በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 22

የጥናት ልማዳችሁን አሻሽሉ!

የጥናት ልማዳችሁን አሻሽሉ!

“ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]።”—ፊልጵ. 1:10

መዝሙር 35 ‘ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ እወቁ’

የትምህርቱ ዓላማ *

1. አንዳንዶች ማጥናት የሚከብዳቸው ለምን ሊሆን ይችላል?

በዛሬው ጊዜ ሰዎች ለኑሮ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማሟላት ብዙ ይለፋሉ። በርካታ ወንድሞቻችን ለቤተሰባቸው የሚያስፈልገውን መሠረታዊ ነገር ለማቅረብ ረጅም ሰዓት መሥራት ይጠበቅባቸዋል። ሌሎች ብዙ ክርስቲያኖች ደግሞ ወደ ሥራ ሲሄዱና ከሥራ ሲመለሱ ረጅም ሰዓት በጉዞ ያጠፋሉ። ራሳቸውን ለማስተዳደር ሲሉ አድካሚ የጉልበት ሥራ የሚሠሩም አሉ። እነዚህ ትጉ ወንድሞችና እህቶች በእያንዳንዱ ቀን መጨረሻ ላይ በጣም እንደሚደክማቸው የታወቀ ነው! በዚህ ድካም ላይ፣ ማጥናት የሚባለውን ነገር ሲያስቡት ከባድ ዳገት ሊሆንባቸው ይችላል።

2. ለጥናት አመቺ ሆኖ ያገኛችሁት የትኛውን ጊዜ ነው?

2 ሆኖም ሁላችንም በአምላክ ቃልና በክርስቲያናዊ ጽሑፎቻችን ላይ ጥልቀት ያለው ጥናት የምናደርግበት ጊዜ መመደብ አለብን። ከይሖዋ ጋር ያለን ዝምድናም ሆነ የዘላለም ሕይወት ተስፋችን የተመካው እንዲህ በማድረጋችን ላይ ነው! (1 ጢሞ. 4:15, 16) አንዳንዶች ጸጥታ የሰፈነበትንና አእምሯቸው ንቁ የሆነበትን የጠዋቱን ክፍለ ጊዜ ለጥናት ይጠቀማሉ። ሌሎች ደግሞ ትኩረታቸውን የሚከፋፍሉ ነገሮች በሌሉበት በአመሻሹ ጊዜ ላይ ጥቂት ደቂቃዎችን መድበው መንፈሳዊ ምግብ ይመገባሉ እንዲሁም በዚያ ላይ ያሰላስላሉ።

3-4. በሕትመትም ሆነ በኤሌክትሮኒክ ቅጂ በሚዘጋጁ ጽሑፎች ላይ ምን ማስተካከያዎች ተደርገዋል? ለምንስ?

3 ለጥናት ጊዜ የመመደብን አስፈላጊነት እንደምንቀበል ምንም ጥርጥር የለውም። ጥያቄው ‘ምን እናጥና?’ የሚለው ነው። ‘የሚነበበው ነገር በጣም ብዙ ነው። ፈጽሞ እኩል መሄድ አልቻልኩም’ እንል ይሆናል። አንዳንዶች የሚቀርቡትን መንፈሳዊ ምግቦች በሙሉ በመመገብ ረገድ ቢሳካላቸውም በርካታ ወንድሞቻችን እንዲህ ለማድረግ የሚያስችል ጊዜ ማግኘት ፈታኝ ሆኖባቸዋል። የበላይ አካሉ ይህን ይገነዘባል። በመሆኑም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሕትመትም ሆነ በኤሌክትሮኒክ ቅጂ የሚዘጋጁት ጽሑፎች ብዛት እንዲቀንስ መመሪያ ሰጥቷል።

4 ለምሳሌ ያህል፣ በjw.org® ላይ እንዲሁም በJW ብሮድካስቲንግ ወርሃዊ ፕሮግራሞች ላይ በርካታ አበረታች ተሞክሮዎች ስለሚወጡ የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ መታተሙ እንዲቆም ተደርጓል። ለሕዝብ የሚሰራጩት መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች በአሁኑ ወቅት የሚታተሙት በዓመት ሦስት ጊዜ ብቻ ነው። እነዚህ ማስተካከያዎች የተደረጉበት ዓላማ ሌሎች እንቅስቃሴዎችን የምናደርግበት ተጨማሪ ጊዜ እንድናገኝ አይደለም። ከዚህ ይልቅ “ይበልጥ አስፈላጊ [ለሆኑት] ነገሮች” ትኩረት መስጠት እንድንችል ነው። (ፊልጵ. 1:10) እንግዲያው ቅድሚያ የምንሰጣቸውን ነገሮች መለየት እንዲሁም ከግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን የተሟላ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።

ቅድሚያ የምትሰጧቸውን ነገሮች ለዩ

5-6. ትኩረት ሰጥተን ልናጠናቸው የሚገቡን ጽሑፎች የትኞቹ ናቸው?

5 በምናጠናበት ጊዜ ቅድሚያ ልንሰጣቸው ከሚገቡን ነገሮች መካከል አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው? በየዕለቱ የአምላክን ቃል የምናጠናበት ጊዜ መመደብ እንዳለብን ምንም አያጠያይቅም። ለሳምንታዊው የጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ የሚመደቡት ምዕራፎች እንዲቀንሱ የተደረገው ባነበብነው ነገር ላይ የምናሰላስልበትና ተጨማሪ ምርምር የምናደርግበት በቂ ጊዜ እንድናገኝ ነው። ግባችን የተመደበውን ክፍል አንብበን መጨረስ ብቻ ሳይሆን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ልባችንን እንዲነካውና ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድንቀርብ እንዲረዳን መፍቀድ ሊሆን ይገባል።—መዝ. 19:14

6 ትኩረት ሰጥተን ልናጠናቸው የሚገቡን ሌሎች ጽሑፎች የትኞቹ ናቸው? ለመጠበቂያ ግንብ ጥናትና ለጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲሁም በሳምንቱ መካከል በሚደረገው ስብሰባ ላይ ለሚቀርቡት ሌሎች ክፍሎች ጥሩ ዝግጅት ማድረግ እንዳለብን የታወቀ ነው። በተጨማሪም በየጊዜው የሚወጡትን መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች ተከታትለን ማንበብ ይኖርብናል።

7. በድረ ገጻችን ወይም በJW ብሮድካስቲንግ ላይ የሚወጡትን የተትረፈረፉ ነገሮች ተከታትለን ማንበብ ወይም መመልከት ባንችል ተስፋ መቁረጥ የሌለብን ለምንድን ነው?

7 ሆኖም ‘በjw.org እና በJW ብሮድካስቲንግ ላይ የሚወጡት ነገሮች ራሳቸው እኮ በጣም ብዙ ናቸው!’ ብላችሁ ታስቡ ይሆናል። እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ በአንድ ምግብ ቤት ቡፌ ላይ ብዙ ዓይነት ምግቦች ቀርበዋል። ተመጋቢዎቹ የቀረበውን ምግብ ሁሉ መብላት እንደማይችሉ የታወቀ ነው። በመሆኑም የተወሰኑ ምግቦችን ብቻ መርጠው ይመገባሉ። በተመሳሳይ አንተም በኤሌክትሮኒክ ቅጂ ከሚዘጋጁት ነገሮች ጋር እኩል መሄድ እንዳልቻልክ ከተሰማህ ተስፋ አትቁረጥ። የቻልከውን ያህል ለማንበብ ወይም ለመመልከት ጥረት አድርግ። አሁን ደግሞ ጥናት ምን ነገሮችን እንደሚጨምርና ከጥናታችን የተሻለ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።

ጥናት ሥራ ነው!

8. ለመጠበቂያ ግንብ ጥናት ስትዘጋጁ የትኞቹን ነገሮች ማድረግ ትችላላችሁ? እንዲህ ማድረጋችሁስ ምን ጥቅም አስገኝቶላችኋል?

8 ጥናት ማለት አንድ አስፈላጊ ትምህርት ለመቅሰም ሲባል ትኩረትን ሰብስቦ ማንበብ ማለት ነው። የምናጠናውን ጽሑፍ እንዲሁ ላይ ላዩን ከማንበብና በጥያቄዎቹ መልስ ላይ ከማስመር ያለፈ ነገርን ይጠይቃል። ለምሳሌ ለመጠበቂያ ግንብ ጥናት ስትዘጋጁ በቅድሚያ በርዕሱ መጀመሪያ ላይ ያለውን የትምህርቱን ዓላማ አንብቡ። በመቀጠል በዋናው ርዕስ፣ በንዑስ ርዕሶቹና በክለሳ ጥያቄዎቹ ላይ ቆም ብላችሁ አስቡ። ከዚያም አንቀጾቹን ረጋ ብላችሁ በጥንቃቄ አንብቡ። የአንቀጹን ፍሬ ሐሳብ ለያዘው ዓረፍተ ነገር ትኩረት ስጡ፤ በአብዛኛው ይህ ዓረፍተ ነገር የሚገኘው በአንቀጹ መጀመሪያ ላይ ነው። ፍሬ ሐሳቡን የያዘው ዓረፍተ ነገር ብዙውን ጊዜ አንቀጹ ስለ ምን ጉዳይ እንደሚያብራራ ለማወቅ ይረዳችኋል። ርዕሰ ትምህርቱን ስታነቡ እያንዳንዱ አንቀጽ ከንዑስ ርዕሱ እንዲሁም ከአጠቃላይ ጭብጡ ጋር የሚያያዘው እንዴት እንደሆነ ለማሰብ ሞክሩ። በደንብ የማታውቋቸውን ቃላት እንዲሁም ተጨማሪ ምርምር ልታደርጉባቸው የምትፈልጓቸውን ነጥቦች ማስታወሻችሁ ላይ ያዙ።

9. (ሀ) መጠበቂያ ግንብ በምናጠናበት ጊዜ ለጥቅሶቹ ለየት ያለ ትኩረት መስጠት ያለብን ለምንድን ነው? እንዲህ ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው? (ለ) በኢያሱ 1:8 ላይ እንደተገለጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ከማንበብ በተጨማሪ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

9 በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ የምናጠናው፣ መጽሐፍ ቅዱስን ነው። በመሆኑም ለጥቅሶቹ በተለይም በጉባኤ ላይ ለሚነበቡት ጥቅሶች ልዩ ትኩረት ስጡ። በጥቅሶቹ ላይ ያሉት ቁልፍ ቃላት ወይም ሐረጎች የአንቀጹን ዋና ሐሳብ የሚደግፉት እንዴት እንደሆነ ለማስተዋል ሞክሩ። በተጨማሪም ጊዜ ወስዳችሁ በጥቅሶቹ ላይ ለማሰላሰልና እነዚህን ጥቅሶች በግል ሕይወታችሁ ተግባራዊ ማድረግ የምትችሉት እንዴት እንደሆነ ለማሰብ ጥረት አድርጉ።—ኢያሱ 1:8ን አንብብ።

ወላጆች፣ ማጥናት የሚቻልበትን መንገድ ለልጆቻችሁ አስተምሩ (አንቀጽ 10⁠ን ተመልከት) *

10. በዕብራውያን 5:14 መሠረት ወላጆች በቤተሰብ አምልኳቸው ላይ ልጆቻቸው እንዴት ማጥናትና ምርምር ማድረግ እንደሚችሉ ማስተማር ያለባቸው ለምንድን ነው?

10 ወላጆች ሳምንታዊው የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማቸው ለልጆቻቸው አስደሳች እንዲሆን እንደሚፈልጉ ግልጽ ነው። ደግሞም በእያንዳንዱ የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማቸው ላይ ስለ የትኛው ጉዳይ እንደሚወያዩ አስቀድመው ማሰብ ይኖርባቸዋል። ሆኖም በየሳምንቱ አንድ ለየት ያለ ነገር ወይም ጨዋታ ማዘጋጀት እንዳለባቸው ሊሰማቸው አይገባም። ወላጆች በቤተሰብ አምልኳቸው ላይ የJW ብሮድካስቲንግን ወርሃዊ ፕሮግራም መመልከት ወይም አልፎ አልፎ የኖኅን መርከብ እንደመሥራት ያሉ የተለዩ ነገሮችን ሊያደርጉ ቢችሉም ልጆቻቸው እንዴት ማጥናት እንደሚችሉ ማስተማራቸውም አስፈላጊ እንደሆነ አይዘነጉም። ለምሳሌ ልጆች ለጉባኤ ስብሰባዎች እንዴት መዘጋጀት እንደሚችሉ ወይም በትምህርት ቤት ባጋጠማቸው ጉዳይ ላይ ምርምር ማድረግ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ መማር አለባቸው። (ዕብራውያን 5:14ን አንብብ።) ልጆች ጊዜ ወስደው ስለ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ርዕሰ ጉዳይ የማጥናት ልማድ ካዳበሩ በጉባኤ፣ በወረዳና በክልል ስብሰባዎች ላይ የሚቀርቡትን ንግግሮች መከታተል ቀላል ይሆንላቸዋል፤ እነዚህ ንግግሮች ቪዲዮ ባይኖራቸው እንኳ ትኩረታቸውን ሰብስበው ለማዳመጥ ላይቸገሩ ይችላሉ። እርግጥ ነው፣ ለእያንዳንዱ የጥናት ፕሮግራም የምንመድበው ጊዜ ርዝማኔ የልጆቹን ዕድሜና ባሕርይ ያገናዘበ መሆን ይኖርበታል።

11. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን ራሳቸውን ችለው ትርጉም ያለው ጥናት እንዲያደርጉ ማሠልጠናችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

11 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችንም እንዴት ማጥናት እንደሚችሉ መማር አለባቸው። አዲሶች ሳሉ ለጥናታቸው ወይም ለጉባኤ ስብሰባዎች ሲዘጋጁ መልሱን አስምረው ስለመጡ ብቻ ደስ ይለናል። ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን ራሳቸውን ችለው ምርምር ማድረግና ትርጉም ባለው መንገድ ማጥናት እንዲችሉ ልናሠለጥናቸው ይገባል። ይህም ችግር ሲያጋጥማቸው ሮጠው ወደ አንድ ወንድም ወይም እህት ከመሄድ ይልቅ በጽሑፎቻችን ላይ ምርምር አድርገው ጠቃሚ ምክር እንዲያገኙ ይረዳቸዋል።

ግብ ይዛችሁ አጥኑ

12. የትኞቹን ግቦች በአእምሯችን ይዘን ልናጠና እንችላለን?

12 ማጥናት የማትወድ ዓይነት ሰው ከሆንክ ከጥናት ደስታ ማግኘት ፈጽሞ እንደማይቻል ይሰማህ ይሆናል። ሆኖም ጥናትን አስደሳች ማድረግ ይቻላል። መጀመሪያ ላይ አጠር ላለ ጊዜ በማጥናት ጀምር፤ ከዚያም ቀስ በቀስ ጊዜውን ረዘም ማድረግ ትችላለህ። ስታጠና አንድ ዓይነት ግብ ይኑርህ። እርግጥ ዋናው ግባችን ወደ ይሖዋ ይበልጥ መቅረብ ነው። ሆኖም አንድ ሰው ለጠየቀን ጥያቄ መልስ እንደመስጠት ወይም ላጋጠመን ችግር መፍትሔ እንደማግኘት ያሉ በአጭር ጊዜ የሚደረስባቸውን ግቦች ይዘን ማጥናት እንችላለን።

13. (ሀ) አንድ ወጣት ስለሚያምንባቸው ነገሮች ለሌሎች ለማስረዳት ምን ሊያደርግ ይችላል? አብራራ። (ለ) በቆላስይስ 4:6 ላይ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

13 ለምሳሌ፣ ትምህርት በመከታተል ላይ ያለህ ወጣት ነህ? ክፍል ውስጥ ስለ ዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ እየተማራችሁ ነው እንበል። በዚህ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ደግፈህ መናገር ብትፈልግም ብቃቱ እንደሌለህ ይሰማህ ይሆናል። ስለዚህ በጉዳዩ ላይ ምርምር ማድረግ ያስፈልግሃል ማለት ነው! ምርምር በምታደርግበት ጊዜ ሁለት ግቦችን በአእምሮህ ልትይዝ ትችላለህ፤ እነሱም (1) አምላክ ሁሉንም ነገሮች እንደፈጠረ ያለህን እምነት ማጠናከር (2) የምታምንበትን ነገር አሳማኝ በሆነ መንገድ ለሌሎች ማስረዳት ናቸው። (ሮም 1:20፤ 1 ጴጥ. 3:15) በቅድሚያ ‘አስተማሪው ሕይወት በዝግመተ ለውጥ እንደመጣ ለማስተማር የትኞቹን ማስረጃዎች አቅርቧል?’ ብለህ ራስህን ልትጠይቅ ትችላለህ። ከዚያም ጽሑፎቻችንን ተጠቅመህ ጥልቀት ያለው ምርምር አድርግ። የምታምንበትን ነገር ለሌሎች ማስረዳት የምታስበውን ያህል ከባድ ላይሆን ይችላል። አብዛኞቹ ሰዎች በዝግመተ ለውጥ የሚያምኑት አንድ የሚያከብሩት ሰው ይህ ጽንሰ ሐሳብ እውነት እንደሆነ ስለነገራቸው ብቻ ነው። አንድ ወይም ሁለት አሳማኝ ነጥቦችን ካገኘህ በቅን ልቦና ተነሳስተው ጥያቄ ለሚያቀርቡ ሰዎች አጥጋቢ መልስ መስጠት ትችላለህ።—ቆላስይስ 4:6ን አንብብ።

የማወቅ ፍላጎታችሁ እንዲቀሰቀስ አድርጉ

14-16. (ሀ) በደንብ ስለማታውቀው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ይበልጥ ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው? (ለ) በአንቀጹ ውስጥ የተጠቀሱትን ጥቅሶች ተጠቅመህ ስለ አሞጽ መጽሐፍ ይበልጥ የተሟላ መረጃ ማግኘት የምትችለው እንዴት እንደሆነ አብራራ። (“ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱት ሰዎች ጋር በሚገባ ተዋወቅ!” የሚለውንም ሣጥን ተመልከት።)

14 ለምሳሌ በቅርቡ በምናደርገው የጉባኤ ስብሰባ ላይ፣ አናሳ ተብለው የሚጠሩት ነቢያት * ከጻፏቸው መጻሕፍት መካከል አንዱን እንመረምራለን እንበል፤ ምናልባትም ይህን መጽሐፍ ስለጻፈው ነቢይ እምብዛም አታውቅ ይሆናል። በቅድሚያ ልትወስደው የሚገባህ እርምጃ ይህ ነቢይ ስለጻፈው ነገር የማወቅ ጉጉትህ እንዲቀሰቀስ ማድረግ ነው። እንዲህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

15 መጀመሪያ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ራስህን ጠይቅ፦ ‘ስለዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ ምን የማውቀው ነገር አለ? ይህ ሰው ማን ነው? ይኖር የነበረው የት ነው? መተዳደሪያውስ ምን ነበር?’ ስለ ጸሐፊው ይበልጥ ማወቅህ፣ የተጠቀመባቸውን ቃላትና የጠቀሳቸውን ምሳሌዎች በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት ያስችልሃል። መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ የጸሐፊውን ባሕርይ የሚያንጸባርቁ አገላለጾችን ለማስተዋል ሞክር።

16 ከዚያም መጽሐፉ የተጻፈው መቼ እንደሆነ ለማወቅ ጥረት አድርግ። በአዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ከገጽ 1594-1595 ላይ ያለውን “የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ሰንጠረዥ” የሚለውን ሣጥን በመመልከት ይህን በቀላሉ ማወቅ ትችላለህ። ተጨማሪ መረጃ ሀ6 ላይ የሚገኘውን ስለ ነቢያትና ስለ ነገሥታት የሚገልጸውን ሰንጠረዥ ማየትህም ሊጠቅምህ ይችላል። እያጠናህ ያለኸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ትንቢታዊ ይዘት ያለው ስለሆነ መጽሐፉ በተጻፈበት ወቅት የነበረውን ሁኔታ ለማወቅ ጥረት ማድረግህ አስፈላጊ ነው። ‘ይህ ነቢይ፣ ሕዝቡ የትኛውን መጥፎ ዝንባሌ ወይም ልማድ እንዲያስተካክል ለመርዳት እየሞከረ ነበር? እሱ በኖረበት ዘመን የኖሩ አንዳንድ ሰዎች እነማን ናቸው?’ የተሟላ መረጃ ለማግኘት ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትን ማጣቀስ ያስፈልግህ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ ነቢዩ አሞጽ በኖረበት ዘመን ስለተከናወኑት ነገሮች ይበልጥ የተሟላ መረጃ ለማግኘት በ2 ነገሥት እና በ2 ዜና ላይ ያሉ አንዳንድ ጥቅሶችን ማመሣከርህ ሊጠቅምህ ይችላል፤ እነዚህ ጥቅሶች ለ​አሞጽ 1:1 በተዘጋጁት የኅዳግ ማጣቀሻዎች ላይ ይገኛሉ። በተጨማሪም ከአሞጽ ጋር በተመሳሳይ ዘመን ላይ የኖረው ሆሴዕ የጻፈውን መጽሐፍ ልታጣቅስ ትችላለህ። እነዚህ ሁሉ መረጃዎች አሞጽ ስለኖረበት ዘመን ይበልጥ ማወቅ እንድትችል ይረዱሃል።—2 ነገ. 14:25-28፤ 2 ዜና 26:1-15፤ ሆሴዕ 1:1-11፤ አሞጽ 1:1

ለዝርዝር ጉዳዮች ትኩረት ስጡ

17-18. በአንቀጹ ውስጥ የተጠቀሱትን ምሳሌዎች ወይም የራስህን ምሳሌ በመጠቀም ጥቃቅን ለሚመስሉ ዝርዝር ጉዳዮች ትኩረት መስጠት የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትን አስደሳች ለማድረግ እንዴት እንደሚረዳ አብራራ።

17 መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ በአእምሯችን አንዳንድ ጥያቄዎችን ማንሳታችን ጠቃሚ ነው። ለምሳሌ በዘካርያስ ምዕራፍ 12 ላይ የሚገኘውን ስለ መሲሑ ሞት የሚናገረውን ትንቢት እያነበባችሁ ነው እንበል። (ዘካ. 12:10) ቁጥር 12 ላይ ስትደርሱ “የናታን ቤት” በመሲሑ ሞት ምክንያት አምርሮ እንደሚያለቅስ የሚገልጽ ዘገባ አነበባችሁ። ይህን ነጥብ እንዲሁ አንብባችሁ ከማለፍ ይልቅ ቆም ብላችሁ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ልትጠይቁ ትችላላችሁ፦ ‘በናታን ቤትና በመሲሑ መካከል ያለው ዝምድና ምንድን ነው? ስለዚህ ጉዳይ ተጨማሪ መረጃ ማግኘት የሚቻልበት መንገድ ይኖር ይሆን?’ ከዚያም ምርምር ማድረግ ትጀምራላችሁ። ለዚህ ጥቅስ የተዘጋጀው የኅዳግ ማጣቀሻ ወደ 2 ሳሙኤል 5:13, 14 ይመራችኋል፤ እዚያ ላይ ናታን ከንጉሥ ዳዊት ልጆች መካከል አንዱ እንደሆነ ታነብባላችሁ። በኅዳግ ማጣቀሻው ላይ የተጠቀሰው ሁለተኛው ጥቅስ ማለትም ሉቃስ 3:23, 31 ደግሞ ናታን በማርያም የትውልድ ሐረግ መስመር በኩል የኢየሱስ ቅድመ አያት እንደሆነ ይገልጻል። * አሁን የማወቅ ጉጉታችሁ ይበልጥ ይጨምራል! ኢየሱስ በዳዊት የዘር ሐረግ በኩል እንደሚመጣ በትንቢት መነገሩን ታውቃላችሁ። (ማቴ. 22:42) ሆኖም ዳዊት ከ20 የሚበልጡ ወንዶች ልጆች አሉት። ታዲያ ዘካርያስ የናታንን ቤት ለይቶ በመጥቀስ በኢየሱስ ሞት እንደሚያለቅስ መናገሩ የሚገርም አይደለም?

18 ሌላም ምሳሌ እንመልከት። በሉቃስ ምዕራፍ አንድ ላይ መልአኩ ገብርኤል ወደ ማርያም ሄዶ ስለምትወልደው ልጅ የሚከተለውን መልእክት እንደነገራት እናነብባለን፦ “[እሱ] ታላቅ ይሆናል፤ የልዑሉም አምላክ ልጅ ይባላል፤ ይሖዋ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘላለም ንጉሥ ሆኖ ይገዛል።” (ሉቃስ 1:32, 33) ይህን ጥቅስ ስናነብ አብዛኛውን ጊዜ የምናተኩረው በጥቅሱ የመጀመሪያ ክፍል ላይ ማለትም ኢየሱስ ‘የልዑሉ አምላክ ልጅ’ እንደሚባል በሚገልጸው ሐሳብ ላይ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ገብርኤል፣ ኢየሱስ ‘ንጉሥ ሆኖ እንደሚገዛም’ ትንቢት ተናግሯል። ይህን ሐሳብ ስናነብ፣ ማርያም እነዚህን ቃላት ስትሰማ ምን ስሜት አድሮባት ሊሆን እንደሚችል ልናስብ እንችላለን። ገብርኤል ከተናገረው ሐሳብ በመነሳት ኢየሱስ ንጉሥ ሄሮድስን ወይም ከእሱ በኋላ በእስራኤል ላይ ከሚነግሡት ገዢዎች መካከል አንዱን ተክቶ እንደሚነግሥ አስባ ይሆን? ኢየሱስ ንጉሥ ከሆነ ማርያም የንጉሥ እናት የመሆን ክብር የምታገኝ ከመሆኑም ሌላ ከቤተሰቧ ጋር በቤተ መንግሥት ውስጥ ትኖራለች ማለት ነው። ሆኖም ማርያም ለገብርኤል ስለዚህ ጉዳይ እንዳነሳችለት የሚጠቁም ምንም ማስረጃ የለም፤ በተጨማሪም ሁለቱ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንደጠየቁት በመንግሥቱ ውስጥ ለየት ያለ ቦታ እንዲሰጣት እንደጠየቀች የሚገልጽ ዘገባ አናገኝም። (ማቴ. 20:20-23) ይህን ዝርዝር መረጃ ማወቃችን ማርያም ምን ያህል ትሑት ሴት እንደሆነች ይበልጥ እንድናስተውል ይረዳናል!

19-20. በያዕቆብ 1:22-25 እና 4:8 ላይ እንደተገለጸው፣ የምናጠናበት ዓላማ ምንድን ነው?

19 የአምላክን ቃልም ሆነ ክርስቲያናዊ ጽሑፎቻችንን የምናጠናበት ዋነኛ ዓላማ ወደ ይሖዋ ይበልጥ መቅረብ እንደሆነ እናስታውስ። በተጨማሪም በአምላክ ፊት ‘ምን እንደምንመስል’ በትክክል ማወቅና እሱን ለማስደሰት የትኞቹን ለውጦች ማድረግ እንዳለብን መረዳት እንፈልጋለን። (ያዕቆብ 1:22-25⁠ን እና 4:8ን አንብብ።) እንግዲያው ምንጊዜም ማጥናት ከመጀመራችን በፊት ይሖዋ መንፈሱን እንዲሰጠን መጸለያችን አስፈላጊ ነው። ይሖዋ ከምናጠናው ነገር ሙሉ ተጠቃሚ መሆንና እሱ በሚያየን መንገድ ራሳችንን ማየት እንድንችል ይረዳን ዘንድ ልንለምነው ይገባል።

20 መዝሙራዊው ስለ አንድ ታማኝ የአምላክ አገልጋይ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “በይሖዋ ሕግ ደስ ይለዋል፤ ሕጉንም በቀንና በሌሊት በለሆሳስ ያነበዋል። . . . የሚሠራውም ሁሉ ይሳካለታል።” (መዝ. 1:2, 3) የሁላችንም ምኞት ልክ እንደዚህ ታማኝ የአምላክ አገልጋይ መሆን ነው።

መዝሙር 88 መንገድህን አሳውቀኝ

^ አን.5 ይሖዋ ልናነብባቸው፣ ልናጠናቸውና ልንመለከታቸው የምንችላቸውን በርካታ ነገሮች በልግስና ሰጥቶናል። ይህ ርዕስ ምን ማጥናት እንዳለባችሁ ለመወሰን ይረዳችኋል፤ በተጨማሪም ከጥናታችሁ የበለጠ ጥቅም ለማግኘት የሚረዷችሁን ተግባራዊ ምክሮች ይዟል።

^ አን.14 ተጨማሪ ማብራሪያ፦ አናሳ ነቢያት ተብለው የሚጠሩት ከሆሴዕ እስከ ሚልክያስ ያሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የጻፉት ነቢያት ናቸው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.63 የሥዕሉ መግለጫ፦ ወላጆች ለሳምንታዊው የመጠበቂያ ግንብ ጥናት እንዴት መዘጋጀት እንደሚቻል ለልጆቻቸው ሲያሳዩ።

^ አን.65 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ወንድም የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ ስለሆነው ስለ አሞጽ ምርምር ሲያደርግ። ከበስተ ጀርባው የሚታዩት ሥዕሎች ወንድም የመጽሐፍ ቅዱስን ዘገባ ሲያነብና ባነበበው ላይ ሲያሰላስል በዓይነ ሕሊናው የሚሥላቸውን ነገሮች የሚያሳዩ ናቸው።