በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 2

ከኢየሱስ ታናሽ ወንድም ተማሩ

ከኢየሱስ ታናሽ ወንድም ተማሩ

“የአምላክና የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ የሆነው ያዕቆብ።”—ያዕ. 1:1

መዝሙር 88 መንገድህን አሳውቀኝ

ማስተዋወቂያ *

1. ያዕቆብ ያደገው ምን ዓይነት ቤተሰብ ውስጥ ነው?

 የኢየሱስ ወንድም የሆነው ያዕቆብ ያደገው በመንፈሳዊ ጠንካራ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ ነው። * ወላጆቹ ዮሴፍና ማርያም ይሖዋን በጣም የሚወዱ ከመሆኑም ሌላ እሱን ለማገልገል የቻሉትን ሁሉ ያደርጉ ነበር። ያዕቆብ ሌላም በረከት አግኝቷል። ታላቅ ወንድሙ፣ ከጊዜ በኋላ መሲሕ የሆነው ኢየሱስ ነው። ያዕቆብ የዚህ ቤተሰብ አባል በመሆኑ ምንኛ ታድሏል!

ያዕቆብ በልጅነቱ ከኢየሱስ ጋር ያሳለፈው ጊዜ ታላቅ ወንድሙን በደንብ እንዲያውቀው አስችሎታል (አንቀጽ 2⁠ን ተመልከት)

2. ያዕቆብ ታላቅ ወንድሙን እንዲያደንቀው የሚያደርጉት ምን ምክንያቶች ነበሩት?

2 ያዕቆብ ታላቅ ወንድሙን እንዲያደንቀው የሚያደርጉ ብዙ ምክንያቶች ነበሩ። (ማቴ. 13:55) ለምሳሌ፣ ኢየሱስ ገና በ12 ዓመቱ ቅዱሳን መጻሕፍትን በደንብ ያውቅ ስለነበር በኢየሩሳሌም የነበሩትን የተማሩ ሽማግሌዎች እንኳ አስደምሟቸው ነበር። (ሉቃስ 2:46, 47) ያዕቆብ በአናጺነት ሙያ ከኢየሱስ ጋር አብሮ ሠርቶ ሊሆን ይችላል። እንደዚያ ከሆነ ደግሞ ወንድሙን በደንብ የማወቅ አጋጣሚ እንዳገኘ የታወቀ ነው። ናታን ሆመር ኖር ብዙውን ጊዜ እንዲህ ይል ነበር፦ “ከአንድ ሰው ጋር አብራችሁ ስትሠሩ ግለሰቡን ይበልጥ ታውቁታላችሁ።” * ያዕቆብ ሌላስ ምን አስተውሎ ሊሆን ይችላል? ኢየሱስ “በአካልና በጥበብ እያደገ እንዲሁም በአምላክና በሰው ፊት ይበልጥ ሞገስ እያገኘ” ሲሄድ አስተውሎ መሆን አለበት። (ሉቃስ 2:52) ከዚህ አንጻር ያዕቆብ ከመጀመሪያዎቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አንዱ እንደሚሆን እንጠብቅ ይሆናል። እውነታው ግን ይህ አይደለም።

3. ያዕቆብ ኢየሱስ አገልግሎቱን በጀመረበት ወቅት ተቀብሎታል?

3 ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት ያዕቆብ ደቀ መዝሙሩ አልሆነም። (ዮሐ. 7:3-5) እንዲያውም ያዕቆብ፣ ኢየሱስን “አእምሮውን ስቷል” ካሉት ዘመዶቹ አንዱ ሊሆን ይችላል። (ማር. 3:21) በኋላ ላይ ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ በተሰቀለበት ወቅትም ያዕቆብ ከእናታቸው ከማርያም ጋር በቦታው እንደነበር የሚጠቁም ነገር የለም።—ዮሐ. 19:25-27

4. የትኞቹን ነጥቦች እንመረምራለን?

4 በኋላ ላይ ግን ያዕቆብ በኢየሱስ አመነ። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥም የተከበረ ሽማግሌ ሆነ። በዚህ ርዕስ ላይ ከያዕቆብ የምናገኛቸውን ሁለት ትምህርቶች እንመለከታለን፦ (1) ምንጊዜም ትሑት መሆን ያለብን ለምንድን ነው? እንዲሁም (2) ውጤታማ አስተማሪዎች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

እንደ ያዕቆብ ምንጊዜም ትሑት ሁኑ

ያዕቆብ ኢየሱስ ከተገለጠለት በኋላ በትሕትና እርምጃ ወስዷል፤ ከዚያ ጊዜ አንስቶ ታማኝ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ሆኖ አገልግሏል (ከአንቀጽ 5-7⁠ን ተመልከት)

5. ያዕቆብ፣ ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ሲገለጥለት ምን ምላሽ ሰጠ?

5 ያዕቆብ የኢየሱስ ታማኝ ተከታይ የሆነው መቼ ነው? ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ “ለያዕቆብ ታየ፤ ቀጥሎም ለሐዋርያቱ በሙሉ ታየ።” (1 ቆሮ. 15:7) ያዕቆብ ከኢየሱስ ጋር የተገናኘበት ይህ አጋጣሚ በሕይወቱ ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል። በኋላ ላይ ሐዋርያቱ ኢየሩሳሌም ባለ አንድ ደርብ ላይ ሆነው ቃል የተገባላቸውን መንፈስ ቅዱስ ይጠባበቁ በነበረበት ወቅት ያዕቆብ አብሯቸው ነበር። (ሥራ 1:13, 14) ከጊዜ በኋላ ያዕቆብ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የበላይ አካል አባል ሆኖ የማገልገል መብት አግኝቷል። (ሥራ 15:6, 13-22፤ ገላ. 2:9) ከ62 ዓ.ም. ገደማ በፊት ደግሞ በመንፈስ መሪነት ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ደብዳቤ ጽፏል። ተስፋችን ሰማያዊም ይሁን ምድራዊ ይህ ደብዳቤ በዛሬው ጊዜ ያለነውን ሁሉ ይጠቅመናል። (ያዕ. 1:1) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖረው ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ እንደዘገበው ያዕቆብ የአይሁድ ሊቀ ካህናት የሆነው ሐናንያ (የሐና ልጅ) ባስተላለፈው ትእዛዝ ተገድሏል። ያዕቆብ ምድራዊ ሕይወቱን እስካጠናቀቀበት ጊዜ ድረስ ይሖዋን በታማኝነት አገልግሏል።

6. ያዕቆብ በዘመኑ ከነበሩት የሃይማኖት መሪዎች የሚለየው በምንድን ነው?

6 ያዕቆብ ትሑት ነበር። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ያዕቆብ በኋላ ላይ ኢየሱስን ሲያገኘው የሰጠውን ምላሽ በዘመኑ የነበሩ ብዙዎቹ የሃይማኖት መሪዎች ከሰጡት ምላሽ ጋር ማነጻጸር ይቻላል። ያዕቆብ፣ ኢየሱስ የአምላክ ልጅ መሆኑን የሚያሳይ የማያሻማ ማስረጃ ሲያገኝ በትሕትና ተቀብሏል። በኢየሩሳሌም የነበሩት የካህናት አለቆች ግን እንዲህ አላደረጉም። ለምሳሌ፣ ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት እንዳስነሳው መካድ አልቻሉም። ሆኖም ኢየሱስ የይሖዋ ወኪል መሆኑን የሚያሳየውን ማስረጃ ከመቀበል ይልቅ ኢየሱስንም ሆነ አልዓዛርን ለመግደል ተነሱ። (ዮሐ. 11:53፤ 12:9-11) በኋላ ላይ ደግሞ ኢየሱስ ራሱ ከሞት ሲነሳ ይህን እውነታ ከሕዝቡ ለመደበቅ አሲረዋል። (ማቴ. 28:11-15) ኩራት እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች መሲሑን እንዳይቀበሉ አድርጓቸዋል።

7. ኩራትን ማስወገድ ያለብን ለምንድን ነው?

7 የምናገኘው ትምህርት፦ ኩራትን አስወግዱ፤ እንዲሁም ምንጊዜም ለመማር ፈቃደኞች ሁኑ። የልባችን የደም ሥሮች እንዲደድሩና ልባችን መምታት እንዲከብደው የሚያደርግ በሽታ አለ፤ ኩራትም ልክ እንደዚህ በሽታ ምሳሌያዊው ልባችን እንዲደነድንና የይሖዋን መመሪያ ለመቀበል አሻፈረኝ እንድንል ሊያደርገን ይችላል። ፈሪሳውያን ልባቸው እንዲደነድን ፈቅደው ነበር፤ ኢየሱስ የአምላክ መንፈስ እንዳለውና የአምላክ ልጅ እንደሆነ የሚያሳየውን ግልጽ ማስረጃ ለመቀበል ፈቃደኛ እንዳይሆኑ ያደረጋቸው ይህ ነው። (ዮሐ. 12:37-40) ይህ አካሄዳቸው አደገኛ ነበር፤ ምክንያቱም የዘላለም ሕይወት የማግኘት አጋጣሚያቸውን አሳጥቷቸዋል። (ማቴ. 23:13, 33) እንግዲያው ምንጊዜም የአምላክ ቃል እና መንፈስ ቅዱስ ማንነታችንን እንዲቀርጹት እንዲሁም በአስተሳሰባችን እና በውሳኔያችን ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድሩ መፍቀዳችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! (ያዕ. 3:17) ያዕቆብ ትሑት ስለነበር ከይሖዋ ለመማር ፈቃደኛ ሆኗል። ደግሞም ቀጥሎ እንደምንመለከተው ያዕቆብ ውጤታማ አስተማሪ መሆን የቻለው ትሑት በመሆኑ ነው።

እንደ ያዕቆብ ውጤታማ በሆነ መንገድ አስተምሩ

8. ጥሩ አስተማሪዎች ለመሆን ምን ይረዳናል?

8 ያዕቆብ በጣም የተማረ የሚባል ሰው አልነበረም። በዘመኑ የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች እሱን የሚያዩት ሐዋርያው ጴጥሮስን እና ሐዋርያው ዮሐንስን ያዩበት በነበረው መንገድ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም፤ በእነሱ አመለካከት ‘ያልተማረና ተራ’ ተደርጎ የሚቆጠር ሰው ነበር። (ሥራ 4:13) ሆኖም ያዕቆብ ውጤታማ አስተማሪ መሆን ችሏል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በስሙ የሚጠራውን መጽሐፍ ስናነብ ይህን በግልጽ ማየት እንችላለን። እኛም ልክ እንደ ያዕቆብ በዓለማዊ ትምህርት ብዙም አልገፋን ይሆናል። ያም ቢሆን በይሖዋ መንፈስ እርዳታና ከድርጅቱ በምናገኘው ጠቃሚ ሥልጠና እኛም ጥሩ አስተማሪዎች መሆን እንችላለን። እስቲ ያዕቆብ በአስተማሪነት ረገድ የተወውን ምሳሌ እንዲሁም ከእሱ ምሳሌነት ምን ትምህርት እንደምናገኝ እንመርምር።

9. ያዕቆብ የተጠቀመበትን የማስተማሪያ ዘዴ ግለጽ።

9 ያዕቆብ ከባድ ቃላት ወይም የተወሳሰበ ማብራሪያ አልተጠቀመም። በመሆኑም መልእክቱን የሚያነቡት ሰዎች ምን ማድረግ እንዳለባቸውና የተባሉትን ነገር እንዴት ማድረግ እንደሚችሉ መረዳት አልከበዳቸውም። ለምሳሌ ክርስቲያኖች ግፍ ሲደርስባቸው በውስጣቸው ምሬት ሳያድር ሁኔታውን በጽናት መቋቋም እንዳለባቸው ለማስተማር እንዴት ያለ ቀላል መንገድ እንደተጠቀመ እንመልከት። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የጸኑትን ደስተኞች እንደሆኑ አድርገን እንቆጥራቸዋለን። ስለ ኢዮብ ጽናት ሰምታችኋል፤ በውጤቱም ይሖዋ ያደረገለትን አይታችኋል፤ በዚህም ይሖዋ እጅግ አፍቃሪና መሐሪ እንደሆነ ተመልክታችኋል።” (ያዕ. 5:11) ያዕቆብ ለትምህርቱ ዋና መሠረት አድርጎ የተጠቀመው ቅዱሳን መጻሕፍትን እንደሆነ ልብ በሉ። የአምላክን ቃል ተጠቅሞ፣ ይሖዋ እንደ ኢዮብ ያሉ ለእሱ ታማኝ የሆኑ ሰዎችን ምንጊዜም እንደሚባርክ አንባቢዎቹን አስገንዝቧቸዋል። ያዕቆብ ቀላል ቃላትና ለመረዳት የማይከብድ ማብራሪያ በመጠቀም ነጥቡን አስተላልፏል። በመሆኑም የአንባቢዎቹ ትኩረት እንዲያርፍ ያደረገው በእሱ ላይ ሳይሆን በይሖዋ ላይ ነው።

10. ያዕቆብን በማስተማር ዘዴው ልንመስለው የምንችልበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?

10 የምናገኘው ትምህርት፦ መልእክታችሁ ቀላል እንዲሆን አድርጉ፤ እንዲሁም ከአምላክ ቃል አስተምሩ። ግባችን በእውቀታችን ሌሎችን ማስደመም መሆን የለበትም፤ ከዚህ ይልቅ የምናስተምራቸው ሰዎች ይሖዋ ባለው ጥልቅ እውቀት እንዲሁም ለእነሱ ባለው አሳቢነት ልባቸው እንዲነካ እንፈልጋለን። (ሮም 11:33) ምንጊዜም ከቅዱሳን መጻሕፍት የምናስተምር ከሆነ ይህንን ግባችንን ማሳካት እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችንን እኛ በእነሱ ቦታ ብንሆን ኖሮ ምን እንደምናደርግ ልንነግራቸው አይገባም። ከዚህ ይልቅ እነሱ ራሳቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያሉ ምሳሌዎችን እንዲያስቡባቸው እንዲሁም የይሖዋ አስተሳሰብ እና ስሜት ምን እንደሆነ ለማስተዋል እንዲጥሩ ልንረዳቸው ይገባል። እንዲህ ካደረግን እርምጃ ለመውሰድ የሚያነሳሳቸው እኛን ሳይሆን ይሖዋን ለማስደሰት ያላቸው ፍላጎት ይሆናል።

11. በያዕቆብ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ምን ችግሮች ነበሩባቸው? እሱስ ምን ምክር ሰጥቷቸዋል? (ያዕቆብ 5:13-15)

11 ያዕቆብ እውነታውን ከግምት ያስገባ ነበር። ያዕቆብ ከጻፈው ደብዳቤ እንደምንረዳው የእምነት ባልንጀሮቹ ያሉባቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያውቅ ነበር፤ እነዚህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመወጣት የሚረዳ ግልጽ መመሪያም ሰጥቷቸዋል። ለምሳሌ አንዳንድ ክርስቲያኖች የተሰጣቸውን ምክር ቶሎ ተግባራዊ አያደርጉም ነበር። (ያዕ. 1:22) ሌሎች ለሀብታሞች ያዳሉ ነበር። (ያዕ. 2:1-3) አንደበታቸውን መቆጣጠር የሚቸገሩም ነበሩ። (ያዕ. 3:8-10) እነዚህ ከባድ ችግሮች ቢሆኑም ያዕቆብ በእምነት ባልንጀሮቹ ተስፋ አልቆረጠባቸውም። በደግነት ሆኖም በግልጽ ምክር ሰጥቷቸዋል። በመንፈሳዊ የሚንገዳገዱ ካሉም የሽማግሌዎችን እርዳታ እንዲጠይቁ አበረታቷቸዋል።ያዕቆብ 5:13-15ን አንብብ።

12. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችንን ለመርዳት ጥረት ስናደርግ አዎንታዊ መሆናችንን የምናሳየው እንዴት ነው?

12 የምናገኘው ትምህርት፦ እውነታውን ከግምት አስገቡ፤ ሆኖም ለሌሎች አዎንታዊ አመለካከት ይኑራችሁ። መጽሐፍ ቅዱስን የምናስጠናቸው ብዙ ሰዎች፣ የተማሩትን ተግባራዊ ማድረግ ያታግላቸው ይሆናል። (ያዕ. 4:1-4) መጥፎ ልማዶቻቸውን ሙሉ በሙሉ ማስወገድና የክርስቶስ ዓይነት ባሕርያት ማዳበር ጊዜ ሊወስድባቸው ይችላል። የያዕቆብን ምሳሌ በመከተል ጥናቶቻችንን ሊያስተካክሉት የሚገባውን ነገር በድፍረት ልንነግራቸው ይገባል። በተጨማሪም ምንጊዜም ስለ እነሱ አዎንታዊ መሆን ይኖርብናል፤ ይሖዋ ትሑት ሰዎችን ወደ ራሱ እንደሚስብና በሕይወታቸው ውስጥ ለውጥ ለማድረግ የሚያስፈልጋቸውን ጥንካሬ እንደሚሰጣቸው እንተማመናለን።—ያዕ. 4:10

13. ያዕቆብ 3:2 እና የግርጌ ማስታወሻው እንደሚጠቁመው ያዕቆብ የትኛውን እውነታ ተቀብሏል?

13 ያዕቆብ ለራሱ ተገቢው አመለካከት ነበረው። ያዕቆብ ያደገበት ቤተሰብ ወይም ያገኛቸው መብቶች ከሌሎች ልዩ እንደሚያደርጉት ወይም ከመንፈሳዊ ወንድሞቹ እና እህቶቹ እንደሚያስበልጡት አልተሰማውም። የእምነት ባልንጀሮቹን “የተወደዳችሁ ወንድሞቼ” ሲል ጠርቷቸዋል። (ያዕ. 1:16, 19፤ 2:5) በሌሎች ዘንድ እንከን የሌለበት መስሎ ለመታየት አልሞከረም፤ ከዚህ ይልቅ “ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንሳሳታለን” በማለት ራሱንም አካትቷል።ያዕቆብ 3:2ን እና የግርጌ ማስታወሻውን አንብብ።

14. ስህተት እንደምንሠራ በሐቀኝነት መናገር ያለብን ለምንድን ነው?

14 የምናገኘው ትምህርት፦ ሁላችንም ኃጢአተኞች እንደሆንን አስታውሱ። ከምናስተምራቸው ሰዎች የተሻልን እንደሆንን አድርገን ማሰብ የለብንም። ለምን? ጥናታችን ጨርሶ እንደማንሳሳት እንዲሰማው ካደረግን መቼም ቢሆን የአምላክን መሥፈርቶች ማሟላት እንደማይችል ሊሰማው ይችላል። ከዚህ ይልቅ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን መከተል እንቸገር የነበረበት ጊዜ እንደነበረና ይሖዋ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን እንድንወጣ እንዴት እንደረዳን ልንነግረው እንችላለን። ይህም እሱም የይሖዋ አገልጋይ መሆን እንደሚችል እንዲሰማው ያደርጋል።

ያዕቆብ የተጠቀመባቸው ምሳሌዎች ቀላል፣ ግልጽና ውጤታማ ነበሩ (ከአንቀጽ 15-16⁠ን ተመልከት) *

15. ያዕቆብ ምን ዓይነት ምሳሌዎች ተጠቅሟል? (ያዕቆብ 3:2-6, 10-12)

15 ያዕቆብ ልብ የሚነኩ ምሳሌዎች ተጠቅሟል። በምሳሌ ተጠቅሞ ውጤታማ በሆነ መንገድ በማስተማር ረገድ የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ እንዳገኘ ግልጽ ቢሆንም ታላቅ ወንድሙ ኢየሱስ የተጠቀመባቸውን ምሳሌዎች ማጥናቱም ጠቅሞት መሆን አለበት። ያዕቆብ የተጠቀመባቸው ምሳሌዎች ቀላል ናቸው፤ ምሳሌዎቹ የያዙት ትምህርትም ግልጽ ነው።ያዕቆብ 3:2-6, 10-12ን አንብብ።

16. ውጤታማ ምሳሌዎች መጠቀም ያለብን ለምንድን ነው?

16 የምናገኘው ትምህርት፦ ውጤታማ ምሳሌዎች ተጠቀሙ። ውጤታማ ምሳሌዎች ጆሮን ወደ ዓይን የመቀየር ኃይል አላቸው። የምናስተምራቸው ሰዎች፣ ነገሩን በዓይነ ሕሊናቸው እንዲሥሉት ይረዷቸዋል። በአእምሯቸው ውስጥ ምስል መፈጠሩ ደግሞ ቁልፍ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ለማስታወስ ያስችላቸዋል። ኢየሱስ ውጤታማ ምሳሌዎችን በመጠቀም ረገድ የተዋጣለት አስተማሪ ነበር፤ ወንድሙ ያዕቆብም የእሱን ምሳሌ ተከትሏል። እስቲ ያዕቆብ ከተጠቀመባቸው ምሳሌዎች አንዱን እንመልከት፤ ይህ ምሳሌ ውጤታማ የሆነው ለምን እንደሆነም እንመረምራለን።

17. በያዕቆብ 1:22-25 ላይ የሚገኘው ምሳሌ በጣም ውጤታማ የሆነው ለምንድን ነው?

17 ያዕቆብ 1:22-25ን አንብብ። ያዕቆብ ስለ መስተዋት የሰጠው ምሳሌ ውጤታማ የሆነባቸውን የተለያዩ ምክንያቶች መጥቀስ ይቻላል። ሊያጎላ የፈለገው ነጥብ ግልጽ ነው፦ ከአምላክ ቃል ጥቅም ማግኘት ከፈለግን ከማንበብ ባለፈ ያነበብነውን ተግባራዊ ማድረግ አለብን። ያዕቆብ የመረጠው ቶሎ ወደ አንባቢዎቹ አእምሮ ሊመጣ የሚችል ምሳሌ ነው፦ በመስተዋት መልኩን እያየ ያለ ሰው። ታዲያ ያዕቆብ ሊያስተላልፍ የፈለገው ነጥብ ምንድን ነው? አንድ ሰው በመስተዋት መልኩን ሲያይ ሊያስተካክል የሚገባው ነገር ቢያስተውልና ከዚያ በኋላ ምንም ባያደርግ ሞኝነት ነው። በተመሳሳይም እኛ የአምላክን ቃል ስናነብ በባሕርያችን ላይ ልናስተካክለው የሚገባ ነገር ብናስተውልና ምንም እርምጃ ባንወስድ ሞኝነት ይሆንብናል።

18. ምሳሌ ስንጠቀም የትኞቹን ሦስት ነገሮች ማድረግ አለብን?

18 ምሳሌ ስትጠቀሙ የሚከተሉትን ሦስት ነገሮች በማድረግ ያዕቆብን መምሰል ትችላላችሁ፦ (1) ምሳሌው ልታስተላልፉት የፈለጋችሁትን ነጥብ ለማጉላት የሚረዳችሁ መሆኑን አረጋግጡ። (2) ቶሎ ወደ አድማጮቻችሁ አእምሮ ሊመጣ የሚችል ምሳሌ ተጠቀሙ። (3) ምሳሌው የሚያስተላልፈውን ትምህርት ግልጽ አድርጉ። ተስማሚ ምሳሌ ማግኘት ከተቸገራችሁ ጽሑፎቻችን ላይ ማግኘት ትችላላችሁ፤ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ማውጫ (እንግሊዝኛ) ላይ “ምሳሌዎች (Illustrations)” በሚለው ሥር ተመልከቱ። በዚህ ክፍል ሥር፣ ልትጠቀሙባቸው የምትችሉ ብዙ ምሳሌዎች ታገኛላችሁ። አንድ ነገር ግን አስታውሱ፦ ምሳሌዎች እንደ ድምፅ ማጉያ ናቸው። ልታስተላልፉት የፈለጋችሁትን ነጥብ ያጎሉላችኋል። ስለዚህ በምሳሌ ልታስረዱ የሚገባው ቁልፍ ነጥቦችን ብቻ ነው። እርግጥ ነው፣ የማስተማር ችሎታችንን ማሻሻል የምንፈልግበት ዋነኛ ምክንያት በተቻለ መጠን ብዙዎች የይሖዋን ደስተኛ ቤተሰብ እንዲቀላቀሉ መርዳት እንጂ ወደ ራሳችን ትኩረት መሳብ አይደለም።

19. መንፈሳዊ ቤተሰባችንን እንደምንወድ የምናሳየው እንዴት ነው?

19 ማናችንም ብንሆን ፍጹም ከሆነ ታላቅ ወንድም ጋር የማደግ መብት አላገኘንም። ሆኖም ክርስቲያን ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ባቀፈው ትልቅ ቤተሰብ ውስጥ ሆነን ይሖዋን የማገልገል መብት አግኝተናል። አብረናቸው ጊዜ በማሳለፍ፣ ከእነሱ ትምህርት በመቅሰም እንዲሁም በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ በታማኝነት አብረናቸው በመካፈል እንደምንወዳቸው እናሳያለን። በአመለካከታችን፣ በምግባራችን እና በምናስተምርበት መንገድ የያዕቆብን ምሳሌ ለመከተል የምንጥር ከሆነ ይሖዋን እናስከብራለን፤ እንዲሁም ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች አፍቃሪ ወደሆነው የሰማዩ አባታችን እንዲቀርቡ መርዳት እንችላለን።

መዝሙር 114 “በትዕግሥት ጠብቁ”

^ ያዕቆብና ኢየሱስ ያደጉት አብረው ነው። በመሆኑም ያዕቆብ ፍጹም የሆነውን የአምላክ ልጅ በወቅቱ ከነበሩት ከአብዛኞቹ ሰዎች የበለጠ ያውቀው ነበር። በኋላ ላይ ያዕቆብ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበረው የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ እንደ ዓምድ ለመሆን በቅቷል። በዚህ ርዕስ ላይ ከኢየሱስ ታናሽ ወንድም ሕይወትና ትምህርት ምን እንደምንማር እንመለከታለን።

^ ኢየሱስ ለያዕቆብ የእናቱ ልጅ ነው፤ ስለዚህ ወንድሙ ነው። ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው ያዕቆብ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በስሙ የሚጠራውን ደብዳቤ ጽፏል።

^ ናታን ሆመር ኖር የበላይ አካል አባል ነበር። ምድራዊ ሕይወቱን ያጠናቀቀው በ1977 ነው።

^ የሥዕሉ መግለጫ፦ ያዕቆብ አንደበትን በአግባቡ አለመጠቀም ያለውን አደጋ ለማጉላት ትንሽ እሳትን ምሳሌ አድርጎ ተጠቅሟል፤ ይህ ምሳሌ ሰዎች በቀላሉ ሊረዱት የሚችሉት ነው።