በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

1918—የዛሬ መቶ ዓመት

1918—የዛሬ መቶ ዓመት

የጥር 1, 1918 መጠበቂያ ግንብ መግቢያው ላይ “1918 ምን ይዞ ይመጣ ይሆን?” የሚል ሐሳብ ይዞ ወጥቶ ነበር። በወቅቱ ታላቁ ጦርነት በአውሮፓ ገና እንደተፋፋመ ነበር፤ ሆኖም በዚያ ዓመት መጀመሪያ አካባቢ የተከናወኑት ነገሮች ለመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችም ሆነ ለመላው የዓለም ሕዝብ የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ የሚያመላክቱ ይመስል ነበር።

ዓለም ስለ ሰላም አወራ

ጥር 8, 1918 ፕሬዚዳንት ውድሮ ዊልሰን ለዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ባቀረቡት ንግግር ላይ “ፍትሕና ዘላቂ ሰላም” ለማምጣት አስፈላጊ ናቸው ብለው ያሰቧቸውን 14 ነጥቦች ዘረዘሩ። በንግግራቸው ላይ በአገሮች መካከል ግልጽነት የሰፈነበት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲኖር፣ የከባድ ጦር መሣሪያዎች ቅነሳ እንዲደረግና “ትላልቆቹንም ሆነ ትናንሾቹን መንግሥታት እኩል” ተጠቃሚ የሚያደርግ “የዓለም መንግሥታት ማኅበር” እንዲቋቋም ሐሳብ አቀረቡ። ፕሬዚዳንቱ ያቀረቧቸው “አሥራ አራት ነጥቦች” ከጊዜ በኋላ የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር ሲቋቋምና የቬርሳይ የሰላም ስምምነት ሲደረግ ያገለገሉ ሲሆን በውጤቱም ታላቁ ጦርነት ሊቆም ችሏል።

ተቃዋሚዎች ተሸነፉ

ከዚያ በፊት የነበረው ዓመት * ብጥብጥ የነገሠበት ቢሆንም ዎች ታወር ባይብል ኤንድ ትራክት ሶሳይቲ ባደረገው ዓመታዊ ስብሰባ ላይ የተከናወኑት ነገሮች ለመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ የተስፋ ጭላንጭል የሚፈነጥቁ ይመስል ነበር።

ከቤቴል እንዲወጡ የተደረጉ ትልቅ ኃላፊነት የነበራቸው ሰዎች ጥር 5, 1918 በተደረገው በዚህ ስብሰባ ላይ ድርጅቱን ለመቆጣጠር ሙከራ አደረጉ። ታማኝ ተጓዥ የበላይ ተመልካች የነበረው ሪቻርድ ባርበር ስብሰባውን በጸሎት ከፈተ። ባለፈው ዓመት ስለተከናወነው ሥራ የሚገልጽ ሪፖርት ከቀረበ በኋላ ዓመታዊው የዳይሬክተሮች ምርጫ ተካሄደ። ወንድም ባርበር፣ ጆሴፍ ራዘርፎርድንና ሌሎች ስድስት ወንድሞችን በዕጩነት አቀረበ። ከተቃዋሚዎቹ ወገን የነበረ አንድ ጠበቃ ደግሞ ከቤቴል የተባረሩትን ጨምሮ ሰባት ሰዎችን በዕጩነት አቀረበ። ሆኖም ተቃዋሚዎቹ በምርጫው ተሸነፉ። ባለድርሻ አካላቱ ወንድም ራዘርፎርድንና ሌሎች ስድስት ታማኝ ወንድሞችን በከፍተኛ አብላጫ ድምፅ ዳይሬክተር አድርገው መረጧቸው።

በዚያ ስብሰባ ላይ የተገኙ ብዙ ወንድሞች ይህ ስብሰባ “ከዚያ በፊት ካደረጓቸው ስብሰባዎች ሁሉ ይበልጥ የይሖዋን በረከት ያዩበት” እንደሆነ ተናግረዋል። ሆኖም ደስታቸው ብዙም አልዘለቀም።

ያለቀለት ሚስጥር ለተባለው መጽሐፍ የተሰጠ ምላሽ

የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ያለቀለት ሚስጥር የተባለውን መጽሐፍ ለብዙ ወራት ሲያሰራጩ ቆይተው ነበር። ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በውስጡ ላለው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተዋል።

በካናዳ የሚያገለግል ኤድዋርድ ክሪስት የሚባል ተጓዥ የበላይ ተመልካች፣ አንድ ባልና ሚስት ያለቀለት ሚስጥር የተባለውን መጽሐፍ አንብበው በአምስት ሳምንት ውስጥ እውነትን እንደተቀበሉ ተናግሯል! “ባልና ሚስቱ ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ የወሰኑ ሲሆን አስደናቂ እድገት እያደረጉ ነው” ብሏል።

ይህን መጽሐፍ ያገኘ አንድ ሰው፣ ያነበበውን ነገር ወዲያውኑ ለጓደኞቹ አካፈላቸው። መልእክቱ በኃይል “መቶት” ነበር። ተሞክሮውን ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ሦስተኛ ጎዳና በሚባለው መንገድ ላይ በእግር እየሄድኩ ሳለ የሆነ ነገር ትከሻዬ ላይ መታኝ፤ የመታኝ ጡብ መስሎኝ ነበር፤ ለካስ ‘ያለቀለት ሚስጥር’ የተባለው መጽሐፍ ኖሯል። መጽሐፉን ወደ ቤት ወስጄ ሙሉውን አነበብኩት። . . . ከጊዜ በኋላ ስሰማ መጽሐፉን በመስኮት የወረወረው አንድ የተናደደ . . . ሰባኪ ነበር። . . . ሰባኪው ዕድሜ ልኩን ካከናወነው ከየትኛውም ድርጊት ይበልጥ ይህ ድርጊቱ በርካታ ሰዎች ሕያው ተስፋ እንዲያገኙ እንዳስቻለ እርግጠኛ ነኝ። . . . በዚህ ሰው ቁጣ ምክንያት ዛሬ እኛ አምላክን ማወደስ ችለናል።”

እንዲህ ዓይነት የቁጣ ምላሽ የሰጠው ያ ሰባኪ ብቻ አልነበረም። የካናዳ ባለሥልጣናት ያለቀለት ሚስጥር የተባለው መጽሐፍ ሕዝብን ለዓመፅ የሚያነሳሳና ወታደራዊ እንቅስቃሴን የሚቃወም ሐሳብ እንደያዘ በመግለጽ የካቲት 12, 1918 መጽሐፉ እንዲታገድ አደረጉ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ በዩናይትድ ስቴትስ ያሉ ባለሥልጣናትም ተመሳሳይ እርምጃ ወሰዱ። የመንግሥት ወኪሎች የድርጅቱን መሪዎች ለመክሰስ የሚያስችል ማስረጃ ለማግኘት የቤቴል መኖሪያ ቤትን እንዲሁም በኒው ዮርክ፣ በፔንስልቬንያና በካሊፎርኒያ ያሉ ቢሮዎችን ፈተሹ። መጋቢት 14, 1918 የዩናይትድ ስቴትስ የፍትሕ ቢሮ ያለቀለት ሚስጥር የተባለው መጽሐፍ መታተሙና መሰራጨቱ ለጦርነቱ እንቅፋት እንደሚፈጥር እንዲሁም በወታደራዊ እንቅስቃሴ ጣልቃ ከመግባት ጋር በተያያዘ የወጣውን ሕግ እንደሚጥስ በመግለጽ መጽሐፉ እንዲታገድ ውሳኔ አስተላለፈ።

ታሰሩ!

ግንቦት 7, 1918 የፍትሕ ቢሮው ሮበርት ማርቲን፣ አሌክሳንደር ማክሚላን፣ ጆሴፍ ራዘርፎርድ፣ ፍሬድሪክ ሮቢሰን፣ ክሌይተን ዉድዎርዝ፣ ጆቫኒ ዴቼካ፣ ጆርጅ ፊሸርና ዊሊያም ቫን አምበርግ የተባሉት ወንድሞች ተይዘው እንዲታሰሩ የፍርድ ቤት ማዘዣ አወጣ። እነዚህ ወንድሞች “ሆን ብለው ሕግ በመጣስና ወንጀል በመፈጸም ሰዎች እንዳይታዘዙ፣ አገር እንዲከዱ እንዲሁም በዩናይትድ ስቴትስ የጦር ሠራዊትና የባሕር ኃይል ውስጥ ገብተው እንዳያገለግሉ ያነሳሳሉ” የሚል ክስ ቀርቦባቸው ነበር። የፍርድ ሂደቱ የጀመረው ሰኔ 5, 1918 ሲሆን ገና ከጅምሩ በእነዚህ ወንድሞች ላይ መፈረዱ እንደማይቀር ግልጽ ነበር። ለምን?

የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ፣ ወንድሞች ጥሰውታል ተብለው የተከሰሱበትን ሕግ “ፕሮፓጋንዳን የሚቃወም ውጤታማ መሣሪያ” በማለት ጠርቶታል። ግንቦት 16, 1918 ምክር ቤቱ “ተገቢ የሆነ ዓላማ ይዘው እንዲሁም በንጹሕ ልቦና ተነሳስተው እውነት የሆነውን ነገር” ለሚያሰራጩ ሰዎች ከለላ ለመስጠት የቀረበውን የሕግ ማሻሻያ ሳያጸድቀው ቀረ። የምክር ቤቱ ክርክር በዋነኝነት ያተኮረው ያለቀለት ሚስጥር በተባለው መጽሐፍ ላይ ነበር። የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ሕጋዊ መዝገብ ይህን መጽሐፍ አስመልክቶ የሚከተለውን ሐሳብ አስፍሯል፦ “እንዲህ ላለው አደገኛ ፕሮፓጋንዳ ዓይነተኛ ምሳሌ ሆኖ የሚጠቀሰው ‘ያለቀለት ሚስጥር’ የተባለው መጽሐፍ ነው። . . . መጽሐፉ ወታደሮች የእኛን ዓላማ እንዳይቀበሉ የሚያደርግና ለወታደራዊ ምልመላው እምቢተኞች እንዲሆኑ የሚያነሳሳ ነው።”

ሰኔ 20, 1918 በተሰየመው ችሎት ላይ የተገኙት እማኝ ዳኞች፣ ስምንቱ ወንድሞች በቀረቡባቸው ክሶች ሁሉ ጥፋተኞች እንደሆኑ ተስማሙ። በማግስቱ ዳኛው የፍርድ ውሳኔ አስተላለፉ። እንዲህ ብለዋል፦ “እነዚህ ተከሳሾች . . . አጥብቀው ሲከራከሩለትና ሲያሰራጩት የነበረው ሃይማኖታዊ ፕሮፓጋንዳ ከአንድ የጀርመን ሠራዊት ክፍለ ጦር ይበልጥ አደገኛ ነው። . . . ቅጣቱም ከባድ ሊሆን ይገባል።” ከሁለት ሳምንት በኋላ እነዚህ ስምንት ወንድሞች ከ10 እስከ 20 ዓመት የሚደርስ ፍርድ ተበይኖባቸው በአትላንታ፣ ጆርጂያ ወዳለው የፌዴራል ማረሚያ ቤት ገቡ።

የስብከቱ ሥራ ቀጠለ

በዚህ ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ኃይለኛ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል። የፌደራል የምርመራ ቢሮ (FBI) እያንዳንዱን እንቅስቃሴያቸውን በመመርመር በሺዎች የሚቆጠሩ ሰነዶችን አዘጋጅቶ ነበር። እነዚህ መዛግብት ወንድሞቻችን በስብከቱ ሥራ ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ እንዳደረጉ ያሳያሉ።

የኦርላንዶ፣ ፍሎሪዳ ፖስታ ቤት ሹም ለፌዴራል ምርመራ ቢሮ በጻፉት ደብዳቤ ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “[የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች] ከቤት ወደ ቤት በመስበክ ከተማዋን እያካለሉ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ የሚሰብኩት በማታ ነው። . . . የመጣው ይምጣ ብለው መስበካቸውን ለመቀጠል የቆረጡ ይመስላል።”

የጦር ሠራዊቱ አባል የነበረ አንድ ኮሎኔል፣ ከጊዜ በኋላ የበላይ አካል አባል ሆኖ ያገለገለውን የፍሬዴሪክ ፍራንዝን እንቅስቃሴ ለፌዴራል ምርመራ ቢሮው ሪፖርት ለማድረግ ደብዳቤ ጽፎ ነበር። ኮሎኔሉ “ፍሬድሪክ ፍራንዝ . . . ‘ያለቀለት ሚስጥር’ የተባለውን መጽሐፍ በመሸጡ ሥራ ንቁ ተሳትፎ ያደረገ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ቅጂዎችን አሰራጭቷል” በማለት ጽፏል።

ከጊዜ በኋላ የበላይ አካል አባል ሆኖ ያገለገለው ቻርለስ ፌከልም ከባድ ስደት አጋጥሞታል። ባለሥልጣናቱ ያለቀለት ሚስጥር የተባለውን መጽሐፍ አሰራጭቷል በሚል ያሰሩት ከመሆኑም ሌላ የሚጻጻፋቸውን ደብዳቤዎች ይከታተሉ ነበር። ወንድም ፌከል “ከኦስትሪያ የመጣ ባዕድ ጠላት” የሚል ስም ተሰጥቶት በባልቲሞር፣ ሜሪላንድ ለአንድ ወር ያህል ታስሯል። ለመርማሪዎቹ በድፍረት ምሥክርነት በሰጠበት ወቅት በ1 ቆሮንቶስ 9:16 ላይ የሚገኙትን “ምሥራቹን ባልሰብክ ወዮልኝ!” የሚሉትን የጳውሎስን ቃላት እንዳስታወሰ ተናግሯል። *

የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ የስብከቱን ሥራ በቅንዓት ከማከናወን በተጨማሪ በአትላንታ የታሰሩትን ወንድሞች ለማስፈታት የሚያስችል ፊርማ ለማሰባሰብ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። አና ጋርድነር እንዲህ በማለት ታስታውሳለች፦ “ሁልጊዜም የምንሠራው ነገር ነበረን። ወንድሞች እስር ቤት እንደገቡ ወዲያውኑ ፊርማ ማሰባሰብ ጀመርን። ይህን የምናደርገው ከቤት ወደ ቤት እየሄድን ነበር። በሺዎች የሚቆጠሩ ፊርማዎችን አሰባስበናል! ለምናነጋግራቸው ሰዎች የታሰሩት ወንድሞች እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደሆኑና እስር ቤት የገቡት ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንደሆነ እንነግራቸው ነበር።”

ትላልቅ ስብሰባዎች

በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የወንድማማች ማኅበሩን በመንፈሳዊ ለማጠናከር ዘወትር ትላልቅ ስብሰባዎች ይደረጉ ነበር። መጠበቂያ ግንብ ላይ የሚከተለው ሐሳብ ወጥቶ ነበር፦ “በዓመቱ ውስጥ . . . ከ40 የሚበልጡ ትላልቅ ስብሰባዎች ተደርገዋል። . . . ከሁሉም ስብሰባዎች አስደሳች ሪፖርቶች ደርሰውናል። ቀደም ሲል ትላልቅ ስብሰባዎች የሚደረጉት በበጋ ወራት ማብቂያ ላይ ወይም በመጸው ወራት መጀመሪያ ላይ ብቻ ነበር፤ አሁን ግን በየወሩ ትላልቅ ስብሰባዎች ይደረጋሉ።”

ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ለምሥራቹ በጎ ምላሽ መስጠታቸውን ቀጥለው ነበር። በክሊቭላንድ፣ ኦሃዮ በተደረገ አንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ 1,200 ገደማ የሚሆኑ ተሰብሳቢዎች የተገኙ ሲሆን 42 ሰዎች ተጠምቀዋል፤ ከተጠማቂዎቹ መካከል “ለአምላክ ያለው አድናቆትና ራሱን ለመወሰን ያለው ፍላጎት ብዙ አዋቂዎችን የሚኮንን” አንድ ትንሽ ልጅ ነበር።

ከዚያ በኋላስ?

የ1918 መገባደጃ ሲቃረብ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ከፊታቸው የሚጠብቃቸውን ነገር በተመለከተ እርግጠኞች አልነበሩም። በብሩክሊን ከነበረው ንብረት ውስጥ የተወሰነው የተሸጠ ሲሆን ዋና መሥሪያ ቤቱም ወደ ፒትስበርግ፣ ፔንስልቬንያ ተዛወረ። አመራር ይሰጡ የነበሩት ወንድሞች እስር ቤት በነበሩበት ወቅት ቀጣዩ የባለ ድርሻዎች ዓመታዊ ስብሰባ ጥር 4, 1919 እንዲደረግ ፕሮግራም ተያዘ። ታዲያ ምን ይከሰት ይሆን?

ወንድሞቻችን በስብከቱ ሥራቸው በጽናት ቀጥለው ነበር። ውጤቱ መልካም እንደሚሆን እርግጠኞች ከመሆናቸው የተነሳ የ1919 የዓመት ጥቅስ እንዲሆን የመረጡት “አንቺን ለማጥቃት የተሠራ ማንኛውም መሣሪያ ይከሽፋል” የሚለውን ጥቅስ ነበር። (ኢሳ. 54:17) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ እምነታቸውን የሚያጠናክርና ከፊታቸው ለሚጠብቃቸው ታላቅ ሥራ ብርታት የሚሰጥ አስገራሚ ለውጥ ለማስተናገድ ራሳቸውን አዘጋጅተው ነበር።

^ አን.6 በ2017 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) ከገጽ 172-176 ላይ የወጣውን “የዛሬ መቶ ዓመት—1917” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.22 የቻርለስ ፌከልን የሕይወት ታሪክ ለማንበብ በመጋቢት 1, 1969 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ላይ የወጣውን “በመልካም ሥራ መጽናት የሚያስገኘው ደስታ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።