የጥናት ርዕስ 1
የአምላክ ቃል “እውነት” እንደሆነ ተማመኑ
የ2023 የዓመት ጥቅስ፦“የቃልህ ፍሬ ነገር እውነት ነው።”—መዝ. 119:160
መዝሙር 96 የአምላክ መጽሐፍ ውድ ሀብት ነው
ማስተዋወቂያ a
1. በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት የሌላቸው ለምንድን ነው?
በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ማንን እንደሚያምኑ ግራ ገብቷቸዋል። የሚያከብሯቸው ሰዎች ለምሳሌ ፖለቲከኞች፣ ሳይንቲስቶችና በንግዱ ዓለም ያሉ ሰዎች ለእነሱ ጥቅም የሚያስቡ መሆኑን ይጠራጠራሉ። በተጨማሪም ለሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት አክብሮት የላቸውም። በመሆኑም እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች ‘እንመራበታለን’ የሚሉትን መጽሐፍ ቅዱስን በጥርጣሬ ዓይን ማየታቸው አያስገርምም።
2. በመዝሙር 119:160 መሠረት ስለ ምን ጉዳይ እርግጠኞች መሆን ይኖርብናል?
2 እኛ የይሖዋ አገልጋዮች፣ እሱ “የእውነት አምላክ” እንደሆነና ምንጊዜም ለእኛ ጥቅም እንደሚያስብ እርግጠኞች ነን። (መዝ. 31:5፤ ኢሳ. 48:17) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን ሐሳብ ልንተማመንበት እንደምንችል እንዲሁም “[የቃሉ] ፍሬ ነገር እውነት” እንደሆነ እናውቃለን። (መዝሙር 119:160ን አንብብ።) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር በጻፉት ሐሳብ እንስማማለን፤ እንዲህ ብለዋል፦ “አምላክ የተናገረው ማንኛውም ነገር ውሸት ሊሆን ወይም ሊከሽፍ የሚችልበት ምንም መንገድ የለም። የአምላክ ሕዝቦች አምላክን ስለሚያምኑት እሱ በተናገረው ነገር መተማመን ይችላሉ።”
3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
3 ሌሎች እንደ እኛ በአምላክ ቃል ላይ እምነት እንዲኖራቸው መርዳት የምንችለው እንዴት ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት መጣል የምንችልባቸውን ሦስት ምክንያቶች እስቲ እንመልከት። የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት አለመቀየሩን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች መፈጸማቸውን እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ ያለውን የሰዎችን ሕይወት የመለወጥ ኃይል እንመለከታለን።
የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት አልተቀየረም
4. አንዳንዶች የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት በትክክል መተላለፉን የሚጠራጠሩት ለምንድን ነው?
4 ይሖዋ አምላክ መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጻፍ 40 የሚያህሉ ታማኝ ሰዎችን ተጠቅሟል። ሆኖም እነዚህ ሰዎች በእጃቸው ከጻፏቸው የመጀመሪያ ጽሑፎች መካከል አንዱም በዘመናችን አይገኝም። ዛሬ የሚገኙት መጻሕፍት የግልባጭ ግልባጭ ናቸው። በዚህም የተነሳ አንዳንዶች ‘በዛሬው ጊዜ ያለው መጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያዎቹ ጸሐፊዎች ያሰፈሩትን ሐሳብ በትክክል ያስተላልፋል?’ የሚል ጥያቄ ይፈጠርባቸዋል። ታዲያ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት አለመቀየሩን እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን?
5. የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት የተገለበጡት እንዴት ነው? (የሽፋኑን ሥዕል ተመልከት።)
5 ይሖዋ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ተጠብቆ እንዲቆይ ስለፈለገ ሐሳቡ እንዲገለበጥ ትእዛዝ ሰጥቷል። የእስራኤል ነገሥታት ሕጉን በእጃቸው እንዲገለብጡ እንዲሁም ሌዋውያን ሕጉን ለሕዝቡ እንዲያስተምሩ አዝዟቸው ነበር። (ዘዳ. 17:18፤ 31:24-26፤ ነህ. 8:7) አይሁዳውያን ከባቢሎን ግዞት ከተመለሱ በኋላ አንዳንድ የተካኑ ገልባጮች የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን በርካታ ግልባጮች ማዘጋጀት ጀመሩ። (ዕዝራ 7:6) እነዚህ ሰዎች ጠንቃቃ ነበሩ። ከጊዜ በኋላ ገልባጮቹ ሁሉም ነገር በትክክል መገልበጡን ለማረጋገጥ ሲሉ እያንዳንዱን ቃል ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱን ፊደል መቁጠር ጀመሩ። ያም ቢሆን ሰዎቹ ፍጹማን ስላልሆኑ መጽሐፍ ቅዱስን በሚገለብጡበት ወቅት አንዳንድ ትናንሽ ስህተቶችን ሠርተዋል። ሆኖም ለእያንዳንዱ መጽሐፍ ብዙ ግልባጮች ስለተዘጋጁ እነዚህን ስህተቶች ለይቶ ማወቅ ይቻላል። እንዴት?
6. መጽሐፍ ቅዱስ ሲገለበጥ የተሠሩ ስህተቶችን ለይቶ ማወቅ የሚቻለው እንዴት ነው?
6 በዘመናችን ያሉ ምሁራን፣ መጽሐፍ ቅዱስን የገለበጡት ሰዎች ያስገቧቸውን ስህተቶች ለመለየት የሚያስችል አስተማማኝ መንገድ አላቸው። ለምሳሌ ያህል፣ 100 ሰዎች አንድን ገጽ እንዲገለብጡ ተጠየቁ እንበል። አንደኛው ሰው በሚገለብጥበት ወቅት አነስተኛ ስህተት ሠራ። ይህን ስህተት ለይቶ ማውጣት የሚቻልበት አንዱ መንገድ፣ እሱ ያዘጋጀውን ቅጂ ከሌሎቹ ቅጂዎች ጋር ማወዳደር ነው። በተመሳሳይም ምሁራን የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎችን በማወዳደር አንዱ ገልባጭ በስህተት የጨመረውን ወይም የቀነሰውን ሐሳብ ለይተው ማወቅ ይችላሉ።
7. መጽሐፍ ቅዱስን የገለበጡት ሰዎች ምን ያህል ጠንቃቆች ነበሩ?
7 መጽሐፍ ቅዱስን የገለበጡት ሰዎች መልእክቱን በትክክል ለማስፈር ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ይህን የሚያረጋግጥ አንድ ምሳሌ እንመልከት። በዘመናችን የሚገኘው ጥንታዊው የተሟላ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂ የሌኒንግራድ ኮዴክስ ይባላል። የተጻፈውም በ1008 ወይም በ1009 ዓ.ም. ነው። ይሁንና ከሌኒንግራድ ኮዴክስ በ1,000 ዓመት የሚበልጥ ዕድሜ ያላቸው በርካታ ጥንታዊ ቅጂዎችና ቁርጥራጮች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተገኝተዋል። አንዳንዶች እነዚህ ጥንታዊ ቅጂዎች ለ1,000 ዓመት ያህል በተደጋጋሚ ሲገለበጡ የቆዩ ከመሆኑ አንጻር ከሌኒንግራድ ኮዴክስ ጋር ምንም ተመሳሳይነት እንደማይኖራቸው ያስቡ ይሆናል። ሁኔታው ግን ከዚህ ጨርሶ የተለየ ነው። ጥንታዊዎቹን ቅጂዎች ከጊዜ በኋላ ከተዘጋጁት ቅጂዎች ጋር ያወዳደሩ ምሁራን፣ ከጥቂት የቃላት ልዩነቶች ውጪ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት በትክክል እንደተላለፈ አረጋግጠዋል።
8. የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን ቅጂዎች ከሌሎች ጥንታዊ መጻሕፍት ቅጂዎች ጋር በማወዳደር ምን መደምደሚያ ላይ መድረስ ይቻላል?
8 የጥንቶቹ ክርስቲያኖችም ቅዱሳን መጻሕፍትን ይገለብጡ ነበር። በግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚካተቱትን 27 መጻሕፍት በጥንቃቄ ይገለብጡ የነበረ ሲሆን ቅጂዎቹን ለስብሰባና ለስብከት ይጠቀሙባቸው ነበር። አንድ ምሁር በዘመናችን የሚገኙትን የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ጥንታዊ ቅጂዎች በዚያው ዘመን ከተዘጋጁ ሌሎች መጻሕፍት ጋር ካወዳደሩ በኋላ እንዲህ ብለዋል፦ “በጥቅሉ ሲታይ ከሌሎች መጻሕፍት ይልቅ [የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች] በብዛት ይገኛሉ፤ . . . ይዘታቸውም ከሌሎቹ ይበልጥ የተሟላ ነው።” አናቶሚ ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “አንድ ሰው በዘመናችን በሚገኝ አስተማማኝ [የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት] ትርጉም ላይ የሚያነበው ነገር ጸሐፊዎቹ ራሳቸው ካሰፈሩት ሐሳብ ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ መተማመን ይችላል።”
9. በኢሳይያስ 40:8 መሠረት የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በተመለከተ ምን መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን?
9 ባለፉት መቶ ዘመናት የነበሩ ገልባጮች በጥንቃቄ ያከናወኑት ሥራ፣ በዛሬው ጊዜ የምናነበውና የምናጠናው መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ እንዲሆን ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል። b ለሰው ልጆች ያስተላለፈው መልእክት ሳይበረዝ እስከ ዘመናችን ተጠብቆ እንዲቆይ ያደረገው ይሖዋ እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም። (ኢሳይያስ 40:8ን አንብብ።) እርግጥ አንዳንዶች፣ መጽሐፍ ቅዱስ መልእክቱ ሳይበረዝ እስከ ዘመናችን መቆየቱ በራሱ የአምላክ ቃል መሆኑን የሚያሳይ በቂ ማስረጃ ሊሆን እንደማይችል ይሰማቸዋል። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ መሪነት መጻፉን የሚያሳዩ አንዳንድ ማስረጃዎችን እንመልከት።
የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች አስተማማኝ ናቸው
10. የ2 ጴጥሮስ 1:21ን እውነተኝነት የሚያረጋግጥ ፍጻሜውን ያገኘ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ጥቀስ። (ሥዕሎቹን ተመልከት።)
10 መጽሐፍ ቅዱስ ፍጻሜያቸውን ያገኙ በርካታ ትንቢቶችን ይዟል። እንዲያውም አንዳንዶቹ የተፈጸሙት ከተጻፉ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ነው። እነዚህ ትንቢቶች መፈጸማቸውን ታሪክ ይመሠክራል። ይህ መሆኑ አያስገርመንም፤ ምክንያቱም የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢቶች ያስጻፈው ይሖዋ መሆኑን እናውቃለን። (2 ጴጥሮስ 1:21ን አንብብ።) የጥንቷን የባቢሎን ከተማ አወዳደቅ በተመለከተ የተነገሩትን ትንቢቶች እንደ ምሳሌ እንውሰድ። በስምንተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ነቢዩ ኢሳይያስ፣ በወቅቱ ኃያል ከተማ የነበረችው ባቢሎን ድል እንደምትደረግ በመንፈስ ተመርቶ ትንቢት ተናግሯል። ድል የሚያደርጋት ቂሮስ የተባለ ሰው እንደሆነም ጭምር ተናግሯል፤ በተጨማሪም ከተማዋ ድል የምትደረገው እንዴት እንደሆነ በዝርዝር ገልጿል። (ኢሳ. 44:27–45:2) ከዚህም ሌላ ኢሳይያስ፣ ባቢሎን ከጊዜ በኋላ እንደምትደመሰስ እንዲሁም ሙሉ በሙሉ ባድማ እንደምትሆን ተናግሯል። (ኢሳ. 13:19, 20) እነዚህ ትንቢቶች በትክክል ተፈጽመዋል። ባቢሎን በ539 ዓ.ዓ. በሜዶናውያንና በፋርሳውያን እጅ ወደቀች። ይህች ታላቅ ከተማ ትገኝበት የነበረው ቦታ አሁን የፍርስራሽ ክምር ሆኗል።—ለዘላለም በደስታ ኑር! በተባለው መጽሐፍ ኤሌክትሮኒክ ቅጂ ምዕራፍ 03 ነጥብ 5 ላይ የሚገኘውን መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ባቢሎን ጥፋት አስቀድሞ ተናግሯል የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት።
11. ዳንኤል 2:41-43 በዛሬው ጊዜ እየተፈጸመ ያለው እንዴት እንደሆነ አብራራ።
11 የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ያገኙት በጥንት ዘመን ብቻ አይደለም፤ በዛሬው ጊዜም አንዳንድ ትንቢቶች ሲፈጸሙ እያየን ነው። ለምሳሌ ዳንኤል ስለ አንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘበትን አስደናቂ መንገድ እንመልከት። (ዳንኤል 2:41-43ን አንብብ።) ትንቢቱ፣ ይህ ጥምር የዓለም ኃያል መንግሥት በከፊል እንደ ብረት “ብርቱ፣” በከፊል ደግሞ እንደ ሸክላ “ደካማ” እንደሚሆን ይናገራል። ይህ ትንቢት በትክክል ተፈጽሟል። ብሪታንያ እና አሜሪካ በሁለቱም የዓለም ጦርነቶች ላይ ለተገኘው ድል ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል፤ እንዲሁም አሁንም ድረስ ታላቅ የጦር ኃይል አላቸው። ይህም እንደ ብረት ብርቱ መሆናቸውን ያሳያል። ሆኖም ዜጎቻቸው በሠራተኛ ማኅበራት፣ በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እንቅስቃሴ እንዲሁም ነፃነት ለማግኘት በሚደረጉ ትግሎች አማካኝነት መብታቸውን ለማስጠበቅ በተደጋጋሚ ስለሚነሱ የእነዚህ መንግሥታት ኃይል ተዳክሟል። የዓለምን ፖለቲካ የሚያጠኑ አንድ ምሁር በቅርቡ እንዲህ ብለዋል፦ “በዓለም ላይ ካሉት በኢንዱስትሪ የበለጸጉ ዲሞክራሲያዊ አገራት መካከል የዩናይትድ ስቴትስን ያህል በፖለቲካ የተከፋፈለ አገር የለም።” የዚህ የዓለም ኃያል መንግሥት ሌላ ክፍል የሆነችው ብሪታንያ ደግሞ በተለይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት፣ ከአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ጋር ሊኖራት ከሚገባው ግንኙነት ጋር በተያያዘ ዜጎቿ ስምምነት ላይ ለመድረስ ተቸግረዋል። እነዚህ ክፍፍሎች በመኖራቸው የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት ቆራጥ እርምጃ መውሰድ አዳጋች ሆኖበታል።
12. የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ስለ ምን ነገር እርግጠኞች እንድንሆን ይረዱናል?
12 እስካሁን ፍጻሜያቸውን ያገኙ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች መኖራቸው አምላክ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሰጣቸው ተስፋዎች እንደሚፈጸሙ ይበልጥ እርግጠኛ እንድንሆን ያደርገናል። “ማዳንህን እናፍቃለሁ፤ ቃልህ ተስፋዬ ነውና” በማለት ወደ ይሖዋ የጸለየውን መዝሙራዊ ስሜት እንጋራለን። (መዝ. 119:81) ይሖዋ በደግነት ተነሳስቶ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት “የተሻለ ሕይወትንና ተስፋን” ሰጥቶናል። (ኤር. 29:11) የወደፊት ተስፋችን የተመካው በሰዎች ጥረት ላይ ሳይሆን ይሖዋ በገባቸው ቃሎች ላይ ነው። እንግዲያው የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢቶች በጥንቃቄ በማጥናት በአምላክ ቃል ላይ ያለንን እምነት ማጠናከራችንን እንቀጥል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ሚሊዮኖችን ረድቷል
13. በመዝሙር 119:66, 138 መሠረት መጽሐፍ ቅዱስ እምነት የሚጣልበት መሆኑን የሚያሳየው ሌላው ማስረጃ ምንድን ነው?
13 በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት ለመጣል የሚያነሳሳን ሌላው ማስረጃ ሰዎች ምክሩን ሲከተሉ የሚያገኙት ጥቅም ነው። (መዝሙር 119:66, 138ን አንብብ።) ለምሳሌ ሊፋቱ ተቃርበው የነበሩ ባለትዳሮች አሁን በአንድነትና በደስታ እየኖሩ ነው። ልጆቻቸው ሰላምና ፍቅር በሰፈነበት ክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ የማደግ ልዩ አጋጣሚ አግኝተዋል።—ኤፌ. 5:22-29
14. የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በሥራ ላይ ማዋል የሰዎችን ሕይወት እንደሚቀይር የሚያሳይ ምሳሌ ጥቀስ።
14 አደገኛ ወንጀለኞች እንኳ ጥበብ የሚንጸባረቅበትን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በመከተላቸው ሕይወታቸውን መቀየር ችለዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ጃክ c የተባለን አንድ እስረኛ የረዳው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት። ጃክ ዓመፀኛ ወንጀለኛ ነበር፤ የሞት ፍርድ ከተፈረደባቸው እጅግ አደገኛ ወንጀለኞች መካከል አንዱ እሱ ነበር። አንድ ቀን ግን ጃክ በሌላ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ ተገኘ። ጥናቱን የመሩት ወንድሞች ያሳዩት ደግነት ልቡን ስለነካው እሱም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በሕይወቱ ውስጥ ተግባራዊ ሲያደርግ ምግባሩ አልፎ ተርፎም ስብዕናው መቀየር ጀመረ። ከጊዜ በኋላ ጃክ ያልተጠመቀ አስፋፊ ለመሆን ብቃቱን አሟላ፤ በኋላም ተጠመቀ። ለሌሎች እስረኞች ስለ አምላክ መንግሥት በቅንዓት ይሰብክ ነበር። ቢያንስ አራት እስረኞች እውነትን እንዲማሩም ረድቷል። የሞት ፍርዱ የሚፈጸምበት ጊዜ ሲደርስ ጃክ ሙሉ በሙሉ ሌላ ሰው ሆኖ ነበር። ከጠበቆቹ አንዷ እንዲህ ብላለች፦ “ጃክ ከ20 ዓመት በፊት የማውቀው ያው ሰው አይደለም። የይሖዋ ምሥክሮች ትምህርት ሕይወቱን ቀይሮታል።” የጃክ የሞት ፍርድ ቢፈጸምም የእሱ ምሳሌ በአምላክ ቃል መተማመን እንደምንችል እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት የመለወጥ ኃይል እንዳለው የሚያሳይ ትልቅ ማስረጃ ነው።—ኢሳ. 11:6-9
15. በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ሕዝቦች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በሥራ ላይ በማዋላቸው ከሌሎች የተለዩ የሆኑት እንዴት ነው? (ሥዕሉን ተመልከት።)
15 የይሖዋ ሕዝቦች የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በሥራ ላይ ስለሚያውሉ አንድነት አላቸው። (ዮሐ. 13:35፤ 1 ቆሮ. 1:10) በተለይም በዓለም ላይ ከሚታየው የፖለቲካ፣ የዘር እንዲሁም ማኅበራዊ ክፍፍል አንጻር ሰላማችንና አንድነታችን አስደናቂ ነው። ዣን የተባለ አንድ ወጣት በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ያለውን አንድነት ማየቱ በሕይወቱ ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል። ዣን ያደገው በአንድ የአፍሪካ አገር ውስጥ ነው። በሚኖርበት አገር የእርስ በርስ ጦርነት ሲነሳ የጦር ሠራዊቱን ተቀላቀለ። በኋላ ግን ወደ አጎራባች አገር ሸሸ። በዚያም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘ። ዣን እንዲህ ብሏል፦ “እውነተኛውን ሃይማኖት የሚከተሉ ሰዎች በፖለቲካ ውስጥ እንደማይገቡና በመካከላቸው ክፍፍል እንደሌለ ተማርኩ። ከዚህ ይልቅ እርስ በርስ ይዋደዳሉ።” አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “አገሬን ከጥቃት ለመከላከል ሕይወቴን ሰጥቼ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ስማር ግን ሕይወቴን ለይሖዋ ለመስጠት ተነሳሳሁ።” ዣን ሙሉ በሙሉ ተቀይሯል። ከእሱ የተለየ ዘር ካላቸው ሰዎች ጋር ከመዋጋት ይልቅ አንድነት የሚያስገኘውን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ላገኘው ሰው ሁሉ ያካፍላል። የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር የተለያየ አስተዳደግና ባህል ያላቸውን ሰዎች የሚጠቅም መሆኑ በአምላክ ቃል ላይ እምነት መጣል እንደምንችል የሚያሳይ አሳማኝ ማስረጃ ነው።
በአምላክ የእውነት ቃል መተማመናችሁን ቀጥሉ
16. በአምላክ ቃል ላይ ያለንን እምነት ማጠናከራችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
16 የዓለም ሁኔታ ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ ሲሄድ በእውነት ላይ ያለን እምነት መፈተኑ አይቀርም። አንዳንድ ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኝነት ወይም ይሖዋ በዘመናችን አገልጋዮቹን ለመምራት ታማኝና ልባም ባሪያን ስለመሾሙ ጥርጣሬ ሊዘሩብን ይሞክሩ ይሆናል። ሆኖም የይሖዋ ቃል ሁልጊዜም እውነት እንደሆነ እርግጠኞች ከሆንን በእምነታችን ላይ የሚሰነዘሩትን እንዲህ ያሉ ጥቃቶች መመከት እንችላለን። የይሖዋን ‘ሥርዓት በሕይወታችን ዘመን ሁሉ፣ እስከ መጨረሻው ለመጠበቅ’ ቁርጥ ውሳኔ እናደርጋለን። (መዝ. 119:112) ለሌሎች ስለ እውነት መናገር እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር እንዲከተሉ ማበረታታት ‘አያሳፍረንም።’ (መዝ. 119:46) ከዚህም ሌላ ስደትን ጨምሮ ማንኛውም አስቸጋሪ ሁኔታ ቢደርስብን “በትዕግሥትና በደስታ” መጽናት እንችላለን።—ቆላ. 1:11፤ መዝ. 119:143, 157
17. የዓመት ጥቅሳችን ምን ያስታውሰናል?
17 ይሖዋ እውነትን ስላሳወቀን ምንኛ አመስጋኞች ነን! ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በውዥንብርና በነውጥ በተሞላው በዚህ ዓለም ውስጥ ይህ እውነት ያረጋጋናል፤ ዓላማ ያለው ሕይወት እንዲኖረንና ግልጽ መመሪያ እንድናገኝ ይረዳናል። በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር አስደሳች ሕይወት እንደምንመራ ተስፋ ይሰጠናል። የ2023 የዓመት ጥቅሳችን የአምላክ ቃል ፍሬ ነገር እውነት እንደሆነ ያላችሁን እምነት እንዲያጠናክርላችሁ ምኞታችን ነው።—መዝ. 119:160
መዝሙር 94 ለአምላክ ቃል አመስጋኝ መሆን
a ለ2023 እምነት የሚያጠናክር የዓመት ጥቅስ ተመርጦልናል፦ “የቃልህ ፍሬ ነገር እውነት ነው።” (መዝ. 119:160) እናንተም በዚህ ሐሳብ እንደምትስማሙ ምንም ጥያቄ የለውም። ሆኖም ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ እውነትና አስተማማኝ መመሪያ የያዘ መሆኑን አያምኑም። ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስና በውስጡ ባለው ምክር እንዲተማመኑ ለመርዳት ልንጠቀምባቸው የምንችላቸውን ሦስት ማስረጃዎች በዚህ ርዕስ ላይ እንመለከታለን።
b መጽሐፍ ቅዱስ እስከ ዘመናችን ተጠብቆ ስለቆየበት መንገድ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት jw.orgን ክፈትና በመፈለጊያው ላይ “ታሪክ እና መጽሐፍ ቅዱስ” ብለህ ጻፍ።
c አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።