በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 3

ልብህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው?

ልብህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው?

“ከምንም ነገር በላይ ልብህን ጠብቅ።”—ምሳሌ 4:23

መዝሙር 36 ልባችንን እንጠብቅ

የትምህርቱ ዓላማ *

1-3. (ሀ) ይሖዋ ሰለሞንን ይወደው የነበረው ለምንድን ነው? ሰለሞን ምን በረከቶችን አግኝቷል? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ የየትኞቹን ጥያቄዎች መልስ እንመረምራለን?

ሰለሞን የእስራኤል ንጉሥ የሆነው ገና በወጣትነቱ ነበር። በግዛቱ መጀመሪያ አካባቢ ይሖዋ በሕልም ተገልጦ “እንድሰጥህ የምትፈልገውን ጠይቅ” አለው። ሰለሞንም እንዲህ በማለት መለሰ፦ “እኔ ገና አንድ ፍሬ ልጅና ተሞክሮ የሌለኝ [ነኝ]። . . . ስለሆነም አገልጋይህ ሕዝብህን መዳኘት . . . እንዲችል ታዛዥ ልብ ስጠው።” (1 ነገ. 3:5-10) ሰለሞን “ታዛዥ ልብ” እንዲሰጠው መጠየቁ ምን ያህል ልኩን የሚያውቅ ሰው እንደነበር ያሳያል። በእርግጥም ይሖዋ ሰለሞንን ይወደው የነበረ መሆኑ ምንም አያስገርምም! (2 ሳሙ. 12:24) አምላካችን፣ በወጣቱ ንጉሥ መልስ በጣም ስለተደሰተ ለሰለሞን “ጥበበኛና አስተዋይ ልብ” ሰጠው።—1 ነገ. 3:12

2 ሰለሞን ታማኝ በነበረባቸው ጊዜያት ሁሉ ብዙ በረከቶችን አግኝቷል። “ለእስራኤል አምላክ ለይሖዋ ስም” ቤተ መቅደስ የመገንባት ትልቅ መብት ተሰጥቶታል። (1 ነገ. 8:20) በተጨማሪም ከአምላክ ያገኘው ጥበብ በብዙዎች ዘንድ እውቅና አትርፎለታል። ከዚህም ሌላ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተናገራቸው ነገሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙ ሦስት መጻሕፍት ላይ ተመዝግበዋል። ከእነዚህ መጻሕፍት መካከል አንዱ የምሳሌ መጽሐፍ ነው።

3 “ልብ” የሚለው ቃል በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ መቶ ጊዜ ያህል ተጠቅሶ ይገኛል። ለምሳሌ ያህል፣ ምሳሌ 4:23 “ከምንም ነገር በላይ ልብህን ጠብቅ” ይላል። በዚህ ጥቅስ ላይ “ልብ” የሚለው ቃል ምን ያመለክታል? በዚህ ርዕስ ውስጥ የዚህን ጥያቄ መልስ እንመረምራለን። በተጨማሪም የሚከተሉትን ሁለት ጥያቄዎች መልስ እንመለከታለን፦ ሰይጣን ልባችንን ለማጥቃት ወይም ለመበከል የሚሞክረው እንዴት ነው? እኛስ ልባችንን ለመጠበቅ ምን ማድረግ እንችላለን? ምንጊዜም ለአምላክ ታማኝ ሆነን ለመኖር የእነዚህን ወሳኝ ጥያቄዎች መልስ ማወቅ ያስፈልገናል።

“ልብ” የሚለው ቃል ምን ትርጉም አለው?

4-5. (ሀ) “ልብ” የሚለውን ቃል ትርጉም ለማወቅ መዝሙር 51:6 የሚረዳን እንዴት ነው? (ለ) አካላዊ ጤንነታችንን በመጠበቅና ውስጣዊ ማንነታችንን በመጠበቅ መካከል ምን ተመሳሳይነት አለ?

4 በምሳሌ 4:23 ላይ የሚገኘው “ልብ” የሚለው ቃል “የውስጥ ሰውነትን” ለማመልከት ተሠርቶበታል። (መዝሙር 51:6 እና የግርጌ ማስታወሻውን አንብብ።) በሌላ አባባል “ልብ” የሚለው ቃል የውስጥ ሐሳብን፣ ስሜትን፣ ዝንባሌንና ምኞትን ያመለክታል። ቃሉ ከውጭ ስንታይ የምንመስለውን ሳይሆን ውስጣዊ ማንነታችንን ይጠቁማል።

5 ውስጣዊ ማንነታችንን መጠበቅ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ለመረዳት አካላዊ ጤንነታችንን እንደ ምሳሌ አድርገን መውሰድ እንችላለን። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ሰውነታችን ጤናማ እንዲሆን ከፈለግን የተመጣጠነ ምግብ መመገብና አዘውትረን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ይኖርብናል። በተመሳሳይም መንፈሳዊ ጤንነታችንን መጠበቅ ከፈለግን የተመጣጠነ መንፈሳዊ ምግብ መመገብና በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት አዘውትረን በተግባር ማሳየት ይኖርብናል። እምነታችንን በተግባር ማሳየት፣ የተማርናቸውን ነገሮች ተግባራዊ ማድረግንና ስለምናምንባቸው ነገሮች ለሌሎች መናገርን ይጨምራል። (ሮም 10:8-10፤ ያዕ. 2:26) በሁለተኛ ደረጃ፣ ውስጣችን በበሽታ ቢጠቃም ከውጫዊ ገጽታችን በመነሳት ጤናማ የሆንን ሊመስለን ይችላል። በተመሳሳይም በውስጣችን የተሳሳተ ምኞት እያቆጠቆጠ ቢሆንም በቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ስለምንካፈል ብቻ ጠንካራ እምነት ያለን ሊመስለን ይችላል። (1 ቆሮ. 10:12፤ ያዕ. 1:14, 15) ሰይጣን በእሱ አስተሳሰብ ሊበክለን እንደሚሞክር መዘንጋት አይኖርብንም። ለመሆኑ ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው? እኛስ ራሳችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

ሰይጣን ልባችንን ለማጥቃት የሚሞክረው እንዴት ነው?

6. የሰይጣን ዓላማ ምንድን ነው? ይህን ዓላማውን ለማሳካት የሚሞክረውስ እንዴት ነው?

6 ሰይጣን ልክ እንደ እሱ የይሖዋን መሥፈርቶች የምናቃልልና በራስ ወዳድነት ምኞት የምንመራ ዓመፀኞች እንድንሆን ይፈልጋል። እርግጥ ነው፣ ሰይጣን የእሱ ዓይነት አስተሳሰብ እንዲኖረንና ከእሱ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ድርጊት እንድንፈጽም ሊያስገድደን አይችልም። በመሆኑም ዓላማውን ዳር ለማድረስ ሌሎች መንገዶችን ይጠቀማል። ለምሳሌ ያህል፣ በእሱ አስተሳሰብ በተበከሉ ሰዎች እንድንከበብ ያደርጋል። (1 ዮሐ. 5:19) ይህን የሚያደርገው እንዲህ ካሉ ሰዎች ጋር ጊዜ እንድናሳልፍ ስለሚፈልግ ነው፤ ሰይጣን መጥፎ ጓደኝነት አስተሳሰባችንንና ድርጊታችንን ‘እንደሚያበላሸው’ ወይም እንደሚበክለው እያወቅንም የተሳሳተ ውሳኔ እንድናደርግ ይፈልጋል። (1 ቆሮ. 15:33) ይህ ዘዴ ከንጉሥ ሰለሞን ጋር በተያያዘ ሠርቶለታል። ሰለሞን በርካታ የባዕድ አገር ሴቶችን አግብቶ ነበር፤ እነዚህ ሴቶች በሰለሞን ላይ ‘ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደሩበት’ ሲሆን “ቀስ በቀስ ልቡ” ከይሖዋ እንዲርቅ አድርገውታል።—1 ነገ. 11:3 ግርጌ

ሰይጣን ልብህን በእሱ አስተሳሰብ ለመበከል የሚያደርገውን ጥረት መከላከል የምትችለው እንዴት ነው? (አንቀጽ 7⁠ን ተመልከት) *

7. ሰይጣን የእሱን አስተሳሰብ ለማስፋፋት የሚጠቀምበት ሌላኛው ዘዴ ምንድን ነው? በዚህ ረገድ ጠንቃቆች መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

7 ሰይጣን የእሱን አስተሳሰብ ለማስፋፋት ፊልሞችንና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን ይጠቀማል። ሰይጣን የሌሎችን ታሪክ መስማት እንደሚያስደስተን ያውቃል፤ በተጨማሪም እነዚህ ታሪኮች እኛን ከማዝናናት ባለፈ አስተሳሰባችንን፣ ስሜታችንና ድርጊታችንን እንደሚቀርጹት ይገነዘባል። ኢየሱስ ታሪኮችን በመጠቀም ሰዎችን አስተምሯል። ስለ ደጉ ሳምራዊና ስለ አባካኙ ልጅ የተናገራቸውን ታሪኮች እንደ ምሳሌ መውሰድ እንችላለን። (ማቴ. 13:34፤ ሉቃስ 10:29-37፤ 15:11-32) ሆኖም በሰይጣን አስተሳሰብ የተበከሉ ሰዎችም አስተሳሰባችንን ለማበላሸት ይህንኑ ዘዴ ሊጠቀሙ ይችላሉ። በመሆኑም ሚዛናዊ መሆን ያስፈልገናል። አስተሳሰባችንን የማይበክሉ አዝናኝና አስተማሪ ፊልሞች እንዲሁም የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች እንዳሉ የታወቀ ነው። ሆኖም ጠንቃቃ መሆን ይኖርብናል። የምንዝናናባቸውን ፕሮግራሞች ስንመርጥ ራሳችንን እንደሚከተለው ብለን መጠየቃችን አስፈላጊ ነው፦ ‘ይህ ፊልም ወይም የቴሌቪዥን ፕሮግራም ለሥጋ ምኞቶቼ መሸነፍ ምንም ችግር እንደሌለው የሚያስተምር ነው?’ (ገላ. 5:19-21፤ ኤፌ. 2:1-3) አንድ ፕሮግራም ሰይጣናዊ አስተሳሰብን የሚያስፋፋ እንደሆነ ከተገነዘብን ምን ማድረግ ይኖርብናል? እንዲህ ያለውን ፕሮግራም ልክ እንደ ተላላፊ በሽታ በመቁጠር ልንርቀው ይገባል!

8. ወላጆች፣ ልጆቻቸው ልባቸውን እንዲጠብቁ መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?

8 ወላጆች፣ ሰይጣን ልባቸውን ለመበከል ከሚያደርገው ጥረት ልጆቻችሁን የመጠበቅ ልዩ ኃላፊነት ተጥሎባችኋል። ልጆቻችሁን ቃል በቃል ከበሽታ ለመጠበቅ የተቻላችሁን ያህል ጥረት እንደምታደርጉ ምንም ጥርጥር የለውም። ለዚህ ስትሉ ቤታችሁን በንጽሕና የምትይዙ ከመሆኑም ሌላ እናንተንም ሆነ ልጆቻችሁን ለበሽታ ሊያጋልጡ የሚችሉ ነገሮችን ታስወግዳላችሁ። በተመሳሳይም ልጆቻችሁን ለሰይጣን አስተሳሰብ ሊያጋልጧቸው ከሚችሉ ፊልሞች፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎችና ድረ ገጾች ልትጠብቋቸው ይገባል። ይሖዋ የልጆቻቸሁን መንፈሳዊ ደህንነት የመጠበቅ ሥልጣን ሰጥቷችኋል። (ምሳሌ 1:8፤ ኤፌ. 6:1, 4) በመሆኑም በመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች ላይ የተመሠረቱ ሕጎችን ለቤተሰባችሁ ማውጣት ሊያስፈራችሁ አይገባም። የትኞቹን ነገሮች ማየት እንደሚፈቀድላቸውና የትኞቹን ነገሮች ማየት እንደማይፈቀድላቸው ለትናንሽ ልጆቻችሁ ንገሯቸው፤ እንዲሁም ይህን ውሳኔ ያደረጋችሁበትን ምክንያት አስረዷቸው። (ማቴ. 5:37) ከፍ እያሉ ሲሄዱ ደግሞ በይሖዋ መሥፈርት ላይ ተመሥርተው ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር በራሳቸው መለየት እንዲችሉ አሠልጥኗቸው። (ዕብ. 5:14) ልጆቻችሁ የምትናገሩትን ነገር በመስማት ትምህርት የሚቀስሙ ቢሆንም ይበልጥ ትምህርት የሚያገኙት ግን የምታደርጉትን ነገር በማየት እንደሆነ አስታውሱ።—ዘዳ. 6:6, 7፤ ሮም 2:21

9. ሰይጣን ከሚያስፋፋቸው ሐሳቦች መካከል አንዱ የትኛው ነው? ይህ አስተሳሰብ አደገኛ የሆነውስ ለምንድን ነው?

9 በተጨማሪም ሰይጣን ከይሖዋ አስተሳሰብ ይልቅ በሰዎች ጥበብ እንድንታመን በማድረግ ልባችንን ለመበከል ይሞክራል። (ቆላ. 2:8) ሰይጣን ከሚያስፋፋቸው ሐሳቦች መካከል አንዱን ማለትም ‘በሕይወት ውስጥ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ነገር ቁሳዊ ሀብት ማካበት ነው’ የሚለውን ሐሳብ እንደ ምሳሌ መውሰድ እንችላለን። እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ሀብታም ሊሆኑም ላይሆኑም ይችላሉ። የሆነው ሆኖ ግን ራሳቸውን አደጋ ላይ መጣላቸው አይቀርም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ቁሳዊ ሀብትን በማካበት ላይ ከማተኮራቸው የተነሳ እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ሲሉ ጤናቸውን፣ ከቤተሰባቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት፣ አልፎ ተርፎም ከአምላክ ጋር የመሠረቱትን ወዳጅነት መሥዋዕት ሊያደርጉ ይችላሉ። (1 ጢሞ. 6:10) ጥበበኛ የሆነው ሰማያዊ አባታችን ለገንዘብ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረን ስለሚረዳን አመስጋኝ ልንሆን ይገባል።—መክ. 7:12፤ ሉቃስ 12:15

ልባችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

በጥንት ዘመን እንደነበሩ ጠባቂዎችና የበር ጠባቂዎች ንቁ በመሆንና ፈጣን እርምጃ በመውሰድ ጎጂ ተጽዕኖዎች ወደ ልባችሁ እንዳይገቡ ተከላከሉ (አንቀጽ 10-11⁠ን ተመልከት) *

10-11. (ሀ) ራሳችንን ለመጠበቅ ምን ማድረግ ይኖርብናል? (ለ) በጥንት ዘመን የነበሩ ጠባቂዎች ምን ያደርጉ ነበር? ሕሊናችን እንደ ጠባቂ ሊሆንልን የሚችለውስ እንዴት ነው?

10 ልባችንን በመጠበቅ ረገድ እንዲሳካልን ከፈለግን አደጋዎችን ለይተን ማወቅና ራሳችንን ለመጠበቅ ፈጣን እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። በምሳሌ 4:23 ላይ “ጠብቅ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ጠባቂዎች የሚያከናውኑትን ሥራ ያስታውሰናል። በንጉሥ ሰለሞን ዘመን የነበሩ ጠባቂዎች በከተማዋ ቅጥር ላይ የሚቆሙ ሲሆን አደጋ መቅረቡን ሲያዩ የማስጠንቀቂያ ድምፅ ያሰሙ ነበር። ይህን ሁኔታ በአእምሯችን መሣላችን ሰይጣን አስተሳሰባችንን እንዳያበላሸው ለመከላከል ምን ማድረግ እንዳለብን እንድንገነዘብ ይረዳናል።

11 በጥንት ዘመን የነበሩ ጠባቂዎች፣ ከከተማዋ በር ጠባቂዎች ጋር ተባብረው ይሠሩ ነበር። (2 ሳሙ. 18:24-26) ሁለቱ ጠባቂዎች፣ ጠላት በሚቃረብበት ጊዜ ሁሉ የከተማዋ በሮች መዘጋታቸውን በማረጋገጥ የከተማዋን ደህንነት በጋራ ይጠብቁ ነበር። (ነህ. 7:1-3) ሰይጣን ልባችንን ለመውረር በሌላ አባባል በአስተሳሰባችን፣ በስሜታችን፣ በዝንባሌያችን ወይም በምኞታችን ላይ ተጽዕኖ ለማድረግ ሲሞክር በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነው ሕሊናችን * እንደ ጠባቂ በመሆን ያስጠነቅቀናል። ሕሊናችን የማስጠንቀቂያ ድምፅ በሚያሰማበት ጊዜ ሁሉ ማስጠንቀቂያውን መስማትና ምሳሌያዊ በሮቻችንን መዝጋት ይኖርብናል።

12-13. ምን ለማድረግ ልንፈተን እንችላለን? ሆኖም በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

12 የሰይጣን አስተሳሰብ ተጽዕኖ እንዳያሳድርብን መከላከል የምንችለው እንዴት እንደሆነ የሚያሳይ አንድ ምሳሌ እንመልከት። ይሖዋ ‘የፆታ ብልግናና ማንኛውም ዓይነት ርኩሰት በመካከላችን ከቶ መነሳት’ እንደሌለበት አስተምሮናል። (ኤፌ. 5:3) ሆኖም የሥራ ባልደረቦቻችን ወይም አብረውን የሚማሩ ልጆች የብልግና ወሬዎችን ማውራት ቢጀምሩ ምን እናደርጋለን? ‘ፈሪሃ አምላክ በጎደለው መንገድ መኖራችንንና ዓለማዊ ምኞቶችን መከተላችንን መተው’ እንዳለብን እናውቃለን። (ቲቶ 2:12) ጠባቂ የሆነው ሕሊናችን በዚህ ጊዜ የማስጠንቀቂያ ድምፅ ሊያሰማ ይችላል። (ሮም 2:15) ታዲያ ማስጠንቀቂያውን እንሰማለን? አንዳንድ ጊዜ፣ እኩዮቻችን የሚያወሩትን ወሬ ለመስማት ወይም የሚላላኩትን ምስል ለማየት እንፈተን ይሆናል። ሆኖም ምሳሌያዊ በሮቻችንን መዝጋት የሚገባን በዚህ ጊዜ ነው፤ ይህን ለማድረግ ርዕሱን መቀየር ወይም ከአካባቢው ዞር ማለት እንችላለን።

13 እኩዮቻችን መጥፎ ነገሮችን እንድናስብ ወይም የተሳሳተ እርምጃ እንድንወስድ የሚያሳድሩብንን ተጽዕኖ መቋቋም ድፍረት ይጠይቃል። ሆኖም ይሖዋ የምናደርገውን ጥረት እንደሚመለከት እንዲሁም ሰይጣናዊ አስተሳሰቦችን ለመቋቋም የሚያስፈልገንን ብርታትና ጥበብ እንደሚሰጠን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (2 ዜና 16:9፤ ኢሳ. 40:29፤ ያዕ. 1:5) ይሁንና ልባችንን ለመጠበቅ ሌላ ምን ማድረግ እንችላለን?

ነቅታችሁ ጠብቁ

14-15. (ሀ) ልባችንን ለምን ነገር መክፈት ይኖርብናል? እንዲህ ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው? (ለ) ምሳሌ 4:20-22 ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችን የተሻለ ጥቅም ለማግኘት የሚረዳን እንዴት ነው? (“ ማሰላሰል የሚቻለው እንዴት ነው?” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

14 ልባችንን ለመጠበቅ በምሳሌያዊ ሁኔታ የልባችንን በር በመዝጋት መጥፎ ተጽዕኖዎችን መከላከላችን ብቻ በቂ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የልባችንን በር በመክፈት በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድሩብንን ነገሮች ማስገባትም ይኖርብናል። እስቲ ዙሪያውን ስለታጠረ ከተማ የጠቀስነውን ምሳሌ በድጋሚ እንመልከት። በር ጠባቂዎቹ የጠላት ወረራን ለመከላከል የከተማዋን በሮች ይዘጉ ነበር፤ ሆኖም በሌሎች ጊዜያት የከተማዋን በሮች ከፍተው ምግብና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ማስገባት ይኖርባቸዋል። በሮቹ ሁሌም ዝግ ከሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች ለረሃብ መዳረጋቸው አይቀርም። እኛም በተመሳሳይ የአምላክ አስተሳሰብ ለሚያሳድረው በጎ ተጽዕኖ ምንጊዜም ልባችንን ክፍት ማድረግ ይኖርብናል።

15 መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋን አስተሳሰብ ይዟል፤ በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን ባነበብን ቁጥር የይሖዋ አስተሳሰብ በእኛ አስተሳሰብ፣ ስሜትና ድርጊት ላይ ተጽዕኖ እንዲያደርግ እንፈቅድለታለን። ታዲያ ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችን የተሻለ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? ጸሎት በጣም አስፈላጊ ነው። አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቤን ከመጀመሬ በፊት ይሖዋ በቃሉ ውስጥ ያሉትን ‘አስደናቂ ነገሮች አጥርቼ [ማየት]’ እንድችል እንዲረዳኝ እጸልያለሁ።” (መዝ. 119:18) በተጨማሪም ባነበብነው ነገር ላይ ማሰላሰል ይኖርብናል። ስንጸልይ፣ ስናነብና ስናሰላስል የአምላክ ቃል ‘ልባችን ውስጥ’ ዘልቆ ስለሚገባ የይሖዋን አስተሳሰብ ይበልጥ እየወደድነው እንሄዳለን።—ምሳሌ 4:20-22ን አንብብ፤ መዝ. 119:97

16. በርካታ ወንድሞችና እህቶች ከJW ብሮድካስቲንግ ምን ጥቅም አግኝተዋል?

16 የአምላክ አስተሳሰብ ተጽዕኖ እንዲያሳድርብን የምንፈቅድበት ሌላው መንገድ ደግሞ JW ብሮድካስቲንግ ላይ የሚወጡትን ቪዲዮዎች መመልከት ነው። አንድ ባልና ሚስት እንዲህ ብለዋል፦ “ወርሃዊ ፕሮግራሞቹ በእርግጥም የጸሎታችን መልስ እንደሆኑ ይሰማናል! ስናዝን ወይም ብቸኝነት ሲሰማን ያበረታቱናል እንዲሁም ያጠናክሩናል። ቤት ውስጥ ስንሆን አብዛኛውን ጊዜ ሙዚቃዎቹን እንከፍታቸዋለን። ምግብ ስናበስል፣ ቤት ስናጸዳ ወይም ቁጭ ብለን ሻይ ስንጠጣ እናዳምጣቸዋለን።” እነዚህ ፕሮግራሞች ልባችንን ለመጠበቅ ይረዱናል። የይሖዋን አስተሳሰብ ማዳበርና የሰይጣን አስተሳሰብ የሚያሳድርብንን ተጽዕኖ መከላከል የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያሠለጥኑናል።

17-18. (ሀ) በ1 ነገሥት 8:61 ላይ እንደተገለጸው ከይሖዋ የተማርናቸውን ነገሮች ተግባራዊ ማድረጋችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል? (ለ) ከንጉሥ ሕዝቅያስ ታሪክ ምን እንማራለን? (ሐ) በመዝሙር 139:23, 24 ላይ ከሚገኘው የዳዊት ጸሎት ጋር በሚስማማ መልኩ ምን ብለን መጸለይ እንችላለን?

17 ትክክል የሆነውን ማድረግ የሚያስገኘውን ጥቅም በተመለከትን ቁጥር እምነታችን እየጠነከረ ይሄዳል። (ያዕ. 1:2, 3) ይሖዋ እኛን ልጆቼ ብሎ መጥራት እንደሚያኮራው ስለምናውቅ ልባችን በደስታ ይሞላል፤ እንዲሁም እሱን ለማስደሰት ያለን ፍላጎት ይጨምራል። (ምሳሌ 27:11) የሚያጋጥመን እያንዳንዱ ፈተና፣ አሳቢ የሆነውን አባታችንን የምናገለግለው በግማሽ ልብ እንዳልሆነ የምናሳይበት አጋጣሚ ይሰጠናል። (መዝ. 119:113) ፈተናዎችን በጽናት በመወጣት ይሖዋን በሙሉ ልባችን እንደምንወደው ማለትም የእሱን ትእዛዛት ለመጠበቅና ፈቃዱን ለመፈጸም ከልባችን እንደቆረጥን እናሳያለን።—1 ነገሥት 8:61ን አንብብ።

18 እርግጥ ነው፣ ፍጽምና የጎደለን ሰዎች ስለሆንን ስህተት እንደምንሠራ የታወቀ ነው። በዚህ ጊዜ የንጉሥ ሕዝቅያስን ታሪክ እናስታውስ። ሕዝቅያስ ስህተት የሠራባቸው ጊዜያት ነበሩ። ሆኖም ንስሐ በመግባት “በሙሉ ልብ” ይሖዋን ማገልገሉን ቀጥሏል። (ኢሳ. 38:3-6፤ 2 ዜና 29:1, 2፤ 32:25, 26) እንግዲያው ሰይጣን ልባችንን በእሱ አስተሳሰብ ለመበከል የሚያደርገውን ጥረት እንቋቋም። ይሖዋ “ታዛዥ ልብ” እንዲሰጠን እንጸልይ። (1 ነገ. 3:9፤ መዝሙር 139:23, 24ን አንብብ።) ከምንም ነገር በላይ ልባችንን የምንጠብቅ ከሆነ ለይሖዋ ታማኝ ሆነን መኖር እንችላለን።

መዝሙር 54 “መንገዱ ይህ ነው”

^ አን.5 ለይሖዋ ያለንን ታማኝነት ጠብቀን እንኖራለን ወይስ ሰይጣን አታሎ ከአምላክ እንዲያርቀን እንፈቅድለታለን? የዚህ ጥያቄ መልስ የተመካው በሚደርስብን ፈተና ክብደት ላይ ሳይሆን ልባችንን ለመጠበቅ በምናደርገው ጥረት ላይ ነው። “ልብ” የሚለው ቃል ምን ትርጉም አለው? ሰይጣን ልባችንን ለማጥቃት የሚሞክረው እንዴት ነው? ልባችንን መጠበቅ የምንችለውስ እንዴት ነው? ይህ ርዕስ ለእነዚህ ወሳኝ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።

^ አን.11 ተጨማሪ ማብራሪያ፦ ይሖዋ የራሳችንን አስተሳሰብ፣ ስሜትና ድርጊት በመመርመር ራሳችንን የመዳኘት ችሎታ ሰጥቶናል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ችሎታ “ሕሊና” በማለት ይጠራዋል። (ሮም 2:15፤ 9:1) በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊና የሚባለው የምናስበው፣ የምናደርገው ወይም የምንናገረው ነገር ጥሩ ወይም መጥፎ መሆኑን ለመዳኘት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን የይሖዋን መሥፈርቶች የሚጠቀም ሕሊና ነው።

^ አን.56 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ የተጠመቀ ወንድም ቴሌቪዥን እየተመለከተ ሳለ የብልግና ይዘት ያላቸው ነገሮች መታየት ይጀምራሉ። ምን እርምጃ እንደሚወስድ መወሰን ይኖርበታል።

^ አን.58 የሥዕሉ መግለጫ፦ በጥንት ዘመን የሚኖር አንድ ጠባቂ ወደ ከተማዋ አደጋ እየመጣ መሆኑን ያያል። ከዚያም ከታች ላሉት የበር ጠባቂዎች ይነግራቸዋል። እነሱም ወዲያውኑ የከተማዋን በሮች በመዝጋትና ከውስጥ በመቀርቀር ፈጣን እርምጃ ይወስዳሉ።