በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 5

በስብሰባዎች ላይ መገኘታችን ስለ እኛ ምን ይጠቁማል?

በስብሰባዎች ላይ መገኘታችን ስለ እኛ ምን ይጠቁማል?

“ጌታ እስከሚመጣ ድረስ ሞቱን ታውጃላችሁ።”—1 ቆሮ. 11:26

መዝሙር 18 ለቤዛው አመስጋኝ መሆን

የትምህርቱ ዓላማ *

1-2. (ሀ) ይሖዋ በጌታ ራት ላይ የተገኙትን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲመለከት ትኩረት የሚያደርገው ምን ላይ ነው? (ሽፋኑን ተመልከት።) (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

ይሖዋ በዓለም ዙሪያ በጌታ ራት ላይ የተገኙትን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲመለከት ምን ላይ እንደሚያተኩር ለማሰብ ሞክር። በዝግጅቱ ላይ የተገኙትን በርካታ ሰዎች በጥቅሉ ሳይሆን በግለሰብ ደረጃ ይመለከታል። ለምሳሌ ያህል፣ በየዓመቱ በታማኝነት በዚህ ስብሰባ ላይ የሚገኙትን ሰዎች ያያል። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ በስብሰባው ላይ የሚገኙት፣ የሚደርስባቸውን ከባድ ስደት ተቋቁመው ሊሆን ይችላል። ሌሎች ደግሞ በሳምንታዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረው ባይገኙም በመታሰቢያው በዓል ላይ የግድ መገኘት እንዳለባቸው ስለሚሰማቸው ፈጽሞ አይቀሩም። በተጨማሪም ይሖዋ በመታሰቢያው በዓል ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኙ ሰዎችንም ያያል፤ ምናልባትም እነዚህ ሰዎች በበዓሉ ላይ የተገኙት ምን እንደሚከናወን ለማወቅ ፈልገው ሊሆን ይችላል።

2 ይሖዋ በመታሰቢያው በዓል ላይ የተገኙትን በርካታ ሰዎች ሲያይ እንደሚደሰት ምንም ጥርጥር የለውም። (ሉቃስ 22:19) ሆኖም ይሖዋ በዋነኝነት ትኩረት የሚያደርገው በሰዎቹ ብዛት ላይ ሳይሆን ሰዎቹን በስብሰባው ላይ እንዲገኙ ባነሳሳቸው ምክንያት ላይ ነው። በይሖዋ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሰዎቹ ይህን እርምጃ ለመውሰድ የተነሳሱበት ውስጣዊ ግፊት ነው። በዚህ ርዕስ ውስጥ የሚከተለውን ወሳኝ ጥያቄ እንመረምራለን፦ በዓመት አንድ ጊዜ በሚከበረው የመታሰቢያ በዓል ላይ ብቻ ሳይሆን ይሖዋ እሱን ለሚወዱ ሰዎች ባዘጋጃቸው ሳምንታዊ ስብሰባዎችም ላይ የምንገኘው ለምንድን ነው?

በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በጌታ ራት ላይ ይገኛሉ (አንቀጽ 1-2⁠ን ተመልከት)

ትሕትና በስብሰባዎች ላይ እንድንገኝ ያነሳሳናል

3-4. (ሀ) በስብሰባዎች ላይ የምንገኘው ለምንድን ነው? (ለ) በስብሰባዎች ላይ መገኘታችን ስለ እኛ ምን ይጠቁማል? (ሐ) በ1 ቆሮንቶስ 11:23-26 ላይ ከሚገኘው ሐሳብ አንጻር የመታሰቢያው በዓል ፈጽሞ ሊያመልጠን የማይገባው ለምንድን ነው?

3 በጉባኤ ስብሰባ ላይ የምንገኝበት ዋነኛው ምክንያት የአምልኳችን ክፍል ስለሆነ ነው። ሌላው ምክንያት ደግሞ በስብሰባዎች ላይ ከይሖዋ ስለምንማር ነው። ኩሩ የሆኑ ሰዎች መማር የሚያስፈልጋቸው ነገር እንዳለ አይሰማቸውም። (3 ዮሐ. 9) እኛ ግን ከእነሱ በተቃራኒ ከይሖዋና እሱ እየተጠቀመበት ካለው ድርጅት ለመማር ከፍተኛ ጉጉት አለን።—ኢሳ. 30:20፤ ዮሐ. 6:45

4 በስብሰባዎች ላይ መገኘታችን ትሑት እንደሆንን ማለትም ለመማር ዝግጁና ፈቃደኛ እንደሆንን ይጠቁማል። የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ በሚከበርበት ምሽት ላይ የምንገኘው ግዴታችን እንደሆነ ስለሚሰማን ብቻ ሳይሆን ኢየሱስ “ይህን ሁልጊዜ ለመታሰቢያዬ አድርጉት” በማለት የሰጠውን መመሪያ በትሕትና ስለምንታዘዝ ነው። (1 ቆሮንቶስ 11:23-26ን አንብብ።) ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ይህ ዝግጅት ስለ ወደፊቱ ጊዜ ያለንን ተስፋ የሚያጠናክርልን ከመሆኑም ሌላ ይሖዋ ምን ያህል እንደሚወደን እንድናስታውስ ያደርገናል። ሆኖም ይሖዋ ማበረታቻ ማግኘት የሚያስፈልገን በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ እንዳልሆነ ያውቃል። በመሆኑም ሳምንታዊ ስብሰባዎችን ያዘጋጀልን ሲሆን በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ እንድንገኝ አሳስቦናል። ትሕትና ይህን ማሳሰቢያ እንድንከተል ያነሳሳናል። በየሳምንቱ ለእነዚህ ስብሰባዎች በመዘጋጀትና በስብሰባዎቹ ላይ በመገኘት የተወሰኑ ሰዓታትን እናሳልፋለን።

5. ትሑት የሆኑ ሰዎች ይሖዋ ያቀረበላቸውን ግብዣ የሚቀበሉት ለምንድን ነው?

5 በየዓመቱ በርካታ ትሑት የሆኑ ሰዎች ይሖዋ ከእሱ እንዲማሩ ያቀረበላቸውን ግብዣ ይቀበላሉ። (ኢሳ. 50:4) አብዛኛውን ጊዜ በመታሰቢያው በዓል ላይ ከተገኙ በኋላ በሌሎች ስብሰባዎችም ላይ መገኘት ይጀምራሉ። (ዘካ. 8:20-23) እኛም ሆን እነዚህ ሰዎች ‘ረዳታችንና ታዳጊያችን’ ከሆነው ከይሖዋ መማርና የእሱን አመራር መቀበል ያስደስተናል። (መዝ. 40:17) ደግሞስ ከይሖዋና እሱ እጅግ ከሚወደው ከልጁ ከኢየሱስ የመማርን ያህል አስደሳችና ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ምን ነገር ሊኖር ይችላል?—ማቴ. 17:5፤ 18:20፤ 28:20

6. ትሕትና አንድን ግለሰብ በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኝ የረዳው እንዴት ነው?

6 በየዓመቱ በሚከበረው የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ ላይ በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች እንዲገኙ ለመጋበዝ ጥረት እናደርጋለን። በርካታ ትሑት ሰዎች ግብዣችንን በመቀበላቸው ጥቅም አግኝተዋል። እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት። ከተወሰኑ ዓመታት በፊት አንድ ግለሰብ የመጋበዣ ወረቀቱን ከአንድ ወንድም ተቀበለ፤ ሆኖም በስብሰባው ላይ መገኘት እንደማይችል ለወንድም ነገረው። ይሁንና የመታሰቢያው በዓል በሚከበርበት ምሽት ወንድም፣ ይህ ግለሰብ ወደ ስብሰባ አዳራሹ ሲገባ ሲያይ በጣም ተገረመ። ሰውየው በተደረገለት ሞቅ ያለ አቀባበል እጅግ የተደነቀ ሲሆን ከዚያ በኋላ በሳምንታዊ ስብሰባዎቻችን ላይ መገኘት ጀመረ። እንዲያውም በአንድ ዓመት ውስጥ ስብሰባ ላይ ያልተገኘው ሦስት ጊዜ ብቻ ነው። ለመሆኑ እንዲህ ያለ ምላሽ እንዲሰጥ ያነሳሳው ምንድን ነው? ገር መሆኑ አመለካከቱን ለመቀየር ረድቶታል። የጋበዘው ወንድም ከጊዜ በኋላ ስለዚህ ሰው ሲናገር “በጣም ትሑት ሰው ነው” ብሏል። ይሖዋ ይህን ግለሰብ ወደ እውነተኛው አምልኮ እንደሳበው ምንም ጥርጥር የለውም፤ በአሁኑ ጊዜ ይህ ሰው የተጠመቀ ወንድማችን ሆኗል።—2 ሳሙ. 22:28፤ ዮሐ. 6:44

7. በስብሰባዎች ላይ በመገኘትና መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ የምናገኘው ትምህርት ትሑት ለመሆን የሚረዳን እንዴት ነው?

7 በስብሰባዎች ላይ በመገኘትና መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ የምናገኘው ትምህርት ትሑት ለመሆን ይረዳናል። ከመታሰቢያው በዓል በፊት ባሉት ሳምንታት የምናደርጋቸው ስብሰባዎች አብዛኛውን ጊዜ ኢየሱስ በተወው ምሳሌ እንዲሁም ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ በመስጠት ባሳየው ትሕትና ላይ ያተኮሩ ናቸው። ከመታሰቢያው በዓል በፊት ባሉት ቀናት ደግሞ ከኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ ጋር በተያያዘ ስለተከናወኑት ነገሮች የሚገልጹትን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች እንድናነብ እንበረታታለን። እንዲህ ባሉ ስብሰባዎች ላይ በመገኘትና እነዚህን ዘገባዎች በማንበብ የምናገኛቸው ትምህርቶች ኢየሱስ ለእኛ ሲል ለከፈለው መሥዋዕት ያለንን አመስጋኝነት ያሳድጉልናል። በተጨማሪም በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ብንሆንም እንኳ ልክ እንደ ኢየሱስ ትሑት እንድንሆንና የይሖዋን ፈቃድ እንድንፈጽም ያነሳሱናል።—ሉቃስ 22:41, 42

ድፍረት በስብሰባዎች ላይ እንድንገኝ ይረዳናል

8. ኢየሱስ ድፍረት ያሳየው እንዴት ነው?

8 ድፍረት በማሳየት ረገድም ቢሆን የኢየሱስን ምሳሌ ለመከተል ጥረት እናደርጋለን። ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ባሉት ቀናት ድፍረት ያሳየው እንዴት እንደሆነ ለማሰብ ሞክሩ። ተቃዋሚዎቹ ብዙም ሳይቆይ እንደሚያዋርዱት፣ እንደሚገርፉትና እንደሚገድሉት ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። (ማቴ. 20:17-19) ያም ቢሆን ሞትን ለመጋፈጥ ፈቃደኛ ሆኗል። አልፎ የሚሰጥበት ጊዜ ሲደርስ፣ በጌትሴማኒ ከእሱ ጋር አብረው ለነበሩት ታማኝ ሐዋርያቱ “ተነሱ፣ እንሂድ። እነሆ፣ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቧል” ብሏቸዋል። (ማቴ. 26:36, 46) ከዚያም መሣሪያ የያዙ ሰዎች ሊያስሩት ሲመጡ ወደፊት ራመድ ብሎ የሚፈልጉት ሰው እሱ እንደሆነ የነገራቸው ከመሆኑም ሌላ ሐዋርያቱን እንዲተዉአቸው አዟቸዋል። (ዮሐ. 18:3-8) ኢየሱስ ያሳየው ድፍረት እንዴት አስደናቂ ነው! በዛሬው ጊዜ ያሉ ቅቡዓን ክርስቲያኖችና የሌሎች በጎች አባላት ድፍረት በማሳየት ረገድ ኢየሱስን ለመምሰል ጥረት ያደርጋሉ። እንዴት?

ደፋር በመሆን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘትህ ሌሎችን ያበረታታል (አንቀጽ 9⁠ን ተመልከት) *

9. (ሀ) አዘውትረን በስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ድፍረት የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? (ለ) የእኛ ምሳሌ በእምነታቸው ምክንያት የታሰሩ ወንድሞቻችንን የሚረዳው እንዴት ነው?

9 በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ሥር በስብሰባዎች ላይ አዘውትረን ለመገኘት ድፍረት ማሳየት ሊያስፈልገን ይችላል። አንዳንድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በስብሰባዎች ላይ የሚገኙት የደረሰባቸውን ሐዘን፣ የሚሰማቸውን የተስፋ መቁረጥ ስሜት አሊያም ያለባቸውን የጤና ችግር ተቋቁመው ነው። ሌሎች ደግሞ የቤተሰባቸው አባላት ወይም የመንግሥት ባለሥልጣናት ከባድ ተቃውሞ ቢያደርሱባቸውም በድፍረት በስብሰባዎች ላይ ይገኛሉ። በዚህ ረገድ የምንተወው ምሳሌ በእምነታቸው ምክንያት የታሰሩ ወንድሞቻችንን እንዴት እንደሚረዳ ለማሰብ ሞክሩ። (ዕብ. 13:3) እነዚህ ወንድሞች የሚደርስብንን መከራ ተቋቁመን ይሖዋን ማገልገላችንን እንደቀጠልን ሲሰሙ እምነታቸው ይጠናከራል፤ ይበልጥ ደፋር ይሆናሉ እንዲሁም እስከ መጨረሻው ንጹሕ አቋማቸውን ለመጠበቅ የሚያስችል ብርታት ያገኛሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ ተመሳሳይ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር። ሮም ውስጥ ታስሮ በነበረበት ወቅት ወንድሞቹ አምላክን በታማኝነት እያገለገሉ እንደሆኑ በሰማ ቁጥር ይደሰት ነበር። (ፊልጵ. 1:3-5, 12-14) ከእስር እንደተፈታ ወይም ሊፈታ ጥቂት ጊዜ ሲቀረው ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ደብዳቤ ጽፎ ነበር። በዚህ ደብዳቤ ላይ እነዚያን ታማኝ ክርስቲያኖች ‘እርስ በርሳቸው እንደ ወንድማማች መዋደዳቸውን እንዲቀጥሉ’ እንዲሁም መሰብሰባቸውን ቸል እንዳይሉ አሳስቧቸዋል።—ዕብ. 10:24, 25፤ 13:1

10-11. (ሀ) በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ እነማንን መጋበዝ ይኖርብናል? (ለ) ኤፌሶን 1:7 እንዲህ ለማድረግ የሚያነሳሳንን ምክንያት የሚገልጸው እንዴት ነው?

10 ዘመዶቻችንን፣ የሥራ ባልደረቦቻችንን እንዲሁም ጎረቤቶቻችንን በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ በመጋበዝ ደፋር እንደሆንን ማሳየት እንችላለን። እነዚህን ሰዎች የምንጋብዛቸው ለምንድን ነው? ይሖዋና ኢየሱስ ላደረጉልን ነገር ያለን ጥልቅ አድናቆት ሰዎችን በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ ከመጋበዝ ወደኋላ እንዳንል ያደርገናል። እነሱም ይሖዋ በቤዛው አማካኝነት ካሳየው “ጸጋ” ተጠቃሚ መሆን የሚችሉበትን መንገድ እንዲማሩ እንፈልጋለን።—ኤፌሶን 1:7ን አንብብ፤ ራእይ 22:17

11 ደፋሮች በመሆን አንድ ላይ መሰብሰባችን አምላክና ልጁ በላቀ ሁኔታ ያሳዩትን አንድ ሌላ ግሩም ባሕርይ የምናሳይበት አጋጣሚ ይሰጠናል።

ፍቅር በስብሰባዎች ላይ እንድንገኝ ግድ ይለናል

12. (ሀ) ስብሰባዎቻችን ለይሖዋና ለኢየሱስ ያለንን ፍቅር የሚያጠናክሩልን እንዴት ነው? (ለ) ሁለተኛ ቆሮንቶስ 5:14, 15 ምን እንድናደርግ ያበረታታናል?

12 ለይሖዋና ለኢየሱስ ያለን ፍቅር በስብሰባዎች ላይ እንድንገኝ ግድ ይለናል። በስብሰባዎች ላይ የምንማረው ትምህርት ደግሞ በምላሹ ለይሖዋና ለልጁ ያለንን ፍቅር ያጠናክርልናል። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እነሱ ስላደረጉልን ነገር አዘውትረን እንማራለን። (ሮም 5:8) በተለይም የመታሰቢያው በዓል ይሖዋና ኢየሱስ ለእኛ ብቻ ሳይሆን የቤዛውን ዋጋማነት ላልተገነዘቡ ሰዎች ጭምር ያላቸውን ጥልቅ ፍቅር እንድናስታውስ ይረዳናል። ይህን መገንዘባችን በአመስጋኝነት ስሜት እንድንሞላ ስለሚያደርገን በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ኢየሱስን ለመምሰል እንጣጣራለን። (2 ቆሮንቶስ 5:14, 15ን አንብብ።) በተጨማሪም ቤዛውን ያዘጋጀልንን ይሖዋን ለማወደስ እንነሳሳለን። እሱን ማወደስ የምንችልበት አንዱ መንገድ ደግሞ በስብሰባዎች ላይ ከልብ የመነጨ ሐሳብ መስጠት ነው።

13. ለይሖዋና ለልጁ ያለን ፍቅር ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? አብራራ።

13 ለይሖዋና ለልጁ ያለን ፍቅር ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ ማሳየት የምንችለው ለእነሱ ስንል መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኛ በመሆን ነው። አብዛኛውን ጊዜ በስብሰባዎች ላይ ለመገኘት የተለያዩ መሥዋዕቶችን እንከፍላለን። በርካታ ጉባኤዎች አንደኛውን ስብሰባ የሚያደርጉት በሥራ ቀናት አመሻሹ ላይ ስለሆነ አብዛኞቻችን ድካም እንደሚሰማን አያጠራጥርም። ሌላኛው ስብሰባ የሚደረገው ደግሞ ብዙዎች እረፍት ላይ በሚሆኑበት የሳምንቱ የመጨረሻ ቀን ላይ ነው። ታዲያ ድካም እየተሰማንም በስብሰባዎች ላይ ለመገኘት የምናደርገውን ጥረት ይሖዋ ያስተውላል? እንዴታ! እንዲያውም በዚህ ረገድ ይበልጥ ትግል ባደረግን መጠን ይሖዋም ለእሱ የምናሳየውን ፍቅር ይበልጥ ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል።—ማር. 12:41-44

14. ኢየሱስ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር በማሳየት ረገድ ምን ምሳሌ ትቷል?

14 ኢየሱስ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር በማሳየት ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። ለደቀ መዛሙርቱ ሲል ሕይወቱን አሳልፎ ከመስጠት ባለፈ በእያንዳንዱ ቀን ከራሱ ፍላጎት ይልቅ ለእነሱ ፍላጎት ቅድሚያ ይሰጥ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በጣም ደክሞት ወይም ተጨንቆ በነበረበት ጊዜ እንኳ ከተከታዮቹ ጋር ጊዜ አሳልፏል። (ሉቃስ 22:39-46) በተጨማሪም ትኩረት ያደረገው ከሌሎች በሚያገኘው ነገር ላይ ሳይሆን ለሌሎች በሚሰጠው ነገር ላይ ነበር። (ማቴ. 20:28) ለይሖዋና ለወንድሞቻችን ያለን ፍቅር ጠንካራ ከሆነ በጌታ ራት ላይም ሆነ በሌሎች የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እናደርጋለን።

15. ይበልጥ ትኩረት የምናደርገው እነማንን በመርዳት ላይ ነው?

15 በዓለም ላይ ያለው ብቸኛውና እውነተኛው የወንድማማች ማኅበር አባል እንደመሆናችን መጠን አዲሶች ከእኛ ጋር በስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ ለመጋበዝ አቅማችን የፈቀደውን ያህል ብዙ ሰዓት ማሳለፋችን ያስደስተናል። ሆኖም ይበልጥ ትኩረት የምናደርገው ‘በእምነት የሚዛመዱንን’ የቀዘቀዙ አስፋፊዎች በመርዳት ላይ ነው። (ገላ. 6:10) እነዚህን አስፋፊዎች በስብሰባዎች በተለይ ደግሞ በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ በማበረታታት ለእነሱ ያለንን ፍቅር እናሳያለን። ልክ እንደ ይሖዋና እንደ ኢየሱስ ሁሉ እኛም አንድ የቀዘቀዘ ክርስቲያን አፍቃሪ አባታችንና እረኛችን ወደሆነው ወደ ይሖዋ ሲመለስ እጅግ ደስ ይለናል።—ማቴ. 18:14

16. (ሀ) እርስ በርስ መበረታታት የምንችለው እንዴት ነው? ስብሰባዎቻችን ምን ጥቅም ያስገኙልናል? (ለ) ይህ ወር ኢየሱስ በዮሐንስ 3:16 ላይ የተናገራቸውን ቃላት ለማስታወስ ጥሩ ጊዜ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

16 በመጪዎቹ ሳምንታት በተቻለን መጠን በርካታ ሰዎችን ሚያዝያ 19, 2019 (ሚያዝያ 11, 2011) ዓርብ ምሽት ላይ በምናከብረው የመታሰቢያ በዓል ላይ እንዲገኙ እንጋብዝ። (“ ሰዎችን ለመጋበዝ ጥረት ታደርጋላችሁ?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ዓመቱን ሙሉ፣ ይሖዋ ባዘጋጀልን በሁሉም ስብሰባዎች ላይ አዘውትረን በመገኘት እርስ በርስ እንበረታታ። ወደ ሥርዓቱ መደምደሚያ ይበልጥ እየተቃረብን ስንሄድ ትሑት፣ ደፋርና አፍቃሪ ሆነን ለመቀጠል በስብሰባዎች ላይ መገኘት ያስፈልገናል። (1 ተሰ. 5:8-11) ይሖዋና ልጁ ላሳዩን ወደር የለሽ ፍቅር ያለንን አድናቆት በሙሉ ልባችን እናሳይ!—ዮሐንስ 3:16ን አንብብ።

መዝሙር 126 ነቅተህ ኑር፣ ጸንተህ ቁም፣ በርታ

^ አን.5 በዚህ ዓመት ውስጥ ከምናደርጋቸው ስብሰባዎች ሁሉ የላቀ ግምት የሚሰጠው ሚያዝያ 19, 2019 (ሚያዝያ 11, 2011) ዓርብ ምሽት ላይ የምናከብረው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ነው። በዚህ ስብሰባ ላይ ለመገኘት የሚያነሳሳን ምንድን ነው? ይሖዋን ማስደሰት ስለምንፈልግ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። በዚህ ርዕስ ውስጥ በመታሰቢያው በዓል ላይም ሆነ በሳምንታዊ ስብሰባዎቻችን ላይ መገኘታችን ስለ እኛ ምን እንደሚጠቁም እንመለከታለን።

^ አን.52 የሥዕሉ መግለጫ፦ በእምነቱ ምክንያት የታሰረ አንድ ወንድም ከቤተሰቡ የተላከለትን የሚያበረታታ ደብዳቤ ሲያነብ። የቤተሰቡ አባላት እንዳልረሱትና በአካባቢያቸው ሕዝባዊ ዓመፅ ቢኖርም ለይሖዋ ታማኝ ሆነው እንደቀጠሉ ማወቁ አስደስቶታል።