በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እነዚህን ነገሮች “ታማኝ ለሆኑ ሰዎች አደራ ስጥ”

እነዚህን ነገሮች “ታማኝ ለሆኑ ሰዎች አደራ ስጥ”

“ከእኔ የሰማኸውንና ብዙዎች የመሠከሩለትን ነገር፣ ታማኝ ለሆኑ ሰዎች አደራ ስጥ፤ እነሱም በበኩላቸው ሌሎችን ለማስተማር ብቃቱን ያሟላሉ።”—2 ጢሞ. 2:2

መዝሙሮች፦ 103, 101

1, 2. ብዙ ሰዎች ለሥራቸው ምን አመለካከት አላቸው?

አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ራሳቸውን የሚለኩት ከሚያከናውኑት ሥራ አንጻር ነው። ብዙዎች የአንድን ሰው ማንነት የሚመዝኑት በተሰማራበት የሙያ መስክ ወይም ባለው ኃላፊነት ነው። እንዲያውም በአንዳንድ ባሕሎች ሰዎች አንድን ግለሰብ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲተዋወቁ ከሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች መካከል አንዱ “ሥራህ ምንድን ነው?” የሚል ነው።

2 መጽሐፍ ቅዱስም ሰዎችን ካከናወኑት ሥራ አንጻር የሚገልጽበት ጊዜ አለ። ለምሳሌ “ቀረጥ ሰብሳቢው ማቴዎስ፣” ‘ቆዳ ፋቂው ስምዖን’ እንዲሁም “የተወደደው ሐኪም ሉቃስ” በማለት ይናገራል። (ማቴ. 10:3፤ ሥራ 10:6፤ ቆላ. 4:14) አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ያላቸው መንፈሳዊ መብት ወይም ኃላፊነት ከስማቸው ጋር አብሮ ተጠቅሷል። ንጉሥ ዳዊትን፣ ነቢዩ ኤልያስን እንዲሁም ሐዋርያው ጳውሎስን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ ሰዎች አምላክ የሰጣቸውን ኃላፊነት ከፍ አድርገው ተመልክተውታል። እኛም ያሉንን የአገልግሎት መብቶች በአድናቆት ልንመለከት ይገባል።

3. በዕድሜ የገፉ ወንድሞች ወጣቶችን ማሠልጠናቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

3 ብዙዎቻችን ሥራችንን የምንወደው ከመሆኑም ሌላ ዕድሜ ልካችንን ብንሠራው ደስ ይለናል። የሚያሳዝነው ግን ከአዳም ጊዜ አንስቶ እያንዳንዱ ትውልድ ያረጅና በሌላ ትውልድ ይተካል። (መክ. 1:4) ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ እንዲህ ያለው ለውጥ እውነተኛ ክርስቲያኖች ለየት ያለ ተፈታታኝ ሁኔታ እንዲያጋጥማቸው አድርጓል። የይሖዋ ሕዝቦች የሚያከናውኑት ሥራ ስፋት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። የይሖዋ ድርጅት፣ ምሥራቹን በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች ለማዳረስ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን እየተጠቀመ ነው። አንዳንድ በዕድሜ የገፉ ወንድሞች እንዲህ ካለው ለውጥ ጋር እኩል መራመድ ከባድ ሊሆንባቸው ይችላል። (ሉቃስ 5:39) ይህን ብንተወው እንኳ፣ ወጣቶች በዕድሜ ከገፉት አንጻር ሲታይ የተሻለ ኃይልና ጥንካሬ እንዳላቸው የታወቀ ነው። (ምሳሌ 20:29) በመሆኑም በዕድሜ የገፉ ወንድሞች፣ ወጣቶች * ተጨማሪ ኃላፊነት እንዲቀበሉ ማዘጋጀታቸው ፍቅር የሚንጸባረቅበትና ምክንያታዊ ነው።—መዝሙር 71:18ን አንብብ።

4. አንዳንዶች ለሌሎች ኃላፊነት መስጠት የሚከብዳቸው ለምንድን ነው? (“ አንዳንዶች ኃላፊነት ከመስጠት ወደኋላ የሚሉት ለምንድን ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

4 በኃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ ወንድሞች፣ ለወጣቶች ኃላፊነት መስጠት ሊከብዳቸው ይችላል። አንዳንዶች የሚወዱትን መብት እንዳያጡ ይሰጋሉ። ሌሎች ደግሞ እነሱ ካልተቆጣጠሩት ሥራው በትክክል እንደማይሠራ ያስባሉ። አንዳንዶች ደግሞ ሌላ ሰው የሚያሠለጥኑበት ጊዜ እንደሌላቸው ይሰማቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ወጣቶች ተጨማሪ ኃላፊነት ሳይሰጣቸው ሲቀር ትዕግሥት እንዳያጡ መጠንቀቅ አለባቸው።

5. በዚህ የጥናት ርዕስ ላይ የትኞቹን ነጥቦች እንመለከታለን?

5 እስቲ ለሌሎች ኃላፊነት የመስጠትን ጉዳይ ከሁለት አቅጣጫ እንመልከተው። አንደኛ፣ በዕድሜ የገፉ ወንድሞች ወጣቶች ተጨማሪ ኃላፊነት ለመቀበል ብቁ እንዲሆኑ ማሠልጠን የሚችሉት እንዴት እንደሆነና ይህን ማድረጋቸው አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነ እንመለከታለን። (2 ጢሞ. 2:2) ሁለተኛ፣ ወጣት ወንድሞች ተሞክሮ ካላቸው ወንድሞች ጋር አብረው ሲሠሩ እንዲሁም ከእነሱ ሥልጠና ሲያገኙ ትክክለኛ አመለካከት መያዝ ያለባቸው ለምን እንደሆነ እንመረምራለን። በቅድሚያ ግን ንጉሥ ዳዊት፣ ልጁን ለአንድ ትልቅ ኃላፊነት ብቁ እንዲሆን የረዳው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።

ዳዊት ሰለሞንን አዘጋጅቶታል እንዲሁም ደግፎታል

6. ንጉሥ ዳዊት ምን ማድረግ ፈልጎ ነበር? ይሖዋስ ምን ምላሽ ሰጠው?

6 ዳዊት በርካታ ዓመታትን በስደት ካሳለፈ በኋላ ንጉሥ ሆኖ ምቹ በሆነ ቤት ውስጥ መኖር ጀመረ። ዳዊት ለይሖዋ አገልግሎት የሚውል “ቤት” ወይም ቤተ መቅደስ አለመኖሩ ስላሳሰበው ቤተ መቅደስ ለመሥራት ፈለገ። በመሆኑም ለነቢዩ ናታን እንዲህ ሲል ነገረው፦ “የይሖዋ የቃል ኪዳኑ ታቦት በድንኳን ውስጥ ተቀምጦ ሳለ ይኸው እኔ ከአርዘ ሊባኖስ በተሠራ ቤት ውስጥ እየኖርኩ ነው።” ናታንም “እውነተኛው አምላክ ከአንተ ጋር ስለሆነ በልብህ ያለውን ነገር ሁሉ አድርግ” አለው። ሆኖም ይሖዋ ከዚህ የተለየ መመሪያ አስተላለፈ። “የምኖርበትን ቤት የምትሠራልኝ አንተ አይደለህም” ብሎ ለዳዊት እንዲነግረው ናታንን አዘዘው። ይሖዋ ዳዊትን መባረኩን እንደሚቀጥል ቃል የገባለት ቢሆንም ቤተ መቅደሱን የሚገነባው ግን እሱ ሳይሆን ልጁ ሰለሞን እንደሆነ ገለጸለት። በዚህ ጊዜ ዳዊት ምን ምላሽ ሰጠ?—1 ዜና 17:1-4, 11, 12፤ 29:1

7. ዳዊት ይሖዋ ለሰጠው መመሪያ ምን ምላሽ ሰጠ?

7 ዳዊት ለቤተ መቅደሱ ግንባታ የሚመሰገነው እሱ እንደማይሆን ቢያውቅም ለግንባታው ድጋፍ ከመስጠት ወደኋላ አላለም። ደግሞም ሕንፃው የተጠራው የዳዊት ሳይሆን የሰለሞን ቤተ መቅደስ ተብሎ ነው። ዳዊት የልቡን ፍላጎት ማሳካት ባለመቻሉ አዝኖ ሊሆን ቢችልም የግንባታ ሥራውን ሙሉ በሙሉ ደግፏል። በራሱ ተነሳሽነት ግንባታውን የሚያከናውኑ ሠራተኞችን ያደራጀ ሲሆን ለግንባታው የሚሆን ብረት፣ መዳብ፣ ብር፣ ወርቅ እንዲሁም የአርዘ ሊባኖስ ሳንቃዎችን አከማችቷል። በተጨማሪም ሰለሞንን እንዲህ በማለት አበረታቶታል፦ “አሁንም ልጄ ሆይ፣ ይሖዋ ከአንተ ጋር ይሁን፤ ስለ አንተም በተናገረው መሠረት ተሳክቶልህ የአምላክህን የይሖዋን ቤት ለመሥራት ያብቃህ።”—1 ዜና 22:11, 14-16

8. ዳዊት ልጁ ሰለሞን ብቁ እንዳልሆነ ሊያስብ ይችል የነበረው ለምንድን ነው? ሆኖም ምን አድርጓል?

8 አንደኛ ዜና መዋዕል 22:5ን አንብብ። ዳዊት ልጁ ሰለሞን እንዲህ ያለውን ከባድ ሥራ ለመምራት ብቁ እንዳልሆነ ሊያስብ ይችል ነበር። ምክንያቱም ቤተ መቅደሱ “እጅግ የሚያምር” መሆን ይኖርበታል፤ ሰለሞን ደግሞ በዚያ ወቅት ‘ገና ወጣትና ተሞክሮ የሌለው’ ነበር። ሆኖም ዳዊት፣ ሰለሞን የተሰጠውን ሥራ መወጣት እንዲችል ይሖዋ እንደሚረዳው ተገንዝቦ ነበር። በመሆኑም ግንባታውን ለመደገፍ ማከናወን በሚችለው ነገር ላይ ትኩረት በማድረግ ለግንባታው የሚያስፈልገውን ቁሳቁስ በብዛት ማሰባሰብ ጀመረ።

ሌሎችን በማሠልጠን ተደሰቱ

ወጣቶች ተጨማሪ ኃላፊነት ለመቀበል ብቁ ሲሆኑ ማየት ያስደስታል (አንቀጽ 9ን ተመልከት)

9. በዕድሜ የገፉ ወንድሞች ኃላፊነታቸውን ለሌሎች መስጠታቸው ቅር ሊያሰኛቸው የማይገባው ለምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።

9 በዕድሜ የገፉ ወንድሞች ኃላፊነታቸውን ለወጣት ወንድሞች ሲያስረክቡ ቅር ሊሰኙ አይገባም። ምክንያቱም ወጣቶች ኃላፊነት ለመሸከም ብቁ እንዲሆኑ መሠልጠናቸው ሥራው በተሻለ መንገድ እንዲከናወን ያስችላል። የተሾሙ ወንድሞች፣ እነሱ ያሠለጠኗቸው ወጣት ወንድሞች የእነሱን ሥራ ለመረከብ ብቁ ሆነው ሲገኙ ከፍተኛ እርካታ ሊሰማቸው ይገባል። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ ልጁን መኪና መንዳት የሚያስተምርን አንድ አባት እናስብ። ልጁ ትንሽ ሳለ አባቱ ሲነዳ በትኩረት ይመለከታል። ልጁ ከፍ እያለ ሲሄድ ደግሞ አባትየው፣ የሚያደርገውን ነገር ለልጁ ያብራራለታል። ከዚያም ልጁ መኪና መንዳት የሚችልበት ዕድሜ ላይ ሲደርስ አባቱ ተጨማሪ መመሪያ እየሰጠው መንዳት ይጀምራል። መጀመሪያ ላይ አባትና ልጅ እየተቀያየሩ መኪናውን ይነዱ ይሆናል፤ ሆኖም አባትየው በዕድሜ እየገፋ ሲሄድ አብዛኛውን ጊዜ የሚነዳው ልጁ ይሆናል። ጥበበኛ የሆነው አባት ልጁ መኪናውን በመንዳቱ ይደሰታል እንጂ ‘ለምን እኔ አልነዳሁም’ ብሎ ቅር አይሰኝም። በተመሳሳይም በዕድሜ የገፉ ወንድሞች፣ ወጣቶችን በማሠልጠን ቲኦክራሲያዊ መብቶችን ለመቀበል ብቁ እንዲሆኑ በመርዳታቸው ኩራት ይሰማቸዋል።

10. ሙሴ ክብር ወይም ሥልጣን ስለማግኘት ምን አመለካከት ነበረው?

10 በዕድሜ የገፉ ወንድሞች፣ ሌሎች መብት ሲያገኙ ቅናት እንዳያድርባቸው መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። በእስራኤላውያን ሰፈር ውስጥ ያሉ አንዳንድ ሰዎች እንደ ነቢያት በመሆን ትንቢት መናገር በጀመሩ ጊዜ ሙሴ ምን እንደተሰማው እስቲ እንመልከት። (ዘኁልቁ 11:24-29ን አንብብ።) የሙሴ ረዳት የሆነው ኢያሱ ሊከለክላቸው ፈልጎ ነበር። ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ኢያሱ እነዚህ ሰዎች የሙሴን ተሰሚነትና ሥልጣን እየተጋፉ እንዳለ ተሰምቶት ነበር። ሆኖም ሙሴ ኢያሱን እንዲህ አለው፦ “ስለ እኔ ተቆርቁረህ ነው? አትቆርቆር፤ የይሖዋ ሕዝቦች በሙሉ ነቢያት ቢሆኑና ይሖዋ መንፈሱን ቢሰጣቸው እንዴት ደስ ባለኝ!” ሙሴ በጉዳዩ ላይ የይሖዋ እጅ እንዳለበት ተገንዝቦ ነበር። ሙሴ ለራሱ ክብር ከመፈለግ ይልቅ ሁሉም የይሖዋ አገልጋዮች ተመሳሳይ መንፈሳዊ ስጦታ እንዲኖራቸው እንደሚመኝ ገለጸ። በዛሬው ጊዜም አንዳንድ መብቶች ከእኛ ይልቅ ለሌሎች ሊሰጡ ይችላሉ፤ ታዲያ በዚህ ወቅት የሙሴን ምሳሌ በመከተል ልንደሰት አይገባም?

11. አንድ ወንድም ኃላፊነታቸውን ለሌላ ሰው ሲያስረክቡ ምን ተሰምቷቸዋል?

11 በዘመናችንም ለአሥርተ ዓመታት ጠንክረው የሠሩ እንዲሁም ተጨማሪ ኃላፊነት ለመሸከም ብቁ እንዲሆኑ ሌሎችን የረዱ በርካታ ምሳሌ የሚሆኑ ወንድሞች አሉ። እስቲ የወንድም ፒተርን ምሳሌ እንመልከት። ወንድም ፒተር በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ከ74 ዓመታት በላይ ያሳለፉ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 35 ዓመቱን በአውሮፓ በሚገኝ አንድ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ አገልግለዋል። እኚህ ወንድም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ፣ የአገልግሎት ዘርፍ የበላይ ተመልካች ነበሩ። አሁን ግን ከወንድም ፒተር ጋር ለበርካታ ዓመታት አብሮ የሠራው ፖል የተባለ ወንድም ይህን ኃላፊነት ተረክቧል። ወንድም ፒተር ስለዚህ ለውጥ ምን እንደተሰማቸው ሲጠየቁ እንዲህ ብለዋል፦ “ተጨማሪ ኃላፊነት ለመቀበል የሠለጠኑና ሥራውንም በጥሩ ሁኔታ የሚያከናውኑ ወንድሞች በመኖራቸው በጣም ደስተኛ ነኝ።”

በዕድሜ ለገፉ ወንድሞች አድናቆት ይኑራችሁ

12. ስለ ሮብዓም ከሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ምን ትምህርት እናገኛለን?

12 ሰለሞን ከሞተ በኋላ ልጁ ሮብዓም በእሱ ምትክ ንጉሥ ሆነ። ሮብዓም ኃላፊነቱን እንዴት መወጣት እንዳለበት ምክር በፈለገ ጊዜ በቅድሚያ ሽማግሌዎቹን ጠየቀ። ነገር ግን ሽማግሌዎቹ የሰጡትን ምክር አልተቀበለም! ከዚህ ይልቅ አብሮ አደጎቹ የነበሩትንና አሁን የእሱ አገልጋይ የሆኑትን ወጣቶች ምክር ሰማ። ውጤቱ አስከፊ ነበር። (2 ዜና 10:6-11, 19) ከዚህ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው? በዕድሜ የገፉና ተሞክሮ ያካበቱ ወንድሞችን ምክር መጠየቅ እንዲሁም የሚሰጡንን ምክር ማጤን ብልህነት ነው። ወጣቶች ቀደም ሲል የነበረውን አሠራር የግድ መከተል አለባቸው ማለት ባይሆንም በዕድሜ የገፉ ወንድሞች የሚሰጡትን ምክር ውድቅ ለማድረግ መቸኮል አይኖርባቸውም።

13. ወጣቶች በዕድሜ ከገፉት ጋር ተባብረው መሥራት የሚችሉት እንዴት ነው?

13 አንዳንድ ወጣት ወንድሞች፣ በዕድሜ የገፉ ወንድሞችም የሚሳተፉበትን ሥራ የማስተባበር ኃላፊነት ተቀብለው ይሆናል። እነዚህ ወንድሞች አሁን ይህን ኃላፊነት ቢረከቡም ውሳኔ ከማድረጋቸው በፊት ጥበብና ተሞክሮ ያላቸውን በዕድሜ የገፉ ወንድሞች ማማከራቸው ጠቃሚ ነው። የአገልግሎት ዘርፍ የበላይ ተመልካች በመሆን ወንድም ፒተርን የተካው ፖል እንዲህ ብሏል፦ “ጊዜ በመመደብ ወንድም ፒተርን ምክር እጠይቃለሁ፤ አብረውኝ የሚሠሩ ሌሎችም እንዲሁ እንዲያደርጉ አበረታታቸዋለሁ።”

14. በጢሞቴዎስና በሐዋርያው ጳውሎስ መካከል ከነበረው የትብብር መንፈስ ምን እንማራለን?

14 ወጣቱ ጢሞቴዎስ ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር ለበርካታ ዓመታት አብሮ ሠርቷል። (ፊልጵስዩስ 2:20-22ን አንብብ።) ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፎላቸዋል፦ “በጌታ ልጄ የሆነውን የምወደውንና ታማኝ የሆነውን ጢሞቴዎስን የምልክላችሁ ለዚህ ነው። እሱም በየስፍራው በሚገኙ ጉባኤዎች ሁሉ ሳስተምር የምጠቀምባቸውን ይኸውም ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር በተያያዘ አገልግሎቴን የማከናውንባቸውን ዘዴዎች ያሳስባችኋል።” (1 ቆሮ. 4:17) ይህ አጭር መግለጫ ጳውሎስና ጢሞቴዎስ ምን ያህል ተባብረው ይሠሩ እንደነበር በግልጽ ያሳያል። ጳውሎስ ‘ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር በተያያዘ አገልግሎቱን የሚያከናውንባቸውን ዘዴዎች’ ጊዜ ወስዶ ለጢሞቴዎስ አስተምሮታል። ጢሞቴዎስም የተሰጠውን ሥልጠና በሚገባ የተቀበለ ሲሆን በጳውሎስ ዘንድ ተወዳጅነትን አትርፏል፤ ጢሞቴዎስ በቆሮንቶስ ያሉትን ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ፍላጎት ማሟላት እንደሚችል ጳውሎስ ተማምኖበት ነበር። ጳውሎስ፣ በዛሬው ጊዜ በጉባኤ ውስጥ ወንድሞችን ለኃላፊነት ብቁ እንዲሆኑ ለሚያሠለጥኑ ሽማግሌዎች ጥሩ ምሳሌ ይሆናል።

ሁላችንም የምናበረክተው አስተዋጽኦ አለ

15. ጳውሎስ በሮም ላሉ ክርስቲያኖች የሰጠው ምክር ለውጦች ሲያጋጥሙን የሚረዳን እንዴት ነው?

15 የምንኖረው አስደሳች ክንውኖች እየተፈጸሙ ባሉበት ወቅት ነው። የይሖዋ ድርጅት ምድራዊ ክፍል በብዙ አቅጣጫዎች እድገት እያደረገ ነው፤ ይህ ደግሞ አንዳንድ ለውጦች ማድረግን ይጠይቃል። ለውጡ እኛን የሚነካ በሚሆንበት ጊዜ ትሑት በመሆን ከራሳችን ይልቅ በይሖዋ ፈቃድ ላይ ትኩረት እናድርግ። እንዲህ ማድረጋችን አንድነታችንን ያጠናክረዋል። ጳውሎስ በሮም ላሉ ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እያንዳንዱ ሰው ከሚገባው በላይ ስለ ራሱ በማሰብ ራሱን ከፍ አድርጎ አይመልከት፤ ከዚህ ይልቅ አምላክ ለእያንዳንዱ በሰጠው እምነት መሠረት ጤናማ አስተሳሰብ እንዳለው በሚያሳይ መንገድ እንዲያስብ፣ በመካከላችሁ ያለውን እያንዳንዱን ሰው በተሰጠኝ ጸጋ እመክራለሁ። በአንድ አካል ላይ ብዙ የአካል ክፍሎች አሉን፤ ደግሞም ሁሉም የአካል ክፍሎች አንድ ዓይነት ተግባር አያከናውኑም፤ ልክ እንደዚሁ እኛም ብዙ ብንሆንም እንኳ ከክርስቶስ ጋር ባለን አንድነት አንድ አካል ነን፤ ደግሞም አንዳችን የሌላው የአካል ክፍል ነን።”—ሮም 12:3-5

16. በዕድሜ የገፉ ወንድሞች፣ ወጣቶች እንዲሁም ሚስቶች በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ያለውን ሰላምና አንድነት ለመጠበቅ ምን ማድረግ ይችላሉ?

16 እንግዲያው ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን፣ የይሖዋን መንግሥት ፈቃድ ለመፈጸም ጠንክረን እንሥራ። እናንት በዕድሜ የገፋችሁ ወንድሞች፣ እየሠራችሁት ያለውን ሥራ መረከብ እንዲችሉ ወጣቶችን አሠልጥኑ። እናንት ወጣቶች፣ ኃላፊነት ለመቀበል ራሳችሁን አቅርቡ፤ ትሑት ሁኑ፤ እንዲሁም በዕድሜ ለገፉ ወንድሞች ምንጊዜም አክብሮት ይኑራችሁ። እናንት ሚስቶች፣ የአቂላን ሚስት የጵርስቅላን ምሳሌ ተከተሉ፤ ጵርስቅላ እሷና ባለቤቷ በሕይወታቸው ውስጥ ለውጥ ባጋጠማቸው ጊዜም ባለቤቷን በታማኝነት ደግፋለች።—ሥራ 18:2

17. ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ምን እንደሚያደርጉ ተማምኖባቸው ነበር? ምን ሥራ እንዲያከናውኑስ አሠልጥኗቸዋል?

17 ሌሎች ተጨማሪ ኃላፊነት እንዲቀበሉ በማሠልጠን ረገድ ከሁሉ የላቀው ምሳሌያችን ኢየሱስ ነው። ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱ የሚያበቃበት ጊዜ እንደሚመጣና ሥራውን ሌሎች እንደሚረከቡት ያውቅ ነበር። ደቀ መዛሙርቱ ፍጹም ባይሆኑም እንኳ በእነሱ ላይ ይተማመን ስለነበር ከእሱ የሚበልጥ ሥራ እንደሚያከናውኑ ነግሯቸዋል። (ዮሐ. 14:12) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን በሚገባ ያሠለጠናቸው ሲሆን እነሱም በወቅቱ ይታወቅ በነበረው ዓለም ምሥራቹን ከዳር እስከ ዳር አዳርሰዋል።—ቆላ. 1:23

18. ከፊታችን ምን ተስፋ ተዘርግቶልናል? በአሁኑ ጊዜስ ምን ማድረግ እንችላለን?

18 ኢየሱስ ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ ከሰጠ በኋላ ትንሣኤ አግኝቶ ወደ ሰማይ ተመልሷል፤ በዚያም “ከየትኛውም መስተዳድር፣ ሥልጣን፣ ኃይልና ጌትነት . . . እጅግ የላቀ ቦታ [ተሰጥቶታል]።” (ኤፌ. 1:19-21) እኛም አርማጌዶን ከመምጣቱ በፊት ታማኝ ሆነን ከሞትን ጽድቅ በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ ከሞት እንነሳለን፤ በዚያ ወቅት እያንዳንዳችን የሚያስደስተንን ሥራ እንሠራለን። እስከዚያው ድረስ ግን ሁላችንም የምናከናውነው በጣም አስፈላጊ ሥራ አለ፤ ይህም ምሥራቹን የመስበኩና ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ነው። እንግዲያው ወጣቶችም ሆንን በዕድሜ የገፋን፣ ‘ምንጊዜም የጌታ ሥራ የበዛልን እንሁን።’—1 ቆሮ. 15:58

^ አን.3 በዚህ የጥናት ርዕስ ላይ ‘ወጣቶች’ የሚለው አገላለጽ፣ በዕድሜ ወጣት የሆኑትን ብቻ ሳይሆን ይህን የዕድሜ ክልል ያለፉትንና በመካከለኛ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙትንም ሊያካትት ይችላል።