በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 4

የጌታ ራት—በሰማይ ስላለው ንጉሣችን የሚያስተምር ቀለል ያለ ዝግጅት

የጌታ ራት—በሰማይ ስላለው ንጉሣችን የሚያስተምር ቀለል ያለ ዝግጅት

‘ይህ ሥጋዬን ያመለክታል። ይህ “የቃል ኪዳን ደሜን” ያመለክታል።’—ማቴ. 26:26-28

መዝሙር 16 ያህ ልጁን ሾሟል አወድሱት

የትምህርቱ ዓላማ *

1-2. (ሀ) ኢየሱስ የሞቱ መታሰቢያ ቀለል ባለ መንገድ እንዲከበር እንደሚያደርግ መጠበቃችን ምክንያታዊ የሚሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ ያሳያቸውን የትኞቹን ባሕርያት እንመረምራለን?

በየዓመቱ በሚከበረው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ላይ የሚከናወኑትን ነገሮች መግለጽ ትችላላችሁ? አብዛኞቻችን በጌታ ራት በዓል ላይ የሚከናወኑትን ዋና ዋና ነገሮች መዘርዘር እንደማይከብደን ምንም ጥርጥር የለውም። ለምን? ምክንያቱም ዝግጅቱ ምንም የተወሳሰበ ነገር የለውም። ሆኖም የጌታ ራት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው በዓል ነው። ከዚህ አንጻር ‘በዓሉ ይህን ያህል ቀለል ያለ እንዲሆን የተደረገው ለምንድን ነው?’ የሚል ጥያቄ ሊፈጠርብን ይችላል።

2 ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት አስፈላጊ የሆኑ እውነቶችን ግልጽ፣ ያልተወሳሰበና ለመረዳት ቀላል በሆነ መንገድ በማስተማር ይታወቅ ነበር። (ማቴ. 7:28, 29) የሞቱ መታሰቢያ * ከሚከበርበት መንገድ ጋር በተያያዘም ቀላል ሆኖም ትልቅ ትርጉም ያዘለ ዝግጅት አድርጎልናል። እስቲ ስለዚህ ዝግጅት እንዲሁም ኢየሱስ ስለተናገራቸውና ስላደረጋቸው አንዳንድ ነገሮች እንመልከት። እንዲህ ማድረጋችን ኢየሱስ ምን ያህል ትሑት፣ ደፋርና አፍቃሪ እንደሆነ እንድናስተውል የሚረዳን ከመሆኑም ሌላ እሱን ይበልጥ መምሰል የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያስገነዝበናል።

ኢየሱስ ትሑት ነው

በመታሰቢያው በዓል ላይ የሚቀርበው ቂጣና የወይን ጠጅ ኢየሱስ ለእኛ ሲል ሕይወቱን እንደሰጠንና በአሁኑ ጊዜ በሰማይ በመግዛት ላይ ያለ ንጉሣችን እንደሆነ ያስታውሰናል (አንቀጽ 3-5⁠ን ተመልከት)

3. ማቴዎስ 26:26-28፣ ኢየሱስ ያቋቋመው የመታሰቢያ በዓል ቀለል ያለ እንደሆነ የሚያሳየው እንዴት ነው? ኢየሱስ በዝግጅቱ ላይ የትኞቹን ሁለት ነገሮች ተጠቅሟል?

3 ኢየሱስ 11 ታማኝ ሐዋርያቱ በተገኙበት የሞቱን መታሰቢያ በዓል አቋቁሟል። ከፋሲካው ማዕድ የተረፈውን ነገር ተጠቅሞ ይህን ቀለል ያለ ዝግጅት አድርጓል። (ማቴዎስ 26:26-28ን አንብብ።) ለዚህ ዝግጅት የተጠቀመው በማዕዱ ላይ ቀርቦ የነበረውን ያልቦካ ቂጣና ወይን ብቻ ነው። ኢየሱስ ለሐዋርያቱ እነዚህ ሁለት ነገሮች በቅርቡ ለእነሱ ሲል መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርበውን ፍጹም የሆነውን ሥጋውንና ደሙን እንደሚያመለክቱ ነገራቸው። ሐዋርያቱ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ይህ አዲስ ዝግጅት፣ ቀለል ያለ መሆኑ ያን ያህል አላስገረማቸው ይሆናል። ለምን?

4. ኢየሱስ ለማርታ የሰጣት ምክር የመታሰቢያው በዓል ዝግጅት ቀለል ያለ እንዲሆን ያደረገበትን ምክንያት ለማወቅ የሚረዳን እንዴት ነው?

4 ኢየሱስ ከተወሰኑ ወራት በፊት ማለትም አገልግሎቱን በጀመረበት በሦስተኛው ዓመት ላይ የቅርብ ጓደኞቹ ወደሆኑት ወደ አልዓዛር፣ ማርታና ማርያም ቤት በሄደ ጊዜ ያደረገውን ነገር እንመልከት። ሁሉም ሰው ዘና ብሎ እያለ ኢየሱስ ማስተማር ጀመረ። ማርታም በቦታው ነበረች፤ ሆኖም ቤቷ ለተገኘው ለዚህ የተከበረ እንግዳ ትልቅ ግብዣ በማዘጋጀት ተጠምዳ ስለነበር ትኩረቷ ተከፋፍሏል። ኢየሱስ ይህን ስላስተዋለ ለማርታ በደግነት ምክር ሰጣት፤ ምክሩ ትልቅ ግብዣ ማዘጋጀት የግድ አስፈላጊ እንዳልሆነ እንድታስተውል የሚረዳ ነበር። (ሉቃስ 10:40-42) ኢየሱስ ለማርታ የሰጣትን ይህንኑ ምክር፣ ከጊዜ በኋላ መሥዋዕት ሆኖ ከመሞቱ ከጥቂት ሰዓታት በፊት እሱ ራሱ ተግባራዊ አድርጎታል። ለመታሰቢያ በዓሉ የተጠቀመበት ማዕድ ቀለል ያለ እንዲሆን አድርጓል። ይህ ስለ ኢየሱስ ምን ያስተምረናል?

5. የመታሰቢያው በዓል ዝግጅት ቀለል ያለ መሆኑ ስለ ኢየሱስ ምን ይጠቁማል? ይህስ በፊልጵስዩስ 2:5-8 ላይ ከሚገኘው ሐሳብ ጋር የሚስማማው እንዴት ነው?

5 ኢየሱስ በንግግሩም ሆነ በድርጊቱ ምንጊዜም ትሑት ነበር። በመሆኑም ምድር ላይ ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ያሳየው ትልቅ ትሕትና ሊያስገርመን አይገባም። (ማቴ. 11:29) ከጥቂት ጊዜ በኋላ በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ከሁሉ የላቀ ቦታ የሚሰጠውን መሥዋዕት እንደሚያቀርብና ይሖዋም ከሞት አስነስቶ በሰማይ ክብራማ ቦታ እንደሚሰጠው ያውቅ ነበር። ያም ቢሆን የሞቱ መታሰቢያ ለየት ባለ መንገድ እንዲከበር በማድረግ ወደ ራሱ ተገቢ ያልሆነ ትኩረት አልሳበም። ከዚህ ይልቅ ደቀ መዛሙርቱ በዓመት አንድ ጊዜ በዚህ ቀለል ያለ ዝግጅት አማካኝነት የሞቱን መታሰቢያ እንዲያከብሩ ነግሯቸዋል። (ዮሐ. 13:15፤ 1 ቆሮ. 11:23-25) ቀለል ያለ ሆኖም ለሥነ ሥርዓቱ ተስማሚ የሆነው ይህ ዝግጅት ኢየሱስ ኩሩ እንዳልነበር ይጠቁማል። በሰማይ ያለው ንጉሣችን ካሉት ግሩም ባሕርያት መካከል አንዱ ትሕትና በመሆኑ ደስተኞች ነን።—ፊልጵስዩስ 2:5-8ን አንብብ።

6. ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ኢየሱስ ትሕትና በማሳየት ረገድ የተወውን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

6 ትሕትና በማሳየት ረገድ ኢየሱስን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው? ከራሳችን ይልቅ የሌሎች ሰዎችን ፍላጎት በማስቀደም ነው። (ፊልጵ. 2:3, 4) ኢየሱስ በምድር ላይ ያሳለፈውን የመጨረሻ ምሽት ለማሰብ ሞክሩ። ኢየሱስ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አሰቃቂ በሆነ መንገድ እንደሚገደል ያውቃል፤ ያም ሆኖ ከሁሉ በላይ ያሳሰበው በእሱ ሞት ምክንያት ከባድ ሐዘን ላይ የሚወድቁት ታማኝ ሐዋርያቱ ሁኔታ ነበር። በመሆኑም የመጨረሻውን ምሽት ያሳለፈው እነሱን በማስተማር፣ በማበረታታትና በማጽናናት ነው። (ዮሐ. 14:25-31) ኢየሱስ ትሑት ስለሆነ ከራሱ ይልቅ የሌሎች ሰዎች ደህንነት ያሳስበው ነበር። በእርግጥም በዚህ ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል!

ኢየሱስ ደፋር ነው

7. ኢየሱስ የጌታ ራት በዓልን ካቋቋመ ብዙም ሳይቆይ አስደናቂ ድፍረት ያሳየው እንዴት ነው?

7 ኢየሱስ የጌታ ራት በዓልን ካቋቋመ ብዙም ሳይቆይ አስደናቂ ድፍረት አሳይቷል። እንዴት? አባቱ ለእሱ ያለውን ፈቃድ መፈጸሙ አምላክን ሰድቧል በሚል አሳፋሪ ወንጀል እንደሚያስከስሰውና እንደሚያስገድለው ቢያውቅም የአባቱን ፈቃድ ከመፈጸም ወደኋላ አላለም። (ማቴ. 26:65, 66፤ ሉቃስ 22:41, 42) ኢየሱስ የይሖዋን ስም ለማክበር፣ የአምላክን ሉዓላዊነት ለመደገፍና ንስሐ የሚገቡ የሰው ልጆች የዘላለም ሕይወት የሚያገኙበትን በር ለመክፈት ሲል ንጹሕ አቋሙን ፍጹም በሆነ መንገድ ጠብቋል። ከዚህም በላይ ኢየሱስ ተከታዮቹን በቅርቡ ለሚጠብቃቸው ነገር አዘጋጅቷቸዋል።

8. (ሀ) ኢየሱስ ለታማኝ ሐዋርያቱ ምን ነገሮችን ነግሯቸዋል? (ለ) ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ባሉት ዓመታት ውስጥ ተከታዮቹ ድፍረት ያሳዩት እንዴት ነው?

8 በተጨማሪም ኢየሱስ በወቅቱ ተሰምቶት ሊሆን በሚችለው ጭንቀት ላይ ከማተኮር ይልቅ ታማኝ ሐዋርያቱ በሚያስፈልጋቸው ነገር ላይ ትኩረት በማድረግ ድፍረት እንዳለው አሳይቷል። ይሁዳ እንዲወጣ ካደረገ በኋላ ያቋቋመው ቀለል ያለ በዓል ወደፊት በመንፈስ ለሚቀቡ ተከታዮቹ፣ የአዲሱ ቃል ኪዳን ተካፋይ መሆናቸው ያስገኘላቸውን መብትና የፈሰሰው ደሙ ያስገኘላቸውን ጥቅም ያስታውሳቸዋል። (1 ቆሮ. 10:16, 17) ኢየሱስ ተከታዮቹ ለሰማያዊው ጥሪ ብቁ እንዲሆኑ ለመርዳት ሲል እሱም ሆነ አባቱ ከእነሱ ምን እንደሚጠብቁ አሳውቋቸዋል። (ዮሐ. 15:12-15) በተጨማሪም ለሐዋርያቱ ከፊታቸው ስለሚጠብቃቸው መከራ ነግሯቸዋል። ከዚያም ራሱን ምሳሌ አድርጎ በመጥቀስ “አይዟችሁ!” ብሏቸዋል። (ዮሐ. 16:1-4ሀ, 33) በርካታ ዓመታት ካለፉ በኋላም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ የራስን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግና ድፍረት በማሳየት ረገድ የተወውን ምሳሌ መከተላቸውን ቀጥለው ነበር። በራሳቸው ላይ ከባድ ጉዳት ቢያስከትልባቸውም እንኳ በተለያዩ መከራዎች ሥር እርስ በርስ ይደጋገፉ ነበር።—ዕብ. 10:33, 34

9. ድፍረት በማሳየት ረገድ ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

9 እኛም በተመሳሳይ ድፍረት በማሳየት ረገድ ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ እንከተላለን። ለምሳሌ ያህል፣ በእምነታቸው ምክንያት ስደት እየደረሰባቸው ያሉ ወንድሞቻችንን ለመርዳት ድፍረት ማሳየት ያስፈልገናል። አንዳንድ ጊዜ ወንድሞቻችን ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለእስር ይዳረጉ ይሆናል። በዚህ ወቅት እነሱን ለመርዳት አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል፤ ይህም ለእነሱ ጥብቅና መቆምን ይጨምራል። (ፊልጵ. 1:14፤ ዕብ. 13:19) ከዚህም ሌላ “በድፍረት” መስበካችንን በመቀጠል የኢየሱስን ምሳሌ መከተል እንችላለን። (ሥራ 14:3) ሰዎች ቢቃወሙን ወይም ስደት ቢያደርሱብንም እንኳ ልክ እንደ ኢየሱስ የመንግሥቱን መልእክት ለማወጅ ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል። አንዳንዴ ግን ድፍረት እንደሚጎድለን እናስተውል ይሆናል። ታዲያ በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ እንችላለን?

10. ከመታሰቢያው በዓል በፊት ባሉት ሳምንታት ምን ልናደርግ ይገባል? ለምንስ?

10 የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ስላስገኘልን ተስፋ ማሰባችን ይበልጥ ደፋሮች እንድንሆን ይረዳናል። (ዮሐ. 3:16፤ ኤፌ. 1:7) ከመታሰቢያው በዓል በፊት ባሉት ሳምንታት፣ ለቤዛው ያለንን አድናቆት የምናሳድግበት ልዩ አጋጣሚ እናገኛለን። በዚህ ወቅት ለመታሰቢያው በዓል የተዘጋጀውን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ማንበባችንና ከኢየሱስ ሞት ጋር በተያያዙ ክንውኖች ላይ ማሰላሰላችን አስፈላጊ ነው። እንዲህ ማድረጋችን የጌታ ራት በዓልን ለማክበር በምንሰበሰብበት ወቅት ስለ ቂጣውና ስለ ወይን ጠጁ እንዲሁም እነዚህ ነገሮች ስለሚወክሉት ወደር የለሽ መሥዋዕት ይበልጥ የተሟላ ግንዛቤ እንዲኖረን ይረዳናል። ይሖዋና ኢየሱስ ስላደረጉልን ነገሮች ስናውቅ እንዲሁም እነሱ ያደረጉት ነገር እኛንም ሆነ የምንወዳቸውን ሰዎች የሚጠቅመው እንዴት እንደሆነ ስንገነዘብ ተስፋችን የሚጠናከር ከመሆኑም ሌላ እስከ መጨረሻው በድፍረት ለመጽናት እንገፋፋለን።—ዕብ. 12:3

11-12. እስካሁን የትኞቹን ነገሮች ተመልክተናል?

11 እስካሁን እንደተመለከትነው፣ የጌታ ራት ውድ ስለሆነው የቤዛው ዝግጅት ብቻ ሳይሆን ኢየሱስ ስላሳያቸው ግሩም ባሕርያት ማለትም ስለ ትሕትናውና ስለ ድፍረቱ እንድናስብ ያደርገናል። ኢየሱስ በዛሬው ጊዜም በሰማይ ሊቀ ካህናት ሆኖ ለእኛ ሲማልድ እነዚህን ባሕርያት የሚያንጸባርቅ በመሆኑ ምንኛ አመስጋኞች ነን! (ዕብ. 7:24, 25) በመሆኑም ለዚህ ያለንን ልባዊ አድናቆት ለማሳየት ኢየሱስ ባዘዘን መሠረት የሞቱን መታሰቢያ በዓል በታማኝነት ማክበር ይኖርብናል። (ሉቃስ 22:19, 20) ይህን በዓል የምናከብረው በዓመቱ ውስጥ ትልቅ ቦታ በሚሰጠው ቀን ማለትም ኒሳን 14 በሚውልበት ዕለት ነው።

12 የጌታ ራት፣ ቀለል ያለ ዝግጅት መሆኑ ኢየሱስ ያሳየውን ሌላ ባሕርይ እንድናስተውል ያደርገናል። ይህ ባሕርይ ኢየሱስን ለእኛ ሲል እንዲሞት አነሳስቶታል፤ በተጨማሪም ምድር ላይ ሰው ሆኖ በኖረበት ጊዜ ሁሉ በዚህ ባሕርይው ይታወቅ ነበር። ይህ ባሕርይ ምንድን ነው?

ኢየሱስ አፍቃሪ ነው

13. ዮሐንስ 15:9 እና 1 ዮሐንስ 4:8-10 ይሖዋና ኢየሱስ ያሳዩትን ፍቅር የሚገልጹት እንዴት ነው? እነሱ ካሳዩት ፍቅር የሚጠቀሙትስ እነማን ናቸው?

13 ኢየሱስ ያደረገው ነገር ሁሉ ይሖዋ ለእኛ ያለውን ጥልቅ ፍቅር ፍጹም በሆነ መንገድ ያንጸባርቃል። (ዮሐንስ 15:9ን እና 1 ዮሐንስ 4:8-10ን አንብብ።) ኢየሱስ ፍቅሩን ያሳየበት ከሁሉ የላቀው መንገድ ደግሞ ለእኛ ሲል ሕይወቱን መሥዋዕት ማድረጉ ነው። ቅቡዓንም ሆን ‘የሌሎች በጎች’ አባላት ይሖዋና ልጁ በዚህ መሥዋዕት አማካኝነት ካሳዩን ፍቅር ተጠቃሚዎች ነን። (ዮሐ. 10:16፤ 1 ዮሐ. 2:2) ሌላው ቀርቶ ኢየሱስ በመታሰቢያው በዓል ላይ የተጠቀመበት ነገር እንኳ ለደቀ መዛሙርቱ ያለውን ፍቅርና አሳቢነት ያሳያል። እንዴት?

ኢየሱስ በፍቅር ተነሳስቶ የመታሰቢያው በዓል ቀለል ያለ ዝግጅት እንዲሆን አድርጎልናል፤ ይህም በዓሉ ለበርካታ መቶ ዓመታት በተለያዩ ሁኔታዎች ሥር እንዲከበር አስችሏል (አንቀጽ 14-16⁠ን ተመልከት) *

14. ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ያለውን ፍቅር ያሳየው እንዴት ነው?

14 ኢየሱስ የመታሰቢያው በዓል ውስብስብ የሆነ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ሳይሆን ቀለል ያለ ዝግጅት እንዲሆን በማድረግ በመንፈስ ለተቀቡት ተከታዮቹ ያለውን ፍቅር አሳይቷል። ከጊዜ በኋላ እነዚህ ቅቡዓን ደቀ መዛሙርት የመታሰቢያውን በዓል በየዓመቱ ማክበር የሚኖርባቸው ሲሆን ይህን የሚያደርጉት እስርን ጨምሮ በተለያዩ ሁኔታዎች ሥር ሆነው ነው። (ራእይ 2:10) ታዲያ የኢየሱስን ትእዛዝ መጠበቅ ችለው ይሆን? እንዴታ!

15-16. አንዳንዶች በከባድ ሁኔታዎች ሥርም እንኳ የጌታ ራትን ማክበር የቻሉት እንዴት ነው?

15 ከመጀመሪያው መቶ ዘመን ጀምሮ እስከ ዘመናችን ድረስ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ ለማክበር ጥረት አድርገዋል። የጌታ ራትን ሲያከብሩ በተቻላቸው መጠን ኢየሱስ ያቋቋመውን ሥርዓት ለመከተል ሞክረዋል፤ አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ያደረጉት በከባድ ሁኔታዎች ሥር ሆነው ነው። እስቲ የሚከተሉትን ምሳሌዎች እንመልከት። ወንድም ሃሮልድ ኪንግ ቻይና ውስጥ ብቻውን ታስሮ በነበረበት ወቅት የጌታ ራትን ለማክበር ዘዴ መቀየስ አስፈልጎት ነበር። እዚያው ያገኛቸውን ነገሮች ተጠቅሞ ለመታሰቢያው በዓል የሚያስፈልገውን ቂጣና የወይን ጠጅ በድብቅ አዘጋጅቷል። በተጨማሪም የመታሰቢያው በዓል የሚውልበትን ቀን በተቻለው መጠን በጥንቃቄ አስልቷል። በበዓሉ ቀን በታሰረበት ክፍል ውስጥ ብቻውን ሆኖ በመዘመር፣ በመጸለይና ቅዱስ ጽሑፋዊ ንግግር በማቅረብ በዓሉን አክብሯል።

16 ሌላም ምሳሌ መጥቀስ እንችላለን። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ታስረው የነበሩ እህቶች የጌታ ራትን ለማክበር ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለዋል። ሆኖም የመታሰቢያው በዓል ቀለል ያለ ዝግጅት ስለሆነ በዓሉን ማንም ሳያያቸው ማክበር ችለዋል። በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፦ “ሁላችንም ተጠጋግተን ክብ ሠርተን ቆምን። በመካከላችንም በነጭ ጨርቅ የተሸፈነው ቂጣውና ወይኑ በአጭር በርጩማ ላይ ተቀምጦ ነበር። የኤሌክትሪክ መብራት ያበራን እንደሆን ሊያዩን ስለሚችሉ በክፍሉ ውስጥ ያበራነው ሻማ ነበር። . . . ባለን ኃይል ሁሉ ቅዱስ ስሙን ለማስከበር ላባታችን የገባነውን ልባዊ ስዕለት እንደገና አደስን።” እነዚህ ክርስቲያኖች ያሳዩት እምነት እንዴት የሚያስደንቅ ነው! ኢየሱስ የመታሰቢያው በዓል ቀለል ያለ ዝግጅት እንዲሆን ማድረጉ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ሥርም እንኳ በዓሉን እንድናከብር አስችሎናል፤ በዚህ መንገድ ለእኛ ያለውን ጥልቅ ፍቅር አሳይቷል!

17. ራሳችንን የትኞቹን ጥያቄዎች ልንጠይቅ እንችላለን?

17 የጌታ ራትን የምናከብርበት ዕለት እየተቃረበ ሲሄድ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ራሳችንን መጠየቃችን ተገቢ ነው፦ ‘ፍቅር በማሳየት ረገድ ኢየሱስን ይበልጥ መምሰል የምችለው እንዴት ነው? ከራሴ ፍላጎት ይልቅ ለእምነት ባልንጀሮቼ ፍላጎት ቅድሚያ እሰጣለሁ? ወንድሞቼና እህቶቼ ከአቅማቸው በላይ የሆነ ነገር እንዲያደርጉ እጠብቃለሁ ወይስ የአቅም ገደብ እንዳለባቸው እገነዘባለሁ?’ ምንጊዜም ኢየሱስን ለመምሰልና “የሌላውን ስሜት [ለመረዳት]” ጥረት እናድርግ።—1 ጴጥ. 3:8

ትሕትና፣ ድፍረትና ፍቅር በማሳየት ረገድ ኢየሱስን ምሰሉ

18-19. (ሀ) ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን? (ለ) ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው?

18 ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ክርስቲያኖች የጌታ ራትን እንዲያከብሩ የተሰጣቸውን ትእዛዝ መጠበቅ አያስፈልጋቸውም። ኢየሱስ በታላቁ መከራ ወቅት ‘ሲመጣ’ ምድር ላይ የቀሩትን “የተመረጡ” ቅቡዓን ወደ ሰማይ ይሰበስባል፤ ከዚያ በኋላ የመታሰቢያውን በዓል ማክበር እናቆማለን።—1 ቆሮ. 11:26፤ ማቴ. 24:31

19 የመታሰቢያው በዓል በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ከሁሉ የላቀ ትሕትና፣ ድፍረትና ፍቅር የታየበት ዝግጅት ነው፤ የይሖዋ ሕዝቦች የመታሰቢያው በዓል መከበሩን ካቆመ በኋላም እንኳ ይህን ቀለል ያለ ዝግጅት በደስታ እንደሚያስታውሱት እርግጠኞች መሆን እንችላለን። በጌታ ራት ላይ የመገኘት አጋጣሚ ያገኙ ሁሉ ወደፊት ስለዚህ ልዩ ዝግጅት ለሌሎች እንደሚናገሩ ምንም ጥርጥር የለውም። ሆኖም በዛሬው ጊዜ ከዚህ ዝግጅት ተጠቃሚ መሆን ከፈለግን ትሕትና፣ ድፍረትና ፍቅር በማሳየት ረገድ ኢየሱስን ለመምሰል ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ አለብን። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ይሖዋ ወሮታችንን እንደሚከፍለን መተማመን እንችላለን።—2 ጴጥ. 1:10, 11

መዝሙር 13 ምሳሌያችን የሆነው ክርስቶስ

^ አን.5 በቅርቡ የክርስቶስን ሞት ለማሰብ የጌታ ራት በዓልን እናከብራለን። ይህ ቀለል ያለ ዝግጅት ኢየሱስ ስላሳየው ትሕትና፣ ድፍረትና ፍቅር ብዙ ነገር ያስተምረናል። በዚህ ርዕስ ውስጥ ኢየሱስ ያሳያቸውን እነዚህን ግሩም ባሕርያት ማንጸባረቅ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

^ አን.2 ተጨማሪ ማብራሪያ፦ መታሰቢያ የሚለው ቃል ትልቅ ቦታ የሚሰጠውን ክንውን አሊያም ግለሰብ ለማስታወስ ወይም ለማክበር ሲባል ለየት ያለ ነገር ማድረግን ያመለክታል።

^ አን.56 የሥዕሉ መግለጫ፦ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች የመታሰቢያውን በዓል ሲያከብሩ የሚያሳዩ ምስሎች፦ በመጀመሪያው መቶ ዘመን፤ በ1800ዎቹ መጨረሻ፤ በናዚ ማጎሪያ ካምፕ እንዲሁም በዘመናችን በደቡብ አሜሪካ ውስጥ ሞቃታማ የአየር ንብረት ባለበት አገር በሚገኝ ክፍት የስብሰባ አዳራሽ።