በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 5

“ጊዜያችሁን በተሻለ መንገድ ተጠቀሙበት”

“ጊዜያችሁን በተሻለ መንገድ ተጠቀሙበት”

“የምትመላለሱት ጥበብ እንደጎደላቸው ሳይሆን እንደ ጥበበኛ ሰዎች መሆኑን ምንጊዜም በጥንቃቄ አስተውሉ፤ . . . ጊዜያችሁን በተሻለ መንገድ ተጠቀሙበት።”—ኤፌ. 5:15, 16

መዝሙር 8 ይሖዋ መጠጊያችን ነው

ማስተዋወቂያ *

1. ከይሖዋ ጋር ጊዜ ማሳለፍ የምንችለው እንዴት ነው?

 ከምንወዳቸው ሰዎች ጋር ጊዜ ማሳለፍ ያስደስተናል። ጥሩ ትዳር ያላቸው ባልና ሚስት ብቻቸውን አብረው የሚያሳልፉት ምሽት ሲያገኙ ደስ ይላቸዋል። ወጣቶች ከጓደኞቻቸው ጋር ጊዜ ማሳለፍ ያስደስታቸዋል። ደግሞም ሁላችንም ከእምነት አጋሮቻችን ጋር ጊዜ ማሳለፍ እንፈልጋለን። ከምንም በላይ ግን ከአምላካችን ጋር ጊዜ ማሳለፍ ትልቅ ደስታ ይሰጠናል። ወደ እሱ በመጸለይ፣ ቃሉን በማንበብ እንዲሁም በዓላማውና በድንቅ ባሕርያቱ ላይ በማሰላሰል ከእሱ ጋር ጊዜ ማሳለፍ እንችላለን። በእርግጥም ከይሖዋ ጋር የምናሳልፈው ጊዜ ለእኛ በጣም ውድ ነው!—መዝ. 139:17

2. ምን እንቅፋት የሚሆንብን ነገር አለ?

2 ከይሖዋ ጋር ጊዜ ማሳለፍ የሚያስደስተን ነገር ቢሆንም እንቅፋት የሚሆንብን አንድ ነገር አለ፤ ጊዜያችን በጣም የተጣበበ ነው። በመሆኑም ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የሚሆን ጊዜ ማግኘት ሊከብደን ይችላል። ሰብዓዊ ሥራ፣ የቤተሰብ ኃላፊነት እና ሌሎች አስፈላጊ እንቅስቃሴዎች ጊዜያችንን በጣም ስለሚይዙብን ለመጸለይ፣ ለማጥናት ወይም ለማሰላሰል ጊዜ እንደሌለን ሊሰማን ይችላል።

3. ጊዜያችንን የሚሻማብን ሌላው ነገር ምንድን ነው?

3 ሳይታወቀን ጊዜያችንን የሚሻማብን ሌላም ነገር አለ። ጠንቃቆች ካልሆንን በራሳቸው ምንም ስህተት የሌለባቸው አንዳንድ እንቅስቃሴዎች ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ የምንጠቀምበትን ጊዜ ሊሰርቁብን ይችላሉ። በመዝናኛ የምናሳልፈውን ጊዜ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ሁላችንም አልፎ አልፎ ዘና ማለታችን ይጠቅመናል። ሆኖም ጤናማ መዝናኛም እንኳ ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የምናውለው ጊዜ እስክናጣ ድረስ ጊዜያችንን ሊሻማብን ይችላል። በመሆኑም ለመዝናኛ ከተገቢው ያለፈ ቦታ እንዳንሰጥ መጠንቀቅ ይኖርብናል።—ምሳሌ 25:27፤ 1 ጢሞ. 4:8

4. በዚህ ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

4 በዚህ ርዕስ ላይ፣ ቅድሚያ ልንሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን መወሰን አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነ እንመለከታለን። በተጨማሪም ከይሖዋ ጋር የምናሳልፈውን ጊዜ በተሻለ መንገድ መጠቀም የምንችለው እንዴት እንደሆነና ይህን ጊዜ በጥበብ መጠቀማችን ምን ጥቅም እንደሚያስገኝልን እናያለን።

ጥበብ ያለበት ምርጫ አድርግ፤ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን ወስን

5. በኤፌሶን 5:15-17 ላይ የሚገኘው ምክር አንድ ወጣት ከሁሉ የተሻለውን የሕይወት ጎዳና እንዲመርጥ የሚረዳው እንዴት ነው?

5 ከሁሉ የተሻለውን የሕይወት ጎዳና ምረጥ። ወጣቶች ‘የትኛውን የሕይወት ጎዳና ልምረጥ?’ የሚለው ጉዳይ ብዙ ጊዜ ያሳስባቸዋል። በአንድ በኩል የትምህርት ቤት አማካሪዎችና የማያምኑ የቤተሰብ አባላት፣ በዓለም ላይ አንቱ የሚያስብል ሥራ ለማግኘት ከፍተኛ ትምህርት እንዲከታተሉ ይገፋፏቸው ይሆናል። ይህ አካሄድ በአብዛኛው ጊዜያቸውን ሙሉ በሙሉ ይወስድባቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ወላጆቻቸውና በጉባኤ ውስጥ ያሉ ክርስቲያኖች ሕይወታቸውን ይሖዋን ለማገልገል እንዲጠቀሙበት ያበረታቷቸው ይሆናል። ታዲያ ይሖዋን የሚወድ አንድ ወጣት ከሁሉ የተሻለውን ውሳኔ ለማድረግ ምን ይረዳዋል? ኤፌሶን 5:15-17 ማንበቡና በዚያ ላይ ማሰላሰሉ ይጠቅመዋል። (ጥቅሱን አንብብ።) አንድ ወጣት ይህን ጥቅስ ካነበበ በኋላ እንደሚከተለው ብሎ ራሱን ሊጠይቅ ይችላል፦ ‘“የይሖዋ ፈቃድ” ምንድን ነው? እሱ የሚደሰተው ምን ዓይነት ውሳኔ ባደርግ ነው? ጊዜዬን ከሁሉ በተሻለ መንገድ መጠቀም የምችለው የትኛውን ጎዳና ብከተል ነው?’ “ቀኖቹ ክፉዎች” እንደሆኑና በሰይጣን የሚመራው ይህ ሥርዓት በቅርቡ እንደሚጠፋ አስታውሱ። እንግዲያው ሕይወታችንን የይሖዋን ሞገስ በሚያስገኝልን መንገድ መጠቀማችን የጥበብ አካሄድ ነው።

6. ማርያም ምን ምርጫ አድርጋለች? ጥበብ የሚንጸባረቅበት ምርጫ የሆነውስ ለምንድን ነው?

6 ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን ወስን። አንዳንዴ ጊዜያችንን በተሻለ መንገድ መጠቀም፣ በራሳቸው ምንም ስህተት ከሌለባቸው ሁለት እንቅስቃሴዎች አንዱን መምረጥ ይጠይቃል። ኢየሱስ ወደ ማርያም እና ወደ ማርታ ቤት እንደሄደ የሚገልጸው በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ ታሪክ ነጥቡን ያጎላልናል። እንግዳ ተቀባይ የሆነችው ማርታ ኢየሱስን የማስተናገድ መብት በማግኘቷ በጣም ተደስታ ትልቅ ድግስ ለማዘጋጀት ጉድ ጉድ ማለት ጀመረች። እህቷ ማርያም ግን ይህን አጋጣሚ ልትጠቀምበት ስለፈለገች ከጌታዋ ጎን ቁጭ ብላ ትምህርቱን ማዳመጥ ጀመረች። ማርታ ኢየሱስን ለማስተናገድ የተነሳችው መልካም አስባ እንደሆነ የታወቀ ነው፤ ኢየሱስ ግን “ማርያም . . . የተሻለውን ድርሻ መርጣለች” ብሏል። (ሉቃስ 10:38-42 ግርጌ) ከጊዜ በኋላ ማርያም በዚያን ዕለት ምን ምግብ እንደቀረበ እንኳ ትዝ አይላት ይሆናል። ከኢየሱስ የተማረችውን ነገር ግን ፈጽሞ እንደማትረሳው የታወቀ ነው። ማርያም ከኢየሱስ ጋር ለምታሳልፈው ጊዜ ትልቅ ቦታ እንደሰጠች ሁሉ እኛም ከይሖዋ ጋር የምናሳልፈውን ጊዜ ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን። ታዲያ ይህን ጊዜ በተሻለ መንገድ መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?

ከይሖዋ ጋር የምታሳልፈውን ጊዜ ከሁሉ በተሻለ መንገድ ተጠቀምበት

7. ጸሎት፣ ጥናትና ማሰላሰል በጣም አስፈላጊ የሆኑት ለምንድን ነው?

7 ጸሎት፣ ጥናትና ማሰላሰል የአምልኳችን ክፍል እንደሆኑ አስታውስ። ስንጸልይ በጣም ከሚወደን የሰማዩ አባታችን ጋር እየተነጋገርን ነው። (መዝ. 5:7) መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና የጥበብ ሁሉ ምንጭ የሆነውን ‘የአምላክን እውቀት’ እየቀሰምን ነው። (ምሳሌ 2:1-5) ስናሰላስል ደግሞ ይሖዋ ስላሉት ማራኪ ባሕርያት እንዲሁም ለፍጥረታቱ ስላለው አስደናቂ ዓላማና እኛ በዚህ ዓላማ ውስጥ ስላለን ቦታ እናስባለን። ታዲያ ከዚህ የተሻለ ጊዜያችንን ልንጠቀምበት የምንችልበት መንገድ አለ? ይሁንና ለይሖዋ ልናውል አስበን የወሰንነውን ጊዜ ውጤታማ በሆነ መንገድ ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው?

የግል ጥናት ለማድረግ ምቹ የሆነ ጸጥ ያለ ስፍራ ማግኘት ትችላለህ? (ከአንቀጽ 8-9⁠ን ተመልከት)

8. ኢየሱስ በምድረ በዳ ጊዜውን ከተጠቀመበት መንገድ ምን ትምህርት እናገኛለን?

8 የሚቻል ከሆነ ጸጥ ያለ ቦታ ምረጥ። ኢየሱስ ያደረገውን እንደ ምሳሌ እንመልከት። ምድራዊ አገልግሎቱን ከመጀመሩ በፊት 40 ቀናት በምድረ በዳ አሳልፏል። (ሉቃስ 4:1, 2) እንዲህ ባለ ጸጥ ያለ ስፍራ ኢየሱስ ወደ ይሖዋ መጸለይና አባቱ ለእሱ ስላለው ፈቃድ ማሰላሰል የሚችልበት ጥሩ አጋጣሚ ነበረው። ኢየሱስ እንዲህ ማድረጉ ከፊቱ ለሚጠብቀው ፈተና አዘጋጅቶት እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ታዲያ ኢየሱስ ከተወው ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? የምትኖረው ተለቅ ያለ ቤተሰብ ውስጥ ከሆነ ቤት ውስጥ ጸጥ ያለ ስፍራ ማግኘት አስቸጋሪ ሊሆንብህ ይችላል። ሁኔታህ እንዲህ ከሆነ ከቤት ውጭ ተስማሚ የሆነ ቦታ ማግኘት ትችል ይሆን? ለምሳሌ፣ ጁሊ የተባለች እህት ወደ ይሖዋ መጸለይ ስትፈልግ የምታደርገው ይህን ነው። እሷና ባለቤቷ የሚኖሩት ፈረንሳይ ውስጥ ባለ ትንሽ አፓርታማ ውስጥ ነው፤ ብቻዋን የምትሆንበትና ትኩረቷ የማይከፋፈልበት ጊዜ ማግኘት ትቸገራለች። “ስለዚህ በየቀኑ ወደ መናፈሻ ሄጄ በእግሬ እንሸራሸራለሁ” በማለት ጁሊ ተናግራለች። “እዚያ ብቻዬን መሆንና ትኩረቴ ሳይከፋፈል የልቤን አውጥቼ ለይሖዋ መናገር እችላለሁ።”

9. ኢየሱስ ሥራ የሚበዛበት ቢሆንም ከይሖዋ ጋር ላለው ዝምድና ትልቅ ቦታ እንደሚሰጥ ያሳየው እንዴት ነው?

9 ኢየሱስ በሥራ የተጠመደ ነበር። ምድራዊ አገልግሎቱን ሲያከናውን ብዙ ሕዝብ በሄደበት ሁሉ ይከተለው ነበር፤ ሁሉም ጊዜውን እንዲሰጣቸው ይፈልጉ ነበር። በአንድ ወቅት ‘የከተማው ሰው ሁሉ’ እሱን ለማየት ‘በደጅ ተሰበሰበ።’ ያም ሆኖ ኢየሱስ ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና የሚያጠናክርበት ጊዜ አመቻችቷል። በማለዳ ገና ጎህ ሳይቀድ ከአባቱ ጋር ብቻውን የሚያሳልፈው ጊዜ ለማግኘት “ገለል ወዳለ ስፍራ” ሄደ።—ማር. 1:32-35

10-11. በማቴዎስ 26:40, 41 መሠረት በጌትሴማኒ የአትክልት ስፍራ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ምን ወቅታዊ ምክር ሰጣቸው? የተፈጠረው ሁኔታ ግን ምንድን ነው?

10 በኋላም ኢየሱስ አገልግሎቱን ሊያጠናቅቅ ሲል በምድር ላይ ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት፣ ማሰላሰልና መጸለይ የሚችልበት ጸጥ ያለ ስፍራ ለማግኘት ሄደ። በጌትሴማኒ የአትክልት ስፍራ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ቦታ አገኘ። (ማቴ. 26:36) በዚህ አጋጣሚ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ስለ ጸሎት ወቅታዊ ምክር ሰጣቸው።

11 እስቲ የተፈጠረውን ሁኔታ እንመልከት። ወደ ጌትሴማኒ የአትክልት ስፍራ በደረሱበት ወቅት በጣም መሽቶ ምናልባትም እኩለ ሌሊት አልፎ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ሐዋርያቱን “ነቅታችሁ ጠብቁ” ካላቸው በኋላ ሊጸልይ ሄደ። (ማቴ. 26:37-39) እሱ እየጸለየ ሳለ ግን እነሱ እንቅልፍ ወሰዳቸው። ኢየሱስ ተኝተው ሲያገኛቸው “ነቅታችሁ ጠብቁ፤ ሳታሰልሱም ጸልዩ” በማለት በድጋሚ አሳሰባቸው። (ማቴዎስ 26:40, 41ን አንብብ።) በጭንቀት እንደተዋጡና እንደደከማቸው ተረድቶላቸው ነበር። ኢየሱስ እንዳዘነላቸው በሚያሳይ መንገድ “ሥጋ . . . ደካማ ነው” አላቸው። ከዚያ በኋላም ኢየሱስ ሁለት ጊዜ ሊጸልይ ሄደ፤ ሲመለስ ግን ደቀ መዛሙርቱ ሲጸልዩ ሳይሆን ተኝተው አገኛቸው።—ማቴ. 26:42-45

ይበልጥ ንቁ በምትሆንበት ሰዓት ላይ ለመጸለይ ጊዜ መመደብ ትችላለህ? (አንቀጽ 12⁠ን ተመልከት)

12. አንዳንዴ በጣም ከመወጠራችን ወይም ከመድከማችን የተነሳ መጸለይ ሲከብደን ምን ማድረግ እንችላለን?

12 ትክክለኛ ጊዜ ምረጥ። አንዳንዴ በጣም ከመወጠራችን ወይም ከመድከማችን የተነሳ መጸለይ ሊከብደን ይችላል። አንተም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞህ የሚያውቅ ከሆነ እንዲህ የሚሰማህ አንተ ብቻ እንዳልሆንክ አስታውስ። ታዲያ ምን ማድረግ ትችላለህ? በቀኑ መጨረሻ የመጸለይ ልማድ ያላቸው አንዳንድ ክርስቲያኖች ምሽት ላይ ትንሽ ቀደም ብለው ያን ያህል ድካም በማይሰማቸው ሰዓት መጸለያቸው ጠቃሚ እንደሆነ አስተውለዋል። ሌሎች ደግሞ የሚጸልዩበት አኳኋን ትልቅ ለውጥ እንደሚያመጣ ተገንዝበዋል። አንዳንዴ ግን በጣም ከመጨነቅህ ወይም ተስፋ ከመቁረጥህ የተነሳ መጸለይ ቢከብድህስ? ይህን ስሜትህን ለይሖዋ ንገረው። ሩኅሩኁ አባታችን ይህን ስሜትህን እንደሚረዳልህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።—መዝ. 139:4

ስብሰባ ላይ ሆነህ ለሚደርሱህ የጽሑፍ መልእክቶችና ኢሜይሎች መልስ ላለመስጠት ጥረት ታደርጋለህ? (ከአንቀጽ 13-14⁠ን ተመልከት)

13. የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎቻችን ከይሖዋ ጋር በምናሳልፈው ጊዜ ጣልቃ የሚገቡት እንዴት ነው?

13 ስታጠና ትኩረት የሚከፋፍሉ ነገሮችን አስወግድ። ጸሎት ከይሖዋ ጋር ያለንን ወዳጅነት ማጠናከር የምንችልበት አንዱ አቅጣጫ ብቻ ነው። የአምላክን ቃል ማጥናታችን እና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘታችንም ወደ አምላክ ይበልጥ እንድንቀርብ ይረዳናል። በጥናትና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የምታሳልፈውን ጊዜ ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመጠቀም ማድረግ የምትችለው ነገር አለ? እስቲ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ስብሰባ ላይ ስሆን ወይም በማጠናበት ወቅት ብዙውን ጊዜ ትኩረቴን የሚከፋፍለው ምንድን ነው?’ ምናልባት ትኩረታችንን የሚከፋፍለው የስልክ ጥሪዎችን መቀበል አሊያም በስልካችን ወይም በሌላ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ለሚላኩልን ኢሜይሎችና ሌሎች የጽሑፍ መልእክቶች መልስ መስጠት ይሆን? በዛሬው ጊዜ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች እነዚህ ጠቃሚ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች አሏቸው። አንዳንድ ተመራማሪዎች እንደሚናገሩት በአንድ ነገር ላይ ትኩረት ለማድረግ በምንሞክርበት ወቅት ስልካችን አጠገባችን መሆኑ ብቻውን ትኩረታችንን ሊከፋፍለው ይችላል። አንድ የሥነ ልቦና ፕሮፌሰር እንዲህ ብለዋል፦ “ትኩረትህ እያከናወንከው ባለኸው ሥራ ላይ አይሆንም። አእምሮህ ሌላ ቦታ ነው።” በወረዳ ወይም በክልል ስብሰባ ወቅት ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት ብዙውን ጊዜ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎቻችን ሌሎችን እንዳይረብሹ አስፈላጊውን ማስተካከያ እንድናደርግ ይነገረናል። ብቻችንን ሆነን ከይሖዋ ጋር በምናሳልፈው ጊዜም እነዚህ መሣሪያዎቻችን እኛን እንዳይረብሹን ተመሳሳይ ጥንቃቄ ማድረግ እንችል ይሆን?

14. በፊልጵስዩስ 4:6, 7 መሠረት ይሖዋ ትኩረታችንን እንድንሰበስብ የሚረዳን እንዴት ነው?

14 ትኩረትህን ለመሰብሰብ እንዲረዳህ ይሖዋን ጠይቀው። በምታጠናበት ወቅት ወይም ስብሰባ ላይ ሆነህ ሐሳብህ የሚዋልል ከሆነ ይሖዋን እንዲረዳህ ጠይቀው። የሚያስጨንቅ ነገር አጋጥሞህ ከሆነ ጭንቀትህን ትተህ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ቀላል ላይሆንልህ ይችላል፤ እንዲህ ማድረግህ ግን አስፈላጊ ነው። ልብህን ብቻ ሳይሆን ‘አእምሮህንም’ የሚጠብቅልህ ሰላም ለማግኘት ጸልይ።ፊልጵስዩስ 4:6, 7ን አንብብ።

ከይሖዋ ጋር የምናሳልፈው ጊዜ የሚክስ ነው

15. ከይሖዋ ጋር ጊዜ ማሳለፍ የሚያስገኘው አንዱ ጥቅም ምንድን ነው?

15 ጊዜ መድበህ ይሖዋን የምታነጋግረው፣ የምታዳምጠውና ስለ እሱ የምታስብ ከሆነ በእጅጉ ትጠቀማለህ። እንዴት? አንደኛ ጥሩ ውሳኔ የማድረግ ችሎታህ ይሻሻላል። መጽሐፍ ቅዱስ “ከጥበበኞች ጋር የሚሄድ ጥበበኛ ይሆናል” ይላል። (ምሳሌ 13:20) በመሆኑም የጥበብ ምንጭ ከሆነው ከይሖዋ ጋር ጊዜ ስታሳልፍ ይበልጥ ጥበበኛ ትሆናለህ። በተጨማሪም ይሖዋን ማስደሰትና እሱን ከሚያሳዝኑ ውሳኔዎች መራቅ ስለምትችልበት መንገድ የተሻለ ግንዛቤ ይኖርሃል።

16. ከይሖዋ ጋር ጊዜ ማሳለፋችን የማስተማር ችሎታችንን የሚያሻሽለው እንዴት ነው?

16 ሁለተኛ የማስተማር ችሎታህ ይሻሻላል። ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ስናስተምር አንዱ ዋነኛው ግባችን ጥናታችን ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንዲቀርብ መርዳት ነው። የሰማዩ አባታችንን ባነጋገርነውና ባዳመጥነው መጠን ይበልጥ እንወደዋለን፤ ጥናታችን እሱን እንዲወደው ለመርዳትም የተሻለ ብቃት ይኖረናል። ኢየሱስን እንደ ምሳሌ መውሰድ ይቻላል። ስለ አባቱ ይናገር የነበረው ሞቅ ባለ እና ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ስለነበር ታማኝ ተከታዮቹ ይሖዋን መውደድ ቀላል ሆኖላቸዋል።—ዮሐ. 17:25, 26

17. ጸሎትና የግል ጥናት እምነታችንን ለማጠናከር የሚረዱን እንዴት ነው?

17 ሦስተኛ እምነትህ ይበልጥ ይጠናከራል። አምላክን እንዲመራህ፣ እንዲያጽናናህ ወይም እንዲደግፍህ ስትለምነው ምን እንደሚፈጠር ለማሰብ ሞክር። ይሖዋ ለጸሎትህ ምላሽ በሰጠህ ቁጥር በእሱ ላይ ያለህ እምነት ይጠናከራል። (1 ዮሐ. 5:15) እምነትህ እንዲጠናከር የሚረዳህ ሌላው ነገር ምንድን ነው? የግል ጥናት። ደግሞም “እምነት የሚገኘው ቃሉን ከመስማት ነው።” (ሮም 10:17) ጠንካራ እምነት ማዳበር ግን እንዲሁ እውቀት ከመሰብሰብ ያለፈ ነገርን ይጠይቃል። ሌላ ምን ማድረግ ያስፈልገናል?

18. የማሰላሰልን አስፈላጊነት በምሳሌ አስረዳ።

18 በተማርነው ነገር ላይ ማሰላሰል ያስፈልገናል። የመዝሙር 77 ጸሐፊ ያጋጠመውን ነገር እንደ ምሳሌ እንመልከት። እሱና ወገኖቹ እስራኤላውያን የይሖዋን ሞገስ እንዳጡ ስለተሰማው በጣም ተጨንቆ ነበር። ጭንቀቱ እንቅልፍ ነስቶት ነበር። (ከቁጥር 2-8) ታዲያ ምን አደረገ? ይሖዋን እንዲህ አለው፦ “በሥራዎችህም ሁሉ ላይ አሰላስላለሁ፤ ያከናወንካቸውንም ነገሮች አውጠነጥናለሁ።” (ቁጥር 12) እርግጥ ነው፣ ይህ መዝሙራዊ ይሖዋ በቀደመው ጊዜ ለሕዝቡ ያደረጋቸውን ነገሮች በደንብ ያውቅ ነበር፤ ሆኖም በተጨነቀበት ወቅት “አምላክ ሞገሱን ማሳየት ረስቷል? ወይስ ቁጣው ምሕረት ከማሳየት እንዲቆጠብ አድርጎታል?” ብሎ አስቦ ነበር። (ቁጥር 9) መዝሙራዊው ይሖዋ ባከናወናቸው ነገሮችና በቀደሙት ዘመናት ምሕረትና ርኅራኄ ባሳየበት መንገድ ላይ አሰላሰለ። (ቁጥር 11) ውጤቱ ምን ሆነ? መዝሙራዊው ይሖዋ ሕዝቡን እንደማይተው ያለው እምነት ተጠናከረ። (ቁጥር 15) አንተም በተመሳሳይ ቀደም ሲል ይሖዋ ለሕዝቡ ባደረገውና በግለሰብ ደረጃ ለአንተ ባደረገልህ ነገር ላይ ስታሰላስል እምነትህ ይበልጥ ይጠናከራል።

19. ከይሖዋ ጋር ጊዜ ማሳለፋችን ምን ሌላ ጥቅም ያስገኝልናል?

19 አራተኛውና ከሁሉም የላቀው ጥቅም ደግሞ ለይሖዋ ያለህ ፍቅር ይጨምራል። ከየትኛውም ባሕርይ የበለጠ ፍቅር ይሖዋን እንድትታዘዘው፣ እሱን ለማስደሰት ስትል መሥዋዕትነት እንድትከፍል እንዲሁም ማንኛውንም መከራ በጽናት እንድትቋቋም ያነሳሳሃል። (ማቴ. 22:37-39፤ 1 ቆሮ. 13:4, 7፤ 1 ዮሐ. 5:3) በእርግጥም ለእኛ ከይሖዋ ጋር ከመሠረትነው የጠበቀ ወዳጅነት የሚበልጥብን ምንም ነገር የለም።—መዝ. 63:1-8

20. ከይሖዋ ጋር የምታሳልፈውን ጊዜ ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመጠቀም ምን ለማድረግ አስበሃል?

20 ጸሎት፣ ጥናትና ማሰላሰል የአምልኳችን ክፍል እንደሆኑ አትርሳ። ልክ እንደ ኢየሱስ ከይሖዋ ጋር ጊዜ ለማሳለፍ የሚያስችልህ ጸጥ ያለ ስፍራ ፈልግ። ትኩረት የሚከፋፍሉ አላስፈላጊ ነገሮችን አርቅ። በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ስትካፈል ትኩረትህን መሰብሰብ እንድትችል የይሖዋን እርዳታ ጠይቅ። ጊዜህን ከሁሉ በተሻለ መንገድ ለመጠቀም የምትጥር ከሆነ ይሖዋ በአዲሱ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት በመስጠት አብዝቶ ይክስሃል።—ማር. 4:24

መዝሙር 28 የይሖዋ ወዳጅ መሆን

^ ይሖዋ ከማንም በላይ የምንቀርበው ወዳጃችን ነው። ከእሱ ጋር ያለንን ወዳጅነት ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን፤ ስለ እሱ ይበልጥ ማወቅም እንፈልጋለን። አንድን ሰው በደንብ ለማወቅ ጊዜ ይጠይቃል። ከይሖዋ ጋር ያለን ዝምድና እየተጠናከረ እንዲሄድ በምናደርገው ጥረትም ይህ እውነት ነው። ሆኖም ሕይወታችን በውጥረት የተሞላ ነው። ታዲያ ወደ ሰማዩ አባታችን ለመቅረብ የሚሆን ጊዜ ለማግኘት ምን ማድረግ እንችላለን? ይህን ማድረጋችንስ የሚጠቅመን እንዴት ነው?