በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 2

መዝሙር 132 አንድ ሆነናል

ባሎች፣ ሚስቶቻችሁን አክብሯቸው

ባሎች፣ ሚስቶቻችሁን አክብሯቸው

“እናንተ ባሎች . . . አክብሯቸው።”1 ጴጥ. 3:7

ዓላማ

ባሎች በቃልም ሆነ በተግባር ለሚስቶቻቸው አክብሮት ማሳየት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

1. ይሖዋ የትዳርን ዝግጅት ያቋቋመበት አንዱ ምክንያት ምንድን ነው?

 ይሖዋ ‘ደስተኛ አምላክ’ ነው፤ እኛም ደስተኞች እንድንሆን ይፈልጋል። (1 ጢሞ. 1:11) በሕይወታችን ደስተኛ እንድንሆን የሚያስችሉንን ብዙ ስጦታዎች ሰጥቶናል። (ያዕ. 1:17) ከእነዚህ ስጦታዎች አንዱ ትዳር ነው። አንድ ወንድና አንዲት ሴት ሲጋቡ አንዳቸው ሌላውን ለመውደድ፣ ለማክበርና ለመንከባከብ ቃል ይገባሉ። ፍቅራቸውን እያጠናከሩ መኖራቸው እውነተኛ ደስታ ያስገኝላቸዋል።—ምሳሌ 5:18

2. በዛሬው ጊዜ ብዙ ትዳሮች ያሉበት ሁኔታ ምን ይመስላል?

2 የሚያሳዝነው፣ በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ባለትዳሮች በሠርጋቸው ዕለት የገቡትን ቃል ይረሳሉ። በዚህም ምክንያት ደስታ ርቋቸዋል። የዓለም የጤና ድርጅት በቅርቡ ያወጣው ሪፖርት እንደሚናገረው፣ ብዙ ባሎች በሚስቶቻቸው ላይ አካላዊ ጥቃት ይሰነዝራሉ፤ የሚያቃልል ንግግር ይናገራሉ፤ እንዲሁም ስሜት የሚጎዳ ነገር ያደርጋሉ። እንዲህ ያለው ባል በሌሎች ሰዎች ፊት ሲሆን ሚስቱን በአክብሮት ሊይዛት ይችላል፤ ቤት ውስጥ ግን ይበድላታል። በተጨማሪም ብዙ ባሎች ፖርኖግራፊ የሚመለከቱ በመሆኑ ምክንያት ትዳራቸው ውጥረት ነግሦበታል።

3. አንዳንድ ባሎች ሚስታቸውን አክብሮት በጎደለው መንገድ የሚይዙት ለምን ሊሆን ይችላል?

3 አንዳንድ ባሎች ሚስታቸውን አክብሮት በጎደለው መንገድ የሚይዙት ለምን ሊሆን ይችላል? ግልፍተኛ የሆነ አባት ያሳደጋቸው በመሆኑ የተነሳ ሚስትን መበደል ምንም ችግር እንደሌለው ሊሰማቸው ይችላል። ሌሎች ደግሞ ያደጉበት ባሕል “እውነተኛ ወንድ” የበላይነቱን ለማሳየት ኃይል መጠቀም እንዳለበት እንዲያስቡ አድርጓቸው ሊሆን ይችላል። ሌሎች ወንዶች ቁጣቸውን ጨምሮ ስሜታቸውን መቆጣጠር እንዳለባቸው አልተማሩም። አንዳንድ ወንዶች ደግሞ አዘውትረው ፖርኖግራፊ በመመልከታቸው የተነሳ ለሴቶችም ሆነ ለፆታ ግንኙነት የተዛባ አመለካከት አዳብረዋል። ከዚህም በተጨማሪ፣ አንዳንድ ሪፖርቶች የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሁኔታውን እንዳባባሰው ይናገራሉ። ምክንያቱ ምንም ሆነ ምን፣ ባል ሚስቱን አክብሮት በጎደለው መንገድ መያዙ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም።

4. ክርስቲያን ባሎች ከምን መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል? ለምንስ?

4 ክርስቲያን ባሎች ለሴቶች ተገቢ ያልሆነ አመለካከት እንዳያዳብሩ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። a ለምን? አንዱ ምክንያት፣ የአንድ ሰው አስተሳሰብ ወደ ተግባር ሊያመራው የሚችል መሆኑ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም የነበሩትን ቅቡዓን ክርስቲያኖች “ይህ ሥርዓት እንዲቀርጻችሁ አትፍቀዱ” በማለት አስጠንቅቋቸዋል። (ሮም 12:1, 2) ጳውሎስ በሮም ለነበሩት ክርስቲያኖች ደብዳቤ በጻፈበት ወቅት ጉባኤው ከተቋቋመ ረዘም ያለ ጊዜ አልፎ ነበር። ሆኖም ጳውሎስ የተናገረው ሐሳብ፣ ጉባኤው ውስጥ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች የዓለም ልማድና አስተሳሰብ አሁንም ተጽዕኖ እያሳደረባቸው እንደነበር ይጠቁማል። አስተሳሰባቸውንና ባሕርያቸውን እንዲያስተካክሉ የመከራቸው ለዚህ ነው። ይህ ምክር ዛሬ ላሉ ክርስቲያን ባሎችም ይሠራል። የሚያሳዝነው፣ አንዳንድ ክርስቲያን ባሎች የዓለም አስተሳሰብ ተጽዕኖ ስላሳደረባቸው በሚስቶቻቸው ላይ ጥቃት እስከመሰንዘር ደርሰዋል። b ይሖዋ፣ ባሎች ሚስቶቻቸውን በምን መንገድ እንዲይዙ ይጠብቅባቸዋል? የጭብጡ ጥቅስ ለዚህ መልስ ይሰጠናል።

5. በ1 ጴጥሮስ 3:7 መሠረት ባሎች ሚስቶቻቸውን በምን መንገድ መያዝ ይኖርባቸዋል?

5 አንደኛ ጴጥሮስ 3:7ን አንብብ። ይሖዋ፣ ባሎች ሚስቶቻቸውን እንዲያከብሩ አዟቸዋል። ሚስቱን የሚያከብር ባል ደግነትና ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ይይዛታል። በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ አንድ ባል ሚስቱን በአክብሮት መያዝ የሚችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን። በመጀመሪያ ግን፣ ሚስትን በአክብሮት አለመያዝ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ እንመልከት።

ሚስታችሁን አክብሮት በጎደለው መንገድ ከመያዝ ተቆጠቡ

6. ይሖዋ በሚስታቸው ላይ አካላዊ ጥቃት ስለሚሰነዝሩ ባሎች ምን ይሰማዋል? (ቆላስይስ 3:19)

6 አካላዊ ጥቃት ከመሰንዘር ተቆጠቡ። ይሖዋ ዓመፀኞችን ይጠላል። (መዝ. 11:5) በሚስታቸው ላይ ጥቃት የሚሰነዝሩ ባሎችን በቀጥታ አውግዟል። (ሚል. 2:16፤ ቆላስይስ 3:19ን አንብብ።) የጭብጡ ጥቅስ በሆነው በ1 ጴጥሮስ 3:7 ላይ እንደተገለጸው፣ ባል ሚስቱን በአክብሮት የማይዝ ከሆነ ከይሖዋ ጋር ያለው ዝምድና ይበላሻል። ይሖዋ ጸሎቱን እንኳ ላይሰማው ይችላል።

7. በኤፌሶን 4:31, 32 መሠረት ባሎች ከምን ዓይነት ንግግር ሊቆጠቡ ይገባል? (“ተጨማሪ ማብራሪያ” የሚለውንም ተመልከት።)

7 ከመሳደብ ተቆጠቡ። አንዳንድ ባሎች ሚስታቸውን በቁጣና ስሜትን በሚጎዳ ቃል ይናገራሉ። ይሁንና ይሖዋ ‘ቁጣን፣ ንዴትን፣ ጩኸትንና ስድብን’ ይጠላል። c (ኤፌሶን 4:31, 32ን አንብብ።) እሱ ሁሉንም ነገር ይሰማል። አንድ ባል ሌላ ሰው በሌለበት ጊዜም እንኳ ሚስቱን የሚያነጋግርበትን መንገድ ይሖዋ በቁም ነገር ይመለከተዋል። ሚስቱን በአጉል ቃላት የሚያነጋግር ባል አደጋ ላይ የሚጥለው ትዳሩን ብቻ ሳይሆን ከአምላክ ጋር ያለውን ወዳጅነትም ጭምር ነው።—ያዕ. 1:26

8. ይሖዋ ለፖርኖግራፊ ምን ዓይነት አመለካከት አለው? ለምንስ?

8 ፖርኖግራፊ ከማየት ተቆጠቡ። ይሖዋ ለፖርኖግራፊ ምን ዓይነት አመለካከት አለው? ይጠላዋል። ስለዚህ አንድ ባል የብልግና ምስሎችን ሲመለከት ከይሖዋ ጋር ያለውን ወዳጅነት ከማበላሸቱም በተጨማሪ ሚስቱን ያዋርዳል። d ይሖዋ፣ ባሎች ለሚስቶቻቸው በተግባር ብቻ ሳይሆን በአስተሳሰብም ጭምር ታማኝ እንዲሆኑ ይጠብቅባቸዋል። ኢየሱስ እንደተናገረው፣ አንዲትን ሴት በፍትወት ስሜት የሚመለከት ሰው “በልቡ” ከእሷ ጋር አመንዝሯል። eማቴ. 5:28, 29

9. ይሖዋ፣ ባሎች በፆታ ግንኙነት ረገድ ከራስ ወዳድነት እንዲርቁ የሚጠብቅባቸው ለምንድን ነው?

9 በፆታ ግንኙነት ረገድ ሚስታችሁ የማትፈልገውን ነገር እንድታደርግ አታስገድዷት። አንዳንድ ባሎች በፆታ ግንኙነት ወቅት ሚስታቸው የማትፈልገውን ወይም ሕሊናዋ የማይፈቅድላትን ነገር እንድታደርግ ያስገድዳሉ። ይሖዋ እንዲህ ያለውን አሳቢነት የጎደለውና ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅበት ምግባር ይጠላል። ይሖዋ፣ አንድ ባል ሚስቱን እንዲወዳት፣ እንዲሳሳላትና ስሜቷን እንዲያከብርላት ይጠብቅበታል። (ኤፌ. 5:28, 29) ይሁንና አንድ ክርስቲያን ባል ሚስቱን በአክብሮት የማይዝና ፖርኖግራፊ የሚመለከት ከሆነስ? አስተሳሰቡንና ምግባሩን ማስተካከል የሚችለው እንዴት ነው?

ባሎች መጥፎ ልማዳቸውን ማሸነፍ የሚችሉት እንዴት ነው?

10. ባሎች ኢየሱስ ከተወው ምሳሌ ምን ትምህርት ያገኛሉ?

10 አንድ ባል አክብሮት በጎደለውና በሚያዋርድ መንገድ ሚስቱን መያዙን እንዲያቆም ምን ሊረዳው ይችላል? ኢየሱስን ለመምሰል ጥረት ማድረግ ይችላል። ኢየሱስ ባያገባም ደቀ መዛሙርቱን የያዘበት መንገድ ባሎች ሚስቶቻቸውን እንዴት ሊይዙ እንደሚገባ የሚያሳይ ግሩም ምሳሌ ይሆናል። (ኤፌ. 5:25) ለምሳሌ ኢየሱስ ሐዋርያቱን ከያዘበትና ካነጋገረበት መንገድ ባሎች ምን ትምህርት ሊያገኙ እንደሚችሉ እንመልከት።

11. ኢየሱስ ሐዋርያቱን የያዘው እንዴት ነው?

11 ኢየሱስ ሐዋርያቱን ደግነት በሚንጸባረቅበትና ክብራቸውን በሚጠብቅ መንገድ ይዟቸዋል። ክፉ ቃል ተናግሯቸው ወይም ጨቁኗቸው አያውቅም። ኢየሱስ ጌታቸው ቢሆንም እንኳ ኃይሉን ተጠቅሞ በእነሱ ላይ ያለውን ሥልጣን ለማሳየት አልሞከረም። ከዚህ ይልቅ በትሕትና አገልግሏቸዋል። (ዮሐ. 13:12-17) እንዲህ ብሏቸዋል፦ “[ከእኔ] ተማሩ፤ እኔ ገርና በልቤ ትሑት ነኝ፤ ለራሳችሁም እረፍት ታገኛላችሁ።” (ማቴ. 11:28-30) ኢየሱስ ገር እንደነበረ ልብ በሉ። አንድ ሰው ገር ነው ሲባል ደካማ ነው ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ራሱን ለመግዛት የሚያስችል ውስጣዊ ጥንካሬ አለው። የሚያበሳጭ ነገር ቢያጋጥመውም እንኳ ይረጋጋል፤ እንዲሁም ስሜቱን ይቆጣጠራል።

12. ኢየሱስ ሌሎችን የሚያነጋግረው እንዴት ነበር?

12 ኢየሱስ አንደበቱን የተጠቀመበት ሌሎችን ለማጽናናትና ለማበረታታት ነው። ተከታዮቹን ሻካራ ቃል አልተናገራቸውም። (ሉቃስ 8:47, 48) ተቃዋሚዎቹ በሰደቡትና ሊያበሳጩት በሞከሩ ጊዜም እንኳ “መልሶ አልተሳደበም።” (1 ጴጥ. 2:21-23) እንዲያውም ኢየሱስ በክፉ ቃል ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ዝም ለማለት የመረጠበት ጊዜ አለ። (ማቴ. 27:12-14) ይህ ለክርስቲያን ባሎች ግሩም ምሳሌ ይሆናቸዋል።

13. በማቴዎስ 19:4-6 ላይ እንደተገለጸው አንድ ባል ‘ከሚስቱ ጋር መጣበቅ’ የሚችለው እንዴት ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

13 ኢየሱስ፣ ባሎች ለሚስቶቻቸው ታማኝ መሆን እንዳለባቸው አስተምሯል። አባቱ፣ ባል ‘ከሚስቱ ጋር መጣበቅ’ እንዳለበት የተናገረውን ሐሳብ ጠቅሷል። (ማቴዎስ 19:4-6ን አንብብ።) በዚህ ጥቅስ ላይ “መጣበቅ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ግስ ቃል በቃል ሲተረጎም “በሙጫ መጣበቅ” የሚል ትርጉም ይሰጣል። በመሆኑም በባልና በሚስት መካከል ያለው የትዳር ጥምረት በሙጫ የተጣበቁ ያህል ጠንካራ ሊሆን ይገባል። ይህ ጥምረታቸው ከተበጠሰ በሁለቱም ላይ ጉዳት መከሰቱ አይቀርም። ከሚስቱ ጋር እንዲህ ዓይነት ጥምረት የመሠረተ ባል ከሁሉም ዓይነት ፖርኖግራፊ ይርቃል። “ከንቱ ነገር እንዳያዩ” ዓይኖቹን ወዲያውኑ ይመልሳል። (መዝ. 119:37) ከሚስቱ በስተቀር ማንኛዋንም ሴት በፆታ ስሜት ላለመመልከት ከዓይኑ ጋር ቃል ኪዳን ይገባል ሊባል ይችላል።—ኢዮብ 31:1

ታማኝ ባል ፖርኖግራፊ ለመመልከት ፈቃደኛ አይሆንም (አንቀጽ 13⁠ን ተመልከት) g


14. ሚስቱን የሚበድል ባል ከይሖዋም ሆነ ከሚስቱ ጋር ያለውን ዝምድና ለማስተካከል የትኞቹን እርምጃዎች መውሰድ አለበት?

14 በሚስቱ ላይ አካላዊ ጥቃት የሚሰነዝር ወይም የሚሳደብ ባል ከይሖዋም ሆነ ከሚስቱ ጋር ያለውን ዝምድና ለማስተካከል ተጨማሪ እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርበታል። እነዚህ እርምጃዎች የትኞቹ ናቸው? አንደኛ፣ ከባድ ችግር እንዳለበት አምኖ ይቀበላል። ከይሖዋ እይታ የተሰወረ ምንም ነገር የለም። (መዝ. 44:21፤ መክ. 12:14፤ ዕብ. 4:13) ሁለተኛ፣ ሚስቱን መበደሉን ይተዋል፤ እንዲሁም ባሕሪውን ያስተካክላል። (ምሳሌ 28:13) ሦስተኛ፣ ሚስቱን ይቅርታ ይጠይቃል፤ የይሖዋንም ምሕረት ይለምናል። (ሥራ 3:19) ከዚህም በተጨማሪ፣ ለውጥ ለማድረግ እንዲያነሳሳው እንዲሁም አስተሳሰቡን፣ ንግግሩንና ተግባሩን ለመቆጣጠር እንዲረዳው ይሖዋን ይለምናል። (መዝ. 51:10-12፤ 2 ቆሮ. 10:5፤ ፊልጵ. 2:13) አራተኛ፣ ለማንኛውም ዓይነት ዓመፅና ስድብ ጥላቻ ለማዳበር ጥረት በማድረግ ከጸሎቱ ጋር የሚስማማ እርምጃ ይወስዳል። (መዝ. 97:10) አምስተኛ፣ በጉባኤው ውስጥ ካሉ አፍቃሪ እረኞች እርዳታ ለማግኘት አፋጣኝ እርምጃ ይወስዳል። (ያዕ. 5:14-16) ስድስተኛ፣ ወደፊት እነዚህ ልማዶች እንዳያገረሹበት የሚረዳው ዕቅድ ያወጣል። ፖርኖግራፊ የሚመለከት ባልም እነዚህኑ እርምጃዎች መውሰድ አለበት። ባሕሪውን ለማስተካከል የሚያደርገውን ጥረት ይሖዋ ይባርክለታል። (መዝ. 37:5) ነገር ግን አንድ ባል አክብሮት የጎደለው ድርጊት ከመፈጸም መቆጠቡ ብቻ በቂ አይደለም። ሚስቱን በአክብሮት መያዝን መማርም አለበት። ይህን ማድረግ የሚችለው እንዴት ነው?

ሚስታችሁን በአክብሮት መያዝ የምትችሉት እንዴት ነው?

15. አንድ ባል ለሚስቱ ፍቅሩን መግለጽ የሚችለው እንዴት ነው?

15 ፍቅራችሁን ግለጹ። አስደሳች ትዳር ያላቸው አንዳንድ ባሎች፣ በየዕለቱ በሆነ መንገድ ለሚስታቸው ፍቅራቸውን ለመግለጽ ጥረት ያደርጋሉ። (1 ዮሐ. 3:18) አንድ ባል ትናንሽ በሚመስሉ ነገሮች እንኳ ለሚስቱ ያለውን ፍቅር ሊገልጽ ይችላል፤ ለምሳሌ እጇን ሊይዛት ወይም እቅፍ ሊያደርጋት ይችላል። የጽሑፍ መልእክት በመላክ “ናፍቀሽኛል” ወይም “ውሎ እንዴት ነው?” ሊላት ይችላል። አልፎ አልፎ ደግሞ ደብዳቤ በመጻፍ ምን ያህል እንደሚወዳት ሊገልጽላት ይችላል። አንድ ባል እነዚህን ነገሮች ሲያደርግ ለሚስቱ አክብሮት ያሳያል፤ እንዲሁም ትዳራቸውን ያጠናክራል።

16. አንድ ባል ለሚስቱ አድናቆቱን መግለጽ ያለበት ለምንድን ነው?

16 አድናቆታችሁን ግለጹ። ሚስቱን በአክብሮት የሚይዝ ባል አድናቆቱን ይገልጽላታል፤ እንዲሁም ያበረታታታል። ይህን ማድረግ የሚችልበት አንዱ መንገድ እሱን ለመደገፍ ስትል ለምታደርገው ነገር ሁሉ አስታውሶ ማመስገን ነው። (ቆላ. 3:15) አንድ ባል ሚስቱን ከልቡ ሲያሞግሳት ደስ ይላታል። ልቧ ይረጋጋል፤ እንዲሁም እንደምትወደድና እንደምትከበር ይሰማታል።—ምሳሌ 31:28

17. አንድ ባል ለሚስቱ አክብሮት ማሳየት የሚችለው እንዴት ነው?

17 ደግነት አሳዩ፤ ፍላጎቷንም አክብሩ። ሚስቱን የሚወድ ባል ትልቅ ቦታ ይሰጣታል፤ እንዲሁም ይሳሳላታል። ከይሖዋ ያገኛት ውድ ስጦታ እንደሆነች አድርጎ ይመለከታታል። (ምሳሌ 18:22፤ 31:10) ከፆታ ግንኙነት ጋር በተያያዙ ጉዳዮችም ጭምር በደግነትና በአክብሮት ይይዛታል። የማትፈልገውን፣ እንደሚያዋርዳት የሚሰማትን ወይም ሕሊናዋ የማይፈቅድላትን ፆታዊ ተግባር እንድትፈጽም አይጠይቃትም። f እሱም ራሱ ቢሆን በይሖዋ ፊት ንጹሕ ሕሊና ይዞ ለመኖር ጥረት ያደርጋል።—ሥራ 24:16

18. ባሎች ምን ቁርጥ ውሳኔ ሊያደርጉ ይገባል? (“ ባሎች ለሚስቶቻቸው አክብሮት ማሳየት የሚችሉባቸው አራት መንገዶች” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

18 ባሎች፣ በሁሉም የሕይወታችሁ ክፍሎች ሚስታችሁን በአክብሮት ለመያዝ የምታደርጉትን ጥረት ይሖዋ እንደሚመለከትና እንደሚያደንቅ እርግጠኞች መሆን ትችላላችሁ። አክብሮት ከጎደለው ድርጊት በመራቅ እንዲሁም ለሚስታችሁ ደግነትና ፍቅር በማሳየት እሷን በአክብሮት ለመያዝ ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ። እንዲህ ካደረጋችሁ ሚስታችሁን እንደምትወዷትና ከፍ አድርጋችሁ እንደምትመለከቷት ታሳያላችሁ። ሚስታችሁን በአክብሮት በመያዝ ከምንም ይበልጥ ትልቅ ዋጋ ያለውን ከይሖዋ ጋር ያላችሁን ዝምድና ከአደጋ መጠበቅ ትችላላችሁ።—መዝ. 25:14

መዝሙር 131 “አምላክ ያጣመረውን”

a ባሎች በጥር 2024 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ለሴቶች የይሖዋ ዓይነት አመለካከት አለህ?” የሚለውን ርዕስ ማንበባቸው ይጠቅማቸዋል።

b በቤት ውስጥ ጥቃት የሚፈጸምባቸው ሴቶች “ተጨማሪ ርዕሰ ጉዳዮች” በሚለው ዓምድ ሥር የወጣውን “የቤት ውስጥ ጥቃት ለሚደርስባቸው የሚሆን እርዳታ” የሚለውን ርዕስ ከ​jw.org ወይም ከ​JW ላይብረሪ ላይ ማንበብ ይችላሉ።

c ተጨማሪ ማብራሪያ፦ “ስድብ” የሚለው ቃል በሚያዋርዱና ሻካራ በሆኑ ቃላት መናገርንና የማያባራ ትችት መሰንዘርን ያካትታል። አንድ ሰው የሚናገረው ሌሎችን የሚያቃልል ነገር ሁሉ እንደ ስድብ ይቆጠራል።

dፖርኖግራፊ ትዳራችሁን ሊያናጋው ይችላል” የሚለውን ርዕስ jw.org ወይም JW ላይብረሪ ላይ ተመልከት።

e ፖርኖግራፊ የሚመለከት ባል ያላቸው ሚስቶች በነሐሴ 2023 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “የትዳር አጋርሽ ፖርኖግራፊ የሚመለከት ከሆነ” የሚለውን ርዕስ ማንበብ ይችላሉ።

f መጽሐፍ ቅዱስ ባልና ሚስት ከሚፈጽሙት የፆታ ግንኙነት ጋር በተያያዘ ንጹሕ ወይም ርኩስ የሆኑት ምግባሮች የትኞቹ እንደሆኑ አይዘረዝርም። ባለትዳር የሆኑ ክርስቲያኖች ይሖዋን ለማክበር፣ የትዳር አጋራቸውን ለማስደሰትና ንጹሕ ሕሊና ለመያዝ የሚያስችላቸውን ውሳኔ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ይህ በባለትዳሮቹ መካከል ያለ የግል ጉዳይ ስለሆነ በጥቅሉ ሲታይ ስለዚህ ጉዳይ ከሌሎች ጋር መነጋገር አያስፈልጋቸውም።

g የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድን ወንድም የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ የሥራ ባልደረቦቹ ፖርኖግራፊ የያዘ መጽሔት እንዲመለከት ሲጋብዙት።