በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 23

‘የያህ ነበልባል’ እንዳይከስም አድርጉ

‘የያህ ነበልባል’ እንዳይከስም አድርጉ

“የፍቅር ወላፈን የእሳት ወላፈን ነው፤ የያህም ነበልባል ነው።”—መኃ. 8:6

መዝሙር 131 “አምላክ ያጣመረውን”

ማስተዋወቂያ a

1. መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ ፍቅርን የሚገልጸው እንዴት ነው?

 “የፍቅር ወላፈን የእሳት ወላፈን ነው፤ የያህም ነበልባል ነው። ጎርፍ ፍቅርን ሊያጠፋው አይችልም፤ ወንዞችም ጠራርገው ሊወስዱት አይችሉም።” b (መኃ. 8:6, 7) ይህ ለእውነተኛ ፍቅር የተሰጠ እንዴት ያለ ግሩም መግለጫ ነው! እነዚህ ቃላት ለባለትዳሮች የሚያበረታታ ሐሳብ ይዘዋል፦ በመካከላችሁ የማይከስም ፍቅር ሊኖር ይችላል።

2. አንድ ባልና ሚስት በመካከላቸው ያለው ፍቅር እንዳይቀዘቅዝ ከፈለጉ ምን ማድረግ አለባቸው?

2 ባለትዳሮች ዕድሜያቸውን በሙሉ የማይከስም ፍቅር ሊኖራቸው የሚችለው የበኩላቸውን ጥረት ካደረጉ ብቻ ነው። ለምሳሌ እሳት ያለማቋረጥ እንዲነድ ከተፈለገ ማገዶ ሊጨመርበት ይገባል። ማገዶ ካልተጨመረበት እሳቱ ቀስ በቀስ መጥፋቱ አይቀርም። በተመሳሳይም አንድ ባልና ሚስት ዕድሜያቸውን በሙሉ በመካከላቸው ጠንካራ ፍቅር ሊኖር ይችላል። ግን ይህ ሊሆን የሚችለው ጥምረታቸውን ለማጠናከር ጥረት ካደረጉ ብቻ ነው። አንዳንድ ጊዜ ባለትዳሮች በመካከላቸው ያለው ፍቅር እየቀዘቀዘ እንዳለ ሊሰማቸው ይችላል፤ በተለይም በኢኮኖሚ ችግር፣ በጤና እክል ወይም ልጆችን ማሳደግ በሚፈጥረው ውጥረት የተነሳ ጫና ሲበዛባቸው እንዲህ ሊሰማቸው ይችላል። እንግዲያው ባለትዳር ከሆናችሁ በትዳራችሁ ውስጥ ‘የያህ ነበልባል’ እንዳይከስም ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው? ጥምረታችሁን ማጠናከርና አስደሳች የትዳር ሕይወት መምራት የምትችሉባቸውን ሦስት መንገዶች በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን። c

ከይሖዋ ጋር ያላችሁን ወዳጅነት ማጠናከራችሁን ቀጥሉ

ልክ እንደ ዮሴፍና እንደ ማርያም ባሎችም ሆኑ ሚስቶች ከይሖዋ ጋር ጠንካራ ወዳጅነት ሊኖራቸው ይገባል (አንቀጽ 3⁠ን ተመልከት)

3. ባለትዳሮች ከይሖዋ ጋር ጠንካራ ወዳጅነት መመሥረታቸው ፍቅራቸው እንዳይከስም የሚረዳቸው እንዴት ነው? (መክብብ 4:12) (ሥዕሉንም ተመልከት።)

3 ‘የያህ ነበልባል’ እንዳይከስም ከተፈለገ ባሎችም ሆኑ ሚስቶች ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ዝምድና ለማጠናከር ጥረት ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። ከይሖዋ ጋር ጠንካራ ወዳጅነት መመሥረታቸው ትዳራቸውን የሚያጠናክረው እንዴት ነው? አንድ ባልና ሚስት ከሰማዩ አባታቸው ጋር ያላቸውን ወዳጅነት ከፍ አድርገው የሚመለከቱት ከሆነ ምክሮቹን ወዲያውኑ በሥራ ላይ ያውላሉ። ይህ ደግሞ በመካከላቸው ያለው ፍቅር እንዲቀዘቅዝ ሊያደርጉ የሚችሉ ችግሮችን ለማስወገድ ወይም ለማሸነፍ ይረዳቸዋል። (መክብብ 4:12ን አንብብ።) በተጨማሪም መንፈሳዊ የሆኑ ሰዎች እንደ ደግነት፣ ትዕግሥትና ይቅር ባይነት ያሉትን ባሕርያት በማዳበር ይሖዋን ለመምሰል ጥረት ያደርጋሉ። (ኤፌ. 4:32–5:1) ባለትዳሮች እነዚህን ባሕርያት የሚያሳዩ ከሆነ በመካከላቸው ያለው ፍቅር ማደጉ አይቀርም። በትዳር ዓለም ከ25 ዓመት በላይ ያሳለፈች ሌና የተባለች እህት “መንፈሳዊ የሆነን ሰው መውደድና ማክበር ቀላል ነው” በማለት ተናግራለች።

4. ይሖዋ የመሲሑ ወላጆች እንዲሆኑ ዮሴፍንና ማርያምን የመረጣቸው ለምንድን ነው?

4 አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ እንመልከት። ይሖዋ ለመሲሑ ወላጆች ሲመርጥ በወቅቱ ከነበሩት በርካታ የዳዊት ዘሮች መካከል ዮሴፍንና ማርያምን መርጧል። ለምን? ሁለቱም በግለሰብ ደረጃ ከይሖዋ ጋር ጠንካራ ወዳጅነት ነበራቸው። ይሖዋም በትዳራቸው ውስጥ እሱን እንደሚያስቀድሙ እርግጠኛ ነበር። ባለትዳሮች፣ ከዮሴፍና ከማርያም ምን ትምህርት ታገኛላችሁ?

5. ባሎች ከዮሴፍ ምን ትምህርት ያገኛሉ?

5 ዮሴፍ የይሖዋን መመሪያ ለመከተል ፈቃደኛ ነበር፤ ይህም ጥሩ ባል እንዲሆን ረድቶታል። አምላክ ቢያንስ ሦስት ጊዜ ለዮሴፍ ቤተሰቡን የሚነካ መመሪያ ሰጥቶታል። ትልቅ ለውጥ ማድረግ ቢጠይቅበትም እንኳ በሦስቱም ጊዜያት የይሖዋን መመሪያ ወዲያውኑ ታዟል። (ማቴ. 1:20, 24፤ 2:13-15, 19-21) ዮሴፍ የአምላክን መመሪያ በመከተል ማርያምን ከጉዳት ጠብቋታል፣ ደግፏታል እንዲሁም የሚያስፈልጋትን ነገር አሟልቶላታል። ዮሴፍ ያደረገው ነገር ማርያም ለእሱ ያላትን ፍቅርና አክብሮት ምንኛ አጠናክሮት ይሆን! ባሎች፣ ቤተሰቦቻችሁን ከምትንከባከቡበት መንገድ ጋር በተያያዘ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያ በመፈለግ የዮሴፍን ምሳሌ መከተል ትችላላችሁ። d ለውጥ ማድረግ ቢጠይቅባችሁም እንኳ የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር የምትከተሉ ከሆነ ለሚስቶቻችሁ ያላችሁን ፍቅር ታሳያላችሁ፤ ትዳራችሁንም ታጠናክራላችሁ። በትዳር ዓለም ከ20 ዓመት በላይ ያሳለፈች በቫኑዋቱ የምትኖር እህት እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ የይሖዋን መመሪያ ለማግኘት ጥረት ሲያደርግና መመሪያውን በሥራ ላይ ሲያውል ለእሱ ያለኝ አክብሮት ይጨምራል። እተማመንበታለሁ፤ እንዲሁም ጥሩ ውሳኔ እንደሚያደርግ እርግጠኛ ነኝ።”

6. ሚስቶች ከማርያም ምን ትምህርት ያገኛሉ?

6 ማርያም በግለሰብ ደረጃ ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት መሥርታ ነበር። እምነቷ በዮሴፍ ላይ የተመካ አልነበረም። ቅዱሳን መጻሕፍትን በሚገባ ታውቅ ነበር። ለማሰላሰልም ጊዜ መድባለች። (ሉቃስ 2:19, 51) ማርያም መንፈሳዊ ሴት መሆኗ ግሩም ሚስት እንድትሆን እንደረዳት ምንም ጥያቄ የለውም። በዛሬው ጊዜም በርካታ ሚስቶች የማርያምን ምሳሌ ለመከተል ጥረት ያደርጋሉ። ለምሳሌ ኤሚኮ የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “ከማግባቴ በፊት በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የምካፈልበት የራሴ ፕሮግራም ነበረኝ። ካገባሁ በኋላ ግን የሚጸልየውም ሆነ የቤተሰብ አምልኮ የሚመራው ባለቤቴ ስለሆነ መንፈሳዊነቴ በእሱ ላይ የተመካ መሆን እንደጀመረ አስተዋልኩ። ከይሖዋ ጋር ባለኝ ወዳጅነት ረገድ የራሴን የኃላፊነት ሸክም መሸከም እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። ስለዚህ ከአምላኬ ጋር ብቻዬን ሆኜ የምጸልይበት፣ መጽሐፍ ቅዱስን የማነብበትና በእሱ ሐሳቦች ላይ የማሰላስልበት ጊዜ መደብኩ።” (ገላ. 6:5) ሚስቶች፣ ከይሖዋ ጋር ያላችሁን ወዳጅነት ባጠናከራችሁ መጠን ባሎቻችሁ እናንተን የሚያመሰግኑበትና የሚወዱበት ተጨማሪ ምክንያት ያገኛሉ።—ምሳሌ 31:30

7. ባለትዳሮች አብረው ይሖዋን ማምለክን በተመለከተ ከዮሴፍና ከማርያም ምን ትምህርት ያገኛሉ?

7 በሌላ በኩል ደግሞ ዮሴፍና ማርያም ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ወዳጅነት ለማጠናከር በጋራ ጥረት አድርገዋል። በቤተሰብ ደረጃ ይሖዋን ማምለክ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ተገንዝበው ነበር። (ሉቃስ 2:22-24, 41፤ 4:16) በተለይ የቤተሰባቸው ቁጥር እያደገ ሲመጣ ይህን ማድረግ ከብዷቸው መሆን አለበት፤ ሆኖም በቤተሰብ ደረጃ ይሖዋን ማምለካቸውን ቀጥለዋል። በዛሬው ጊዜ ላሉ ባለትዳሮች እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ትተዋል! እናንተም እንደ ዮሴፍና እንደ ማርያም ልጆች ካሏችሁ በስብሰባዎች ላይ መገኘት ወይም ለቤተሰብ አምልኮ ጊዜ መመደብ ከባድ ሊሆንባችሁ ይችላል። ሁለታችሁ ብቻ ሆናችሁ የምታጠኑበት ወይም የምትጸልዩበት ጊዜ መመደብ ደግሞ ይበልጥ ከባድ ሊሆን ይችላል። ያም ቢሆን አብራችሁ ሆናችሁ ይሖዋን ስታመልኩ ከእሱ ጋርም ሆነ በመካከላችሁ ያለው ወዳጅነት እንደሚጠናከር አትዘንጉ። ስለዚህ ለአምልኳችሁ ቅድሚያ ስጡ።

8. በትዳራቸው ውስጥ ችግር ያጋጠማቸው ክርስቲያኖች ከቤተሰብ አምልኮ ይበልጥ ጥቅም ለማግኘት ምን ማድረግ ይችላሉ?

8 ይሁንና በትዳራችሁ ውስጥ ችግር ካጋጠማችሁስ? አብራችሁ ሆናችሁ የቤተሰብ አምልኮ ለማድረግ ያን ያህል ላትነሳሱ ትችላላችሁ። ሁኔታው እንደዚያ ከሆነ፣ ሁለታችሁንም የሚማርክ ርዕሰ ጉዳይ መርጣችሁ አጭርና አስደሳች ውይይት በማድረግ መጀመር ትችላላችሁ። እንዲህ ማድረጋችሁ ጥምረታችሁን ሊያጠናክር እንዲሁም አብራችሁ ሆናችሁ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ለመካፈል ያላችሁን ፍላጎት ሊጨምረው ይችላል።

አብራችሁ ጊዜ አሳልፉ

9. ባለትዳሮች አብረው ጊዜ ማሳለፍ ያለባቸው ለምንድን ነው?

9 ባለትዳሮች፣ አብራችሁ ጊዜ ማሳለፋችሁም ፍቅራችሁ እንዳይከስም ይረዳችኋል። እንዲህ ማድረጋችሁ በአስተሳሰብም ሆነ በስሜት እየተራራቃችሁ እንዳትሄዱ ያግዛችኋል። (ዘፍ. 2:24) ከ15 ዓመት በፊት ትዳር የመሠረቱት ሊሊያ እና ሩስላን ከተጋቡ ብዙም ሳይቆይ ምን እንደተገነዘቡ እንመልከት። ሊሊያ እንዲህ ብላለች፦ “ያሰብነውን ያህል አብረን ብዙ ጊዜ ማሳለፍ እንደማንችል ተገነዘብን። ሕይወታችን በሰብዓዊ ሥራ፣ በቤት ውስጥ ሥራና በኋላም ልጆችን በማሳደግ የተጨናነቀ ነበር። ሁለታችን ብቻ አብረን የምናሳልፈው ጊዜ ለማግኘት ጥረት ካላደረግን እየተራራቅን እንደምንሄድ ተገነዘብን።”

10. ባለትዳሮች በኤፌሶን 5:15, 16 ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት በሥራ ላይ ማዋል የሚችሉት እንዴት ነው?

10 ባለትዳሮች አብረው የሚያሳልፉት ጊዜ ለማግኘት ምን ማድረግ ይችላሉ? አስቀድማችሁ ዕቅድ በማውጣት አብራችሁ የምታሳልፉት ጊዜ መመደብ ሊያስፈልጋችሁ ይችላል። (ኤፌሶን 5:15, 16ን አንብብ።) ኡዞንዱ የተባለ በናይጄርያ የሚኖር ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ፕሮግራም በማወጣበት ጊዜ እኔና ባለቤቴ ብቻችንን ሆነን የምናሳልፈውን ጊዜ አካትታለሁ፤ እንዲሁም ለዚህ ጊዜ ቅድሚያ እሰጣለሁ።” (ፊልጵ. 1:10) በሞልዶቫ የሚኖር የወረዳ የበላይ ተመልካች ሚስት የሆነችው አናስታሲያ ጊዜዋን በተሻለ መንገድ ለመጠቀም ምን እንደምታደርግ እስቲ እንመልከት። እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ የጉባኤ ኃላፊነቶቹን በሚወጣበት ወቅት እኔ የግል ሥራዎቼን ለመጨራረስ ጥረት አደርጋለሁ። ይህም በኋላ ላይ አብረን ጊዜ ለማሳለፍ ያስችለናል።” ይሁንና ፕሮግራማችሁ ከመጣበቡ የተነሳ አብራችሁ የምታሳልፉት ጊዜ ማግኘት ብትቸገሩስ?

ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር በየትኞቹ እንቅስቃሴዎች መካፈል ትችላላችሁ? (ከአንቀጽ 11-12⁠ን ተመልከት)

11. አቂላና ጵርስቅላ በየትኞቹ እንቅስቃሴዎች አብረው ይካፈሉ ነበር?

11 ባለትዳሮች በጥንቶቹ ክርስቲያኖች ዘንድ ተወዳጅ የነበሩት አቂላና ጵርስቅላ ከተዉት ምሳሌ ትምህርት ማግኘት ይችላሉ። (ሮም 16:3, 4) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ትዳራቸው ብዙ መረጃ ባይሰጠንም አብረው ይሠሩ፣ ይሰብኩና ሌሎችን ይረዱ እንደነበረ ይነግረናል። (ሥራ 18:2, 3, 24-26) እንዲያውም አቂላና ጵርስቅላ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለየብቻ ተጠቅሰው አያውቁም።

12. ባለትዳሮች አብረው ጊዜ እንዲያሳልፉ ምን ሊረዳቸው ይችላል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

12 ባለትዳሮች የአቂላንና የጵርስቅላን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው? እናንተም ሆናችሁ የትዳር አጋራችሁ ያሉባችሁን የተለያዩ ኃላፊነቶች ለማሰብ ሞክሩ። አንዳንዶቹን ሥራዎች ለብቻችሁ ከማከናወን ይልቅ አብራችሁ ልትሠሩ ትችሉ ይሆን? ለምሳሌ አቂላና ጵርስቅላ አብረው ይሰብኩ ነበር። እናንተስ አዘውትራችሁ አብራችሁ ለማገልገል ፕሮግራም ታወጣላችሁ? አቂላና ጵርስቅላ አብረው ይሠሩም ነበር። እርግጥ ነው፣ እናንተ አንድ ዓይነት ሥራ አይኖራችሁ ይሆናል። ይሁንና የቤት ውስጥ ሥራዎችን አብራችሁ ማከናወን ትችሉ ይሆን? (መክ. 4:9) አንድን ነገር ተባብራችሁ ስታከናውኑ አንድነታችሁ ይጠናከራል፤ አብራችሁ ለማውራት የሚያስችል አጋጣሚም ታገኛላችሁ። ሮበርትና ሊንዳ በትዳር ዓለም ከ50 ዓመት በላይ አሳልፈዋል። ሮበርት እንዲህ ብሏል፦ “እውነቱን ለመናገር በመዝናኛ ያን ያህል ጊዜ አብረን አናሳልፍም። ሆኖም ዕቃ ሳጥብ ባለቤቴ ዕቃዎቹን ስታደርቅ ወይም ደጅ አትክልት ስንከባከብ መጥታ አብራኝ ስትሠራ በጣም ደስ ይለኛል። አብረን መሥራታችን ይበልጥ ያቀራርበናል። ፍቅራችን እያደገ ይሄዳል።”

13. ባለትዳሮች አንድነታቸውን ለማጠናከር ምን ማድረግ አለባቸው?

13 ይሁንና አንድ ላይ ስለሆናችሁ ብቻ አንድነታችሁ ይጠናከራል ማለት እንዳልሆነ አስታውሱ። በብራዚል የምትኖር አንዲት ባለትዳር እንዲህ ብላለች፦ “በዛሬው ጊዜ ሕይወታችን በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ከመሞላቱ የተነሳ በአንድ ጣሪያ ሥር ስለምንኖር ብቻ አብረን ጊዜ እያሳለፍን እንዳለን ሊሰማን ይችላል። ሆኖም አንድ ላይ መሆናችን ብቻ በቂ እንዳልሆነ ተገንዝቤያለሁ። ለባለቤቴ ተገቢውን ትኩረት ልሰጠውም ይገባል።” ብሩኖ እና ባለቤቱ ቴይስ አንዳቸው ለሌላው ትኩረት ለመስጠት ጥረት የሚያደርጉት እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት። ብሩኖ እንዲህ ብሏል፦ “አብረን ጊዜ በምናሳልፍበት ወቅት ስልካችንን ትተን እርስ በርስ በምናደርገው ጭውውት ላይ ብቻ እናተኩራለን።”

14. ባለትዳሮች አብረው ጊዜ ማሳለፍ የማያስደስታቸው ከሆነ ምን ማድረግ ይችላሉ?

14 ይሁንና አብራችሁ ጊዜ ማሳለፍ የማያስደስታችሁ ቢሆንስ? ምናልባት የሚማርካችሁ ነገር የተለያየ ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ አንዳችሁ ሌላውን የሚያበሳጭ ባሕርይ ይኖራችሁ ይሆናል። ታዲያ ምን ማድረግ ትችላላችሁ? ቀደም ሲል የጠቀስነውን የእሳት ምሳሌ መለስ ብለን እንመልከት። እሳቱ ወዲያውኑ ቦግ ብሎ አይነድም። ከትንሽ ጭራሮ አንስቶ ቀስ በቀስ ተለቅ ተለቅ ያሉ እንጨቶች ሊጨመሩበት ይገባል። እናንተም በተመሳሳይ በየቀኑ ጥቂት ደቂቃዎች ብቻ አብራችሁ በማሳለፍ ለምን አትጀምሩም? ግጭት ሊፈጥር በሚችል ሳይሆን ሁለታችሁንም በሚያስደስታችሁ እንቅስቃሴ ለመካፈል ሞክሩ። (ያዕ. 3:18) በዚህ መንገድ ከትንሹ መጀመራችሁ ፍቅራችሁን ለማቀጣጠል ሊረዳችሁ ይችላል።

አንዳችሁ ሌላውን በአክብሮት ያዙ

15. ባለትዳሮች ፍቅራቸው እንዳይከስም ከፈለጉ መከባበራቸው ወሳኝ የሆነው ለምንድን ነው?

15 በትዳር ውስጥ መከባበር በጣም ወሳኝ ነው። አክብሮት እሳት በደንብ እንዲነድ ከሚያደርገው ኦክስጅን ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ኦክስጅን ከሌለ እሳቱ ወዲያውኑ ይጠፋል። በተመሳሳይም ባለትዳሮች እርስ በርስ የማይከባበሩ ከሆነ ፍቅራቸው ወዲያውኑ ሊቀዘቅዝ ይችላል። በሌላ በኩል ግን፣ እርስ በርስ ለመከባበር ጥረት የሚያደርጉ ባልና ሚስት ፍቅራቸው እንዳይከስም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። ይሁንና ልብ ልንለው የሚገባ አንድ ነገር አለ። ዋናው ነገር እናንተ አክብሮት እንደምታሳዩ የሚሰማችሁ መሆኑ ሳይሆን የትዳር ጓደኛችሁ እንደምታከብሩት የሚሰማው መሆኑ ነው። ፔኒ እና አሬት በትዳር ዓለም ከ25 ዓመት በላይ አሳልፈዋል። ፔኒ እንዲህ ብላለች፦ “እርስ በርስ ስለምንከባበር ቤታችን ፍቅር የሰፈነበት ቦታ ነው። አንዳችን የሌላውን አመለካከት እንደምናከብር ስለምናውቅ ስሜታችንን ለመግለጽ ነፃነት ይሰማናል።” ይሁንና የትዳር ጓደኛችሁ ከልባችሁ እንደምታከብሩት እንዲሰማው ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው? የአብርሃምንና የሣራን ምሳሌ እስቲ እንመልከት።

ክርስቲያን ባሎች ሚስቶቻቸውን በጥሞና በማዳመጥ ስሜታቸውን እንደሚያከብሩላቸው ማሳየት ይኖርባቸዋል (አንቀጽ 16⁠ን ተመልከት)

16. ባሎች ከአብርሃም ምሳሌ ምን ትምህርት ያገኛሉ? (1 ጴጥሮስ 3:7) (ሥዕሉንም ተመልከት።)

16 አብርሃም ሣራን በአክብሮት ይይዛት ነበር። አመለካከቷን ከግምት ያስገባ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ስሜቷን አክብሮላታል። ለምሳሌ በአንድ ወቅት ሣራ በጭንቀት በመዋጧ ስሜቷን አውጥታ ለአብርሃም ነግራው ነበር፤ እንዲያውም ለደረሰባት ነገር እሱን ወቅሳዋለች። ታዲያ አብርሃም በዚህ ጊዜ ተቆጣ? በፍጹም። ሣራ እንደምትገዛለትና እንደምትደግፈው ያውቅ ነበር። አብርሃም በጥሞና ያዳመጣት ከመሆኑም ሌላ ጉዳዩን ለመፍታት ጥረት አደረገ። (ዘፍ. 16:5, 6) እኛስ ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ባሎች፣ ለቤተሰባችሁ ውሳኔ የማድረግ ሥልጣን እንዳላችሁ የታወቀ ነው። (1 ቆሮ. 11:3) ያም ቢሆን፣ ውሳኔ ከማድረጋችሁ በፊት የትዳር ጓደኛችሁን አመለካከት ግምት ውስጥ ብታስገቡ ፍቅር ይሆናል፤ በተለይ ውሳኔው እሷንም የሚነካ በሚሆንበት ጊዜ እንዲህ ማድረጋችሁ ተገቢ ነው። (1 ቆሮ. 13:4, 5) አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የትዳር ጓደኛችሁ ውጥረት ውስጥ ከመግባቷ የተነሳ ስሜታዊ ሆና ትናገር ይሆናል። በዚህ ጊዜ እሷን በጥሞና በማዳመጥ ስሜቷን እንደምታከብሩላት ታሳያላችሁ? (1 ጴጥሮስ 3:7ን አንብብ።) አንጄላ እና ዲሚትሪ በትዳር ዓለም 30 ዓመት ገደማ አሳልፈዋል። አንጄላ ባለቤቷ እንደምትከበር እንዲሰማት የሚያደርገው እንዴት እንደሆነ ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “በምበሳጭበት ወይም እንዲሁ ማውራት በምፈልግበት ጊዜ ዲሚትሪ ምንጊዜም ጆሮ ሰጥቶ ያዳምጠኛል። በጣም ስሜታዊ በምሆንበት ጊዜም እንኳ በትዕግሥት ይይዘኛል።”

17. ሚስቶች ከሣራ ምሳሌ ምን ትምህርት ያገኛሉ? (1 ጴጥሮስ 3:5, 6)

17 ሣራ፣ አብርሃም የሚያደርጋቸውን ውሳኔዎች በመደገፍ እንደምታከብረው አሳይታለች። (ዘፍ. 12:5) ለምሳሌ በአንድ ወቅት አብርሃም ያልተጠበቁ እንግዶች ሲመጡበት እነሱን ለማስተናገድ አሰበ። በመሆኑም ሣራ የምትሠራውን ነገር ትታ በርከት ያለ ቂጣ እንድትጋግር ጠየቃት። (ዘፍ. 18:6) ሣራም አፋጣኝ እርምጃ በመውሰድ የአብርሃምን ውሳኔ እንደምትደግፍ አሳይታለች። ሚስቶች፣ የባሎቻችሁን ውሳኔ በመደገፍ የሣራን ምሳሌ መከተል ትችላላችሁ። እንዲህ ስታደርጉ ትዳራችሁ ይጠናከራል። (1 ጴጥሮስ 3:5, 6ን አንብብ።) ባለፈው አንቀጽ ላይ የተጠቀሰው ዲሚትሪ ባለቤቱ እንደሚከበር እንዲሰማው የምታደርገው እንዴት እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “አንጄላ ከእኔ የተለየ አመለካከት በሚኖራት ጊዜም ጭምር ውሳኔዎቼን ለመደገፍ የምታደርገውን ጥረት በጣም አደንቃለሁ። ውሳኔው ጥሩ ውጤት በማያስገኝበት ጊዜም እንኳ አትተቸኝም።” ደግሞም የሚያከብረንን ሰው መውደድ በጣም ቀላል ነው!

18. ባለትዳሮች በመካከላቸው ያለው ፍቅር እንዳይከስም ጥረት ማድረጋቸው ምን ጥቅም ያስገኝላቸዋል?

18 በዛሬው ጊዜ ሰይጣን በክርስቲያን ባለትዳሮች መካከል ያለውን ፍቅር ለማጥፋት ጥረት ያደርጋል። ባለትዳሮች በመካከላቸው ያለው ፍቅር ከጠፋ ከይሖዋ መራቅ ሊጀምሩ እንደሚችሉ ያውቃል። ይሁንና እውነተኛ ፍቅርን ሊያጠፋው የሚችል ምንም ነገር የለም! እንግዲያው በትዳራችሁ ውስጥ ያለው ፍቅር በመኃልየ መኃልይ ላይ የተጠቀሰው ዓይነት እንዲሆን ምኞታችን ነው። በትዳራችሁ ውስጥ ለይሖዋ ቅድሚያ ለመስጠት፣ አብራችሁ የምታሳልፉት ጊዜ ለመመደብና አንዳችሁ የሌላውን ስሜት ለማክበር ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ። እንዲህ ካደረጋችሁ፣ ትዳራችሁ የእውነተኛ ፍቅር ምንጭ ለሆነው ለይሖዋ ክብር ያመጣል። እንዲሁም ያለማቋረጥ ማገዶ እንደሚጨመርበት እሳት ፍቅራችሁ ለዘላለም ሲነድ ይኖራል።

መዝሙር 132 አንድ ሆነናል

a ይሖዋ ለሰው ልጆች ትዳርን ስጦታ አድርጎ ሰጥቷቸዋል። ጋብቻ፣ ባልና ሚስት ልዩ የሆነ ፍቅር እንዲያጣጥሙ ያስችላል። ይሁንና አንዳንድ ጊዜ ይህ ፍቅር ሊቀዘቅዝ ይችላል። ባለትዳር ከሆናችሁ ይህ ርዕስ በመካከላችሁ ያለው ፍቅር እንዳይከስም ለማድረግ እንዲሁም ደስተኛ የትዳር ሕይወት ለመምራት ይረዳችኋል።

b የማይለዋወጥና ዘላቂ የሆነው እውነተኛ ፍቅር ‘የያህ ነበልባል’ ተብሎ የተጠራው የዚህ ዓይነቱ ፍቅር ምንጭ ይሖዋ ስለሆነ ነው።

c የትዳር ጓደኛችሁ የማያምን ቢሆንም እንኳ እነዚህ ሐሳቦች ጥምረታችሁን ለማጠናከር ሊረዷችሁ ይችላሉ።—1 ቆሮ. 7:12-14፤ 1 ጴጥ. 3:1, 2

d ለምሳሌ jw.org እና JW Library® ላይ “ለቤተሰብ” በሚለው ዓምድ ሥር የሚወጡት ተከታታይ ርዕሶች የያዙትን ጠቃሚ ምክር ተመልከቱ።