በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 1

“እኔ አምላክህ ነኝና አትጨነቅ”

“እኔ አምላክህ ነኝና አትጨነቅ”

“እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ። እኔ አምላክህ ነኝና አትጨነቅ። አበረታሃለሁ፤ አዎ እረዳሃለሁ።”—ኢሳ. 41:10

መዝሙር 7 ይሖዋ ኃይላችን

የትምህርቱ ዓላማ *

1-2. (ሀ) በኢሳይያስ 41:10 ላይ የሚገኘው መልእክት ዮሺኮ የተባለችን እህት የረዳት እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ይህ መልእክት ተጠብቆ እንዲቆይ ያደረገው ለምንድን ነው?

ዮሺኮ የተባለች አንዲት ታማኝ እህት አሳዛኝ ነገር ተነገራት። ዮሺኮ በጥቂት ወራት ውስጥ እንደምትሞት ሐኪሟ ገለጸችላት። በዚህ ወቅት ምን ተሰማት? በጣም የምትወደው አንድ ጥቅስ ትዝ አላት፤ ጥቅሱ ኢሳይያስ 41:10 ነው። (ጥቅሱን አንብብ።) ከዚያም ለሐኪሟ ይሖዋ እጇን እንደያዛት ስለሚሰማት ምንም እንደማትፈራ ነገረቻት። * በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘው የሚያጽናና መልእክት እህታችን በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ እንድትታመን ረድቷታል። ይህ ጥቅስ እኛም ከባድ ፈተና በሚያጋጥመን ወቅት መረጋጋት እንድንችል ይረዳናል። ጥቅሱ የሚረዳን እንዴት እንደሆነ ለማወቅ በቅድሚያ አምላክ በኢሳይያስ በኩል ይህን መልእክት ያስነገረበትን ምክንያት እንመልከት።

2 ይሖዋ በኢሳይያስ አማካኝነት እነዚህን ቃላት ያጻፈው፣ ከጊዜ በኋላ በግዞት ወደ ባቢሎን የሚወሰዱትን አይሁዳውያን ለማጽናናት ነበር። ሆኖም ይሖዋ አይሁዳውያን ግዞተኞች ብቻ ሳይሆኑ ከዚያ በኋላ የሚኖሩ ሌሎች ሕዝቦቹም እንዲጠቀሙበት ሲል ይህ መልእክት እስከ ዘመናችን ድረስ እንዲቆይ አድርጓል። (ኢሳ. 40:8፤ ሮም 15:4) ዛሬ የምንኖረው “ለመቋቋም [በሚያስቸግር] በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” ውስጥ እንደመሆኑ መጠን በኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው ማበረታቻ ከምንጊዜውም ይበልጥ ያስፈልገናል።—2 ጢሞ. 3:1

3. (ሀ) የ2019 የዓመት ጥቅስ እንዲሆን የተመረጠው ኢሳይያስ 41:10 የትኞቹን ማረጋገጫዎች ይዟል? (ለ) እነዚህ ማረጋገጫዎች የሚያስፈልጉን ለምንድን ነው?

3 በዚህ ርዕስ ውስጥ በኢሳይያስ 41:10 ላይ የሚገኙትን ይሖዋ የሰጣቸውን ሦስት እምነት የሚያጠናክሩ ማረጋገጫዎች እንመለከታለን፤ እነሱም፦ (1) ከእኛ ጋር እንደሚሆን፣ (2) አምላካችን እንደሆነ፣ (3) እንደሚረዳን የሰጣቸው ማረጋገጫዎች ናቸው። በዛሬው ጊዜ ሁላችንም እነዚህ ማረጋገጫዎች * ያስፈልጉናል፤ ምክንያቱም ልክ እንደ ዮሺኮ በሕይወታችን ውስጥ ፈታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል። በተጨማሪም በዓለም ላይ እየተከናወኑ ያሉት መጥፎ ነገሮች የሚያሳድሩብንን ተጽዕኖ መቋቋም ይኖርብናል። አልፎ ተርፎም አንዳንዶቻችን ኃያላን መንግሥታት የሚያደርሱብንን ስደት መጋፈጥ ሊያስፈልገን ይችላል። እስቲ እነዚህን ሦስት ማረጋገጫዎች አንድ በአንድ እንመርምር።

“እኔ ከአንተ ጋር ነኝ”

4. (ሀ) ይሖዋ የሰጠን የመጀመሪያው ማረጋገጫ ምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።) (ለ) ይሖዋ ለእኛ ያለውን ስሜት የገለጸው እንዴት ነው? (ሐ) እነዚህ ቃላት ምን ስሜት ያሳድሩብሃል?

4 ይሖዋ የሰጠን የመጀመሪያው ማረጋገጫ “እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ” የሚል ነው። * ይሖዋ ለእኛ ሙሉ ትኩረቱን በመስጠትና ፍቅሩን በመግለጽ ከእኛ ጋር እንደሆነ ያሳያል። ለእኛ ያለውን ስሜት የገለጸው እንዴት እንደሆነ ለማስተዋል ሞክር። “አንተ በዓይኔ ፊት ውድ ሆነሃልና፤ የተከበርክም ነህ፤ እኔም ወድጄሃለሁ” በማለት ተናግሯል። (ኢሳ. 43:4) ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ፍቅሩን እንዳያሳይ ሊያግድ የሚችል አንዳች ኃይል የለም፤ ለእኛ ያለው ታማኝነት ፈጽሞ አይናወጥም። (ኢሳ. 54:10) ይሖዋ ለእኛ ፍቅር እንዳለውና ወዳጃችን እንደሆነ ማወቃችን ልባችን በድፍረት እንዲሞላ ያደርጋል። ይሖዋ ለወዳጁ ለአብራም (አብርሃም) ጥበቃ እንዳደረገለት ሁሉ ለእኛም ጥበቃ ያደርግልናል። አብራምን “አትፍራ። እኔ ጋሻ እሆንሃለሁ” ብሎታል።—ዘፍ. 15:1

በይሖዋ እርዳታ በማንኛውም የፈተና ወንዝ ወይም ነበልባል ውስጥ ማለፍ እንችላለን (አንቀጽ 5-6⁠ን ተመልከት) *

5-6. (ሀ) ይሖዋ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ሊረዳን እንደሚፈልግ እንዴት እናውቃለን? (ለ) ከዮሺኮ ተሞክሮ ምን ትምህርት እናገኛለን?

5 ይሖዋ የሚደርሱብንን ፈተናዎች መቋቋም እንድንችል ሊረዳን ይፈልጋል፤ ለሕዝቦቹ የሰጣቸው የሚከተለው ማረጋገጫ ይህን ያሳያል፦ “በውኃዎች መካከል ስታልፍ እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ በወንዞችም መካከል ስትሻገር አያሰምጡህም። በእሳት መካከል ስትሄድ አትቃጠልም፤ ነበልባሉም አይፈጅህም።” (ኢሳ. 43:2) እነዚህ ቃላት ምን ትርጉም አላቸው?

6 ይሖዋ በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንደሚያስወግድልን ቃል አልገባም፤ ሆኖም የችግር ‘ወንዝ’ እንዲያሰምጠን ወይም የፈተና ‘ነበልባል’ ዘላቂ ጉዳት እንዲያደርስብን እንደማይፈቅድ ቃል ገብቶልናል። ከእኛ ጋር እንደሚሆንና እነዚህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ‘እንድናልፍ’ እንደሚረዳን ማረጋገጫ ሰጥቶናል። ሆኖም ይሖዋ የሚረዳን እንዴት ነው? ይሖዋ ፍርሃታችንን እንድናሸንፍና እንድንረጋጋ ይረዳናል፤ ይህም ከሞት ጋር ፊት ለፊት በምንፋጠጥበት ጊዜም እንኳ ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ ያስችለናል። (ኢሳ. 41:13) ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ዮሺኮ ይህ እውነት መሆኑን በሕይወቷ ተመልክታለች። ልጇ ይህን አስመልክታ ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “እናታችን የነበራት መረጋጋት በጣም የሚያስገርም ነበር። ይሖዋ ውስጣዊ ሰላም እንደሰጣት በግልጽ ማየት ይቻል ነበር። እስከሞተችበት ቀን ድረስ ለነርሶችና ለሌሎች ታካሚዎች ስለ ይሖዋና እሱ ስለሰጣቸው ተስፋዎች ትናገር ነበር።” ከዮሺኮ ተሞክሮ ምን ትምህርት እናገኛለን? አምላክ “እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ” በማለት በገባው ቃል ላይ እምነት ማሳደራችን የሚያጋጥሙንን ተፈታታኝ ሁኔታዎች በድፍረት እንድንጋፈጥ ይረዳናል።

“እኔ አምላክህ ነኝ”

7-8. (ሀ) ይሖዋ የሰጠው ሁለተኛው ማረጋገጫ ምንድን ነው? ምን ትርጉምስ አለው? (ለ) ይሖዋ በግዞት የተወሰዱትን አይሁዳውያን ‘አትጨነቁ’ ያላቸው ለምን ነበር? (ሐ) የይሖዋን ሕዝቦች ያረጋጋቸው በኢሳይያስ 46:3, 4 ላይ የሚገኘው የትኛው ማበረታቻ ነው?

7 ይሖዋ በኢሳይያስ በኩል ያጻፈው ሁለተኛው ማረጋገጫ ደግሞ “እኔ አምላክህ ነኝና አትጨነቅ” የሚል ነው። በዚህ ጥቅስ ላይ ያለው “አትጨነቅ” የሚለው ቃል ምን ትርጉም ያስተላልፋል? “መጨነቅ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ “የሆነ ነገር ይጎዳኛል ብሎ በመስጋት ወደ ኋላ እየዞሩ መመልከትን” ወይም “አደጋ ላይ የወደቀ ሰው እንደሚያደርገው በፍርሃት ወዲያ ወዲህ ማማተርን” ያመለክታል።

8 ይሖዋ በግዞት ወደ ባቢሎን የሚወሰዱትን አይሁዳውያን ‘አትጨነቁ’ ያላቸው ለምንድን ነው? ምክንያቱም የባቢሎን ነዋሪዎች ፍርሃት እንደሚያድርባቸው ስላወቀ ነው። ፍርሃት የሚያድርባቸው ለምንድን ነው? አይሁዳውያን በግዞት በሚቆዩባቸው 70 ዓመታት መገባደጃ አካባቢ ባቢሎን በኃያሉ የሜዶ ፋርስ ሠራዊት ጥቃት ስለሚሰነዘርባት ነው። ይሖዋ ሕዝቡን ከባቢሎን ምርኮ ነፃ ለማውጣት ይህን ሠራዊት ይጠቀምበታል። (ኢሳ. 41:2-4) ባቢሎናውያንና በዚያ የሚኖሩት ሌሎች ሕዝቦች ጠላት እየተቃረበ መሆኑን ሲያውቁ እርስ በርስ “አይዞህ፣ በርታ” በመባባል አንዳቸው ሌላውን ለማደፋፈር ይሞክራሉ። ከዚህም ሌላ ጥበቃ እንደሚያደርጉላቸው ተስፋ በማድረግ ተጨማሪ ጣዖታትን ይሠራሉ። (ኢሳ. 41:5-7) በሌላ በኩል ግን ይሖዋ እንደሚከተለው በማለት በግዞት ያሉትን አይሁዳውያን አረጋግቷቸዋል፦ “እስራኤል ሆይ፣ አንተ ግን [በዙሪያህ ካሉት ሕዝቦች በተለየ] አገልጋዬ ነህ . . . እኔ አምላክህ ነኝና አትጨነቅ።” (ኢሳ. 41:8-10) ይሖዋ “እኔ አምላክህ ነኝ” እንዳለ ልብ በሉ። ይሖዋ እነዚህን ቃላት በመናገር ታማኝ አገልጋዮቹን እንዳልረሳቸው ማለትም አሁንም አምላካቸው እንደሆነና እነሱም ሕዝቦቹ እንደሆኑ አረጋግጦላቸዋል። “እሸከማችኋለሁ . . . እንዲሁም እታደጋችኋለሁ” ብሏቸዋል። እነዚህ የሚያጽናኑና የሚያበረታቱ ቃላት በግዞት የተወሰዱትን አይሁዳውያን እንዳጠናከሯቸው ምንም ጥርጥር የለውም።—ኢሳይያስ 46:3, 4ን አንብብ።

9-10. መፍራት የማይኖርብን ለምንድን ነው? ምሳሌ ስጥ።

9 የዓለም ሁኔታ ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ መሄዱ በዙሪያችን ያሉ ሰዎችን ከምንጊዜውም ይበልጥ እንዲጨነቁ አድርጓቸዋል። እርግጥ እነዚህ ችግሮች እኛንም ይነኩናል። ሆኖም መፍራት አይኖርብንም። ይሖዋ “እኔ አምላክህ ነኝ” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቶናል። ይህ ሐሳብ ለመረጋጋት የሚያስችል ጠንካራ ምክንያት ነው የምንለው ለምንድን ነው?

10 እስቲ የሚከተለውን ምሳሌ እንመልከት፦ ጂም እና ቤን የተባሉ ሁለት ሰዎች በአንድ አውሮፕላን እየተጓዙ ነው። ሆኖም የሚጓዙበት አውሮፕላን በኃይለኛ ነፋስ ምክንያት መንገጫገጭ ጀመረ። አውሮፕላኑ ወደ ላይና ወደ ታች እየተናወጠ ባለበት ወቅት በድምፅ ማጉያው “ለተወሰነ ጊዜ ያህል ለበረራ አስቸጋሪ በሆነ የአየር ሁኔታ ውስጥ ስለምናልፍ እባካችሁ የደህንነት ቀበቷችሁን እሰሩ” የሚል ማስታወቂያ ተነገረ። ጂም በጣም ፈራ። ሆኖም የአውሮፕላን አብራሪው “ከበረራው ክፍል አብራሪያችሁ ነኝ። ምንም የሚያሰጋ ነገር ስለሌለ አትጨነቁ” በማለት ተናገረ። በዚህ ጊዜ ጂም በብስጭት ጭንቅላቱን እየነቀነቀ “አሁን ይሄ ማጽናኛ መሆኑ ነው?” ይላል። ዞር ብሎ ሲያይ ግን ቤን ምንም እንዳልተጨነቀ ያስተውላል። በመሆኑም “እንዲህ ልትረጋጋ የቻልከው እንዴት ነው?” በማለት ጠየቀው። ቤንም ፈገግ ብሎ “አብራሪውን በደንብ ስለማውቀው ነው። አባቴ ነው!” አለው። አክሎም “ቆይ ስለ አባቴ ልንገርህ። አባቴ ምን ያህል ጎበዝ አብራሪ እንደሆነ ብታውቅ አንተም መረጋጋትህ አይቀርም” በማለት ነገረው።

11. በአውሮፕላን ስለሚጓዙት ሁለት ሰዎች ከሚናገረው ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?

11 ከዚህ ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? ልክ እንደ ቤን እኛም በሰማይ ያለው አባታችንን ይሖዋን በሚገባ ስለምናውቀው መረጋጋት እንችላለን። ይሖዋ በዚህ ሥርዓት የመጨረሻ ቀናት ውስጥ የሚያጋጥሙንን እንደ ኃይለኛ ነፋስ ያሉ ችግሮች ተቋቁመን ማለፍ እንድንችል እንደሚረዳን እናውቃለን። (ኢሳ. 35:4) በይሖዋ ስለምንታመን በዙሪያችን ያለው ዓለም በፍርሃት ሲርድ እኛ ግን ተረጋግተን መኖር እንችላለን። (ኢሳ. 30:15) በተጨማሪም ቤን እንዳደረገው እኛም በአምላክ ላይ እምነት ለመጣል ያስቻሉንን ምክንያቶች ለሰዎች እንናገራለን። እነዚህ ሰዎችም ልክ እንደ እኛ፣ ምንም ዓይነት ችግር ቢያጋጥማቸው ይሖዋ እንደሚደግፋቸው እርግጠኞች መሆን ይችላሉ።

“አበረታሃለሁ [እንዲሁም] እረዳሃለሁ”

12. (ሀ) ይሖዋ የሰጠው ሦስተኛው ማረጋገጫ ምንድን ነው? (ለ) ስለ ይሖዋ ‘ክንድ’ የሚናገረው ሐሳብ ምን ይጠቁማል?

12 ይሖዋ የሰጠው ሦስተኛው ማረጋገጫ “አበረታሃለሁ፤ አዎ እረዳሃለሁ” የሚል ነው። ኢሳይያስ “ይሖዋ በኃይል ይመጣል፤ ክንዱም ስለ እሱ ይገዛል” በማለት ይሖዋ ሕዝቡን የሚያበረታው ወይም የሚያጠነክረው እንዴት እንደሆነ ቀደም ብሎ ገልጿል። (ኢሳ. 40:10) አብዛኛውን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ “ክንድ” የሚለውን ቃል ኃይልን ለማመልከት በምሳሌያዊ ሁኔታ ይጠቀምበታል። በመሆኑም የይሖዋ ‘ክንድ እንደሚገዛ’ የሚገልጸው ሐሳብ ይሖዋ ኃያል ንጉሥ እንደሆነ ይጠቁማል። በጥንት ጊዜ ለነበሩ አገልጋዮቹ ድጋፍና ጥበቃ ለማድረግ ወደር የለሽ ኃይሉን እንደተጠቀመበት ሁሉ በዛሬው ጊዜም በእሱ የሚታመኑ አገልጋዮቹን ለማጠናከርና ለመጠበቅ ኃይሉን ይጠቀማል።—ዘዳ. 1:30, 31፤ ኢሳ. 43:10 ግርጌ

ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ጥበቃ የሚያደርግበትን ኃያል ክንድ ማሸነፍ የሚችል ምንም ዓይነት መሣሪያ የለም (አንቀጽ 12-16⁠ን ተመልከት) *

13. (ሀ) ይሖዋ እንደሚያበረታን የገባውን ቃል የሚጠብቀው በተለይ በየትኛው ጊዜ ነው? (ለ) ይሖዋ ጠንካራና ልበ ሙሉ እንድንሆን የሚረዳ ምን ዋስትና ሰጥቶናል?

13 በተለይ ተቃዋሚዎች ስደት በሚያደርሱብን ጊዜ ይሖዋ “አበረታሃለሁ” በማለት የገባውን ቃል ይጠብቃል። በዛሬው ጊዜ በአንዳንድ የዓለማችን ክፍሎች ተቃዋሚዎች የስብከቱ ሥራችንን ለማስቆምና በድርጅታችን ላይ እገዳ ለመጣል ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ነው። ሆኖም እንዲህ ያለ ጥቃት ሲሰነዘርብን ከልክ በላይ አንጨነቅም። ይሖዋ የሰጠን ዋስትና ጠንካራና ልበ ሙሉ እንድንሆን ይረዳናል። “አንቺን ለማጥቃት የተሠራ ማንኛውም መሣሪያ ይከሽፋል” በማለት ቃል ገብቶልናል። (ኢሳ. 54:17) ይህ ጥቅስ ሦስት አስፈላጊ እውነታዎችን እንድንገነዘብ ያደርገናል።

14. የአምላክ ጠላቶች በእኛ ላይ ጥቃት መሰንዘራቸው የማያስደንቀን ለምንድን ነው?

14 አንደኛ፣ የክርስቶስ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን ሰዎች እንደሚጠሉን እንጠብቃለን። (ማቴ. 10:22) ኢየሱስ በመጨረሻዎቹ ቀናት ደቀ መዛሙርቱ ከባድ ስደት እንደሚደርስባቸው አስቀድሞ ተናግሯል። (ማቴ. 24:9፤ ዮሐ. 15:20) ሁለተኛ፣ የኢሳይያስ ትንቢት ተቃዋሚዎቻችን እኛን በመጥላት ብቻ እንደማይመለሱ ከዚህ ይልቅ እኛን ለማጥቃት የተለያዩ መሣሪያዎችን እንደሚጠቀሙ አስጠንቅቋል። እነዚህ መሣሪያዎች መሠሪ ማታለያዎችን፣ ዓይን ያወጡ ውሸቶችንና ከባድ ስደትን ያካትታሉ። (ማቴ. 5:11) ጠላቶቻችን እኛን ለመውጋት እነዚህን መሣሪያዎች እንዳይጠቀሙ ይሖዋ አይከለክላቸውም። (ኤፌ. 6:12፤ ራእይ 12:17) ሆኖም መፍራት አይኖርብንም። ለምን?

15-16. (ሀ) ማስታወስ ያለብን ሦስተኛው እውነታ ምንድን ነው? ኢሳይያስ 25:4, 5 ይህን ሐሳብ የሚደግፈውስ እንዴት ነው? (ለ) ኢሳይያስ 41:11, 12 ከእኛ ጋር የሚዋጉ ሁሉ ምን እንደሚጠብቃቸው ይገልጻል?

15 ሦስተኛው እውነታ መልሱን ይሰጠናል። ይሖዋ እኛን ለማጥቃት የተሠራ ‘ማንኛውም መሣሪያ እንደሚከሽፍ’ ተናግሯል። አንድ ግንብ፣ አውዳሚ ከሆነ ውሽንፍር እንደሚከልል ሁሉ ይሖዋም ‘ከጨቋኞች ቁጣ’ ይከልለናል። (ኢሳይያስ 25:4, 5ን አንብብ።) ጠላቶቻችን በእኛ ላይ ዘላቂ ጉዳት ለማድረስ የሚያደርጉት ጥረት ሁሉ ይከሽፋል።—ኢሳ. 65:17

16 በተጨማሪም ይሖዋ በእኛ ላይ “የተቆጡ ሁሉ” ወደፊት ምን እንደሚጠብቃቸው በዝርዝር በመግለጽ በእሱ ላይ ያለንን እምነት እንድናጠናክር ረድቶናል። (ኢሳይያስ 41:11, 12ን አንብብ።) ጠላቶቻችን እኛን ለማጥቃት የቱንም ያህል ቢጥሩ ወይም ውጊያው የቱንም ያህል ቢፋፋም ውጤቱ የታወቀ ነው፦ የአምላክን ሕዝቦች የሚቃወሙ ሁሉ “እንዳልነበሩ ይሆናሉ፤ ይጠፋሉም።”

በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረን በማንበብ በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከር እንችላለን (አንቀጽ 17-18⁠ን ተመልከት) *

17-18. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባችን በአምላክ ላይ ያለንን እምነት የሚያጠናክርልን እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ። (ለ) በ2019 የዓመት ጥቅስ ላይ ማሰላሰላችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

17 በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከር የምንችለው እሱን ይበልጥ በማወቅ ነው። አምላክን በሚገባ ማወቅ የምንችልበት ብቸኛው መንገድ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት ማንበብና ባነበብነው ነገር ላይ ማሰላሰል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ከዚህ በፊት ለሕዝቦቹ ጥበቃ ያደረገው እንዴት እንደሆነ የሚገልጹ አስተማማኝ ዘገባዎችን ይዟል። እነዚህ ዘገባዎች ይሖዋ በዛሬው ጊዜም እንደሚንከባከበን ያለንን እምነት ያጠናክሩልናል።

18 ኢሳይያስ፣ ይሖዋ ለእኛ ጥበቃ የሚያደርገው እንዴት እንደሆነ ለማሳየት ግሩም የሆነ አገላለጽ ተጠቅሟል። ይሖዋን እንደ እረኛ፣ አገልጋዮቹን ደግሞ እንደ ግልገሎች አድርጎ ገልጿቸዋል። ኢሳይያስ ይሖዋን አስመልክቶ ሲናገር “ግልገሎቹን በክንዱ ይሰበስባል፤ በእቅፉም ይሸከማቸዋል” ብሏል። (ኢሳ. 40:11) ይሖዋ በኃያል ክንዶቹ እቅፍ እንዳደረገን ስናስብ የደህንነትና የመረጋጋት ስሜት አይሰማንም? ታማኝና ልባም ባሪያ የተለያዩ ችግሮች ቢያጋጥሙንም ተረጋግተን መኖር እንድንችል ይረዳን ዘንድ የ2019 የዓመት ጥቅስ እንዲሆን የመረጠው ኢሳይያስ 41:10⁠ን ነው፤ ጥቅሱ “እኔ አምላክህ ነኝና አትጨነቅ” ይላል። እነዚህን የሚያጽናኑና የሚያበረታቱ ቃላት አሰላስሉባቸው። ወደፊት የሚያጋጥሟችሁን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመጋፈጥ ብርታት ይሰጧችኋል።

መዝሙር 38 ጠንካራ ያደርግሃል

^ አን.5 ለ2019 የተመረጠው የዓመት ጥቅስ በዓለማችን ላይም ሆነ በግል ሕይወታችን ውስጥ መጥፎ ነገሮች በሚከሰቱበት ጊዜም እንኳ ተረጋግተን ለመኖር የሚያስችሉንን ሦስት ምክንያቶች ይገልጻል። በዚህ ርዕስ ውስጥ እነዚህን ምክንያቶች የምንመረምር ሲሆን ይህም ከልክ በላይ እንዳንጨነቅና ይበልጥ በይሖዋ እንድንታመን ይረዳናል። በዓመት ጥቅሱ ላይ አሰላስሉበት። ከቻላችሁ ደግሞ ጥቅሱን በቃላችሁ ለመያዝ ጥረት አድርጉ። እንዲህ ማድረጋችሁ ወደፊት የሚያጋጥሟችሁን ተፈታታኝ ሁኔታዎች በድፍረት ለመጋፈጥ ይረዳችኋል።

^ አን.3 ተጨማሪ ማብራሪያ፦ ማረጋገጫ የሚለው አገላለጽ አንድ ነገር መፈጸሙ እንደማይቀር እንድንተማመን የሚያደርግን እምነት የሚጣልበት ሐሳብ ያመለክታል። ይሖዋ የሚሰጠን ማረጋገጫ ወደፊት ሊያጋጥሙን የሚችሉትን ችግሮች እያሰብን ከልክ በላይ እንዳንጨነቅ ይረዳናል።

^ አን.4 የግርጌ ማስታወሻ፦ “አትፍራ” የሚለው ቃል ሦስት ጊዜ ማለትም በኢሳይያስ 41:10, 13 እና 14 ላይ ተጠቅሶ ይገኛል። በተጨማሪም እነዚህ ጥቅሶች “እኔ” (ይሖዋን ያመለክታል) የሚለውን ቃል በተደጋጋሚ ይጠቅሳሉ። ኢሳይያስ “እኔ” የሚለውን ቃል በተደጋጋሚ እንዲጠቀም ይሖዋ በመንፈሱ የመራው ለምንድን ነው? አንድን አስፈላጊ እውነታ ይኸውም ፍርሃታችንን ማሸነፍ የምንችለው በይሖዋ በመታመን ብቻ እንደሆነ ጎላ አድርጎ ለመግለጽ ነው።

^ አን.52 የሥዕሉ መግለጫ፦ የአንድ ቤተሰብ አባላት በሥራ ቦታ፣ ከጤና ጋር በተያያዘ፣ በአገልግሎትና በትምህርት ቤት ተፈታታኝ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው።

^ አን.54 የሥዕሉ መግለጫ፦ ወንድሞችና እህቶች በመኖሪያ ቤት ውስጥ ስብሰባ እያደረጉ ሳሉ የታጠቁ ፖሊሶች ገብተው ስብሰባውን ቢያቋርጡባቸውም አልተሸበሩም።

^ አን.56 የሥዕሉ መግለጫ፦ ቋሚ የሆነ የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራም ለመጽናት የሚያስችል ብርታት ይሰጠናል።