ይህን ያውቁ ኖሯል?
ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ፣ ፊልጶስ ሲያነጋግረው በምን ዓይነት ሠረገላ ውስጥ ነበር?
በአዲስ ዓለም ትርጉም ላይ “ሠረገላ” ተብሎ የተተረጎመው የበኩረ ጽሑፉ ቃል የተለያዩ ዓይነት ሠረገላዎችን ሊያመለክት ይችላል። (ሥራ 8:28, 29, 38) ይሁንና ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ የተጠቀመበት ሠረገላ ለጦርነት ወይም ለውድድር ከሚያገለግለው አነስተኛ ሠረገላ የሚበልጥ ሳይሆን አይቀርም። እዚህ መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ የሚያደርጉንን አንዳንድ ምክንያቶች እስቲ እንመልከት።
ኢትዮጵያዊው ከፍተኛ ባለሥልጣን ከመሆኑም ሌላ ረጅም ርቀት ተጉዟል። ይህ ሰው “የኢትዮጵያ ንግሥት የህንደኬ ባለሥልጣንና የገንዘቧ ሁሉ ኃላፊ” ነበር። (ሥራ 8:27) የጥንቷ ኢትዮጵያ ግዛት የአሁኗን ሱዳን እንዲሁም የአሁኗን ግብፅ ደቡባዊ ክፍል ያካትት ነበር። ኢትዮጵያዊው ሙሉውን መንገድ የተጓዘው በአንድ ሠረገላ ላይሆን ቢችልም እንኳ ለረጅሙ ጉዞው የያዘው ብዙ ጓዝ እንደሚኖረው ምንም ጥያቄ የለውም። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለጉዞ ያገለግሉ ከነበሩት ሠረገላዎች መካከል አራት መንኮራኩርና ጣሪያ ያላቸው ሠረገላዎች ይገኙበታል። አክትስ—አን ኢክሴጄቲካል ኮሜንተሪ የተባለው መጽሐፍ እንደሚገልጸው “እንዲህ ያለው ሠረገላ ብዙ ጓዝ ለመያዝ፣ ጉዞን አመቺ ለማድረግ፣ ካስፈለገም ረጅም ርቀት ለመጓዝ ያስችላል።”
ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ከፊልጶስ ጋር በተገናኘበት ወቅት እያነበበ ነበር። ዘገባው “ፊልጶስ ከሠረገላው ጎን እየሮጠ ጃንደረባው የነቢዩ ኢሳይያስን መጽሐፍ ጮክ ብሎ ሲያነብ” እንደሰማ ይገልጻል። (ሥራ 8:30) ረጅም ርቀት ለመጓዝ የሚያገለግሉት ሠረገላዎች የሚዘጋጁት በፍጥነት ለመጓዝ በሚያስችል መንገድ አልነበረም። ጃንደረባው ሠረገላው ውስጥ ሆኖ ማንበብ፣ ፊልጶስም በእግሩ ሮጦ ሠረገላው ላይ መድረስ የቻለው እንዲህ ያሉት ሠረገላዎች ቀስ ብለው ስለሚጓዙ ሊሆን ይችላል።
ኢትዮጵያዊው ‘ፊልጶስን ሠረገላው ላይ ወጥቶ አብሮት እንዲቀመጥ ለምኖታል።’ (ሥራ 8:31) ለውድድር በሚያገለግሉት ሠረገላዎች ላይ ነጂዎቹ የሚጓዙት ቆመው ነው። ለጉዞ በሚያገለግሉት ተለቅ ያሉ ሠረገላዎች ውስጥ ግን ጃንደረባውንም ሆነ ፊልጶስን ለማስቀመጥ የሚያስችል በቂ ቦታ ይኖራል።
በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 8 ላይ የሚገኘውን በመንፈስ መሪነት የተጻፈ ዘገባ እንዲሁም ታሪካዊ ማስረጃዎችን መሠረት በማድረግ፣ ጽሑፎቻችን ላይ በሚወጡት ሥዕሎች ላይ ማስተካከያ ተደርጓል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስለ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ በወጡ ጽሑፎቻችን ላይ የሚታየው ሠረገላ ለውድድር ወይም ለጦርነት የሚያገለግለው ዓይነት አነስተኛ ሠረገላ ሳይሆን ለጉዞ የሚያገለግለው ዓይነት ተለቅ ያለ ሠረገላ ነው።