሄሮድስ ኢየሱስን ለመግደል እንዳሰበ ለዮሴፍ ከነገረው በኋላ ሕፃኑ ኢየሱስና ወላጆቹ ወደ ግብፅ ተሰደዱ። ሄሮድስ እስኪሞት ድረስም በዚያው ቆዩ። (ማቴ. 2:13, 14, 19-21) ከተወሰኑ አሥርተ ዓመታት በኋላ ደግሞ የጥንቶቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በደረሰባቸው ከባድ ስደት የተነሳ “በይሁዳና በሰማርያ ክልሎች ሁሉ ተበተኑ።” (ሥራ 8:1) ኢየሱስ ከተከታዮቹ መካከል ብዙዎቹ ቤታቸውን ጥለው ለመሸሽ እንደሚገደዱ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። “በአንድ ከተማ ስደት ሲያደርሱባችሁ ወደ ሌላ ከተማ ሽሹ” ብሎ ነበር። (ማቴ. 10:23) አንድ ሰው የሚሰደድበት ምክንያት ምንም ይሁን ምን፣ ስደት ምንጊዜም ከባድ ነው።
4, 5. ስደተኞች (ሀ) በሚሸሹበት ጊዜ (ለ) በመጠለያ ውስጥ በሚኖሩበት ወቅት ምን ዓይነት አደገኛ ሁኔታዎች ሊያጋጥሟቸው ይችላሉ?
4 ስደተኞች በሚሸሹበት ጊዜም ሆነ በስደተኞች መጠለያ ውስጥ በሚኖሩበት ወቅት አደገኛ ሁኔታዎች ሊያጋጥሟቸው ይችላሉ። የሊጄ ታናሽ ወንድም የሆነው ጋድ እንዲህ ብሏል፦ “ለበርካታ ሳምንታት በእግራችን የተጓዝን ሲሆን በመንገዳችን ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አስከሬን አልፈናል። በወቅቱ 12 ዓመቴ ነበር። እግሬ በጣም ስላበጠ ጥለውኝ እንዲሄዱ ለቤተሰቤ አባላት ነገርኳቸው። አባቴ ግን ለዓማፂያኑ ጥሎኝ መሄድ ስላልፈለገ ተሸክሞኝ መጓዝ ጀመረ። ወደ ይሖዋ እንጸልይና በእሱ እንታመን የነበረ ሲሆን የምንጨነቀው ለእያንዳንዱ ቀን ስለሚያስፈልገን ነገር ብቻ ነበር፤ አንዳንድ ጊዜ የምንበላው በመንገዳችን ላይ የምናገኘውን ማንጎ ብቻ ነበር።”—ፊልጵ. 4:12, 13
5 አብዛኞቹ የሊጄ ቤተሰብ አባላት፣ በተለያዩ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መጠለያዎች ውስጥ ብዙ ዓመታት አሳልፈዋል። እዚያም ቢሆን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ገጥመዋቸዋል። በአሁኑ ወቅት የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኖ የሚያገለግለው ሊጄ እንዲህ ብሏል፦ “ብዙዎቹ ሰዎች ሥራ የላቸውም። ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ቁጭ ብለው በማውራት፣ በመጠጣትና ቁማር በመጫወት ነበር፤ ከዚህም ሌላ ስርቆትና የሥነ ምግባር ብልግና የተለመዱ ነገሮች ናቸው።” በመጠለያው ውስጥ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች ይህን መጥፎ ተጽዕኖ ለመቋቋም ራሳቸውን በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ሙሉ በሙሉ ማስጠመድ ነበረባቸው። (ዕብ. 6:11, 12፤ 10:24, 25) በመንፈሳዊ ጤናሞች ሆነው ለመቀጠል ሲሉ ጊዜያቸውን ጠቃሚ በሆኑ እንቅስቃሴዎች ያሳልፉ ነበር፤ እንዲያውም ብዙዎቹ አቅኚዎች ነበሩ። በምድረ በዳ እንደነበሩት እስራኤላውያን ሁሉ እነሱም ያሉበት ሁኔታ ከጊዜ በኋላ እንደሚቀየር በማስታወስ አዎንታዊ አመለካከት ይዘው ለመቀጠል ይጥሩ ነበር።—2 ቆሮ. 4:18
ለስደተኞች ፍቅር ማሳየት
6, 7. (ሀ) “የአምላክ ፍቅር” ክርስቲያኖች ለተቸገሩ ወንድሞቻቸው ምን እንዲያደርጉ ያነሳሳቸዋል? (ለ) ምሳሌ ስጥ።
6 “የአምላክ ፍቅር” አንዳችን ለሌላው ፍቅር እንድናሳይ ግድ ይለናል፤ በተለይ ደግሞ አስከፊ ሁኔታዎች ላጋጠሟቸው ወንድሞቻችን ይህን ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። (1 ዮሐንስ 3:17, 18ን አንብብ።) በመጀመሪያው መቶ ዘመን በይሁዳ ረሃብ በተከሰተ ጊዜ በይሁዳ የነበሩትን ክርስቲያኖች ለመርዳት የእምነት ባልንጀሮቻቸው ዝግጅት አደረጉ። (ሥራ 11:28, 29) ሐዋርያው ጳውሎስና ጴጥሮስም፣ ክርስቲያኖች አንዳቸው ለሌላው የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ እንዲያሳዩ ምክር ሰጥተዋል። (ሮም 12:13፤ 1 ጴጥ. 4:9) ክርስቲያኖች ሊጎበኟቸው የሚመጡ ወንድሞችን እንዲቀበሉ የሚጠበቅባቸው ከሆነ በሕይወታቸው ላይ አደጋ የተጋረጠባቸውን ወይም በእምነታቸው ምክንያት ስደት የደረሰባቸውን የእምነት አጋሮቻቸውንማ ሊቀበሏቸው እንደሚገባ ምንም ጥያቄ የለውም!—ምሳሌ 3:27ን አንብብ። *
7 በቅርቡ በምሥራቃዊ ዩክሬን በተነሳው ግጭትና ስደት ምክንያት ወንዶችን፣ ሴቶችንና ልጆችን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ሕይወታቸውን ማጣታቸው የሚያሳዝን ነው። አብዛኞቹን ግን ዩክሬን ውስጥ በሌሎች ቦታዎች ያሉ መንፈሳዊ ወንድሞቻቸው ተቀብለዋቸዋል፤ ሌሎች በርካቶች ደግሞ በሩሲያ ያሉ የእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋ አርፈዋል። በሁለቱም አገሮች ውስጥ የሚገኙት ስደተኛ የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ‘የዓለም ክፍል እንዳልሆኑ’ በማስታወስ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ረገድ የገለልተኝነት አቋማቸውን ጠብቀዋል፤ እንዲሁም “የአምላክን ቃል ምሥራች” በቅንዓት መስበካቸውን ቀጥለዋል።—ዮሐ. 15:19፤ ሥራ 8:4
ስደተኞች እምነታቸውን እንዲያጠናክሩ መርዳት
8, 9. (ሀ) ስደተኞች በሄዱበት አገር ምን ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሊያጋጥሟቸው ይችላሉ? (ለ) ስደተኞችን በትዕግሥት ልንረዳቸው የሚገባው ለምንድን ነው?
8 አንዳንዶች በሚኖሩበት አገር ውስጥ ወደ ሌላ አካባቢ ለመሄድ የተገደዱ ሲሆን ሌሎች ብዙዎች ግን ጨርሶ ወደማያውቁት አገር ተሰደዋል። መንግሥታት ለስደተኞቹ ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ሊሰጧቸው ቢችሉም ስደተኞቹ የለመዱትን ምግብ አያገኙ ይሆናል። ሞቃት ከሆኑ አካባቢዎች የመጡ ስደተኞች በሕይወታቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በጣም ቀዝቃዛ በሆነ አካባቢ መኖር ሲጀምሩ ራሳቸውን ከብርድ ለመከላከል እንዴት መልበስ እንዳለባቸው ላያውቁ ይችላሉ። የመጡት ከገጠራማ አካባቢዎች ከሆነ ደግሞ ዘመናዊ የቤት ዕቃዎችን አጠቃቀም አያውቁ ይሆናል።
9 አንዳንድ መንግሥታት፣ ስደተኞቹ ከአዲሱ አካባቢያቸው ጋር እንዲላመዱ የሚረዱ ዝግጅቶች አሏቸው። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ ስደተኞቹ በጥቂት ወራት ውስጥ ራሳቸውን እንዲችሉ ይጠበቅባቸዋል። ከለውጡ ጋር መላመድ በጣም ከባድ ሊሆንባቸው ይችላል። በአንድ በኩል አዲስ ቋንቋና ባሕል መልመድ በሌላ በኩል ደግሞ ከጊዜ አጠቃቀም፣ ከቀረጥና ከሌሎች ነገሮች ክፍያ፣ ከትምህርት ቤት እንዲሁም ልጆችን ከመቅጣት ጋር በተያያዘ ምን እንደሚጠበቅባቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ማወቅ ብሎም ተግባራዊ ማድረግ ምን ያህል ከባድ ሊሆን እንደሚችል አስቡት! እንዲህ ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጠሟቸውን ወንድሞችና እህቶች በትዕግሥትና በአክብሮት ልትረዷቸው ትችላላችሁ?—ፊልጵ. 2:3, 4
10. ስደተኛ የሆኑ ወንድሞቻችንን እምነት ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)
10 በተጨማሪም አንዳንድ ጊዜ ባለሥልጣናት፣ ስደተኛ የሆኑ ወንድሞቻችን በሄዱበት አካባቢ ከሚገኘው ጉባኤ ጋር መገናኘት አስቸጋሪ እንዲሆንባቸው ሊያደርጉ ይችላሉ። አንዳንድ መንግሥታዊ ድርጅቶች፣ ወንድሞቻችን ጉባኤ አዘውትረው እንዳይገኙ እንቅፋት የሚሆንባቸውን ሥራ እንዲሠሩ ሊያስገድዷቸው ሞክረዋል፤ ይህን ለማድረግ ፈቃደኞች ካልሆኑ የሚያደርጉላቸውን ድጋፍ እንደሚያቋርጡባቸው አሊያም ጥገኝነት እንደሚከለክሏቸው ነግረዋቸዋል። ጥቂት ወንድሞች ስለፈሩና ምንም ምርጫ እንደሌላቸው ስለተሰማቸው እንዲህ ያለውን ሥራ ለመሥራት ተስማምተዋል። በመሆኑም ስደተኛ የሆኑ ወንድሞቻችንን፣ በተቻለ መጠን እንደደረሱ ለማግኘት ጥረት ማድረጉ በጣም አስፈላጊ ነው። ስለ እነሱ እንደምናስብ እንዲያውቁ ማድረጋችን ጠቃሚ ነው። ርኅራኄ ማሳየታችንና የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ መስጠታችን እምነታቸውን ያጠናክረዋል።—ምሳሌ 12:25፤ 17:17
ለስደተኞች የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ መስጠት
11. (ሀ) ስደተኞች መጀመሪያ ላይ ምን ዓይነት እርዳታ ያስፈልጋቸዋል? (ለ) ስደተኛ የሆኑ ወንድሞች አመስጋኝ መሆናቸውን ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?
11 ወንድሞቻችን እኛ ወዳለንበት አካባቢ እንደደረሱ ምግብ፣ ልብስ ወይም ሌሎች መሠረታዊ ነገሮችን መስጠት ሊያስፈልገን ይችላል። * ለአንድ ወንድም ክራባት እንደመስጠት ያለ ቀላል የሚመስል የደግነት ተግባር እንኳ ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። ስደተኛ የሆኑት ወንድሞችም፣ ሌሎች አንድ ነገር ሊያደርጉላቸው እንደሚገባ ከመጠበቅ ይልቅ ለተደረገላቸው እርዳታ አመስጋኝ ሊሆኑ ይገባል፤ ይህም በእንግድነት የተቀበሏቸው ወንድሞች በመስጠታቸው እንዲደሰቱ ያደርጋል። እርግጥ ነው፣ ስደተኛ የሆኑት ወንድሞች ሁልጊዜ የሌሎችን ልግስና የሚጠብቁ ከሆነ ለራሳቸው ያላቸውን አክብሮት ሊያጡ ብሎም ከወንድሞቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት ሊሻክር ይችላል። (2 ተሰ. 3:7-10) ያም ቢሆን ስደተኞች እርዳታ አያስፈልጋቸውም ማለት አይደለም።
12, 13. (ሀ) ለስደተኞች የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ መስጠት የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ምሳሌ ስጥ።
12 ለስደተኞች የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ መስጠት ሲባል ብዙ ገንዘብ መስጠት አለብን ማለት አይደለም፤ በዋነኝነት የሚያስፈልጋቸው ነገር ጊዜና ትኩረት ነው። የሕዝብ መጓጓዣ መጠቀም እንዲሁም ለጤና ጠቃሚ የሆኑ ምግቦችን በርካሽ ዋጋ ማግኘት የሚችሉበትን መንገድ ብናሳያቸው እንደሚጠቀሙ የታወቀ ነው፤ በተጨማሪም ለሥራ ሊገለገሉባቸው የሚችሉ መሣሪያዎችን
ማግኘት ወይም ገቢ የሚያስገኝላቸውን ሙያ መማር የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ልንጠቁማቸው እንችላለን። እነዚህ ነገሮች ቀላል ቢመስሉም ለስደተኞቹ ትልቅ ጥቅም አላቸው። ከሁሉ በላይ ደግሞ ከአዲሱ ጉባኤያቸው ጋር በደንብ እንዲተዋወቁ ልትረዷቸው ትችላላችሁ። የሚቻል ከሆነ ወደ ጉባኤ ይዛችኋቸው ሂዱ። ከዚህም ሌላ በክልላችሁ ውስጥ የመንግሥቱን መልእክት ለሰዎች እንዴት መንገር እንደሚችሉ ጠቁሟቸው። ስደተኛ የሆኑትን ወንድሞችና እህቶች አገልግሎት ይዛችኋቸው ውጡ።13 በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ አራት ስደተኞች ወደ አንድ ጉባኤ ሲሄዱ፣ በዚያ ያሉት ሽማግሌዎች መኪና መንዳትና ኮምፒውተር መጠቀም ያስተማሯቸው ከመሆኑም ሌላ የሥራ ማመልከቻ እንዴት እንደሚጻፍ አሳዩአቸው፤ እንዲሁም ለይሖዋ አገልግሎት ቅድሚያ ለመስጠት ጊዜያቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ረዷቸው። (ገላ. 6:10) ብዙም ሳይቆይ አራቱም አቅኚዎች ሆኑ። ወንድሞች ያደረጉላቸው እገዛ ብሎም እነሱ ራሳቸው መንፈሳዊ ግቦች ላይ ለመድረስ ያደረጉት ጥረት በመንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉና በሰይጣን ሥርዓት ውስጥ እንዳይጠላለፉ ረድቷቸዋል።
14. (ሀ) ስደተኞች ምን ዓይነት ፈተናዎችን መቋቋም ያስፈልጋቸዋል? (ለ) ምሳሌ ስጥ።
14 እንደ ሌሎች ክርስቲያኖች ሁሉ በስደት ላይ የሚገኙ ወንድሞችና እህቶችም፣ ከይሖዋ ጋር ካላቸው ዝምድና ይልቅ ለቁሳዊ ነገሮች ቅድሚያ እንዲሰጡ የሚቀርብላቸውን ፈተና እና የሚደርስባቸውን ጫና መቋቋም ይኖርባቸዋል። * ቀደም ሲል የተጠቀሰው ሊጄም ሆነ ወንድሞቹና እህቶቹ በሚሸሹበት ወቅት አባታቸው ስለ እምነት ያስተማራቸውን ነገር ፈጽሞ አይረሱትም። ሊጄ እንዲህ ብሏል፦ “አባታችን ከያዝናቸው ጥቂት ነገሮች መካከል መሠረታዊ ያልሆኑትን አንድ በአንድ እያወጣ ጣላቸው። በመጨረሻም ባዶ የሆነውን ቦርሳ እያሳየን ‘ቦርሳው ውስጥ ከነበሩት ነገሮች መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ አያስፈልጉንም!’ አለን።”—1 ጢሞቴዎስ 6:8ን አንብብ።
ስደተኞች ይበልጥ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ማሟላት
15, 16. የስደተኞችን (ሀ) መንፈሳዊ (ለ) ስሜታዊ ፍላጎት ለማሟላት ምን ማድረግ እንችላለን?
15 ስደተኛ የሆኑ ሰዎች ከቁሳዊ እርዳታ ይበልጥ የሚያስፈልጋቸው ነገር መንፈሳዊና ስሜታዊ ፍላጎታቸውን ማሟላት ነው። (ማቴ. 4:4) ሽማግሌዎች፣ ስደተኞቹ በሚናገሩት ቋንቋ የተዘጋጁ ጽሑፎችን በመስጠት እንዲሁም የእነሱን ቋንቋ ከሚናገሩ ወንድሞች ጋር በማገናኘት ሊረዷቸው ይችላሉ። በርካታ ስደተኞች በጣም ከሚቀርቧቸው ዘመዶቻቸው፣ ጎረቤቶቻቸውና የጉባኤያቸው አባላት ተለያይተዋል። በመካከላችን ሲሆኑ ይሖዋ እንደሚወዳቸውና እንደሚያስብላቸው እንዲሰማቸው ልናደርግ ይገባል። ይህ ካልሆነ ግን ባሕላቸውንና ያሳለፉትን ሕይወት ከሚያውቁ የማያምኑ ዘመዶቻቸው አሊያም የአገራቸው ሰዎች ጋር ለመቀራረብ ሊፈተኑ ይችላሉ። (1 ቆሮ. 15:33) በጉባኤ ውስጥ የባይተዋርነት ስሜት እንዳይሰማቸው የምናደርግ ከሆነ “የባዕድ አገር ሰዎችን ይጠብቃል” ከተባለለት ከይሖዋ ጋር አብረን የመሥራት መብት እናገኛለን።—መዝ. 146:9
16 እንደ ኢየሱስና ቤተሰቡ ሁሉ በስደት ወደ ሌላ አገር የሄዱ አንዳንድ ሰዎችም አሳዳጆቻቸው በሥልጣን ላይ እስካሉ ድረስ ወደ አገራቸው መመለስ አይችሉ ይሆናል። ከዚህም ሌላ ሊጄ እንደተናገረው “የቤተሰባቸው አባላት ተገደው ሲደፈሩና ሲገደሉ የተመለከቱ በርካታ ወላጆች፣ ልጆቻቸውን እነዚህ አስከፊ ድርጊቶች ወደተፈጸሙበት ቦታ መልሰው መውሰድ አይፈልጉም።” ስደተኞችን በሚቀበሉ አገሮች ውስጥ ያሉ ወንድሞች፣ እንዲህ ያለ ስሜትን የሚጎዳ ችግር ያጋጠማቸውን ሰዎች ለማጽናናት ‘የሌላውን ስሜት መረዳት፣ የወንድማማች መዋደድ ማሳየት፣ ከአንጀት መራራት እንዲሁም ትሑት መሆን’ ያስፈልጋቸዋል። (1 ጴጥ. 3:8) ከአገራቸው ተሰደው የወጡ ብዙዎች፣ ሌሎችን መቅረብ ሊከብዳቸው እንዲሁም ስላጋጠማቸው መከራ በተለይ በልጆቻቸው ፊት ማውራት ሊያሳፍራቸው ይችላል። ‘እኔ በእነሱ ቦታ ብሆን ኖሮ ምን እንዲደረግልኝ እፈልግ ነበር?’ ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ።—ማቴ. 7:12
ይሖዋን ለማያውቁ ስደተኞች መስበክ
17. ስደተኞች ምሥራቹን በመስማታቸው እረፍት ያገኙት እንዴት ነው?
17 በዛሬው ጊዜ ብዙ ስደተኞች የሚመጡት በስብከቱ ሥራችን ላይ ገደብ ከተጣለባቸው አገሮች ነው። ስደተኞችን በሚቀበሉ አገሮች ውስጥ ላሉ ቀናተኛ ምሥክሮች ምስጋና ይግባቸውና፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች “የመንግሥቱን ቃል” ለመጀመሪያ ጊዜ የመስማት አጋጣሚ አግኝተዋል። (ማቴ. 13:19, 23) ‘ሸክማቸው የከበዳቸው’ ብዙ ሰዎች በስብሰባዎቻችን ላይ ተገኝተው መንፈሳዊ እርዳታ በማግኘታቸው “አምላክ በእርግጥ በመካከላችሁ ነው” ለማለት ችለዋል።—ማቴ. 11:28-30፤ 1 ቆሮ. 14:25
18, 19. ለስደተኞች ስንሰብክ ጥበበኞች እንደሆንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
18 ለስደተኞች የሚሰብኩ ክርስቲያኖች “ጠንቃቆች” አልፎ ተርፎም ‘ብልሆች’ መሆን ይኖርባቸዋል። (ማቴ. 10:16፤ ምሳሌ 22:3) የሚያሳስባቸውን ጉዳይ ሲነግሯችሁ በጥሞና ማዳመጥ ያለባችሁ ቢሆንም ስለ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ከመወያየት ተቆጠቡ። ቅርንጫፍ ቢሮውም ሆነ የአካባቢው ባለሥልጣናት የሚሰጧችሁን መመሪያ ተከተሉ፤ ራሳችሁንም ሆነ ሌሎችን ለአደጋ የሚያጋልጥ ምንም ነገር አታድርጉ። ለስደተኞቹ ሃይማኖትና ባሕል አክብሮት እንዳላችሁ አሳዩ። ለምሳሌ ያህል፣ ከአንዳንድ አገሮች የሚመጡ ሰዎች ተገቢ ስለሚባለው የሴቶች አለባበስ የራሳቸው አመለካከት ያላቸው ሲሆን ከዚያ የተለየ አለባበስ ቅር ያሰኛቸዋል። ስለዚህ ለስደተኞች ስትሰብኩ እነሱን ላለማስከፋት በአለባበሳችሁ ረገድ መጠንቀቅ ያስፈልጋችኋል።
19 ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ላይ እንደተጠቀሰው ደግ ሳምራዊ፣ እኛም የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑትን ጨምሮ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሰዎችን መርዳት እንፈልጋለን። (ሉቃስ 10:33-37) ይህን ማድረግ የምንችልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ደግሞ ለእነዚህ ሰዎች ምሥራቹን መስበክ ነው። በርካታ ስደተኞችን የረዳ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “እኛ የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆንን እና ዋነኛ ዓላማችን ሰዎችን በመንፈሳዊ እንጂ በቁሳዊ መርዳት እንዳልሆነ ገና ከጅምሩ ግልጽ ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። አለዚያ አንዳንዶች ወደ እኛ የሚመጡት ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት ብቻ ሊሆን ይችላል።”
አስደሳች ውጤቶች
20, 21. (ሀ) ለስደተኞች ክርስቲያናዊ ፍቅር ማሳየታችን ምን ጥሩ ውጤት ያስገኛል? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?
20 ‘ለባዕድ አገር ሰዎች’ ክርስቲያናዊ ፍቅር ማሳየታችን ጥሩ ውጤት ያስገኛል። ለምሳሌ፣ የአንዲት እህት ቤተሰቦች ኤርትራ ውስጥ በደረሰባቸው ስደት ምክንያት ወደ ሱዳን ሸሹ። አራት ልጆቿ በረሃ ውስጥ ለስምንት ቀናት ያህል አድካሚ የሆነ ጉዞ ካደረጉ በኋላ ሱዳን ደረሱ። እህት እንዲህ ብላለች፦ “ሱዳን ያሉት ወንድሞች እንደ ቤተሰባቸው አድርገው የተቀበሏቸው ሲሆን ምግብ፣ ልብስና መኖሪያ እንዲሁም ለመጓጓዣ የሚሆን ገንዘብ ሰጧቸው። የሚያመልኩት አምላክ አንድ ስለሆነ ብቻ የባዕድ አገር ሰዎችን ቤታቸው የሚቀበሉ የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ናቸው!”—ዮሐንስ 13:35ን አንብብ።
21 በስደት አሊያም በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ ከአገራቸው ውጭ ስለሚኖሩ ሰዎች በርካታ ልጆችስ ምን ማለት ይቻላል? የሚቀጥለው ርዕስ እነዚህ ልጆች ይሖዋን በደስታ እንዲያገለግሉ ሁላችንም ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያብራራል።
^ አን.2 በዚህ ርዕስ ውስጥ “ስደተኛ” የሚለውን ቃል የምንጠቀመው ከጦርነት፣ ከጥቃት ወይም ከተፈጥሮ አደጋ ለማምለጥ ሲሉ ከሚኖሩበት ቦታ ተፈናቅለው በአገራቸው ውስጥ ወደ ሌላ ቦታ የሸሹ አሊያም ወደ ውጭ አገር ለመሄድ የተገደዱ ሰዎችን ለማመልከት ነው። የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር እንደገለጸው በዛሬው ጊዜ በዓለም ዙሪያ “ከ113 ሰዎች 1ዱ . . . ከሚኖርበት አካባቢ ይፈናቀላል።”
^ አን.6 በጥቅምት 2016 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 8-12 ላይ የወጣውን “ለእንግዶች ደግነት ማሳየትን አትርሱ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
^ አን.11 ስደተኞች ወደ አንድ አካባቢ ከደረሱ ብዙም ሳይቆይ ሽማግሌዎች የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ የተደራጀ ሕዝብ ምዕራፍ 8 አንቀጽ 30 ላይ የሚገኘውን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ሽማግሌዎች በአገራቸው ወደሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ በjw.org አማካኝነት ደብዳቤ በመጻፍ፣ ስደተኞቹ ከመጡባቸው ጉባኤዎች ጋር መገናኘት ይችላሉ። እስከዚያው ድረስ ግን ሽማግሌዎች፣ ስደተኞቹን ስለ ጉባኤያቸውና ስለ አገልግሎታቸው አሳቢነት በሚንጸባረቅበት መንገድ በመጠየቅ ስላሉበት መንፈሳዊ ሁኔታ ማወቅ ይችላሉ።
^ አን.14 በሚያዝያ 15, 2014 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 17-26 ላይ የወጡትን “ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚችል የለም” እና “ደፋር ሁን—ይሖዋ ረዳትህ ነው!” የሚሉ ርዕሶች ተመልከት።