በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 22

‘በቅድስና ጎዳና’ ላይ መጓዛችሁን ቀጥሉ

‘በቅድስና ጎዳና’ ላይ መጓዛችሁን ቀጥሉ

“በዚያም አውራ ጎዳና ይኖራል፤ ደግሞም ‘የቅድስና ጎዳና’ ተብሎ ይጠራል።”—ኢሳ. 35:8

መዝሙር 31 ከአምላክ ጋር ሂድ!

ማስተዋወቂያ a

1-2. በባቢሎን ይኖሩ የነበሩት አይሁዳውያን የትኛውን አስፈላጊ ውሳኔ ማድረግ ነበረባቸው? (ዕዝራ 1:2-4)

 አዋጁ ወጥቷል! ለ70 ዓመት ገደማ በባቢሎን ግዞተኞች ሆነው የኖሩት አይሁዳውያን ወደ አገራቸው ወደ እስራኤል እንዲመለሱ ተፈቅዶላቸዋል። (ዕዝራ 1:2-4ን አንብብ።) ይህ ሊሆን የቻለው ይሖዋ ስለረዳቸው ብቻ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ባቢሎናውያን ግዞተኞቻቸውን የመልቀቅ ልማድ አልነበራቸውም። (ኢሳ. 14:4, 17) አሁን ግን ባቢሎን ወድቃለች። አዲሱ ገዢም አይሁዳውያን ባቢሎንን ለቀው መውጣት እንደሚችሉ ነገራቸው። በመሆኑም በእያንዳንዱ አይሁዳዊ በተለይም በቤተሰብ ራሶች ፊት አንድ አስፈላጊ ውሳኔ ተደቅኗል፤ ባቢሎንን ለቀው ለመውጣት ወይም እዚያው ለመቅረት መወሰን ነበረባቸው። ይሁንና እንዲህ ያለውን ውሳኔ ማድረግ ቀላል አልነበረም። ለምን?

2 ብዙዎቹ በዕድሜ የገፉ ስለነበሩ ያንን አስቸጋሪ ጉዞ ማድረግ ይከብዳቸዋል። በተጨማሪም አብዛኞቹ አይሁዳውያን የተወለዱት በባቢሎን ስለነበር ‘ቤቴ’ የሚሉት ባቢሎንን ነው። በእነሱ ዓይን እስራኤል የአያቶቻቸው እንጂ የእነሱ አገር አይደለም። አንዳንድ አይሁዳውያን በባቢሎን የተደላደለ ሕይወት መሥርተው የነበረ ይመስላል። በመሆኑም የሞቀ ቤታቸውንና ንግዳቸውን ትተው ወደማያውቁት አገር መሄድ ከብዷቸው ሊሆን ይችላል።

3. ወደ እስራኤል የሚመለሱት ታማኝ አይሁዳውያን ምን በረከት ይጠብቃቸዋል?

3 በታማኞቹ አይሁዳውያን ዓይን ወደ እስራኤል መመለስ የሚያስገኘው ጥቅም ከሚከፍሉት ከማንኛውም መሥዋዕት እጅግ የላቀ ነው። የሚያገኙት ትልቁ በረከት ከአምልኳቸው ጋር የተያያዘ ነው። በባቢሎን ከ50 የሚበልጡ አረማዊ ቤተ መቅደሶች ቢኖሩም በዚያ ከተማ ውስጥ የይሖዋ መቅደስ አልነበረም። እስራኤላውያን በሙሴ ሕግ መሠረት የሚጠበቅባቸውን መሥዋዕት ማቅረብ የሚችሉበት መሠዊያ አልነበረም፤ እንዲሁም እነዚህን መሥዋዕቶች የሚያቀርብ የተደራጀ የክህነት ሥርዓት አልነበረም። በተጨማሪም በዚያ የነበሩት ጣዖት አምላኪዎች ቁጥር ከይሖዋ ሕዝቦች ቁጥር በእጅጉ ይበልጣል፤ እነዚህ ሰዎች ደግሞ ለይሖዋም ሆነ ለመሥፈርቶቹ አክብሮት አልነበራቸውም። በመሆኑም ፈሪሃ አምላክ የነበራቸው በሺዎች የሚቆጠሩ አይሁዳውያን ወደ አገራቸው ተመልሰው ንጹሕ አምልኮን መልሰው ለማቋቋም ጓጉተው ነበር።

4. ይሖዋ ወደ እስራኤል ለሚመለሱት አይሁዳውያን ምን ዓይነት እርዳታ እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቷል?

4 ከባቢሎን ወደ እስራኤል የሚወስደው መንገድ አስቸጋሪ ከመሆኑም ሌላ አራት ወር ገደማ ይወስዳል። ሆኖም ይሖዋ ወደዚያ እንዳይመለሱ ሊያግዳቸው የሚችለውን ማንኛውንም እንቅፋት እንደሚያስወግድላቸው ቃል ገብቶላቸዋል። ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የይሖዋን መንገድ ጥረጉ! በበረሃ ለአምላካችን አውራ ጎዳናውን አቅኑ። . . . ወጣ ገባውም መሬት ይስተካከል፤ ጎርበጥባጣውም ምድር ሸለቋማ ሜዳ ይሁን።” (ኢሳ. 40:3, 4) በበረሃ መሃል የሚያልፍን አንድ አውራ ጎዳና በዓይነ ሕሊናህ ለመሣል ሞክር፤ በተራሮች መካከል የሚያልፍ ለጥ ያለ መንገድ ነው። መቼም እንዲህ ያለው መንገድ ለተጓዦች በጣም አመቺ ነው። ተራራ እየወጡ፣ ሸለቆ እየወረዱ ከመጓዝ እንዲህ ባለው ቀጥ ያለ አውራ ጎዳና ላይ መጓዝ በጣም ይቀልላል። የሚወስደው ጊዜም በእጅጉ ያጥራል።

5. ከባቢሎን ወደ እስራኤል የሚወስደው ምሳሌያዊ አውራ ጎዳና ምን የሚል ስም ተሰጥቶታል?

5 በዛሬው ጊዜ ያሉ በርካታ አውራ ጎዳናዎች መጠሪያ ስም ወይም መለያ ቁጥር አላቸው። ኢሳይያስ የጠቀሰው ምሳሌያዊ አውራ ጎዳናም ስም አለው። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “በዚያም አውራ ጎዳና ይኖራል፤ ደግሞም ‘የቅድስና ጎዳና’ ተብሎ ይጠራል። ንጹሕ ያልሆነ ሰው አይጓዝበትም።” (ኢሳ. 35:8) ይህ ሐሳብ በዚያ ዘመን ለነበሩት እስራኤላውያን ምን ትርጉም ነበረው? ለእኛስ ምን ትርጉም አለው?

“የቅድስና ጎዳና”—ጥንትና ዛሬ

6. መንገዱ “የቅድስና ጎዳና” ተብሎ የተጠራው ለምንድን ነው?

6 “የቅድስና ጎዳና”—እንዴት ያለ ግሩም ስም ነው! ይሁንና መንገዱ “የቅድስና ጎዳና” ተብሎ የተጠራው ለምንድን ነው? መልሶ በተቋቋመው የእስራኤል ብሔር ውስጥ ንጹሕ ላልሆነ ሰው ቦታ አይኖርም፤ የፆታ ብልግና፣ ጣዖት አምልኮ ወይም ሌላ ከባድ ኃጢአት የሚፈጽም ማንኛውም አይሁዳዊ በዚያ መኖር አይፈቀድለትም። ወደ አገራቸው የተመለሱት አይሁዳውያን ለአምላካቸው “ቅዱስ ሕዝብ” መሆን ነበረባቸው። (ዘዳ. 7:6) ይህ ሲባል ግን፣ ባቢሎንን ለቀው የወጡት አይሁዳውያን ይሖዋን ለማስደሰት ምንም ዓይነት ማስተካከያ ማድረግ አይጠበቅባቸውም ማለት አይደለም።

7. አንዳንድ አይሁዳውያን ምን ዓይነት ለውጥ ማድረግ ያስፈልጋቸው ነበር? ምሳሌ ስጥ።

7 ቀደም ሲል እንደተመለከትነው፣ አብዛኞቹ አይሁዳውያን የተወለዱት በባቢሎን ስለሆነ ብዙዎቹ ከባቢሎናውያን አስተሳሰብና መሥፈርቶች ጋር ተላምደው ሊሆን ይችላል። የመጀመሪያዎቹ አይሁዳውያን ወደ እስራኤል ከተመለሱ ከአሥርተ ዓመታት በኋላ ዕዝራ አንዳንዶቹ አይሁዳውያን ከጣዖት አምላኪ ሴቶች ጋር ትዳር እንደመሠረቱ ተገነዘበ። (ዘፀ. 34:15, 16፤ ዕዝራ 9:1, 2) ከዓመታት በኋላም ገዢው ነህምያ፣ እስራኤል ውስጥ የተወለዱ አንዳንድ ልጆች የአይሁዳውያንን ቋንቋ እንኳ እንደማይችሉ ሲገነዘብ በጣም ደንግጦ ነበር። (ዘዳ. 6:6, 7፤ ነህ. 13:23, 24) የአምላክ ቃል በዋነኝነት የተጻፈው በዕብራይስጥ ከመሆኑ አንጻር እነዚህ ልጆች ዕብራይስጥ ሳይችሉ ለይሖዋ ፍቅር ማዳበርና እሱን ማምለክ የሚችሉት እንዴት ነው? (ዕዝራ 10:3, 44) ስለዚህ እነዚህ አይሁዳውያን ትልቅ ለውጥ ማድረግ ነበረባቸው። ይሁንና ከባቢሎን ይልቅ ንጹሑ አምልኮ ቀስ በቀስ መልሶ እየተቋቋመ ባለበት በእስራኤል እንዲህ ያለውን ለውጥ ማድረግ ቀላል ነው።—ነህ. 8:8, 9

ከ1919 ዓ.ም. አንስቶ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች ከታላቂቱ ባቢሎን ወጥተው ‘በቅድስና ጎዳና’ ላይ መጓዝ ጀምረዋል (አንቀጽ 8⁠ን ተመልከት)

8. በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት የተከናወነውን ነገር ማወቅ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? (የሽፋኑን ሥዕል ተመልከት።)

8 አንዳንዶች እንዲህ ብለው ያስቡ ይሆናል፦ ‘የሚገርም ታሪክ ነው። ይሁንና በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት አይሁዳውያን ምን እንዳጋጠማቸው ማወቃችን የሚጠቅመን ነገር አለ?’ አዎ፣ አለ። ምክንያቱም እኛም በምሳሌያዊ ሁኔታ ‘በቅድስና ጎዳና’ ላይ እየተጓዝን ነው። ቅቡዓንም ሆንን “ሌሎች በጎች” በቅድስና ጎዳና ላይ መጓዛችንን መቀጠል ይኖርብናል። ምክንያቱም ይህ መንገድ በመንፈሳዊው ገነት በኩል አድርጎ ወደፊት መንግሥቱ ወደሚያመጣቸው በረከቶች ይወስደናል። b (ዮሐ. 10:16) ከ1919 ዓ.ም. አንስቶ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች ከታላቂቱ ባቢሎን ማለትም ከሐሰት ሃይማኖት ወጥተው በዚህ ምሳሌያዊ መንገድ ላይ መጓዝ ጀምረዋል። አንተም ከእነሱ መካከል እንደምትገኝ ጥያቄ የለውም። ይህ መንገድ የተከፈተው ከመቶ ዓመት ገደማ በፊት ቢሆንም አውራ ጎዳናውን የማዘጋጀቱ ሥራ ከዚያ በፊት ባሉት በርካታ መቶ ዘመናት ሲከናወን ቆይቷል።

መንገዱን ማዘጋጀት

9. ከኢሳይያስ 57:14 ጋር በሚስማማ መልኩ ‘የቅድስና ጎዳናን’ የማዘጋጀት ሥራ የተከናወነው እንዴት ነው?

9 አይሁዳውያኑ ከባቢሎን ሲወጡ ይሖዋ እንቅፋቶችን ሁሉ አስወግዶላቸው ነበር። (ኢሳይያስ 57:14ን አንብብ።) በዘመናችን ካለው “የቅድስና ጎዳና” ጋር በተያያዘስ ምን ማለት ይቻላል? ከ1919 በፊት በነበሩት በርካታ መቶ ዓመታት፣ ይሖዋ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች ከታላቂቱ ባቢሎን የሚያስወጣውን መንገድ እንዲጠርጉ አድርጎ ነበር። (ከኢሳይያስ 40:3 ጋር አወዳድር።) እነዚህ ሰዎች፣ ከጊዜ በኋላ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ከታላቂቱ ባቢሎን ወጥተው የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ መልሶ ወደተቋቋመበት መንፈሳዊ ገነት መግባት እንዲችሉ አስፈላጊውን መንፈሳዊ የመንገድ ሥራ አከናውነዋል። ይህ “የመንገድ ሥራ” ምን ነገሮችን ያካትታል? መንገዱን ለማዘጋጀት ከተከናወኑት ሥራዎች መካከል አንዳንዶቹን እስቲ እንመልከት።

ለበርካታ መቶ ዓመታት ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች ከታላቂቱ ባቢሎን የሚያስወጣውን መንገድ ሲያዘጋጁ ቆይተዋል (ከአንቀጽ 10-11⁠ን ተመልከት)

10-11. መጽሐፍ ቅዱስን የማተሙና የመተርጎሙ ሥራ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት እንዲሰራጭ ያደረገው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

10 ሕትመት። እስከ 15ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ድረስ መጽሐፍ ቅዱስ የሚገለበጠው በእጅ ነበር። ሥራው ረጅም ጊዜ ይወስድ የነበረ ሲሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች በቀላሉ የማይገኙና በጣም ውድ ነበሩ። የማተሚያ ማሽን ከተፈለሰፈ በኋላ ግን መጽሐፍ ቅዱስን ማተምና ማሰራጨት ይበልጥ ቀላል ሆነ።

11 ትርጉም። ለበርካታ መቶ ዓመታት መጽሐፍ ቅዱስ በዋነኝነት የሚገኘው በላቲን ቋንቋ ነበር፤ ላቲን መረዳት የሚችሉት ደግሞ የተማሩ ሰዎች ብቻ ነበሩ። ይሁንና የሕትመት ሥራ እየተስፋፋ ሲሄድ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ተራው ሕዝብ ወደሚጠቀምባቸው ቋንቋዎች የመተርጎሙን ሥራ አጧጧፉት። አሁን የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢዎች ቀሳውስቱ የሚያስተምሯቸውን ነገር ከትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር ማወዳደር ይችላሉ።

ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች ከታላቂቱ ባቢሎን የሚያስወጣውን መንገድ ሲያዘጋጁ ቆይተዋል (ከአንቀጽ 12-14⁠ን ተመልከት) c

12-13. በ19ኛው መቶ ዘመን፣ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያጠኑ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች የሐሰት ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን ማጋለጥ የጀመሩት እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።

12 የመጽሐፍ ቅዱስ ማጥኛ መሣሪያዎች። መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት ያጠኑ የነበሩ ሰዎች በአምላክ ቃል ውስጥ ካነበቡት ነገር ብዙ ትምህርት ቀስመዋል። ያገኙትንም ትምህርት ለሌሎች ከማካፈል ወደኋላ አላሉም። ይህ ደግሞ ቀሳውስቱን በጣም ያበሳጫቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በ19ኛው መቶ ዘመን ቅን ልብ ያላቸው የተወሰኑ ሰዎች አብያተ ክርስቲያናቱ የሚያስተምሯቸውን የሐሰት ትምህርቶች የሚያጋልጡ ትራክቶችን ማሳተም ጀመሩ።

13 በ1835 ገደማ ሄንሪ ግሩ የተባለ ፈሪሃ አምላክ ያለው ሰው ሙታን ያሉበትን ሁኔታ የሚያብራራ ትራክት አሳተመ። በትራክቱ ላይ፣ ያለመሞት ባሕርይ የአምላክ ስጦታ እንጂ አብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት እንደሚያስተምሩት አብሮን የሚወለድ ነገር እንዳልሆነ ከቅዱሳን መጻሕፍት አብራራ። በ1837 ጆርጅ ስቶርዝ የተባለ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ በባቡር እየሄደ ሳለ ይህን ትራክት አገኘ። ትራክቱን ካገኘ በኋላ አንድ ወሳኝ እውነት እንደተማረ ተገነዘበ። የተማረውንም ነገር ለሌሎች ለመናገር ወሰነ። በ1842 “ምርምር የሚያሻው ጥያቄ—ክፉዎች የማትሞት ነፍስ አለቻቸው?” በሚል አጓጊ ርዕስ ተከታታይ ንግግሮችን አቀረበ። ጆርጅ ስቶርዝ ያዘጋጃቸው ጽሑፎች ቻርልስ ቴዝ ራስል በተባለ ወጣት ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳድረዋል።

14. ወንድም ራስልና አጋሮቹ ከእነሱ ዘመን በፊት ከተሠራው መንፈሳዊ የመንገድ ሥራ የተጠቀሙት በየትኞቹ መንገዶች ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

14 ወንድም ራስልና አጋሮቹ ከእነሱ ዘመን በፊት ከተሠራው መንፈሳዊ የመንገድ ሥራ የተጠቀሙት በየትኞቹ መንገዶች ነው? ጥናታቸውን ሲያከናውኑ ከእነሱ ዘመን በፊት የተዘጋጁ መዝገበ ቃላትን፣ ኮንኮርዳንሶችን እንዲሁም የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን ማመሣከር ችለው ነበር። እንደ ሄንሪ ግሩ እና ጆርጅ ስቶርዝ ያሉ ሰዎች ካከናወኑት የመጽሐፍ ቅዱስ ምርምርም በእጅጉ ተጠቅመዋል። ወንድም ራስልና አጋሮቹ ራሳቸውም የተለያዩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ርዕሰ ጉዳዮችን የሚዳስሱ በርካታ መጻሕፍትንና ትራክቶችን በማሳተም ለመንፈሳዊው የመንገድ ሥራ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

15. በ1919 የትኞቹ ወሳኝ ነገሮች ተከናወኑ?

15 በ1919 የአምላክ ሕዝቦች ከታላቂቱ ባቢሎን ነፃ ወጡ። በዚያው ዓመት “ታማኝና ልባም ባሪያ” ተሾመ፤ በተጨማሪም ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች አዲስ በተከፈተው “የቅድስና ጎዳና” ላይ እንዲጓዙ መርዳት ጀመረ። (ማቴ. 24:45-47) ባለፉት ዘመናት ለኖሩት ታማኝ “የመንገድ ሠራተኞች” ምስጋና ይግባቸውና በአዲሱ አውራ ጎዳና ላይ የሚጓዙ ሁሉ ስለ ይሖዋ ዓላማዎች ያላቸው እውቀት እያደገ መጣ። (ምሳሌ 4:18) ሕይወታቸውን ከይሖዋ መሥፈርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ መምራትም ቻሉ። ይሖዋ፣ ሕዝቦቹ ሁሉንም ለውጥ በአንድ ጊዜ እንዲያደርጉ አልጠበቀባቸውም። ከዚህ ይልቅ፣ በጊዜ ሂደት ሕዝቡን ማጥራት ጀመረ። (“ ይሖዋ ደረጃ በደረጃ ሕዝቡን አጥርቷል” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ወደፊት፣ በምናደርገው ነገር በሙሉ አምላካችንን ማስደሰት ስንችል በጣም ደስተኞች እንደምንሆን ምንም ጥያቄ የለውም!—ቆላ. 1:10

“የቅድስና ጎዳና” አሁንም ክፍት ነው

16. ከ1919 ወዲህ ‘በቅድስና ጎዳና’ ላይ ምን ዓይነት የመንገድ ሥራ ተከናውኗል? (ኢሳይያስ 48:17፤ 60:17)

16 ሁሉም መንገዶች በየጊዜው እድሳት ሊደረግላቸው ይገባል። ከ1919 ወዲህ ‘በቅድስና ጎዳና’ ላይ የሚከናወነው የመንገድ ሥራ ቀጥሏል፤ በዚህም የተነሳ ተጨማሪ ሰዎች ከታላቂቱ ባቢሎን መውጣት ቻሉ። በቅርቡ የተሾመው ታማኝና ልባም ባሪያ ኃላፊነቱን መወጣት ጀመረ። ከዚያም በ1921 የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ለአዲሶች ለማስተማር የሚረዳ ጽሑፍ አዘጋጀ። የአምላክ በገና (በአማርኛ አይገኝም) የተባለው ይህ ጽሑፍ በ36 ቋንቋዎች የተተረጎመ ከመሆኑም ሌላ ስድስት ሚሊዮን የሚያክሉ ቅጂዎች ተሰራጭተዋል፤ እንዲሁም ብዙዎች በዚህ መጽሐፍ አማካኝነት እውነትን መማር ችለዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ለመምራት የሚያስችል ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለ ግሩም መሣሪያ አግኝተናል። በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ይሖዋ ድርጅቱን በመጠቀም ‘በቅድስና ጎዳና’ ላይ ሁላችንም መጓዛችንን እንድንቀጥል የሚረዳ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ያለማቋረጥ እያቀረበልን ነው።—ኢሳይያስ 48:17፤ 60:17ን አንብብ።

17-18. “የቅድስና ጎዳና” የት ያደርሰናል?

17 አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ሲጀምር ‘በቅድስና ጎዳና’ ላይ ለመጓዝ አጋጣሚ ተከፈተለት ሊባል ይችላል። አንዳንዶች ጥቂት መንገድ ብቻ ተጉዘው ከአውራ ጎዳናው ይወጣሉ። ሌሎች ደግሞ እስከ መዳረሻቸው ድረስ ከመንገዱ ላለመውጣት ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል። ይሁንና መዳረሻቸው የት ነው?

18 “የቅድስና ጎዳና” ሰማያዊ ተስፋ ያላቸውን ክርስቲያኖች በሰማይ ወዳለው ‘የአምላክ ገነት’ ይወስዳቸዋል። (ራእይ 2:7) ምድራዊ ተስፋ ያላቸውን ክርስቲያኖች ደግሞ ሁሉም ሰው ፍጹም ወደሚሆንበት የክርስቶስ ሺህ ዓመት ግዛት መጨረሻ ያደርሳቸዋል። በዚህ አውራ ጎዳና ላይ መጓዝ ጀምረህ ከሆነ እባክህ ወደ ኋላ አትመልከት። በተጨማሪም አዲሱ ዓለም ውስጥ እስክትገባ ድረስ ከዚህ መንገድ አትውጣ። “መልካም መንገድ” እንመኝልሃለን!

መዝሙር 24 ኑ! ወደ ይሖዋ ተራራ

a ይሖዋ ከባቢሎን ወደ እስራኤል የሚወስደውን ምሳሌያዊ አውራ ጎዳና “የቅድስና ጎዳና” በማለት ጠርቶታል። በዘመናችንስ ይሖዋ ለሕዝቦቹ መንገድ አዘጋጅቶላቸዋል? አዎ! ከ1919 ዓ.ም. አንስቶ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ከታላቂቱ ባቢሎን ወጥተው ‘በቅድስና ጎዳና’ ላይ መጓዝ ጀምረዋል። ሁላችንም ወደ መዳረሻችን እስክንደርስ ድረስ በዚህ ጎዳና ላይ መጓዛችንን መቀጠል ይኖርብናል።

c የሥዕሉ መግለጫ፦ ወንድም ራስልና አጋሮቹ ከእነሱ ዘመን በፊት የተዘጋጁ የመጽሐፍ ቅዱስ ማጥኛ መሣሪያዎችን ተጠቅመዋል።