በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 41

‘በታላቁ መከራ’ ወቅት ታማኝነታችሁን ጠብቁ

‘በታላቁ መከራ’ ወቅት ታማኝነታችሁን ጠብቁ

“እናንተ ለእሱ ታማኝ የሆናችሁ ሁሉ፣ ይሖዋን ውደዱ! ይሖዋ ታማኞችን ይጠብቃል።”—መዝ. 31:23

መዝሙር 129 ጸንተን እንጠብቃለን

ማስተዋወቂያ *

1-2. (ሀ) በቅርቡ መንግሥታት ምን ብለው ያውጃሉ? (ለ) ለየትኞቹ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ያስፈልገናል?

መንግሥታት አስቀድሞ በትንቢት የተነገረውን “ሰላምና ደህንነት ሆነ!” የሚለውን አዋጅ ሲያውጁ የሚኖረውን ሁኔታ ለማሰብ እንሞክር። በዓለም ላይ ታይቶ የማይታወቅ ሰላም እንደሰፈነ በመግለጽ ይፎክሩ ይሆናል። መንግሥታት በዓለም ላይ ያሉትን ሁኔታዎች በቁጥጥራቸው ሥር ማድረግ እንደቻሉ ሊያሳምኑን ይሞክራሉ። ይሁን እንጂ ከዚያ በኋላ የሚፈጸሙት ነገሮች ጨርሶ ከቁጥጥራቸው ውጭ ናቸው! እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንደሚገልጸው “ያልታሰበ ጥፋት ድንገት ይመጣባቸዋል፤ ደግሞም በምንም ዓይነት አያመልጡም።”—1 ተሰ. 5:3

2 ከዚህ አንጻር መልስ የሚያሻቸው አስፈላጊ ጥያቄዎች አሉ፦ ‘በታላቁ መከራ’ ወቅት ምን ይከናወናል? ይሖዋ በዚያ ጊዜ ምን እንድናደርግ ይጠብቅብናል? በታላቁ መከራ ወቅት ታማኝ ለመሆን ከአሁኑ ራሳችንን ማዘጋጀት የምንችለውስ እንዴት ነው?—ማቴ. 24:21

‘በታላቁ መከራ’ ወቅት ምን ይከናወናል?

3. በራእይ 17:5, 15-18 መሠረት አምላክ ‘ታላቂቱ ባቢሎንን’ የሚያጠፋት እንዴት ነው?

3 ራእይ 17:5, 15-18ን አንብብ። “ታላቂቱ ባቢሎን” ትጠፋለች! ቀደም ሲል እንደተገለጸው በዚህ ጊዜ የሚፈጠሩት ሁኔታዎች ከመንግሥታት ቁጥጥር ውጭ ናቸው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ‘አምላክ ሐሳቡን ዳር እንዲያደርሱ በልባቸው ያኖረዋል።’ ይህ ሐሳብ ምንድን ነው? ሕዝበ ክርስትናን ጨምሮ በዓለም ላይ ያሉ የሐሰት ሃይማኖቶችን በሙሉ ማጥፋት ነው። * አምላክ ይህን ሐሳብ ‘በደማቁ ቀይ አውሬ አሥር ቀንዶች’ ልብ ውስጥ ያኖረዋል። አሥሩ ቀንዶች፣ ‘አውሬውን’ ይኸውም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን የሚደግፉትን የፖለቲካ ኃይሎች በሙሉ ያመለክታሉ። (ራእይ 17:3, 11-13፤ 18:8) እነዚህ የፖለቲካ ኃይሎች በሐሰት ሃይማኖት ላይ ጥቃት መሰንዘራቸው ታላቁ መከራ መጀመሩን የሚጠቁም ምልክት ይሆናል። ይህም በዓለም ላይ ያሉ ሰዎችን ሁሉ የሚነካ ድንገተኛና አስደንጋጭ ክንውን ይሆናል።

4. (ሀ) መንግሥታት በሐሰት ሃይማኖት ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ምክንያት አድርገው የሚያቀርቡት ነገር ምን ሊሆን ይችላል? (ለ) የእነዚህ ሃይማኖቶች የቀድሞ አባላት ምን ያደርጉ ይሆናል?

4 መንግሥታት በታላቂቱ ባቢሎን ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ምክንያት አድርገው የሚያቀርቡት ነገር ምን እንደሆነ አናውቅም። መንግሥታት፣ የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም እንቅፋት እንደሆኑና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ሁልጊዜ እጃቸውን እንደሚያስገቡ ይናገሩ ይሆናል። አሊያም ደግሞ እነዚህ የሃይማኖት ድርጅቶች ከልክ ያለፈ ሀብትና ንብረት እንዳካበቱ ይገልጹ ይሆናል። (ራእይ 18:3, 7) በዚህ ጥቃት የሚጠፉት የእነዚህ ሃይማኖቶች አባላት በሙሉ እንዳልሆኑ ማሰቡ ምክንያታዊ ይመስላል። መንግሥታት በሚሰነዝሩት ጥቃት የሚጠፉት የሃይማኖት ድርጅቶቹ ሳይሆኑ አይቀሩም። እነዚህ የሃይማኖት ድርጅቶች ከጠፉ በኋላ የቀድሞ አባሎቻቸው፣ የሃይማኖት መሪዎቻቸው እንዳታለሏቸው ስለሚገነዘቡ ከእነዚህ ሃይማኖቶች ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌላቸው ይገልጹ ይሆናል።

5. ይሖዋ ታላቁን መከራ በተመለከተ ምን ቃል ገብቷል? ለምንስ?

5 መጽሐፍ ቅዱስ የታላቂቱ ባቢሎን ጥፋት ምን ያህል ጊዜ እንደሚወስድ አይነግረንም፤ ሆኖም በአንጻራዊ ሁኔታ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚፈጸም እናውቃለን። (ራእይ 18:10, 21) ይሖዋ፣ ‘ምርጦቹ’ እና እውነተኛው ሃይማኖት ከጥፋቱ እንዲተርፉ ሲል የመከራው ‘ቀኖች እንዲያጥሩ’ እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል። (ማር. 13:19, 20) ይሁንና ታላቁ መከራ ከሚጀምርበት ጊዜ አንስቶ እስከ አርማጌዶን ጦርነት ባለው ጊዜ ውስጥ ይሖዋ ምን እንድናደርግ ይጠብቅብናል?

ምንጊዜም ከይሖዋ ንጹሕ አምልኮ ጎን ቁሙ

6. ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ያለንን ግንኙነት ማቋረጣችን ብቻውን በቂ አይደለም የምንለው ለምንድን ነው?

6 ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ ከታላቂቱ ባቢሎን እንዲለዩ ይፈልጋል። ይሁን እንጂ ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ያለንን ግንኙነት ማቋረጣችን ብቻውን በቂ አይደለም። ከእውነተኛው ሃይማኖት ይኸውም ከይሖዋ ንጹሕ አምልኮ ጎን ለመቆም ቁርጥ አቋም መውሰድ አለብን። ይህን ማድረግ የምንችልባቸውን ሁለት መንገዶች እስቲ እንመልከት።

በአስቸጋሪ ጊዜያትም እንኳ አብረን መሰብሰባችንን ፈጽሞ አንተው (አንቀጽ 7ን ተመልከት) *

7. (ሀ) የይሖዋን የጽድቅ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች መደገፋችንን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ዕብራውያን 10:24, 25 በተለይ በአሁኑ ወቅት ለአምልኮ አብረን መሰብሰባችን አስፈላጊ መሆኑን የሚያጎላው እንዴት ነው?

7 አንደኛ፣ የይሖዋን የጽድቅ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች መደገፋችንን መቀጠል ይኖርብናል። ዓለም የሚመራባቸውን መሥፈርቶች ልንቀበል አይገባም። ለምሳሌ ማንኛውንም ዓይነት የፆታ ብልግና አንደግፍም፤ ይህም ተመሳሳይ ፆታ ባላቸው ሰዎች መካከል የሚፈጸም ጋብቻንና ግብረ ሰዶማውያን የሚከተሏቸውን የአኗኗር ዘይቤዎች ያካትታል። (ማቴ. 19:4, 5፤ ሮም 1:26, 27) ሁለተኛ፣ ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ይሖዋን ማምለካችንን መቀጠል አለብን። በስብሰባ አዳራሾቻችን፣ ካልተቻለ ደግሞ በግል ቤቶች ውስጥ ሌላው ቀርቶ በድብቅ እንኳ በመሰብሰብ እንዲህ ማድረግ ይኖርብናል። ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥመን ለአምልኮ አብረን የመሰብሰብ ልማዳችንን በፍጹም መተው የለብንም። እንዲያውም “ቀኑ እየቀረበ መምጣቱን ስናይ ከበፊቱ ይበልጥ ይህን [ማድረግ]” ይኖርብናል።ዕብራውያን 10:24, 25ን አንብብ።

8. የምንሰብከው መልእክት ወደፊት ምን ዓይነት ሊሆን ይችላል?

8 በታላቁ መከራ ወቅት የምንሰብከው መልእክት የሚቀየር ይመስላል። በአሁኑ ወቅት የመንግሥቱን ምሥራች እየሰበክንና ሰዎችን ደቀ መዛሙርት ለማድረግ እየጣርን ነው። በታላቁ መከራ ወቅት ግን የምናውጀው እንደ በረዶ ድንጋይ ኃይለኛ የሆነ መልእክት ሊሆን ይችላል። (ራእይ 16:21) በሰይጣን ዓለም ላይ ስለሚመጣው ጥፋት እናውጅ ይሆናል። የምናውጀው መልእክት ምን እንደሚሆንና በምን መንገድ እንደምናውጀው በእርግጠኝነት የምናውቀው ጊዜው ሲደርስ ነው። ከመቶ ለሚበልጡ ዓመታት አገልግሎታችንን ለማከናወን ስንጠቀምባቸው የቆየናቸውን ዘዴዎች እንጠቀም ይሆን? ወይስ መልእክታችንን በሌላ መንገድ እናውጅ ይሆን? ይህን ጊዜ የሚያሳየን ይሆናል። የምንሰብክበት መንገድ ምንም ይሁን ምን፣ የአምላክን የፍርድ መልእክት በድፍረት የማወጅ መብት የሚኖረን ይመስላል!—ሕዝ. 2:3-5

9. የምንሰብከው መልእክት መንግሥታትን ምን እንዲያደርጉ ሊያነሳሳቸው ይችላል? ሆኖም ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

9 የምንሰብከው መልእክት መንግሥታት እኛን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ጸጥ ለማሰኘት እንዲነሱ ሳያደርጋቸው አይቀርም። በአሁኑ ጊዜ አገልግሎታችንን ለማከናወን በይሖዋ እርዳታ እንደምንታመን ሁሉ በዚያን ጊዜም የእሱ ድጋፍ ያስፈልገናል። አምላካችን የእሱን ፈቃድ ለማድረግ የሚያስፈልገንን ኃይል እንደሚሰጠን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ሚክ. 3:8

በአምላክ ሕዝቦች ላይ ለሚሰነዘረው ጥቃት ተዘጋጁ

10. በሉቃስ 21:25-28 ላይ አስቀድሞ እንደተነገረው አብዛኞቹ ሰዎች በታላቁ መከራ ወቅት ምን ይሰማቸዋል?

10 ሉቃስ 21:25-28ን አንብብ። በታላቁ መከራ ወቅት፣ በዓለም ላይ ያሉ የማይናወጡ መስለው የሚታዩ ነገሮች መጥፋት ሲጀምሩ ሰዎች በድንጋጤ ይዋጣሉ። በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ከሁሉ በከፋው በዚያ ጊዜ፣ ሰዎች ለገዛ ሕይወታቸው ስለሚሰጉ “የሚያደርጉት ጠፍቷቸው ይጨነቃሉ።” (ሶፎ. 1:14, 15) በዚያ ወቅት የይሖዋ ሕዝቦችም ጭምር ሕይወት የበለጠ አስቸጋሪ ሊሆንባቸው ይችላል። የዓለም ክፍል አለመሆናችን አንዳንድ ችግሮችን ሊያስከትልብን ይችላል። ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ መሠረታዊ ነገሮችን እንኳ እናጣ ይሆናል።

11. (ሀ) የሐሰት ሃይማኖት ከጠፋ በኋላ ሰዎች ትኩረታቸውን በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የሚያደርጉት ለምንድን ነው? (ለ) ታላቁን መከራ መፍራት የማያስፈልገን ለምንድን ነው?

11 የሐሰት ሃይማኖቶች ከጠፉ በኋላ በሆነ ወቅት ላይ ሰዎች፣ የራሳቸው የሃይማኖት ድርጅቶች ጠፍተው ሳለ የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖት አለመጥፋቱን ያስተውላሉ፤ ይህም ሊያበሳጫቸው ይችላል። በዚህ ምክንያት የሚፈጠረውን ተቃውሞ መገመት አያዳግትም፤ ሰዎች በማኅበራዊ ድረ ገጾችም ጭምር ቁጣቸውን ይገልጹ ይሆናል። መንግሥታትም ሆኑ ገዢያቸው የሆነው ሰይጣን የእኛ ሃይማኖት ብቻ ከጥፋት በመትረፉ ይጠሉናል። ሃይማኖቶችን በሙሉ ከምድር ገጽ ለማጥፋት ያደረጉት ጥረት አለመሳካቱን ይረዳሉ። በመሆኑም ትኩረታቸውን በእኛ ላይ ያደርጋሉ። በዚህ ወቅት መንግሥታት የማጎጉ ጎግ ሆነው ይነሳሉ። * ኃይላቸውን አስተባብረው በመነሳት በይሖዋ ሕዝብ ላይ ከባድ ጥቃት ይሰነዝራሉ። (ሕዝ. 38:2, 14-16) በዚያ ወቅት ስለሚኖረው ሁኔታ ዝርዝር ነገሮችን ስለማናውቅ፣ ሊፈጠሩ ስለሚችሉት ነገሮች አሁን ላይ ሆነን ስናስብ ስጋት ሊያድርብን ይችላል። ይሁን እንጂ እርግጠኛ የምንሆንበት አንድ ነገር አለ፦ ታላቁን መከራ መፍራት አያስፈልገንም። ይሖዋ ሕይወታችንን ለማትረፍ የሚያስችሉንን መመሪያዎች ይሰጠናል። (መዝ. 34:19) ‘መዳናችን እየቀረበ እንደሆነ’ ስለምናውቅ ‘ራሳችንን ቀና አድርገን ቀጥ ብለን መቆም’ እንችላለን። *

12. “ታማኝና ልባም ባሪያ” ወደፊት ለሚመጣው ነገር ሲያዘጋጀን የቆየው እንዴት ነው?

12 “ታማኝና ልባም ባሪያ” ታላቁን መከራ በታማኝነት ማለፍ እንድንችል ሲያዘጋጀን ቆይቷል። (ማቴ. 24:45) ይህን ያደረገባቸው በርካታ መንገዶች አሉ፤ ለአብነት ያህል፣ ከ2016-2018 ያደረግናቸውን ወቅታዊ የክልል ስብሰባዎች መጥቀስ እንችላለን። የይሖዋ ቀን እየተቃረበ ሲሄድ የሚያስፈልጉንን ባሕርያት እንድናዳብር በእነዚህ የክልል ስብሰባዎች ላይ ተበረታተናል። እስቲ ስለ እነዚህ ባሕርያት በአጭሩ እንመልከት።

ታማኝነትን፣ ጽናትን እና ድፍረትን ይበልጥ ለማዳበር ጥረት አድርጉ

‘ታላቁን መከራ’ በሕይወት ለማለፍ ከአሁኑ ተዘጋጁ (ከአንቀጽ 13-16ን ተመልከት) *

13. ለይሖዋ ያለንን ታማኝነት ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው? ከአሁኑ ይህን ማድረጋችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

13 ታማኝነት፦ የ2016 የክልል ስብሰባ ጭብጥ “ምንጊዜም ለይሖዋ ታማኝ ሁኑ!” የሚል ነበር። ይህ ስብሰባ፣ በግለሰብ ደረጃ ከይሖዋ ጋር ጠንካራ ዝምድና መመሥረታችን ለእሱ ታማኝ ለመሆን እንደሚረዳን አስተምሮናል። ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ ከልብ መጸለይና ቃሉን በትጋት ማጥናት እንዳለብን ማሳሰቢያ ተሰጥቶናል። ይህን ማድረጋችን በጣም አስቸጋሪ የሆኑ ፈተናዎችን እንኳ ለመቋቋም ኃይል ይሰጠናል። የሰይጣን ሥርዓት ወደ ፍጻሜው እየተቃረበ ሲሄድ ለአምላክም ሆነ ለመንግሥቱ ያለን ታማኝነት ይበልጥ እንደሚፈተን እንጠብቃለን። ሰዎች የሚሰነዝሩብን ፌዝ የሚቀጥል ይመስላል። (2 ጴጥ. 3:3, 4) በተለይ ደግሞ በዚያን ጊዜ የገለልተኝነት አቋማችንን የሚፈትኑ ተጨማሪ ሁኔታዎች ስለሚያጋጥሙን መዘባበቻ መሆናችን አይቀርም። በታላቁ መከራ ወቅት ታማኝነታችንን መጠበቅ እንድንችል ከአሁኑ ታማኝነታችንን ማጠናከር ይኖርብናል።

14. (ሀ) በምድር ላይ ያለውን ሥራ ከሚመሩት ወንድሞች ጋር በተያያዘ ምን ለውጥ ይኖራል? (ለ) በዚያ ጊዜ ታማኝ መሆን የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

14 በታላቁ መከራ ወቅት፣ በምድር ላይ ሥራውን ከሚመሩት ወንድሞች ጋር በተያያዘ ለውጥ ይኖራል። ታላቁ መከራ ከጀመረ በኋላ የሆነ ወቅት ላይ፣ በምድር ላይ የቀሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሙሉ በአርማጌዶን ጦርነት ለመካፈል ወደ ሰማይ ይሰበሰባሉ። (ማቴ. 24:31፤ ራእይ 2:26, 27) በመሆኑም የበላይ አካሉ በምድር ላይ ከእኛ ጋር አይሆንም ማለት ነው። ያም ቢሆን የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት እንደተደራጁ ይቀጥላሉ። የሌሎች በጎች አባላት የሆኑ ብቃት ያላቸው ወንድሞች ሥራውን ተረክበው አመራር ይሰጣሉ። እነዚህን ወንድሞች በመደገፍና አምላክ ለእነሱ የሚሰጣቸውን መመሪያ በመከተል ለይሖዋ ታማኝ መሆናችንን ማሳየት ይኖርብናል። በሕይወት መትረፋችን የተመካው ይህን በማ ድረጋችን ላይ ነው!

15. ጽናትን ይበልጥ ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? ከአሁኑ እንዲህ ማድረጋችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

15 ጽናት፦ የ2017 የክልል ስብሰባ ጭብጥ “ተስፋ አትቁረጡ!” የሚል ነበር። ይህ ስብሰባ አስቸጋሪ የሆኑ ሁኔታዎችን በጽናት የማለፍ ችሎታ እንድናዳብር ረድቶናል። መጽናታችን የተመካው ባለንበት ሁኔታ ላይ እንዳልሆነ ተምረናል። ከዚህ ይልቅ ጽናትን ይበልጥ ማዳበር የምንችለው በይሖዋ በመታመን ነው። (ሮም 12:12) ኢየሱስ “እስከ መጨረሻው የሚጸና ግን ይድናል” በማለት የገባውን ቃል በፍጹም አንርሳ። (ማቴ. 24:13 ግርጌ) ይህ ተስፋ፣ ምንም ዓይነት ፈታኝ ሁኔታ ቢያጋጥመን በታማኝነት መጽናት እንዳለብን ይጠቁመናል። በዛሬው ጊዜ የሚያጋጥመንን እያንዳንዱን ፈተና በጽናት ከተወጣን ለታላቁ መከራ የሚያስፈልገንን ጥንካሬ ከአሁኑ እናዳብራለን።

16. ደፋር መሆናችን የተመካው በምን ላይ ነው? ከአሁኑ ድፍረት ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?

16 ድፍረት፦ የ2018 የክልል ስብሰባ ጭብጥ “ደፋር ሁኑ!” የሚል ነበር። ይህ ስብሰባ ደፋር መሆናችን የተመካው በራሳችን ችሎታ ላይ እንዳልሆነ አስታውሶናል። እንደ ጽናት ሁሉ፣ እውነተኛ ድፍረትም የሚገኘው በይሖዋ በመታመን ነው። በይሖዋ ይበልጥ ለመታመን ምን ማድረግ እንችላለን? ቃሉን በየዕለቱ ማንበባችንና በጥንት ጊዜ ይሖዋ ሕዝቡን እንዴት እንዳዳነ ማሰላሰላችን በዚህ ረገድ ይረዳናል። (መዝ. 68:20፤ 2 ጴጥ. 2:9) በታላቁ መከራ ወቅት መንግሥታት በእኛ ላይ ጥቃት ሲሰነዝሩ ደፋሮች መሆንና ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በይሖዋ መታመን ይኖርብናል። (መዝ. 112:7, 8፤ ዕብ. 13:6) በአሁኑ ወቅት በይሖዋ የምንታመን ከሆነ የጎግን ጥቃት ለመቋቋም የሚያስችል ድፍረት ማዳበር እንችላለን። *

መዳናችሁን በጉጉት ተጠባበቁ

ኢየሱስና በሰማይ ያለው ሠራዊቱ በቅርቡ በሚካሄደው የአርማጌዶን ጦርነት የአምላክን ጠላቶች ለማጥፋት ይመጣሉ! (አንቀጽ 17⁠ን ተመልከት)

17. አርማጌዶንን መፍራት የሌለብን ለምንድን ነው? (ሽፋኑን ተመልከት።)

17 ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተገለጸው አብዛኞቻችን መላ ሕይወታችንን የኖርነው በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ ነው። ሆኖም ታላቁን መከራ በሕይወት የማለፍ አጋጣሚም አለን። የአርማጌዶን ጦርነት፣ የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ታላቅ ፍጻሜ ይሆናል። ይሁንና አርማጌዶንን የምንፈራበት ምንም ምክንያት የለም። ለምን? ምክንያቱም አርማጌዶን የአምላክ ጦርነት ነው። (ምሳሌ 1:33፤ ሕዝ. 38:18-20፤ ዘካ. 14:3) ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ይሖዋ የሚሰጠውን መመሪያ በመከተል ሠራዊቱን ለውጊያ ያዘምታል። ከሞት የተነሱ ቅቡዓንና እልፍ አእላፋት መላእክት አብረውት ይሆናሉ። በአንድነት ሆነው ከሰይጣን፣ ከአጋንንቱና በምድር ላይ ካሉት ግብረ አበሮቻቸው ጋር ይዋጋሉ።—ዳን. 12:1፤ ራእይ 6:2፤ 17:14

18. (ሀ) ይሖዋ ምን ዋስትና ሰጥቶናል? (ለ) ራእይ 7:9, 13-17 የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት እንድትጠባበቅ የሚረዳህ እንዴት ነው?

18 ይሖዋ፣ ሕዝቦቹን “ለማጥቃት የተሠራ ማንኛውም መሣሪያ [እንደሚከሽፍ]” ዋስትና ሰጥቶናል። (ኢሳ. 54:17) “እጅግ ብዙ ሕዝብ” የሚሆኑ የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች ‘ታላቁን መከራ በሕይወት ያልፋሉ!’ ከዚያ በኋላም ለይሖዋ ቅዱስ አገልግሎት ማቅረባቸውን ይቀጥላሉ። (ራእይ 7:9, 13-17ን አንብብ።) በእርግጥም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈረው ሐሳብ የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት እንድንጠባበቅ የሚያደርግ ነው! ‘ይሖዋ ታማኞችን እንደሚጠብቅ’ እናውቃለን! (መዝ. 31:23) ይሖዋን የሚወዱና እሱን የሚያወድሱ ሁሉ ቅዱስ ስሙን ከነቀፋ ነፃ ሲያደርግ በማየት ይደሰታሉ።—ሕዝ. 38:23

19. በቅርቡ ምን ዓይነት ግሩም ሕይወት ይጠብቀናል?

19 በ2 ጢሞቴዎስ 3:2-5 ላይ የሚገኘው ሐሳብ፣ የሰይጣን ተጽዕኖ በሌለበት አዲስ ዓለም ውስጥ የሚኖሩትን ሰዎች ባሕርይ የሚገልጽ ቢሆን ኖሮ ምን ተብሎ ሊጻፍ እንደሚችል እስቲ አስበው። (“ በዚያን ጊዜ ሰዎች የሚኖራቸው ባሕርይ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) የበላይ አካል አባል ሆኖ ያገለገለው ወንድም ጆርጅ ጋንጋስ * ሁኔታውን እንዲህ ሲል ገልጾታል፦ “ሰዎች ሁሉ፣ ወንድም ወይም እህት በሚሆኑበት ጊዜ ዓለም ምንኛ አስደሳች ቦታ ይሆን! በቅርቡ በአዲሱ ሥርዓት ውስጥ የመኖር መብት ይኖራችኋል። እንደ ይሖዋ ለዘላለም መኖር እንችላለን።” ወደፊት እንዴት ያለ ግሩም ሕይወት ይጠብቀናል!

መዝሙር 122 ጸንታችሁ ቁሙ፣ አትነቃነቁ!

^ አን.5 በቅርቡ በሰው ዘር ሁሉ ላይ “ታላቅ መከራ” እንደሚመጣ እናውቃለን። በዚያ ወቅት የአምላክ አገልጋዮች ምን ያጋጥማቸዋል? ይሖዋ በዚያ ጊዜ ምን እንድናደርግ ይጠብቅብናል? በታላቁ መከራ ወቅት ታማኝ ለመሆን በአሁኑ ጊዜ የትኞቹን ባሕርያት ይበልጥ ማዳበር ያስፈልገናል? በዚህ ርዕስ ላይ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን።

^ አን.3 ተጨማሪ ማብራሪያ፦ ሕዝበ ክርስትና የሚለው አገላለጽ ክርስቲያን እንደሆኑ የሚናገሩ ሆኖም ይሖዋን እሱ ባወጣው መሥፈርት መሠረት እንዲያመልኩ ተከታዮቻቸውን የማያስተምሩ ሃይማኖቶችን ያመለክታል።

^ አን.11 ተጨማሪ ማብራሪያ፦ የማጎጉ ጎግ የሚለው አገላለጽ (በአጭሩ ጎግ ተብሎም ይጠራል) በታላቁ መከራ ወቅት በንጹሕ አምልኮ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ግንባር የሚፈጥሩ ብሔራትን ያመለክታል።

^ አን.11 የግርጌ ማስታወሻ፦ ከአርማጌዶን ጦርነት በፊት ስለሚኖሩት ክንውኖች ሰፋ ያለ ማብራሪያ ለማግኘት የአምላክ መንግሥት እየገዛ ነው! የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 21 ተመልከት። የማጎጉ ጎግ ስለሚሰነዝረው ጥቃትና ይሖዋ በአርማጌዶን ጦርነት ወቅት ሕዝቡን ስለሚታደግበት መንገድ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ደግሞ የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ መልሶ ተቋቋመ! የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 17 እና 18 ተመልከት።

^ አን.16 “ፍቅር ለዘላለም ይኖራል!” የሚል ጭብጥ ያለው የ2019 የክልል ስብሰባ፣ ይሖዋ በፍቅሩ ጥበቃ ስለሚያደርግልን ምንጊዜም ደህንነታችን እንደሚጠበቅ የሚያረጋግጥ ነው።—1 ቆሮ. 13:8

^ አን.19 በታኅሣሥ 1, 1994 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን ‘ሥራው ተከተለው’ የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.65 የሥዕሎቹ መግለጫ፦ በታላቁ መከራ ወቅት የተወሰኑ የይሖዋ ምሥክሮች ጫካ ውስጥ በድፍረት የጉባኤ ስብሰባ ሲያካሂዱ።

^ አን.67 የሥዕሎቹ መግለጫ፦ እጅግ ብዙ ሕዝብ የሚሆኑ የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች ታላቁን መከራ በሕይወት በማለፋቸው ተደስተው።