በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እየመራን ባለው በክርስቶስ ላይ እምነት ይኑራችሁ

እየመራን ባለው በክርስቶስ ላይ እምነት ይኑራችሁ

“መሪያችሁ አንድ እሱም ክርስቶስ [ነው]።”—ማቴ. 23:10

መዝሙሮች፦ 16, 14

1, 2. ሙሴ ከሞተ በኋላ ኢያሱ ምን ተፈታታኝ ሁኔታ አጋጥሞታል?

ይሖዋ የተናገራቸው ቃላት አሁንም በኢያሱ ጆሮ ላይ እያቃጨሉ ነው፤ ይሖዋ እንዲህ ብሎት ነበር፦ “አገልጋዬ ሙሴ ሞቷል። እንግዲህ አንተም ሆንክ ይህ ሕዝብ ተነስታችሁ ዮርዳኖስን በመሻገር ለእስራኤላውያን ወደምሰጣቸው ምድር ግቡ።” (ኢያሱ 1:1, 2) ወደ 40 ለሚጠጉ ዓመታት የሙሴ አገልጋይ ለነበረው ለኢያሱ ይህ ፈጽሞ ያልተጠበቀ ለውጥ ነበር!

2 ለረጅም ጊዜ እስራኤልን ሲመራ የቆየው ሙሴ ስለነበር ኢያሱ ‘የአምላክ ሕዝቦች እኔን እንደ መሪያቸው አድርገው ይቀበሉኝ ይሆን?’ የሚለው ጉዳይ አሳስቦት ሊሆን ይችላል። (ዘዳ. 34:8, 10-12) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ማመሣከሪያ ጽሑፍ ኢያሱ 1:1, 2⁠ን አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ጥንትም ሆነ ዛሬ፣ ለአንድ አገር ደህንነት እጅግ አስጊ ከሆኑት ወቅቶች መካከል አንዱ የሥልጣን ሽግግር የሚደረግበት ጊዜ ነው።”

3, 4. ይሖዋ ኢያሱን ላሳየው እምነት የባረከው እንዴት ነው? ራሳችንን ምን ብለን ልንጠይቅ እንችላለን?

3 ኢያሱ እንዲፈራ የሚያደርገው በቂ ምክንያት የነበረው ቢሆንም በጥቂት ቀናት ውስጥ ቆራጥ እርምጃ ወስዷል። (ኢያሱ 1:9-11) ኢያሱ በአምላክ የታመነ ሲሆን አምላክም አላሳፈረውም። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሰፈረው ዘገባ እንደሚያሳየው ይሖዋ ኢያሱንና ሕዝቡ የሆኑትን እስራኤላውያንን ወኪሉ በሆነ መልአክ አማካኝነት መርቷቸዋል። ይህ መልአክ “ቃል” ተብሎ የተጠራው የአምላክ የበኩር ልጅ ነው ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ነው።—ዘፀ. 23:20-23፤ ዮሐ. 1:1

4 እስራኤላውያን ከሙሴ አመራር ወደ ኢያሱ አመራር በተሸጋገሩበት ወቅት የነበረውን ለውጥ በይሖዋ እርዳታ በተሳካ ሁኔታ ማለፍ ችለዋል። እኛም የምንኖረው ታሪካዊ ለውጦች በሚደረጉበት ዘመን ላይ ነው፤ የአምላክ ድርጅት በፍጥነት ወደፊት እየገሰገሰ ነው። በመሆኑም ‘መሪያችን ሆኖ በተሾመው በኢየሱስ ላይ እምነት ለመጣል የሚያስችል በቂ ምክንያት አለን?’ ብለን መጠየቃችን ተገቢ ነው። (ማቴዎስ 23:10ን አንብብ።) እስቲ ይሖዋ በጥንት ዘመን የነበሩ ሕዝቦቹ ለውጥ ባጋጠማቸው ጊዜ አስተማማኝ በሆነ መንገድ የመራቸው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።

የአምላክን ሕዝቦች ወደ ከነአን መርቶ ማስገባት

5. ኢያሱ በኢያሪኮ አቅራቢያ ሳለ ምን አጋጠመው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

5 እስራኤላውያን ዮርዳኖስን ከተሻገሩ ብዙም ሳይቆይ ኢያሱ አንድ ያልተጠበቀ ነገር አጋጠመው። በኢያሪኮ አቅራቢያ ሳለ የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ የያዘ አንድ ሰው ፊት ለፊቱ ቆሞ አየ። ኢያሱ ይህ ሰው ማን እንደሆነ ስላላወቀ “ከእኛ ወገን ነህ ወይስ ከጠላቶቻችን?” ብሎ ጠየቀው። ሰውየው የሰጠው ምላሽ ኢያሱን አስገርሞት መሆን አለበት። ይህ ሰው ለአምላክ ሕዝቦች ጥበቃ የሚያደርገው “የይሖዋ ሠራዊት አለቃ” ነው። (ኢያሱ 5:13-15ን አንብብ።) ሌሎች ቦታዎች ላይ ይሖዋ ኢያሱን እንዳነጋገረው የሚገልጹ ዘገባዎች ቢኖሩም ይሖዋ ኢያሱን ያነጋገረው በቀጥታ ሳይሆን ወኪሉ በሆነው መልአክ አማካኝነት እንደሆነ ጥርጥር የለውም፤ ደግሞም ይሖዋ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ሕዝቡን በዚህ መንገድ አነጋግሯል።—ዘፀ. 3:2-4፤ ኢያሱ 4:1, 15፤ 5:2, 9፤ ሥራ 7:38፤ ገላ. 3:19

6-8. (ሀ) ይሖዋ ከሰጣቸው መመሪያዎች መካከል አንዳንዶቹ ከሰው አመለካከት አንጻር ሲታዩ ግራ ሊያጋቡ የሚችሉት ለምንድን ነው? (ለ) መመሪያዎቹ ጥበብ የሚንጸባረቅባቸውና በትክክለኛው ጊዜ ላይ የተሰጡ ናቸው የምንለው ለምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

6 መሪ ሆኖ የተሾመው መልአክ የኢያሪኮ ከተማን ድል ማድረግ ስለሚቻልበት መንገድ ለኢያሱ ግልጽ መመሪያዎች ሰጠው። መልአኩ ከሰጠው መመሪያዎች መካከል አንዳንዶቹ መጀመሪያ ላይ ውጤታማ አይመስሉም ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ ሁሉም ወንዶች እንዲገረዙ ትእዛዝ የሰጠ ሲሆን ይህም ወንዶቹ ለተወሰኑ ቀናት መንቀሳቀስ እንዳይችሉ የሚያደርግ ነበር። ለውጊያ ብቁ የሆኑት ወንዶች በዚህ ወቅት እንዲገረዙ ማድረግ በእርግጥ ጥበብ ነው?—ዘፍ. 34:24, 25፤ ኢያሱ 5:2, 8

7 ራሳቸውን መከላከል የማይችሉት እነዚህ የእስራኤል ወታደሮች ጠላት በሰፈራቸው ላይ ጥቃት ቢሰነዝር ቤተሰባቸውን ማዳን የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ሳያሳስባቸው አይቀርም። ሆኖም አንድ ያልተጠበቀ ነገር ተከሰተ! ኢያሪኮ “በእስራኤላውያን የተነሳ ጥርቅም ተደርጋ [እንደተዘጋች]” የሚገልጽ ወሬ ተሰማ። (ኢያሱ 6:1) ይህ ያልተጠበቀ ሁኔታ እስራኤላውያን በአምላክ አመራር ላይ ያላቸውን እምነት ምንኛ አጠናክሮት ይሆን!

8 በተጨማሪም እስራኤላውያን በኢያሪኮ ላይ ጥቃት እንዳይሰነዝሩ ከዚህ ይልቅ ለስድስት ቀን ከተማዋን በቀን አንድ ጊዜ፣ በሰባተኛው ቀን ላይ ደግሞ ሰባት ጊዜ እንዲዞሯት ትእዛዝ ተሰጣቸው። አንዳንድ ወታደሮች ‘ለምን ጊዜያችንንና ጉልበታችንን ዝም ብለን እናባክናለን?’ ብለው አስበው ሊሆን ይችላል። በዓይን የማይታየው የእስራኤል መሪ ማለትም ይሖዋ ግን የሚያደርገውን ነገር ያውቅ ነበር። የእሱን መመሪያ መከተላቸው የእስራኤላውያንን እምነት ያጠናከረላቸው ከመሆኑም ሌላ ከኢያሪኮ ኃያል ተዋጊዎች ጋር ፊት ለፊት ከመጋፈጥ አድኗቸዋል።—ኢያሱ 6:2-5፤ ዕብ. 11:30 *

9. የአምላክ ድርጅት የሚሰጠንን መመሪያ መከተል ያለብን ለምንድን ነው? ምሳሌ ስጥ።

9 ከዚህ ዘገባ ምን ትምህርት እናገኛለን? አንዳንድ ጊዜ ድርጅቱ አዳዲስ መመሪያዎችን የሰጠበትን ምክንያት ሙሉ በሙሉ መረዳት ሊከብደን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን ለስብሰባዎች፣ ለግል ጥናትና ለአገልግሎት እንድንጠቀም የተሰጠን መመሪያ መጀመሪያ ላይ ጥቅሙ አልታየን ይሆናል። አሁን ግን ሁኔታችን እስከፈቀደ ድረስ እነዚህን መሣሪያዎች መጠቀማችን ያለውን ጥቅም ተገንዝበን መሆን አለበት። ምንም እንኳ መጀመሪያ ላይ ጥርጣሬ ሊያድርብን ቢችልም እንዲህ ያሉ ለውጦች ያስገኙትን ጥሩ ውጤት መመልከታችን እምነታችን እንዲጨምርና አንድነታችን እንዲጠናከር ያደርጋል።

ክርስቶስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ጉባኤውን የመራው እንዴት ነው?

10. ግርዘትን አስመልክቶ የተነሳው ክርክር መፍትሔ እንዲያገኝ ጉዳዩን ወደ በላይ አካሉ የመራው ማን ነበር?

10 ቆርኔሌዎስ ወደ ክርስትና ከተለወጠ ከ13 ዓመታት ገደማ በኋላ እንኳ አይሁዳውያን የሆኑ አንዳንድ ክርስቲያኖች ግርዘትን ደግፈው ይከራከሩ ነበር። (ሥራ 15:1, 2) በአንጾኪያ ክፍፍል ሲፈጠር ጳውሎስ ጉዳዩን በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው የበላይ አካል እንዲያቀርብ ተወሰነ። ሆኖም ከዚህ ውሳኔ በስተጀርባ ያለው ማን ነበር? ጳውሎስ “የሄድኩት በተገለጠልኝ ራእይ መሠረት ነበር” ብሏል። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው፣ የበላይ አካሉ ለጉዳዩ መፍትሔ እንዲያበጅ ሲል ሁኔታውን በዚህ መንገድ የመራው ክርስቶስ ነው።—ገላ. 2:1-3

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የክርስቶስ አመራር በግልጽ ይታይ ነበር (አንቀጽ 10, 11⁠ን ተመልከት)

11. (ሀ) አይሁዳውያን አማኞች ግርዘትን በተመለከተ የትኛውን አመለካከት ይዘው ቀጥለዋል? (ለ) ጳውሎስ በኢየሩሳሌም የነበሩትን ሽማግሌዎች መደገፍ ፈታኝ እንዲሆንበት የሚያደርግ ምን ሁኔታ አጋጥሞት ነበር? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

11 በክርስቶስ አመራር ሥር ያለው የበላይ አካል አይሁዳዊ ያልሆኑ ክርስቲያኖች መገረዝ እንደማያስፈልጋቸው ግልጽ አደረገ። (ሥራ 15:19, 20) ሆኖም ይህ ውሳኔ ከተላለፈ በርካታ ዓመታት ቢያልፉም ልጆቻቸውን የሚገርዙ ብዙ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ነበሩ። በኢየሩሳሌም ያሉት ሽማግሌዎች ጳውሎስ የሙሴን ሕግ እንደማይጠብቅ የሚናፈሰውን ወሬ ሲሰሙ ለጳውሎስ ያልተጠበቀ መመሪያ ሰጡት። * (ሥራ 21:20-26) ሽማግሌዎቹ አራት ሰዎችን ይዞ ወደ ቤተ መቅደሱ እንዲሄድ ነገሩት፤ ይህን መመሪያ የሰጡት፣ ሰዎች ጳውሎስ “ሕጉን [ያከብራል]” ብለው እንዲያስቡ ለማድረግ ሲሉ ነው። ጳውሎስ ችግሩ ያለው እሱ ጋ ሳይሆን ስለ ግርዘት ትክክለኛ ግንዛቤ የሌላቸው አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ጋ እንደሆነ በመግለጽ፣ የተሰጠውን መመሪያ ለመቀበል ሊያንገራግር ይችል ነበር። ሆኖም የተሰጠውን መመሪያ በትሕትና በመቀበል ሽማግሌዎች በአማኞች መካከል አንድነት ለማስፈን የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚደግፍ አሳይቷል። ይሁንና ‘ኢየሱስ በሞቱ አማካኝነት የሙሴን ሕግ የሻረ ቢሆንም ጉዳዩ መፍትሔ ሳያገኝ ይህን ያህል ረጅም ጊዜ እንዲቆይ የፈቀደው ለምንድን ነው?’ ብለን እንጠይቅ ይሆናል።—ቆላ. 2:13, 14

12. ክርስቶስ የግርዘት ጉዳይ መፍትሔ ሳያገኝ ለተወሰነ ጊዜ እንዲቀጥል የፈለገው ለምን ሊሆን ይችላል?

12 አንዳንዶች አዳዲስ ማስተካከያዎችን ለመቀበል ጊዜ ይወስድባቸዋል። አይሁዳውያን ክርስቲያኖችም አመለካከታቸውን ለማስተካከል በቂ ጊዜ ያስፈልጋቸው ነበር። (ዮሐ. 16:12) አንዳንድ አይሁዳውያን አማኞች ግርዘት ከአምላክ ጋር ልዩ ዝምድና እንዳላቸው የሚያሳይ ምልክት መሆኑ እንዳበቃ መቀበል ከብዷቸው ነበር። (ዘፍ. 17:9-12) ሌሎች ደግሞ በአይሁድ ማኅበረሰብ መካከል ለየት ብለው መታየታቸው ለስደት እንዳይዳርጋቸው ፈርተው ነበር። (ገላ. 6:12) ከጊዜ በኋላ ግን ክርስቶስ፣ ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት በጻፋቸው ደብዳቤዎች አማካኝነት ተጨማሪ መመሪያዎችን ሰጥቷል።—ሮም 2:28, 29፤ ገላ. 3:23-25

ክርስቶስ አሁንም ጉባኤውን እየመራ ነው

13. በዛሬው ጊዜ የክርስቶስን አመራር ለመደገፍ ምን ሊረዳን ይችላል?

13 ድርጅቱ አንዳንድ ለውጦች ያደረገበትን ምክንያት ሙሉ በሙሉ መረዳት በሚከብደን ጊዜ ክርስቶስ ጥንት የነበሩ የአምላክ ሕዝቦችን የመራበትን መንገድ ማሰባችን ጠቃሚ ነው። በኢያሱ ጊዜም ሆነ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቶስ ለአምላክ ሕዝቦች በቡድን ደረጃ ጥበቃ ለማድረግ፣ እምነታቸውን ለማጠናከርና አንድነታቸውን እንዲጠብቁ ለመርዳት ሲል ምንጊዜም ጥበብ የተንጸባረቀበት መመሪያ ይሰጥ ነበር።—ዕብ. 13:8

14-16. “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚሰጠው መመሪያ ክርስቶስ ለመንፈሳዊ ደህንነታችን እንደሚያስብ የሚያሳየው እንዴት ነው?

14 “ታማኝና ልባም ባሪያ” በተገቢው ጊዜ የሚሰጠን መመሪያ ኢየሱስ እንደሚወደንና ለመንፈሳዊ ደህንነታችን እንደሚያስብ ያሳያል። (ማቴ. 24:45) የአራት ልጆች አባት የሆነው ማርክ እንዲህ ብሏል፦ “ሰይጣን በቤተሰቦች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ጉባኤዎችን ለማዳከም ይሞክራል። በየሳምንቱ የቤተሰብ አምልኮ እንድናደርግ የተሰጠን ማበረታቻ ለቤተሰብ ራሶች ‘ቤተሰባችሁን ከጥቃት ጠብቁ!’ የሚል ግልጽ መልእክት ይዟል።”

15 ክርስቶስ እየሰጠን ያለውን አመራር ስናስተውል መሪያችን መንፈሳዊ እድገት እንድናደርግ ሊረዳን እንደሚፈልግ እንገነዘባለን። ፓትሪክ የተባለ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “መጀመሪያ ላይ አንዳንዶች የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባዎችን በትናንሽ ቡድኖች ተከፋፍሎ ማድረግ ያለው ጥቅም አልታያቸውም ነበር። ሆኖም ይህ ዝግጅት ከኢየሱስ ዋነኛ ባሕርያት መካከል አንዱን ማለትም ለደካሞች ያለውን አሳቢነት በግልጽ የሚያሳይ ነው። አይናፋር የሆኑ ወይም በአገልግሎት ንቁ ተሳትፎ የማያደርጉ ወንድሞችና እህቶች ተፈላጊ እንደሆኑና ጠቃሚ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ እንዲሰማቸው ያደርጋል፤ በመሆኑም መንፈሳዊ እድገት ማድረግ ችለዋል።”

16 ክርስቶስ መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ከማሟላት በተጨማሪ በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ ካሉት ሥራዎች ሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ በሆነው ሥራ ላይ እንድናተኩር ይረዳናል። (ማርቆስ 13:10ን አንብብ።) በቅርቡ ሽማግሌ ሆኖ የተሾመው አንድሬ ድርጅቱ የሚሰጣቸውን አዳዲስ መመሪያዎች ምንጊዜም ትኩረት ሰጥቶ ይከታተላል። እንዲህ ብሏል፦ “በቅርቡ በቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ የሚያገለግሉ ወንድሞች ቁጥር እንዲቀንስ መደረጉ የጊዜውን አጣዳፊነትና በስብከቱ ሥራ ላይ ትኩረት የማድረግን አስፈላጊነት እንድናስታውስ የሚያደርግ ነው።”

የክርስቶስን አመራር በታማኝነት ደግፉ

17, 18. በቅርቡ ከተደረጉት ለውጦች ጋር ራሳችንን ማስማማታችን ባስገኘልን ጥቅም ላይ ማተኮራችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

17 በመግዛት ላይ ያለው ንጉሣችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚሰጠው መመሪያ የወደፊቱን ጊዜ ግምት ውስጥ ያስገባ ነው። እንግዲያው በቅርቡ ከተደረጉት ለውጦች ጋር ራሳችንን ማስማማታችን ባስገኘልን ጥቅም ላይ ለማተኮር ጥረት እናድርግ። ለምሳሌ በቤተሰብ አምልኳችሁ ላይ ከሳምንታዊ ስብሰባዎች ወይም ከአገልግሎት ጋር በተያያዘ የተደረጉት ለውጦች ምን ጥቅም እንዳስገኙላችሁ ልትወያዩ ትችላላችሁ።

ቤተሰቦችህና ሌሎች የጉባኤው አባላት ከይሖዋ ድርጅት ጋር እኩል እንዲራመዱ እየረዳህ ነው? (አንቀጽ 17, 18⁠ን ተመልከት)

18 የይሖዋ ድርጅት ከሚሰጠን መመሪያዎች በስተጀርባ ያለውን መንፈስና እነዚህን መመሪያዎች መከተል በሚያስገኘው ጥቅም ላይ ማሰላሰላችን መመሪያዎቹን በደስታ እንድንታዘዝ ይረዳናል። ለምሳሌ ያህል፣ የሚታተሙ ጽሑፎች ቁጥር እንዲቀንስ መደረጉ የድርጅቱ ወጪ እንዲቀንስ አድርጓል፤ በተጨማሪም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀማችን በዓለም ዙሪያ የሚከናወነውን የስብከቱን ሥራ ይበልጥ ለማስፋፋት አስችሏል። እንግዲያው ሁኔታችን የሚፈቅድ ከሆነ የሕትመት ውጤቶችንና ሚዲያዎችን በኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎቻችን ለመጠቀም ጥረት እናድርግ። ይህ ክርስቶስን መደገፍ የምንችልበት አንዱ መንገድ ነው፤ ክርስቶስ የድርጅቱን ሀብት ከሁሉ በተሻለ መንገድ እንድንጠቀምበት ይፈልጋል።

19. የክርስቶስን አመራር መደገፋችን ምን ጥቅም ያስገኛል?

19 የክርስቶስን አመራር ከልብ መደገፋችን የሌሎችን እምነት የሚያጠናክር ከመሆኑም ሌላ ለአንድነታችን አስተዋጽኦ ያበረክታል። አንድሬ በዓለም ዙሪያ ያለው የቤቴል ቤተሰብ ቁጥር እንዲቀንስ የተደረገውን ማስተካከያ አስመልክቶ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ቀደም ሲል በቤቴል ያገለግሉ የነበሩ ወንድሞች ለለውጡ የሰጡትን አዎንታዊ ምላሽ መመልከቴ እምነቴ እንዲጨምርና ለእነሱ አክብሮት እንዲያድርብኝ አድርጓል። የተሰጣቸውን ማንኛውንም ምድብ ተቀብለው በደስታ በማገልገል ከይሖዋ ሠረገላ ጋር እኩል እንደሚጓዙ አሳይተዋል።”

በመሪያችን ላይ እምነት ይኑራችሁ

20, 21. (ሀ) መሪያችን በሆነው በክርስቶስ ላይ እምነት መጣል ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) በቀጣዩ ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?

20 የተሾመው ንጉሣችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅርቡ ‘ድሉን ያጠናቅቃል’፤ እንዲሁም “የሚያስፈሩ ተግባሮችን ያከናውናል።” (ራእይ 6:2፤ መዝ. 45:4) በዛሬው ጊዜም እንኳ የአምላክን ሕዝቦች ይህ ሥርዓት ከተደመደመ በኋላ ለሚኖራቸው ሕይወት እያዘጋጃቸው ነው፤ በአዲሱ ዓለም ውስጥ እያንዳንዳችን ከሞት የተነሱ ሰዎችን በማስተማሩና ምድርን ወደ ገነትነት በመቀየሩ ሥራ ላይ የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናበረክታለን።

21 በተሾመው ንጉሣችን ላይ ሙሉ እምነት እስከጣልን ድረስ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ቢኖሩም ንጉሣችን ወደ አዲሱ ዓለም እየመራ እንደሚያስገባን ጥርጥር የለውም። (መዝሙር 46:1-3ን አንብብ።) አንዳንድ ጊዜ ግን በሕይወታችን ውስጥ ያልተጠበቀ ለውጥ ሲያጋጥመን ለውጡን መቀበል ከባድ ሊሆንብን ይችላል። ታዲያ በዚህ ወቅት ውስጣዊ ሰላማችንን እንዳናጣና በይሖዋ ላይ ያለንን ጠንካራ እምነት ይዘን እንድንቀጥል ምን ሊረዳን ይችላል? ቀጣዩ ርዕስ የዚህን ጥያቄ መልስ ይዟል።

^ አን.8 የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች በኢያሪኮ ፍርስራሽ ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው የእህል ክምችት አግኝተዋል፤ ይህም ከተማዋ ለረጅም ጊዜ ተከባ እንዳልቆየችና የእህል ክምችቷ እንዳላለቀ የሚጠቁም ነው። እስራኤላውያን ከኢያሪኮ ምንም ነገር እንዳይወስዱ ታዘው የነበረ ከመሆኑ አንጻር ከተማዋን የወረሩት በትክክለኛ ወቅት ላይ ነው ማለት ይቻላል፤ ምክንያቱም ጊዜው የመከር ወቅት በመሆኑ ከከተማዋ ውጭ በማሳዎች ላይ የተትረፈረፈ እህል ማግኘት ይችሉ ነበር።—ኢያሱ 5:10-12

^ አን.11 በመጋቢት 15, 2003 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 24 ላይ የወጣውን “ጳውሎስ ያጋጠመውን ፈተና በትሕትና ተወጣ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።