ፍቅራችሁ እንዳይቀዘቅዝ ተጠንቀቁ
“ክፋት እየበዛ ስለሚሄድ የብዙዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል።”—ማቴ. 24:12
1, 2. (ሀ) ኢየሱስ በማቴዎስ 24:12 ላይ የተናገረው ሐሳብ የመጀመሪያ ፍጻሜውን ያገኘው በማን ላይ ነበር? (ለ) የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ከጥንቶቹ ክርስቲያኖች አብዛኞቹ ፍቅራቸው እንዳልቀዘቀዘ የሚጠቁመው እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)
ኢየሱስ ‘የዚህን ሥርዓት መደምደሚያ’ አስመልክቶ ከሰጠው ምልክት ገጽታዎች አንዱ ‘የብዙዎች ፍቅር የሚቀዘቅዝ’ መሆኑ ነው። (ማቴ. 24:3, 12) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት አይሁዳውያን የአምላክ ሕዝብ እንደሆኑ ቢናገሩም ለአምላክ ያላቸው ፍቅር ቀዝቅዞ ነበር።
2 በሌላ በኩል ግን በወቅቱ የነበሩት አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ‘ስለ ክርስቶስ የሚናገረውን ምሥራች’ በመስበኩ ሥራ በትጋት ይካፈሉ እንዲሁም ለአምላክ፣ ለእምነት ባልንጀሮቻቸውና ለሌሎች ሰዎች ፍቅር እንዳላቸው የሚያሳይ ነገር ያከናውኑ ነበር። (ሥራ 2:44-47፤ 5:42) ያም ቢሆን በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ የኢየሱስ ተከታዮች ፍቅራቸው ቀዝቅዞ ነበር።
3. የአንዳንድ ክርስቲያኖች ፍቅር እንዲቀዘቅዝ ያደረገው ምን ሊሆን ይችላል?
3 ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ከተነሳ በኋላ፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በኤፌሶን የነበረውን ጉባኤ “የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፤ ይኸውም መጀመሪያ ላይ የነበረህን ፍቅር ትተሃል” ብሎት ነበር። (ራእይ 2:4) እነዚህ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ፍቅራቸውን እንዲተዉ ያደረጋቸው ምን ሊሆን ይችላል? ለዚህ አንዱ ምክንያት፣ በዙሪያቸው ያሉት በሥጋዊ ፍላጎታቸው ላይ የሚያተኩሩ ሰዎች ያሳደሩባቸው ተጽዕኖ ሊሆን ይችላል። (ኤፌ. 2:2, 3) በዛሬው ጊዜ እንዳሉት በርካታ ከተሞች ሁሉ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረችው ኤፌሶንም መጥፎ ድርጊቶች የተስፋፉባት ከተማ ነበረች። ከተማዋ በጣም ሀብታም ስትሆን ነዋሪዎቿ ትኩረታቸው በዋነኝነት ያረፈው በመዝናኛ እንዲሁም የቅንጦትና የተመቻቸ ሕይወት በመምራት ላይ ነበር። ደስታ ያመጣሉ በሚባሉ ነገሮች በመጠመዳቸው ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ማሳየት አልቻሉም። በተጨማሪም ዓይን ያወጣ ምግባርና ልቅ የሆነ የሥነ ምግባር ብልግና ተስፋፍቶ ነበር።
4. (ሀ) በዘመናችን የሰዎች ፍቅር የቀዘቀዘው እንዴት ነው? (ለ) ፍቅራችን ምንጊዜም ጠንካራ እንዲሆን ማድረግ ያለብን በየትኞቹ ሦስት አቅጣጫዎች ነው?
4 ኢየሱስ ፍቅር እንደሚቀዘቅዝ የተናገረው ትንቢት በዘመናችንም እየተፈጸመ ነው። በዛሬው ጊዜ ያሉ ሰዎች ለአምላክ ያላቸው ፍቅር እየቀነሰ መጥቷል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለአምላክ ጀርባቸውን የሰጡ ሲሆን የሰው ልጆች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ሰብዓዊ ተቋማት መፍታት እንደሚችሉ ይሰማቸዋል። በመሆኑም ይሖዋ አምላክን የማያመልኩ ሰዎች ፍቅራቸው ይበልጥ እየቀዘቀዘ ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን በኤፌሶን የነበረው ጉባኤ ካጋጠመው ሁኔታ መመልከት እንደሚቻለው፣ በዛሬው ጊዜ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖችም በሚመሩት የተደላደለ ሕይወት ረክተው ሊቀመጡና ፍቅራቸው ሊቀዘቅዝ ይችላል። በመሆኑም ፍቅራችን ምንጊዜም ጠንካራ እንዲሆን ማድረግ ያለብን በየትኞቹ ሦስት አቅጣጫዎች እንደሆነ እስቲ እንመልከት፤ እነሱም (1) ለይሖዋ ያለን ፍቅር፣ (2) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሚገኘው እውነት ያለን ፍቅር፣ (3) ለወንድሞቻችን ያለን ፍቅር ናቸው።
ለይሖዋ ያለን ፍቅር
5. ለአምላክ ፍቅር ማዳበር ያለብን ለምንድን ነው?
5 ኢየሱስ ፍቅር እንደሚቀዘቅዝ ማስጠንቀቂያ በሰጠበት ዕለት፣ ከሁሉ አስበልጠን ልንወደው የሚገባው ማንን እንደሆነ ተናግሯል። ኢየሱስ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “‘አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ አእምሮህ ውደድ።’ ይህ ከሁሉ የሚበልጠውና የመጀመሪያው ትእዛዝ ነው።” (ማቴ. 22:37, 38) በእርግጥም ለአምላክ ጥልቅ ፍቅር ማዳበራችን የይሖዋን ትእዛዛት እንድንፈጽም፣ እንድንጸና እንዲሁም ክፉ የሆነውን ነገር እንድንጠላ ያነሳሳናል። (መዝሙር 97:10ን አንብብ።) ይሁን እንጂ ሰይጣንና በእሱ ቁጥጥር ሥር ያለው ዓለም ለአምላክ ያለን ፍቅር እንዲቀዘቅዝ ለማድረግ ይጥራሉ።
6. ሰዎች ለአምላክ ያላቸው ፍቅር መቀዝቀዙ ምን አስከትሏል?
6 ዓለም ስለ ፍቅር ያለው አመለካከት የተዛባ ነው። ሰዎች ከፈጣሪ ይልቅ “ራሳቸውን የሚወዱ” ሆነዋል። (2 ጢሞ. 3:2) ሰይጣን በሚመራው በዚህ ዓለም ውስጥ “የሥጋ ምኞት፣ የዓይን አምሮትና ኑሮዬ ይታይልኝ [የሚለው መንፈስ]” በስፋት ይታያል። (1 ዮሐ. 2:16) ሐዋርያው ጳውሎስ፣ የእምነት ባልንጀሮቹ ሥጋዊ ምኞቶችን ለማርካት ከመጣር መቆጠብ እንዳለባቸው ሲያሳስብ እንዲህ ብሏል፦ “በሥጋዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ሞት ያስከትላልና፤ . . . በሥጋዊ ነገሮች ላይ ማተኮር የአምላክ ጠላት ያደርጋል።” (ሮም 8:6, 7) በእርግጥም ቁሳዊ ነገሮችን በማሳደድ ወይም የፆታ ፍላጎታቸውን በማርካት ላይ ያተኮሩ ሰዎች ለሐዘንና ለብዙ ሥቃይ ተዳርገዋል።—1 ቆሮ. 6:18፤ 1 ጢሞ. 6:9, 10
7. በዛሬው ጊዜ ያሉ የክርስቶስ ተከታዮች ምን አደጋዎች ተጋርጠውባቸዋል?
7 በአንዳንድ አገሮች ውስጥ አምላክ የለም የሚሉ፣ መኖሩን በእርግጠኝነት ማወቅ እንደማይቻል የሚናገሩ አሊያም የዝግመተ ለውጥን ጽንሰ ሐሳብ የሚያራምዱ ምሁራን፣ ሰዎች ለአምላክ ያላቸው ፍቅር እንዲቀዘቅዝ ብቻ ሳይሆን ጨርሶ በአምላክ እንዳያምኑ የሚያደርጉ ሐሳቦችን ያስፋፋሉ። አንድ ሰው በፈጣሪ መኖር ሊያምን የሚችለው ሞኝ አሊያም ማስተዋል የሚጎድለው ከሆነ ብቻ እንደሆነ ብዙዎችን አሳምነዋል። በሌላ በኩል ደግሞ የሳይንስ ሊቃውንት ትልቅ ቦታ ይሰጣቸዋል፤ በመሆኑም ሰዎች ለፈጣሪያችን ሊሰጥ የሚገባውን ክብር ለእነሱ እየሰጡ ነው። (ሮም 1:25) እንደነዚህ ላሉ ትምህርቶች ጆሯችንን የምንሰጥ ከሆነ ከይሖዋ ልንርቅና ፍቅራችን ሊቀዘቅዝ ይችላል።—ዕብ. 3:12
8. (ሀ) በርካታ የይሖዋ አገልጋዮች ምን ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል? (ለ) መዝሙር 136 ምን ማረጋገጫ ይሰጠናል?
8 በተስፋ መቁረጥ ስሜት ከተሸነፍንም እምነታችን ሊዳከምና ለአምላክ ያለን ፍቅር ሊቀዘቅዝ ይችላል። ሰይጣን በሚቆጣጠረው በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ ሁላችንም 1 ዮሐ. 5:19) ምናልባትም ከዕድሜ መግፋት፣ ከጤና መታወክ ወይም ከኢኮኖሚያዊ ችግሮች ጋር እየታገልን ሊሆን ይችላል። አሊያም ደግሞ ብቃት የለኝም የሚለው ስሜት፣ የጠበቅናቸው ነገሮች አለመፈጸማቸው ወይም የግል ድክመቶቻችን ይረብሹን ይሆናል። ይሁንና እንዲህ ያሉት ሁኔታዎች ወይም ስሜቶች፣ ይሖዋ እንደተወን እንዲሰማን ፈጽሞ ሊያደርጉን አይገባም። እንዲያውም ይሖዋ ለእኛ ስላለው ጽኑ ፍቅር በሚገልጹ ሐሳቦች ላይ ማሰላሰል ይኖርብናል። በመዝሙር 136:23 ላይ የሚገኘው “መንፈሳችን ተደቁሶ በነበረበት ጊዜ አስታወሰን፤ ታማኝ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራልና” የሚለው ሐሳብ እንዲህ ያለ ማበረታቻ ይሰጠናል። በእርግጥም ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ያለው ታማኝ ፍቅር ምንጊዜም አይለወጥም። በመሆኑም ይሖዋ “እርዳታ ለማግኘት [የምናቀርበውን] ልመና” እንደሚሰማና ምላሽ እንደሚሰጠን እርግጠኛ መሆን እንችላለን።—መዝ. 116:1፤ 136:24-26
ተስፋ የሚያስቆርጡ ሁኔታዎች አልፎ አልፎ ያጋጥሙናል። (9. ጳውሎስ ለአምላክ ያለው ፍቅር ምንጊዜም ጠንካራ እንዲሆን የረዳው ምንድን ነው?
9 እንደ መዝሙራዊው ሁሉ ጳውሎስም ይሖዋ በሚያደርግለት የማይቋረጥ ድጋፍ ላይ ማሰላሰሉ ብርታት ሰጥቶታል። ጳውሎስ “ይሖዋ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም። ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?” ሲል ጽፏል። (ዕብ. 13:6) ጳውሎስ በይሖዋ ፍቅራዊ እንክብካቤ ላይ ጠንካራ እምነት የነበረው መሆኑ በሕይወቱ ውስጥ ችግሮች ሲያጋጥሙት እጅ እንዳይሰጥ ረድቶታል። ያጋጠሙት አስቸጋሪ ሁኔታዎች በይሖዋ እንዳይተማመን አላደረጉትም። እንዲያውም ጳውሎስ በርካታ የሚያበረታቱ ደብዳቤዎችን የጻፈው እስር ቤት ሆኖ ነው። (ኤፌ. 4:1፤ ፊልጵ. 1:7፤ ፊልሞና 1) በእርግጥም ጳውሎስ ከባድ ፈተናዎች ቢያጋጥሙትም ለአምላክ ያለው ፍቅር ምንጊዜም ጠንካራ ነበር። ይህን ለማድረግ የሚያስችል ብርታት የሰጠው ምንድን ነው? ‘በሚደርስብን መከራ ሁሉ በሚያጽናናን’ እና “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” በሆነው በይሖዋ መታመኑ ነው። (2 ቆሮ. 1:3, 4) እኛስ የጳውሎስን ምሳሌ በመከተል ለይሖዋ ያለን ፍቅር ምንጊዜም ጠንካራ እንዲሆን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
10. ለይሖዋ ያለን ፍቅር ምንጊዜም ጠንካራ እንዲሆን ምን ይረዳናል?
10 ለይሖዋ ያለን ፍቅር ምንጊዜም ጠንካራ እንዲሆን ከሚረዱን መንገዶች አንዱን ጳውሎስ ራሱ ገልጾልናል። ለእምነት ባልንጀሮቹ “ዘወትር ጸልዩ” ሲል ጽፏል። ከጊዜ በኋላ ደግሞ “ሳትታክቱ ጸልዩ” ብሏል። (1 ተሰ. 5:17፤ ሮም 12:12) በጸሎት አማካኝነት ለይሖዋ ሐሳባችንን መግለጻችን ከእሱ ጋር የቀረበ ወዳጅነት እንዲኖረን የሚያስችል መሠረት ነው። (መዝ. 86:3) ጊዜ መድበን ለይሖዋ የውስጣችንን አውጥተን የምንነግረውና ስሜታችንን የምንገልጽለት ከሆነ “ጸሎት ሰሚ” ወደሆነው የሰማዩ አባታችን ይበልጥ መቅረባችን አይቀርም። (መዝ. 65:2) በተጨማሪም ይሖዋ ለጸሎታችን ምላሽ እንደሰጠን ስንመለከት ለእሱ ያለን ፍቅር ያድጋል። “ይሖዋ ለሚጠሩት ሁሉ . . . ቅርብ” መሆኑን ይበልጥ እየተገነዘብን እንሄዳለን። (መዝ. 145:18) ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ በሚያደርግልን ድጋፍ ላይ መተማመናችን ደግሞ የሚያጋጥሙንን ሌሎች የእምነት ፈተናዎች ለመወጣት ይረዳናል።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሚገኘው እውነት ያለን ፍቅር
11, 12. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሚገኘው እውነት ጥልቅ ፍቅር ለማዳበር ምን ይረዳናል?
11 ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን እውነትን እንወዳለን፤ እንዲሁም ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን። ከሁሉ የላቀው የእውነት ምንጭ የአምላክ ቃል ነው። ኢየሱስ ለአባቱ ባቀረበው ጸሎት ላይ “ቃልህ እውነት ነው” ብሏል። (ዮሐ. 17:17) በመሆኑም ለእውነት ፍቅር ማዳበር እንድንችል፣ መጀመሪያ ስለ አምላክ ቃል ትክክለኛ እውቀት መቅሰም ያስፈልገናል። (ቆላ. 1:10) ይህ ግን የጭንቅላት እውቀት ከማካበት ያለፈ ነገርን የሚያካትት ነው። መዝሙር 119ን በመንፈስ መሪነት የጻፈው መዝሙራዊ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መውደድ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ እንደሚጨምር ገልጿል። (መዝሙር 119:97-100ን አንብብ።) ባነበብናቸው ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦች ላይ ለማሰላሰል ወይም በጥልቀት ለማሰብ በየዕለቱ ጊዜ እንመድባለን? የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች በሕይወታችን ተግባራዊ ማድረጋችን ባስገኘልን ጥቅሞች ላይ ስናሰላስል፣ በአምላክ ቃል ውስጥ ለሚገኘው እውነት ያለን አድናቆት እየጨመረ ይሄዳል።
12 መዝሙራዊው አክሎም “የተናገርከው ነገር ለምላሴ እጅግ ጣፋጭ ነው፤ ለአፌም ከማር የበለጠ ይጥማል!” ብሏል። (መዝ. 119:103) እኛም በተመሳሳይ በአምላክ ድርጅት በኩል የምናገኘውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መንፈሳዊ ምግብ እንደ ጣፋጭ ምግብ ማጣጣም እንችላለን። መንፈሳዊውን ምግብ በምሳሌያዊ መንገድ እያጣጣምን መመገባችን፣ የእውነትን “ደስ የሚያሰኙ ቃላት” በሌላ ጊዜ እንድናስታውስና ሌሎችን ለመርዳት እንድንጠቀምበት ያስችለናል።—መክ. 12:10
13. ኤርምያስ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ያለውን እውነት እንዲወድ የረዳው ምንድን ነው? ለአምላክ ቃል ያለው ፍቅርስ ምን እንዲያደርግ አነሳስቶታል?
13 ነቢዩ ኤርምያስ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ለሚገኘው እውነት ፍቅር ነበረው። የአምላክን ቃል በተመለከተ ምን እንደተሰማው ሲገልጽ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ቃልህ ተገኝቷል፤ እኔም በልቼዋለሁ፤ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ በስምህ ተጠርቻለሁና፣ ቃልህ ሐሴት፣ ለልቤም ደስታ ሆነልኝ።” (ኤር. 15:16) ኤርምያስ ውድ በሆነው የአምላክ ቃል ላይ ስላሰላሰለ፣ በምሳሌያዊ መንገድ ቃሉን እንደበላው አድርጎ ተናግሯል። ይህን ማድረጉ፣ በአምላክ ስም የመጠራት መብቱን በአድናቆት እንዲመለከት አድርጎታል። እኛም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሚገኘው እውነት ፍቅር ማዳበራችን በአምላክ ስም የመጠራትና በዚህ የፍጻሜ ዘመን ስለ መንግሥቱ የማወጅ ልዩ መብታችንን ከፍ አድርገን እንድንመለከተው ያነሳሳናል።
14. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሚገኘው እውነት ያለንን ፍቅር ለማሳደግ ምን ይረዳናል?
14 የአምላክን ቃል እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ከማንበብ ሌላ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሚገኘው እውነት ጥልቅ ፍቅር ለማዳበር ምን ሊረዳን ይችላል? በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረን በመገኘት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሚገኘው እውነት ያለን ፍቅር እንዲያድግ ማድረግ እንችላለን። በስብሰባዎች ላይ ትምህርት ከምናገኝባቸው መንገዶች ዋነኛው በመጠበቂያ ግንብ አማካኝነት በየሳምንቱ የምናደርገው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ነው። የሚጠናውን ርዕሰ ጉዳይ በደንብ መረዳት እንድንችል እያንዳንዱን የመጠበቂያ ግንብ የጥናት ርዕስ በሚገባ መዘጋጀት ይኖርብናል። ይህን ማድረግ የምንችልበት አንዱ መንገድ፣ ምዕራፍና ቁጥራቸው ብቻ የተጠቀሱትን ጥቅሶች በሙሉ አውጥተን ማንበብ ነው። በአሁኑ ወቅት የመጠበቂያ ግንብ መጽሔትን በብዙ ቋንቋዎች ከjw.org ድረ ገጽ ላይ ማውረድ ወይም JW Library በተባለው አፕልኬሽን አማካኝነት ማግኘት ይቻላል። በእነዚህ ዝግጅቶች አማካኝነት መጽሔቶችን ስናወርድ በእያንዳንዱ የጥናት ርዕስ ላይ የሚገኙትን ጥቅሶች በቀላሉ አውጥተን ማየት እንችላለን። መጽሔቱን የምናገኝበት መንገድ ምንም ይሁን ምን፣ ጥቅሶቹን በሚገባ ማንበባችንና በጥቅሶቹ ላይ ማሰላሰላችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሚገኘው እውነት ያለንን ፍቅር ያሳድግልናል።—መዝሙር 1:2ን አንብብ።
ለወንድሞቻችን ያለን ፍቅር
15, 16. (ሀ) በዮሐንስ 13:34, 35 መሠረት ምን የማድረግ ግዴታ አለብን? (ለ) ለወንድሞቻችን ያለን ፍቅር ለአምላክና ለመጽሐፍ ቅዱስ ካለን ፍቅር ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው?
15 ኢየሱስ ምድር ላይ ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ እኔ እንደ ወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።”—ዮሐ. 13:34, 35
16 ይሖዋን የምንወድ ከሆነ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንንም ልንወድ ይገባል። ሁለቱ የማይነጣጠሉ ነገሮች ናቸው። ሐዋርያው ዮሐንስ “ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን አምላክ ሊወድ አይችልም” ሲል ጽፏል። (1 ዮሐ. 4:20) በተጨማሪም ለይሖዋ እንዲሁም ለወንድሞቻችን ያለን ፍቅር፣ ለመጽሐፍ ቅዱስ ካለን ፍቅር ጋር የተያያዘ ነገር ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሚገኘው እውነት ያለን ፍቅር፣ አምላክን እንዲሁም ወንድሞቻችንን እንድንወድ የተሰጠንን ቅዱስ ጽሑፋዊ ትእዛዝ ከልባችን እንድንታዘዝ ያነሳሳናል።—1 ጴጥ. 1:22፤ 1 ዮሐ. 4:21
17. ፍቅር ማሳየት የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?
17 አንደኛ ተሰሎንቄ 4:9, 10ን አንብብ። በጉባኤያችን ውስጥ ፍቅር ማሳየት የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው? በዕድሜ የገፉ አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የሚወስዳቸው ሰው ያስፈልጋቸው ይሆናል። መበለት የሆነች አንዲት እህት ደግሞ በቤቷ ውስጥ አንዳንድ የጥገና ሥራዎችን ለማከናወን እርዳታ ሊያስፈልጋት ይችላል። (ያዕ. 1:27) በየትኛውም ዕድሜ ላይ ለሚገኙ ተስፋ የቆረጡ ወይም በመንፈስ ጭንቀት የተዋጡ አሊያም ሌሎች ፈተናዎች ያጋጠሟቸው ወንድሞችና እህቶች ትኩረት፣ ማበረታቻና ማጽናኛ ልንሰጣቸው ይገባል። (ምሳሌ 12:25፤ ቆላ. 4:11) “በእምነት ለሚዛመዱን ሰዎች” በቃልም ሆነ በድርጊት ከልብ እንደምናስብላቸው የምናሳይ ከሆነ ለወንድሞቻችን እውነተኛ ፍቅር እንዳለን እናረጋግጣለን።—ገላ. 6:10
18. ከእምነት አጋሮቻችን ጋር የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት ምን ይረዳናል?
18 መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ክፉ ሥርዓት ‘የመጨረሻ ቀናት’ ራስ ወዳድነትና ስግብግብነት በስፋት እንደሚታይ አስቀድሞ ተናግሯል። (2 ጢሞ. 3:1, 2) በመሆኑም ክርስቲያኖች ለአምላክ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሚገኘው እውነትና ለወንድሞቻቸው ያላቸውን ፍቅር ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አለባቸው። እርግጥ ነው፣ ከእምነት አጋሮቻችን ጋር አለመግባባት የሚያጋጥመን ጊዜ ይኖራል። በዚህ ወቅት በፍቅር ተነሳስተን አለመግባባቱን ደግነት በሚንጸባረቅበት መንገድ ቶሎ መፍታታችን ለሁሉም የጉባኤው አባላት በረከት ያስገኛል! (ኤፌ. 4:32፤ ቆላ. 3:14) እንግዲያው ፍቅራችን መቼም ቢሆን እንዳይቀዘቅዝ እንጠንቀቅ! ለይሖዋ፣ ለቃሉና ለወንድሞቻችን ምንጊዜም ጥልቅ ፍቅር እናሳይ።