በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውነትን ተናገሩ

እውነትን ተናገሩ

“እርስ በርሳችሁ እውነትን ተነጋገሩ።”—ዘካ. 8:16

መዝሙሮች፦ 56, 124

1, 2. በሰው ልጆች ላይ ከሁሉ የከፋ መዘዝ ያስከተለው ነገር ምንድን ነው? ለዚህስ ተጠያቂው ማን ነው?

እንደ ስልክ፣ መብራት፣ መኪናና ማቀዝቀዣ ያሉት የፈጠራ ውጤቶች የዕለት ተዕለት ሕይወታችንን ቀላል ካደረጉልን ግኝቶች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። በተቃራኒው ደግሞ እንደ ጠመንጃ፣ ፈንጂ፣ ሲጋራና አቶሚክ ቦምብ ያሉት የፈጠራ ውጤቶች ሕይወታችን ከበፊቱ ይበልጥ አስጊ ሁኔታ ላይ እንዲወድቅ አድርገዋል። ይሁንና ከእነዚህ ሁሉ በፊት የተፈጠረና በሰው ልጆች ሕይወት ላይ እጅግ አስከፊ መዘዝ ያስከተለ አንድ አዲስ ፈጠራ አለ። ይህ ምንድን ነው? ውሸት ነው! ውሸት ማለት አንድን ሰው ለማታለል ሲባል ሆን ተብሎ የሚነገር እውነት ያልሆነ ነገር ማለት ነው። ታዲያ የመጀመሪያውን ውሸት የፈለሰፈው ወይም የተናገረው ማን ነው? ኢየሱስ ክርስቶስ “የውሸት አባት” ዲያብሎስ እንደሆነ ተናግሯል። (ዮሐንስ 8:44ን አንብብ።) ዲያብሎስ የመጀመሪያውን ውሸት የተናገረው መቼ ነው?

2 ዲያብሎስ የመጀመሪያውን ውሸት የተናገረው በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት በኤደን ገነት ውስጥ ነው። የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ማለትም አዳምና ሔዋን ፈጣሪያቸው ባዘጋጀላቸው ገነት ውስጥ ተደስተው ይኖሩ ነበር። አምላክ እነዚህን ባልና ሚስት “ከመልካምና ክፉ እውቀት ዛፍ” እንዳይበሉ፣ ከበሉ ግን እንደሚሞቱ ነግሯቸው ነበር። ሰይጣን ይህን ትእዛዝ የሚያውቅ ቢሆንም በእባብ አማካኝነት ሔዋንን “መሞት እንኳ ፈጽሞ አትሞቱም” አላት፤ ይህ በጽንፈ ዓለም ውስጥ የተነገረው የመጀመሪያው ውሸት ነው። አክሎም “አምላክ ከዛፉ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንደሚገለጡና መልካምና ክፉን በማወቅ ረገድ እንደ አምላክ እንደምትሆኑ ስለሚያውቅ ነው” በማለት ነገራት።—ዘፍ. 2:15-17፤ 3:1-5

3. ሰይጣን የተናገረው ውሸት ከክፋት የመነጨ ነው የምንለው ለምንድን ነው? ይህ ውሸትስ ምን መዘዝ አስከትሏል?

3 ሰይጣን የተናገረው ውሸት ከክፋት የመነጨ ነበር፤ ምክንያቱም ሔዋን እሱ የተናገረውን ውሸት አምና ፍሬውን ከበላች መሞቷ እንደማይቀር ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። የሚያሳዝነው በመጀመሪያ ሔዋን በኋላም አዳም የይሖዋን ትእዛዝ የጣሱ ሲሆን ከጊዜ በኋላ ሕይወታቸውን አጥተዋል። (ዘፍ. 3:6፤ 5:5) ከዚህ የከፋው ደግሞ በእነሱ ኃጢአት ምክንያት “ሞት ለሰው ሁሉ [የተዳረሰ]” መሆኑ ነው። እንዲያውም “አዳም ትእዛዝ በመተላለፍ የሠራውን ዓይነት ኃጢአት ባልሠሩት ላይም እንኳ ሳይቀር” ሞት ነገሠ። (ሮም 5:12, 14) በመሆኑም የሰው ልጆች በአምላክ የመጀመሪያ ዓላማ መሠረት ፍጹም ሆነው ለዘላለም መኖር አልቻሉም፤ ከዚህ ይልቅ ‘የዕድሜያቸው ርዝማኔ 70 ዓመት፣ ለየት ያለ ጥንካሬ ካላቸው ደግሞ 80 ዓመት’ ገደማ ብቻ ሆነ። በዚያ ላይ ይህ አጭር ሕይወታቸው፣ አብዛኛውን ጊዜ “በችግርና በሐዘን የተሞላ ነው።” (መዝ. 90:10) ሰይጣን የተናገረው ውሸት ያስከተለው መዘዝ ምንኛ አስከፊ ነው!

4. (ሀ) የየትኞቹን ጥያቄዎች መልስ መመርመራችን ተገቢ ነው? (ለ) በመዝሙር 15:1, 2 መሠረት የይሖዋ ወዳጅ መሆን የሚችሉት ምን ዓይነት ሰዎች ብቻ ናቸው?

4 ኢየሱስ የዲያብሎስን ተግባር ሲገልጽ “በእሱ ዘንድ እውነት ስለሌለ በእውነት ውስጥ ጸንቶ አልቆመም” ብሏል። አሁንም ቢሆን በሰይጣን ዘንድ እውነት የለም፤ ምክንያቱም ዛሬም ‘መላውን ዓለም ማሳሳቱን’ ቀጥሏል። (ራእይ 12:9) እኛ ዲያብሎስ እንዲያሳስተን እንደማንፈልግ ግልጽ ነው። ስለዚህ የሚከተሉትን ሦስት ጥያቄዎች መመርመራችን ተገቢ ነው፦ ሰይጣን ሰዎችን እያሳሳተ ያለው እንዴት ነው? አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች የሚዋሹት ለምንድን ነው? እንዲሁም እንደ አዳምና ሔዋን ከይሖዋ ጋር ያለንን ወዳጅነት እንዳናጣ ምንጊዜም ‘እውነትን እንደምንናገር’ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?—መዝሙር 15:1, 2ን አንብብ።

ሰይጣን ሰዎችን እያሳሳተ ያለው እንዴት ነው?

5. በዛሬው ጊዜ ሰይጣን ሰዎችን እያሳሳተ ያለው እንዴት ነው?

5 ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ሰይጣን “የሚሸርበውን ተንኮል [ማወቃችን]” በእሱ ‘ከመታለል’ እንደሚጠብቀን ተገንዝቦ ነበር። (2 ቆሮ. 2:11 ግርጌ) የሐሰት ሃይማኖትን፣ ስግብግብነት የሚንጸባረቅበትን የንግዱን ዓለምና ምግባረ ብልሹ የሆነውን የፖለቲካ ሥርዓት ጨምሮ መላው ዓለም በዲያብሎስ ቁጥጥር ሥር እንደሆነ እናውቃለን። (1 ዮሐ. 5:19) በመሆኑም ሰይጣንና አጋንንቱ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ሰዎች ‘ውሸት እንዲናገሩ’ ተጽዕኖ የሚያሳድሩባቸው መሆኑ የሚያስገርም አይደለም። (1 ጢሞ. 4:1, 2) ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ትላልቅ የንግድ ተቋማትን የሚመሩ ሰዎች ጎጂ የሆኑ ምርቶቻቸውን ለመሸጥ ወይም ሰዎችን አታለው ገንዘብ ለማጋበስ የሐሰት ማስታወቂያዎችን ይጠቀማሉ።

6, 7. (ሀ) የሐሰት ትምህርቶችን የሚያስተምሩ የሃይማኖት መሪዎች ከሁሉ ይበልጥ ተጠያቂ ናቸው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) የሃይማኖት መሪዎች የትኞቹን ውሸቶች ሲያስተምሩ ሰምተሃል?

6 የሐሰት ትምህርቶችን የሚያስተምሩ የሃይማኖት መሪዎች ከሁሉ ይበልጥ ተጠያቂ ናቸው፤ ምክንያቱም እነሱ የሚያስተምሩትን ውሸት የሚያምኑ ሰዎች የዘላለም ሕይወት ተስፋቸው አደጋ ላይ ይወድቃል። አንድ ሰው በሐሰት ትምህርቶች ተታሎ አምላክ የሚጠላውን ነገር ቢያደርግ የዘላለም ሕይወት ተስፋውን ሊያጣ ይችላል። (ሆሴዕ 4:9) ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች በዚህ ረገድ ተጠያቂዎች እንደሆኑ ተገንዝቦ ነበር። በመሆኑም ፊት ለፊት እንዲህ ብሏቸዋል፦ “እናንተ ግብዞች ጸሐፍትና ፈሪሳውያን፣ አንድን ሰው ወደ ይሁዲነት ለመለወጥ በባሕርና በየብስ ስለምትጓዙና ሰውየው በተለወጠ ጊዜ ከእናንተ ይባስ ሁለት እጥፍ ለገሃነም [ለዘላለማዊ ጥፋት] የተገባ እንዲሆን ስለምታደርጉት ወዮላችሁ!” (ማቴ. 23:15) ኢየሱስ ጠንከር ያሉ ቃላትን ተጠቅሞ እነዚህን የሃይማኖት መሪዎች አውግዟቸዋል። በእርግጥም እነዚህ ሰዎች “ነፍሰ ገዳይ” ከሆነው ‘ከአባታቸው ከዲያብሎስ ናቸው።’—ዮሐ. 8:44

7 በዛሬው ጊዜ ፓስተር፣ ቄስና ረቢ ተብለው የሚጠሩትን ጨምሮ በርካታ የሃይማኖት መሪዎች አሉ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት የሃይማኖት መሪዎች ሁሉ እነዚህ የሃይማኖት መሪዎችም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ‘እውነት የሚያፍኑ’ ከመሆኑም ሌላ “የአምላክን እውነት በሐሰት [ይለውጣሉ]።” (ሮም 1:18, 25) ‘አንዴ የዳነ ለሁልጊዜው ድኗል፣’ ‘ነፍስ አትሞትም፣’ ‘የሞተ ሰው በሌላ አካል ተመልሶ ይወለዳል’ እንዲሁም ‘አምላክ ግብረ ሰዶማዊነትንና በተመሳሳይ ፆታ መካከል የሚደረገውን ጋብቻ አይቃወምም’ እንደሚሉት ያሉ የሐሰት ትምህርቶችን ያስተምራሉ።

8. በቅርቡ የፖለቲካ መሪዎች የትኛውን ውሸት እንደሚናገሩ እንጠብቃለን? በዚህ ወቅት የእኛ ምላሽ ምን ሊሆን ይገባል?

8 የፖለቲካ መሪዎችም ውሸት በመናገር ሰዎችን ያሳስታሉ። እነዚህ መሪዎች እስከዛሬ ከተናገሯቸው ውሸቶች ሁሉ የሚከፋው “ሰላምና ደህንነት ሆነ!” በማለት በቅርቡ የሚናገሩት አዋጅ ነው። ሆኖም ይህን አዋጅ ሲናገሩ “ያልታሰበ ጥፋት ድንገት ይመጣባቸዋል።” የፖለቲካ መሪዎች ይህ ሥርዓት በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ እንዳለ ለማስመሰል በሚያደርጉት ጥረት እንዳንታለል እንጠቀቅ! እንደ እውነቱ ከሆነ “የይሖዋ ቀን የሚመጣው ሌባ በሌሊት በሚመጣበት መንገድ መሆኑን . . . በሚገባ [እናውቃለን]።”—1 ተሰ. 5:1-4

አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች የሚዋሹት ለምንድን ነው?

9, 10. (ሀ) አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች የሚዋሹት ለምንድን ነው? ይህስ ምን ውጤት አስከትሏል? (ለ) ከይሖዋ ጋር በተያያዘ ምን ነገር ማስታወስ ይኖርብናል?

9 አንድ አዲስ የፈጠራ ውጤት ተወዳጅነት እያገኘ ሲሄድ በብዛት መመረት ይጀምራል። ከውሸት ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በዛሬው ጊዜ ባለው ማኅበረሰብ ዘንድ ውሸት የተለመደ ነገር ሆኗል፤ ደግሞም ሌሎችን የሚያታልሉት ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ሰዎች ብቻ አይደሉም። ዩዲጂት ባተቻርጂ የተባለው ጸሐፊ “የምንዋሸው ለምንድን ነው?” በሚለው ጽሑፉ ላይ እንደገለጸው “ውሸት የሰው ልጆች ተፈጥሯዊ ባሕርይ እንደሆነ ተደርጎ መታየት ጀምሯል።” አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች የሚዋሹት ከቅጣት ለማምለጥ አሊያም በሌሎች ዘንድ ጥሩ ግምት ለማትረፍ ሲሉ ነው። በተጨማሪም የሠሩትን ስህተትና የፈጸሙትን መጥፎ ድርጊት ለመሸፋፈን ወይም የገንዘብም ሆነ ሌላ ዓይነት ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ይዋሻሉ። ጽሑፉ እንደሚናገረው አንዳንዶች “ለሚያውቋቸው ሰዎች፣ ለሥራ ባልደረቦቻቸው፣ ለጓደኞቻቸው ወይም ለሚወዷቸው ሰዎች ምንም ሳይመስላቸው ቀላልም ሆነ ከባድ በሆኑ ጉዳዮች ይዋሻሉ።”

10 ይህ ሁሉ ውሸት ምን ውጤት አስከትሏል? አለመተማመን እንዲሰፍንና በሰዎች መካከል ያለው ግንኙነት እንዲበላሽ አድርጓል። ለምሳሌ አንድ ታማኝ ባል፣ ሚስቱ በእሱ ላይ እንዳመነዘረችና ይህን ድርጊቷን ለመሸፋፈን ስትል እንደዋሸች ቢያውቅ ምን ያህል ቅስሙ ሊሰበር እንደሚችል አስበው። አሊያም ደግሞ አንድ የቤተሰብ ራስ፣ ቤት ውስጥ ሚስቱንና ልጆቹን እየበደለ ሰው ፊት ሲሆን ግን አፍቃሪ መስሎ ለመታየት መሞከሩ ምንኛ የሚያሳዝን ነው። ሆኖም እንዲህ ያሉት አታላይ ሰዎች ከይሖዋ ምንም ነገር መደበቅ እንደማይችሉ ማስታወስ ይኖርብናል፤ ምክንያቱም “በእሱ ዓይኖች ፊት ሁሉም ነገር የተራቆተና ገሃድ የወጣ ነው።”—ዕብ. 4:13

11. ከሐናንያና ከሰጲራ መጥፎ ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

11 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሰይጣን አምላክን እንዲዋሹ ‘ስላደፋፈራቸው’ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩ አንድ ክርስቲያን ባልና ሚስት ይናገራል። ሐናንያና ሰጲራ የተባሉት እነዚህ ባልና ሚስት ሐዋርያትን ለማታለል ሞክረው ነበር። መሬት ከሸጡ በኋላ፣ ካገኙት ገንዘብ ላይ የተወሰነውን ብቻ ወደ ሐዋርያት ይዘው ሄዱ። ባልና ሚስቱ፣ ከሆኑት በላይ ለጋስ መስለው በመታየት በጉባኤው ዘንድ ለየት ያለ ክብር ማግኘት ፈልገው ነበር። ሆኖም ይሖዋ ድርጊታቸውን የተመለከተ ሲሆን ለዚህም ተገቢውን ቅጣት እንዲቀበሉ አድርጓል።—ሥራ 5:1-10

12. ከክፋት የመነጨ ውሸት የሚዋሹና ንስሐ የማይገቡ ሰዎች ምን ይጠብቃቸዋል? ለምንስ?

12 ይሖዋ ለውሸት ምን አመለካከት አለው? ሰይጣንም ሆነ የእሱን አርዓያ በመከተል ከክፋት የመነጨ ውሸት የሚዋሹና ንስሐ የማይገቡ ሰዎች የሚጠብቃቸው ወደ ‘እሳት ሐይቅ’ መወርወር ነው። (ራእይ 20:10፤ 21:8፤ መዝ. 5:6) ለምን? ምክንያቱም ይሖዋ እንዲህ ያሉ ውሸታሞችን የሚመለከታቸው “በአምላክ ዓይን አስጸያፊ ድርጊቶችን [ከሚፈጽሙ] ሰዎች” ጋር አንድ አድርጎ ነው።—ራእይ 22:15 ግርጌ

13. ስለ ይሖዋ ምን የምናውቀው ነገር አለ? ይህን ማወቃችንስ ምን እንድናደርግ ያነሳሳናል?

13 ይሖዋ “እንደ ሰው [እንደማይዋሽ]” እናውቃለን። እንዲያውም ‘አምላክ ሊዋሽ አይችልም።’ (ዘኁ. 23:19፤ ዕብ. 6:18) ይሖዋ ‘ውሸታም ምላስን ይጠላል።’ (ምሳሌ 6:16, 17) የእሱን ሞገስ ማግኘት ከፈለግን ምንጊዜም እውነት መናገር ይኖርብናል። በመሆኑም ‘አንዳችን ሌላውን አንዋሽም።’—ቆላ. 3:9

‘እርስ በርሳችን እውነትን እንነጋገራለን’

14. (ሀ) ከሐሰት ሃይማኖት ተከታዮች የተለየን እንድንሆን የሚያደርገን ምንድን ነው? (ለ) በሉቃስ 6:45 ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት አብራራ።

14 እውነተኛ ክርስቲያኖች ከሐሰት ሃይማኖት ተከታዮች የሚለዩበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው? ‘እርስ በርሳቸው እውነትን መነጋገራቸው’ ነው። (ዘካርያስ 8:16, 17ን አንብብ።) ጳውሎስ እንደተናገረው “ራሳችንን ብቁ የአምላክ አገልጋዮች አድርገን እናቀርባለን፤ ይህን የምናደርገው . . . እውነት የሆነውን በመናገር” ነው። (2 ቆሮ. 6:4, 7) ኢየሱስ ‘አንደበት የሚናገረው በልብ ውስጥ የሞላውን ነው’ ብሏል። (ሉቃስ 6:45) በአንድ ሰው ልብ ውስጥ የሞላው እውነት ከሆነ በአንደበቱ የሚናገረውም እውነት ይሆናል። ለማያውቃቸው ሰዎች፣ ለሥራ ባልደረቦቹ፣ ለጓደኞቹ ወይም ለሚወዳቸው ሰዎች ቀላልም ሆነ ከባድ በሆኑ ጉዳዮች እውነቱን ይናገራል። እስቲ በሁሉም ነገር ሐቀኛ መሆናችንን ማሳየት የምንችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች እንመልከት።

በዚህች ወጣት እህት ሕይወት ላይ የሚታየውን ችግር አስተውለሃል? (አንቀጽ 15, 16⁠ን ተመልከት)

15. (ሀ) ሁለት ዓይነት ሕይወት መምራት የጥበብ አካሄድ ያልሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ወጣቶች የእኩዮቻቸውን መጥፎ ተጽዕኖ ለመቋቋም ምን ሊረዳቸው ይችላል? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

15 በእኩዮችህ ዘንድ ተቀባይነት የማግኘት ጉዳይ የሚያሳስብህ ወጣት ነህ? እንግዲያው አንዳንድ ወጣቶች እንደሚያደርጉት ሁለት ዓይነት ሕይወት እንዳትመራ ተጠንቀቅ። እነዚህ ወጣቶች ከቤተሰባቸው ወይም ከጉባኤው አባላት ጋር ሲሆኑ ንጹሕ ሥነ ምግባር ያላቸው መስለው ለመታየት ይሞክራሉ፤ ዓለማዊ ከሆኑ እኩዮቻቸው ጋር ሲሆኑ አሊያም ማኅበራዊ ድረ ገፆችን ሲጠቀሙ ግን ፈጽሞ የተለየ ሰው ይሆናሉ። ጸያፍ ቃላትን ሊጠቀሙ፣ ልከኝነት የጎደለው ልብስ ሊለብሱ፣ ወራዳ ሙዚቃዎችን ሊያዳምጡ፣ የአልኮል መጠጦችን ወይም ዕፆችን አላግባብ ሊወስዱ፣ በሚስጥር የፍቅር ጓደኝነት ሊጀምሩ ወይም ከዚህ የከፉ ነገሮችን ሊያደርጉ ይችላሉ። እነዚህ ወጣቶች ሕይወታቸው በሙሉ በውሸት የተሞላ ነው፤ ወላጆቻቸውን፣ የእምነት ባልንጀሮቻቸውንና አምላክን እየዋሹ ነው። (መዝ. 26:4, 5) ይሖዋ ‘ልባችን ከእሱ እጅግ የራቀ ሆኖ’ በከንፈራችን ብቻ ስናከብረው ያውቃል። (ማር. 7:6) እንግዲያው “ልብህ በኃጢአተኞች አይቅና፤ ከዚህ ይልቅ ቀኑን ሙሉ ይሖዋን በመፍራት ተመላለስ” የሚለውን በምሳሌ መጽሐፍ ላይ የሚገኘውን ምክር መከተላችን ምንኛ የተሻለ ነው!—ምሳሌ 23:17 *

16. በልዩ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል ማመልከቻ በምንሞላበት ወቅት ሐቀኛ መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

16 ምናልባትም የዘወትር አቅኚ መሆን ወይም በአንድ ዓይነት ልዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፍ መካፈል ለምሳሌ ቤቴል ገብተህ ማገልገል ትፈልግ ይሆናል። ማመልከቻውን በምትሞላበት ወቅት ከጤንነትህ፣ ከመዝናኛ ምርጫህና ከሥነ ምግባር አቋምህ ጋር በተያያዘ ለቀረቡት ጥያቄዎች ትክክለኛና ሙሉ በሙሉ እውነት የሆነ መልስ መስጠትህ አስፈላጊ ነው። (ዕብ. 13:18) ለምሳሌ አንድ ዓይነት ርኩሰት ወይም አጠያያቂ ድርጊት ፈጽመህ ጉዳዩን ለሽማግሌዎች አልተናገርክ ይሆን? ከሆነ ንጹሕ ሕሊና ኖሮህ ማገልገል እንድትችል የሽማግሌዎችን እርዳታ ጠይቅ።—ሮም 9:1፤ ገላ. 6:1

17. ተቃዋሚዎች ስለ ወንድሞቻችን መረጃ እንድንሰጥ በሚጠይቁን ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

17 የምትኖረው ባለሥልጣናት በስብከቱ ሥራ ላይ እገዳ በጣሉበት አገር ውስጥ ቢሆንና ስለ ወንድሞችህ መረጃ እንድትሰጥ ብትጠየቅ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? የምታወቀውን ሁሉ መናገር አለብህ? ኢየሱስ የሮም አገረ ገዢ ጥያቄዎችን ባቀረበለት ወቅት ያደረገው ምንድን ነው? “ዝም ለማለት ጊዜ አለው፤ ለመናገርም ጊዜ አለው” ከሚለው መሠረታዊ ሥርዓት ጋር በሚስማማ መልኩ ለአንዳንዶቹ ጥያቄዎች ምንም መልስ ከመስጠት ተቆጥቧል! (መክ. 3:1, 7፤ ማቴ. 27:11-14) እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመን ወንድሞቻችንን አደጋ ላይ ላለመጣል አስተዋዮች መሆናችን አስፈላጊ ነው።—ምሳሌ 10:19፤ 11:12

ዝም ማለት አሊያም ሙሉውን እውነት መናገር ያለብህ መቼ እንደሆነ መወሰን የምትችለው እንዴት ነው? (አንቀጽ 17, 18⁠ን ተመልከት)

18. ሽማግሌዎች ስለ ወንድሞቻችን ጉዳይ በሚጠይቁን ጊዜ ምን የማድረግ ኃላፊነት አለብን?

18 የክርስቲያን ጉባኤ አባል የሆነ አንድ ሰው ከባድ ኃጢአት እንደፈጸመ ብታውቅ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? የጉባኤውን ሥነ ምግባራዊ ንጽሕና የመጠበቅ ኃላፊነት ያለባቸው ሽማግሌዎች ስለ ጉዳዩ የምታውቀውን ነገር ይጠይቁህ ይሆናል። በተለይ ጉዳዩ የቅርብ ጓደኛህን ወይም ዘመድህን የሚመለከት በሚሆንበት ጊዜ ምን ታደርጋለህ? “ታማኝ ምሥክር እውነቱን ይናገራል።” (ምሳሌ 12:17፤ 21:28) በመሆኑም ለሽማግሌዎች ከፊሉን ሳይሆን ሙሉውን እውነት የመናገር እንዲሁም ምንም ያልተዛባ መረጃ የመስጠት ኃላፊነት አለብህ። ደግሞም ሽማግሌዎች ስለ ጉዳዩ የተሟላ መረጃ የማግኘት መብት አላቸው፤ ምክንያቱም ኃጢአት የፈጸመው ግለሰብ ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና እንዲያድስ ሊረዱት የሚችሉት ሙሉ መረጃ ሲኖራቸው ብቻ ነው።—ያዕ. 5:14, 15

19. በቀጣዩ ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

19 መዝሙራዊው ዳዊት “ከልብ የመነጨ እውነት ደስ ያሰኝሃል” በማለት ወደ ይሖዋ ጸልዮአል። (መዝ. 51:6) ዳዊት ሐቀኝነት የሚመነጨው ከልብ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። እውነተኛ ክርስቲያኖች በሁሉም የሕይወታቸው ዘርፍ ‘እርስ በርሳቸው እውነትን ይነጋገራሉ።’ የአምላክ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን የተለየን መሆናችንን ማሳየት የምንችልበት ሌላው መንገድ በአገልግሎታችን ለሰዎች እውነትን ማስተማር ነው። ቀጣዩ ርዕስ እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያብራራል።

^ አን.15 ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2 በተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 15 ላይ የሚገኘውን “የእኩዮቼን ተጽዕኖ መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስና ምዕራፍ 16 ላይ የሚገኘውን “ሁለት ዓይነት ሕይወት—መናገር ያለብኝ ለምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።