በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 18

መዝሙር 1 የይሖዋ ባሕርያት

መሐሪ በሆነው “የምድር ሁሉ ዳኛ” ተማመኑ!

መሐሪ በሆነው “የምድር ሁሉ ዳኛ” ተማመኑ!

“የምድር ሁሉ ዳኛ ትክክል የሆነውን ነገር አያደርግም?”ዘፍ. 18:25

ዓላማ

ይህ ርዕስ፣ ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች ከሚያገኙት ትንሣኤ ጋር በተያያዘ ስለ ይሖዋ ምሕረትና ፍትሕ ያለንን ግንዛቤ ያሳድግልናል።

1. ይሖዋ ለአብርሃም የትኛውን የሚያጽናና ትምህርት ሰጠው?

 አብርሃም በአንድ ወቅት ከይሖዋ ጋር ያደረገውን ውይይት ፈጽሞ ሊረሳው አይችልም። አምላክ የሰዶምንና የገሞራን ከተሞች ሊያጠፋ እንዳሰበ በአንድ መልአክ አማካኝነት ለአብርሃም ነገረው። ታማኙ አብርሃም ይህን ሐሳብ መቀበል ከበደው። በመሆኑም “በእርግጥ ጻድቁን ከኃጢአተኛው ጋር አብረህ ታጠፋለህ? . . . የምድር ሁሉ ዳኛ ትክክል የሆነውን ነገር አያደርግም?” በማለት ጠየቀ። ይሖዋ በትዕግሥት ለወዳጁ አንድ ወሳኝ ትምህርት ሰጠው፦ አምላክ ጻድቃንን ፈጽሞ አያጠፋም። ይህ ትምህርት ሁላችንንም ይጠቅመናል፤ እንዲሁም ያጽናናናል።—ዘፍ. 18:23-33

2. ይሖዋ የሚያስተላልፈው ፍርድ ትክክለኛና ምሕረት የሚንጸባረቅበት እንደሆነ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

2 ይሖዋ በሰዎች ላይ የሚያስተላልፈው ፍርድ ትክክለኛና ምሕረት የሚንጸባረቅበት እንደሆነ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው? ‘ይሖዋ የሰውን ልብ እንደሚያይ’ ስለምናውቅ ነው። (1 ሳሙ. 16:7) እንዲያውም “ልብን ሁሉ” ይመረምራል። (1 ዜና 28:9፤ 1 ነገ. 8:39) ይህ አስደናቂ እውነታ ነው። የይሖዋ ፍርድ ከእኛ የመረዳት ችሎታ በእጅጉ የላቀ ነው። በእርግጥም ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ተመርቶ “[ፍርዱ] ፈጽሞ የማይመረመር ነው!” ማለቱ ተገቢ ነው።—ሮም 11:33

3-4. አንዳንድ ጊዜ ምን የሚል ጥያቄ ሊፈጠርብን ይችላል? በዚህ ርዕስ ውስጥስ ምን እንመለከታለን? (ዮሐንስ 5:28, 29)

3 ያም ቢሆን አንዳንድ ጊዜ አብርሃም ያነሳው ዓይነት ጥያቄ ይፈጠርብን ይሆናል። ምናልባትም እንዲህ ብለን ልንጠይቅ እንችላለን፦ ‘በሰዶምና በገሞራ የጠፉትን ጨምሮ ይሖዋ ያጠፋቸው ሰዎች ወደፊት ተስፋ ሊኖራቸው ይችላል? ከእነሱ መካከል አንዳንዶቹ “ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች” በሚያገኙት ትንሣኤ ውስጥ ይካተቱ ይሆን?’—ሥራ 24:15

4 ስለ ትንሣኤ የምናውቀውን ነገር እስቲ መለስ ብለን እንከልስ። ከተወሰነ ጊዜ በፊት ‘ከሕይወት ትንሣኤ’ እና ‘ከፍርድ ትንሣኤ’ ጋር በተያያዘ ባለን ግንዛቤ ላይ ማስተካከያ ተደርጎ ነበር። a (ዮሐንስ 5:28, 29ን አንብብ።) በዚህ አዲስ ግንዛቤ የተነሳ ተጨማሪ ማስተካከያዎችን ማድረግ አስፈላጊ ሆኗል። በዚህኛውና በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እነዚህን ማስተካከያዎች እንመለከታለን። ከይሖዋ የጽድቅ ፍርዶች ጋር በተያያዘ በመጀመሪያ ምን እንደማናውቅ፣ ከዚያም ምን እንደምናውቅ እንመለከታለን።

የማናውቀው ነገር

5. ቀደም ሲል ጽሑፎቻችን በሰዶምና በገሞራ የጠፉትን ሰዎች በተመለከተ ምን ብለው ነበር?

5 ቀደም ሲል በጽሑፎቻችን ላይ፣ ይሖዋ ጻድቃን አይደሉም ብሎ ፍርድ ያስተላለፈባቸው ሰዎች ምን እንደሚያጋጥማቸው የሚገልጽ ሐሳብ ወጥቶ ነበር። በሰዶምና በገሞራ እንደጠፉት ያሉ ሰዎች ወደፊት የትንሣኤ ተስፋ የላቸውም ብለን እንናገር ነበር። ሆኖም ስለ ጉዳዩ ያደረግነው ጸሎት የታከለበት ጥልቅ ምርምር ይህን በእርግጠኝነት መናገር እንደማንችል አስገንዝቦናል። ለምን?

6. ይሖዋ ጻድቃን ባልሆኑ ሰዎች ላይ ስላስተላለፈው ፍርድ ከሚገልጹ ዘገባዎች መካከል አንዳንዶቹን ጥቀስ። ከእነዚህ ታሪኮች ጋር በተያያዘ ምን አናውቅም?

6 ከዚህ ጋር በተያያዘ ሌሎች ጥያቄዎችም ይነሳሉ። ይሖዋ ጻድቃን ባልሆኑ ሰዎች ላይ ስላስተላለፈው ፍርድ የሚገልጹ የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች አሉ። ለምሳሌ በጥፋት ውኃው ወቅት ቁጥራቸው የማይታወቅ ሰዎች ጠፍተዋል። በተጨማሪም ይሖዋ በተስፋይቱ ምድር ይኖሩ የነበሩትን ሰባት ብሔራት እንዲያጠፉ እስራኤላውያንን አዟቸዋል። ከዚህም ሌላ በአንድ መልአክ አማካኝነት በአንድ ምሽት 185,000 አሦራውያን ወታደሮችን አጥፍቷል። (ዘፍ. 7:23፤ ዘዳ. 7:1-3፤ ኢሳ. 37:36, 37) ከእነዚህ ታሪኮች ጋር በተያያዘ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ እርምጃ የወሰደባቸው ሰዎች በሙሉ ለዘላለም እንደሚጠፉና የትንሣኤ ተስፋ እንደማይኖራቸው በግልጽ ይናገራል? አይናገርም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

7. በጥፋት ውኃው ወቅት ወይም በከነአን ከጠፉት ሰዎች ጋር በተያያዘ ምን አናውቅም? (ሥዕሉን ተመልከት።)

7 ይሖዋ በእያንዳንዱ ግለሰብ ላይ ምን የሚል ፍርድ እንዳስተላለፈ አናውቅም፤ ወይም ደግሞ የጠፉት ሰዎች ስለ ይሖዋ የመማርና ንስሐ የመግባት አጋጣሚ አግኝተው የነበረ መሆን አለመሆኑን አናውቅም። መጽሐፍ ቅዱስ በጥፋት ውኃው ወቅት ስለነበረው ሁኔታ ሲናገር ኖኅ “የጽድቅ ሰባኪ” እንደነበር ይናገራል። (2 ጴጥ. 2:5) ሆኖም ኖኅ ያንን ግዙፍ መርከብ እየሠራ በነበረበት ወቅት በምድር ላይ የሚኖረውን እያንዳንዱን ሰው አግኝቶ ስለ ጥፋት ውኃው ለማስጠንቀቅ ጥረት አድርጎ እንደነበረ አይገልጽም። በተመሳሳይም በከነአን ከነበሩት ብሔራት ጋር በተያያዘ እነዚያ ክፉ ሰዎች በሙሉ ስለ ይሖዋ የመማርና አካሄዳቸውን የማስተካከል አጋጣሚ አግኝተው የነበረ መሆን አለመሆኑን አናውቅም።

ኖኅና ቤተሰቡ ግዙፍ የሆነውን መርከብ ሲሠሩ። ኖኅ ከመርከቡ ሥራ ጎን ለጎን በምድር ላይ ያሉትን ሰዎች በሙሉ የጥፋት ውኃው ከመምጣቱ በፊት ለማስጠንቀቅ የተደራጀ የስብከት ዘመቻ እንዳካሄደ የሚገልጽ ሐሳብ የለም (አንቀጽ 7⁠ን ተመልከት)


8. በሰዶምና በገሞራ የነበሩትን ሰዎች በተመለከተ ምን አናውቅም?

8 በሰዶምና በገሞራ ስለነበሩት ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? ጻድቅ ሰው የነበረው ሎጥ በመካከላቸው ይኖር ነበር። ይሁንና ሎጥ ለሁሉም ሰብኮላቸው እንደነበር በእርግጠኝነት እናውቃለን? አናውቅም። ሁሉም ክፉዎች እንደነበሩ ምንም ጥያቄ የለውም፤ ግን ሁሉም ክፉና ደጉን የሚያውቁ ሰዎች ነበሩ? በዚያ ከተማ የነበሩ ብዙ ወንዶች ተሰብስበው የሎጥን እንግዶች ለመድፈር እንደመጡ አስታውስ። መጽሐፍ ቅዱስ ከእነዚህ ሰዎች መካከል ‘ልጆችም’ እንደነበሩ ይናገራል። (ዘፍ. 19:4፤ 2 ጴጥ. 2:7) መሐሪ አምላክ የሆነው ይሖዋ ማናቸውም ትንሣኤ አይገባቸውም ብሎ እንደፈረደ በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን? ይሖዋ በከተማዋ ውስጥ አሥር ጻድቃን እንኳ እንደሌሉ ለአብርሃም ነግሮታል። (ዘፍ. 18:32) ስለዚህ ሰዎቹ ጻድቃን እንዳልነበሩ ግልጽ ነው፤ በመሆኑም ይሖዋ ለድርጊታቸው ተጠያቂ ያደረጋቸው መሆኑ ተገቢ ነው። ይሁንና አንዳቸውም “ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች” በሚያገኙት ትንሣኤ ውስጥ እንደማይካተቱ በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን? አንችልም!

9. ከሰለሞን ጋር በተያያዘ ምን አናውቅም?

9 በሌላ በኩል ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ጻድቃን ከጊዜ በኋላ መጥፎ ጎዳና መከተል እንደጀመሩ ይናገራል። እንዲህ ካሉት ሰዎች መካከል ንጉሥ ሰለሞን ይገኝበታል። ሰለሞን የአምላክን መንገዶች በሚገባ ተምሯል፤ ይሖዋም አትረፍርፎ ባርኮታል። ያም ቢሆን ውሎ አድሮ የሐሰት አማልክትን ማምለክ ጀመረ። ሰለሞን የሠራው ኃጢአት ይሖዋን እጅግ አስቆጥቶታል፤ በብሔሩም ላይ ለበርካታ መቶ ዘመናት የዘለቀ መዘዝ አስከትሏል። እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሰለሞን ‘ከአባቶቹ ጋር እንዳንቀላፋ’ ይናገራል፤ አባቶቹ ከተባሉት መካከል እንደ ንጉሥ ዳዊት ያሉ ታማኝ ሰዎች ይገኙበታል። (1 ነገ. 11:5-9, 43፤ 2 ነገ. 23:13) ይሁንና ሰለሞን የተቀበረበት መንገድ ትንሣኤ እንደሚያገኝ ዋስትና ይሆናል? መጽሐፍ ቅዱስ ይህን በቀጥታ አይናገርም። ይሁንና አንዳንዶች “የሞተ ከኃጢአቱ ነፃ ወጥቷል” የሚለውን ጥቅስ ከዚህ ጋር በተያያዘ ይጠቅሱ ይሆናል። (ሮም 6:7) ይህ ሐሳብ በራሱ እውነት ቢሆንም የሞቱ ሰዎች ሁሉ ይነሳሉ ወይም አንድ ሰው ስለሞተ ብቻ ትንሣኤ ይገባዋል ማለት አይደለም። ትንሣኤ አፍቃሪ የሆነው አምላካችን የሚሰጠው ስጦታ ነው። ይህን ስጦታ የሚሰጠው ለዘላለም እሱን የማገልገል አጋጣሚ ሊሰጣቸው ለሚፈልጋቸው ሰዎች ነው። (ኢዮብ 14:13, 14፤ ዮሐ. 6:44) ታዲያ ሰለሞን ይህን ስጦታ ያገኝ ይሆን? አናውቅም፤ መልሱን የሚያውቀው ይሖዋ ብቻ ነው። የምናውቀው ነገር ቢኖር ይሖዋ ትክክል የሆነውን ነገር እንደሚያደርግ ነው።

የምናውቀው ነገር

10. ይሖዋ ሰዎችን ስለማጥፋት ምን ይሰማዋል? (ሕዝቅኤል 33:11) (ሥዕሉንም ተመልከት።)

10 ሕዝቅኤል 33:11ን አንብብ። ይሖዋ በሰዎች ላይ ፍርድ ከሚያስተላልፍበት መንገድ ጋር በተያያዘ ምን እንደሚሰማው በደግነት ገልጾልናል። ሐዋርያው ጴጥሮስ በመንፈስ ተመርቶ ‘ይሖዋ ማንም እንዲጠፋ አይፈልግም’ በማለት ነቢዩ ሕዝቅኤል የጻፈውን ሐሳብ አስተጋብቷል። (2 ጴጥ. 3:9) ከዚህ አጽናኝ እውነታ አንጻር ይሖዋ ሰዎችን ለዘላለም ለማጥፋት እንደማይቸኩል በእርግጠኝነት እናውቃለን። እሱ እጅግ መሐሪ ነው፤ የሚቻል በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ ምሕረት ያሳያል።

ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች ትንሣኤ በሚያገኙበት ወቅት የተለያዩ ዓይነት ሰዎች ስለ ይሖዋ የመማር አጋጣሚ ያገኛሉ (አንቀጽ 10⁠ን ተመልከት)


11. ትንሣኤ የማያገኙት እነማን ናቸው? ይህንንስ እንዴት እናውቃለን?

11 ትንሣኤ የማያገኙትን ሰዎች በተመለከተ ምን እናውቃለን? መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠን ጥቂት ምሳሌዎችን ብቻ ነው። b ኢየሱስ የአስቆሮቱ ይሁዳ ትንሣኤ እንደማያገኝ ጠቁሟል። c (ማር. 14:21፤ ዮሐ. 17:12) ይሁዳ ሆን ብሎ፣ እያወቀ ይሖዋ አምላክንና ልጁን ተቃውሟል። d (ማር. 3:29) በተመሳሳይም ኢየሱስ እሱን ከተቃወሙት የሃይማኖት መሪዎች አንዳንዶቹ የትንሣኤ ተስፋ የሌለው ጥፋት እንደሚጠብቃቸው ተናግሯል። (ማቴ. 23:33) ሐዋርያው ጳውሎስም ንስሐ የማይገቡ ከሃዲዎች ትንሣኤ እንደማያገኙ ገልጿል።—ዕብ. 6:4-8፤ 10:29

12. ስለ ይሖዋ ምሕረት ምን እናውቃለን? ምሳሌ ስጥ።

12 ይሁንና የይሖዋን ምሕረት በተመለከተ ምን እናውቃለን? ይሖዋ ‘ማንም እንዲጠፋ እንደማይፈልግ’ ያሳየው እንዴት ነው? ከባድ ኃጢአት ለፈጸሙ አንዳንድ ሰዎች ያሳየውን ምሕረት እንመልከት። ንጉሥ ዳዊት ምንዝርንና ነፍስ ግድያን ጨምሮ ከባድ ኃጢአቶችን ፈጽሟል። ያም ቢሆን ዳዊት ንስሐ ስለገባ ይሖዋ በምሕረት ይቅር ብሎታል። (2 ሳሙ. 12:1-13) ንጉሥ ምናሴ በአብዛኛው የሕይወቱ ክፍል እጅግ ክፉ ሰው ነበር። ይሁንና በጣም ክፉ የነበረው ይህ ሰውም እንኳ ንስሐ ሲገባ ይሖዋ ምሕረት በማሳየት ይቅር ብሎታል። (2 ዜና 33:9-16) እነዚህ ምሳሌዎች፣ ይሖዋ ምሕረት ለማሳየት የሚያስችል መሠረት እስካገኘ ድረስ ምሕረት እንደሚያሳይ ያስታውሱናል። እንዲህ ያሉት ሰዎች ከባድ ኃጢአት መፈጸማቸውን ተገንዝበው ንስሐ ስለገቡ ይሖዋ ከሞት ያስነሳቸዋል።

13. (ሀ) ይሖዋ ለነነዌ ሰዎች ምሕረት ያሳያቸው ለምንድን ነው? (ለ) ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ ስለ ነነዌ ሰዎች ምን ብሏል?

13 ይሖዋ ለነነዌ ሰዎች ስላሳየው ምሕረትም እናውቃለን። አምላክ ለዮናስ “ክፋታቸውን አስተውያለሁ” ብሎት ነበር። ሆኖም ከኃጢአታቸው ንስሐ ሲገቡ ይሖዋ በደግነት ይቅር አላቸው። የይሖዋ ምሕረት ከዮናስ እጅግ የሚበልጥ ነበር። ዮናስ በተበሳጨበት ወቅት አምላክ የነነዌ ሰዎች ‘ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ለይተው እንደማያውቁ’ ነግሮታል። (ዮናስ 1:1, 2፤ 3:10፤ 4:9-11) ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ ስለ ይሖዋ ፍትሕና ምሕረት ለማስተማር የእነሱን ታሪክ ምሳሌ አድርጎ ተጠቅሞበታል። ኢየሱስ ንስሐ የገቡት የነነዌ ሰዎች ‘በፍርድ ወቅት እንደሚነሱ’ ተናግሯል።—ማቴ. 12:41

14. ‘የፍርድ ትንሣኤ’ ለነነዌ ሰዎች ምን ትርጉም ይኖረዋል?

14 የነነዌ ሰዎች ‘በፍርድ ወቅት ይነሳሉ’ ሲባል ምን ማለት ነው? ኢየሱስ ወደፊት ‘የፍርድ ትንሣኤ’ እንደሚኖር ተናግሯል። (ዮሐ. 5:29) ይህን ሲል “ጻድቃንም ሆኑ ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች” ስለሚነሱበት የሺህ ዓመት ግዛቱ መናገሩ ነበር። (ሥራ 24:15) ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች የሚያገኙት ትንሣኤ ‘የፍርድ ትንሣኤ’ ነው። ይህም ሲባል ይሖዋና ኢየሱስ የእነዚህን ሰዎች ምግባር እንዲሁም ለሚሰጣቸው መለኮታዊ ትምህርት የሚሰጡትን ምላሽ ይከታተላሉ ማለት ነው። ትንሣኤ ያገኘ አንድ የነነዌ ሰው በንጹሕ አምልኮ ለመካፈል ፈቃደኛ ካልሆነ ‘ጥፋት ይገባዋል’ የሚል ፍርድ ይተላለፍበታል። (ኢሳ. 65:20) ይሖዋን በታማኝነት ለማገልገል የሚመርጡ ሁሉ ግን አዎንታዊ ፍርድ ይሰጣቸዋል። ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ይኖራቸዋል!—ዳን. 12:2

15. (ሀ) ከሰዶምና ከገሞራ ሰዎች መካከል አንዳቸውም ከሞት እንደማይነሱ መናገር የሌለብን ለምንድን ነው? (ለ) በይሁዳ 7 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ እንዴት ልንረዳው ይገባል? (“ ይሁዳ ምን ማለቱ ነበር?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

15 ኢየሱስ የሰዶምና የገሞራ ሰዎች “በፍርድ ቀን” እሱንና ትምህርቱን ለመቀበል ፈቃደኛ ካልሆኑ ሰዎች ይልቅ እንደሚቀልላቸው ተናግሯል። (ማቴ. 10:14, 15፤ 11:23, 24፤ ሉቃስ 10:12) እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነበር? ኢየሱስ በዚህ ወቅት ግነታዊ ዘይቤ እየተጠቀመ እንዳለ እናስብ ይሆናል። ሆኖም ሁኔታው እንደዚያ አይመስልም። ስለ ነነዌ ሰዎች የተናገረው ሐሳብ ቃል በቃል የሚወሰድ እንደሆነ ሁሉ ይሄኛውም ሐሳብ ቃል በቃል የሚወሰድ ይመስላል። e በሁለቱም ቦታዎች ላይ የጠቀሰው ‘የፍርድ ቀን’ ተመሳሳይ እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም። እንደ ነነዌ ነዋሪዎች ሁሉ የሰዶምና የገሞራ ሰዎችም መጥፎ ድርጊት ፈጽመዋል። ሆኖም የነነዌ ሰዎች ንስሐ ለመግባት የሚያስችል አጋጣሚ አግኝተዋል። ከዚህም ሌላ ኢየሱስ ስለ “ፍርድ ትንሣኤ” ምን እንደተናገረ አስታውስ። “ክፉ የሠሩ” ሰዎችም በዚህ ትንሣኤ ውስጥ ይካተታሉ። (ዮሐ. 5:29) ከዚህ አንጻር የሰዶምና የገሞራ ሰዎች የተወሰነ ተስፋ ያላቸው ይመስላል። ከእነሱ መካከል ቢያንስ አንዳንዶቹ ከሞት ይነሱ ይሆናል። እኛም እነሱን ስለ ይሖዋና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የማስተማር አጋጣሚ ልናገኝ እንችላለን።

16. ይሖዋ ማንን ከሞት እንደሚያስነሳ ከሚወስንበት መንገድ ጋር በተያያዘ ምን እናውቃለን? (ኤርምያስ 17:10)

16 ኤርምያስ 17:10ን አንብብ። ይህ ጥቅስ የምናውቃቸውን ነገሮች ጠቅለል አድርጎ ይገልጻል። ይሖዋ ከጥንትም ጀምሮ ‘ልብን ይመረምራል፤ የውስጥ ሐሳብንም ይፈትናል።’ ሁልጊዜ እንደሚያደርገው ሁሉ ወደፊት በሚከናወነው ትንሣኤ ወቅትም “ለእያንዳንዱ እንደ መንገዱ” ይሰጠዋል። ይሖዋ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ጥብቅ ይሆናል፤ የሚቻል በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ ደግሞ ምሕረት ያሳያል። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ በቀጥታ ካልተናገረ በስተቀር አንድ ሰው የትንሣኤ ተስፋ የለውም ብለን መደምደም አይኖርብንም።

“የምድር ሁሉ ዳኛ ትክክል የሆነውን ነገር” ያደርጋል

17. የሞቱ ሰዎች ወደፊት ምን ይጠብቃቸዋል?

17 አዳምና ሔዋን ከሰይጣን ጋር ተባብረው በይሖዋ አምላክ ላይ ካመፁበት ጊዜ አንስቶ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል። “ጠላት” የሆነው ሞት በጣም ብዙ ሰዎችን ቀጥፏል! (1 ቆሮ. 15:26) እነዚህ ሁሉ ሰዎች ወደፊት ምን ይጠብቃቸዋል? የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ታማኝ የክርስቶስ ተከታዮች ማለትም 144,000 ሰዎች ከሞት ተነስተው በሰማይ ላይ የማይሞት ሕይወት ያገኛሉ። (ራእይ 14:1) ይሖዋን የሚወዱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ታማኝ ወንዶችና ሴቶች ትንሣኤ ከሚያገኙት “ጻድቃን” መካከል ይካተታሉ፤ በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛትና በመጨረሻው ፈተና ወቅት ጻድቅ ሆነው ከቀጠሉ ደግሞ በምድር ላይ ለዘላለም ይኖራሉ። (ዳን. 12:13፤ ዕብ. 12:1) በተጨማሪም ይሖዋን አገልግለው የማያውቁ፣ አልፎ ተርፎም “ክፉ የሠሩ” ሰዎችን ጨምሮ “ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች” በሺህ ዓመቱ ግዛት ወቅት አካሄዳቸውን የማስተካከልና ታማኝ የመሆን አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። (ሉቃስ 23:42, 43) ይሁንና አንዳንድ ሰዎች በጣም ክፉ በመሆናቸው እንዲሁም ሆን ብለው በይሖዋና በዓላማዎቹ ላይ በማመፃቸው የተነሳ ይሖዋ እነዚህ ሰዎች ትንሣኤ እንደማያገኙ ወስኗል።—ሉቃስ 12:4, 5

18-19. (ሀ) ይሖዋ በሞቱ ሰዎች ላይ የሚያስተላልፈው ፍርድ ትክክል እንደሆነ መተማመን የምንችለው ለምንድን ነው? (ኢሳይያስ 55:8, 9) (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

18 ይሖዋ ምሕረት ለማሳየትም ሆነ ለማጥፋት የሚያስተላልፈው ማንኛውም ፍርድ ትክክል እንደሆነ ለመተማመን የሚያበቃ ምክንያት አለን? በሚገባ! አብርሃም እንደተገነዘበው ይሖዋ ፍጹም፣ ጥበበኛና መሐሪ የሆነ “የምድር ሁሉ ዳኛ” ነው። ልጁንም አሠልጥኖታል፤ እንዲሁም የመፍረዱን ሥልጣን በሙሉ ለእሱ ሰጥቶታል። (ዮሐ. 5:22) አብም ሆነ ወልድ የእያንዳንዱን ሰው ልብ ማንበብ ይችላሉ። (ማቴ. 9:4) ስለዚህ በእያንዳንዱ ሰው ላይ በሚፈርዱበት ጊዜ “ትክክል የሆነውን ነገር” ያደርጋሉ!

19 ይሖዋ ምንጊዜም ከሁሉ የተሻለውን ነገር እንደሚያደርግ ለመተማመን ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። እኛ የመፍረድ ብቃት እንደሌለን አምነን እንቀበላለን። እሱ ግን ብቃቱ አለው! (ኢሳይያስ 55:8, 9ን አንብብ።) ስለዚህ የመፍረዱን ሥራ በሙሉ ለእሱ እንዲሁም የአባቱን ፍትሕና ምሕረት ፍጹም በሆነ መንገድ ላንጸባረቀው ለንጉሣችን ለኢየሱስ እንተዋለን። (ኢሳ. 11:3, 4) ይሁንና በታላቁ መከራ ወቅት ስለሚተላለፈው መለኮታዊ ፍርድ ምን ማለት እንችላለን? ከዚህ ጋር በተያያዘ ምን አናውቅም? ምንስ እናውቃለን? የሚቀጥለው ርዕስ እነዚህን ጥያቄዎች ይመልስልናል።

መዝሙር 57 ለሁሉም ዓይነት ሰዎች መስበክ

b አዳምን፣ ሔዋንንና ቃየንን በተመለከተ የጥር 1, 2013 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 12 የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።

c በዮሐንስ 17:12 ላይ የሚገኘው ‘የጥፋት ልጅ’ የሚለው አገላለጽ ይሁዳ ሲሞት ዘላለማዊ ጥፋት እንደሚደርስበት ማለትም የትንሣኤ ተስፋ እንደማይኖረው ያመለክታል።

d jw.org ላይ የሚገኘውን “ይቅር የማይባል ኃጢአት አለ?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

e ግነታዊ ዘይቤ አንድን ነጥብ ለማስተላለፍ ሲባል እውነታውን አጋንኖ ወይም አግዝፎ ማቅረብን ያመለክታል። ሆኖም ኢየሱስ ስለ ሰዶምና ገሞራ ሰዎች የተናገረው ሐሳብ ቃል በቃል የሚወሰድ ይመስላል፤ ስለዚህ እንደ ግነታዊ ዘይቤ መቆጠር የለበትም።