በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 23

ወላጆች፣ ልጆቻችሁ ይሖዋን እንዲወዱ እርዷቸው

ወላጆች፣ ልጆቻችሁ ይሖዋን እንዲወዱ እርዷቸው

“አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ አእምሮህ ውደድ።”—ማቴ. 22:37

መዝሙር 134 ልጆች ከአምላክ በአደራ የተሰጡ ናቸው

ማስተዋወቂያ *

1-2. ሁኔታችን ሲለወጥ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የተለየ ትርጉም የሚሰጡን እንዴት እንደሆነ አብራራ።

 በሠርጋቸው ዕለት አምረው ደምቀው የመጡት ሙሽራውና ሙሽሪት ስለ ጋብቻ የሚሰጠውን የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግር በጥሞና እያዳመጡ ነው። በንግግሩ ላይ የሚቀርቡት መሠረታዊ ሥርዓቶች ለእነሱ አዲስ አይደሉም። ከዚያ ዕለት አንስቶ ግን ያ ትምህርት ለእነሱ ልዩ ትርጉም ይኖረዋል። ለምን? በጋብቻ ሕይወታቸው ትምህርቱን ተግባራዊ ማድረግ ስለሚጀምሩ ነው።

2 ክርስቲያን የሆኑ ባልና ሚስት፣ ወላጅ ሲሆኑም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። እስከዚያ ድረስ፣ ልጆች ስለማሳደግ ብዙ ንግግሮችን አዳምጠው ሊሆን ይችላል። አሁን ግን መሠረታዊ ሥርዓቶቹ ለእነሱ የተለየ ትርጉም ይኖራቸዋል። ምክንያቱም ወላጅነት አሁን የእነሱም የቤት ሥራ ነው። ይህ በእርግጥም ትልቅ ኃላፊነት ነው! በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ሁኔታችን ሲቀየር አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ይበልጥ ትርጉም ይሰጡናል። የእስራኤል ነገሥታት እንደታዘዙት ሁሉ የይሖዋ አገልጋዮችም ‘በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ’ ቅዱሳን መጻሕፍትን ማንበብና በዚያ ላይ ማሰላሰል ያለባቸው ለዚህ ነው።—ዘዳ. 17:19

3. በዚህ ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?

3 ወላጆች ክርስቲያኖች ከሚያገኟቸው ታላላቅ መብቶች አንዱን አግኝታችኋል፤ ይህም ልጆቻችሁን ስለ ይሖዋ ማስተማር ነው። ሆኖም ስለ ይሖዋ አምላክ መረጃ ከማስተላለፍ የበለጠ ነገር ማድረግ ይጠበቅባችኋል። ልጆቻችሁ ይሖዋን ከልብ እንዲወዱት መርዳት ያስፈልጋችኋል። ታዲያ ልጆቻችሁ ለይሖዋ ፍቅር እንዲያዳብሩ ለመርዳት ምን ማድረግ ትችላላችሁ? በዚህ ርዕስ ላይ የወላጅነት ሚናችሁን ለመወጣት የሚረዷችሁን አራት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንመረምራለን። (2 ጢሞ. 3:16) አንዳንድ ክርስቲያን ወላጆች የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ተግባራዊ በማድረጋቸው የተጠቀሙት እንዴት እንደሆነም እንመለከታለን።

ለወላጆች ጠቃሚ የሆኑ አራት መሠረታዊ ሥርዓቶች

ምንጊዜም የይሖዋን መመሪያ የምትፈልጉና ጥሩ ምሳሌ ለመሆን ጥረት የምታደርጉ ከሆነ ይህ በልጆቻችሁ ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል? (አንቀጽ 4, 8⁠ን ተመልከት)

4. ወላጆች ልጆቻቸው ይሖዋን እንዲወዱ ለመርዳት የሚረዳቸው አንዱ መሠረታዊ ሥርዓት ምንድን ነው? (ያዕቆብ 1:5)

4 መሠረታዊ ሥርዓት 1፦ የይሖዋን መመሪያ ፈልጉ። ልጆቻችሁ ይሖዋን እንዲወዱ ለመርዳት የሚያስፈልገውን ጥበብ እንዲሰጣችሁ ይሖዋን ጠይቁት። (ያዕቆብ 1:5ን አንብብ።) ከእሱ የተሻለ መካሪ ልታገኙ አትችሉም። እንዲህ የምንልባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉ፤ ሁለቱ ግን እነዚህ ናቸው። አንደኛ፣ የይሖዋን ያህል የወላጅነት ተሞክሮ ያለው የለም። (መዝ. 36:9) ሁለተኛ እሱ የሚሰጠው ጥበብ ያለበት ምክር ምንጊዜም ጠቃሚ ነው።—ኢሳ. 48:17

5. (ሀ) የይሖዋ ድርጅት ወላጆችን ለመርዳት ምን አዘጋጅቷል? (ለ) ቪዲዮው ላይ እንደሚታየው ወንድም አቢሊዮ እና እህት ኡላ ልጆቻቸውን ካሳደጉበት መንገድ ምን ትምህርት አግኝታችኋል?

5 ይሖዋ በቃሉና በድርጅቱ አማካኝነት ልጆቻችሁ እሱን እንዲወዱ ለመርዳት የሚያስችላችሁ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ አቅርቦላችኋል። (ማቴ. 24:45) ለምሳሌ “ለቤተሰብ” በሚለው ተከታታይ ርዕስ ሥር ብዙ ጠቃሚ ምክር ማግኘት ትችላላችሁ። ይህ ዓምድ ለበርካታ ዓመታት ንቁ! መጽሔት ላይ ታትሞ ይወጣ የነበረ ሲሆን አሁን ድረ ገጻችን ላይ ይገኛል። jw.org ላይ የሚወጡ ቃለ መጠይቆችና አጭር ድራማዎችም ወላጆች ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ የይሖዋን ምክር ተግባራዊ ማድረግ እንዲችሉ ይረዷቸዋል። *ምሳሌ 2:4-6

6. አንድ አባት እሱና ባለቤቱ ከይሖዋ ድርጅት ስላገኙት እርዳታ ምን ይሰማዋል?

6 ብዙ ወላጆች ይሖዋ በድርጅቱ አማካኝነት ላደረገው ዝግጅት አድናቆታቸውን ገልጸዋል። ጆ የተባለ አባት እንዲህ ብሏል፦ “ሦስት ልጆችን በእውነት ውስጥ ማሳደግ ቀላል አይደለም። እኔና ባለቤቴ ይሖዋ እንዲረዳን ሁልጊዜ እንጸልያለን። ደግሞም ብዙ ጊዜ እንደተመለከትነው እኛ ለሚያስፈልገን ሁኔታ የሚሠራ ርዕስ ወይም ቪዲዮ ልክ በሚያስፈልገን ጊዜ ላይ ይወጣል። የይሖዋን መመሪያ ባናገኝ ኖሮ ምን ይውጠን ነበር?” ጆ እና ባለቤቱ እንዳስተዋሉት እነዚህ ዝግጅቶች ልጆቻቸውን ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡ ለመርዳት አስችለዋቸዋል።

7. ወላጆች ጥሩ ምሳሌ መሆናቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ሮም 2:21)

7 መሠረታዊ ሥርዓት 2፦ ምሳሌ ሁኑላቸው። ልጆች ወላጆቻቸው የሚያደርጉትን ነገር በደንብ ያያሉ፤ ብዙውን ጊዜም ያዩትን ነገር ይኮርጃሉ። እርግጥ ነው፣ ፍጹም የሆነ ወላጅ የለም። (ሮም 3:23) ያም ሆኖ ጥበበኛ ወላጆች ለልጆቻቸው ጥሩ ምሳሌ ለመሆን የቻሉትን ሁሉ ያደርጋሉ። (ሮም 2:21ን አንብብ።) አንድ አባት ስለ ልጆች ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ልጆች ልክ እንደ ስፖንጅ ስለሆኑ ሁሉንም ነገር በቀላሉ ይይዛሉ። የምንናገረውና የምናደርገው ነገር የማይጣጣም ከሆነ ይህን መገንዘባቸው አይቀርም።” ስለዚህ ልጆቻችን ይሖዋን እንዲወዱ ከፈለግን እኛ ራሳችን ለእሱ ያለን ፍቅር ጠንካራና በግልጽ የሚታይ ሊሆን ይገባል።

8-9. አንድሩ እና ኤማ ከሰጡት ሐሳብ ምን ትምህርት አግኝታችኋል?

8 ወላጆች ልጆቻቸው ይሖዋን እንዲወዱ ሊያስተምሩ የሚችሉባቸው ብዙ መንገዶች አሉ። አንድሩ የተባለ የ17 ዓመት ወንድም ምን እንዳለ እንመልከት፦ “ወላጆቼ ጸሎት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ሁልጊዜ ይነግሩኛል። አባቴ ሁልጊዜ ማታ የራሴን ጸሎት ብጸልይም እንኳ አብሮኝ ይጸልያል። ወላጆቼ ‘የፈለጋችሁትን ያህል ይሖዋን ልታዋሩት ትችላላችሁ’ በማለት ሁልጊዜ ይነግሩናል። ለጸሎት ይህን ያህል ትኩረት መስጠታቸው በእኔ ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል። አሁን ይሖዋን በነፃነት ማነጋገርና እሱን እንደ አፍቃሪ አባቴ መመልከት አይከብደኝም።” ወላጆች ለይሖዋ ያላችሁ ፍቅር በልጆቻችሁ ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ፈጽሞ አቅልላችሁ አትመልከቱት።

9 የኤማንም ምሳሌ እንመልከት። አባቷ ቤተሰቡን ጥሎ ሲሄድ ብዙ ያልተከፈለ ዕዳ ነበረባቸው። ኤማ እንዲህ ብላለች፦ “እናቴ ገንዘብ አጥታ የተቸገረችባቸው ብዙ ጊዜያት ነበሩ፤ ሆኖም ሁልጊዜ የምታወራው ይሖዋ አገልጋዮቹን ምን ያህል እንደሚንከባከብና የሚያስፈልጋቸውን እንደሚያቀርብላቸው ነው። የምታወራውን ነገር እንደምታምንበት ሕይወቷ ራሱ ይመሠክራል። እናቴ እኔን ያስተማረችኝን ነገር እሷም ሠርታበታለች።” ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ወላጆች አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥም እንኳ ለልጆቻቸው ምሳሌ መሆን ይችላሉ።—ገላ. 6:9

10. ብዙ እስራኤላውያን ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ማውራት የሚችሉበት ምን አጋጣሚ ነበራቸው? (ዘዳግም 6:6, 7)

10 መሠረታዊ ሥርዓት 3፦ ልጆቻችሁን ሁልጊዜ አዋሯቸው። ይሖዋ የጥንቶቹን እስራኤላውያን ልጆቻቸውን ስለ እሱ አዘውትረው እንዲያስተምሯቸው አዟቸው ነበር። (ዘዳግም 6:6, 7ን አንብብ።) እነዚህ ወላጆች በየቀኑ ከልጆቻቸው ጋር ማውራትና ለይሖዋ ፍቅር እንዲያድርባቸው መርዳት የሚችሉባቸው በርካታ አጋጣሚዎች ነበሯቸው። ለምሳሌ አንድ እስራኤላዊ ልጅ በእርሻ ወይም በመከር ወቅት አባቱን እያገዘ ብዙ ሰዓታት ሊያሳልፍ ይችላል። እህቱም ብትሆን ልብስ በመስፋት፣ በመሸመንና ሌሎች የቤት ውስጥ ሥራዎችን በማከናወን እናቷን ስታግዝ ትውላለች። ወላጆችና ልጆች አብረው ሲሠሩ ስለ ብዙ ጉዳዮች ማውራት ይችላሉ። ለምሳሌ ስለ ይሖዋ ጥሩነትና ቤተሰባቸውን እንዴት እንደረዳው የማውራት አጋጣሚ ያገኛሉ።

11. ክርስቲያን ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ለማውራት የሚያስችላቸው አንዱ አጋጣሚ ምንድን ነው?

11 አሁን ጊዜው ተቀይሯል። በብዙ አገሮች ውስጥ ወላጆችና ልጆች በቀን ውስጥ አብረው የሚያሳልፉት ሰፋ ያለ ጊዜ ማግኘት አይችሉም። ወላጆች ሥራ ቦታ፣ ልጆች ደግሞ ትምህርት ቤት ይውላሉ። ስለዚህ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ለማውራት የሚያስችሏቸውን አጋጣሚዎች በንቃት መፈለግ አለባቸው። (ኤፌ. 5:15, 16፤ ፊልጵ. 1:10) የቤተሰብ አምልኮ እንዲህ ዓይነት አጋጣሚ ያስገኛል። አሌክሳንደር የተባለ ወጣት ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “አባቴ የቤተሰብ አምልኮ ማድረግ እንድንችል ሁልጊዜ አስፈላጊውን ዝግጅት ያደርጋል። ይህን ጊዜ ምንም ነገር እንዲይዝበት አይፈቅድም። ከጥናቱ በኋላ ደግሞ ዝም ብለን እናወራለን።”

12. የቤተሰብ ራሶች በቤተሰብ አምልኮ ወቅት ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል?

12 የቤተሰብ ራሶች የቤተሰብ አምልኳችሁ ለልጆቻችሁ አስደሳች እንዲሆን ምን ማድረግ ትችላላችሁ? በቅርቡ የወጣውን ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለ ግሩም የሆነ ጽሑፍ ለምን አብራችሁ አታጠኑም? ይህ መጽሐፍ ከልጆቻችሁ ጋር ነፃ የሆነ ውይይት ለማድረግ ግሩም አጋጣሚ ይሰጣችኋል። ልጆቻችሁ ስሜታቸውንና የሚያሳስባቸውን ነገር አውጥተው እንዲነግሯችሁ ከፈለጋችሁ የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማችሁን እነሱን ለመውቀስ ወይም ለመገሠጽ አትጠቀሙበት። ልጆቻችሁ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚጋጭ ሐሳብ ከተናገሩ ላለመበሳጨት ተጠንቀቁ። እንዲያውም ስሜታቸውን አውጥተው ስለገለጹ ደስ ሊላችሁ ይገባል። ምንጊዜም በነፃነት ሐሳባቸውን እንዲናገሩም አበረታቷቸው። ደግሞስ ልጆቻችሁ በእርግጥ ምን እንደሚሰማቸው ካላወቃችሁ እነሱን እንዴት ጥሩ አድርጋችሁ መርዳት ትችላላችሁ?

ወላጆች ተፈጥሮን በማሳየት ለልጆቻቸው ስለ ይሖዋ ባሕርያት ማስተማር የሚችሉት እንዴት ነው? (አንቀጽ 13⁠ን ተመልከት)

13. ወላጆች ልጆቻቸው ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡ ለመርዳት በየትኞቹ አጋጣሚዎች መጠቀም ይችላሉ?

13 ወላጆች ልጆቻችሁ ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡ ለመርዳት በቀን ውስጥ የምታገኟቸውን አጋጣሚዎች በንቃት ተከታተሉ። ስለ አፍቃሪው አምላካችን የምታስተምሯቸው መጽሐፍ ቅዱስ በምታስጠኗቸው ፕሮግራም ላይ ብቻ መሆን የለበትም። ሊሳ የተባለች እናት ምን እንዳለች እንመልከት፦ “ልጆቻችን ተፈጥሮን ሲያዩ ይሖዋን እንዲያስቡ ረድተናቸዋል። ለምሳሌ ልጆቻችን ውሻችን የሚያደርጋቸውን ነገሮች አይተው የሚስቁበት ጊዜ አለ፤ ይህን አጋጣሚ ተጠቅመን፣ ፈጣሪያችን ደስተኛ አምላክ እንደሆነና እኛም በሕይወታችን እንድንደሰት እንደሚፈልግ እናስተምራቸዋለን።”

ወላጆች የልጆቻችሁ ጓደኞች እነማን እንደሆኑ ታውቃላችሁ? (አንቀጽ 14⁠ን ተመልከት) *

14. ወላጆች ልጆቻቸው ጥሩ ጓደኞች እንዲመርጡ መርዳታቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ምሳሌ 13:20)

14 መሠረታዊ ሥርዓት 4፦ ልጆቻችሁ ጥሩ ወዳጆች እንዲያፈሩ እርዷቸው። የምንመርጣቸው ጓደኞች በጥሩም ሆነ በመጥፎ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩብን የአምላክ ቃል በግልጽ ይናገራል። (ምሳሌ 13:20ን አንብብ።) ወላጆች የልጆቻችሁ ጓደኞች እነማን እንደሆኑ ታውቃላችሁ? በአካል አግኝታችኋቸው ወይም ከእነሱ ጋር ጊዜ አሳልፋችሁ ታውቃላችሁ? ልጆቻችሁ ይሖዋን ከሚወዱ ሰዎች ጋር ጓደኝነት እንዲመሠርቱ ለመርዳት ምን ማድረግ ትችላላችሁ? (1 ቆሮ. 15:33) ጥሩ መንፈሳዊ አቋም ያላቸው አንዳንድ ክርስቲያኖችን ከቤተሰባችሁ ጋር ጊዜ እንዲያሳልፉ በመጋበዝ ልጆቻችሁ ጥሩ ጓደኞች እንዲመርጡ መርዳት ትችላላችሁ።—መዝ. 119:63

15. ወላጆች ልጆቻቸው ጥሩ ጓደኞች እንዲመርጡ ለመርዳት ምን ማድረግ ይችላሉ?

15 ቶኒ የተባለን አባት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እሱና ባለቤቱ ልጆቻቸው ጥሩ ጓደኞች እንዲያፈሩ ለመርዳት ምን እንዳደረጉ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ልጆቻችንን ባሳደግንባቸው ዓመታት ሁሉ እኔና ባለቤቴ የተለያየ ዕድሜ፣ ባሕልና አስተዳደግ ያላቸው ወንድሞችንና እህቶችን ቤታችን እንጋብዝ ነበር። አብረናቸው ምሳ እንበላለን ወይም የቤተሰብ አምልኮ እናደርጋለን። ይህ ይሖዋን ከሚወዱና እሱን በደስታ ከሚያገለግሉ ሰዎች ጋር ለመተዋወቅ የሚያስችል ግሩም አጋጣሚ ነው። የወረዳ የበላይ ተመልካቾችን፣ ሚስዮናውያንን እንዲሁም ሌሎችን ቤታችን የማስተናገድ መብት አግኝተናል። ተሞክሯቸው፣ ቅንዓታቸው እንዲሁም ራሳቸውን ሳይቆጥቡ መስጠታቸው በልጆቻችን ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አሳድሯል፤ ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡም ረድቷቸዋል።” እንግዲያው ወላጆች ልጆቻችሁ ጥሩ ጓደኞች እንዲመርጡ ለመርዳት ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ።

ተስፋ አትቁረጡ

16. ወላጆች ልጃችሁ ይሖዋን ማገልገል እንደማይፈልግ ቢናገር ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

16 የቻላችሁትን ሁሉ ጥረት ብታደርጉም ከልጆቻችሁ አንዱ ይሖዋን ማገልገል እንደማይፈልግ ቢገልጽስ? ‘ጥሩ ወላጅ አይደለሁም’ ብላችሁ አትደምድሙ። ይሖዋ ልጃችሁን ጨምሮ ለሁላችንም የመምረጥ ነፃነት ሰጥቶናል፤ ስለዚህ እሱን ለማገልገል ወይም ላለማገልገል መምረጥ እንችላለን። ልጃችሁ ይሖዋን ላለማገልገል ከመረጠ አንድ ቀን እንደሚመለስ ተስፋ አድርጉ። የጠፋውን ልጅ ምሳሌ አስታውሱ። (ሉቃስ 15:11-19, 22-24) ይህ ወጣት ከጽድቅ መንገድ በጣም ርቆ ነበር፤ በመጨረሻ ግን ተመልሷል። አንዳንዶች “ይሄ እኮ ምሳሌ ነው፤ የእውነት የሚፈጸም ነገር ነው እንዴ?” ይሉ ይሆናል። መልሱ “አዎ” ነው! ኢሊ የተባለ ወጣት ያጋጠመው ነገር ይህን ያረጋግጣል።

17. ከኢሊ ተሞክሮ ምን ማበረታቻ ታገኛላችሁ?

17 ኢሊ ወላጆቹ ስላደረጉት ጥረት ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ለይሖዋና ለቃሉ ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር እንዲያድርብኝ ለመርዳት የቻሉትን ሁሉ ጥረዋል። ይሁን እንጂ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ስሆን ማመፅ ጀመርኩ።” ኢሊ ሁለት ዓይነት ሕይወት መምራት ጀመረ። ወላጆቹ እሱን በመንፈሳዊ ለመርዳት ያደረጉትን ጥረትም አልተቀበለም። ከቤት ከወጣ በኋላ ሥነ ምግባር የጎደለው ሕይወት ውስጥ ገባ። ያም ቢሆን አልፎ አልፎ ከአንድ ጓደኛው ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይወያይ ነበር። ኢሊ እንዲህ ብሏል፦ “ለጓደኛዬ ስለ ይሖዋ ብዙ በነገርኩት መጠን እኔም ስለ ይሖዋ ይበልጥ ማሰብ ጀመርኩ። ወላጆቼ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ዘር በልቤ ውስጥ ለመዝራት ብዙ ለፍተዋል፤ በልቤ ውስጥ ተቀብረው የቆዩት እነዚህ ዘሮች ቀስ በቀስ ማደግ ጀመሩ።” ውሎ አድሮ ኢሊ ወደ እውነት ተመለሰ። * ወላጆቹ ከልጅነቱ ጀምሮ ይሖዋን እንዲወድ ስላስተማሩት ምን ያህል ተደስተው እንደሚሆን መገመት ይቻላል።—2 ጢሞ. 3:14, 15

18. ልጆቻቸው ይሖዋን እንዲወዱ ለመርዳት ተግተው ስለሚሠሩ ወላጆች ምን ይሰማችኋል?

18 ወላጆች ታላቅ መብት ተሰጥቷችኋል፤ ይሖዋን የሚያገለግል አዲስ ትውልድ ኮትኩቶ የማሳደግ አደራ ተጥሎባችኋል። (መዝ. 78:4-6) ይህ ቀላል ኃላፊነት አይደለም። ልጆቻችሁን ለመርዳት ለምታደርጉት ከፍተኛ ጥረት ከልባችን ልናመሰግናችሁ እንወዳለን። እንግዲያው ልጆቻችሁ ይሖዋን እንዲወዱ ለመርዳትና በእሱ ተግሣጽና ምክር ለማሳደግ የምትችሉትን ሁሉ ማድረጋችሁን ቀጥሉ። ይህን ካደረጋችሁ አፍቃሪ የሆነው ሰማያዊ አባታችን እንደሚደሰትባችሁ እርግጠኞች መሆን ትችላላችሁ።—ኤፌ. 6:4

መዝሙር 135 የይሖዋ ፍቅራዊ ግብዣ፦ ‘ልጄ ሆይ፣ ጥበበኛ ሁን’

^ ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸውን በጣም ይወዳሉ። የልጆቻቸውን ቁሳዊና ስሜታዊ ፍላጎት ለማሟላት ብዙ ይደክማሉ። ከሁሉ በላይ ግን ይሖዋን መውደድ በልጆቻቸው ልብ ውስጥ እንዲቀረጽ የቻሉትን ሁሉ ያደርጋሉ። ይህ ርዕስ ወላጆች ይህን ግብ ለማሳካት የሚረዷቸውን አራት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ያብራራል።

^ jw.org ላይ የወጣውን ይሖዋ ልጆቻችንን እንዴት እንደምናሳድግ አስተምሮናል የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት።

^ በሚያዝያ 1, 2012 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ አባት የልጁን ጓደኞች ለማወቅ ሲል ከልጁና ከጓደኛው ጋር ቅርጫት ኳስ ሲጫወት።