በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 24

መንፈሳዊ ግቦቻችሁ ላይ መድረስ ትችላላችሁ

መንፈሳዊ ግቦቻችሁ ላይ መድረስ ትችላላችሁ

“ካልታከትን ጊዜው ሲደርስ ስለምናጭድ ተስፋ ቆርጠን መልካም ሥራ መሥራታችንን አንተው።”—ገላ. 6:9

መዝሙር 84 እገዛ የሚያስፈልጋቸውን መርዳት

ማስተዋወቂያ a

1. ብዙዎቻችን ምን ማድረግ ያታግለናል?

 መንፈሳዊ ግብ ካወጣህ በኋላ ግብህ ላይ መድረስ አታግሎህ ያውቃል? b ከሆነ፣ እንዲህ ያለ ሁኔታ ያጋጠመህ አንተ ብቻ አይደለህም። ለምሳሌ ፊሊፕ ይበልጥ አዘውትሮ ለመጸለይና የጸሎቱን ይዘት ለማሻሻል ፈልጎ ነበር፤ ሆኖም ለጸሎት የሚሆን ጊዜ ማግኘት ተቸግሯል። ኤሪካ በስምሪት ስብሰባዎች ላይ በሰዓቱ ለመገኘት ግብ አውጥታ ነበር፤ ሆኖም በሰዓቱ መድረስ ሊሳካላት አልቻለም። ቶማስ መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር ለማንበብ በተደጋጋሚ ሞክሮ ነበር። ሆኖም እንዲህ ብሏል፦ “የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቤን ልወደው አልቻልኩም። ሦስት ጊዜ ሞክሬዋለሁ፤ ሦስቱም ጊዜ ግን ዘሌዋውያን ላይ ስደርስ አቆምኩ።”

2. መንፈሳዊ ግባችን ላይ መድረስ ካቃተን ተስፋ ልንቆርጥ የማይገባው ለምንድን ነው?

2 አንድ መንፈሳዊ ግብ ላይ ለመድረስ ከተቸገርክ ተስፋ ልትቆርጥ አይገባም። ቀላል ግብ ላይ መድረስ እንኳ ጊዜና ጥረት ይጠይቃል። አሁንም ግብህ ላይ ለመድረስ መፈለግህ በራሱ ከይሖዋ ጋር ያለህን ዝምድና ከፍ አድርገህ እንደምትመለከተውና ለእሱ ምርጥህን መስጠት እንደምትፈልግ ያሳያል። ይሖዋ ጥረትህን በእጅጉ ያደንቃል። ደግሞም ከአቅምህ በላይ እንድትሰጠው አይጠብቅብህም። (መዝ. 103:14፤ ሚክ. 6:8) ስለዚህ ግብህ ምክንያታዊና ሁኔታህን ያገናዘበ ሊሆን ይገባል። ታዲያ እንዲህ ያለ ግብ ካወጣህ በኋላ እዚያ ላይ ለመድረስ ምን ማድረግ ትችላለህ? አንዳንድ ምክሮችን እስቲ እንመልከት።

ተነሳሽነት ወሳኝ ነው

ተነሳሽነትህ እንዲጨምር ጸልይ (ከአንቀጽ 3-4⁠ን ተመልከት)

3. ተነሳሽነት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

3 መንፈሳዊ ግቦች ላይ ለመድረስ ተነሳሽነት ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ተነሳሽነት ያለው ሰው ግቡ ላይ ለመድረስ ልባዊ ፍላጎት ስላለው ጠንክሮ ይሠራል። ተነሳሽነት፣ አንድን ጀልባ ወደ ወደቡ እንዲደርስ ከሚገፋ ነፋስ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ነፋሱ መንፈሱን ከቀጠለ መርከበኛው ወደቡ ጋ መድረሱ አይቀርም። ነፋሱ ኃይለኛ ከሆነ ደግሞ ይበልጥ በፍጥነት ሊደርስ ይችላል። በተመሳሳይም ተነሳሽነታችን በጣም ከፍተኛ ከሆነ ግቦቻችን ላይ የመድረሳችን አጋጣሚ ከፍተኛ ይሆናል። በኤል ሳልቫዶር የሚኖር ዴቪድ የተባለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ተነሳሽነት ካላችሁ ተግታችሁ ትሠራላችሁ። ምንም ነገር ግባችሁ ላይ ከመድረስ እንዲያግዳችሁ አትፈቅዱም።” ታዲያ ተነሳሽነትህን ማሳደግ የምትችለው እንዴት ነው?

4. ምን ብለን መጸለይ እንችላለን? (ፊልጵስዩስ 2:13) (ሥዕሉንም ተመልከት።)

4 ተነሳሽነትህ እንዲጨምር ጸልይ። ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት ግብህ ላይ እንድትደርስ ሊያነሳሳህ ይችላል። (ፊልጵስዩስ 2:13ን አንብብ።) አንዳንድ ጊዜ ግብ የምናወጣው ያንን ግብ ማውጣት እንዳለብን ስለሚሰማን ነው፤ ይህ በራሱ ጥሩ ነገር ነው። ሆኖም ግቡ ላይ ለመድረስ ያን ያህል ፍላጎት ላይኖረን ይችላል። በኡጋንዳ የምትኖረው ኖሪና ያጋጠማት ይኸው ነው። ኖሪና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የማግኘት ግብ አውጥታ ነበር፤ ሆኖም ጥሩ አስተማሪ እንደሆነች ስላልተሰማት እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ተነሳሽነት አልነበራትም። ታዲያ የረዳት ምንድን ነው? እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የማግኘት ፍላጎቴን እንዲያሳድግልኝ በየቀኑ በጸሎት እጠይቀው ነበር። የማስተማር ችሎታዬን ለማሻሻል ጥረት በማድረግ ከጸሎቴ ጋር የሚስማማ እርምጃ ወሰድኩ። ከጥቂት ወራት በኋላ፣ ጥናት የማግኘት ፍላጎቴ እንዳደገ አስተዋልኩ። በዚያው ዓመት ሁለት ጥናቶች አገኘሁ።”

5. ተነሳሽነታችንን ለመጨመር በምን ነገር ላይ ማሰላሰል እንችላለን?

5 ይሖዋ ባደረገልህ ነገር ላይ አሰላስል። (መዝ. 143:5) ሐዋርያው ጳውሎስ ይሖዋ ባሳየው ጸጋ ላይ አሰላስሏል፤ ይህም ይሖዋን በትጋት ለማገልገል አነሳስቶታል። (1 ቆሮ. 15:9, 10፤ 1 ጢሞ. 1:12-14) አንተም ይሖዋ ባደረገልህ ነገር ላይ ይበልጥ ባሰላሰልክ መጠን ግብህ ላይ ለመድረስ ያለህ ተነሳሽነት ይበልጥ ይጨምራል። (መዝ. 116:12) በሆንዱራስ የምትኖር አንዲት እህት በዘወትር አቅኚነት የማገልገል ግቧ ላይ እንድትደርስ ምን እንደረዳት እስቲ እንመልከት። እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ ለእኔ ባለው ጥልቅ ፍቅር ላይ አሰላሰልኩ። ወደ ሕዝቦቹ አምጥቶኛል። ይንከባከበኛል፤ እንዲሁም ጥበቃ ያደርግልኛል። እንዲህ ባሉ ነገሮች ላይ ማሰላሰሌ ለይሖዋ ያለኝ ፍቅር እንዲያድግ የረዳኝ ከመሆኑም ሌላ አቅኚ ለመሆን ያለኝን ተነሳሽነት ጨምሮታል።”

6. ተነሳሽነታችንን ለማሳደግ ሌላስ ምን ሊረዳን ይችላል?

6 ግብህ ላይ መድረስህ በሚያስገኛቸው በረከቶች ላይ አተኩር። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ኤሪካ ሰዓት አክባሪ ለመሆን ያወጣችው ግብ ላይ ለመድረስ ምን እንደረዳት እንመልከት። እንዲህ ብላለች፦ “ስምሪት አርፍጄ መድረሴ ብዙ ነገር እንደሚያሳጣኝ ተገነዘብኩ። ቀደም ብዬ ብደርስ ወንድሞችንና እህቶችን ሰላም ማለትና ከእነሱ ጋር ጊዜ ማሳለፍ እችላለሁ። አገልግሎቴን ለማሻሻልና ከአገልግሎቴ ደስታ ለማግኘት የሚረዱ ጠቃሚ ምክሮችንም እሰማለሁ።” ኤሪካ ሰዓት አክባሪ መሆን ባሉት ጥቅሞች ላይ በማተኮሯ ግቧ ላይ መድረስ ችላለች። አንተስ በየትኞቹ በረከቶች ላይ ማተኮር ትችላለህ? ያወጣኸው ግብ ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ወይም ከጸሎት ጋር የተያያዘ ከሆነ ግብህ ላይ መድረስህ ከይሖዋ ጋር ያለህን ዝምድና የሚያጠናክርልህ እንዴት እንደሆነ አስብ። (መዝ. 145:18, 19) ግብህ አንድን ክርስቲያናዊ ባሕርይ ማዳበር ከሆነ ደግሞ ይህ ባሕርይ ከሌሎች ጋር ያለህን ዝምድና የሚያሻሽለው እንዴት እንደሆነ ለማሰብ ሞክር። (ቆላ. 3:14) ግብህ ላይ ለመድረስ የሚያነሳሱህን ምክንያቶች በሙሉ ዘርዝረህ ለምን አትጽፍም? ከዚያም አልፎ አልፎ ዝርዝሩን ተመልከት። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ቶማስ እንዲህ ብሏል፦ “አንድ ግብ ላይ ለመድረስ የሚያነሳሱ ብዙ ምክንያቶች ካሉኝ ግቤ ላይ ለመድረስ ይበልጥ ጥረት አደርጋለሁ።”

7. ሁልዮ እና ባለቤቱ ግባቸው ላይ ለመድረስ የረዳቸው ምንድን ነው?

7 ግብህ ላይ እንድትደርስ ከሚያበረታቱህ ሰዎች ጋር ጊዜ አሳልፍ። (ምሳሌ 13:20) ሁልዮ እና ባለቤቱ አገልግሎታቸውን ለማስፋት ባወጡት ግብ ላይ ለመድረስ ምን እንደረዳቸው እስቲ እንመልከት። ሁልዮ እንዲህ ብሏል፦ “ግባችን ላይ እንድንደርስ የሚያበረታቱን ጓደኞች መረጥን። ስለ ግባችንም ከእነሱ ጋር እንነጋገር ነበር። ብዙዎቹ ተመሳሳይ ግቦች ላይ መድረስ ስለቻሉ ጠቃሚ ምክር ሰጥተውናል። በተጨማሪም ጓደኞቻችን ዕቅዳችን እንዴት እየሄደ እንደሆነ ይጠይቁናል፤ እንዲሁም የሚያስፈልገንን ማበረታቻ ይሰጡናል።”

ተነሳሽነት ስናጣ

ግብህ ላይ ለመድረስ ጥረት አድርግ (አንቀጽ 8⁠ን ተመልከት)

8. ግባችን ላይ ለመድረስ የምንሠራው ተነሳሽነት ሲኖረን ብቻ ከሆነ ውጤቱ ምን ሊሆን ይችላል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

8 እውነቱን እንነጋገር ከተባለ፣ ሁላችንም ተነሳሽነት የምናጣበት ጊዜ ይኖራል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመን ግባችን ላይ ለመድረስ ጥረት ማድረጋችንን እናቆማለን ማለት ነው? በፍጹም። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት፣ ኃይለኛ ነፋስ ካለ አንድ ጀልባ በቀላሉ ወደቡ ጋ መድረስ ይችላል። ይሁንና የነፋሱ ኃይል ሊቀያየር ይችላል። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ምንም ነፋስ ላይኖር ይችላል። ታዲያ ይህ ማለት መርከበኛው ወደፊት መጓዝ አይችልም ማለት ነው? እንደዚያ ማለት አይደለም። ለምሳሌ አንዳንድ ጀልባዎች ሞተር፣ ሌሎች ደግሞ መቅዘፊያ አላቸው። መርከበኛው እነዚህን ነገሮች ተጠቅሞ ወደቡ ጋ መድረስ ይችላል። የእኛም ተነሳሽነት እንደ ነፋሱ መጠኑ ሊቀያየር ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ግባችን ላይ ለመሥራት ያለን ተነሳሽነት ጨርሶ ሊጠፋ ይችላል። ግባችን ላይ ለመድረስ ጥረት የምናደርገው ተነሳሽነት ሲኖረን ብቻ ከሆነ ግባችን ላይ ላንደርስ እንችላለን። ሆኖም መርከበኛው ወደቡ ላይ ለመድረስ ሌሎች መንገዶችን እንደሚፈልግ ሁሉ እኛም ተነሳሽነት ባይኖረንም እንኳ ግባችን ላይ ለመድረስ ጥረት ማድረግ እንችላለን። እንዲህ ማድረግ ራስን መገሠጽ ቢጠይቅም ውጤቱ የሚክስ ይሆናል። ተነሳሽነት ስናጣ ምን ማድረግ እንዳለብን ከመነጋገራችን በፊት አንድ ጥያቄ ለመመለስ እንሞክር።

9. አንድ ግብ ላይ ለመድረስ ተነሳሽነት ባይኖረንም እንኳ እዚያ ግብ ላይ ለመድረስ ጥረት ማድረጋችን ስህተት ነው? አብራራ።

9 ይሖዋ በደስታና በፈቃደኝነት እንድናገለግለው ይፈልጋል። (መዝ. 100:2፤ 2 ቆሮ. 9:7) ታዲያ አንድ መንፈሳዊ ግብ ላይ ለመድረስ ተነሳሽነቱ ከሌለን ጥረት ማድረጋችንን መቀጠላችን ተገቢ ነው? ሐዋርያው ጳውሎስን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ጳውሎስ “ሰውነቴን አጥብቄ እየገሠጽኩ እንደ ባሪያ እንዲገዛልኝ አደርገዋለሁ” ብሏል። (1 ቆሮ. 9:25-27 ግርጌ) ጳውሎስ ይሖዋ የሚጠብቅበትን ነገር ለማድረግ ተነሳሽነት ባይኖረውም እንኳ ራሱን አስገድዶ ትክክለኛውን ነገር አድርጓል። ታዲያ ይሖዋ ጳውሎስ ባደረገው ነገር ተደስቷል? በሚገባ! በተጨማሪም ላደረገው ጥረት ይሖዋ ባርኮታል።—2 ጢሞ. 4:7, 8

10. ተነሳሽነት ባይኖረንም እንኳ አንድ ግብ ላይ ለመድረስ ጥረት ማድረጋችን ምን ጥቅም ይኖረዋል?

10 እኛም ተነሳሽነት ባይኖረንም እንኳ አንድ ግብ ላይ ለመድረስ ጥረት ስናደርግ ይሖዋ ይደሰታል። አንድ ግብ ላይ ለመድረስ የምንጣጣረው ለዚያ ነገር ባለን ፍቅር ተነሳስተን ባይሆንም እንኳ ለእሱ ባለን ፍቅር ተነሳስተን እንደሆነ ስለሚያውቅ ይደሰትብናል። ይሖዋ ጳውሎስን እንደባረከው ሁሉ እኛም ጥረት በማድረጋችን ይባርከናል። (መዝ. 126:5) የይሖዋን በረከት ስናጣጥም ደግሞ ተነሳሽነታችን እየጨመረ ሊሄድ ይችላል። በፖላንድ የምትኖር ሉሲና የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “አንዳንድ ጊዜ፣ በተለይ ሲደክመኝ አገልግሎት ለመውጣት ፍላጎት አይኖረኝም። ያም ቢሆን አገልግሎት ከወጣሁ በኋላ የሚሰማኝ ደስታ በእጅጉ የሚክስ ነው።” እንግዲያው ተነሳሽነት ስናጣ ምን ማድረግ እንደምንችል እንመልከት።

11. ይሖዋ ራሳችንን መግዛት እንድንችል የሚረዳን እንዴት ነው?

11 ራስህን መግዛት እንድትችል ጸልይ። ራስን መግዛት፣ ስሜትንና ድርጊትን የመቆጣጠር ችሎታ ነው። አብዛኛውን ጊዜ፣ ራስን መግዛት መጥፎ ነገር ከማድረግ መታቀብን ያመለክታል። ይሁንና ጥሩ ነገር ለማድረግም ራስን መግዛት ያስፈልገናል። በተለይ ያ ነገር ከባድ ከሆነ ወይም ተነሳሽነት ካጣን ራሳችንን መግዛታችን አስፈላጊ ነው። ራስን መግዛት የአምላክ መንፈስ ፍሬ ገጽታ እንደሆነ አትዘንጋ። በመሆኑም ይህን አስፈላጊ ባሕርይ ማዳበር እንድትችል መንፈስ ቅዱስን እንዲሰጥህ ይሖዋን ጠይቀው። (ሉቃስ 11:13፤ ገላ. 5:22, 23) ቀደም ሲል የተጠቀሰው ዴቪድ ጸሎት የረዳው እንዴት እንደሆነ ተናግሯል። የግል ጥናቱን ቋሚ ማድረግ ፈልጎ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ ራሴን መግዛት እንድችል እንዲረዳኝ ጸለይኩ። በእሱ እርዳታ ጥሩ የጥናት ፕሮግራም ማውጣትና የግል ጥናቴን ቋሚ ማድረግ ችያለሁ።”

12. በመክብብ 11:4 ላይ የሚገኘው መሠረታዊ ሥርዓት ከመንፈሳዊ ግቦች ጋር በተያያዘ የሚሠራው እንዴት ነው?

12 ሁኔታዎች ሙሉ በሙሉ እስኪስተካከሉ አትጠብቅ። በዚህ ዓለም ውስጥ ሁሉ ነገር ሊስተካከልልን እንደማይችል የታወቀ ነው። ሁሉ ነገር እስኪስተካከል ከጠበቅን ግባችን ላይ ፈጽሞ ላንደርስ እንችላለን። (መክብብ 11:4ን አንብብ።) ዴንዬል የተባለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ሁሉም ነገር ሊስተካከል አይችልም። ማድረግ የምንችለው ከሁሉ የተሻለ ነገር ዝም ብሎ መጀመር ነው።” በኡጋንዳ የሚኖር ፖል የተባለ ወንድም ዛሬ ነገ እንዳንል የሚያነሳሳንን ሌላ ምክንያት ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ተፈታታኝ ሁኔታዎች እያሉም ጥረት ማድረግ ስንጀምር ይሖዋ እንዲባርከን አጋጣሚ እንሰጠዋለን።”—ሚል. 3:10

13. ከትናንሽ ግቦች መጀመር ምን ጥቅም አለው?

13 በትንሹ ጀምር። ግባችን ላይ መድረስ በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ ከተሰማን ተነሳሽነታችን ሊጠፋ ይችላል። የአንተም ሁኔታ እንደዚያ ከሆነ ግብህን በትንሽ በትንሹ ልትከፋፍለው ትችል ይሆን? ለምሳሌ ግብህ አንድ ክርስቲያናዊ ባሕርይ ማዳበር ከሆነ መጀመሪያ ላይ ይህን ባሕርይ በትናንሽ መንገዶች ለማንጸባረቅ ለምን አትሞክርም? ግብህ መጽሐፍ ቅዱስን አንብቦ መጨረስ ከሆነ ደግሞ ለጥቂት ደቂቃዎች ብቻ በማንበብ ለምን አትጀምርም? በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ቶማስ መጽሐፍ ቅዱስን በአንድ ዓመት አንብቦ ለመጨረስ ተቸግሮ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “በዚህ ፍጥነት ማንበብ እንደማልችል ተገነዘብኩ። ስለዚህ ሌላ ሙከራ አደረግኩ። በዚህ ጊዜ ግን በየቀኑ ጥቂት አንቀጾችን አንብቤ ለማሰላሰል ግብ አወጣሁ። በመሆኑም ንባቤ አስደሳች እየሆነልኝ መጣ።” ቶማስ ከንባቡ የሚያገኘው ደስታ እየጨመረ ሲመጣ ረዘም ላለ ጊዜ ማንበብ ጀመረ። ውሎ አድሮ መጽሐፍ ቅዱስን አንብቦ መጨረስ ቻለ። c

እንቅፋት ቢያጋጥምህ ተስፋ አትቁረጥ

14. ምን ዓይነት እንቅፋቶች ሊያጋጥሙን ይችላሉ?

14 የሚያሳዝነው፣ ምንም ያህል ተነሳሽነትም ሆነ ራስን የመግዛት ችሎታ ቢኖረን እንቅፋት ሊያጋጥመን ይችላል። ለምሳሌ “ያልተጠበቁ ክስተቶች” ግባችን ላይ ለመሥራት የመደብነውን ጊዜ ሊሻሙብን ይችላሉ። (መክ. 9:11) ተስፋ የሚያስቆርጥና ጉልበታችንን የሚያዳክም ፈተና ሊያጋጥመን ይችላል። (ምሳሌ 24:10) ፍጹም ያልሆነው ሥጋችን ከግባችን ጋር የሚቃረን ድርጊት እንድንፈጽም ሊያደርገን ይችላል። (ሮም 7:23) ወይም ደግሞ ሊደክመን ይችላል። (ማቴ. 26:43) ታዲያ የሚያጋጥመንን እንቅፋት ወይም ያልተጠበቀ ሁኔታ ለመወጣት ምን ይረዳናል?

15. እንቅፋት ካጋጠመን ግባችን ላይ መድረስ አንችልም ማለት ነው? አብራራ። (መዝሙር 145:14)

15 እንቅፋት አጋጥሞሃል ማለት ግብህ ላይ መድረስ አትችልም ማለት እንዳልሆነ አስታውስ። መጽሐፍ ቅዱስ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በተደጋጋሚ ሊያጋጥሙን እንደሚችሉ ይናገራል። ያም ቢሆን በይሖዋ እርዳታ መልሰን መነሳት እንደምንችል በግልጽ ይናገራል። (መዝሙር 145:14ን አንብብ።) ቀደም ሲል የተጠቀሰው ፊሊፕ ስኬትን የሚለካው እንዴት እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ስኬታማ መሆን አለመሆኔ የተመካው ምን ያህል ጊዜ ወድቄያለሁ በሚለው ላይ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ስኬታማነቴ የተመካው ምን ያህል ጊዜ ተነስቼ ወደፊት መጓዜን ቀጥያለሁ በሚለው ላይ ነው።” ቀደም ሲል የተጠቀሰው ዴቪድ እንዲህ ብሏል፦ “እንቅፋቶችንና ያልተጠበቁ ሁኔታዎችን የምመለከታቸው ግቤ ላይ ከመድረስ እንደሚያግዱኝ ነገሮች አድርጌ ሳይሆን ለይሖዋ ያለኝን ፍቅር ለማሳየት እንደሚያስችሉ አጋጣሚዎች አድርጌ ነው።” በእርግጥም፣ እንቅፋት ቢያጋጥምህም እንኳ ግብህ ላይ መሥራትህን መቀጠልህ ይሖዋን ማስደሰት እንደምትፈልግ ያሳያል። ይሖዋ ግብህ ላይ ለመድረስ ጥረት ማድረግህን እንደቀጠልክ ሲመለከት ምንኛ ይደሰት ይሆን!

16. ካጋጠመን እንቅፋት ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን?

16 ካጋጠመህ እንቅፋት ትምህርት ውሰድ። እንቅፋቱ ያጋጠመህ ለምን እንደሆነ አስብ፤ ከዚያም ‘ለቀጣዩ ጊዜ እንዲህ ዓይነት እንቅፋት እንዳያጋጥመኝ ምን ማድረግ እችላለሁ?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። (ምሳሌ 27:12) እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ጊዜ እንቅፋቶች ያወጣነው ግብ ምክንያታዊ እንዳልነበረ ሊያሳዩ ይችላሉ። እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞህ ከሆነ ግብህን መለስ ብለህ በማጤን አሁን ካለህበት ሁኔታ አንጻር እዚህ ግብ ላይ መድረስ ትችል እንደሆነና እንዳልሆነ ገምግም። d ከአቅምህ በላይ የሆነ ግብ ላይ መድረስ ስላቃተህ ይሖዋ አያዝንብህም።—2 ቆሮ. 8:12

17. እስካሁን የደረስንባቸውን ግቦች ማስታወስ ያለብን ለምንድን ነው?

17 እስካሁን የደረስክባቸውን ግቦች አስታውስ። መጽሐፍ ቅዱስ ‘አምላክ ሥራችሁን በመርሳት ፍትሕ አያዛባም’ ይላል። (ዕብ. 6:10) አንተም ብትሆን ልትረሳ አይገባም። ከዚህ ቀደም ስላከናወንካቸው ነገሮች አስብ። ለምሳሌ ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት መሥርተሃል፤ ለሌሎች ስለ እሱ መናገር ጀምረሃል፤ እንዲሁም ተጠምቀሃል። እስካሁን ድረስ እድገት ማድረግና የተለያዩ መንፈሳዊ ግቦች ላይ መድረስ እንደቻልክ ሁሉ አሁንም እድገት ማድረግህን መቀጠልና ያወጣኸው ግብ ላይ መድረስ ትችላለህ።—ፊልጵ. 3:16

በጉዞው ተደሰት (አንቀጽ 18⁠ን ተመልከት)

18. ግባችን ላይ ለመድረስ ጥረት ስናደርግ ምን ማድረግ ይኖርብናል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

18 አንድ መርከበኛ ወደቡ ላይ እንደሚደርስ ሁሉ አንተም በይሖዋ እርዳታ ግብህ ላይ መድረስ ትችላለህ። ይሁንና ብዙዎቹ መርከበኞች የሚያስደስታቸው ወደቡ ላይ መድረሳቸው ብቻ አይደለም፤ ጉዞውንም ይወዱታል። አንተም በተመሳሳይ መንፈሳዊ ግብህ ላይ ለመድረስ ጥረት ስታደርግ እግረ መንገድህን የይሖዋን በረከትና እርዳታ በማስተዋል ደስታ ማግኘት ትችላለህ። (2 ቆሮ. 4:7) ተስፋ ካልቆረጥክ ተጨማሪ በረከቶችንም ታገኛለህ።—ገላ. 6:9

መዝሙር 126 ነቅተህ ኑር፣ ጸንተህ ቁም፣ በርታ

a መንፈሳዊ ግብ እንድናወጣ ሁልጊዜ እንበረታታለን። ሆኖም ጠቃሚ ግብ ብናወጣም እንኳ ግባችን ላይ መድረስ ከባድ ቢሆንብንስ? ይህ ርዕስ፣ ግቦቻችን ላይ ለመድረስ የሚረዱ ጠቃሚ ምክሮች ይሰጠናል።

b ተጨማሪ ማብራሪያ፦ መንፈሳዊ ግብ የሚባለው ይሖዋን ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ ለማገልገልና እሱን ለማስደሰት ስንል ለማሻሻል ወይም ለማሳካት የምንጣጣረው ማንኛውም ነገር ነው። ለምሳሌ አንድን ክርስቲያናዊ ባሕርይ ለማዳበር ወይም እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፣ የግል ጥናት ወይም የመስክ አገልግሎት ካሉ የአምልኳችን ገጽታዎች ጋር በተያያዘ ማሻሻያ ለማድረግ ግብ ልናወጣ እንችላለን።

c በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም ገጽ 10-11 አን. 4⁠ን ተመልከት።

d ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በሐምሌ 15, 2008 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ከራሳችን በምንጠብቀው ነገር ምክንያታዊ በመሆን ደስታ ማግኘት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።