በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 5

መዝሙር 108 የአምላክ ታማኝ ፍቅር

የይሖዋ ፍቅር የትኞቹን በረከቶች አስገኝቶልናል?

የይሖዋ ፍቅር የትኞቹን በረከቶች አስገኝቶልናል?

“ክርስቶስ ኢየሱስ ኃጢአተኞችን ለማዳን ወደ ዓለም መጣ።”1 ጢሞ. 1:15

ዓላማ

ቤዛው የትኞቹን ጥቅሞች እንደሚያስገኝልንና ለይሖዋ ያለንን አመስጋኝነት ማሳየት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

1. ይሖዋን ማስደሰት የምንችለው እንዴት ነው?

 ለአንድ ለምትወደው ሰው ውብና ጠቃሚ የሆነ ልዩ ስጦታ ሰጠኸው እንበል። ግለሰቡ ስጦታውን ሣጥን ውስጥ ቢያስቀምጠውና ከዚያ በኋላ ጨርሶ ባያስታውሰው ምን ይሰማሃል? እንደምታዝን የታወቀ ነው። በሌላ በኩል ግን ግለሰቡ ስጦታውን በሚገባ ሲጠቀምበትና አድናቆቱን ሲገልጽልህ እንደምትደሰት ጥያቄ የለውም። ነጥቡ ምንድን ነው? ይሖዋ ልጁን ሰጥቶናል። ለዚህ ውድ ስጦታና ቤዛውን በማዘጋጀት ላሳየን ፍቅር አመስጋኝነታችንን ስናሳይ ይሖዋ ምንኛ ይደሰት ይሆን!—ዮሐ. 3:16፤ ሮም 5:7, 8

2. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

2 ይሁንና ጊዜ እያለፈ ሲሄድ የቤዛውን ስጦታ አቅልለን መመልከት ልንጀምር እንችላለን። በምሳሌያዊ ሁኔታ የአምላክን ስጦታ ሣጥን ውስጥ እንዳስቀመጥነው ሊቆጠር ይችላል። ስጦታው ስለተሰጠን ደስተኞች ነን፤ ሆኖም ስጦታውን መለስ ብለን አናየውም። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ እንዳያጋጥመን፣ አምላክና ክርስቶስ ላደረጉልን ነገር ያለንን አመስጋኝነት በየጊዜው ማደስ ይኖርብናል። ይህ ርዕስ እንዲህ ለማድረግ ይረዳናል። ቤዛው በአሁኑ ወቅትም ሆነ ወደፊት የትኞቹን ጥቅሞች እንደሚያስገኝልን እንመለከታለን። በተጨማሪም በተለይ በመታሰቢያው በዓል ሰሞን ለይሖዋ ፍቅር ያለንን አድናቆት መግለጽ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እናያለን።

በአሁኑ ጊዜ የምናገኘው ጥቅም

3. ቤዛው በአሁኑ ጊዜ የሚያስገኝልን አንዱ ጥቅም ምንድን ነው?

3 አሁንም እንኳ ከክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት እየተጠቀምን ነው። ለምሳሌ ቤዛውን መሠረት በማድረግ ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር ይለናል። ይሖዋ እኛን ይቅር የማለት ግዴታ የለበትም። ሆኖም ይቅር ሊለን ይፈልጋል። መዝሙራዊው በአመስጋኝነት መንፈስ ተነሳስቶ እንዲህ ሲል ዘምሯል፦ “ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ጥሩ ነህና፤ ይቅር ለማለትም ዝግጁ ነህ።”—መዝ. 86:5፤ 103:3, 10-13

4. ይሖዋ ቤዛውን ያዘጋጀው ለማን ነው? (ሉቃስ 5:32፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:15)

4 አንዳንዶች የይሖዋ ይቅርታ እንደማይገባቸው ይሰማቸው ይሆናል። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ማናችንም ብንሆን የይሖዋ ይቅርታ አይገባንም። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ሐዋርያ ተብሎ ሊጠራ እንደማይገባው’ ተገንዝቦ ነበር። ሆኖም “አሁን የሆንኩትን ለመሆን የበቃሁት በአምላክ ጸጋ ነው” ብሏል። (1 ቆሮ. 15:9, 10) ለኃጢአታችን ንስሐ ከገባን ይሖዋ ይቅር ይለናል። ለምን? ስለሚገባን ሳይሆን ስለሚወደን ነው። የዋጋ ቢስነት ስሜት የሚሰማህ ከሆነ ይሖዋ ቤዛውን ያዘጋጀው ኃጢአት ለሌለባቸው ሰዎች ሳይሆን ንስሐ ለገቡ ኃጢአተኞች መሆኑን አስታውስ።—ሉቃስ 5:32፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:15ን አንብብ።

5. ባከናወንነው አገልግሎት የተነሳ የይሖዋ ምሕረት እንደሚገባን ሊሰማን ይገባል? አብራራ።

5 በይሖዋ አገልግሎት ለበርካታ ዓመታት የተካፈልን ቢሆንም እንኳ ማናችንም ብንሆን የይሖዋ ምሕረት እንደሚገባን ሊሰማን አይገባም። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ያስመዘገብነውን የታማኝነት ታሪክ ከፍ አድርጎ ይመለከታል። (ዕብ. 6:10) ሆኖም ይሖዋ ልጁን የሰጠን ነፃ ስጦታ አድርጎ ነው እንጂ ላከናወንነው አገልግሎት ክፍያ አድርጎ አይደለም። ባከናወንነው አገልግሎት የተነሳ ምሕረት ወይም ለየት ያለ አስተያየት ሊደረግልን እንደሚገባ የሚሰማን ከሆነ ክርስቶስ የሞተው በከንቱ ነው እንደማለት ይሆንብናል።—ከገላትያ 2:21 ጋር አወዳድር።

6. ጳውሎስ በይሖዋ አገልግሎት በትጋት የሠራው ለምንድን ነው?

6 ጳውሎስ በራሱ ጥረት የአምላክን ሞገስ ማግኘት እንደማይችል ያውቅ ነበር። ታዲያ በይሖዋ አገልግሎት በትጋት የሠራው ለምንድን ነው? የይሖዋ ሞገስ የሚገባው ሰው ሆኖ ለመገኘት ሳይሆን ለይሖዋ ጸጋ ያለውን አድናቆት ለማሳየት ነው። (ኤፌ. 3:7) እንደ ጳውሎስ ሁሉ እኛም በቅንዓት የምናገለግለው የይሖዋ ምሕረት የሚገባን ሰዎች ሆነን ለመገኘት ሳይሆን ለይሖዋ ምሕረት ያለንን አድናቆት ለማሳየት ነው።

7. በአሁኑ ጊዜ ከቤዛው የምናገኘው ሌላው ጥቅም ምንድን ነው? (ሮም 5:1፤ ያዕቆብ 2:23)

7 በአሁኑ ጊዜ ከቤዛው የምናገኘው ሌላው ጥቅም ከይሖዋ ጋር በግለሰብ ደረጃ የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት መቻላችን ነው። a ባለፈው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው ስንወለድ ጀምሮ ከአምላክ ጋር ወዳጅነት አልነበረንም። ሆኖም በቤዛው የተነሳ ‘ከአምላክ ጋር ሰላማዊ’ ግንኙነት መመሥረትና ወደ እሱ መቅረብ እንችላለን።—ሮም 5:1፤ ያዕቆብ 2:23ን አንብብ።

8. ይሖዋ የጸሎት መብት ስለሰጠን አመስጋኞች መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

8 ከአምላክ ጋር ወዳጅነት መመሥረታችን የሚያስገኝልንን አንዱን ጥቅም ብቻ እንመልከት—የጸሎት መብት። ይሖዋ የሚያዳምጠው ሕዝቦቹ አንድ ላይ ተሰብስበው የሚያቀርቡትን ጸሎት ብቻ ሳይሆን እያንዳንዳችን በግለሰብ ደረጃ የምናቀርበውን ጸሎትም ጭምር ነው። ጸሎት የልብ መረጋጋትና የአእምሮ ሰላም ይሰጠናል፤ ሆኖም የጸሎት ጥቅም ይህ ብቻ አይደለም። ከአምላክ ጋር ያለንን ወዳጅነት ያጠናክርልናል። (መዝ. 65:2፤ ያዕ. 4:8፤ 1 ዮሐ. 5:14) ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ አዘውትሮ ይጸልይ የነበረው ይሖዋ እንደሚሰማው እንዲሁም መጸለዩ ከአባቱ ጋር ያለውን ወዳጅነት እንደሚያጠናክርለት እርግጠኛ ስለነበረ ነው። (ሉቃስ 5:16) የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት የይሖዋ ወዳጆች እንድንሆን፣ አልፎ ተርፎም እሱን በጸሎት እንድናነጋግረው ስላስቻለን ምንኛ አመስጋኞች ነን!

ወደፊት የምናገኘው ጥቅም

9. ቤዛው ወደፊት ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮችን የሚጠቅማቸው እንዴት ነው?

9 ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ወደፊት ከቤዛው ምን ጥቅም ያገኛሉ? ይሖዋ የዘላለም ሕይወት ይሰጣቸዋል። ብዙ ሰዎች ይህ የማይቻል ነገር እንደሆነ ይሰማቸዋል። ምክንያቱም ላለፉት በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታት ሞት የሰው ልጆች ታሪክ ክፍል ሆኖ ኖሯል። ሆኖም የይሖዋ የመጀመሪያ ዓላማ ሰዎች ለዘላለም እንዲኖሩ ነበር። አዳም ኃጢአት ባይሠራ ኖሮ ማንም ሰው ለዘላለም መኖር የማይቻል ነገር እንደሆነ አይሰማውም ነበር። ደግሞም በዛሬው ጊዜ የዘላለም ሕይወት የሕልም እንጀራ ቢመስልም እንኳ ይሖዋ ይህን አጋጣሚ እንድናገኝ ሲል ልጁን መሥዋዕት እስከማድረግ ድረስ ውድ ዋጋ ስለከፈለ መፈጸሙ እንደማይቀር እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ሮም 8:32

10. ቅቡዓንና ሌሎች በጎች የትኞቹን ተስፋዎች በጉጉት ይጠባበቃሉ?

10 የዘላለም ሕይወት ወደፊት የምናገኘው በረከት ቢሆንም ይሖዋ በአሁኑ ጊዜም ስለዚህ ተስፋ እንድናስብ ይፈልጋል። ቅቡዓኑ ሰማይ ሄደው ከክርስቶስ ጋር ምድርን የሚገዙበትን ጊዜ በጉጉት ይጠባበቃሉ። (ራእይ 20:6) ሌሎች በጎች ደግሞ ከሥቃይና ከሐዘን ተገላግለው ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ይጓጓሉ። (ራእይ 21:3, 4) በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ካላቸው ሌሎች በጎች አንዱ ነህ? ይህ ሁለተኛ ደረጃ ሽልማት አይደለም። የሰው ልጆች የተፈጠሩት በምድር ላይ እንዲኖሩ ነው። በምድር ላይ መኖር የተሟላ ደስታ ያስገኝልናል።

11-12. በገነት ውስጥ የትኞቹን በረከቶች እንደምናገኝ መጠበቅ እንችላለን? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

11 በገነት ውስጥ የሚኖርህ ሕይወት ምን እንደሚመስል ለማሰብ ሞክር። ብታመምስ ወይም ብሞትስ የሚል ስጋት አያድርብህም። (ኢሳ. 25:8፤ 33:24) ይሖዋ ተገቢ የሆኑ ምኞቶችህን በሙሉ ያረካልሃል። ያኔ ምን መማር ትፈልጋለህ? ፊዚክስ? ኬሚስትሪ? ሙዚቃ? ሥዕል? ያኔ የሥነ ሕንፃ፣ የግንባታና የግብርና ባለሙያዎች እንደሚያስፈልጉ ምንም ጥያቄ የለውም። ምግብ የሚያዘጋጁ፣ የተለያዩ መሣሪያዎችን የሚሠሩ እንዲሁም ውቡን መልክዓ ምድር የሚንከባከቡ ሰዎችም ያስፈልጋሉ። (ኢሳ. 35:1፤ 65:21) ለዘላለም ስለምትኖር የፈለግከውን ክህሎት ሁሉ የምታዳብርበት ጊዜ አለህ።

12 ከሞት የተነሱ ሰዎችን መቀበል ምን ያህል አስደሳች ሊሆን እንደሚችል ለማሰብ ሞክር። (ሥራ 24:15) ስፍር ቁጥር የሌላቸውን የፍጥረት ሥራዎች በመመርመር ስለ ይሖዋ ምን ያህል ትምህርት ልታገኝ እንደምትችልም አስብ። (መዝ. 104:24፤ ኢሳ. 11:9) ከሁሉ በላይ ግን፣ ከበደለኝነት ስሜት ሙሉ በሙሉ ነፃ ሆኖ ይሖዋን ማምለክ እንዴት ደስ ይላል! ‘በኃጢአት ለሚገኝ ጊዜያዊ ደስታ’ ብለህ እነዚህን በረከቶች ማጣት ትፈልጋለህ? (ዕብ. 11:25) በጭራሽ! ከእነዚህ በረከቶች አንጻር በአሁኑ ጊዜ የትኛውንም መሥዋዕት ብንከፍል አያስቆጭም። ደግሞም ገነት በሆነች ምድር ውስጥ መኖር ተስፋ ሆኖ እንደማይቀር ልብ በል። እውን ይሆናል። ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ ልጁን ባይሰጠን ኖሮ ይህን ሁሉ በረከት ልናገኝ አንችልም ነበር።

በገነት ውስጥ ለማግኘት የምትጓጓው የትኛውን በረከት ነው? (ከአንቀጽ 11-12⁠ን ተመልከት)


ለይሖዋ ፍቅር ያለህን አድናቆት ግለጽ

13. ለይሖዋ ፍቅር ያለንን አድናቆት መግለጽ የምንችለው እንዴት ነው? (2 ቆሮንቶስ 6:1)

13 ይሖዋ ቤዛውን ስላዘጋጀልን አድናቆታችንን መግለጽ የምንችለው እንዴት ነው? በሕይወታችን ውስጥ ለእሱ ሥራ ቅድሚያ በመስጠት ነው። (ማቴ. 6:33) ደግሞም ኢየሱስ የሞተው “በሕይወት ያሉትም ከእንግዲህ ለራሳቸው ከመኖር ይልቅ ለእነሱ ለሞተውና ለተነሳው እንዲኖሩ” ነው። (2 ቆሮ. 5:15) የይሖዋን ጸጋ ከተቀበልን በኋላ ዓላማውን መሳት እንደማንፈልግ ምንም ጥያቄ የለውም።—2 ቆሮንቶስ 6:1ን አንብብ።

14. በይሖዋ መመሪያ ላይ መተማመን የምንችለው እንዴት ነው?

14 ለይሖዋ ፍቅር ያለንን አድናቆት መግለጽ የምንችልበት ሌላው መንገድ እሱ በሚሰጠን መመሪያ ላይ መተማመን ነው። እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ውሳኔዎችን በምናደርግበት ጊዜ፣ ለምሳሌ ምን ዓይነት ትምህርት እንደምንከታተል ወይም ምን ዓይነት ሥራ እንደምንይዝ ስንወስን ይሖዋን የሚያስደስተው ውሳኔ የትኛው እንደሆነ ማሰብ ይኖርብናል። (1 ቆሮ. 10:31፤ 2 ቆሮ. 5:7) እምነታችንን በተግባር ስናሳይ በይሖዋ ላይ ያለን እምነትና ከእሱ ጋር ያለን ወዳጅነት ይበልጥ ይጠናከራል። ተስፋችንም ይበልጥ አስተማማኝ ይሆንልናል።—ሮም 5:3-5፤ ያዕ. 2:21, 22

15. በመታሰቢያው በዓል ሰሞን ለይሖዋ ፍቅር ያለንን አድናቆት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

15 ለይሖዋ ፍቅር ያለንን አድናቆት ማሳየት የምንችልበት ሌላም መንገድ አለ። እሱም በመታሰቢያው በዓል ሰሞን ለቤዛው ያለንን አመስጋኝነት ለይሖዋ በማሳየት ነው። እኛ ራሳችን በመታሰቢያው በዓል ላይ ከመገኘት ባለፈ ሌሎችም እንዲገኙ ልንጋብዝ እንችላለን። (1 ጢሞ. 2:4) ለምትጋብዛቸው ሰዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ ምን እንደሚከናወን ንገራቸው። ኢየሱስ የሞተው ለምንድን ነው? እና የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ የተባሉትን ቪዲዮዎች ከ​jw.org ላይ ልታሳያቸው ትችላለህ። ሽማግሌዎች የቀዘቀዙ ክርስቲያኖችን ለመጋበዝ ለየት ያለ ጥረት ሊያደርጉ ይገባል። ከጠፉ የይሖዋ በጎች መካከል አንዳንዶቹ ወደ መንጋው ለመመለስ ቢነሳሱ በሰማይም ሆነ በምድር ምን ያህል ደስታ እንደሚኖር ለማሰብ ሞክር። (ሉቃስ 15:4-7) በመታሰቢያው በዓል ላይ እርስ በርስ ሰላም ከመባባል በተጨማሪ አዲሶችንና ለረጅም ጊዜ በበዓሉ ላይ ያልተገኙ ሰዎችን ሰላም ለማለት ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ጥሩ አቀባበል ልናደርግላቸው እንፈልጋለን።—ሮም 12:13

16. በመታሰቢያው በዓል ሰሞን አገልግሎታችንን ማስፋታችን ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

16 በመታሰቢያው በዓል ሰሞን መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችህን ማሳደግ ትችል ይሆን? እንዲህ ማድረግ አምላክና ክርስቶስ ላደረጉልን ነገር አድናቆታችንን መግለጽ የምንችልበት ግሩም መንገድ ነው። በይሖዋ አገልግሎት ይበልጥ በተካፈልን መጠን የእሱን ድጋፍ ይበልጥ እናጣጥማለን፤ በውጤቱም በእሱ ላይ ያለን እምነት ይበልጥ ይጠናከራል። (1 ቆሮ. 3:9) ከዚህም ሌላ ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር በተባለው ቡክሌትና በክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን የስብሰባ አስተዋጽኦ ላይ የሚገኘውን ፕሮግራም ተከትለህ የመታሰቢያውን በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ አንብብ። እንዲያውም በምታነበው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ የተመሠረተ የጥናት ፕሮጀክት ማካሄድ ትችላለህ።

17. ይሖዋን የሚያስደስተው ምንድን ነው? (“ ለይሖዋ ፍቅር አድናቆታችንን መግለጽ የምንችልባቸው መንገዶች” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

17 እርግጥ ነው፣ በዚህ ርዕስ ላይ የተጠቀሱትን ሐሳቦች በሙሉ በሥራ ላይ ለማዋል ሁኔታህ ላይፈቅድልህ ይችላል። ይሁንና ይሖዋ የምታከናውነውን ነገር ከሌሎች ጋር እንደማያወዳድር አስታውስ፤ እሱ የሚያየው ልብህን ነው። ለሰጠህ ውድ ስጦታ ማለትም ለቤዛው ያለህን ልባዊ አመስጋኝነት ሲመለከት ይደሰታል።—1 ሳሙ. 16:7፤ ማር. 12:41-44

18. ይሖዋ አምላክንና ኢየሱስ ክርስቶስን ለማመስገን የሚያነሳሳን ምንድን ነው?

18 ለኃጢአታችን ይቅርታ ማግኘት፣ ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት መመሥረት እንዲሁም የዘላለም ሕይወት ተስፋ ማግኘት የቻልነው ቤዛው ስለተከፈለልን ብቻ ነው። ይሖዋ እነዚህን በረከቶች የምናገኝበትን አጋጣሚ በመክፈት ላሳየን ፍቅር ምንጊዜም አመስጋኝነታችንን እናሳይ። (1 ዮሐ. 4:19) በተጨማሪም ሰብዓዊ ሕይወቱን እስኪሰጠን ድረስ እጅግ ለወደደን ለኢየሱስ ያለንን አድናቆት እናሳይ።—ዮሐ. 15:13

መዝሙር 154 ፍቅር ለዘላለም ይኖራል

a ይሖዋ ከክርስትና ዘመን በፊት የነበሩትን አገልጋዮቹን ገና ቤዛው ባይከፈልም እንኳ ኃጢአታቸውን ይቅር ብሎላቸዋል። ይሖዋ ይህን ያደረገው ልጁ እስከ ሞት ድረስ ታማኝነቱን እንደሚጠብቅ እርግጠኛ ስለነበረ ነው። በመሆኑም በአምላክ ዓይን ያኔም ቤዛው እንደተከፈለ ሊቆጠር ይችላል።—ሮም 3:25