በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 3

መዝሙር 124 ምንጊዜም ታማኝ መሆን

በመከራ ወቅት ይሖዋ ይረዳሃል

በመከራ ወቅት ይሖዋ ይረዳሃል

‘ይሖዋ አጽንቶ ያቆማችኋል።’1 ጴጥ. 5:10

ዓላማ

በመከራ ወቅት የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለብን እንመለከታለን።

1-2. ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ምን ዓይነት ችግሮች ሊያጋጥሟቸው ይችላሉ?

 አስደንጋጭ ሁኔታ ሲያጋጥመን ሕይወታችን በቅጽበት ሊቀየር ይችላል። ለምሳሌ ሉዊስ a የተባለ ታማኝ ወንድም ካንሰር እንዳለበት በምርመራ ታወቀ። ሐኪሙ፣ ከዚህ በኋላ በሕይወት የሚቆየው ለጥቂት ወራት ብቻ እንደሆነ ነገረው። ሞኒካ እና ባለቤቷ ሕይወታቸው በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የተሞላ ነበር። ከዚያም አንድ ቀን ሞኒካ፣ የጉባኤ ሽማግሌ የሆነው ባለቤቷ ለበርካታ ዓመታት ሁለት ዓይነት ሕይወት ሲመራ እንደቆየ አወቀች። ኦሊቪያ የተባለች ያላገባች እህት በአካባቢዋ ከባድ አውሎ ነፋስ በመከሰቱ ቤቷን ለቃ ለመሸሽ ተገደደች። ከጊዜ በኋላ ወደ ቤቷ ስትመለስ አውሎ ነፋሱ ቤቷን ሙሉ በሙሉ እንዳወደመው ተመለከተች። እነዚህ ሰዎች ሕይወታቸው በቅጽበት ተቀይሯል። አንተስ ሕይወትህን ሙሉ በሙሉ የሚቀይር አስደንጋጭ ሁኔታ አጋጥሞህ ያውቃል?

2 ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ብንሆንም እንኳ በሰው ሁሉ ላይ የሚደርሰው መከራና ሕመም ይደርስብናል። ከዚህም ሌላ፣ የአምላክን ሕዝቦች የሚጠሉ ሰዎች ተቃውሞ ወይም ስደት ያደርሱብን ይሆናል። ይሖዋ እንዲህ ያሉ ችግሮች እንዳይደርሱብን ባይከላከልልንም እንደሚረዳን ቃል ገብቶልናል። (ኢሳ. 41:10) በእሱ እርዳታ ደስታችንን መጠበቅ፣ ጥሩ ውሳኔዎችን ማድረግ እንዲሁም በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነንም እንኳ ለእሱ ታማኝ ሆነን መቀጠል እንችላለን። በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ከባድ መከራ ሲያጋጥመን ይሖዋ እኛን ከሚረዳባቸው መንገዶች አራቱን እንመለከታለን። በተጨማሪም የእሱን እርዳታ ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለብን እንመለከታለን።

ይሖዋ ይጠብቅሃል

3. ከባድ መከራ ሲያጋጥመን ምን ማድረግ ሊከብደን ይችላል?

3 ተፈታታኙ ነገር። ከባድ መከራ ሲያጋጥመን በትክክል ማሰብና ውሳኔ ማድረግ ሊከብደን ይችላል። ለምን? ልባችን ከፍተኛ ሥቃይ ውስጥ ሊሆን ይችላል። አእምሯችንም በጭንቀት ሊወጠር ይችላል። በጉም ውስጥ የምንጓዝ ያህል መውጫ መንገዱ ሊጠፋብን ይችላል። ቀደም ሲል የተጠቀሱት ሁለት እህቶች፣ ያጋጠማቸው መከራ ምን ስሜት እንደፈጠረባቸው እንመልከት። ኦሊቪያ እንዲህ ብላለች፦ “አውሎ ነፋሱ ቤቴን ካወደመው በኋላ በግራ መጋባትና በተስፋ መቁረጥ ተዋጥኩ።” ሞኒካም የባሏ ክህደት ስለፈጠረባት ስሜት ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “የተሰማኝ ሐዘን በቃላት ሊገለጽ የሚችል አይደለም። ውስጤን የሚወጋ ሥቃይ ተሰማኝ። የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቼን ማድረግ ተሳነኝ። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሊያጋጥመኝ ይችላል ብዬ ፈጽሞ አስቤ አላውቅም ነበር።” በጭንቀት በምንዋጥበት ጊዜ ይሖዋ ምን ዓይነት እርዳታ እንደሚሰጠን ቃል ገብቶልናል?

4. በፊልጵስዩስ 4:6, 7 መሠረት ይሖዋ ምን ቃል ገብቶልናል?

4 ይሖዋ የሚያደርግልን ነገር። ይሖዋ፣ መጽሐፍ ቅዱስ “የአምላክ ሰላም” በማለት የሚጠራውን ሰላም እንደሚሰጠን ቃል ገብቶልናል። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7ን አንብብ።) እንዲህ ያለው ሰላም ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ከመመሥረት የሚመነጭ አእምሯዊና ልባዊ መረጋጋትን ያመለክታል። ይህ ሰላም “ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ” ነው፤ ልናስብ ከምንችለው በላይ አስደናቂ ነገር ነው። ወደ ይሖዋ አጥብቀህ ከጸለይክ በኋላ ለመግለጽ የሚከብድ ዓይነት የመረጋጋት ስሜት ተሰምቶህ ያውቃል? “የአምላክ ሰላም” ማለት ይህ ነው።

5. የአምላክ ሰላም ልባችንንና አእምሯችንን የሚጠብቅልን እንዴት ነው?

5 ጥቅሱ ‘የአምላክ ሰላም ልባችንንና አእምሯችንን እንደሚጠብቅ’ ይናገራል። “ይጠብቃል” ተብሎ የተተረጎመው የበኩረ ጽሑፉ ቃል አንዲትን ከተማ ከጥቃት የሚጠብቁ ወታደሮችን ለማመልከት ይሠራበት ነበር። በወታደር በምትጠበቅ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ጠባቂዎች እንዳሉ ስለሚያውቁ በሰላም ተኝተው ያድራሉ። በተመሳሳይም የአምላክ ሰላም ልባችንንና አእምሯችንን ሲጠብቅልን ምንም ጉዳት እንደማይደርስብን ስለምናውቅ የመረጋጋት ስሜት ይሰማናል። (መዝ. 4:8) ያለንበት ሁኔታ ወዲያውኑ ባይቀየርም እንኳ እንደ ሐና በተወሰነ መጠን ሰላም ማግኘት እንችላለን። (1 ሳሙ. 1:16-18) ውስጣችን ሲረጋጋ ደግሞ አጥርተን ማሰብና ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ውሳኔዎችን ማድረግ ቀላል ይሆንልናል።

“የአምላክ ሰላም” ልብህንና አእምሮህን እስኪጠብቅልህ ድረስ ጸልይ (ከአንቀጽ 4-6⁠ን ተመልከት)


6. የአምላክን ሰላም ለማግኘት ምን ማድረግ እንችላለን? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

6 ማድረግ ያለብን ነገር። በጭንቀት በምትዋጥበት ጊዜ በምሳሌያዊ ሁኔታ ጠባቂውን ጥራ። እንዲህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? የአምላክን ሰላም እስክታገኝ ድረስ ጸልይ። (ሉቃስ 11:9፤ 1 ተሰ. 5:17) ቀደም ሲል የተጠቀሰው ሉዊስ፣ በሕይወት የሚቆየው ለጥቂት ወራት ብቻ እንደሆነ እሱና ባለቤቱ አና ባወቁበት ወቅት ሁኔታውን ለመቋቋም የረዳቸው ምን እንደሆነ ተናግሯል። እንዲህ ብሏል፦ “እንዲህ ባለው ወቅት ከሕክምናም ሆነ ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ውሳኔ ማድረግ በጣም ከባድ ነው። ሆኖም መጸለያችን ሰላም እንድናገኝ በእጅጉ ረድቶናል።” ሉዊስና ባለቤቱ ወደ ይሖዋ አጥብቀው በተደጋጋሚ በመጸለይ አእምሯዊ ሰላም፣ ልባዊ መረጋጋትና ጥሩ ውሳኔዎችን ለማድረግ የሚያስችል ጥበብ እንዲሰጣቸው እንደለመኑት ተናግረዋል። ደግሞም የእሱን እርዳታ ማየት ችለዋል። አንተም ከባድ መከራ ካጋጠመህ ሳትታክት ጸልይ። እንዲህ ካደረግክ፣ የይሖዋ ሰላም ልብህንና አእምሮህን ይጠብቅልሃል።—ሮም 12:12

አጽንቶ ያቆምሃል

7. ከባድ መከራ ሲያጋጥመን ምን ሊሰማን ይችላል?

7 ተፈታታኙ ነገር። ከባድ መከራ ሲያጋጥመን ስሜታችን፣ አስተሳሰባችን እንዲሁም ለተለያዩ ነገሮች የምንሰጠው ምላሽ እንደ ቀድሞው ሚዛኑን የጠበቀ ላይሆን ይችላል። በስሜት ማዕበል እንደምንናወጥ ሆኖ ሊሰማን ይችላል። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው አና፣ ሉዊስ ከሞተ በኋላ የተለያዩ ዓይነት ስሜቶች ይፈራረቁባት እንደነበር ተናግራለች። እንዲህ ብላለች፦ “የባዶነት ስሜት ሲሰማኝ ለራሴ ማዘን እጀምራለሁ። በተጨማሪም እሱ በመሞቱ እናደዳለሁ።” ከዚህም ሌላ አና ብቸኝነት ይሰማት ነበር፤ እንዲሁም ሉዊስ ጥሩ አድርጎ ይወጣቸው የነበሩት ኃላፊነቶች እሷ ላይ በመውደቃቸው ትበሳጭ ነበር። አንዳንድ ጊዜ፣ በማዕበል በሚናወጥ ባሕር ውስጥ እንዳለች ሆኖ ይሰማት ነበር። እንዲህ ያሉ ስሜቶች ሲያናውጡን ይሖዋ የሚረዳን እንዴት ነው?

8. በ1 ጴጥሮስ 5:10 መሠረት ይሖዋ ምን ቃል ገብቶልናል?

8 ይሖዋ የሚያደርግልን ነገር። ይሖዋ አጽንቶ እንደሚያቆመን ቃል ገብቶልናል። (1 ጴጥሮስ 5:10ን አንብብ።) አንድ መርከብ ማዕበል ሲያጋጥመው በኃይል ሊወዛወዝ ይችላል። ብዙ መርከቦች እንዲህ ያለውን ነውጥ ለመቀነስ የሚያስችል በሁለቱም ወገን ወደ ውኃው ውስጥ የሚገባ ክንፍ አላቸው። ይህ የመርከቡ ክፍል መርከቡ በኃይል እንዳይናወጥ ያደርገዋል፤ ይህም ተሳፋሪዎቹ ጉዳት እንዳይደርስባቸውና ተመችቷቸው እንዲጓዙ ያስችላል። ይሁንና እነዚህ ክንፎች ይበልጥ ውጤታማ የሚሆኑት መርከቡ ወደፊት እየተጓዘ ከሆነ ነው። በተመሳሳይም በመከራ ወቅት በታማኝነት ወደፊት መጓዛችንን ስንቀጥል ይሖዋ አጽንቶ ያቆመናል።

የምርምር መሣሪያዎቻችንን በመጠቀም ሚዛንህን ጠብቅ (ከአንቀጽ 8-9⁠ን ተመልከት)


9. የምርምር መሣሪያዎቻችን ሚዛናችንን ለመጠበቅ የሚረዱን እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

9 ማድረግ ያለብን ነገር። የስሜት ማዕበል ሲያናውጥህ መንፈሳዊ ልማድህን ይዘህ ለመቀጠል የቻልከውን ሁሉ አድርግ። እርግጥ ነው፣ የቀድሞውን ያህል ማድረግ አትችል ይሆናል። ያም ቢሆን፣ ይሖዋ ምክንያታዊ እንደሆነ አስታውስ። (ከሉቃስ 21:1-4 ጋር አወዳድር።) ለግል ጥናትና ለማሰላሰል ጊዜ መድብ። ለምን? ይሖዋ በድርጅቱ አማካኝነት፣ ሚዛናችንን ለመጠበቅ የሚረዱ አስደናቂ ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርቶችን አዘጋጅቶልናል። የሚያስፈልግህን መረጃ ለማግኘት JW ላይብረሪ አፕሊኬሽንን እና የምርምር መርጃ መሣሪያ ለይሖዋ ምሥክሮችን ጨምሮ በቋንቋህ የሚገኙ የምርምር መሣሪያዎችን መጠቀም ትችላለህ። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሞኒካ ስሜቷ መናወጥ ሲጀምር ምክር ለማግኘት የምርምር መሣሪያዎቻችንን እንደምትጠቀም ተናግራለች። ለምሳሌ በመፈለጊያ ሣጥኑ ውስጥ “ቁጣ” ብላ ትጽፋለች። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ “ክህደት” ወይም “ታማኝነት” በሚሉት ቃላት ላይ ምርምር ታደርጋለች። ከዚያም ስሜቷ እስኪረጋጋ ድረስ ታነብባለች። እንዲህ ብላለች፦ “ምርምር ማድረግ የምጀምረው በጭንቀት ተውጬ ነው። በኋላ ግን ይሖዋ እቅፍ እንዳደረገኝ ሆኖ ይሰማኛል። ማንበቤን ስቀጥል ይሖዋ ስሜቴን በሙሉ እንደሚረዳልኝ እንዲሁም እንደሚረዳኝ ተገነዘብኩ።” አንተም ከይሖዋ እንዲህ ያለውን እርዳታ ማግኘትህ ማዕበሉ እስኪረጋጋ ድረስ ሚዛንህን እንድትጠብቅ ይረዳሃል።—መዝ. 119:143, 144

ይሖዋ ይደግፍሃል

10. ከባድ መከራ ሲያጋጥመን ምን ሊሰማን ይችላል?

10 ተፈታታኙ ነገር። ከባድ መከራ ሲያጋጥመን በአካላዊም ሆነ በስሜታዊ እንደዛልን የሚሰማን ጊዜ ይኖራል። ቀደም ሲል በፍጥነት መሮጥ ይችል የነበረ ቢሆንም በደረሰበት ጉዳት የተነሳ እያነከሰ እንደሚሄድ ሯጭ እንደሆንን ሊሰማን ይችላል። ከዚህ በፊት በቀላሉ እናከናውናቸው የነበሩትን ነገሮች ማድረግ ሊከብደን ወይም ደግሞ ያስደስቱን በነበሩት እንቅስቃሴዎች ለመካፈል ተነሳሽነት ልናጣ እንችላለን። እንደ ኤልያስ መነሳት ሊከብደንና መተኛት ብቻ ሊያሰኘን ይችላል። (1 ነገ. 19:5-7) እንደዛልን ሲሰማን ይሖዋ ምን እንደሚያደርግልን ቃል ገብቶልናል?

11. ይሖዋ እኛን የሚረዳበት ሌላው መንገድ ምንድን ነው? (መዝሙር 94:18)

11 ይሖዋ የሚያደርግልን ነገር። ይሖዋ እንደሚደግፈን ቃል ገብቶልናል። (መዝሙር 94:18ን አንብብ።) ጉዳት የደረሰበት ሯጭ ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ ድጋፍ ሊያስፈልገው እንደሚችል ሁሉ እኛም በይሖዋ አገልግሎት መካፈላችንን እንድንቀጥል እርዳታ ሊያስፈልገን ይችላል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመን ይሖዋ የሚከተለውን ዋስትና ሰጥቶናል፦ “‘አትፍራ። እረዳሃለሁ’ የምልህ እኔ፣ አምላክህ ይሖዋ ቀኝ እጅህን ይዣለሁና።” (ኢሳ. 41:13) ንጉሥ ዳዊት እንዲህ ያለውን እርዳታ አግኝቷል። ከፈተናዎችና ከጠላቶቹ ጋር በተጋፈጠበት ወቅት ይሖዋን “ቀኝ እጅህ ይደግፈኛል” ብሎታል። (መዝ. 18:35) ይሁንና ይሖዋ የሚደግፈን እንዴት ነው?

ቤተሰቦችህ፣ ጓደኞችህና ሽማግሌዎች የሚያደርጉልህን ድጋፍ ተቀበል (ከአንቀጽ 11-13⁠ን ተመልከት)


12. በምንዝልበት ጊዜ ይሖዋ እኛን ለመደገፍ እነማንን ሊጠቀም ይችላል?

12 ይሖዋ ብዙውን ጊዜ የሚደግፈን ሌሎች እንዲረዱን በማነሳሳት ነው። ለምሳሌ ዳዊት በዛለበት ወቅት ጓደኛው ዮናታን ወደ እሱ በመምጣት ስሜታዊ ድጋፍና ማበረታቻ ሰጥቶታል። (1 ሳሙ. 23:16, 17) በተጨማሪም ይሖዋ፣ ለኤልያስ ተግባራዊ እርዳታ እንዲሰጠው ኤልሳዕን መርጦታል። (1 ነገ. 19:16, 21፤ 2 ነገ. 2:2) በዛሬው ጊዜም ይሖዋ እኛን ለመደገፍ ቤተሰቦቻችንን፣ ጓደኞቻችንን ወይም ሽማግሌዎችን ሊጠቀም ይችላል። ይሁንና በሐዘን በምንደቆስበት ጊዜ ራሳችንን ማግለል ሊቀናን ይችላል። ብቻችንን መሆን ልንፈልግ እንችላለን። እንዲህ ቢሰማን አያስገርምም። ታዲያ የይሖዋን ድጋፍ ለማግኘት ምን ማድረግ እንችላለን?

13. የይሖዋን ድጋፍ ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

13 ማድረግ ያለብን ነገር። ራስህን ላለማግለል ጥረት አድርግ። ራሳችንን ስናገል እይታችን ስለሚጠብ ስለ ራሳችንና ስላጋጠመን ችግር ብቻ ማሰብ ልንጀምር እንችላለን። እንዲህ ያለው አስተሳሰብ በምናደርጋቸው ውሳኔዎችም ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። (ምሳሌ 18:1) እርግጥ ነው፣ ሁላችንም በተለይ ከባድ መከራ ሲያጋጥመን ብቻችንን መሆን የሚያስፈልገን ጊዜ ይኖራል። ይሁንና ለረጅም ጊዜ ራሳችንን አግልለን ከቆየን ይሖዋ እኛን ለመደገፍ የሚጠቀምበትን መንገድ ልንዘጋ እንችላለን። እንግዲያው በመከራ ውስጥ ስትሆን ከባድ ቢሆንም እንኳ የቤተሰቦችህን፣ የጓደኞችህንና የሽማግሌዎችን እርዳታ ተቀበል። ይሖዋ የሚደግፍህ እነሱን ተጠቅሞ እንደሆነ አስታውስ።—ምሳሌ 17:17፤ ኢሳ. 32:1, 2

ይሖዋ ያጽናናሃል

14. ምን ዓይነት አስፈሪ ሁኔታ ሊያጋጥመን ይችላል?

14 ተፈታታኙ ነገር። በፍርሃት የምንዋጥባቸው ጊዜያት ሊኖሩ ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች በጠላቶቻቸው ወይም በሌሎች ችግሮች የተነሳ በጭንቀት የተዋጡበትና በፍርሃት የተንቀጠቀጡበት ጊዜ እንዳለ ይናገራል። (መዝ. 18:4፤ 55:1, 5) እኛም በትምህርት ቤት፣ በሥራ ቦታ፣ ከቤተሰባችን ወይም ከመንግሥት ተቃውሞ ሊያጋጥመን ይችላል። ምናልባትም በጤና እክል የተነሳ ከሞት ጋር እንፋጠጥ ይሆናል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን እንደ ሕፃን ልጅ ምንም ነገር ማድረግ እንደማንችል ይሰማን ይሆናል። ታዲያ ይሖዋ እንዲህ ባለው ሁኔታ ውስጥ የሚረዳን እንዴት ነው?

15. መዝሙር 94:19 ምን ዋስትና ይሰጠናል?

15 ይሖዋ የሚያደርግልን ነገር። ይሖዋ ያጽናናናል፤ እንዲሁም ያረጋጋናል። (መዝሙር 94:19ን አንብብ።) ይህ ጥቅስ፣ ኃይለኛ ነጎድጓድ በመኖሩ ምክንያት በፍርሃት ተውጣ መተኛት ያቃታትን ትንሽ ልጅ ያስታውሰን ይሆናል። አባቷ መጥቶ ሲያነሳትና እንቅልፍ እስኪወስዳት ድረስ እቅፍ ሲያደርጋት በዓይነ ሕሊናችን ልንሥል እንችላለን። ነጎድጓዱ ባይቆምም እንኳ በአባቷ እቅፍ ውስጥ መሆኗ እንድትረጋጋ ያደርጋታል። እኛም አስፈሪ መከራ ሲያጋጥመን የሰማዩ አባታችን ስሜታችን እስኪረጋጋ ድረስ በምሳሌያዊ ሁኔታ አቅፎ እንዲያባብለን እንፈልግ ይሆናል። ይሁንና ከይሖዋ እንዲህ ያለውን ማጽናኛ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

የሰማዩ አባትህ በቅዱሳን መጻሕፍት አማካኝነት እንዲያጽናናህ ፍቀድለት (ከአንቀጽ 15-16⁠ን ተመልከት)


16. ከይሖዋ ማጽናኛ ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

16 ማድረግ ያለብን ነገር። ወደ ይሖዋ በመጸለይና ቃሉን በማንበብ አዘውትረህ ከእሱ ጋር ጊዜ አሳልፍ። (መዝ. 77:1, 12-14) እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ውጥረት ውስጥ ስትገባ ወዲያውኑ ወደ ይሖዋ ዞር ለማለት ትነሳሳለህ። ፍርሃትህንና ጭንቀትህን ለይሖዋ ንገረው። በቅዱሳን መጻሕፍት አማካኝነት እንዲያነጋግርህና እንዲያጽናናህ ፍቀድለት። (መዝ. 119:28) በምትፈራበት ጊዜ በተለይ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ማንበብህ ያጽናናህ ይሆናል። ለምሳሌ በኢዮብ፣ በመዝሙርና በምሳሌ መጽሐፍ እንዲሁም ኢየሱስ በማቴዎስ ምዕራፍ 6 ላይ በተናገራቸው ቃላት ውስጥ የሚያበረታታ ሐሳብ ማግኘት ትችላለህ። ወደ ይሖዋ የምትጸልይና ቃሉን የምታነብ ከሆነ እሱ የሚሰጥህን ማጽናኛ ማጣጣም ትችላለህ።

17. ስለ ምን ጉዳይ እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

17 በሕይወታችን ውስጥ ከባድ መከራ ሲያጋጥመን ይሖዋ እንደሚደርስልን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። መቼም ቢሆን ብቻችንን አይተወንም። (መዝ. 23:4፤ 94:14) ይሖዋ እንደሚጠብቀን፣ አጽንቶ እንደሚያቆመን፣ እንደሚደግፈን እንዲሁም እንደሚያጽናናን ቃል ገብቶልናል። ኢሳይያስ 26:3 ስለ ይሖዋ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “ሙሉ በሙሉ በአንተ የሚመኩትን ትጠብቃለህ፤ በአንተ ስለሚታመኑ ዘላቂ ሰላም ትሰጣቸዋለህ።” እንግዲያው በይሖዋ ታመን፤ እንዲሁም አንተን ለመርዳት ያደረጋቸውን ዝግጅቶች በሙሉ ጥሩ አድርገህ ተጠቀምባቸው። እንዲህ የምታደርግ ከሆነ በመከራ ወቅትም ብርታት ማግኘት ትችላለህ።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • የይሖዋ እርዳታ የሚያስፈልገን በተለይ መቼ ሊሆን ይችላል?

  • በመከራ ወቅት ይሖዋ የሚረዳን በየትኞቹ አራት መንገዶች ነው?

  • የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብናል?

መዝሙር 12 ታላቁ አምላክ ይሖዋ

a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።