በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 4

ይሖዋ የመታሰቢያውን በዓል ለማክበር የምናደርገውን ጥረት ይባርካል

ይሖዋ የመታሰቢያውን በዓል ለማክበር የምናደርገውን ጥረት ይባርካል

“ይህን ሁልጊዜ ለመታሰቢያዬ አድርጉት።”—ሉቃስ 22:19

መዝሙር 19 የጌታ ራት

ማስተዋወቂያ a

1-2. በየዓመቱ በመታሰቢያው በዓል ላይ የምንገኘው ለምንድን ነው?

 ወደ 2,000 ከሚጠጉ ዓመታት በፊት ኢየሱስ ሕይወቱን ለእኛ ሰጥቷል፤ ይህም የዘላለም ሕይወት የምናገኝበት አጋጣሚ ከፍቶልናል። ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ኢየሱስ ይህን ታላቅ ፍቅር እንዲያስቡ ተከታዮቹን አዟቸው ነበር፤ ቂጣና የወይን ጠጅ ተጠቅሞ ቀለል ባለ መንገድ በዓሉን እንዴት እንደሚያከብሩት አሳያቸው።—1 ቆሮ. 11:23-26

2 ኢየሱስን ከልባችን ስለምንወደው ያዘዘንን እንፈጽማለን። (ዮሐ. 14:15) በየዓመቱ በመታሰቢያው በዓል ሰሞን፣ ኢየሱስ ላደረገልን ነገር አድናቆታችንን ለማሳየት አጋጣሚ እናገኛለን። በዚህ ወቅት የእሱ ሞት ስላስገኘልን ጥቅም ጊዜ ወስደን በጸሎት እናስብበታለን። በአገልግሎት የምናደርገውን ተሳትፎ መጨመርም እንፈልጋለን፤ በተቻለን መጠን ብዙዎች በዚህ ልዩ በዓል ላይ እንዲገኙ እንጋብዛለን። ደግሞም ምንም ነገር በበዓሉ ላይ እንዳንገኝ እንቅፋት እንዲሆንብን አንፈቅድም።

3. በዚህ ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?

3 በዚህ ርዕስ ላይ የይሖዋ ሕዝቦች የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ ለማክበር የተለየ ጥረት የሚያደርጉባቸውን ሦስት አቅጣጫዎች እንመለከታለን፦ (1) ኢየሱስ ባሳየው መንገድ በዓሉን በማክበር፣ (2) ሌሎች በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ በመጋበዝ፣ (3) አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢኖሩም የመታሰቢያውን በዓል በማክበር።

ኢየሱስ ባሳየው መንገድ በዓሉን ማክበር

4. በየዓመቱ በመታሰቢያው በዓል ላይ የትኞቹ እውነቶች ትኩረት ይሰጣቸዋል? እነዚህን እውነቶች እንደ ቀላል ልንመለከታቸው የማይገባውስ ለምንድን ነው? (ሉቃስ 22:19, 20)

4 በየዓመቱ በመታሰቢያው በዓል ላይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግር ይቀርባል፤ ንግግሩ ለበርካታ ጥያቄዎች ግልጽ መልስ ይሰጣል። የሰው ልጆች ቤዛ ያስፈለጋቸው ለምን እንደሆነና የአንድ ሰው ሞት የብዙዎችን ኃጢአት የሚያስተሰርየው እንዴት እንደሆነ እንማራለን። ቂጣውና የወይን ጠጁ ምን እንደሚወክሉ እንዲሁም ከዚያ መካፈል የሚችሉት እነማን እንደሆኑ ማብራሪያ ይሰጣል። (ሉቃስ 22:19, 20ን አንብብ።) በተጨማሪም ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ሰዎች ስለሚያገኟቸው በረከቶች የምናሰላስልበት አጋጣሚ እናገኛለን። (ኢሳ. 35:5, 6፤ 65:17, 21-23) እነዚህን እውነቶች እንደ ቀላል ነገር ልንመለከታቸው አይገባም። በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች እነዚህን እውነቶች አያውቁም፤ የኢየሱስ ሞት ምን ያህል ዋጋ እንዳለውም አይረዱም። የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ ቢያከብሩም ይህን የሚያደርጉት እሱ ባሳየው መንገድ አይደለም። ይህን የምንለው ለምንድን ነው?

5. አብዛኞቹ ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ ኢየሱስ ባሳየው የመታሰቢያው በዓል አከባበር ላይ ምን ለውጥ ተደረገ?

5 አብዛኞቹ የኢየሱስ ሐዋርያት ከሞቱ ብዙም ሳይቆይ አስመሳይ ክርስቲያኖች ወደ ጉባኤው ሰርገው ገቡ። (ማቴ. 13:24-27, 37-39) “ደቀ መዛሙርቱን ወደ ራሳቸው ለመሳብ ጠማማ ነገር” መናገር ጀመሩ። (ሥራ 20:29, 30) እነዚህ አስመሳይ ክርስቲያኖች ካመጧቸው ‘ጠማማ ነገሮች’ አንዱ ኢየሱስ “የብዙዎችን ኃጢአት ለመሸከም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መሥዋዕት” እንደሆነ ከሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር የሚጋጭ ነው፤ መሥዋዕቱ ደጋግሞ መቅረብ እንዳለበት ማስተማር ጀመሩ። (ዕብ. 9:27, 28) በዛሬው ጊዜ በዚህ የሐሰት ትምህርት የሚያምኑ ብዙ ቅን ሰዎች አሉ። “ቅዱስ ቁርባን” b ተብሎ የሚጠራውን ሥርዓት ለማክበር ሲሉ አዘውትረው አንዳንዴም በየቀኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን ይሄዳሉ። አንዳንድ የሃይማኖት ድርጅቶች ደግሞ የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ ያን ያህል ደጋግመው አያከብሩም፤ ሆኖም አብዛኞቹ አባሎቻቸው የኢየሱስ መሥዋዕት ስለሚያስገኘው ጥቅም እምብዛም የሚያውቁት ነገር የለም። ‘የኢየሱስ ሞት እውነት ለኃጢአቴ ይቅርታ ያስገኝልኛል?’ ብለው የሚጠራጠሩም አሉ። እንዲህ ብለው የሚጠይቁት ለምንድን ነው? አንዳንዶች እንዲህ የሚሰማቸው የኢየሱስ መሥዋዕት የኃጢአት ይቅርታ እንደሚያስገኝ የሚጠራጠሩ ሰዎች ባስተማሩት ትምህርት የተነሳ ነው። ታዲያ የኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮች ትክክለኛው ግንዛቤ እንዲገኝ ያደረጉት እንዴት ነው?

6. አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በ1872 ምን መደምደሚያ ላይ ደርሰው ነበር?

6 በ19ኛው መቶ ዘመን ማብቂያ አካባቢ የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በቻርልስ ቴዝ ራስል አመራር ሥር ሆነው ቅዱሳን መጻሕፍትን በጥልቀት ማጥናት ጀመሩ። እነዚህ ሰዎች የኢየሱስ መሥዋዕት ስላለው ዋጋ እንዲሁም የሞቱ መታሰቢያ እንዴት ሊከበር እንደሚገባ እውነቱን ማወቅ ፈልገው ነበር። በ1872 እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የኢየሱስ ቤዛ ለመላው የሰው ዘር ስለሚያስገኘው ጥቅም ትክክለኛው መደምደሚያ ላይ ደረሱ። ያገኙትን እውነት ለራሳቸው ይዘው አልተቀመጡም። በመጻሕፍት፣ በጋዜጦችና በመጽሔቶች በመጠቀም ይህን እውነት አሰራጩ። ብዙም ሳይቆይ እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የመታሰቢያውን በዓል በዓመት አንድ ጊዜ ማክበር ጀመሩ።

7. ቀደም ባሉት ጊዜያት የነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ካደረጉት ምርምር ምን ጥቅም እናገኛለን?

7 እነዚያ ቅን ወንድሞች ያኔ ያደረጉት ምርምር በዛሬው ጊዜ ያለነውንም ጠቅሞናል። እንዴት? ለይሖዋ ምስጋና ይግባውና ስለ ኢየሱስ መሥዋዕት እንዲሁም ስለሚያስገኘው ጥቅም እውነቱ በርቶልናል። (1 ዮሐ. 2:1, 2) በተጨማሪም አምላክን ለሚያስደስቱ ሰዎች ስለተዘረጉላቸው ሁለት ተስፋዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ተምረናል፤ አንዳንዶች በሰማይ የማይሞት ሕይወት፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሌሎች ደግሞ በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት እንደሚያገኙ አውቀናል። ይሖዋ ምን ያህል እንደሚወደንና የኢየሱስ መሥዋዕት ምን ያህል እንደሚጠቅመን መረዳታችን ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ ረድቶናል። (1 ጴጥ. 3:18፤ 1 ዮሐ. 4:9) በመሆኑም እነዚያ ታማኝ ወንድሞች ያኔ እንዳደረጉት በዓሉን ኢየሱስ ባሳየው መንገድ በምናከብርበት ወቅት ሌሎችም አብረውን እንዲገኙ እንጋብዛለን።

ሰዎችን በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ መጋበዝ

ሰዎችን ወደ መታሰቢያው በዓል ለመጋበዝ በሚደረገው ዘመቻ ላይ የተሟላ ተሳትፎ ለማድረግ ምን ማድረግ ትችላለህ? (ከአንቀጽ 8-10⁠ን ተመልከት) e

8. የይሖዋ አገልጋዮች ሌሎችን ወደ መታሰቢያው በዓል ለመጋበዝ ምን አድርገዋል? (ሥዕሉን ተመልከት።)

8 የይሖዋ ሕዝቦች ከቀድሞም ጀምሮ ሰዎችን ወደ መታሰቢያው በዓል ሲጋብዙ ቆይተዋል። በ1881 በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ ወንድሞችና እህቶች በአሌጌኒ፣ ፔንስልቬንያ በሚገኝ መኖሪያ ቤት ውስጥ ይህን ልዩ በዓል ለማክበር እንዲሰበሰቡ ተጋብዘው ነበር። ከጊዜ በኋላ ደግሞ የመታሰቢያው በዓል በጉባኤ ደረጃ መከበር ጀመረ። መጋቢት 1940 አስፋፊዎች በክልላቸው ውስጥ ያሉ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ሁሉ ወደ በዓሉ እንዲጋብዙ ተነገራቸው። በ1960 ጉባኤዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የታተሙ መጋበዣዎች ከቤቴል ተላኩላቸው። ከዚያ ጊዜ ወዲህ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ የመታሰቢያው በዓል መጋበዣዎችን አሰራጭተናል። ይሁንና ሌሎችን ወደ በዓሉ ለመጋበዝ ይህን ያህል ጊዜና ጥረት የምናውለው ለምንድን ነው?

9-10. ሰዎችን ወደ መታሰቢያው በዓል ለመጋበዝ የምናደርገው ጥረት እነማንን ይጠቅማል? (ዮሐንስ 3:16)

9 ሰዎችን ወደ መታሰቢያው በዓል የምንጋብዝበት አንዱ ምክንያት አዲሶች ይሖዋና ኢየሱስ ለሁላችንም ስላደረጉልን ነገር እንዲማሩ ስለምንፈልግ ነው። (ዮሐንስ 3:16ን አንብብ።) በመታሰቢያው በዓል ላይ የሚያዩትና የሚሰሙት ነገር ስለ ይሖዋ ይበልጥ ለመማርና የእሱ አገልጋይ ለመሆን ያነሳሳቸዋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ሆኖም ከዚህ ዝግጅት የሚጠቀሙት እነሱ ብቻ አይደሉም።

10 ይሖዋን ማገልገላቸውን ያቆሙ ሰዎችንም ወደ በዓሉ እንጋብዛለን። ይህን የምናደርገው አምላክ አሁንም ቢሆን እንደሚወዳቸው ለማስታወስ ነው። ብዙዎች ግብዣችንን ተቀብለው በበዓሉ ላይ ይገኛሉ፤ እኛም በደስታ እንቀበላቸዋለን። በመታሰቢያው በዓል ላይ መገኘታቸው ቀደም ሲል ይሖዋን ሲያገለግሉ የነበራቸውን ደስታ ይቀሰቅስባቸዋል። የሞኒካን ምሳሌ እንመልከት። c በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት እንደገና ይሖዋን ማገልገል ጀመረች። በ2021 በመታሰቢያው በዓል ላይ ከተገኘች በኋላ እንዲህ ብላለች፦ “የዘንድሮ የመታሰቢያው በዓል ለእኔ ልዩ ትርጉም አለው። ከ20 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሰዎች መመሥከርና በመታሰቢያው በዓል ላይ እንዲገኙ መጋበዝ ችያለሁ። በዚህ ዘመቻ በሙሉ ልቤ ነው የተካፈልኩት፤ ምክንያቱም ይሖዋና ኢየሱስ ያደረጉልኝ ነገር ልቤን በጥልቅ ነክቶታል።” (መዝ. 103:1-4) ሰዎች ግብዣውን ተቀበሉም አልተቀበሉ በትጋት መጋበዛችንን እንቀጥላለን፤ ምክንያቱም ይሖዋ በምናደርገው ጥረት እንደሚደሰት እርግጠኞች ነን።

11. ሰዎችን ወደ መታሰቢያው በዓል ለመጋበዝ የምናደርገውን ጥረት ይሖዋ የባረከው እንዴት ነው? (ሐጌ 2:7)

11 ይሖዋ ሰዎችን ወደ መታሰቢያው በዓል ለመጋበዝ የምናደርገውን ጥረት በእጅጉ ባርኮልናል። በ2021 በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተነሳ የተጣሉ ገደቦች ቢኖሩም 21,367,603 የደረሰ አዲስ ከፍተኛ የተሰብሳቢዎች ቁጥር አግኝተናል። ይህም በዓለም ዙሪያ ካሉ የይሖዋ ምሥክሮች ከሁለት እጥፍ በላይ ማለት ነው! እርግጥ ነው፣ ይሖዋን የሚያሳስበው ቁጥሩ አይደለም። እሱ ትኩረት የሚሰጠው ለግለሰቦቹ ነው። (ሉቃስ 15:7፤ 1 ጢሞ. 2:3, 4) ይሖዋ ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ፈልገን እንድናገኝ በዚህ የመጋበዣ ዘመቻ እየተጠቀመ እንደሆነ እርግጠኞች ነን።ሐጌ 2:7ን አንብብ።

በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ የመታሰቢያውን በዓል ማክበር

ይሖዋ የመታሰቢያውን በዓል ለማክበር የምናደርገውን ጥረት ይባርካል (አንቀጽ 12⁠ን ተመልከት) f

12. የመታሰቢያውን በዓል ማክበር አስቸጋሪ እንዲሆን የሚያደርጉ ምን ሁኔታዎች ያጋጥሙናል? (ሥዕሉን ተመልከት።)

12 ኢየሱስ በመጨረሻዎቹ ቀናት የተለያዩ አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንደሚገጥሙን ተናግሯል፤ የቤተሰብ ተቃውሞ፣ ስደት፣ ጦርነት፣ ቸነፈርና ሌሎችም። (ማቴ. 10:36፤ ማር. 13:9፤ ሉቃስ 21:10, 11) እነዚህ ሁኔታዎች የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ ማክበር አስቸጋሪ እንዲሆን የሚያደርጉበት ጊዜ አለ። ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እነዚህን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ለመወጣት ምን አድርገዋል? ይሖዋስ የረዳቸው እንዴት ነው?

13. አርተም እስር ቤት ሆኖ የመታሰቢያውን በዓል ለማክበር ያሳየውን ድፍረትና ቁርጠኝነት ይሖዋ የባረከለት እንዴት ነው?

13 እስራት። በእምነታቸው ምክንያት የታሰሩ ወንድሞቻችን የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ ለማክበር የቻሉትን ሁሉ ያደርጋሉ። አርተምን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። በ2020 የመታሰቢያው በዓል ወቅት 17 ካሬ ሜትር በሆነች አምስት ሰው መያዝ የምትችል ክፍል ውስጥ ታስሮ ነበር። አርተም እስር ቤት ቢሆንም እንኳ ለቂጣውና ለወይን ጠጁ የሚያገለግሉ ነገሮችን እንደ ምንም ማግኘት ቻለ፤ ከዚያም የመታሰቢያውን ንግግር ለራሱ ለማቅረብ ተዘጋጀ። አብረውት የታሰሩት ሰዎች ግን አጫሾችና ተሳዳቢዎች ነበሩ። ታዲያ ምን ያደርግ ይሆን? ለአንድ ሰዓት ያህል ሳያጨሱና ሳይሳደቡ መቆየት ይችሉ እንደሆነ ጠየቃቸው። የሚገርመው የመታሰቢያውን በዓል በሚያከብርበት ወቅት ላለመሳደብና ላለማጨስ ተስማሙ። አርተም ከፈለጉ ስለ መታሰቢያው በዓል ሊያብራራላቸው እንደሚችል ነገራቸው። መጀመሪያ ላይ ስለ በዓሉ ምንም ነገር መስማት እንደማይፈልጉ ነግረውት ነበር፤ አርተም የመታሰቢያውን በዓል ሲያከብር ከተመለከቱ በኋላ ግን ጥያቄዎች ያዥጎደጉዱበት ጀመር።

14. በኮቪድ-19 ወቅት የመታሰቢያውን በዓል ለማክበር ምን ጥረት ተደርጓል?

14 የኮቪድ-19 ወረርሽኝ። ይህ ወረርሽኝ በጀመረበት ወቅት የይሖዋ ሕዝቦች የመታሰቢያውን በዓል በአካል ተገናኝተው ማክበር አልቻሉም። ይህ መሆኑ ግን በዓሉን ከማክበር አላገዳቸውም። d ኢንተርኔት ባለባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ጉባኤዎች የመታሰቢያውን በዓል በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት አከበሩ። ኢንተርኔት ማግኘት የማይችሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችስ? በአንዳንድ አገሮች ንግግሩን በቴሌቪዥን ወይም በሬዲዮ ለማሰራጨት ዝግጅት ተደረገ። ከዚህም በተጨማሪ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ንግግሩን ከ500 በሚበልጡ ቋንቋዎች እንዲቀዱት ተደረገ፤ ይህ ዝግጅት የተደረገው ራቅ ባሉ አካባቢዎች የሚኖሩትም በዓሉን ማክበር እንዲችሉ ነው። ከዚያም ወንድሞች የተቀዳውን ንግግር ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ አደረሱላቸው።

15. ሱ ከተባለችው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተሞክሮ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

15 የቤተሰብ ተቃውሞ። አንዳንዶች በመታሰቢያው በዓል ላይ መገኘት አስቸጋሪ እንዲሆንባቸው የሚያደርገው ትልቁ ፈተና የቤተሰብ ተቃውሞ ነው። ሱ የተባለች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ያጋጠማትን እንመልከት። በ2021 በመታሰቢያው በዓል ዋዜማ ላይ ቤተሰቦቿ በጣም ስለተቃወሟት በበዓሉ ላይ መገኘት እንደማትችል ለአስጠኚዋ ነገረቻት። የመጽሐፍ ቅዱስ አስጠኚዋ ሉቃስ 22:44⁠ን አነበበችላት። ከዚያም ከባድ ሁኔታ ውስጥ ስንሆን እንደ ኢየሱስ ይሖዋን በጸሎት መለመንና በእሱ ሙሉ በሙሉ መታመን እንደሚያስፈልገን አብራራችላት። በማግስቱ ሱ ቂጣውንና የወይን ጠጁን ካዘጋጀች በኋላ ለመታሰቢያው በዓል የተዘጋጀውን ልዩ የማለዳ አምልኮ ፕሮግራም ከ​jw.org ላይ ተመለከተች። ምሽት ላይም ክፍሏ ውስጥ ብቻዋን ሆና በዓሉን በስልክ ተከታተለች። ከበዓሉ በኋላ ሱ ለአስጠኚዋ እንዲህ የሚል መልእክት ላከችላት፦ “ትናንትና በጣም ነው ያበረታታሽኝ። በበዓሉ ላይ ለመገኘት በእኔ በኩል የተቻለኝን ሁሉ አድርጌያለሁ፤ ይሖዋ ደግሞ የቀረውን አሳክቶልኛል። ደስታዬንና ምስጋናዬን ለመግለጽ ቃላት ያጥሩኛል!” አንተስ ተመሳሳይ ሁኔታ ቢያጋጥምህ ይሖዋ እንደሚረዳህ ይሰማሃል?

16. ይሖዋ በመታሰቢያው በዓል ላይ ለመገኘት የምናደርገውን ጥረት እንደሚባርከው እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው? (ሮም 8:31, 32)

16 ይሖዋ የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ ለማክበር የምናደርገውን ጥረት ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል። ላደረገልን ነገር አድናቆታችንን ስናሳይ እንደሚባርከን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ሮም 8:31, 32ን አንብብ።) እንግዲያው በዚህ ዓመት በሚከበረው የመታሰቢያ በዓል ላይ ለመገኘትና በመታሰቢያው በዓል ሰሞን መንፈሳዊ እንቅስቃሴያችንን ከፍ ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።

መዝሙር 18 ለቤዛው አመስጋኝ መሆን

a ማክሰኞ ሚያዝያ 4, 2023 በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ ያከብራሉ። ብዙዎቹ በዚህ በዓል ላይ የሚገኙት ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። አንዳንድ የቀዘቀዙ ወንድሞቻችን ደግሞ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ በዓል ላይ ይገኛሉ። አንዳንዶች በበዓሉ ላይ የሚገኙት ብዙ መሰናክሎችን አልፈው ነው። አንተስ ምን ተፈታታኝ ሁኔታ አለብህ? ሁኔታህ ምንም ይሁን ምን፣ ይሖዋ በበዓሉ ላይ ለመገኘት በምታደርገው ጥረት እንደሚደሰት እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።

b ምዕመናኑ በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ ቂጣውና የወይን ጠጁ ቃል በቃል ወደ ክርስቶስ ሥጋና ደም እንደሚቀየሩ ያምናሉ። ይህን ሲሉ ሥነ ሥርዓቱ በተካሄደ ቁጥር የኢየሱስ ሥጋና ደም እንደ አዲስ መሥዋዕት ሆኖ እንደሚቀርብ መግለጻቸው ነው።

c አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

d “የ2021 የመታሰቢያው በዓል አከባበር” የሚሉትን ርዕሶችም jw.org ላይ ተመልከት።

e የሥዕሉ መግለጫ: ከ1960ዎቹ አንስቶ በመታሰቢያው በዓል መጋበዣዎች ላይ ማሻሻያ ሲደረግ ቆይቷል፤ አሁን መጋበዣው ታትሞም ሆነ በኤሌክትሮኒክ ፎርማት ይወጣል።

f የሥዕሉ መግለጫ: የእርስ በርስ ጦርነት ባለበት አካባቢ ወንድሞች የመታሰቢያውን በዓል ሲያከብሩ (ለማሳያ ያህል እንጂ እውነተኛ አይደለም)።