በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 21

የራእይ መጽሐፍ፣ የወደፊት ሕይወትህን የሚመለከት ምን ሐሳብ ይዟል?

የራእይ መጽሐፍ፣ የወደፊት ሕይወትህን የሚመለከት ምን ሐሳብ ይዟል?

“አሜን! ጌታ ኢየሱስ፣ ና።”—ራእይ 22:20

መዝሙር 142 ተስፋችንን አጥብቀን እንያዝ

ማስተዋወቂያ *

1. ሰዎች ሁሉ የትኛውን አስፈላጊ ውሳኔ ማድረግ ያስፈልጋቸዋል?

 በዛሬው ጊዜ ያሉ ሰዎች አንድ አስፈላጊ ውሳኔ ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። የጽንፈ ዓለሙ ገዢ የመሆን መብት ያለውን ይሖዋን መደገፍ ወይም ጨካኝ ጠላቱ ከሆነው ከሰይጣን ዲያብሎስ ጎን መቆም። በዚህ ጉዳይ ላይ መሃል ሰፋሪ መሆን አይቻልም። ሰዎች የሚያደርጉት ውሳኔ ምንም ይሁን ምን ዘላለማዊ ዕጣቸውን ይወስነዋል። (ማቴ. 25:31-33, 46) ‘በታላቁ መከራ’ ወቅት፣ እንዲድኑ ወይም እንዲጠፉ ምልክት የሚደረግባቸው ውሳኔያቸውን መሠረት በማድረግ ነው።—ራእይ 7:14፤ 14:9-11፤ ሕዝ. 9:4, 6

2. (ሀ) ዕብራውያን 10:35-39 ምን እንድናደርግ ያበረታታናል? (ለ) የራእይ መጽሐፍ እንዴት ይጠቅመናል?

2 ዕብራውያን 10:35-39ን አንብብ። አንተ የይሖዋን አገዛዝ ለመደገፍ መርጠህ ከሆነ ጥሩ ውሳኔ አድርገሃል። ሌሎችም ትክክለኛውን ውሳኔ እንዲያደርጉ መርዳት እንደምትፈልግ የታወቀ ነው። ለዚህም በራእይ መጽሐፍ ላይ የሚገኘውን ሐሳብ መጠቀም ትችላለህ። ይህ አስደናቂ መጽሐፍ ይሖዋን የሚቃወሙ ሁሉ ምን እንደሚደርስባቸው ይናገራል። ይህ ብቻ ሳይሆን ግን የእሱን አገዛዝ በታማኝነት የሚደግፉ ሁሉ ምን ዓይነት በረከቶች እንደሚጠብቋቸውም ያጎላል። እንደነዚህ ያሉ አስፈላጊ እውነቶችን መመርመራችን ጠቃሚ ነው። ይህን ማድረጋችን ይሖዋን እስከ መጨረሻው ለማገልገል ያለንን ቁርጠኝነት ያጠናክርልናል። በተጨማሪም የተማርነውን ነገር ለሌሎች በማካፈል ትክክለኛውን ውሳኔ እንዲያደርጉና በውሳኔያቸው እንዲጸኑ ልንረዳቸው እንችላለን።

3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?

3 በዚህ ርዕስ ላይ የሚከተሉትን ጥያቄዎች መልስ እንመረምራለን፦ የአምላክን አገዛዝ የሚደግፉ ሰዎች ምን ይጠብቃቸዋል? በሌላ በኩል ደግሞ በራእይ መጽሐፍ ላይ የተገለጸውን ደማቅ ቀይ አውሬ የሚደግፉ ሁሉ ምን ይደርስባቸዋል?

ታማኝ ሰዎች ምን ይጠብቃቸዋል?

4. ሐዋርያው ዮሐንስ በሰማይ ከኢየሱስ ጋር ቆሞ ያየው የትኛውን ቡድን ነው?

4 ሐዋርያው ዮሐንስ የይሖዋን አገዛዝ የሚደግፉና የዘላለም ሕይወት ሽልማት የሚሰጣቸው ሁለት ቡድኖች በራእይ ተመልክቷል። የመጀመሪያው ቡድን አባላት 144,000 ናቸው። (ራእይ 7:4) የሚወሰዱት ከምድር ሲሆን ሰማይ ሄደው ከኢየሱስ ጋር የአምላክ መንግሥት ክፍል ይሆናሉ። ከእሱ ጋር ሆነው ምድርን ያስተዳድራሉ። (ራእይ 5:9, 10፤ 14:3, 4) ዮሐንስ በራእዩ ላይ በሰማይ በጽዮን ተራራ ላይ ከኢየሱስ ጋር ቆመው አይቷቸዋል።—ራእይ 14:1

5. የ144,000ዎቹ ቀሪዎች በቅርቡ ምን ይሆናሉ?

5 ባለፉት ዘመናት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የ144,000ዎቹ ክፍል እንዲሆኑ ሲመረጡ ቆይተዋል። (ሉቃስ 12:32፤ ሮም 8:17) ሆኖም በመጨረሻዎቹ ቀናት በምድር ላይ ቀሪዎች ወይም ጥቂት ቁጥር ያላቸው ቅቡዓን ብቻ በሕይወት እንደሚኖሩ ለዮሐንስ ተነግሮታል። እነዚህ ‘ቀሪዎች’ ታላቁ መከራ ከመጀመሩ በፊት፣ የይሖዋን ሞገስ እንዳገኙ የሚያሳየው የመጨረሻው “ማኅተም” ይደረግባቸዋል። (ራእይ 7:2, 3፤ 12:17) ታላቁ መከራ ከጀመረ ከተወሰነ ጊዜ በኋላም እነዚህ ቀሪዎች ወደ ሰማይ ይወሰዳሉ፤ እዚያም ታማኝ ሆነው ምድራዊ ሕይወታቸውን ካጠናቀቁት ከሌሎቹ የ144,000 አባላት ጋር ይቀላቀላሉ። ከዚያም ከኢየሱስ ጋር የአምላክ መንግሥት ተባባሪ ገዢዎች ይሆናሉ።—ማቴ. 24:31፤ ራእይ 5:9, 10

6-7. (ሀ) ዮሐንስ ቀጥሎ የትኛውን ቡድን ተመለከተ? ስለ እነሱስ ምን የምናውቀው ነገር አለ? (ለ) ቅቡዓን ቀሪዎችም ሆኑ ‘የእጅግ ብዙ ሕዝብ’ አባላት ራእይ ምዕራፍ 7 ትኩረታቸውን የሚስበው ለምንድን ነው?

6 ዮሐንስ የሰማዩን ቡድን ካየ በኋላ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ተመለከተ። ከ144,000ዎቹ በተቃራኒ የዚህ ቡድን አባላት ሊቆጠሩ አይችሉም። (ራእይ 7:9, 10) ስለ እነሱ ምን የምናውቀው ነገር አለ? ዮሐንስ እንዲህ ተብሏል፦ “እነዚህ ታላቁን መከራ አልፈው የመጡ ናቸው፤ ልብሳቸውንም በበጉ ደም አጥበው ነጭ አድርገውታል።” (ራእይ 7:14) የዚህ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” አባላት ከታላቁ መከራ ከተረፉ በኋላ በምድር ላይ ይኖራሉ፤ እንዲሁም አስደናቂ በረከቶችን ያገኛሉ።—መዝ. 37:9-11, 27-29፤ ምሳሌ 2:21, 22፤ ራእይ 7:16, 17

7 ተስፋችን ወደ ሰማይ መሄድም ሆነ በምድር ላይ መኖር ራእይ ምዕራፍ 7 ላይ ያለው መግለጫ ላይ ራሳችንን ልናገኘው ይገባል። የአምላክን አገልጋዮች ያቀፉት ሁለቱም ቡድኖች እንዴት ያለ አስደናቂ ጊዜ ይጠብቃቸዋል! የይሖዋን አገዛዝ ለመደገፍ በመምረጣችን ያን ጊዜ በጣም እንደምንደሰት የታወቀ ነው። የራእይ መጽሐፍ ስለ ታላቁ መከራ ሌላስ የሚነግረን ነገር ይኖራል?—ማቴ. 24:21

የአምላክ ተቃዋሚዎች ምን ይደርስባቸዋል?

8. ታላቁ መከራ የሚጀምረው በምንድን ነው? ብዙዎቹ ሰዎች የሚሰጡት ምላሽስ ምንድን ነው?

8 ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው በቅርቡ የዓለም መንግሥታት በታላቂቱ ባቢሎን ማለትም በዓለም የሐሰት ሃይማኖቶች ሁሉ ላይ ይነሳሉ። (ራእይ 17:16, 17) ይህ ክንውን የታላቁ መከራ መጀመሪያ ነው። ታዲያ ሰዎች ይህን ሲያዩ ወደ ይሖዋ አምልኮ ይጎርፉ ይሆን? በፍጹም። ከዚህ በተቃራኒ ራእይ ምዕራፍ 6 እንደሚያሳየው ይሖዋን የማያገለግሉ ሰዎች በዚያ ወሳኝ ወቅት ላይ ከለላ ለማግኘት ወደዚህ ዓለም የፖለቲካና የንግድ ሥርዓት ዞር ይላሉ፤ ራእዩ ላይ እነዚህ ነገሮች በተራሮች ተመስለዋል። እነዚህ ሰዎች የአምላክን መንግሥት ስለማይደግፉ ይሖዋ እንደ ተቃዋሚዎቹ ይቆጥራቸዋል።—ሉቃስ 11:23፤ ራእይ 6:15-17

9. የይሖዋ አገልጋዮች በታላቁ መከራ ወቅት ከሌሎች ተለይተው የሚወጡት እንዴት ነው? ይህስ ምን ያስከትልባቸዋል?

9 የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች በዚያ የመከራ ወቅት ከሌሎች ተለይተው እንደሚወጡ የታወቀ ነው። በምድር ላይ ይሖዋን የሚያገለግለውና “ለአውሬው” ድጋፍ ለመስጠት ፈቃደኛ የማይሆነው ብቸኛው ቡድን የይሖዋ ሕዝብ ይሆናል። (ራእይ 13:14-17) ይህ አቋማቸው የይሖዋን ተቃዋሚዎች ቁጣ ያስነሳል። በዚህም የተነሳ፣ ጥምረት የፈጠሩ ብሔራት በምድር ዙሪያ ባሉ የአምላክ ሕዝቦች ላይ ጥቃት ይሰነዝራሉ። ብሔራት የሚወስዱት ይህ የእብደት እርምጃ በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ላይ የማጎጉ ጎግ ጥቃት ተብሎ የተገለጸው ነው።—ሕዝ. 38:14-16

10. በራእይ 19:19-21 ላይ እንደተገለጸው በሕዝቡ ላይ ጥቃት ሲሰነዘር ይሖዋ ምን ምላሽ ይሰጣል?

10 ይሖዋ ለዚህ የጭካኔ ጥቃት ምን ምላሽ ይሰጣል? “ታላቅ ቁጣዬ ይነድዳል” ብሏል። (ሕዝ. 38:18, 21-23) ራእይ ምዕራፍ 19 ከዚያ በኋላ ምን እንደሚከናወን ይነግረናል። ይሖዋ ሕዝቡን ለመታደግና ጠላቶቹን ለመደምሰስ ልጁን ይልከዋል። ኢየሱስ በሚወስደው የመልሶ ማጥቃት እርምጃ “በሰማይ ያሉት ሠራዊቶች” አብረውት ይሆናሉ፤ እነሱም ታማኝ መላእክትና 144,000ዎቹ ናቸው። (ራእይ 17:14፤ 19:11-15) የጦርነቱ ውጤት ምን ይሆናል? ይሖዋን የሚቃወሙ ሰዎችና ድርጅቶች በሙሉ ተጠራርገው ይጠፋሉ።ራእይ 19:19-21ን አንብብ።

ከጦርነቱ በኋላ ሠርግ ይደገሳል

11. የራእይን መጽሐፍ የሚደመድመው ልዩ ክንውን ምንድን ነው?

11 በምድር ያሉ ታማኝ ሰዎች በአምላክ ጠላቶች ላይ ከሚደርሰው ጥፋት ሲተርፉ ምን ያህል እንደሚደሰቱ እስቲ አስበው! ያ ጊዜ ምንኛ አስደሳች ይሆናል! ታላቂቱ ባቢሎን ስትጠፋ በሰማይ ታላቅ የደስታ ጩኸት ይሰማል፤ ሆኖም ከዚያ የበለጠ ደስታ የሚያስገኝ ነገር አለ። (ራእይ 19:1-3) እሱም “የበጉ ሠርግ” ነው፤ እንዲያውም ይህ ክንውን የራእይ መጽሐፍ ታላቅ መደምደሚያ ነው።—ራእይ 19:6-9

12. በራእይ 21:1, 2 መሠረት የበጉ ሠርግ የሚከናወነው መቼ ነው?

12 የበጉ ሠርግ የሚደረገው መቼ ነው? ሁሉም የ144,000ዎቹ አባላት ከአርማጌዶን ጦርነት በፊት በሰማይ ይሆናሉ። ሆኖም የበጉ ሠርግ የሚደረገው በዚህ ወቅት አይደለም። (ራእይ 21:1, 2ን አንብብ።) ሠርጉ የሚከናወነው የአርማጌዶን ጦርነት ከተካሄደና የአምላክ ጠላቶች በሙሉ ከጠፉ በኋላ ነው።—መዝ. 45:3, 4, 13-17

13. የበጉ ሠርግ፣ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ሁሉ ምን ትርጉም አለው?

13 የበጉ ሠርግ፣ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ሁሉ ምን ትርጉም አለው? አንድ ወንድና አንዲት ሴት በጋብቻ እንደሚጣመሩ ሁሉ በዚህ ምሳሌያዊ ጋብቻም ንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስና ‘ሙሽራው’ ማለትም 144,000ዎቹ ይጣመራሉ። ይህ ታላቅ ክንውን፣ ምድርን ለ1,000 ዓመታት የሚያስተዳድረው አዲስ መንግሥት ምሥረታ በዓል ነው።—ራእይ 20:6

ክብር የተላበሰችው ከተማ እና የአንተ የወደፊት ሕይወት

ራእይ ምዕራፍ 21 ላይ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም የተባለችው ምሳሌያዊት ከተማ “ከሰማይ ከአምላክ ዘንድ ስትወርድ” ታይታለች። በሺው ዓመት ግዛት ወቅት ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች የተትረፈረፈ በረከት ታፈስሳለች (ከአንቀጽ 14-16⁠ን ተመልከት)

14-15. ራእይ ምዕራፍ 21 ላይ 144,000ዎቹ ከምን ጋር ተመሳስለዋል? (ሽፋኑን ተመልከት።)

14 ራእይ ምዕራፍ 21 በመቀጠል 144,000ዎቹን “አዲሲቱ ኢየሩሳሌም” ተብላ ከምትጠራ እጅግ ውብ ከተማ ጋር ያመሳስላቸዋል። (ራእይ 21:2, 9) ይህች ከተማ “የ12ቱ የበጉ ሐዋርያት 12 ስሞች” የተጻፈባቸው 12 የመሠረት ድንጋዮች አሏት። ይህ ሐሳብ የዮሐንስን ትኩረት የሚስበው ለምንድን ነው? ምክንያቱም በመሠረት ድንጋዮቹ ላይ ከተጻፉት ስሞች አንዱ የእሱ ነው። ይህ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!—ራእይ 21:10-14፤ ኤፌ. 2:20

15 ይህች ምሳሌያዊት ከተማ ወደር የሌላት ከተማ ናት። የከተማዋ አውራ ጎዳና ንጹሕ ወርቅ ነው፤ ከዕንቁ የተሠሩ 12 በሮች አሏት፤ አጥሮቿና መሠረቶቿ በከበሩ ድንጋዮች ያጌጡ ናቸው፤ የከተማዋ ልኬትም ፍጹም የተመጣጠነ ነው። (ራእይ 21:15-21) አንድ የቀረ ነገር ያለ ግን ይመስላል። ዮሐንስ ቀጥሎ ምን እንዳለ ልብ በል፦ “በከተማዋ ውስጥ ቤተ መቅደስ አላየሁም፤ ሁሉን ቻይ የሆነው ይሖዋ አምላክና በጉ ቤተ መቅደሷ ናቸውና። ከተማዋ የፀሐይም ሆነ የጨረቃ ብርሃን አላስፈለጋትም፤ የአምላክ ክብር ብርሃን ሰጥቷታልና፤ በጉም መብራቷ ነበር።” (ራእይ 21:22, 23) የአዲሲቱ ኢየሩሳሌም አባላት ከይሖዋ ጋር በቀጥታ መገናኘት ይችላሉ። (ዕብ. 7:27፤ ራእይ 22:3, 4) ስለዚህ የዚህች ከተማ ቤተ መቅደስ ይሖዋና ኢየሱስ ናቸው።

‘በወንዝ’ እና ‘በዛፎች’ ከተመሰሉት በረከቶች የሚጠቀሙት እነማን ናቸው? (ከአንቀጽ 16-17⁠ን ተመልከት)

16. በሺው ዓመት የአምላክ መንግሥት ግዛት ወቅት የሰው ልጆች ምን ያገኛሉ?

16 ቅቡዓን ክርስቲያኖች ስለዚህች ከተማ ማሰብ በጣም እንደሚያስደስታቸው የታወቀ ነው። ይሁንና ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖችም ለዚህች ከተማ ትኩረት የሚሰጡበት ምክንያት አላቸው። የአምላክ መንግሥት ለአንድ ሺህ ዓመት በሚገዛበት ወቅት አዲሲቷ ኢየሩሳሌም በሰው ልጆች ላይ ብዙ በረከቶች ታፈስሳለች። ዮሐንስ ሲፈስ ያየው “የሕይወት ውኃ ወንዝ” እነዚህን በረከቶች የሚያመለክት ነው። በወንዙ ግራና ቀኝ ደግሞ “ሕዝቦችን ለመፈወስ የሚያገለግሉ” ቅጠሎች ያሏቸው “የሕይወት ዛፎች” አሉ። (ራእይ 22:1, 2) በዚያ ጊዜ የሚኖሩ የሰው ልጆች በሙሉ ከዚህ ዝግጅት ጥቅም ያገኛሉ። ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች በሙሉ ቀስ በቀስ ወደ ፍጽምና ደረጃ ይደርሳሉ። ሕመም፣ ሥቃይ ወይም የሐዘን እንባ አይኖርም።—ራእይ 21:3-5

17. ራእይ 20:11-13 እንደሚያሳየው በሺው ዓመት ግዛት ወቅት ከሚፈሰው በረከት እነማን ተጠቃሚ ይሆናሉ?

17 እነዚህን አስደናቂ በረከቶች የሚያገኙት እነማን ናቸው? የመጀመሪያ ተጠቃሚ የሚሆኑት ከአርማጌዶን በሕይወት የሚተርፉት እጅግ ብዙ ሕዝብና በአዲሱ ዓለም የሚወልዷቸው ልጆች ናቸው። ሆኖም ራእይ ምዕራፍ 20 ሙታን እንደሚነሱም ይናገራል። (ራእይ 20:11-13ን አንብብ።) በሞት ያንቀላፉ “ጻድቃንም ሆኑ ዓመፀኞች” ተነስተው በምድር ላይ ይኖራሉ፤ “ዓመፀኞች” የተባሉት ስለ ይሖዋ ለማወቅ በቂ አጋጣሚ ሳያገኙ የሞቱ ሰዎች ናቸው። (ሥራ 24:15፤ ዮሐ. 5:28, 29) ይህ ሲባል ታዲያ በሺው ዓመት ግዛት ወቅት ሁሉም ሰው ከሞት ይነሳል ማለት ነው? አይደለም። ይሖዋን ለማገልገል የሚያስችል አጋጣሚ አግኝተው ሆን ብለው ሳይጠቀሙበት የቀሩ ሰዎች ከሞት አይነሱም። እነዚህ ሰዎች በቂ አጋጣሚ አግኝተው ስላልተጠቀሙበት ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ሕይወት ለማግኘት ብቁ አይሆኑም።—ማቴ. 25:46፤ 2 ተሰ. 1:9፤ ራእይ 17:8፤ 20:15

የመጨረሻው ፈተና

18. በሺው ዓመት መጨረሻ በምድር ላይ ምን ዓይነት ሁኔታ ይኖራል?

18 በሺው ዓመት ማብቂያ ላይ በምድር ላይ የሚኖሩ ሁሉ ፍጹም ይሆናሉ። ከአዳም የወረስነው ኃጢአት ተጽዕኖ የሚያደርግበት ሰው አይኖርም። (ሮም 5:12) የአዳም ኃጢአት ያስከተለው እርግማን ሙሉ በሙሉ ይወገዳል። በሺው ዓመት መጨረሻ ላይ በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ፍጹማን ስለሚሆኑ ‘ሕያው ይሆናሉ’ ሊባል ይችላል።—ራእይ 20:5

19. የመጨረሻ ፈተና ያስፈለገው ለምንድን ነው?

19 ኢየሱስ ንጹሕ አቋሙን እንዲያጎድፍ ሰይጣን ላደረገው ጥረት እጅ እንዳልሰጠ እናውቃለን። የሰይጣንን ፈተና በታማኝነት ተወጥቷል። ሆኖም ሰይጣን እንዲፈትናቸው ዕድል ቢሰጠው ፍጹም የሆኑ የሰው ልጆች በሙሉ ታማኝ ይሆናሉ? በሺው ዓመት ማብቂያ ላይ ሰይጣን ከጥልቁ ሲፈታ እያንዳንዳችን ለዚህ የታማኝነት ጥያቄ መልስ ለመስጠት አጋጣሚ እናገኛለን። (ራእይ 20:7) ይህን የመጨረሻ ፈተና በታማኝነት የሚወጡ ሁሉ የዘላለም ሕይወትና እውነተኛ ነፃነት ያገኛሉ። (ሮም 8:21) በይሖዋ ላይ የሚያምፁ ሁሉ ከሰይጣንና ከአጋንንቱ ጋር ለዘላለም ይጠፋሉ።—ራእይ 20:8-10

20. በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ስለሚገኙት አስደናቂ ትንቢቶች ምን ይሰማሃል?

20 የራእይ መጽሐፍን በመቃኘት ያገኘናቸው ሐሳቦች ምን እንዲሰማህ አድርገዋል? በእነዚህ አስደናቂ ትንቢቶች ውስጥ አንተም እንዳለህበት ማወቅህ አስደስቶሃል? ታዲያ ሌሎችም በንጹሕ አምልኮ አብረውን እንዲካፈሉ ለመጋበዝ አልተነሳሳህም? (ራእይ 22:17) ወደፊት ስለሚፈጸሙት አስደናቂ ክንውኖች በመመርመር ልባችንና አእምሯችን ስለተነቃቃ እንደ ሐዋርያው ዮሐንስ ለማለት ተነሳስተናል፦ “አሜን! ጌታ ኢየሱስ፣ ና።”—ራእይ 22:20

መዝሙር 27 የአምላክ ልጆች መገለጥ

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ የራእይ መጽሐፍን ከቃኘንባቸው ተከታታይ ርዕሶች ይህ የመጨረሻው ነው። በዚህ ርዕስ ላይ እንደምንመለከተው ለይሖዋ እስከ መጨረሻው ታማኝ የሚሆኑ ሁሉ አስደናቂ ሕይወት ተዘጋጅቶላቸዋል። የአምላክን አገዛዝ የሚቃወሙ ግን አሳፋሪ ውድቀት ይደርስባቸዋል።