የሕይወት ታሪክ
ከድህነት ወደ ብልጽግና
የተወለድኩት በኢንዲያና፣ ዩናይትድ ስቴትስ በምትገኝ ሊበርቲ የምትባል አንዲት በጣም አነስተኛ ከተማ ውስጥ ነው፤ የምንኖረውም ከግንድ በተሠራች ባለ አንድ ክፍል ቤት ውስጥ ነበር። አንድ ታላቅ ወንድምና ሁለት ታላላቅ እህቶች አሉኝ። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ሁለቱ ታናናሽ ወንድሞቼና ታናሽ እህቴ ተወለዱ።
ትምህርት ቤት ሳለሁ በከተማችን ውስጥ ምንም አዲስ ነገር አልነበረም ማለት ይቻላል። ከአንደኛ ክፍል አንስቶ ትምህርት እስክንጨርስ ድረስ የምንማረው ከተመሳሳይ ተማሪዎች ጋር ነበር፤ እንዲያውም ከከተማዋ ነዋሪዎች የአብዛኞቹን ሰዎች ስም እናውቀዋለን፤ እነሱም ያውቁናል።
በሊበርቲ ከተማ ዙሪያ አነስተኛ እርሻዎች የነበሩ ሲሆን ዋነኛው ሰብል በቆሎ ነበር። እኔ ስወለድ አባቴ በአካባቢው ካሉት ገበሬዎች በአንዱ እርሻ ላይ ተቀጥሮ ይሠራ ነበር። በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ እያለሁ ትራክተር መንዳት ተማርኩ፤ መሠረታዊ የሆነ የእርሻ እውቀትም አዳበርኩ።
አባቴን ወጣት እያለ የማወቅ አጋጣሚ አልነበረኝም። እኔ ስወለድ አባቴ 56 ዓመቱ፣ እናቴ ደግሞ 35 ዓመቷ ነበር። ያም ቢሆን አባቴ ሸንቀጥ ያለ፣ ጤናማና ጠንካራ ሰው ሲሆን ተግቶ መሥራት ይወድ ነበር፤ እኛን ልጆቹንም ታታሪ ሠራተኛ እንድንሆን አሠልጥኖናል። አባቴ ብዙ ገንዘብ ባይኖረውም ጾማችንን አድረን፣ ታርዘን ወይም መጠለያ አጥተን አናውቅም፤ እንዲሁም አዘውትሮ ከእኛ ጋር ጊዜ ያሳልፍ ነበር። አባቴ ሲሞት 93 ዓመቱ ነበር። እናቴ ደግሞ የሞተችው በ86 ዓመቷ ነው። ሁለቱም የይሖዋ ምሥክሮች አልነበሩም። አንድ ወንድሜ ይሖዋን በታማኝነት የሚያመልክ ሲሆን ከ1970ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ ሽማግሌ ሆኖ እያገለገለ ነው።
የልጅነት ሕይወቴ
እናቴ ሃይማኖተኛ ሴት ነበረች። ሁልጊዜ እሁድ እሁድ ወደ ባፕቲስት ቤተ ክርስቲያን ትወስደን ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ
ስለ ሥላሴ የሰማሁት የ12 ዓመት ልጅ እያለሁ ነው። ጉዳዩ ስለከነከነኝ “ኢየሱስ፣ ወልድም አብም ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?” ብዬ እናቴን ጠየቅኳት። እሷም “ልጄ፣ ይሄ ሚስጥር ነው። እኛ ልንረዳው አንችልም” ብላ እንደመለሰችልኝ ትዝ ይለኛል። በእርግጥም ሥላሴ ለእኔ ሚስጥር ነበር። ያም ሆኖ 14 ዓመት ሲሆነኝ በአካባቢያችን በሚገኝ አንድ ጅረት ውስጥ ተጠመቅኩ፤ ሥላሴን ለማመልከት ሲባል ውኃ ውስጥ የጠለቅኩት ሦስት ጊዜ ነው!በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳለሁ ቦክሰኛ የሆነ አንድ ጓደኛ ነበረኝ፤ ይህ ልጅ እኔም ቦክሰኛ እንድሆን አበረታታኝ። ስለዚህ ሥልጠና የጀመርኩ ሲሆን ጎልደን ግላቭስ የሚባል ቦክሰኞችን የሚያሠለጥን ድርጅት ውስጥ ገባሁ። ሆኖም ጎበዝ ቦክሰኛ ስላልነበርኩ ከጥቂት ውድድሮች በኋላ ተውኩት። ከጊዜ በኋላ በዩናይትድ ስቴትስ ሠራዊት ውስጥ በውትድርና እንዳገለግል ተመለመልኩና ወደ ጀርመን ተላክሁ። እዚያ እያለሁ አለቆቼ፣ በተፈጥሮዬ ጥሩ የመምራት ችሎታ እንዳለኝ ስለተሰማቸው ወደ ወታደራዊ መኮንኖች ማሠልጠኛ ላኩኝ። በውትድርና መስክ እንድሰማራ ፈልገው ነበር። እኔ ግን በውትድርና መስክ የመቀጠል ፍላጎት አልነበረኝም፤ በመሆኑም የሁለት ዓመት ግዳጄን ከጨረስኩ በኋላ በ1956 በክብር ተሰናበትኩ። ይሁንና ከዚያ ብዙም ሳይቆይ የአንድ የተለየ ሠራዊት አባል ሆንኩ።
አዲስ ሕይወት ጀመርኩ
እውነትን እስካወቅኩበት ጊዜ ድረስ ወንድ የሚባለው ምን ዓይነት ሰው እንደሆነ የተሳሳተ አመለካከት ነበረኝ። በፊልሞች ላይ የሚታየውና በማኅበረሰቡ ውስጥ የተለመደው አስተሳሰብ በዚህ ረገድ በእጅጉ ተጽዕኖ አሳድሮብኝ ነበር። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰብኩ ወንዶች፣ እንደ ወንድ ሊታዩ እንደማይችሉ አድርጌ አስብ ነበር። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ የተማርኳቸው ነገሮች የሕይወቴን አቅጣጫ ቀየሩት። አንድ ቀን ቄንጠኛ የሆነች ቀይ መኪናዬን በከተማው መካከል እያሽከረከርኩ ሳለ ሁለት ወጣት ሴቶች እጃቸውን በማውለብለብ አስቆሙኝ። ሴቶቹ፣ ታላቅ እህቴን ያገባው ሰው ታናናሽ እህቶች ነበሩ። እነዚህ ወጣቶች የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። ከዚያ በፊት መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች ሰጥተውኝ ቢያውቁም መጠበቂያ ግንብ ጥልቀት ያለው ሐሳብ ስለያዘ ለእኔ እንደማይሆን ተሰምቶኝ ነበር። የዚያን ዕለት ግን የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት በሚባለው ስብሰባ ላይ እንድገኝ ጋበዙኝ፤ በቤታቸው በሚካሄደውና ጥቂት ሰዎች በሚገኙበት በዚህ ስብሰባ ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና ውይይት ይደረጋል። እኔም “እሺ አስብበታለሁ” አልኳቸው። ወጣቶቹ ፈገግ ብለው “ቃል ትገባለህ?” በማለት ጠየቁኝ። እኔም “አዎ፣ ቃል እገባለሁ” አልኳቸው።
እንዲህ ያለ ቃል በመግባቴ በኋላ ላይ ቢቆጨኝም ቃሌን ማጠፍ እንደማልችል ተሰማኝ። ስለዚህ በዚያ ምሽት ወደ ስብሰባው ሄድኩ። ከምንም በላይ ያስገረሙኝ ትናንሾቹ ልጆች ነበሩ። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያላቸው እውቀት አስደነቀኝ! ከእናቴ ጋር እሁድ እሁድ ለዓመታት ቤተ ክርስቲያን እሄድ የነበረ ቢሆንም ያለኝ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት በጣም ውስን ነበር። ከዚያ በኋላ ግን ይበልጥ ለመማር ቆረጥኩ። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማማሁ። ጥናት ከጀመርኩ ብዙም ሳይቆይ፣ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ የግል ስም ይሖዋ እንደሆነ ተማርኩ። ከዓመታት በፊት እናቴን ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ስጠይቃት “ይሖዋ ተብሎ የሚጠራ አንድ ሽማግሌ የሚያመልኩ ሰዎች ናቸው” ብላኝ ነበር። አሁን ግን ዓይኔ የተከፈተ ያህል ሆኖ ተሰማኝ!
እውነትን እንዳገኘሁ ስለገባኝ ፈጣን እድገት አደረግኩ። በዚያ ስብሰባ ላይ በተገኘሁ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ይኸውም መጋቢት 1957 ተጠመቅኩ። ስለ ሕይወት የነበረኝ አመለካከት ተለወጠ። ወንድ የሚባለው ምን ዓይነት ሰው እንደሆነ የነበረኝን አመለካከት ሳስታውስ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እውነተኛ ወንድነት የሚያስተምረውን ነገር በመማሬ ደስ ይለኛል። ኢየሱስ ፍጹም ሰው ነበር። “ወንድ” የተባለ ማንኛውም ሰው ሊወዳደረው የማይችል ብርታትና ኢሳ. 53:2, 7) እውነተኛ የኢየሱስ ተከታይ “ለሰው ሁሉ ገር” መሆን እንዳለበት ተማርኩ።—2 ጢሞ. 2:24
አካላዊ ጥንካሬ ነበረው። ሆኖም ኢየሱስ ተደባድቦ አያውቅም፤ ከዚህ ይልቅ በትንቢት እንደተነገረው ‘መከራ ለመቀበል ፈቃደኛ ሆኗል።’ (በቀጣዩ ዓመት ማለትም በ1958 አቅኚነት ጀመርኩ። ብዙም ሳይቆይ ግን ለተወሰነ ጊዜ ያህል በአቅኚነት ማገልገል አቆምኩ። ለምን? ወደ መጽሐፍ ጥናቱ ከጋበዙኝ ሁለት ወጣት ወይዛዝርት አንዷ የሆነችውን ግሎሪያን ለማግባት ስለወሰንኩ ነው! በዚህ ውሳኔዬ ተቆጭቼ አላውቅም። ግሎሪያ ያን ጊዜም ሆነ አሁን ለእኔ ውድ ዕንቁ ነች። እጅግ ውድ ከሚባለው ዕንቁ ትበልጥብኛለች፤ እሷን በማግባቴ በጣም ደስተኛ ነኝ! እስቲ ስለ ራሷ ትንሽ ታጫውታችሁ፦
“አባቴና እናቴ 17 ልጆች ወልደዋል። እናቴ ታማኝ የይሖዋ ምሥክር ነበረች። የ14 ዓመት ልጅ ሳለሁ እናቴ ሞተች። አባቴ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመረው ያኔ ነበር። እናቴ ከሞተች በኋላ አባዬ ከትምህርት ቤታችን ርዕሰ መምህር ጋር ተመካክሮ አንድ ዝግጅት አደረገ። ታላቅ እህቴ በዚያን ጊዜ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ስለነበረች እኔና እሷ በየተራ (አንድ ቀን እሷ፣ አንድ ቀን እኔ) ትምህርት ቤት መሄድ እንችል እንደሆነ አባቴ ጠየቀ። ይህን ያደረገው በተራ በተራ አንዳችን ቤት ቀርተን ታናናሾቻችንን እንድንጠብቅ እንዲሁም እሱ ከሥራ ከመመለሱ በፊት ለቤተሰቡ ራት እንድናዘጋጅ አስቦ ነው። ርዕሰ መምህራችን በዚህ ሐሳብ ስለተስማማ እህቴ ትምህርቷን እስክትጨርስ ድረስ ትምህርት ቤት የምንሄደው በዚህ መንገድ ነበር። ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰቦች መጽሐፍ ቅዱስን ያስጠኑን ሲሆን በቤተሰባችን ውስጥ ካለነው ልጆች መካከል አሥራ አንዳችን የይሖዋ ምሥክሮች ሆንን። ከድሮ ጀምሮ ዓይናፋር የነበርኩ ቢሆንም የመስክ አገልግሎት ያስደስተኝ ነበር። ሳም ዓይናፋርነቴን በጊዜ ሂደት እንዳሸንፍ ረድቶኛል።”
እኔና ግሎሪያ የካቲት 1959 ተጋባን። አብረን በአቅኚነት ያሳለፍነው ጊዜ አስደሳች ነበር። በዋናው መሥሪያ ቤት ለማገልገል እንጓጓ ስለነበር በዚያው ዓመት ሐምሌ ላይ በቤቴል ለማገልገል አመለከትን። ቃለ መጠይቅ ያደረገልን ሳይመን ክሬከር የሚባል ወንድም ነበር። ወንድም ክሬከር፣ ቤቴል በዚያ ወቅት ባለትዳሮችን እንደማይቀበል ነገረን። በቤቴል የማገልገል ምኞታችን ከዚያ በኋላም አልጠፋም፤ ሆኖም ምኞታችን እስኪፈጸም ረጅም ጊዜ መጠበቅ አስፈልጎናል።
የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ እንድንመደብ ለመጠየቅ ወደ ዋናው መሥሪያ ቤት ደብዳቤ ጻፍን። የተሰጠን አንድ ምርጫ ብቻ ነበር፤ በፓይን ብለፍ፣ አርከንሶ እንድናገለግል ተመደብን። በወቅቱ ፓይን ብለፍ ውስጥ የነበሩት ሁለት ጉባኤዎች ሲሆኑ አንደኛው የነጮች ሌላው ደግሞ የጥቁሮች ነበር። እኛ የተመደብነው 14 አስፋፊዎች ብቻ ባሉበት የጥቁሮች ጉባኤ ውስጥ ነው።
መከፋፈልንና ዘረኝነትን መቋቋም
በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ ነጮችና ጥቁሮች ለየብቻ መሰብሰባቸው ያስገርማችሁ ይሆናል። በአጭር አነጋገር ይህ የሆነው በወቅቱ ምንም ምርጫ ስላልነበረ ነው። የተለያዩ ዘሮች መቀላቀላቸው ሕገ ወጥ እንደሆነ የሚገልጽ ሕግ የነበረ ከመሆኑም በላይ ተቀላቅሎ መሰብሰብ ለጥቃት ሊያጋልጥ ይችላል። በብዙ ቦታዎች፣ ነጮችና ጥቁሮች የሆኑ ወንድሞች ለአምልኮ አንድ ላይ ከተሰበሰቡ ሌሎች ሰዎች የስብሰባ አዳራሻቸውን እንዳያቃጥሉባቸው ይፈሩ ነበር። ደግሞም እንደዚህ ያሉ ነገሮች ተፈጽመዋል። ጥቁር የይሖዋ ምሥክሮች በነጮች ሰፈር ከቤት ወደ ቤት ሲሰብኩ ከተገኙ ሊታሰሩ አልፎ ተርፎም ሊደበደቡ ይችሉ ነበር። በመሆኑም የስብከቱን ሥራ ለማከናወን ስንል ሕጉን ለመታዘዝ ተገደድን፤ ሁኔታዎቹ ወደፊት እንደሚሻሻሉ ተስፋ እናደርግ ነበር።
በአገልግሎት ላይ የተለያዩ ተፈታታኝ ነገሮች አጋጥመውናል። በጥቁሮች ክልል ስንሰብክ አንዳንድ ጊዜ ሳናውቅ የነጮቹን ቤት እናንኳኳለን። በዚህ ጊዜ፣ አጠር ያለ ምሥክርነት ከመስጠት አሊያም መሳሳታችንን በመግለጽ ይቅርታ ጠይቆ ከመሄድ የቱ እንደሚሻል በፍጥነት መወሰን ነበረብን። በዚያ ወቅት በአንዳንድ ቦታዎች እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ያጋጥም ነበር።
በአቅኚነት እያገለገልን ራሳችንን ለማስተዳደር ሰብዓዊ ሥራም መሥራት ነበረብን። ከአብዛኞቹ ሥራዎቻችን በቀን የምናገኘው ገቢ በጣም ትንሽ ነበር። ግሎሪያ የተለያዩ ቤቶችን ታጸዳ ነበር። ጽዳት ከምታከናውንባቸው ቤቶች በአንዱ ላይ ሥራው የሚፈጅባትን ጊዜ በግማሽ መቀነስ እንድትችል እኔ እንድረዳት ተፈቀደልኝ። ያ ቤተሰብ ምሳ ይሰጠን የነበረ ሲሆን እኔና ግሎሪያ ሥራችንን ጨርሰን ከመሄዳችን በፊት ተካፍለን እንበላዋለን። ግሎሪያ ለአንድ ቤተሰብ ደግሞ በየሳምንቱ ልብስ ትተኩሳለች። እኔም አትክልቶቹን እንከባከብ፣ መስተዋት አጸዳ እንዲሁም እንደነዚህ ያሉ ሌሎች ሥራዎችን አከናውን ነበር። እኔና ግሎሪያ አብረን መስተዋት የምናጸዳበት አንድ የነጮች ቤትም ነበር፤ እሷ ከውስጥ እኔ ደግሞ ከውጭ በኩል ሆነን መስተዋቱን እናጸዳለን። ሥራው ሙሉ ቀን ስለሚፈጅ ምሳ ይሰጡናል። ግሎሪያ ከቤተሰቡ ጋር ማዕድ ባትቀርብም ቤት ውስጥ ሆና የምትበላ ሲሆን እኔ ደግሞ ደጅ ጋራዡ ውስጥ ሆኜ እበላ ነበር። በዚህ ቅር አልተሰኘሁም።
የሚሰጡን ምግብ በጣም ጥሩ ከመሆኑም ሌላ ቤተሰቡ ደጎች ነበሩ፤ ከእነሱ ተለይተን እንድንበላ የሚያደርጉት በዚያ ማኅበረሰብ ውስጥ በሰፈነው አመለካከት የተነሳ ነው። በአንድ ወቅት በነዳጅ ማደያ ቆመን እያለ ያጋጠመንን ነገር አስታውሳለሁ። መኪናችንን ነዳጅ ካስሞላን በኋላ ግሎሪያ መጸዳጃ ቤቱን መጠቀም ትችል እንደሆነ ነዳጅ የቀዳልንን ሰው ጠየቅኩት። እሱም ገላመጠኝና “ተቆልፏል” አለኝ።የማይረሱ የደግነት ተግባሮች
በሌላ በኩል ደግሞ ከወንድሞች ጋር ግሩም ጊዜ ያሳለፍን ሲሆን አገልግሎታችንንም እንወደው ነበር! በፓይን ብለፍ መጀመሪያ ላይ የምንኖረው በጉባኤ አገልጋዩ (አሁን የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪ ይባላል) ቤት ነበር። በወቅቱ የዚህ ወንድም ሚስት የይሖዋ ምሥክር አልነበረችም፤ ስለዚህ ግሎሪያ እሷን መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ጀመረች። እኔ ደግሞ ሴት ልጃቸውንና ባሏን ማስጠናት ጀመርኩ። ውሎ አድሮም የጉባኤ አገልጋዩ ባለቤትና ሴት ልጁ ይሖዋን ለማገልገል ወሰኑና ተጠመቁ።
በነጮች ጉባኤ ውስጥም ጥሩ ወዳጆች ነበሩን። እነዚህ ወንድሞች ቤታቸው ራት ይጋብዙን ነበር፤ በእርግጥ ይህን ለማድረግ እስኪጨልም መጠበቅ ነበረባቸው። ኩ ክለክስ ክላን (ኬኬኬ) በመባል የሚታወቀው ዘረኝነትንና ዓመፅን የሚያስፋፋ ድርጅት በዚያን ጊዜ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ ነበር። ሃሎዊን የሚባለው በዓል በሚከበርበት ምሽት ላይ አንድ ሰው የኬኬኬ አባላት የሚለብሱት ዓይነት ልብስ ለብሶ በረንዳው ላይ በኩራት ተቀምጦ እንዳየሁ ትዝ ይለኛል። ይሁንና እንዲህ ያሉ እንቅስቃሴዎች መኖራቸው ወንድሞች ደግነት እንዳያሳዩ አላገዳቸውም። በአንድ ወቅት ወደ ትልቅ ስብሰባ ለመሄድ ገንዘብ አስፈልጎን ነበር፤ ይህን ወጪ መሸፈን እንድንችል አንድ ወንድም የ1950 ሞዴል ፎርድ መኪናችንን ሊገዛን ተስማማ። ይህ ከሆነ ከወር በኋላ አንድ ቀን በበጋው ሙቀት ከቤት ወደ ቤት ስናገለግልና ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ስናስጠና ውለን ወደ ቤት ስንመለስ ደክሞን ነበር። ቤት ስንደርስ ያልጠበቅነው አስደሳች ነገር ገጠመን። መኪናችንን ከቤታችን ፊት ለፊት ቆማ አገኘናት! በመኪናዋ የፊት መስተዋት ላይ “መኪናችሁን በስጦታ መልክ መልሼላችኋለሁ። ወንድማችሁ” የሚል ማስታወሻ አገኘን።
ከአእምሮዬ የማይጠፋ ሌላም የደግነት ተግባር አለ። በ1962 በደቡብ ላንሲንግ፣ ኒው ዮርክ በተካሄደው የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት እንድካፈል ተጋበዝኩ። ይህ ሥልጠና ለጉባኤ ሽማግሌዎች እንዲሁም ለወረዳና ለአውራጃ የበላይ ተመልካቾች የተዘጋጀ ሲሆን አንድ ወር ይፈጃል። ይሁንና ግብዣው የደረሰኝ ሥራ ባልነበረኝ ወቅት ሲሆን ያለን ገንዘብ በጣም ትንሽ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ በፓይን ብለፍ በሚገኝ የቴሌፎን ኩባንያ ውስጥ ለመቀጠር ቃለ መጠይቅ ተደርጎልኝ ነበር። ሥራውን ባገኝ፣ በዚያ ኩባንያ ለመቀጠር የመጀመሪያው ጥቁር ሰው እሆን ነበር። በመጨረሻም ሊቀጥሩኝ እንደሆነ ነገሩኝ። ታዲያ ምን ላደርግ ነው? ወደ ኒው ዮርክ ለመሄድ ገንዘብ አልነበረኝም። በዚያ መሥሪያ ቤት ብቀጠርና ከትምህርት ቤቱ የተላከልኝን ግብዣ ባልቀበል እንደሚሻል ማሰብ ጀመርኩ። እንዲያውም ግብዣውን መቀበል እንደማልችል የሚገልጽ ደብዳቤ ለመጻፍ ተዘጋጅቼ ነበር፤ ከዚያም ፈጽሞ የማልረሳው ነገር ተከሰተ።
የማያምን ባል ያላት የጉባኤያችን እህት አንድ ቀን በማለዳ በራችንን አንኳኳችና አንድ ፖስታ ሰጠችኝ። ፖስታው በገንዘብ የተሞላ ነበር። ለካስ ይህች እህትና ትናንሽ ልጆቿ በማለዳ ተነስተው ወደ ጥጥ እርሻ በመሄድ ሲያርሙ ሰንብተዋል። ይህን ያደረጉት ወደ ኒው ዮርክ ለመሄድ የሚያስችል ገንዘብ እንዳገኝ ብለው
ነው። እህታችን “ወደ ትምህርት ቤቱ ሄደህ የቻልከውን ያህል ተማር፤ ስትመለስ እኛንም ታስተምረናለህ!” አለችኝ። ከዚያም የቴሌፎን ኩባንያውን፣ ሥራ እንድጀምር ከተነገረኝ ጊዜ አምስት ሳምንት አሳልፌ ሥራውን መጀመር እችል እንደሆነ ጠየቅኩ። ኩባንያው ይህ በፍጹም እንደማይቻል ነገረኝ። ሆኖም አስቀድሜ ወስኜ ስለነበር የኩባንያው መልስ በውሳኔዬ ላይ ለውጥ አላመጣም። ያንን ሥራ ባለመያዜ በጣም ደስተኛ ነኝ!ግሎሪያ በፓይን ብለፍ ስላሳለፍነው ጊዜ እንዲህ ትላለች፦ “ክልሉን በጣም ወደድኩት! ከ15 እስከ 20 የሚሆኑ ጥናቶች ነበሩኝ። በመሆኑም ጠዋት ላይ ከቤት ወደ ቤት እንሰብክና ቀሪውን ቀን በሙሉ፣ አንዳንዴም እስከ ማታ 5 ሰዓት ድረስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን እናስጠናለን። አገልግሎት በጣም አስደሳች ነበር! በዚያ ምድብ ብቀጥል ደስ ይለኝ ነበር። እውነቱን ለመናገር፣ ይህን ምድብ ትቼ ወደ ወረዳ ሥራ መግባት አልፈለግኩም፤ ሆኖም ይሖዋ ለእኛ ያሰበው ሌላ ነገር ነበር።” በእርግጥም ይሖዋ ያሰበው ነገር ነበር።
የተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ሕይወት
ፓይን ብለፍ ውስጥ በአቅኚነት እያገለገልን ሳለን ልዩ አቅኚዎች ለመሆን አመለከትን። የአውራጃ የበላይ ተመልካቻችን ቴክሳስ ውስጥ የሚገኝን አንድ ጉባኤ ልዩ አቅኚዎች ሆነን እንድንረዳ ይፈልግ ስለነበር ለማመልከቻችን አዎንታዊ ምላሽ እንደምናገኝ ተስፋ አድርገን ነበር። እንደዚህ ያለው ለውጥ አስደሳች እንደሚሆን ተሰምቶን ነበር። በመሆኑም ከማኅበሩ ምላሽ ለማግኘት በጉጉት መጠባበቅ ጀመርን፤ ሆኖም ፖስታ ሣጥናችንን በከፈትን ቁጥር ባዶውን እናገኘው ነበር። በመጨረሻ አንድ ቀን ደብዳቤ መጣልን፤ ደብዳቤው በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት እንዳገለግል መመደቤን የሚገልጽ ነበር! ይህ የሆነው ጥር 1965 ነው። አሁን የዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ አስተባባሪ የሆነው ወንድም ሊዮን ዊቨርም የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኖ የተሾመው በተመሳሳይ ጊዜ ላይ ነው።
የወረዳ የበላይ ተመልካች መሆን አስፈርቶኝ ነበር። ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት ጄምስ ቶምሰን የሚባል አንድ የአውራጃ የበላይ ተመልካች ብቃቴን ገምግሞ ነበር። ወንድም ቶምሰን፣ ብቃት ያለው የወረዳ የበላይ ተመልካች የሚያስፈልጉትን ችሎታዎች በመጥቀስ ማሻሻል የምችልባቸውን አንዳንድ ነጥቦች በደግነት ጠቁሞኛል። የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ ማገልገል ከጀመርኩ ብዙም ሳይቆይ፣ ወንድም ቶምሰን የሰጠኝ ምክሮች አስፈላጊ እንደነበሩ ተገነዘብኩ። የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ ከተሾምኩ በኋላ አብሬው ያገለገልኩት የመጀመሪያው የአውራጃ የበላይ ተመልካች ወንድም ቶምሰን ነው። መንፈሳዊ አመለካከት ካለው ከዚህ ታማኝ ወንድም ብዙ ነገር ተምሬያለሁ።
በዚያ ወቅት ለወረዳ የበላይ ተመልካቾች ብዙ ሥልጠና አይሰጥም ነበር። አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች አንድን ጉባኤ ሲጎበኝ አብሬው አንድ ሳምንት አሳለፍኩ። በቀጣዩ ሳምንት ደግሞ እኔ ሌላ ጉባኤ ስጎበኝ እሱ አብሮኝ በመሆን ተመለከተኝ። ከዚያም ጠቃሚ ሐሳቦችና አንዳንድ ምክሮችን ሰጠኝ። ከዚያ በኋላ ግን ብቻችንን ተተውን። ለግሎሪያ “ትንሽ አብሮን ቢቆይ አይሻልም ነበር?” እንዳልኳት አስታውሳለሁ። ውሎ አድሮ ግን አንድ ጠቃሚ ነገር ተገነዘብኩ፦ ለመማር ፈቃደኛ እስከሆንን ድረስ
ምንጊዜም ቢሆን ሊረዱን የሚችሉ ግሩም ወንድሞች እናገኛለን። በወቅቱ ተጓዥ የበላይ ተመልካች የነበረው ጄምስ ብራውን እንዲሁም የቤቴል ቤተሰብ አባል የነበረው ፍሬድ ረስክና እንደነዚህ ያሉ ሌሎች ተሞክሮ ያላቸው ወንድሞች ያደረጉልኝን እርዳታ አሁንም ድረስ ከፍ አድርጌ እመለከተዋለሁ።በዚያን ጊዜ ዘረኝነት በእጅጉ ተንሰራፍቶ ነበር። በአንድ ወቅት ቴነሲ ውስጥ በምትገኝ ከተማ አንድን ጉባኤ እየጎበኘን ሳለ የኬኬኬ አባላት ሰልፍ ወጥተው ነበር። በሌላ ጊዜ ደግሞ የአገልግሎት ቡድናችን ሻይ ቡና ለማለት አረፍ ብሎ ሳለ ያጋጠመንን ሁኔታ አልረሳውም። ወደ መጸዳጃ ቤት ስሄድ፣ የነጭ የበላይነት አቀንቃኞች የሚነቀሱት ዓይነት ንቅሳት የተነቀሰ በጣም አስፈሪ መልክ ያለው ሰው ተነስቶ ተከተለኝ። ይሁን እንጂ ከሰውየውም ሆነ ከእኔ ይበልጥ ግዙፍ የሆነ አንድ ነጭ ወንድም ተከትሎን መጣ። ከዚያም “ወንድም ኸርድ፣ ሁሉም ነገር ሰላም ነው?” ብሎ ጠየቀኝ። በዚህ ጊዜ ሰውየው በመጸዳጃ ቤቱ ሳይጠቀም ቶሎ ወጣ። ባሳለፍናቸው ዓመታት ውስጥ ያስተዋልኩት ነገር ቢኖር ለጭፍን ጥላቻ መንስኤው የአንድ ግለሰብ የቆዳ ቀለም ሳይሆን ሁላችንም የተለከፍንበት የአዳም ኃጢአት መሆኑን ነው። ደግሞም የቆዳችን ቀለም ምንም ይሁን ምን ወንድሞቻችን ምንጊዜም ወንድሞቻችን ናቸው፤ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ሊሞቱልን እንኳ ፈቃደኞች ናቸው።
ብልጽግና
በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት 33 ዓመታት ያሳለፍኩ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 21ዱን ዓመታት የአውራጃ የበላይ ተመልካች ነበርኩ። በእነዚህ ዓመታት አበረታች የሆኑ በርካታ ተሞክሮዎች ከማግኘታችንም ሌላ አገልግሎታችን የሚክስ ነበር፤ በመንፈሳዊ ሁኔታ ባለጸጋ ሆነናል። ሌላም አስደሳች ነገር አግኝተናል። የረጅም ጊዜ ሕልማችን ነሐሴ 1997 ላይ እውን ሆነ። በዩናይትድ ስቴትስ ቤቴል እንድናገለግል የተጋበዝን ሲሆን ይህም ለመጀመሪያ ጊዜ ማመልከቻ ካስገባን ከ38 ዓመታት በኋላ መሆኑ ነው። በቀጣዩ ወር የቤቴል አገልግሎታችንን ጀመርን። ወደ ቤቴል የተጠራሁት፣ ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች ለተወሰነ ጊዜ ያህል በሥራው እንዳግዝ ስለፈለጉ መስሎኝ ነበር፤ በኋላ ላይ እንደታየው ግን ነገሩ እንዲህ አልነበረም።
መጀመሪያ የተመደብኩት በአገልግሎት ዘርፍ እንድሠራ ነበር። በዚህ ክፍል ውስጥ ስሠራ ብዙ ትምህርት ቀስሜያለሁ። በአገልግሎት ዘርፍ የሚሠሩት ወንድሞች በመላው አገሪቱ ካሉ የሽማግሌዎች አካላትና ከወረዳ የበላይ ተመልካቾች የሚላኩ ጥንቃቄ የሚያሻቸውና ውስብስብ የሆኑ ብዙ ጥያቄዎችን ያስተናግዱ ነበር። ወንድሞች እኔን በትዕግሥት ለማሠልጠንና ለመርዳት ላደረጉት ጥረት አመስጋኝ ነኝ። ያም ሆኖ እንደገና በዚያ ክፍል ለመሥራት ብመደብ አሁንም ገና ተለማማጅ እንደምሆን ይሰማኛል።
እኔና ግሎሪያ የቤቴልን ሕይወት እንወደዋለን። ከድሮም ጀምሮ ማለዳ የመነሳት ልማድ ነበረን፤ ይህ ልማዳችን በቤቴል ሕይወትም ጠቅሞናል። በቤቴል ለአንድ ዓመት ገደማ ከቆየን በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል የአገልግሎት ኮሚቴ ረዳት ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ። ከዚያም በ1999 የበላይ አካል አባል ሆኜ ተሾምኩ። የበላይ አካል አባል ሆኜ ሳገለግል ብዙ ነገሮችን ተምሬያለሁ፤ ከሁሉ በላይ ከፍ አድርጌ የምመለከተው ትምህርት ግን የክርስቲያን ጉባኤን የሚመራው ማንም ሰው ሳይሆን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን በግልጽ ማየት መቻሌን ነው።
ሕይወቴን መለስ ብዬ ስመለከት አንዳንድ ጊዜ እንደ ነቢዩ አሞጽ እንደሆንኩ ይሰማኛል። የድሆች ምግብ እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠር የነበረውን የሾላ ፍሬ በመውጋት ሥራ ላይ ለተሰማራው ለዚህ ድሃ እረኛ ይሖዋ ትኩረት ሰጥቶታል። አምላክ አሞጽን ነቢይ አድርጎ የሾመው ሲሆን ይህም በመንፈሳዊ የሚያበለጽግ የሥራ ምድብ እንደሆነ ጥያቄ የለውም። (አሞጽ 7:14, 15 ግርጌ) በተመሳሳይም በሊበርቲ፣ ኢንዲያና የሚገኝ የአንድ ድሃ ገበሬ ልጅ ለነበርኩት ለእኔ ይሖዋ ትኩረት ሰጥቶ ዘርዝሬ የማልጨርሳቸው ብዙ በረከቶች በማፍሰስ ባለጸጋ አድርጎኛል! (ምሳሌ 10:22) በእርግጥም በድህነት ያደግኩ ቢሆንም ይሖዋ ፈጽሞ ባልጠበቅኩት መንገድ በመንፈሳዊ ባለጸጋ እንዳደረገኝ ይሰማኛል!