በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 1

መዝሙር 2 ስምህ ይሖዋ ነው

ለይሖዋ ክብር ስጡ

ለይሖዋ ክብር ስጡ

የ2025 የዓመት ጥቅስ፦ “ለስሙ የሚገባውን ክብር ለይሖዋ ስጡ።”መዝ. 96:8

ዓላማ

ለይሖዋ የሚገባውን ክብር መስጠት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንማራለን።

1. በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎች ትኩረታቸው ያረፈው በማን ላይ ነው?

 በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎች ትኩረታቸው በራሳቸው ላይ ብቻ ያረፈ እንደሆነ አስተውላችኋል? ለምሳሌ አንዳንዶች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ወደ ራሳቸው ትኩረት ለመሳብና ስላገኙት ስኬት ጉራ ለመንዛት ብዙ ጥረት ያደርጋሉ። ሆኖም ለይሖዋ አምላክ ክብር የሚሰጡት ሰዎች ቁጥር በአንጻራዊ ሁኔታ አነስተኛ ነው። በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ለይሖዋ ክብር መስጠት ሲባል ምን ማለት እንደሆነና እንዲህ እንድናደርግ የሚያነሳሳን ምን እንደሆነ እንመለከታለን። ከዚህም በተጨማሪ ለይሖዋ የሚገባውን ክብር መስጠት የምንችለው እንዴት እንደሆነና በቅርቡ ደግሞ እሱ ራሱ ስሙን የሚያስቀድሰው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

ለይሖዋ ክብር መስጠት ሲባል ምን ማለት ነው?

2. ይሖዋ በሲና ተራራ ላይ ክብሩን የገለጠው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

2 ክብር ምንድን ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ክብር” የሚለው ቃል አንድን አካል በሌሎች ዘንድ ከፍ ተደርጎ እንዲታይ የሚያደርገውን ማንኛውንም ነገር ያመለክታል። የእስራኤል ብሔር ከግብፅ ባርነት ነፃ ከወጣ ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ አምላክ ክብሩን አስደናቂ በሆነ መንገድ አሳይቷል። እስቲ ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናችሁ ለመሣል ሞክሩ፦ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን በአምላካቸው ፊት ለመቅረብ ሲሉ በሲና ተራራ ግርጌ ተሰብስበዋል። ጥቅጥቅ ያለ ደመና ተራራውን ሸፈነው። በድንገት በተራራው ዙሪያ ጭስ እየተትጎለጎለ ይወጣ ጀመር። መሬቱም በኃይል ተንቀጠቀጠ። መብረቅ፣ ነጎድጓድና ከፍተኛ የቀንደ መለከት ድምፅ አካባቢውን አናወጠው። (ዘፀ. 19:16-18፤ 24:17፤ መዝ. 68:8) ይሖዋ ክብሩን እንዲህ ባለ መንገድ ሲገልጥ እስራኤላውያን ምን ያህል ተደምመው ሊሆን እንደሚችል አስቡት።

ይሖዋ በሲና ተራራ ላይ ለእስራኤላውያን ክብሩን አስደናቂ በሆነ መንገድ ገልጦላቸዋል (አንቀጽ 2⁠ን ተመልከት)


3. ለይሖዋ ክብር መስጠት ሲባል ምን ማለት ነው?

3 ታዲያ ሰዎች ለይሖዋ ክብር መስጠት ይችላሉ? አዎ፣ ይችላሉ። ለይሖዋ ክብር መስጠት የምንችልበት አንዱ መንገድ ስለ ታላቅ ኃይሉና ስለ ማራኪ ባሕርያቱ ለሌሎች በመናገር ነው። የምናከናውናቸው ነገሮች እንዲሳኩልን ላደረገልን እርዳታ እውቅና በመስጠትም ለአምላክ ክብር መስጠት እንችላለን። (ኢሳ. 26:12) ንጉሥ ዳዊት ለይሖዋ ክብር በመስጠት ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። ዳዊት በእስራኤል ሕዝብ ፊት ባቀረበው ጸሎት ላይ እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ ሆይ፣ ታላቅነት፣ ኃያልነት፣ ውበት፣ ግርማና ሞገስ የአንተ ነው፤ በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ የአንተ ነው።” ዳዊት ጸሎቱን ከደመደመ በኋላ “ጉባኤውም ሁሉ . . . ይሖዋን አወደሱ።”—1 ዜና 29:11, 20

4. ኢየሱስ ለይሖዋ ክብር የሰጠው እንዴት ነው?

4 ኢየሱስ በምድር ላይ ሳለ፣ ተአምር መሥራት የቻለው በአምላክ እርዳታ እንደሆነ በመናገር ለአባቱ ክብር ሰጥቷል። (ማር. 5:18-20) ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ስለ አባቱ በተናገረው ነገርና ሰዎችን በያዘበት መንገድ ለይሖዋ ክብር ሰጥቷል። ለምሳሌ በአንድ ወቅት ኢየሱስ በምኩራብ እያስተማረ ነበር። ከሚያዳምጡት ሰዎች መካከል፣ ባደረባት ጋኔን የተነሳ ለ18 ዓመታት ስትሠቃይ የኖረች ሴት ነበረች። ከጋኔኑ የተነሳ በጣም ስለጎበጠች ፈጽሞ ቀና ማለት አትችልም ነበር። እንዴት የሚያሳዝን ነው! ኢየሱስ ለሴትየዋ ስለራራላት ቀረብ ብሎ በደግነት አነጋገራት፤ “አንቺ ሴት፣ ከበሽታሽ ተገላግለሻል” አላት። ከዚያም እጁን ሲጭንባት ወዲያውኑ ቀጥ አለች፤ “አምላክንም ማመስገን ጀመረች።” (ሉቃስ 13:10-13) ሴትየዋ ጤንነቷ ስለተመለሰላት ለአምላክ ክብር ለመስጠት ተነሳስታለች። እኛም እንደ እሷ ለአምላክ ክብር ለመስጠት የሚያነሳሳ አጥጋቢ ምክንያት አለን።

ለይሖዋ ክብር ለመስጠት የሚያነሳሳን ምንድን ነው?

5. ለይሖዋ ክብር ለመስጠት የሚያነሳሱን ምን ምክንያቶች አሉን?

5 ለይሖዋ ክብር የምንሰጠው አክብሮት ስለሚገባው ነው። ይሖዋ ሁሉን ቻይ ነው፤ ኃይሉ ገደብ የለውም። (መዝ. 96:4-7) ጥበቡ ጥልቅ መሆኑ ከፈጠራቸው ነገሮች በግልጽ ይታያል። ሕይወትንም ሆነ ለመኖር የሚያስፈልጉንን ነገሮች በሙሉ የሰጠን እሱ ነው። (ራእይ 4:11) ታማኝ ነው። (ራእይ 15:4) የሚያከናውነው ነገር ሁሉ ይሳካል፤ ቃሉንም ሁልጊዜ ይጠብቃል። (ኢያሱ 23:14) ነቢዩ ኤርምያስ ስለ ይሖዋ እንዲህ ማለቱ የሚያስገርም አይደለም፦ “ከብሔራት ጠቢባን ሁሉ እንዲሁም ከመንግሥቶቻቸው ሁሉ መካከል እንደ አንተ ያለ ማንም የለም።” (ኤር. 10:6, 7) በእርግጥም ለሰማያዊ አባታችን ክብር ለመስጠት የሚያነሳሱን አጥጋቢ ምክንያቶች አሉን። ሆኖም ይሖዋን ማክበር ብቻ ሳይሆን በጣም እንወደዋለን።

6. ይሖዋን የምንወደው ለምንድን ነው?

6 ለይሖዋ ክብር የምንሰጠው ከልባችን ስለምንወደው ነው። ይሖዋ በርካታ ግሩም ባሕርያት ስላሉት እንወደዋለን። መሐሪና ሩኅሩኅ ነው። (መዝ. 103:13፤ ኢሳ. 49:15) ስሜታችንን ይረዳልናል፤ ሥቃያችን ይሰማዋል። (ዘካ. 2:8) ወደ እሱ እንድንቀርብና ወዳጆቹ እንድንሆን ፈቅዶልናል። (መዝ. 25:14፤ ሥራ 17:27) ትሑት ነው፤ “ሰማይንና ምድርን ለማየት ወደ ታች ያጎነብሳል፤ ችግረኛውን ከአፈር ያነሳል።” (መዝ. 113:6, 7) ታዲያ ለታላቁ አምላካችን ክብር ለመስጠት ብንነሳሳ ምን ያስገርማል?—መዝ. 86:12

7. ምን ልዩ አጋጣሚ አግኝተናል?

7 ለይሖዋ ክብር የምንሰጠው ሌሎች ስለ እሱ እንዲያውቁ ስለምንፈልግ ነው። ብዙዎች ስለ ይሖዋ እውነቱን አያውቁም። ለምን? ምክንያቱም ሰይጣን ስለ ይሖዋ መርዘኛ ውሸቶችን በመንዛት አእምሯቸውን አሳውሯል። (2 ቆሮ. 4:4) ሰይጣን፣ ይሖዋ በቀለኛ፣ ለሰዎች የማያስብ እንዲሁም በዓለም ላይ ላሉት ችግሮች መንስኤ እንደሆነ ሰዎችን አሳምኗል። እኛ ግን ስለ አምላካችን እውነቱን እናውቃለን! ስለ ይሖዋ እውነቱን በመናገር ለእሱ ክብር የማምጣት አጋጣሚ አግኝተናል። (ኢሳ. 43:10) መዝሙር 96 ለይሖዋ ክብር ስለ መስጠት ይናገራል። በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን ይህን መዝሙር ስንመረምር ለይሖዋ የሚገባውን ክብር መስጠት ስለምትችሉበት መንገድ ለማሰብ ሞክሩ።

ለይሖዋ የሚገባውን ክብር መስጠት የምንችለው እንዴት ነው?

8. ለይሖዋ ክብር መስጠት የምንችልበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው? (መዝሙር 96:1-3)

8 መዝሙር 96:1-3ን አንብብ። ስለ ይሖዋ በምንናገረው ነገር ለእሱ ክብር መስጠት እንችላለን። በዚህ ጥቅስ ላይ የይሖዋ ሕዝቦች ‘ለይሖዋ እንዲዘምሩ፣’ ‘ስሙን እንዲያወድሱ፣’ ‘የማዳኑን ምሥራች እንዲያውጁ’ እና ‘ክብሩን በብሔራት መካከል እንዲያስታውቁ’ ተጋብዘዋል። እነዚህ ሁሉ ለሰማዩ አባታችን ክብር መስጠት የምንችልባቸው መንገዶች ናቸው። ታማኝ አይሁዳውያንና የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ይሖዋ ስላደረገላቸው መልካም ነገር ከመናገርና ለስሙ ጥብቅና ከመቆም ወደኋላ አላሉም። (ዳን. 3:16-18፤ ሥራ 4:29) እኛስ እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

9-10. ከአንጀሊና ተሞክሮ ምን ትምህርት አግኝታችኋል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

9 በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖረውን የእህት አንጀሊናን a ተሞክሮ እንደ ምሳሌ እንመልከት። በምትሠራበት ድርጅት ውስጥ ለይሖዋ ስም በድፍረት ጥብቅና ቆማለች። ድርጅቱ አዳዲስ ሠራተኞች ራሳቸውን የሚያስተዋውቁበት ስብሰባ አዘጋጀ። አንጀሊናም አዲስ ሠራተኛ እንደመሆኗ መጠን በስብሰባው ላይ ተገኘች። አንጀሊና የይሖዋ ምሥክር በመሆኗ ያገኘችውን ደስታ የሚያሳዩ ፎቶግራፎችን አዘጋጀች። ሆኖም የአንጀሊና ተራ ልክ ከመድረሱ በፊት አብሯት የሚሠራ ሌላ ሰው በይሖዋ ምሥክር ቤተሰብ ውስጥ እንዳደገ ተናገረ። በምናምንባቸው ነገሮች ላይም ያሾፍ ጀመር። አንጀሊና እንዲህ ብላለች፦ “ልቤ መምታት ጀመረ። ሆኖም ‘አንድ ሰው ስለ ይሖዋ ውሸት እየተናገረ እንዴት ዝም ልል እችላለሁ? ለእሱ ጥብቅና መቆም ይኖርብኛል’ ብዬ አሰብኩ።”

10 የሥራ ባልደረባዋ ንግግሩን ሲጨርስ አንጀሊና በልቧ አጭር ጸሎት አቀረበች። ከዚያም ደግነት በሚንጸባረቅበት ቃና እንዲህ አለችው፦ “የእኔም አስተዳደግ ከአንተ ጋር ይመሳሰላል። ያደግኩት በይሖዋ ምሥክር ቤተሰብ ውስጥ ነው፤ አሁንም የይሖዋ ምሥክር ነኝ።” ሁኔታው የሚያስጨንቅ ቢሆንም አንጀሊና ተረጋግታ በመንፈሳዊ ዝግጅቶች ላይ የተነሳቻቸውን ደስ የሚሉ ፎቶግራፎች አሳየች፤ እንዲሁም በዘዴ ስለ እምነቷ አስረዳች። (1 ጴጥ. 3:15) ታዲያ ምን ውጤት አገኘች? አንጀሊና ንግግሯን ስትጨርስ የሰውየው አመለካከት ረገብ አለ። እንዲያውም ልጅ ሳለ ከይሖዋ ምሥክር ቤተሰቡ ጋር አስደሳች ጊዜ እንዳሳለፈ ተናገረ። አንጀሊና እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ ጥብቅና ልንቆምለት የሚገባው አምላክ ነው። ለስሙ ጥብቅና መቆም ታላቅ ክብር ነው።” እኛም ብንሆን ሌሎች ለይሖዋ ክብር በማይሰጡበት ጊዜም እንኳ እሱን የማወደስና ለእሱ ክብር የመስጠት ልዩ መብት አግኝተናል።

በንግግራችን፣ ለይሖዋ ክብር መስጠት እንችላለን (አንቀጽ 9-10⁠ን ተመልከት) b


11. በታሪክ ዘመናት ሁሉ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች በመዝሙር 96:8 ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ ያደረጉት እንዴት ነው?

11 መዝሙር 96:8ን አንብብ። ባሉን ውድ ነገሮች ለይሖዋ ክብር መስጠት እንችላለን። ከጥንትም ጀምሮ የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች በዚህ መንገድ ክብር ሰጥተውታል። (ምሳሌ 3:9) ለምሳሌ እስራኤላውያን ለቤተ መቅደሱ ግንባታና እንክብካቤ የሚውል መዋጮ አበርክተዋል። (2 ነገ. 12:4, 5፤ 1 ዜና 29:3-9) አሳቢ የሆኑ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት “በንብረታቸው” እሱንና ሐዋርያቱን አገልግለዋቸዋል። (ሉቃስ 8:1-3) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖችም ለመንፈሳዊ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው የእርዳታ መዋጮ ልከዋል። (ሥራ 11:27-29) እኛም በዛሬው ጊዜ በፈቃደኝነት በምናደርገው መዋጮ ለይሖዋ ክብር መስጠት እንችላለን።

12. የምናደርገው መዋጮ ለይሖዋ ክብር የሚያመጣው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

12 የምናደርገው መዋጮ ለይሖዋ ክብር የሚያመጣው እንዴት እንደሆነ የሚያሳይ አንድ ተሞክሮ እንመልከት። በ2020 ዚምባብዌ ውስጥ ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ድርቅ ተከስቶ ነበር። ፕሪስካ የተባለችን እህት ጨምሮ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ለረሃብ ተዳርገው ነበር። ድርቁ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ቢፈጥርም ፕሪስካ ረቡዕንና ዓርብን ለአገልግሎት መድባ ነበር፤ እርሻ በሚታረስበት ጊዜም እንኳ በእነዚህ ቀናት ታገለግላለች። በመንደሩ የሚኖሩ ሰዎች እርሻዋን ከማረስ ይልቅ አገልግሎት በመውጣቷ “ቤተሰብሽን በረሃብ ልትጨርሺ ነው” እያሉ ያሾፉባት ነበር። እሷም በልበ ሙሉነት “ይሖዋ አገልጋዮቹን አሳፍሯቸው አያውቅም” ብላ ትመልስላቸዋለች። ብዙም ሳይቆይ ፕሪስካ ድርጅታችን የላከው የእርዳታ ቁሳቁስ ደረሳት። እነዚህ የእርዳታ ቁሳቁሶች ሊደርሷት የቻሉት በፈቃደኝነት በምናደርገው መዋጮ የተነሳ ነው። አንዳንዶቹ ጎረቤቶቿ በዚህ በጣም ስለተደነቁ ፕሪስካን “አምላክ አሳፍሮሽ አያውቅም፤ ስለዚህ ስለ እሱ መማር እንፈልጋለን” አሏት። ሰባት ጎረቤቶቿ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመሩ።

ባሉን ውድ ነገሮች ለይሖዋ ክብር መስጠት እንችላለን (አንቀጽ 12⁠ን ተመልከት) c


13. ምግባራችን ለይሖዋ ክብር የሚያመጣው እንዴት ነው? (መዝሙር 96:9)

13 መዝሙር 96:9ን አንብብ። በምግባራችን ለይሖዋ ክብር መስጠት እንችላለን። በይሖዋ መቅደስ ውስጥ የሚያገለግሉት ካህናት አካላዊ ንጽሕናቸውን መጠበቅ ነበረባቸው። (ዘፀ. 40:30-32) ሆኖም ሥነ ምግባራዊ ንጽሕና ከአካላዊ ንጽሕናም የበለጠ አስፈላጊ ነው። (መዝ. 24:3, 4፤ 1 ጴጥ. 1:15, 16) “አሮጌውን ስብዕና” ማለትም ርኩስ አስተሳሰቦችንና ልማዶችን ለማስወገድና “አዲሱን ስብዕና” ለመልበስ ማለትም የይሖዋን ክብራማ ባሕርያት የሚያንጸባርቅ አስተሳሰብና ምግባር እንዲኖረን ለማድረግ የምንችለውን ሁሉ ጥረት ልናደርግ ይገባል። (ቆላ. 3:9, 10) ሥነ ምግባራቸው የተበላሸና እጅግ ዓመፀኛ የነበሩ ሰዎችም እንኳ በይሖዋ እርዳታ መለወጥና አዲሱን ስብዕና መልበስ ይችላሉ።

14. ከጃክ ተሞክሮ ምን ትምህርት እናገኛለን? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

14 የጃክን ተሞክሮ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ጃክ ዓመፀኛና አደገኛ ሰው ከመሆኑ የተነሳ “ጋኔኑ” የሚል ቅጽል ስም ወጥቶለት ነበር። ጃክ በፈጸማቸው ወንጀሎች የተነሳ ሞት ተፈረደበት። ሆኖም ፍርዱ የሚፈጸምበትን ጊዜ እየተጠባበቀ ሳለ ወደዚያ እስር ቤት ደጋግሞ ከሚመጣ ወንድም ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማማ። ጃክ በጣም መጥፎ ሰው የነበረ ቢሆንም አሮጌውን ስብዕናውን አውልቆ ጣለ። ውሎ አድሮ ደግሞ ለጥምቀት ብቁ ሆነ። ጃክ በጣም ከመለወጡ የተነሳ የሞት ፍርዱ የሚፈጸምበት ቀን ሲደርስ ከእስር ቤቱ ጠባቂዎች አንዳንዶቹ እሱን በሚሰናበቱበት ጊዜ ዓይናቸው እንባ አቅርሮ ነበር። እስር ቤቱ ውስጥ የሚሠራ አንድ ወታደር እንዲህ ብሏል፦ “እዚህ ካሉት እስረኞች ሁሉ እንደ ጃክ ያለ መጥፎ ሰው አልነበረም። አሁን ግን ከሁሉም የተሻለ ሰው ሆኗል።” ጃክ ከተገደለ በኋላ፣ በቀጣዩ ሳምንት ወንድሞች በእስር ቤቱ ሳምንታዊ ስብሰባ ለማድረግ ሲሄዱ በስብሰባው ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘ አንድ እስረኛ ተመለከቱ። በስብሰባው ላይ እንዲገኝ ያነሳሳው ምንድን ነው? ጃክ ባደረገው ለውጥ በጣም ስለተገረመ ይሖዋን ለማገልገል ምን ማድረግ እንደሚያስፈልገው ማወቅ ፈልጎ ነበር። ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ምግባራችን ለሰማዩ አባታችን ክብር ያመጣል።—1 ጴጥ. 2:12

በምግባራችን ለይሖዋ ክብር መስጠት እንችላለን (አንቀጽ 14⁠ን ተመልከት) d


ይሖዋ በቅርቡ ስሙን የሚያስከብረው እንዴት ነው?

15. ይሖዋ በቅርቡ ስሙን ሙሉ በሙሉ የሚያስከብረው እንዴት ነው? (መዝሙር 96:10-13)

15 መዝሙር 96:10-13ን አንብብ። የመዝሙር 96 የመጨረሻ ቁጥሮች ይሖዋ ጻድቅ ፈራጅና ንጉሥ እንደሆነ ይገልጻሉ። ይሖዋ በቅርቡ ስሙን የሚያስከብረው እንዴት ነው? በሚያስተላልፋቸው ፍርዶች አማካኝነት ነው። በቅርቡ፣ በስሙ ላይ ነቀፋ ያመጣችውን ታላቂቱ ባቢሎንን ያጠፋታል። (ራእይ 17:5, 16፤ 19:1, 2) የታላቂቱ ባቢሎንን ጥፋት የተመለከቱ አንዳንድ ሰዎች አብረውን በእውነተኛው አምልኮ መካፈል ይጀምሩ ይሆናል። በመጨረሻም፣ ይሖዋ በአርማጌዶን መላውን የሰይጣን ሥርዓት ያጠፋዋል፤ እሱን የሚቃወሙትንና ስሙን የሚሰድቡትን ሁሉ ይደመስሳል። የሚወዱትን፣ የሚታዘዙትንና ለእሱ ክብር በመስጠታቸው የሚኮሩትን ደግሞ ያድናቸዋል። (ማር. 8:38፤ 2 ተሰ. 1:6-10) የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ሲያበቃ ከሚኖረው የመጨረሻ ፈተና በኋላ ይሖዋ ስሙን ሙሉ በሙሉ ያስቀድሳል። (ራእይ 20:7-10) በዚያ ጊዜ “ውኃ ባሕርን እንደሚሸፍን፣ ምድርም የይሖዋን ክብር በማወቅ ትሞላለች።”—ዕን. 2:14

16. ቁርጥ ውሳኔያችሁ ምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

16 በምድር ላይ ያለ ሰው ሁሉ ለስሙ የሚገባውን ክብር ለይሖዋ በሚሰጥበት ጊዜ መገኘት ምንኛ ያስደስታል! እስከዚያው ድረስ ግን፣ ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ ለአምላካችን ክብር በመስጠት የበኩላችንን ድርሻ መወጣት እንችላለን። የበላይ አካሉ ለዚህ ወሳኝ ጉዳይ ትኩረት እንድንሰጥ ለመርዳት ሲል መዝሙር 96:8 የ2025 የዓመት ጥቅስ እንዲሆን ወስኗል፦ “ለስሙ የሚገባውን ክብር ለይሖዋ ስጡ።”

በመጨረሻ በምድር ላይ ያለ ሰው ሁሉ ለስሙ የሚገባውን ክብር ለይሖዋ ይሰጣል (አንቀጽ 16⁠ን ተመልከት)

መዝሙር 12 ታላቁ አምላክ ይሖዋ

a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

b የሥዕሉ መግለጫ፦ የአንጀሊናን ተሞክሮ የሚያሳይ የትወና ፎቶግራፍ።

c የሥዕሉ መግለጫ፦ የፕሪስካን ተሞክሮ የሚያሳይ የትወና ፎቶግራፍ።

d የሥዕሉ መግለጫ፦ የጃክን ተሞክሮ የሚያሳይ የትወና ፎቶግራፍ።