በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተፈታታኝ ሁኔታ በሚያጋጥመን ጊዜም ልካችንን ማወቅ

ተፈታታኝ ሁኔታ በሚያጋጥመን ጊዜም ልካችንን ማወቅ

“ልክህን አውቀህ ከአምላክህ ጋር [ሂድ]።”—ሚክ. 6:8

መዝሙሮች፦ 48, 80

1-3. ከይሁዳ የመጣው ስሙ ያልተጠቀሰ ነቢይ የሠራው ስህተት ምን ነበር? ይህስ ምን አስከትሎበታል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

ኢዮርብዓም ንጉሥ በነበረበት ዘመን ይሖዋ ለዚህ ከሃዲ ንጉሥ ከባድ የፍርድ መልእክት እንዲያስተላልፍ አንድ ነቢይ ከይሁዳ ላከ። ትሑት የነበረው ይህ ነቢይ የይሖዋን መልእክት በታማኝነት ያደረሰ ሲሆን ይሖዋም አገልጋዩን ከንጉሡ አስፈሪ ቁጣ ጠብቆታል።—1 ነገ. 13:1-10

2 ነቢዩ ወደ ቤቱ ሲመለስ በቤቴል አቅራቢያ ከሚኖር አንድ አረጋዊ ሰው ጋር በድንገት ተገናኘ። አረጋዊው ሰው የይሖዋ ነቢይ እንደሆነ ተናገረ። ሰውዬው፣ ወጣቱን ነቢይ በማታለል በእስራኤል ‘ምግብ እንዳይበላና ውኃ እንዳይጠጣ’ እንዲሁም ‘በመጣበት መንገድ እንዳይመለስ’ ይሖዋ የሰጠውን ግልጽ መመሪያ እንዲጥስ አደረገው። ይሖዋ በዚህ አልተደሰተም። ይህ የይሖዋ ነቢይ ወደ ቤቱ ሲመለስ አንድ አንበሳ መንገድ ላይ አገኘውና ገደለው።—1 ነገ. 13:11-24

3 በአንድ ወቅት ልኩን ያውቅ የነበረው ይህ ነቢይ የዚያን አታላይ አረጋዊ ቃል በመስማት እንዲህ ያለ የእብሪት እርምጃ የወሰደው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ የሚናገረው ነገር የለም። ሆኖም ይህ ነቢይ ‘ልኩን አውቆ ከአምላክ ጋር መሄድ’ እንዳለበት ጨርሶ የዘነጋ ይመስላል። (ሚክያስ 6:8ን አንብብ።) ‘ከይሖዋ ጋር መሄድ’ የሚለው አገላለጽ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት በአምላክ መታመንን፣ ሉዓላዊነቱን መደገፍን እንዲሁም አመራሩን መከተልን ለማመልከት ነው። ልኩን የሚያውቅ ሰው አፍቃሪና ሁሉን ቻይ ወደሆነው አባቱ አዘውትሮ መጸለይ እንደሚችል ደግሞም ይህን ማድረግ እንዳለበት በሚገባ ይገነዘባል። ይህ ነቢይ ይሖዋ መመሪያዎቹን ግልጽ እንዲያደርግለት መጠየቅ ይችል ነበር፤ ሆኖም ቅዱሳን መጻሕፍት እንዲህ እንዳደረገ አይናገሩም። እኛም አንዳንድ ጊዜ ከባድ ውሳኔዎችን ማድረግ የሚጠይቁ ሁኔታዎች ያጋጥሙን ይሆናል፤ በዚህ ወቅት ትክክለኛው ውሳኔ የቱ እንደሆነ ግልጽ ላይሆንልን ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን ልካችንን በማወቅ የይሖዋን አመራር መፈለጋችን ከባድ ስህተቶችን ከመሥራት ይጠብቀናል።

4. በዚህ የጥናት ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?

4 ቀደም ባለው ርዕስ ላይ፣ ልክን ማወቅ በአሁኑ ጊዜም ለክርስቲያኖች አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነና ይህን ባሕርይ ማንጸባረቅ ምን ነገሮችን እንደሚያካትት ተምረናል። ነገር ግን ይህን ባሕርይ ማሳየት ተፈታታኝ እንዲሆንብን የሚያደርጉ ምን ሁኔታዎች ያጋጥሙናል? ይህን አስፈላጊ ባሕርይ ማዳበር የምንችለውስ እንዴት ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት በቅድሚያ ልካችንን ማወቅ ተፈታታኝ እንዲሆንብን የሚያደርጉ ሦስት የተለመዱ ሁኔታዎችን እንመለከታለን፤ እንዲሁም ከእያንዳንዱ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ጥበብ የሚንጸባረቅበት እርምጃ መውሰድ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን።—ምሳሌ 11:2

ያለንበት ሁኔታ ሲቀየር

5, 6. ቤርዜሊ ልኩን እንደሚያውቅ ያሳየው እንዴት ነው?

5 ያለንበት ሁኔታ ሲቀየር ወይም ተጨማሪ ኃላፊነት ሲሰጠን ልካችንን ማወቅ ተፈታታኝ ሊሆንብን ይችላል። የ80 ዓመት አረጋዊ የሆነው ቤርዜሊ፣ ዳዊት ቤተ መንግሥቱ ውስጥ አብሮት እንዲኖር ግብዣ ሲያቀርብለት ታላቅ ክብር ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው። ቤርዜሊ የዳዊትን ግብዣ መቀበሉ ከንጉሡ ጋር ይበልጥ ለመቀራረብ ያስችለው ነበር። ሆኖም ቤርዜሊ ግብዣውን አልተቀበለም። ለምን? ምክንያቱም ዕድሜው ገፍቶ ስለነበር ለንጉሡ ሸክም መሆን አልፈለገም። ስለዚህ ቤርዜሊ በእሱ ምትክ ኪምሃም (ልጁ ሳይሆን አይቀርም) እንዲሄድ ሐሳብ አቀረበ።—2 ሳሙ. 19:31-37

6 ቤርዜሊ ጥሩ ውሳኔ እንዲያደርግ የረዳው ልኩን ማወቁ ነው። የዳዊትን ግብዣ ያልተቀበለው ተጨማሪ ኃላፊነት ለመሸከም ብቁ እንዳልሆነ ስለተሰማው አሊያም የጡረታ ዘመኑን ዘና ብሎ ማሳለፍ ስለፈለገ አልነበረም። ይህን ያደረገው ያለበት ሁኔታ እንደተቀየረና የአቅም ገደብ እንዳለበት አምኖ ስለተቀበለ ነው። ከአቅሙ በላይ የሆነ የኃላፊነት ሸክም መሸከም አልፈለገም። (ገላትያ 6:4, 5ን አንብብ።) ሥልጣን፣ ኃላፊነት ወይም እውቅና በማግኘት ላይ ትኩረት ካደረግን በውስጣችን የራስ ወዳድነትና የፉክክር መንፈስ ሊያቆጠቁጥ ይችላል፤ ይህም የኋላ ኋላ ለሐዘን ይዳርገናል። (ገላ. 5:26) ከዚህ በተቃራኒ ግን ልካችንን ማወቃችን ከወንድሞቻችን ጋር ተባብረን በመሥራት፣ ችሎታችንንና አቅማችንን ለአምላክ ክብር ለማምጣትና ሌሎችን ለመርዳት እንድንጠቀምበት ያነሳሳናል።—1 ቆሮ. 10:31

7, 8. ልካችንን ማወቃችን በራሳችን ከመታመን እንድንርቅ የሚረዳን እንዴት ነው?

7 ብዙውን ጊዜ ተጨማሪ ኃላፊነት ሲሰጠን ከቀድሞው የበለጠ ሥልጣን ይኖረናል፤ ይህ ደግሞ ልክን ማወቅ ተፈታታኝ እንዲሆንብን ያደርጋል። ነህምያ በኢየሩሳሌም ያሉት የአምላክ ሕዝቦች እየደረሰባቸው ያለውን መከራ በሰማበት ወቅት ወደ ይሖዋ ልባዊ ጸሎት አቀረበ። (ነህ. 1:4, 11) ንጉሥ አርጤክስስ ነህምያን የአውራጃው ገዢ አድርጎ ሲሾመው ይሖዋ ለነህምያ ጸሎት መልስ እንደሰጠው ግልጽ ነበር። ነህምያ ከፍተኛ ኃላፊነት፣ ሀብትና ትልቅ ሥልጣን ቢኖረውም በራሱ ተሞክሮና ችሎታ ጨርሶ አልታመነም። ከዚህ ይልቅ ከአምላክ ጋር መሄዱን ቀጥሏል። የአምላክን ሕግ በማንበብ ምንጊዜም የይሖዋን አመራር እንደሚፈልግ አሳይቷል። (ነህ. 8:1, 8, 9) ነህምያ ሌሎችን የሚጨቁን ሰው አልነበረም፤ እንዲያውም በራሱ ወጪ ያገለግላቸው ነበር።—ነህ. 5:14-19

8 ነህምያ የተወው ምሳሌ፣ ልካችንን ማወቃችን የሥራ ምድባችን ሲለወጥ ወይም ተጨማሪ ኃላፊነት ሲሰጠን በራሳችን ከመታመን እንድንቆጠብ የሚረዳን እንዴት እንደሆነ ያሳያል። አንድ ሽማግሌ ባካበተው ልምድ ብቻ በመተማመን በቅድሚያ ይሖዋን በጸሎት ሳይጠይቅ የጉባኤ ጉዳዮችን ማከናወን ሊጀምር ይችላል። አንዳንዶች ደግሞ ቀድመው ውሳኔ ካደረጉ በኋላ ይሖዋ ውሳኔያቸውን እንዲባርክላቸው ይጸልያሉ። ሆኖም ይህ ልክን ማወቅ ሊባል ይችላል? ልኩን የሚያውቅ ሰው ምንጊዜም በይሖዋ ፊትና በአምላክ ዝግጅት ውስጥ ያለውን ቦታ ይገነዘባል። ከይሖዋ አንጻር ሲታይ የእኛ ችሎታ እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ እናውቃለን። በተለይም ያጋጠመን ሁኔታ ወይም ችግር ከዚህ በፊት ያለፍንበት ከሆነ በራሳችን እንዳንታመን ልንጠነቀቅ ይገባል። (ምሳሌ 3:5, 6ን አንብብ።) ሁላችንም የአምላክ ቤተሰብ አባላት ነን፤ በመሆኑም ተጨማሪ ሥልጣን ለማግኘት ወይም ከሌሎች ልቀን ለመታየት ከመሞከር ይልቅ የቤተሰብና የጉባኤ ኃላፊነቶቻችንን በመወጣት ላይ ትኩረት ልናደርግ ይገባል።—1 ጢሞ. 3:15

ትችት ሲሰነዘርብን ወይም አድናቆት ሲቸረን

9, 10. ልክን ማወቅ ተገቢ ያልሆነ ትችት ሲሰነዘርብን የሚረዳን እንዴት ነው?

9 ተገቢ ያልሆነ ትችት ሲሰነዘርብን ስሜታችንን መቆጣጠር አስቸጋሪ ሊሆንብን ይችላል። ሐና ጣውንቷ ፍናና ሁሌ በነገር እየጎነተለች ስለምታበሳጫት ብዙ ጊዜ ታለቅስ ነበር። ሐና ባለቤቷ ይወዳት የነበረ ቢሆንም መሃን ነበረች። በአንድ ወቅት ደግሞ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ እየጸለየች ሳለ ሊቀ ካህናቱ ኤሊ የሰከረች ስለመሰለው ወቀሳ ሰነዘረባት። ሐና በዚህ ወቅት ምን ተሰምቷት ሊሆን እንደሚችል እስቲ አስበው! ያም ቢሆን ሐና ልኳን የምታውቅ ሰው ስለነበረች ስሜቷን መቆጣጠርና ለኤሊ በአክብሮት ምላሽ መስጠት ችላለች። ሐና ያቀረበችው ልብ የሚነካ ጸሎት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል። ጸሎቷ እምነቷን፣ አመስጋኝነቷንና አድናቆቷን በሚገልጹ ቃላት የተሞላ ነው።—1 ሳሙ. 1:5-7, 12-16፤ 2:1-10

10 በተጨማሪም ልካችንን ማወቃችን “ምንጊዜም ክፉውን በመልካም [ማሸነፍ]” እንድንችል ይረዳናል። (ሮም 12:21) በሰይጣን ሥርዓት ውስጥ ስንኖር ግፍ ሲፈጸም ማየት የተለመደ ነገር ነው፤ ስለዚህ በክፉ አድራጊዎች ምግባር ከልክ በላይ እንዳንበሳጭ ልንጠነቀቅ ይገባል። (መዝ. 37:1) ችግሩ የተፈጠረው ከመንፈሳዊ ወንድሞቻችን ወይም እህቶቻችን ጋር በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ ቁስሉ ይበልጥ ሊሰማን ይችላል። ልኩን የሚያውቅ ሰው እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመው የኢየሱስን ምሳሌ ይከተላል። ኢየሱስ “ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም። . . . ከዚህ ይልቅ በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን በአደራ [ሰጥቷል]።” (1 ጴጥ. 2:23) ኢየሱስ በቀል የይሖዋ እንደሆነ ያውቅ ነበር። (ሮም 12:19) ክርስቲያኖችም ትሑት እንዲሆኑ እንዲሁም ‘ክፉን በክፉ እንዳይመልሱ’ ምክር ተሰጥቷቸዋል።—1 ጴጥ. 3:8, 9

11, 12. (ሀ) ከልክ ያለፈ አድናቆት ወይም ምስጋና ሲቀርብልን ልካችንን ማወቃችን የሚረዳን እንዴት ነው? (ለ) ልክን ማወቅ በአለባበስና በአጋጌጥ ምርጫችን እንዲሁም በምናሳየው ምግባር ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር ይገባል?

11 ከልክ ያለፈ አድናቆት በሚቸረን ወይም ምስጋና በሚቀርብልን ጊዜም ልካችንን ማወቅ ተፈታታኝ ሊሆንብን ይችላል። አስቴር፣ የነበረችበት ሁኔታ በአንድ ጊዜ ሲቀየር የሰጠችውን ግሩም ምላሽ እንመልከት። አስቴር በጣም ውብ ሴት ነበረች፤ ለአንድ ዓመት ያህል ደግሞ ለየት ያለ የውበት እንክብካቤ አግኝታለች። ከመላው የፋርስ ግዛት ከመጡና የንጉሡን ትኩረት ለማግኘት ከሚፎካከሩ በርካታ ወጣት ሴቶች ጋር በየዕለቱ ትገናኝ ነበር። ያም ቢሆን አስቴር ምንጊዜም ሥርዓታማና ጭምት ሴት ነበረች። አርጤክስስ ንግሥት አድርጎ ከመረጣት በኋላም እንኳ ኩሩ ወይም ትዕቢተኛ አልሆነችም።—አስ. 2:9, 12, 15, 17

አለባበሳችንና አጋጌጣችን ለይሖዋና ለሌሎች አክብሮት እንዳለን ያሳያል? ወይስ ልካችንን በማወቅ ረገድ ችግር እንዳለብን ይጠቁማል? (አንቀጽ 12ን ተመልከት)

12 ልካችንን ማወቃችን ምንጊዜም ሥርዓታማ የሆነ አለባበስና አጋጌጥ እንዲኖረን እንዲሁም ተገቢ ምግባር እንድናሳይ ይረዳናል። የሰዎችን ልብ መማረክ የምንችለው ጉራ በመንዛት ወይም አላስፈላጊ ትኩረት ወደ ራሳችን በመሳብ ሳይሆን “የሰከነና ገር መንፈስ” በማሳየት እንደሆነ እንገነዘባለን። (1 ጴጥሮስ 3:3, 4ን አንብብ፤ ኤር. 9:23, 24) በልባችን ውስጥ የኩራት ስሜት ካለ ውሎ አድሮ በድርጊታችን መታየቱ አይቀርም። ለምሳሌ ያህል፣ ልዩ መብት እንዳለን፣ አንዳንድ ሚስጥሮችን እንደምናውቅ ወይም ኃላፊነት ካላቸው ወንድሞች ጋር የተለየ ቅርርብ እንዳለን ጠቆም እናደርግ ይሆናል። አሊያም ደግሞ የሌሎች አስተዋጽኦ ያለበት አንድ ሐሳብ ወይም ድርጊት የእኛ ብቻ እንደሆነ በሚያስመስል መልኩ ልናወራ እንችላለን። በዚህ ረገድም ቢሆን ኢየሱስ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል። ኢየሱስ የተናገረው አብዛኛው ነገር በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተወሰደ ነበር። ኢየሱስ በንግግሩ ልኩን እንደሚያውቅ አሳይቷል፤ ይህን ያደረገው አድማጮቹ የሚናገረው ነገር በራሱ እውቀትና ጥበብ ላይ የተመሠረተ ሳይሆን ከይሖዋ የመጣ እንደሆነ እንዲያውቁ ይፈልግ ስለነበር ነው።—ዮሐ. 8:28

ውጤቱን በእርግጠኝነት በማናውቅበት ጊዜ

13, 14. ልክን ማወቅ ጥሩ ውሳኔ እንድናደርግ የሚረዳን እንዴት ነው?

13 ውሳኔዎችን በምናደርግበት ጊዜም ልካችንን ማወቅ ተፈታታኝ ሊሆንብን ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ በቂሳርያ በነበረበት ወቅት፣ ወደ ኢየሩሳሌም ከሄደ ለእስር እንደሚዳረግ ነቢዩ አጋቦስ ነግሮት ነበር። አልፎ ተርፎም ሊገደል ይችላል። ወንድሞች ሁኔታው ስላስፈራቸው ጳውሎስን እንዳይሄድ ይለምኑት ጀመር። ጳውሎስ ግን ወንድሞች ባቀረቡለት ሐሳብ አልተስማማም። ጳውሎስ ከልክ በላይ በራሱ አልታመነም፤ በሌላ በኩል ደግሞ በፍርሃት አልተሽመደመደም። ልኩን በማወቅ ሙሉ በሙሉ በይሖዋ የታመነ ሲሆን ይሖዋ የፈቀደውን ነገር ሁሉ ለመቀበል ተዘጋጅቶ ነበር፤ በመሆኑም ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ወሰነ። በዚህ ጊዜ ወንድሞች፣ ጳውሎስ ያደረገውን ውሳኔ መቃወማቸውን በመተው ልካቸውን እንደሚያውቁ አሳይተዋል።—ሥራ 21:10-14

14 ውሳኔያችን የሚያስከትለውን ውጤት በእርግጠኝነት ማወቅ ወይም መቆጣጠር በማንችልበት ጊዜም እንኳ ልክን ማወቅ ትክክለኛውን ውሳኔ እንድናደርግ ይረዳናል። ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ ዓይነት የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፍ ለመካፈል ወሰንን እንበል፤ የጤና ችግር ቢያጋጥመንስ? በዕድሜ የገፉ ወላጆቻችን የእኛ እንክብካቤ ቢያስፈልጋቸውስ? ደግሞስ በዕድሜ ከገፋን በኋላ ማን ይንከባከበናል? የቱንም ያህል ብንጸልይ ወይም ምርምር ብናደርግ እንዲህ ላሉት ጥያቄዎች የተሟላ መልስ ማግኘት አንችልም። (መክ. 8:16, 17) በይሖዋ ላይ ያለን እምነት የአቅም ገደብ ያለብን መሆኑን እንድናውቅ ብቻ ሳይሆን ይህን አምነን እንድንቀበልም ይረዳናል። ስለ ጉዳዩ ምርምር ካደረግን፣ ሌሎችን ካማከርንና የይሖዋን አመራር ለማግኘት ከጸለይን በኋላ የአምላክ መንፈስ ከሚሰጠን አመራር ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። (መክብብ 11:4-6ን አንብብ።) በዚህ መንገድ ውሳኔ ካደረግን ይሖዋ ውሳኔያችንን ሊባርከው አሊያም ደግሞ በግባችን ላይ ማስተካከያ እንድናደርግ ሊረዳን ይችላል።—ምሳሌ 16:3, 9

ልክን ማወቅን ማዳበር

15. ስለ ይሖዋ ማሰላሰላችን ምንጊዜም ትሑት እንድንሆን የሚረዳን እንዴት ነው?

15 ልክን ማወቅ ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት ተመልክተናል፤ ታዲያ ይህን ባሕርይ ይበልጥ ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? አራት መንገዶችን እንመልከት። አንደኛ፣ እጅግ አስደናቂ በሆኑት የይሖዋ ባሕርያትና እሱ ባለው ከፍተኛ ቦታ ላይ በአድናቆት ማሰላሰላችን ልክን ማወቅን እንድናዳብርና ይሖዋን ይበልጥ እንድንፈራው ይረዳናል። (ኢሳ. 8:13) የምንጓዘው ከአንድ መልአክ ወይም ከተራ ሰው ጋር ሳይሆን ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ጋር እንደሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። ይህን መገንዘባችን ‘ከኃይለኛው የአምላክ እጅ በታች ራሳችንን ዝቅ እንድናደርግ’ ያነሳሳናል።—1 ጴጥ. 5:6

16. ይሖዋ ባሳየን ፍቅር ላይ ማሰላሰላችን ልካችንን እንድናውቅ የሚረዳን እንዴት ነው?

16 ሁለተኛ፣ ይሖዋ ባሳየን ፍቅር ላይ ማሰላሰላችን ልክን ማወቅን እንድናዳብር ይረዳናል። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ እምብዛም ክብር የማይሰጣቸውን የአካል ክፍሎች ይሖዋ ‘ታላቅ ክብር እንዳለበሳቸው’ ገልጿል። (1 ቆሮ. 12:23, 24) በተመሳሳይም፣ የአቅም ገደቦች ቢኖሩብንም ይሖዋ ለእያንዳንዳችን ያስብልናል። ከሌሎች ጋር አያወዳድረንም፤ እንዲሁም ስህተት በምንሠራበት ጊዜም እንኳ ለእኛ ፍቅር ማሳየቱን አያቋርጥም። ይሖዋ እንደሚወደን እርግጠኞች ስለሆንን በእሱ ቤት ውስጥ በየትኛውም ቦታ ቢሆን ተረጋግተን እናገለግላለን።

17. በወንድሞቻችን አዎንታዊ ጎን ላይ ለማተኮር ጥረት ማድረጋችን ምን እንድናደርግ ያነሳሳናል?

17 ሦስተኛ፣ ልክ እንደ ይሖዋ ሌሎች ባላቸው አዎንታዊ ጎን ላይ ማተኮራችን በይሖዋ አገልግሎት ውስጥ ለተሰጠን ቦታ ያለን አድናቆት እንዲጨምር ያደርጋል። የሰዎችን ትኩረት ለመሳብ ወይም በሌሎች ላይ ለመሠልጠን ከመሞከር ይልቅ ልካችንን በማወቅ የሌሎችን ምክር እንጠይቃለን፤ እንዲሁም የሚሰጡንን ሐሳብ እንቀበላለን። (ምሳሌ 13:10) ወንድሞቻችን መብት ሲያገኙ አብረናቸው እንደሰታለን። በተጨማሪም ይሖዋ ‘በዓለም ዙሪያ በመላው የወንድማማች ማኅበር ውስጥ ያሉትን ወንድሞቻችንን’ እንደባረካቸው ስናይ እሱን ለማወደስ እንገፋፋለን።—1 ጴጥ. 5:9

18. ልካችንን የምናውቅ ሰዎች ለመሆን ሕሊናችንን ማሠልጠን የምንችለው እንዴት ነው?

18 አራተኛ፣ ሕሊናችንን በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ስናሠለጥን ይበልጥ ልካችንን እያወቅን እንሄዳለን። ልካችንን በማወቅ ነገሮችን ከይሖዋ አመለካከት አንጻር ለመመልከት ጥረት ማድረጋችን ደግሞ አምላክን የሚያስደስቱ ውሳኔዎችን ለማድረግ ይረዳናል። አዘውትረን በማጥናት፣ በመጸለይ እንዲሁም የተማርነውን ተግባራዊ በማድረግ ሕሊናችንን ቀስ በቀስ ማሠልጠን እንችላለን። (1 ጢሞ. 1:5) በተጨማሪም ለሌሎች ቅድሚያ መስጠትን እንማራለን። እኛ ድርሻችንን ከተወጣን ይሖዋ ልክን ማወቅንና ሌሎች አምላካዊ ባሕርያትን እንድናዳብር በመርዳት ‘ሥልጠናችን እንዲጠናቀቅ’ እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል።—1 ጴጥ. 5:10

19. ለዘላለም ልካችንን አውቀን እንድንሄድ ምን ይረዳናል?

19 ከይሁዳ የመጣው ስሙ ያልተጠቀሰ ነቢይ የፈጸመው አንድ የእብሪት ድርጊት ሕይወቱንና ከአምላክ ጋር የነበረውን ጥሩ ዝምድና አሳጥቶታል። እኛ ግን ተፈታታኝ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙን ጊዜም እንኳ ልካችንን እንደምናውቅ ማሳየት እንችላለን። ከእኛ በፊት የነበሩ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች እንዲሁም በዘመናችን ያሉ ልካቸውን የሚያውቁ ክርስቲያኖች ይህን ማድረግ እንደሚቻል አሳይተዋል። ከይሖዋ ጋር መሄዳችንን በቀጠልን መጠን ይበልጥ ልካችንን የምናውቅ ሰዎች እንሆናለን። (ምሳሌ 8:13) አሁን ያለን ቦታ ምንም ይሁን ምን ከይሖዋ ጋር መሄድ በራሱ አስደናቂና ወደር የማይገኝለት መብት ነው። ለዚህ መብት ከፍተኛ አድናቆት ይኑረን፤ በተጨማሪም ለዘላለም ልካችንን አውቀን ከይሖዋ ጋር ለመሄድ የተቻለንን ጥረት እናድርግ።